ለአላህ ብሎ የመዋደድ መርህ (ክፍል 3)

0
5090

ወንድማማችነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዙ መንገዶች

እስልምና በሙስሊም ወንድሞች መካከል ውዴታን ሊጨምሩ የሚችሉ መንገዶችን አመላክቷል። ወንድሞች በነኚህ ምልከታዎች የሠሩ እንደሆነ ወንድማማችነታቸው ጥብቅ ይሆናል። ግንኙነታቸውም ጥልቀት ይኖረዋል።

  1. አንድ ሰው ወንድሙን የወደደ እንደሆነ እንደሚወደው ይንገረው

አቡዳውድ እና ቲርሚዚ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው ወንድሙን የወደደ እንደሆነ እንደሚወደው ይንገረው።”

አቡ ዳውድ ከአነስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት አንድ ሰውዬ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘንድ ተቀምጦ ሣለ አንድ ሌላ ሰው አለፈ። ሰውየውም “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኔ ይህን ሰው እወደዋለሁ።” አላቸው። ነቢዪም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “እንደምትወደው አሣውቀሀዋልን?” አሉት። ሰውየውም “የለም አልነገርኩትም።” አላቸው። እርሣቸውም“በል አሣውቀው።” አሉት። ተከትሎት ሄዶ እንደሚወደው ነገረው። ሰውየውም “ለርሱ ብለህ የወደድከኝ አላህ ይውደድህ።” በማለት መለሠለት።

2.አንድ ወንድም ከወንድሙ ተለይቶ ከሄደ በሩቅ እርሱ በሌለበት አስታውሦ ዱዓእ እንዲያደርግለት ይጠይቀው

አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚ እንደዘገቡት ዑመር እንዲህ አለ፦“ዑምራ ለማድረግ ፈልጌ ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አስፈቀድኳቸው። እርሣቸውም ፈቀዱልኝና እንዲህ አሉኝ “ወንድምዬ! በዱዓእህ አትርሣን።” ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እጅግ ከመደሠታቸው የተነሣ  “ዱኒያ ሙሉዋን ከሚሠጠኝ ይህችን ቃል እመርጣለሁ።” ብለዋል። በሌላ ዘገባ ደግሞ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዑመርን“ወንድሜ ሆይ! ከዱዓእህ አጋራን።” እንዳሉት ተላልፏል። ሙስሊም እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሙስሊም የአላህ ባሪያ ወንድሙ በሌለበት በሩቅ ዱዓእ ያደረገለት እንደሆነ መልዓክ “ላንተም ተመሣሣዩን።” ይለዋል።

3. አንድ ወንድም ወንድሙን ያገኘ እንደሆነ ፊቱን ፈታ ያድርግ

ከአቢ ዘር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “መልካምን ነገርን ትንሽ ናት ብለህ አትናቅ። ወንድምህን ፈታ ባለ ፊት ማግኘት ቢሆንም እንኳ።” አንድ ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን ሲያገኝ እሱን በማግኘቱ ብቻ ከምንም በላይ መደሠትና ደስ መሠኘቱንም በፊቱ ላይ ማስነበብ ይኖርበታል።

4. አንድ ወንድም ወንድሙን ያገኘ እንደሆነ ተሸቀዳድሞ ይጨብጠው

አቡ ዳውድ አልበራእ ብኑ ማሊክን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፦ “ሁለት ሙስሊሞች ተገናኝተው የተጨባበጡ እንደሆነ ከመለያየታቸው በፊት አላህ ምህረትን ይለግሣቸዋል።”

5.ደጋግሞ ሙስሊም ወንድምን መዘየር

ኢማም ማሊክ አል ሙወጠእ በተባለ ኪታባቸው ውስጥ እንዳሠፈሩት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል “ውዴታዬ ስለኔ ብለው ለተዋደዱት፣ ስለኔ ብለው ለተቀማመጡትና ስለኔ ብለው አብረው ለተጎሳቆሉት ሆነች።” 

6.በየአጋጣሚዎች የደስታ መልእክት ማስተላለፍ

ጦበራኒ አነስ ኢብኑ ማሊክን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በመጥቀስ ሰጊር በተባለ መፅሃፋቸው ውስጥ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ወንድሙ የሚወደውን ነገር በማግኘቱ መደሰቱን የገለፀለት ሰው የትንሣኤ ቀን ልእልናው ከፍ ያለ አላህ ያስደስተዋል።”

የተሻለው የደስታ መግለጫ ዱዓእ እንዲህ ቢሆን ይመረጣል

  • ልጅ የተወለደለት እንደሆነ

“የተሠጠህን አላህ ይባርክልህ። ሰጪውንም አመስጋኝ ሁን። ጎልምሦና ደርሦ የሱን ግልጋሎት ለማግኘት ያብቃህ።”

  • መንገድ ቆይቶ ለተመለሰ ሰው

“በሠላም ለመለሰህ፣ ነገሮችን ለሰበሰበልህና ውለታውን ለዋለልህ አላህ ምስጋና ይሁን።”

  • ከጅሃድ ውሎ የገባ እንደሆነ

“ምስጋና ድልህን ለሠጠህ፣ ከፍ ላረገህና ላከበረህ ጌታ ይሁን።”

  • ከሀጅ ለተመለሠ ሰው

“አላህ ሀጅህን ይቀበል፣ ወንጀልህን ይማር። ወጭህንም ይተካልህ።”

  • ያገባ እንደሆነ ደግሞ

“አላህ ይባርክልህ። ባንተም ላይ በረከቱን ያውርድ። በመልካም ነገር ላይም ያሠባስባችሁ።”

  • ከዒድ ላት በኋላ ደግሞ

“አላህ ከኛም ከናንተም ይቀበል።”

  • በጎ ውለታ የዋለለት እንደሆነ ደግሞ

“አላህ ይባርክህ። ቤተሰብህንና ንብረትህንም ይባርክልህ። በመልካምም ይመንዳህ።”

ከዚህም ሌላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማለትም በበዓላት ወቅት፣ አንድ ወንድም ድልን አሊያም ሰኬትን የተጎናፀፈ እንደሆነ እና በሌላም ሌላም ጊዜ አጋጣሚዎችን በመጠበቅ ስጦታዎችን ቢያበረክትለት ግንኙነታቸው ይጠብቃል።

አነስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም“ስጦታ ተሠጣጡ። ስጦታ ውዴታን ያወርሣል። ጥላቻን ያስወግዳልና።” ብለዋል።

ጦበራኒ ከእናታችን ዓኢሻ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ስጦታ ተሠጣጡ ትዋደዳላችሁ።” ብለዋል።

7. የወንድምን ሃጃ /ጉዳይ/ ለመፈፀም አብዝቶ መጨነቅና ማሰብ

ሙስሊም ከአቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ከዱኒያ ጭንቀቶች መካከል ከአንዱ ጭንቅ አማኝን የገላገለ ሰው ከትንሣኤ ቀን ጭንቀቶች ከአንዱ አላህ ይገላግለዋል። አንድ ነገር የከበደውን ሰው ያግራራለት ሰው አላህ በዱኒያም ሆነ በአኺራ ያግራራለታል። የሙስሊምን ነውር የሸፈነን ሰው አላህ ነውሩን ይሸፍንለታል። አንድ ወንድም ወንድሙን በመርዳት ላይ እስከዘወተረ ድረስ አላህ ይረዳዋል።፡”

8. በመጨረሻም አንድ ሙስሊም ወንድሙ በርሱ ላይ ያለውን ሀቆች በሙሉ መወጣት ይኖርበታል

አንድ ወንድም በሌላኛው ወንድሙ ላይ ያለው ሀቅ ምን ምን እንደሆነ በተለያዩ የነቢዩ ሀዲሶች ላይ ተዘርዝሯል። ከነኚህም መካከል ሲታመም መጠየቅ፣ የጋበዘው እንደሆነ ምላሽ መስጠት፣ ሲያስነጥሰው የርሀምከላህ በማለት ማስደሠት፣ ሲበደል ማገዝ እና የመሣሰሉት የተለመዱት ናቸው።

ማጠቃለያ

አንድ ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን እንደሚወደው የነገረው እንደሆነ፣ ተራርቀው ሣሉ እሱ በሌለበት ዱዓእ እንደሚያደርግለት ካሣወቀው፣ ባገኘው ጊዜ በፈግታና በሠላምታ የሚቀበለው ከሆነ፣ በደስታው ጊዜ ደስ እንዳለው በመግለፅ የእንኳን ደስ አለህ መልእክት ካስተላለፈለት፣ በየአጋጣሚዎችም ስጦታ የሚሠጠው ከሆነ፣ በየጊዜውም ስለ አጠቃላይ ሁኔተዎች ከጠየቀውና ከዘየረው፣ ጉዳዮቹንም ለመፈፀም ከፍተኛ ሀሣብና ፍላጎት ካሣየለት፣ ሀዘኑና ህመሙን ለመካፈል ዝግጁ የሆነ እንደሆነ.. እነኚህንም አጠቃላይ ሀቆች በተሟላ መልኩ የፈፀመ እንደሆነ የውዴታ ገመዳቸው ይበልጥ የመጠናከሩ ነገር አያጠራጥርም። ከቃል አልፎ በተግባር የተንፀባረቀው የውዴታ ትርጉሙም ያኔ ግልፅ ብሎ ይነበባል። ወንድማማችነትን ማሳደግና ማበልፀግ የሚቻለው በዚህ መልኩ ጥረት ሲደረግ ነው። የቀረውን ቀናትና ጊዜያት እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጥልቀቱ ሥር ስለሚሰድ ትስስሩ ይበልጥ የፀና ይሆናል።

(ይቀጥላል…..)


 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here