የለውጥ አብዮት በረመዷን!

0
6075

ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አልሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል-ዓለሚን ወስ-ሶላቱ ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ፡፡ ወዐላ ኣሊሂ ወሳሕቢሂ ወመን ዋላህ አም-ማ ባዕድ፡-


በአላህ ስም እጅግ አዛኝ ሩሕሩህ በሆነው፡፡ ምስጋና ለዐለማት ጌታ ለአላህ ብቻ የተገባ ነው፡፡ የአላህ እዝነቱና ሰላምታው በአላህ መልእክተኛ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና በተከተሏቸው ሁሉ ላይ ይሁን፡፡

ሁሉንም ዒባዳ ችግር ውስጥ የሚጥል ትልቁ በሽታ ያንን ዒባዳ መልመድ ነው፡፡ ዒባዳውን ስንለምደው መሰላቸት በቀስታ ልባችን ውስጥ ይገባል፡፡ ከመሰልቸታችን ተከትሎ መዋለል እና ዒባዳውን ማቋረጥ ይከተላል፡፡ ስለዚህ አስተዋይ እና የኢማን ጥንካሬ ያላቸው ክቡር ሰዎች ይህንን ክቡር እንግዳ እንደ አዲስ ማየት አለባቸው፡፡ በየአመቱ የተለየ እንግዳ ነው፡፡

ፍሬውን የምንቆርጥበት ጊዜው ቋሚ እንዲሆን፣የበጎ ነገር ምንጩ ሳይደርቅ እንዲቆይ፣ትርፉ እንዲጎመራ፣አዝመራው እንዲደምቅ፣ቋሚነት እንዲኖረው፣የየአመቱን ረመዷን እንደ አዲስ እንግዳ መቀበል አለብን፡፡ ረመዷንን ልክ እንደከበረ ድንጋይ (እንደ ሉል) መቁጠር አለብን፡፡ ብርሀን  ሲያርፍበት የተለያዩ ቀለማት ከውስጡ ይንፀባረቃሉ፡፡ ያኔ ስልቹነትና ስንፍና እንዳልነበሩ ይሆናሉ፡፡ ወኔና ብርታት ልቦች ውስጥ ይነግሳሉ፡፡

እስኪ የዚህን አመት ረመዷን አዲስ ጣዕም እንስጠው፤አዲስ ሥራ እንስጠው፤በህይወታችን ውስጥ አዲስ ሚና እንዲጫወት እናድርገው፤ ረመዳንን የለውጥ አጋዣችን እንዲሆን እናድርገው፡፡ ያንተ ለውጥ ኡመቱን በሙሉ ይለውጣል፤የእኛ ለውጥ የአሏህን ሥራ ይቀይራል፡፡ይህንን ጉዳይ የሚከተለው አንቀፅ ይነግረናል፡፡

إِنَّ اللَّهَ لَا يُغَيِّرُ مَا بِقَوْمٍ حَتَّىٰ يُغَيِّرُوا مَا بِأَنفُسِهِمْ

አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ በነፍሶቻቸው ያለውን (ኹኔታ) እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም፡፡ ሱረቱል ራእድ(13፣11)

ነገርግን የብዙዎቻችን ልብ ይህንን እውነታ ላለመቀበል ተዘግቷል፡፡ ለውጥ ባለፉት ዘመናት አስፈላጊ ከነበረ፤ዛሬ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ውድ ወንድሞችና እህቶች ! ህዝባችን ያለበትን አዘቅት ተመልከቱ!

በሙስሊሙ ዓለም ላይ የሚፈሰው ደም ልባችንን አያደማውም?! በቁጭት አያናደንም?! በየዕለቱ ይፈርሳል እየተባለ የሚጠበቀው የሙስሊሞች ሁሉ ንብረት ምርኮኛው “አል-አቅሷ” እንቅልፍ አይነሳንም?! በሁሉም ዘርፍ እኛ ሙስሊሞች ወደ ኋላ መቅረታችን አያቃጥለንም?! በኢኮኖሚው ዘርፍ አዝጋሚ ልማት ሲመዘገብስ?! በማህበራዊ ህይወት ዘርፍ በድሆች ሂሳብ የሃብታሞች ብልፅግና ሲያድግስ?! ወንጀል ተንሰራፍቶ ሰላም ሲጠፋስ?! ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ወንጀሎች ሲበረክቱስ?! አጥፍቶ መጥፋት እና ተያያዥ ጭንቀቶች ሲንሰራፉ?! ይህ ሁሉ ልባችንን አይሰረስረውም?! አያስቆጨንም?! …………

በፖለቲካዊ ዘርፍ ወንድምህን የ‹‹ጠላት ጠላትን ወዳጅ አድርግ›› መርሃችን ሆኗል፤በመሃላችን የመሳሪያ ድምፅ አይሏል፤በአጥፊ መሳሪያዎች መፎካከርና መዛዛት ጀምረናል፡፡

ለኢስላም እና ለሙስሊሞች ለሚጨነቁ ሁሉ!!

እንደውም ህያው ለሆኑ ሰዎች በሙሉ… የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ረመዷን ከወርቅ በላይ የሆነ ውድ አጋጣሚ እንደሆነ እንንገራችሁ፡፡ ይህንን የምንለው በሦስት ምክንያቶች ነው፡-

1.ረዥም የለውጥ ጊዜ፡-  ፆመኛ ሰላሳ ቀን በፍቃዱና በፍላጎቱ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከወሲብ ፍላጎት ይታቀባል፡፡ ስሜቱን ይቆጣጠራል፡፡ ለስድብና ለውዝግብ ምላሽ አይሰጥም፡፡ እኔ ፆመኛ ነኝ በሚለው ቃል ሥር ይደበቃል፡፡

ይህ የጊዜ ርዝመት እውነተኛ ኒያ ከታከለበት የሚጠበቀውን ለውጥ ለመፍጠር ይበቃል፡፡ የስነልቦና ምሁራን  አንድ ሰው አንድን ተግባር ከስድስት እስከ ሰባት ቀናት አከታትሎ ከሠራው የስነልቦናው አካል ማድረግ እንደሚችል እና ያንን ጠባይ መንፈሱ ውስጥ መትከል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም ጊዜው ጀነት የሚከፈትበት፣ የጀሀነም በሮች የሚዘገቡት፣ ሰይጣናት በመታሰራቸው ኃይላቸው የሚደክምበት፣ ይደርሱበት የነበረው ቦታ ላይ ከመድረስ የሚሳናቸው የተባረኩ ቀናት ናቸው፡፡ የአሏህ ይቅርታ ሁሉን አዳርሶ በየእለቱ ከእሳት ነፃ የሚያደረጉ ሰዎች ይበረክታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ውጤቱን አመርቂ፣ ለውጡን ቋሚ የሚያደርጉ ብዙ መንገዶችም ከመኖራቸው ጋር ነው፡፡

አዎን! የለውጥ ጊዜው በረመዷን ውስጥ ሰላሳ ቀን ይፈጃል፡፡ ፍቱን የሆኑ መድሃኒቶች የምንወስድባቸው ተከታታይ ሰላሳ ቀናት ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ፈውስ ማስገኘቱ፣ በሽታን ከሥሩ መንቀሉ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ከመለኮት ከተሰጡ የስልጠና ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ አንድ ሰው በየዕለቱ ትንሽ የሚባልን አንድን ተግባር  መፈፀሙ እንኳን ብዙ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ብዙ ስራዎች ተሰብስበውለት ሲተገብራቸውስ? ረመዷን ከዚህ አኳያ ራሱን ላሰናዳ በፕሮግራምና በእቅድ ለሚመራ  ሰውም ሆነ ላልተሰናዳ (እቅድ ለሌለው) ሰው የሚሆን ሙሉ ስርዓት እንኳን አለው፡፡ ሌሎች የአመቱ ወራት የሌላቸው ብዙ ነገር እርሱ ብቻ አለው፡፡ ታዲያ እንዴት በዚህ ጊዜ አትለወጥም!?

ከዚህ ጊዜ የተሻለ ምቹ እድል አታገኝም !!!

እሺ ዛሬ ካልሆነ በጌታችን አላህ ይሁንብን መቼ ይሆን የምትለወጠው!? አንድን ሰው መልካም ነገር በአንድ ወቅት ሰርቶ መልሶ መተዉ የሰራው በጎ ሥራ በልብ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ያዳክመዋል፡፡… ነገርግን በጎ ስራ ቋሚና ተከታታይ ከሆነ በልብ  ላይ የሚያሳድረው ጫና መልካም ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው የአሏህ እዝነት ሆኖ አንድ ወር ሙሉ እንድንፆም አሏህ በእኛ ላይ ግዴታውን የደነገገው፡፡ ያለምክንያት ማፍጠርን እርም ያደረገው፡፡ አንድ ቀንም ቢሆን ማፍጠር አይቻልም፡፡ ነገሩ በግርድፉ ሲታይ ግዳጅ ይመስላል፡፡ ነገርግን ውስጠ ነገሩ ፀጋና ቱሩፋት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ይህንን ወር በትክክል የፆመ ሙስሊም ልቡ ሲነካና በታላቅ መንፈስ ልቡ ታጥኖ የምታየው፡፡ ከወሩ በኋላ መቀጠል እና መዘውተር በሰውየው ስራ ይወሰናል፡፡ ያካበተውን ኃብት መጠበቅ ይቻላል?! ከመርሳት እና ከቸልተኝነት ይጠነቀቃል?! ወይስ ትርፉን እና ኃብቱን በመንገድ ላይ ይጥላል!?…

2.ከህዝብ ጋር አብሮነት፡- ነፍስህን ከጎረቤቶችህ እና ከስራ ባልደረቦችህ ተለይታ ፆማ ካገኘሃት፣ ወይም የሰውን ክብር ከሚያጎድፉ ሰዎች ርቀህ ምላስህን ከጠበቅክ፣ ወይም በኃጢያታቸው ከሚኮሩ ሰዎች መሀል አይናፋር ሆነህ ከተገኘህ በእንዲህ መሰል ጊዜዎች ግፊቶችን ተቋቁመህ ራስህን መጠበቅ ከቻልክ ይህ አቻ የሌለው ትልቅ ጀግንነት ነው፡፡

ይህ ረመዷን ውስጥ የማታገኘው ጭንቀት ነው!

በረመዷን አንተ ከብዙ ህዝብ ጋር ነው የምትፆመው፣ግርማ ሞገስ ካለው የሙእሚኖች ማዕበል ጋር ነው፡፡ ወደ ተራዊሕ ሶላት የምትሄደው፣ በሺዎች ከሚቆጠሩ የአሏህ ምህረት ከጃዮች ጋር የቁርዓን ኺትማዎችን ታደምጣለህ፡፡ ስለዚህ መንገድህን የያዙ ሰዎች በማነሳቸው ቅሬታ አይኖርህም፡፡ እንደውም ትበረታታለህ፡፡ ልብህ ይጠነክራል፡፡ በጎ ሥራዎችን ለመከወን ስሜትህ ይነሳል፡፡ ከወሩ በፊት ሰነፍ ብትሆንም አሁን ግን ትነቃለህ፡፡

ይህን ማነቃቂያ ከረመዷን ውጭ አታገኘውም፡፡ እንደ ረመዷን መቼ መስጂዶች ይሞላሉ!? በቁርዓኑ ወር ሰዎች የአሏህን ቃል በማንበብ እንደሚወዳደሩትስ መቼ ይወዳደራሉ!? ያኔ ለድሆች እጃችው እንደሚፈታው እና ችግረኞችን እንደሚደግፉት መቼ ይፈታል!? ስለዚህ ወንድሜ ሆይ! እህቴ ሆይ!  ለነፍስህ ድረስላት! ከአመቱ ቀናት ሁሉ የበለጠው ትልቁ የትርፍ ጊዜ እንዳያመልጥህ !!

  1. ሁለንተናዊ ለውጥ፡- በዚህ ፅሁፍ ውስጥ እንደምታገኘው የሚጠበቀው ለውጥ አምስት መሰረታዊ ገፅዎችን ይነካካል፡፡ የሰዎችን ህይወት በሙሉ ዝርዝሩ ይዳስሰዋል፡-

ልማዶች፡- በዲንህና ወይም ዱንያህ ላይ ብዙ በረከቶችን ያሳጡህን ነገሮች ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

አምልኮዎች /ዒባዳዎች/፡- እነዚህ ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ እነርሱን በመተግበር ሰው ወደ ጌታው የሚቀርብባቸው ዋና ዋና የአምልኮ ተግባራት፡፡ ለምሳሌ፡- ሶላት፣ ፆም፣ ሶደቃ እና ሐጅን የመሳሰሉት፡፡ ወይም ሰውየው እነርሱን በመተዉ ከጌታ ጋር የሚቃረብባቸው  እርም የተደረጉ ተግባራት፡፡

የቀልብ ሥራዎች ፡- እነዚህ ታላላቅ የቀልብ ሥራዎች ሁሉ ያካትታሉ፡፡ አጅራቸው የከበዱ ግዙፍ የልብ ተግባራትን ያጠቃልላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- አሏህን መፍራት (ኹሹዕ)፣ ሙራቀባ (አላህን መጠባበቅ)፣ ውሳኔውን መውደድ (ሪዷ)፣ ትእግስት (ሶብር) እና የመሳሰሉት ሁሉ ይጠቀሳሉ፡፡

ከሰዎች ጋር ያለን ትስስር፡- ከቤተሰቦችህ፣ ከጎረቤቶችህ፣ ከወዳጆችህና ከጓደኛህም ጋር የሚኖርህ ግንኙነት፤እንደውም ከሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የሚኖርህ ትስስር እዚህ ውስጥ ይቃኛል፡፡

ግንዛቤዎችህ፡- የተሳሳቱ ግንዛቤዎችህ፣ አጥፊ እምነቶችህ፣ አፍራሽ የሆኑ ፉካሬዎችህ በሙሉ እዚህ ውስጥ ታይተዋል፡፡ንግግርህን በሙሉ የሚቆጣጠሩና የብዙ ሰዎችም የግንዛቤ አካል የሆኑ ሃሳቦችህ በሙሉ ተጠቃለዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ ለውጥ ግዙፍ ነው! ቅርፊቱን አልፎ ፍሬውን የሚነካ፤ገፅታን ጥሶ አስኳሉን የሚዳስስ፡፡ ስለዚህ መራሩን ተጨባጭ መቀየር ከፈለግን ትልቅ ሥራና ረጅም ትእግስት ያስፈልገናል፡፡ የአሏህን መንገድ ከተውን ጀምሮ ከገባንበት ከጨለማው ምሽግ እንድንወጣ ዘንድ ስራ መጀመራችን ክብር ነው፡፡  ክብሩን የሚጨምረው ደግሞ የጀመርነው በተከበረው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ረመዷን ከተለወጥን እስካሁን መዘግየታችን አይጎዳንም፡፡ ክብር ልቅና በስተመጨረሻ ላመነ፣ ለፀና እና ለታገሰ ሰው ነው፡፡ቀድሞ መጓዝ ከጀመረ በኋላ በመጨረሻው ሰዐት ለተኛው ሰው አይደለም፡፡

ክቡራን ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ! ይህ ወር የተባረከ ወር ነው በናንተ ላይ ያጠለለው፡፡ በወሩ ውስጥ ባለው የተባረከ ለሊት ውስጥ የተባረከው መፅሀፍ ወርዶበታል፡፡ ይህ ግልፅና የማያሻማ ነገር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ወር ውስጥ እነዚህን የለውጥ ገፅታዎች ህይወትህን ካላላበስክ በየትኛው ጊዜ ነው ሚሳካልህ?!


 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here