እድገት የሠዎች ሁሉ ፍላጎት ነው። ዛሬ ዛሬ ሁሉም ኃይማቶችና ባህሎች ስለ ልማትና እድገት ያስባሉ። መንግሥታት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚሊዮኖች ፈሰስ እያደረጉ ነው። ሠዎች ስለ ልማት ስትራቴጂዎች፣ ስለ እድገት ፕላን፣ ወዘተ ያወራሉ።
ሙስሊሞችም ስለራሳቸውና ስለማኅበረሰባቸው እድገት፤ አሁን ካሉበት ነባራዊ ኹኔታ እንዴት ወደተሻለ ተጨባጭ መሄድ እንዳለባቸው በጽኑ ማሰብ ይገባቸዋል።
ልማትና እድገት የኢስላም መሠረታዊ ግብና ዓላማ ነው። ኢስላም የግለሠቦችንም ሆነ የሕብረተሰብን እድገትና መሻሻል ይፈልጋል። ሁሉም ሠዎች እንደችሎታና ልፋታቸው ሊያድጉ ይገባል። ልማት ማለት የግለሠብና የሕብረተሠብ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ማደግ ነው። አላህም ለሠው ልጆች የተለያየ አቅምና ችሎታ ሠጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ሠውም በተሠጠው እምቅ ችሎታ ተጠቅሞና ራሱን ማሳደግና ነገውን ማሳመር የራሱ ኃላፊነት ነው።
እድገት ቁሳዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካ እንደሆነው ሁሉ ሞራላዊና መንፈሳዊም መሆን አለበት። መንፈሳዊና ሞራላዊ ጉዳዮቻቸውን ረስተው በቁሳዊ መሻሻል ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ ግለሠቦችና ሐገራት እድገታቸው ረጅም ጊዜ አይቆይም።
ሆኖም፤ እንደ ኢስላም እይታ ልማት ማለት ሚዛንንና ሕብር (harmony)፣ ፍትህና ሠላም፣ ብልጽግናና ያማረ ሕይወትን መፍጠር ነው። ማለትም እድገቱ ሠውን ምሉዕ በሆነ ሁኔታ ነፍስን ከሥጋ ሥጋን ከአዕምሮ ሳይነጥል መቀየርና ማሻሻል ነው። የእስልምና እድገት ትርጓሜ አዕምሮን ጨፍልቆ አካልን የሚያፋፋ ወይም ነፍስን እንደ ሻማ አቅልጦ አዕምሮን የሚያበለጽግ አይደለም። ሦስቱም አስፈላጊ በመሆናቸው እኩል እንክብካቤና ጥበቃ ያሻቸዋል። ልማትና እድገት በእስልምና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት። እድገት ቁሳዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካ እንደሆነው ሁሉ ሞራላዊና መንፈሳዊም መሆን አለበት። መንፈሳዊና ሞራላዊ ጉዳዮቻቸውን ረስተው በቁሳዊ መሻሻል ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ ግለሠቦችና ሐገራት እድገታቸው ረጅም ጊዜ አይቆይም። ዛሬ እንደምናየው ሞራልና መንፈስ ያልተካተቱበት ኢኮኖሚያዊና ቁሳዊ እድገት ውጤቱ ጭንቀት፣ ድብርትና የስነ-ልቦና በሽታ ነው።
ከዚህ የሚከተሉት ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው እድገትና ልማት ለማረጋገጥ የሚረዱ መሠረታዊ ነጥቦችን ከኢስላም አንጻር እናያለን።
- ተዝኪያህ– መንፈሳዊ እድገት
- ተርቢያህ– ሞራላዊ እድገት
- ተንሚያህ– ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት
- ተጠዉር– የትምህርትና ባህላዊ እድገት
- ተቀዱም– ሥልጣኔያዊ እድገት።
እያንዳንዳቸውን በዝርዝር እንቃኛቸው፡-
1. ተዝኪያህ
የእድገት ወሳኙ ክፍል ነው። ተዝኪያህ ለመልካም እድገት ቅድመ-ሁኔታ የሆነ መጥራራት ነው። ያለ መንፈሣዊ ንጽህና (ተዝኪያህ) ጤናማ እድገት አይታሰብም። እርሻ አርሶ፣ ከአዝዕርቱ ላይ አረምና አላስፈላጊ ሳሮችን እያስወገደ ሳይሠለች ውሃ እያጠጣ የከረመ ትጉህ ገበሬ አመርቂ ውጤት እንደሚጠብቀው ሁሉ መንፈሳዊ ንጽህናው ያልተጓደለ እድገትም ፍሬው ያማረ ይሆናል። ኢስላምም ከኛ የሚጠብቀው ከኃጢያታችን እንድንጸጸት፣ ከመጥፎ ባህሪያታችንም እንድንታቀብ፣ ሠውነታችንን በውዱዕ፣ በሶላት፣ በዚክር (አላህን በማስታወስ)፣ በጾምና በሦደቃ (በምጽዋት) እንድንመግበው ነው። ዕለት ተዕለት እውቀታችንን እንድናዳብር ለቤተሠባችንና ለማኅበረሰባችንም መልካም እንድንውልም ይጠብቅብናል። ከዚህ በኋላ ቀስ በቀስ የምንጠብቀውን መልካም፣ ጤናማ እና ሁሉን አቀፍ እድገት ማረጋገጥ ይቻላል።
2. ተርቢያህ
ተርቢያ ቃል በቃል ስንተረጉመው ማሳደግ እና ማሻሻል ማለት ነው። ቃሉ ከትምህርት ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ብዙ ጊዜም ‘ታዕሊም’ እና ‘ተርቢያ’ የሚሉትን ቃላት በጋራ እንጠቀማለን። ትምህርት መረጃን፣ እውቀትን እና ክህሎትን መቀበል ሲሆን በአንጻሩ ተርቢያህ ግለሠቡን በዲሲፕሊንና በሞራል ማሳደግ ነው። እውቀት በራሱ አያድንም። የሚያስፈልገው እውቀትን በአግባቡ መጠቀም ነው። ልጆች ገና ከልጅነታቸው አንስቶ በከፍተኛ ሞራል ሊያድጉ ይገባል። ወላጆችም የወላጅነት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ወላጆች የልጆቻቸው ጓደኞች እንደሆኑ ማወቅና ለኢስላማዊ ትምህርታቸውም ትኩረት ሊሠጡ ይገባል።
ተርቢያ አስፈላጊነቱ ለልጆች ብቻ አይደለም። ወጣቶች እና ጎልማሶችም ቀጣይነት ያለው ተርቢያ ሊሠጣቸው ይገባል። ይህ ሊረጋገጥ የሚችለውም በልዩ የተርቢያ ፕሮግራሞችና ሥራዎች ነው። ሠዎች መታወስን (ተዝኪር) እንደሚፈልጉት ሁሉ መልካም እና ዋጋ ያለው መንገድን ይከተሉ ዘንድ አስታዋሽ ያስፈልጋቸዋል።
3. ተንሚያህ
ተንሚያህ ቀስ በቀስ የማደግ እና የመለወጥ ሒደት ነው። ተንሚያ ላይ ያለው ቁም ነገር እድገት እንዲሁ ድንገት የሚመጣ ነገር አለመሆኑ ነው። ተንሚያህ ማለት በጥንቃቄና በክትትል ተክልን እንደማሳደግ ነው። ይኸው መንገድም ነው ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ እድገት ያገለግላል። ኢስላማዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት ኢኮኖሚና ማኅበሠብን ነጣጥሎ አያይም። ኢኮኖሚያዊ ‘ተንሚያህ’ የኢኮኖሚ ምንጮችን፣ ማሳደግ እና ማሻሻል እንዲሁም ድህነትን ማስወገድ፣ በራስ መብቃቃትና የራስ ኃብትን ማፍራት ነው። ማኅበራዊ ተንሚያ የሚተባበሩ ቤተሰቦች፣ የሚተሳሰቡ ጎረቤቶች፣ የዘር፣ የቀለም እና የዕምነት ልዩነት የሚያቻችል ሲቪል ማኅበረሰብ መገንባት ነው። ሁሉንም እድገቶች የሚያካትተው የፖለቲካ ተንሚያ አለ። ፖለቲካዊ ተንሚያ ሕግና ሥርዓት የሚከበርበት፣ ትብብርና ምክክር (የሚታይበት) ማኅበረሰብ መገንባት ነው።
4. ተጠዉር
ተጠዉር ከአንድ ደረጃ ወደ አንድ ደረጃ መሸጋገር ነው። አላህም በሱረቱ ኑህ ምዕራፍ 71 አንቀጽ 41 ላይ ፍጥረትን ደረጃ በደረጃ እንዳስገኘ ይገልጻል።
እድገትም በደረጃ ነው። ሁሌም ቢሆን ከአንድ ደረጃ ወደተሻለው መሻጋገር አለብን። በኢስላማዊ እድገት ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ በትምህርትና በባህል መሻሻል ማሳየት ይኖርበታል። በዚህ ማኅበረሠብ ውስጥ የአዕምሮ እድገት መጨመር ሕዝቡም የአላህን ሳይንሳዊና ተፈጥሯዊ ተዓምራት ማድነቅ መልመድ አለበት። ባህሉም የሞራሉን ጥንካሬ፣ የአዕመሮውን ምጥቀት ማሳየት አለበት። ተጠዉር ማለት ዛሬያችን ከትናንታችን፣ ነገአችንም ከዛሬያችን መሻል ማለት ነው። አኼራችንም ከዱንያችን ይበልጥ ማማር አለበት። ይሔ እንግዲህ የእያንዳንዱ ሙስሊም ግለሠብ እቅድና ዓላማ መሆን አለበት።
5. ተቀዱም
ተቀዱም የሥልጣኔ እድገትና ልማት ነው። ልክ እንደ ተጠውር ተቀዱምም ደረጃ በደረጃ ይከሰታል። ሆኖም፤ ተቀዱም ግን የሁሉም ማኅበረሰብ ለውጥ ነው። የግለሠቦች እድገት፣ ወይም የጥቂት ልሂቃን መሻሻል ተቀዱምን አያመጣም። ተቀዱም እንዲመጣ ሁሉም ማኅበረሠብ መለወጥ አለበት። የጥረታችን የመጨረሻ ግብም ይኼው መሆን አለበት። ቤቶቻችንም ሆነ መስጂዶቻችን፣ ትምህርት ቤቶቻችንና ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ባዛሮቻችንና ፋብሪካዎቻችን፣ ባንኮቻችንና የኢንቨስትመንት ኩባንያዎቻችን፣ ፍርድ ቤቶቻችንና ፓርላማችን፣ የፖሊስና ወታደራዊ ተቋሞቻችን ሁሉ ወደዚህኛው እድገት ሊያፋጥኑን ይገባል። ወላጆች በቤት ውስጥ፣ ኢማሞች በመስጂድ፣ ነጋዴዎች ገበያ ቦታ፣ ሠራተኞች በፋብሪካ፣ ዳኞች በችሎት፣ ፖሊሶች በከተማ፣ ከንቲባዎች፣ የክልል አስተዳደሮች፣ ሁሉም በተናጠልና በጋራ ተቀዱምን ማምጣት ግባቸው ሊሆን ግድ ነው። አለበለዚያ፤ ሁሉም ካልተሳተፈበት ተቀዱም እውን አይሆንም።
እድገት ትዕግስትና ትግል ይጠይቃል። ትግሉ የሚካሄደው ከኢ-ፍትሃዊነት፣ ከሙስናና ከመጥፎ አስተሳሰቦች ጋር ሁሉ ነው። ትግሉ ለሠዎች ሁሉ ሞራላዊና ቁሳዊ እድገት ለማስገኘት የሚችል አዎንታዊ መሆን አለበት። ይህ የልማት ሥራ ግለሠባዊም የጋራም ነው። ውጤታማ እንዲሆንም የሁሉን ጥረት ይሻል።