በኢማን ከፍ ማለት

0
4839

በኢማን ከፍ የማለት አስፈላጊነት

አንድ ሙስሊም በቀልቡ ውስጥ ወደ ዘላለማዊው ዓለም የመመለስና ከዚህች አታላይ ዓለም ችላ የማለት ስሜት ቦታ ከተሰማው፤ ድንገት ከመድረሱ በፊት ለማይቀረው ሞት ዝግጁ ሆኖ ከጠበቀ፤ አላህ ሱ.ወ ሲወሣ ቀልቡ የሚደነግጥ የልብ ምቱም የሚጨምር ከሆነ፤ በውስጡም የፍርሃት የመተናነስና ስብርብር የማለት ስሜት ከተሰማው፤ ሶላት በሚሰግድበት ወይንም ዚክር በሚያደርግበት ወቅት በህያው ቀልብ ከሆነ፤ ከያንዳንዱ የአምልኮ ተግባር  በኋላ ልቡ ስትለሰልስ የሚታወቀው ከሆነ፤ ሶላት ሲሰግድ፣ ዚክር ሲያደርግ፣ ቁርኣን ሲቀራ ጥፍጥና የሚያገኝ ከሆነ፤ ዱዓ በሚያደርግበት ወቅት ፈጣሪው አጠገቡ ያለ ያህል ተሰምቶት የሚመሳጠረው ከሆነ… ያኔ የኢማን አቋሙ ደህና ነውና አላህን ያመስግን፡፡ ነገርግን በነፍሱ ውስጥ ከአላህ ትእዛዛት የመሠላቸት ሰሜት ከተሰማው ለምሳሌ ከጀመዓ ሶላት የሚዘገይ፣ ሱናዎችን የማይሰግድ፣ቁርኣንን ጭራሽ የማይከፍት፣ ለሀላል እና ሀራም ግድ የሌለው፣ ዐይኑን ሀራም ከማየት የማይሰብር፣ ጊዜውን በአልባሌ ነገር የሚያጠፋ፣ ቀልቡ በቅርቢቱ ዓለም ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ በሷ ሽልማቶች ይበልጥ ለመጌጥ የሚስገበገብ  ከሆነ… ኢማኑ ወርዶ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነውና ያለው ያኔ ነፍሱን ይገምግም፡፡ ሁኔታውንም በደንብ ያጣራ፡፡

ኢማን በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ሁሌም ከፍ ዝቅ ሲል ይኖራል፡፡ አላህን በመታዘዝ ይጨምራል፡፡ ሀጢኣትና ወንጀል በመሥራት ይቀንሣል፡፡ አቡ ጃዕፈር የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሶሃባ ከሆነው አያቱ ዑመይር ኢብኑ ሁበይብ እንዳስተላለፈው ‹‹ኢማን ይጨምራል ይቀንሣል፡፡›› አለ፡፡ ‹‹በምንድነው የሚጨምረው በምንስ ነው የሚቀንሰው?›› ? ተባለ፡፡ ‹አላህን ስናወሣ፣ ስናመሰግነውና ስንቀድሰው ያ የመጨመሩ ምልክት ነው፡፡ ከተዘናጋን እና ከረሣነው ደግሞ መቀነሱን ነው የሚያመላክተን፡፡› አለ፡፡

አንድ ሙስሊም ኢማኑ እንዲጨምር ጉጉቱ ካለው  የቀልቡን ነገር ይጠንቀቅ፡፡ ቀልብ የአምልኮ ሁሉ ማዕከል ነውና፡፡ ከውዴታ እስከ ጥላቻ፣ ከፍራቻ እስከ ክጀላ.. የሁሉም ስሜቶችና ክስተቶች  መሰባሰቢያ ነው፡፡ አላህም ሱ.ወ የሚያየው ቀልብን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከሁሉም የሰውነት ክፍሎች በላይ ለቀልብ ትልቅ ቦታን ሰጥቷል፡፡ የአላህ መልእክተኛም ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል

 ‹‹አዋጅ ስሙ! በሰውነት ውስጥ አንዲት ቁራጭ ሥጋ አለች፡፡ እሷ የተስተካከለች አንደሆነ ሰውነት ሁሉ ይስተካከላል፡፡ እሷ የተበላሸች እንደሆነ ደግሞ ሰውነት ሁሉ ይበላሻል፡፡ ስሙ! እሷም ቀልብ ናት፡፡››

ቀልባችን ዘወትር ህያው እንድትሆን የሚያግዙ መንገዶች

  • ከቁርኣን ጋር መኖር
  • አላህን ማውሣት ማብዛት
  • የለሊት ሶላት
  • መስጅድ መመላለስ ማብዛት
  • የመልካም ሥራ መሸመቻ ወቅቶችንና በላጭ ጊዜያቶችን መጠቀም
  • ፆም ማብዛት
  • ማስተንተን
  • የአላህን ትእዛዛት ለመፈፀም መሽቀዳደም መልካም ሥራዎችን ማብዛት

    ከቁርኣን ጋር መኖር

    ኢማንን ለመጨመር የቁርኣን አስፈላጊነት

    ቁርኣን ትልቁ ኢማን መጨመሪያ መንገድ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ ይላል፡-

    وَإِذَا تُلِيَتْ عَلَيْهِمْ آيَاتُهُ زَادَتْهُمْ إِيمَانًا

    በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ …..ሱረቱል አንፋል 8፥2

    ቀልብ የአላህ ፍጥረት ነው፡፡ ቁርኣን ደግሞ የአላህ ንግግር ነው፡፡ በትክክለኛ ተፈጥሮአዊ ባህሪ በሁለቱ መካከል መዋሀድ ሊኖር ደግሞ ግድ ነው፡፡ ቁርኣንን ያህል ትቶ ወደተከበረውና ሀያሉ አላህ የሚያደርሰውን ሌላ መንገድ የሚፈልግ ሰው ምንኛ ደካማና አሣዛኝ ነው! አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

    يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَتْكُم مَّوْعِظَةٌ مِّن رَّبِّكُمْ وَشِفَاءٌ لِّمَا فِي الصُّدُورِ وَهُدًى وَرَحْمَةٌ لِّلْمُؤْمِنِينَ

    እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ግሳጼ በደረቶች ውስጥም ላለው (የመጠራጠር በሽታ) መድኃኒት ለምእምናንም ብርሃንና እዝነት በእርግጥ መጣችላችሁ፡፡ ዩኑስ 10፥57

    ሁሉም ቀልቦች በቁርኣን ይጠቀሙ ይሆን?! በአላህ ያላመኑ ከሀዲያንስ? ቁርኣንን በመስማት ሁሉም ልቦችና ይርዳሉን? ሁሉም ሰውነቶችም ይኮማተራሉ?  ለምንድነው ቁርኣን እያዳመጥን ምንም የማይሰማን?

    ቁርኣን ሁሌም ቁርኣን ነው፡፡ ነገርግን ችግሩ ያለው ቀልብ ላይ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ ይላል

    قُلْ هُوَ لِلَّذِينَ آمَنُوا هُدًى وَشِفَاءٌ ۖ وَالَّذِينَ لَا يُؤْمِنُونَ فِي آذَانِهِمْ وَقْرٌ وَهُوَ عَلَيْهِمْ عَمًى

    እርሱ ለእነዚያ ለአመኑት መምሪያና መፈወሻ ነው፡፡ እነዚያም የማያምኑት በጆሮዎቻቸው ውስጥ ድንቁርና ነው፡፡ (አይሰሙትም)፡፡ እነርሱም በእነርሱ ላይ እውርነት ነው፡፡ እነዚያ ከሩቅ ስፍራ እንደሚጥጠሩ ናቸው፡፡ ፉሲለት 41፥44

    ስለሆነም በቁርኣን መጠቀም የፈለገ ሰው በአላህ ፍራቻ የታነፀ መሆን አለበት፡፡

فَذَكِّرْ بِالْقُرْآنِ مَن يَخَافُ وَعِيدِ

    ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ፡፡ ቃፍ 50፥45

طه

مَا أَنزَلْنَا عَلَيْكَ الْقُرْآنَ لِتَشْقَىٰ

ጠ.ሀ. (ጣ ሃ)፥ ቁርኣንን ባንተ ላይ እንድትቸገር አላወረድንም፡፡ ጣሀ 20፥1-2

በቁርኣን መኖር ከፈለግን የተለያዩ መንገዶች እንጠቁም

1.ማንበብ ፦ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቁርኣንን እንድናነነብ በአል ሙዘሚል ምዕራፍ ውስጥ በአንድ አንቀፅ ውስጥ ሁለት ጊዜ አዞናል፡፡ ነቢዩንም ሰ.ዐ.ወ ቁርኣንን በደንብ እንዲያነቡ አዟል

وَرَتِّلِ الْقُرْآنَ تَرْتِيلًا

ቁርኣንንም በዝግታ ማንበብን አንብብ፡፡ አል-ሙዘሚል 73፥3

وَأَقْوَمُ قِيلًا

ለማንበብም ትክክለኛ ናት፡፡ አል-ሙዘሚል 73፥6

ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ቁርኣንን ማንበብ ትሩፋቱ ምን ያህል እንደሆነ እንዲህ በማለት ነግረውናል፡፡

 ‹ ከአላህ ቁርኣን አንድ ፊደል ያነበበ ሰው በዚያ አሥር ምንዳ ያገኛል፡፡ ‹አሊፍ ላም ሚም› ሲል አንድ ፊደል ነው አልላችሁም፡፡ ነገር ግን አሊፍ አንድ ፊደል ነው፤ ላምም አንድ ፊደል ሚምም አንድ ፊደል፡፡

ቁርኣንን ማንበብ የፈለገ ሰው ሊከተላቸው የሚገቡ ሥርኣቶች

  • ኒያን ማስገኘት (ሀሣብን መሰብሰብ) የአላህን ውዴታ መፈለግ
  • ውዱእ ማድረግ፡፡ ኢስቲዓዛ እና በስመላህ (አኡዙ ቢላህ ሚን አሸ ሸይጧኒ አር ረጂም እና ቢስሚላህ አርረህማኒ አርረሂም)
  • በላጭ ጊዜዎችን መጠቀም፡፡ በቀን ውስጥ ካሉት ከወቅቶች ሁሉ በላጭ የሚባለው አላህ ለባሮቹ የሚገለፅበት የሊለት የመጨረሻው አንድ ሦስተኛ ክፍል ነው፡፡
  • ጥሩ ቦታን መምረጥ፥ በላጩ መስጅድ ውስጥ ነው፡፡ ቤት ውስጥም ሆኖ ልብን ከሚሰርቅ እና ሀሳብን ከሚወስድ የራቀ ፀጥ ያለ ቦታ መልካም ነው፡፡
  • ወደ አላህ መጠጋት፡፡ ጭንቅ ጥብብ እንዳለው ሰው በሙሉ ሀሳብ ወደሱ መመለስና ስኬትን መፈለግ
  • ቁርኣን በሚያነቡበት ጊዜ ማስተንተን፤ በሀሣብ ከመዋለልና ከመዳከር መቆጠብ
  • አብሣሪ የሆኑ የቁርኣን አንቀፆች ሲያጋጥሙ በስሜት መንጎድና አላህን ከእዝነቱ መጠየቅ፡፡ አስጠንቃቂ የሆኑ አንቀፆች ሲያጋጥሙደግሞ መደንገጥ፤ አላህ ከነርሱ ከተቆጣባቸው እንዳያረገን መለመን፡፡
  • የቁርኣን ንግግሮች እኛን እያንዳንዳችንን በግል እንደሚመለከቱንና አላህም እኛን እያናገረ እንደሆነ አድርገን ማሰብ፡፡ በዚህም ከኛ ምን እንደሚፈለግ ለመገንዘብ ለረጅም ጊዜ ቆም በማለት ስለ ክልከላዎች እና ትእዛዛቱ ማስተንተን

ቁርአንን ማስተንተን

አንድ ሰው ቁርኣንን በጥልቀት የሚያስተንትነበት ጊዜ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ቁርኣን እኛ ላይም በኛ ላይም ማስረጃ ነው፡፡ ታላቁ ነቢያችንም ሰ.ዐ.ወ ይህንኑ ብለዋል፡፡

 والقرآن حجة لك أو عليك

ቁርአን ለአንተ ወይም በአንተ ላይ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ሙስሊም እንደዘገቡት፡፡

እየተሠላቸ አሊያም እየደበረው ቁርኣንን የሚያነብ ሰው ቁርኣንን በሱ ላይ ማስረጃ እንዳይሆን ያሠጋል፡፡ አላህ(ሱወ) ቁርኣንን እንድናስተነትን ጋብዞናል፡፡

كِتَابٌ أَنزَلْنَاهُ إِلَيْكَ مُبَارَكٌ لِّيَدَّبَّرُوا آيَاتِهِ وَلِيَتَذَكَّرَ أُولُو الْأَلْبَابِ

(ይህ) ወዳንተ ያወረድነው ብሩክ መጽሐፍ ነው፡፡ አንቀጾቹን እንዲያስተነትኑና የአእምሮዎች ባለቤቶችም እንዲገሰጹ (አወረድነው)፡፡ ሷድ 38፥29

إِنَّ الَّذِينَ ارْتَدُّوا عَلَىٰ أَدْبَارِهِم مِّن بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُمُ الْهُدَى ۙ الشَّيْطَانُ سَوَّلَ لَهُمْ وَأَمْلَىٰ لَهُمْ

እነዚያ ለእነርሱ ቅኑ መንገድ ከተብራራላቸው በኋላ ወደ ኋላቸው የተመለሱት ሰይጣን ለእነርሱ መመለሳቸውን ሸለመላቸው፡፡ ለእነርሱም አዝዘናጋቸው፡፡ ሙሀመድ 47፥25

አንዳንዴ ሸይጧን ወደ እኛ በመምጣት ‹ቁርኣንን የማስተንተን አቅሙ የለህም ችሎታህም አይደለም፡፡ ይህ የኡለማኦች ሥራ ነው፡፡› ሊለን ይችላል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

لَوْ أَنزَلْنَا هَٰذَا الْقُرْآنَ عَلَىٰ جَبَلٍ لَّرَأَيْتَهُ خَاشِعًا مُّتَصَدِّعًا مِّنْ خَشْيَةِ اللَّهِ ۚ وَتِلْكَ الْأَمْثَالُ نَضْرِبُهَا لِلنَّاسِ لَعَلَّهُمْ يَتَفَكَّرُونَ

ይህንን ቁርኣን በተራራ ላይ ባወረድነው ኖሮ ከአላህ ፍራቻ (የተነሳ) ተዋራጅ ተሰንጣቂ ኾኖ ባየኸው ነበር፡፡ ይህችንም ምሳሌ ይገመግሙ ዘንድ ለሰዎች እንገልፃለን፡፡ አል ሀሽር 59፥21

ማስተንተን በጎ ትሩፋቶች አሉት

የአላህን ቁርኣንን መልእክቶች ማስተንተን ከአንዱ ዓለም ወደ ሌላኛው ዓለም ሰውን ያጓጉዛል፡፡ ከአንዱ ሁኔታ ወደ ሌላኛው ሰውን ይቀይራል፡፡ ታላቁ ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ ረ.ዐ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ በሞቱ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በመደናገጣቸው የሆነውን ሁሉ ማመን አቅቷቸው ‹እስቲ ሙሀመድ ሞቷል የሚል ካለ!› በማለት ሰይፋቸውን እስከ መምዘዝ ደርሰው ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ ቁርኣን ነበር አላህ የወደደውን ነገር ወደ መውደድና መቀበል ዓለም የመለሣቸው፡፡ ይህም የሆነው ታላቁ ኸሊፋ አቡበክር አስስዲቅ

وَمَا مُحَمَّدٌ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ ۚ أَفَإِن مَّاتَ أَوْ قُتِلَ انقَلَبْتُمْ عَلَىٰ أَعْقَابِكُمْ

ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ታዲያ ቢሞት ወይም ቢገደል ወደ ኋላችሁ ትገለበጣላችሁን፡፡ አልዒምራን 3፥144

የሚለውን የቁርኣን አንቀፅ ባነበቡ ጊዜ ቁርኣንን በእርጋታ በማስተንተናቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሆነ ሷሊህ ሰውም ከዝንጉነትና በዓለማዊ ጥቅም ከመደለል ወደ ሥራና ትጋት ወደ አላህን አምላኪ ቁጥብነት መንገድ ተመልሰዋል፡፡ ይህ የሆነው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የሀያሉንና የተከበረውን የአላህን ቁርኣን መልእክት ካነበቡ በኋላ ነው፡፡

وَفِي السَّمَاءِ رِزْقُكُمْ وَمَا تُوعَدُونَ

فَوَرَبِّ السَّمَاءِ وَالْأَرْضِ إِنَّهُ لَحَقٌّ مِّثْلَ مَا أَنَّكُمْ تَنطِقُونَ

ሲሳያችሁም የምትቀጠሩትም (ፍዳና ምንዳ) በሰማይ ውስጥ ነው፡፡ በሰማይና በምድር ጌታም እምላለሁ፡፡ እርሱ እናንተ እንደምትናገሩት ብጤ እርግጠኛ ነው፡፡ አዛሪያት 51፤22

ከቁርኣን የተወሰነውን ክፍል መሀፈዝ ( በቃል መሸምደድ)

ከአላህ ንግግር ባዶ የሆነ ቀልብ እንደ ባዶ ቤት ነው፡፡ ምንም የሌለበት ኦና፡፡ የአላህ ንግግር ብርሃን ነው፡፡ ቀልብን ያበራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀፈዙትን (በቃል የያዙትን) ነገር ላለመርሣት ቁርኣን ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ቁርኣን ከሰዎች ልብ ውስጥ በእስር ላይ ካለች ግመል በላይ አምላጭ ነውና፡፡ በመሆኑም በየሶላቱ እና በተገኘው ክፍተት ሁሉ ከወንድምም ጋር በመተዋወስ ቁርኣንን ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡

በቁርኣን ውስጥ በክልከላና በትእዛዝ የመጡ ነገሮችን መተግበር

ይህ የቁርኣን ትልቁ ዓላማ ነው፡፡ የማንበብ እና የማስተንተን ጫፉም መተግበር ነው፡፡ ኢብኑ መስዑድ ረ.ዐ እንዲህ ይላሉ ‹ እኛ ከቁርኣን የከበደን ቃሉን መሸምደድ ነው፡፡ በሱ መሥራት ግን ገርቶልናል፡፡ ከኛ በኋላ የሚመጡት ግን ቁርኣንን መሀፈዝ ይገራላቸዋል፡፡ መተግበሩ ግን ይከብዳቸዋል፡፡›

ታላቁ ኸሊፋ ዑመር ረ.ዐ የአል በቀራን ምዕራፍ የሀፈዙት በአሥራ ሁለት አመታት ውስጥ ነበር፡፡ ሲያከትሙም ግመል አርደዋል፡፡ ይህ ሊገርመን አይገባም፡፡ ለምን ቢባል ሣይሰሩበት አንድንም የቁርኣን አንቀፅ የማያልፉ በመሆኑ ነውና፡፡

የአቢ ሁዘይፋ አገልጋይ የሆነው ሳሊም በአልየማማ ጦርነት ወቅት ባንዲራ ተሸክሞ ለራሱ  ‹ቁርኣንን የተሸከምኩት እኔ ከዚህ ከሸሸሁ ምንኛ መጥፎ ነኝ!› ይል ነበር፡፡ ቀኝ እጁ ስትቆረጥ በግራው ግራው ደግሞ ስትቆረጥ በአንገቱ ሥር እየያዘ በመጨረሻም ሰማእት ሆኖ ወደቀ፡፡

ስለሆነም እኛ ቁርኣንን በማንበብ፣ በማስተንተንና በመሀፈዝ፣ የሀፈዝነው እንዳይጠፋብን በመደጋገም እንዲሁም አዘውትረን የቁርኣንን ተእዛዝትና ክልከላዎችን በመተግበር ከቁርኣን ጋር ልንር ይገባል፡፡

********** ይቀጥላል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here