ሱነኑል ፊጥራ (ጦሀራ – ክፍል 6)

0
4037

አላህ ለነብያት የመረጠላቸው ሱናዎች አሉ። እኛንም እንድንከተላቸው አዞናል። እነዚያን ሱናዎች (መንገዶች) ደግሞ የኃይማኖቱ ምልክት አደረጋቸው። በሁሉም ዘመን ያሉ መለኮታዊ ድንጋጌዎች ሁሉ የሚጋሯቸው ያልተሻሩ ህጎች ናቸው። ብዙ ጊዜ ይከሰታሉ። የነብያት የተከታዮች መለዮዎች ናቸው። እነዚህ ነገሮች ሱነኑል-ፊጥራ ይባላሉ። ከዚህ በታች ተተንትነዋል፦

  1. ግርዛት

የወንድ ብልትን ባርኔጣ የሚሸፍን ቆዳ መቁረጥ ማለት ነው። ምክንያቱም ግርዛት ከስሩ ቆሻሻ እንዳይከማች፣ ከሽንት ማደራረቅ በተሟላ ሁኔታ እንዲገኝ እና የወሲብ ለዛ እንዳይጓደል ይጠቅማል። ይህን የወንዶችን ግርዛት አስመልክቶ ነው።

ከአቡሁረይራ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

اختتن إبراهيم خليل الرحمن بعدما أتت عليه ثمانون سنة ، واختتن بالقدوم

“ኢብራሂም የአር-ራህማን ወዳጅ ሰማንያ አመት ከሞላው በኋላ ተገረዙ። በመፍለጫ ነበር የተገረዙት።” (ቡኻሪይ ዘግበውታል)

ግርዛት እንደ አብዛኞቹ ዑለሞች እምነት ግዴታ ነው። ሻፊዒዮች ህፃን ከተወለደ ሰባተኛው ቀን ላይ መሆኑ ይወደዳል ብለው ያምናሉ። ሸውካኒይ ግን “የግርዛትን ወቅት የሚገድብም ይሁን ግዴታነቱን የሚጠቁም ምንም አይነት ማስረጃ የለም ብለዋል።”

  1. የብልትን ፀጉር መላጨት እና የብብትን ፀጉር መንጨት

እነዚህ ሁለቱም ሱናዎች ናቸው። መላጨትም ሆነ በመቀስ ማሳጠር ይቻላል። መንጨትም፣ በኑራ ማስወገድም ያብቃቃዋል። ነወዊይ የብልትን ፀጉር ስለማስወገድ “መላጨት ይሻላል።” ብለዋል።

  1. ጥፍርን መቁረጥ እና ቀድሞ ቀመስን (የላይኛውን የከንፈር ፀጉር) ማስወገድ ወይም ማስተካከል

ቀድሞ ቀመስን በመላጨትም ሆነ በማስተካከል ሱናው ይገኛል። ለሁለቱም ማስረጃ የሚሆኑ ሶሒህ ዘገባዎች ተገኝተዋል። በኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) ሐዲስ ውስጥ እንዳለው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

خالفوا المشركين : وفسروا اللحى ، وأحفوا الشوارب

“አጋሪዎችን ተለያይዋቸው። የአገጭ ፂማችሁን አስረዝሙ። ቀድሞ ቀመሶቻችሁን አስተካክሉ።” (ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል)

በአቢ ሁረይራ ሐዲስ ውስጥ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 خمس من الفطرة : الاستحداد ، والختان ، وقص الشارب ، ونتف الابط ، وتقليم الاظافر

“አምስት ነገሮች ከተፈጥሮአዊ ሱናዎች መሀል ናቸው፦ የብልት ፀጉርን መላጨት፣ ግርዛት፣ ቀድሞ ቀመስን ማሳጠር፣ የብብት ፀጉርን መንጨት እና ጥፍርን መቁረጥ።” (ጀመዓዎች ዘግበውታል)

ስለዚህ ቀድሞ ቀመስን በመላጨትም ይሁን በማሳጠር ሱናው ይገኛል። ዋናው ነገር ቀድሞ ቀመሱ ረዝሞ ምግብ እና መጠጥ እንዳይንጠለጠልበት ወይም ቆሻሻ እንዳይሰበሰብበት ማድረግ ነው።

የብልት ፀጉርን መላጨት፣ የብብት ፀጉርን መንጨት፣ ጥፍርን መቁረጥ እና ቀድሞ ቀመስን መላጨት ወይም ማስተካከል በየሳምንቱ መስራቱ ንፅህናና ውበትን ለማሟላት፣ ነፍስን ለማዝናናት መልካም ነው። አካል ላይ ፀጉር መኖሩ የአእምሮ ውጥረትና ድብርት ይፈጥራል። ነገርግን እነዚህን ነገሮች እስከ አርባ ቀን ድረስ መተው ተፈቅዷል። ከዚያ በላይ ለመተው ግን ምንም አይነት ማሳሰቢያ (ሩኸሷ) የለም። ምክንያቱም አነስ በሐዲሳቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ቀድሞ ቀመስን ለመላጨት፣ ጥፍርን ለመቁረጥ፣ የብብት ፀጉርን ለመንጨት፣ የብልት ፀጉርን ለመላጨት ከአርባ ቀን በላይ እንዳናሳልፍ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ቀነ-ገደብ አድርገዋል።” አሕመድ፣ አቡዳዉድ እና ሌሎችም ዘግበውታል።

  1. የአገጭን ፂም ማጎፈር እና እንዲበረክት መተው

የግርማ ሞገስ ነፀ-ብራቅ ነው። ለመላጨት የቀረበ ማሳጠርን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እጅግ ረዝሞ አስጠያፊ እስከሚሆን ድረስ መተውም አያስፈልግም። መካከለኛ መሆኑ ይወደዳል። መሀለኝነት ሁሉም ነገር ላይ ተወዳጅ ነው። ፂም የሙሉ ወንድነት ምልክት ነው። ጉብዝናንም ጠቋሚ ነው።

ከኢብኑ ዑመር እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

خالفوا المشركين: وفروا اللحى ، وأحفوا الشوارب

“ሙሽሪኮችን ንቀፏቸው የአገጭ ፂማችሁን አጎፍሩ። ቀድሞ ቀመሳችሁን አስተካክሉ።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል።) ቡኻሪይ ለብቻቸው ተከታዩን ጨምረዋል፦ “ኢብኑ ዑመር ሐጅ ወይም ዑምራ ያደረጉ ጊዜ የአገጫቸውን ፂም በእጃችው ይጨብጣሉ። ከዚያም የተረፈውን ይቆርጡታል”።

  1. ፀጉርን መንከባከብ

ፀጉርን ካሳደገው እና ሳያሳጥር ከተወው ቅባት በመቀባት እና በማበጠር መንከባከብ ሱና ነው። ምክንያቱም በአቢሁረይራ ሐዲስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) “ፀጉር ያለው ሰው ይንከባከበው።” ብለዋል። (አቡዳዉድ ዘግበውታል)

የራስን ፀጉር መላጨት ይፈቀዳል። ለሚንከባከበው ሰው ደግሞ ማሳደግ ይፈቀዳል። ምክንያቱም በኢብኑ ዑመር ሐዲስ ውስጥ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 احلقوا كله أو ذروا كله

“(ፀጉራችሁን) ሁሉንም ላጩት ወይም ሁሉንም ተውት!” (አሕመድ፣ ሙስሊም፣ አቡዳውድ እና ነሳኢይ ዘግበውታል)

ከፊል ፀጉርን ላጭቶ ከፊሉን መተው (ቀዘዕ) ግን ይጠላል። ምክንያቱም ናፊዕ ከኢብኑ ዑመር እንደዘገቡት፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘ቀዘዕን’ ከልክለዋል።” ከዚያም “ቀዘዕ ምንድን ነው ተብሎ ናፊዕ ተጠየቁ። እርሳቸውም “ከፊል ፀጉሩን ላጭቶ ከፊሉን መተው ነው።” አሉ።” (ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል)

በተጨማሪም በቅርብ ያስቀደምነው የኢብኑ ዑመር ሐዲስም ለምንለው ብይን ማስረጃ ይሆናል።

  1. ሽበትን አለመንጨት፣ እንዳለ ማቆየት

ሽበትን – ፂም ላይም ይሁን ራስ ላይ- እንዳለ መተው ሱና ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሴትና ወንድ እኩል ናቸው። ምክንያቱም ዐምር ቢን ሹዐይብ ከአባቱ ከዚያም ከአያቱ ይዞ በዘገበው ሐዲስ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 لا تنتف الشيب فإنه نور المسلم ، ما من مسلم يشيب شيبة في الاسلام إلا كتب الله له بها حسنة ، ورفعه بها درجة ، وحط عنه بها خطيئة

“ሽበትን አትንጭ። እርሱ የሙስሊም ብርሃን ነው። ማንኛውም ሙስሊም በእስልምና ውስጥ አንዲትን ሽበትም አይሸብትም አላህ በርሷ አንድ ሐሰና (የበጎ ስራ ምንዳ) የፃፈለት፣ አንድ ደረጃውን ከፍ ያደረገለት እና በርሷ አንድ ሐጢያትን ያራገፈለት ቢሆን እንጂ።” (አሕመድ፣ አቡዳዉድ፣ ቲርሙዚይ፣ ነሳኢይ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

  1. ሽበትን በሒና ማቅላት ወይም ቢጫ ቀለም መቀባት

ምክንያቱም በአቡሁረይራ ሐዲስ እንደተዘገበው፦ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

  إن اليهود والنصارى لا يصبغون فخالفوهم

“አይሁድና ነሷራዎች ሒና ወይም መሰል ቀለሞችን አይለቀለቁም። ንቀፏቸው።” (ጀመዓዎች ዘግበውታል)

በተጨማሪም በአቡ ዘር ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:-

إن أحسن ما غيرتم به هذا الشيب الحناء والكتم

“ይህን ሽበታችሁን ከምትለውጡባቸው ነገሮች ምርጡ ሒና እና አል-ከተም ናቸው።” (አምስቱ ዘግበውታል) አል-ከተም ወደ ወደመቅላት የተጠጋ ጥቁር ቀለም የሚወጣው በቃይ ነገር ነው።

ሽበትን በጥቁር ቀለም መቀባት በተመለከተ፡-

ጃቢር (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የመካ ድል እለት አቡ ቁሀፋ (የአቡበከር /ረ.ዐ/ አባት) ራሳቸው በሽበት ተንቀልቅሎ (ነጭ ሆኖ) ወደ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) መጡ የአላህ መለእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ)፡-

اذهبوا به إلى بعض نسائه فلتغيره بشئ وجنبوه السواد

“ወደ ሚስቶቹ ወደ አንዷ ሂዱና የፀጉሩን ቀለም በሆነ ነገር ትቀይረው በጥቁር ቀለም ግን እንዳይሆን” በማለት ተናግረዋል። ጀመአዎቹ ዘግበውታል ቡኻሪና ቲርሚዚ ሲቀሩ። ኡለማዎች ይህ ክልከላ በልዩ ሁኔታ ለአቡበከር (ረ.ዐ) አባት የተቀመጠ ነው ብለዋል። ስለሆነም ለሁሉም ሰው ተፈፃሚ አይሆንም። ነጭ ፀጉርን ማጥቆር አቡ ቁሀፋን ለመሰለ ትልቅ ሽማግሌ ሰው የሚመጥን  አይደለምና።

አል ሀፊዝ ኢብኑ ሐጀር ፈትሁል ባሪ በተሰኘው መጽሃፋቸው ከኢብኑ ሺሀብ አዝዙህሪ እንዳወሩት እንዲህ ይሉናል ወጣት በነበርንበት ሰዓት ፀጉራችንን በጥቁር ቀለም እናቀልም ነበር። ነገር ግን እድሜያችን ሲገፋና ሰውነታችን ሲደክም ነጭ እንደሆነ ሳናቀልም እንተወው ነበር ማለታቸውን ዘግበዋል።

  1. ሚስክ እና ነፍስን ደስ የሚያሰኙ፣ ልብን የሚከፍቱ፣ መንፈስን የሚያነቁ፣ አካልን የሚያበረታቱና ኃይል የሚለግሱ ሌሎች ሽቶዎን መቀባት

ምክንያቱም በአነስ ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 حبب إلي من الدنيا النساء الطيب وجعلت قرة عيني في الصلاة

“ከዱንያ ውስጥ ሴቶችና ሽቶ እኔ ጋር ተወደዱ። የዓይኔ ማረፊያም በሶላት ውስጥ ተደረገች።” (አሕመድ እና ነሳኢይ ዘግበውታል)

በአቢሁረይራም ሐዲስ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 من عرض عليه طيب فلا يرده ، فإنه خفيف المحمل طيب الرائحة

“ሽቶ የቀረበለት ሰው አይመልሰው። እርሱ ለመሸከም ቀላል ነው። ሽታው ግን ጣፋጭ ነው።” (ሙስሊም፣ ነሳኢይ እና አቡዳውድ ዘግበውታል)።

*****

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here