ኢስላም እያንዳንዱን የሰው ልጅ ህይወት ክፍል የሚያካልል እጅግ የመጠቀና አለማቀፋዊ የሆነ ሃይማኖት ነው። ስለ ባህል ያለውን እይታ ስንገመግም ደግሞ ውበቱ ጎልቶ ይታየናል።
በዛሬው መጣጥፍ የኢስላማዊ ባህልን አንፀባራቂ ገፅታ ለመቃኘት እንሞክራለን።
“እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልእክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ሚዛናዊ ህዝቦች አደረግናችሁ ።” (አልበቀራ 2፡143)
“እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ስሆን የኢብራሂምን መንገድ መራኝ እሱም ከአጋሪዎች አልነበረም። በል። ስግደቴም፣ መገዛቴም፣ ህይወቴም፣ ሞቴም ለአለማት ጌታ ለአላህ ነው። ለርሱ ተጋሪ የለውም በዚህም ታዘዝኩ። እኔ የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ። በል ።” (አል አንዓም 6፡ 161-163)
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሁላችሁም በመታዘዝ ውስጥ ግቡ። የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ እርሱ ለናንተ ግልፅ ጠላት ነውና።”(አል በቀራ 2፡ 208-209)
ባህል ምንድነው?
ባህል ሲባል ብዙ ሰዎች ሙያዊ ጥበብ፣ ሙዚቃ ወይንም ማህበራዊ ልማዶች ብቻ ይመስላቸዋል። በዐረብኛ “ሰቃፋ” የሚል ሥያሜ ያለው ሲሆን ትርጉሙም ሠፊና ጥልቅ ነው። ባህል በአንድ ማህበራዊ ቡድን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚማማሩት፣ የሚፈጥሩትና የሚለዋወጡት የባህሪና የእሣቤ መወራረስ ነው። አንዱን ማህበረሰብ ከሌላኛው የምንለይበት ከመሆኑም በላይ ሰዎችንም ከእንሠሣት ለመለየት ባህል አይነተኛ ሚና አለው። የአንድ ህዝብ ባህል ስንልም እምነታቸውን፣ የሥነምግባር መመሪያቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የአምልኮ ሥርአታቸውን፣ ሙያቸውን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራቸውን፣ የአለባበሣቸውን ሁኔታ፣ የምግብ አመራረታቸውንና አዘገጃጀታቸውን፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ሥርአታቸውን ሁሉ ያጠቃልላል ።
በኢስላም ባህል ልዩና ጉልህ የሆነ ትርጉም አለው። ኢስላማዊ ባህል ትርጉሙ ዐረብኛ፤ የምሥራቁ አለም አሊያም የመካከለኛው ምሥራቅ አይደለም። የማይቀያርና ቋሚ የሆነ ወጥ ትርጉምም መለያው አይደለም። ባህል በኢስላም ዓይነቱ የተለያየና ሥርጭቱም ሰፊ ነው። በኢስላማዊ ባህል ውስጥ አንዳንድ ነገሮች በሁሉም ሙስሊሞች ዘንድ ወጥ የሆነ ትርጉምና ዓለማቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ሰፊ ሥርጭት ያላቸውና ከሀገር ሀገር ከህዝብ ህዝብ የተለያየ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ዓለማቀፋዊነታቸው ቁርኣንና ሱናን (ሀዲስን) መሠረት ያደረገ ሲሆን ነጠላ ባህሪያቶቻቸው ደግሞ እንደየሀገሩ ህዝቦች ልማድ መለያየት የተለያዩ ናቸው። በዚህም የተነሣ ለምሳሌ ዐረባዊ (ምንጩ ከዐረብ የሆነ) የሆነ የኢስላም ባህል፣ የህንድና ፓኪስታን ኢስላማዊ ባህል፣ የኢትዮጵያ ኢስላማዊ ባህል፣ እንዲሁም የቻይና የአሜሪካና አሊያም የምእራባውያን ኢስላማዊ ባህል ወ.ዘ.ተ. ብለን ልንዘረዝር እንችላለን።
እኛ ሙስሊሞች በዚህች ዓለም ላይ የትም ብንኖር የኛን ልዩ የሆነ ኢስላማዊ ባህላችንን ማሣደግ ይገባናል። ከሌሎች የተለያየ ባህል ካላቸው ሰዎችም ጋር ተቀላቅለን መኖር ይኖርብናል። ባህላችን በቁርኣንና በሱና (ነቢያዊ ፈለግ) እንዲሁም በሰው ልጆች የህይወት ልምድና አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ነው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሁሉም ህዝቦች እውቀት ተጠቃሚ ሆነናልና። ዛሬም ባህላችን ጠንካራና ተራማጅ ሆኖ እንዲቀጥል ለሁሉም ጠቃሚ እውቀቶችም እራሣችንን ክፍት ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህም ሆኖ ግን የኢስላማዊ ባህላችንን መሠረታዊ የሆኑ ባህሪዎችና እሴቶች ማወቅ ግድ ይለናል። በየትኛዉም የዓለም ክፍል ብንኖር እነኚህን እሴቶች መርሣት አይኖርብንም። እነኚህ እሴቶች ወጥና ቋሚ ሲሆኑ ኢስላማዊ ባህልም ያለነሱ ትርጉም አይኖረውም።
የኢስላማዊ ባህሎች ልዩ ባህሪያት
1. አምላክን ማእከል ያደረጉ (አምላክ ተኮር) ናቸው
ኢስላማዊ ባህላችን አምላክን ማእከል ደረገ ነዉ። የምንመራውም ጥብቅ በሆነ የተውሂድ (በአላህ አንድነት ማመን) ሥርእት ነው። በነቢያት፣ በአላህ መልእክተኞችና በመጨረሻም በመጨረሻው የአላህ መልእክተኛ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አማካይነት ወደኛ በደረሰው አምላከዊ መመሪያ እናምናለን። ከሞት በኋላ ህይወት ስለመኖሩና በፍርዱ ቀንም እናምናለን። በዋነኛነት በአምልኮ ተግባራትና እራስን ለአላህ በማስገዛት በሰላት፣ በፆም፣ በዘካና በሀጅ ተግባራት ላይ እናተኩራለን። እንዲሁም አላህ አንዳንድ ነገሮችን ለኛ መፍቀዱንና አንዳንድ ነገሮችን መከልከሉን እናውቃለን። ለሀላል ነገር ከፍተኛ ትኩረት እንሠጣለን፤ ሀራም ነገሮችንም እንርቃለን።
2. እኩልነት መቻቻልና ወንድማማችነት
ኢስላማዊ ባህላችን ሰዎች ሁሉ እኩል መሆናቸው ላይ አፅንኦት ይሠጣል። የቀለምም ሆነ የዘር መድልዎን አይቀበልም። የሰው ልጆችም ሆኑ አጠቃላይ የአላህ ፍጡራን ጠቀሜታና የየራሣቸው ዋጋ እንዳላቸው እናምናለን። የእምነት ነፃነትን የምንቀበል ሲሆን በሃይማኖት ጉዳይ ማስገደድ የሌለ መሆኑንም እምነታችን ያስተምረናል። ባህላችን ከሌሎች የሰው ልጅ እምነቶች አንፃር በተለይም ከመፅሃፉ ባለቤቶች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) አንጻር የመቻቻል ባህሪ አለው። ሁሉም ሙስሊሞች ወንድማማቾችና እህትማማቾች ናቸው። በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በሀገር፣ በፖለቲካ አመለካከት አሊያም ከኢኮኖሚ አንፃር የመለያየቱ ነገር እንዳለ ሆኖ በእምነት ወንድማማችነት ፅንሰ ሀሣብ በእጅጉ መጠናከር ይኖርበታል። ከሁሉም የሰው ልጆች በተለይም ከጎረቤቶቻችን ጋር መልካም ግንኙነት ሊኖረን ይገባል።
3. የማክበርና የግብረገብነት ባህሪ
ባህላችን ለሰው ልጆች ክብር ትልቅ ቦታ ይሠጣል። ሞራላቸውንም ይጠብቃል። እውነተኛነት፣ ታማኝነት፣ ትህትና እና ንጽህና ላይ ትኩረት ያደርጋል። ማባከንን፣ ታይታን (ለይዩልኝ መሥራትን)፣ ፅንፈኝነትንና የመሣሰሉትን መጥፎ ባህሪዎች ያወግዛል። ባህላችን በራስ መተማመንንና እራስን መቻልን ያስተምራል። በመመጽወትና በጎነት ላይ ያነሣሣል። ባህላችን ቤተሰባዊ ጥንካሬን መሠረት ያደረገ ሲሆን በዋናነትም መልካም የባልና ሚስት ግንኙነትን፣ ጥሩ የልጆች አስተዳደግን፣ ሰፊና የተደራጀ ቤተሰብን፣ ታላላቆችን በማክበርና በማፍቀር ላይ ትልቅ አፅንኦት ይሠጣል። ዝሙትን፣ ሴሰኝነትን፣ ግብረሰዶማዊነትን፣ ቁማርን፣ የአደንዛዠ እፅ ተጠቃሚነትን ያወግዛል። በየትኛውም ጊዜ ላይ ብንሆን፤ በየትኛውም ማህበረሰብ መካከል ብንኖር እነኚህን ነገሮች አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል። ባህላችን በነዚህ ነገሮች ላይ እስካልተመሠረተ ድረስ ጥሩና እውነተኛ ሙስሊሞች መሆን አይቻለንም።
4. አዳጊ ፣ ተራማጅና ዓለማቀፋዊነት ባህሪ አለው
ኢስላማዊ ባህላችን እራሱን የጣለ መናኝ አይደለም። ከዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ጋር እራሱን ያስተሣስራል። በትግል ይታወቃል፣ ለለውጥ ያነሣሣል፣ በማህበራዊ ፍትህ ያዛል፤ ጭቆናንና ወንጀል ማስወገድ ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሣቀሣል። በትምህርትና እውቀት በመፈለግ ያበረታታል። ኢስላማዊ ባህላችን በሃይማኖታዊና አለማዊ እውቀቶች መካከል ልዩነት አያደርግም። ሁሉም እውቀቶች ጠቃሚ ናቸው ብሎ ያምናል። ለዚህም አእምሮአችንን ክፍት ማድረግና የትኛውንም ጠቃሚ ጥበብ ከየትኛውም ምንጭ ይሁን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። ኢስላማዊው ባህል ጠቃሚ የሆኑ ጥበባትን፣ ኪነ ህንፃን፣ ሥነ ውበትን፣ ጤናን፣ ጤናማ አካባቢና ንጹህ መዝናኛን ያበረታታል።
5. ብቸኛና ወጣ ያለ አይደለም (non-exclusivist) ወደ ትክክለኛው መንገድ ጥሪ በማድረግ (ደዕዋ) ላይ የተመሠረተና ጥሩ አሣቢም ነው
በመጨረሻም የምናነሣው ነጥብ ኢስላማዊ ባህላችን መልካም ነገሮችን ከጥበብና መልካም ትእግስት ጋር እንድናስኬድ የሚያበረታታ መሆኑን ነው። የኛ ባህል የሌሎች ባህሎች ሁሉ ብቸኛ ገዠ ሆኖ ይቀመጥ ሌላው አንድም ሣይቀር ይወገድ አሊያም አድልዎ ይደረግበት አንልም። ያለአንዳች ልዩነት ህዝቦችን ሁሉ ወደ ኢስላም መጋበዙ ትክክል እንደሆነ እናምናለን። ባህላችን ሌሎችን በማድመጥና ከሌሎች ጋር በመወያየት አጥብቆ ያምናል። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጥሩ እንደሆነና ኢስላምን ለማወቅና ለመማር እድሉ ቢሠጠው አርኪና ሁሉን ያሟላ ሃይማኖት መሆኑን ይደርስበታል የሚል እምነት አለን። ጊዜው ቢርቅም በመጨረሻ እውነት ታብባለች ውሸትም ትከስማለችና። ከዚህም በተጨማሪ ባህላችን በትእግስተኘነት ይመክረናል። ፅናት በተሞላበት መልኩም በርትተን እንድንሠራና እምነታችንንም የዓለማት ሁሉ ገዠ በሆነው በፈጣሪያችን አላህ ላይ እንድንጥል ያስታውሰናል።
ከላይ የገለፅናቸው ነገሮች በሙሉ ታማኝና ግልፅ የሆኑ ሃይማኖታዊ ምንጮችን መሠረት ያደረጉ ናቸው። አብዛኞቻችንም እነኚህ ነገሮች እንቀበላለን የሚል እምነት አለን። በመሆኑም ሁልጊዜም ለሃይማኖታችን ባህሎች ከፍተኛ ትኩረት እንድንሠጥ እናሣስባለን። እክሎች ሲያጋጥሙን ለማስወገድ የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በትክክለኛው መንገድ ላይ እንዲያፀናንና በዚህች ዓለም ላይ ሰላምንና ፍትህን እንድናሰፍን ይረዳን እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊነትንና ጭቆናን እንድናስወግድ ይረዳን ዘንድ አላህን እንለምነዋለን።