ረመዳንና የለውጥ ክፍሎቹ

0
5511
Man on top of mountain

እንኳን ለተከበረው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ፡፡ የረመዳን ወር ሙስሊሞች በጉጉት የሚጠብቁት ታላቅ ወር ነው፡፡ ረመዳን ለአጠቃላይ ማንነታችን ነፍስን ለማስተካከልና ለማረቅ ውድ የለውጥ አጋጣሚም ነው፡፡ ይህ የተላቀ ወር የለውጥ ክፍሉ በፆም ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ የአላህ ፍራቻን ያጎናፃፋል፡፡ሙስሊሞች ከፆሙና ከያዘው ሀይማኖታዊ ፋይዳ አንፃር የመንፈሳዊና የስነምግባር ከፍታ የሚገኝበት ወር እያሉ ይሰይሙታል፡፡

የለውጥ ክፍሎቹ ከሁኔታ ወደ ሁኔታ፣ ከግለሰብ ወደ ግለሰብ፣ከቦታ ወደ ቦታ፣ ከባህሪ ወደ ባህሪ ልዩነት ሲኖረው በአጠቃላይ ሙሉ የለውጥ ክፍሎችን ይዳስስልናል፡፡

1- ሙስሊም ከፈጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት

በዚህ የተቀደሰ ወር አንድ ባሪያ ከፈጣሪው አላህ ጋር የሚኖረው ግንኙነት እጅግ ከፍ ብሎና ልቆ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ቀረቤታ በዚህ ወርም ሆነ በተቀሩት ወራትም የሚቀጥልና ግዴታ ነው፡፡ የረመዳን ጌታ የተቀሩት ወራትም ጌታ ነውና፡፡ የአላህን ትእዛዛትን መፈፀም ሆነ ከእርሱ ጋር ያለውን ቀረቤታ ለአንድ ወር ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ይህ የለውጥ መንገድ ቀጣይነት ያለውና ዘወትር ትእዛዝን በመፈፀም የታጀበ ነው፡፡ይህ ጉዞ ዘውታሪነትን አንዲላበስና እስከእለተ ፍፃሜ መቃረቢያ እንዲሰነብት ደረጃ በደረጃ የሚያበቃው ነው፡፡

فعن عائشة – رضي الله عنها – أنها قالت: سئل النبي – صلى الله عليه وسلم -: أي الأعمال أحب إلى الله؟

 قال: ((أدومُها وإن قل))

 አዒሻ(ረዐ) በዘገበችው ሀዲስ ላይ እንዲህ ትላለች፡፡ መልእክተኛው(ሰዐወ) ተጠየቁ፡ የትኛው ስራ ነው ወደ አላህ የተወደደ ?            እንዲህ ሲሉ መለሱ፡ (ዘውታሪ የሆነው…ትንሽ እንኳ ቢሆን!)

2- ሙስሊም ከነፍሱ ጋር ያለው ግንኙነት

የረመዳን ወር ነፍስን ለመታደግ፣ እርሷን ለመተሳሰብ፣ወደ መልካም ቦታ ለመግራት መልካም የለውጥ አጋጣሚ ነው፡፡ ለውጥ የሚጀምረው ነፍስን ከማስተካከል ነው፡፡ ያለባትን ስህተት ለማስተካከል ሁልጊዜ የሚቀጥልና ተከታታይ ልማድ ሆኖ የሚቀር ክትትል ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ክትትል ግለሰቡን ወደ ተሻለ መስመር ያደርሰዋል፡፡

يقول الحسن البصري – رحمه الله – : “المؤمن قوَّام على نفسه، يحاسب نفسَه لله – عز وجل – وإنما خفَّ الحسابُ يوم القيامة على قومٍ حاسَبوا أنفسَهم في الدنيا، وإنما شقَّ الحساب يوم القيامة على قوم أخَذوا هذا الأمرَ من غير محاسبة”.

ሀሰን አልበስሪ (ረዐ) እንዲህ ይላሉ፡ ሙእሚን የራሱ ነፍስ ላይ ብርቱ ነው፤ ለአላህ ብሎ ነፍሱን ይተሳሰባል፤በዚህ አለም ላይ ነፍሳቸውን የተሳሰቡ ሰዎች አላህ(ሱወ) ነገ (የውመል ቂያማ) ሂሳባቸውን ያቀልላቸዋል፡፡ ነፍሳቸውን ከመተሳሰብ የተዉ(የተዘናጉ) ሰዎችን ደግሞ አላህ ሂሳባቸውን ያከብድባቸዋል፡፡

3- ሙስሊም ከቤተሰቡና ከቅርብ ዘመዶቹ ጋር ያለው ግንኙነት

ሰዎች በበርካታ ጉዳዮቻቸው ተወጥረው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የዘነጉት ነገር ቢኖር ዝምድና ነው፡፡ቤተዘመድን ለመጠየቅና ለመንከባከብ ይህ ወር እጅግ ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡ረመዳን በዝምድና መካካል ቀጣይነት ያለውን ትስስር የሚጀመርበት ታላቅ ወር ነውና ተጠቀምበት፡፡ ይህ የነብዩ ሀዲስ ብቻውን የሚበቃን ይመስለኛል፡፡

حديث النبي – صلى الله عليه وسلم – عن الرحم، حيث قال: ((إن الله خلَق الخلْق، حتى إذا فرغ من خلقه، قالت الرحم: هذا مقام العائذِ بك من القطيعة، قال: نعم، أما ترضين أن أَصِل من وصلك، وأقطع من قطعك؟ قالت: بلى يا رب، قال: فهو لك))،

 قال رسول الله – صلى الله عليه وسلم -: فاقرؤوا إن شئتم: ﴿ فَهَلْ عَسَيْتُمْ إِنْ تَوَلَّيْتُمْ أَنْ تُفْسِدُوا فِي الْأَرْضِ وَتُقَطِّعُوا أَرْحَامَكُمْ ﴾ 

 አቡሁረይራ (ረ.ዐ) በዘገበው ሀዲስ ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፣ “አላህ ፍጥረትን ሰርቶ ሲጨርስ ‘ረሂም’ (ዝምድና) ወደ አላህ መጥታ ቆመች፤ አላህ (ሱ.ወ) ‘ምንሆነሽ ነው’ ሲላት ‘ዝምድናን ከሚያበላሹ (የዝምድናን ገመድ ከሚበጥሱ) በአንተ እጠበቃለሁ’ አለች። አላህም (ሱ.ወ) ‘አንቺን የሚቀጥል ችሮታዬን ባደርግለት፣ የሚቆርጥሽን ችሮታዬን ብከለክለው ይበቃሻል ወይ?’ ሲላት ‘አዎን ጌታዬ ሆይ!’ አለች። አላህም (ሱ.ወ) ‘ይህንኑ አድርጌልሻለሁ’ አላት።”

አቡሁረይራ ዘገባዉን ቀጥሎ፣ “ብትፈልጉ ይህን የቁርአን አንቀፅ አንብቡ፣ “በምድር ላይ ስልጣን (ሀይል) ቢሰጣችሁ በምድር ላይ ሀፂያትን ባስፋፋችሁ እና ዝምድናን ባበላሻችሁ ነበር?!” ማለታቸውን ዘግቧል። (ቡኻሪ ዘግበውታል)

4- ሙስሊም ከማህበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት

ይህ የእርስ በእርስ ግንኙነት ከሌሎች ግንኙነቶች አንፃር እጅግ እይታው ከፍ ያለ ሲሆን እያንዳንዱ እንቅስቃሴም በተግባር የሚገለፅ ነው፡፡ሙስሊሞች በማህበረሰባዊ ስራዎች ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባው ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆንም ተገቢ ነው፡፡በማህበረሰባዊ ግልጋሎቶች ላይ መከባበር፣መረዳዳትን ያጠቃለለ ስራዎች የሚሰሩበት የለውጥ ክፍል ነው፡፡

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ فَأَصْلِحُوا بَيْنَ أَخَوَيْكُمْ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ

ምእመናኖች ወንድማመቾች ናቸው፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ፡፡ ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡ አልሁጁራት 49፤10

ويقول رسول الله – صلى الله عليه وسلم -: ((مثل المؤمنين في توادِّهم وتراحمهم وتعاطفهم مثل الجسد، إذا اشتكى منه شيء تداعى له سائر الجسد بالسهر والحمى)) 

መልእክተኛው(ሰዐወ) እንዲህ ይላሉ፡ “ሙስሊሞች እርስ በርስ መዋደዳቸው፣ በእዝነታቸውና በርህራሄያቸው እንደ አንድ ሰውነት ናቸው። አንዱ የሰውነት ክፍል የታመመ እንደሆነ ሌላው የሰውነት ክፍል በትኩሣት እና ያለ እንቅልፍ በማደር ይታመማል” (ቡኻሪና ሙስሊም)

5- ሙስሊም ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር

ይህ ማህበረሰባዊ ለውጥ ከስብከት በዘለለ መልኩ በተግባር እንዲገለፅም ኢስላም ያዛል፡፡ ከሌሎች ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የማህበረሰባዊ ስራዎችን አለመተግበር ከኢስላማዊ መርህ ጋርም ያጋጫል፡፡አንድ ሰው ሁልጊዜም ቢሆን ጉጉቱ መልእክተኛውን(ሰዐወ) መከተልና እርሳቸውን መምሰል ይኖርበታል፡፡ መልእክተኛው(ሰዐወ) ደግሞ ከሙስሊሙም ጋር ሆነ ሙስሊም ካልሆኑ የማህበረሰቡ አካሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በጥበብና በእዝነት ብሎም በመልካም ግሳፄ የታጀበ ነው፡፡ይህም ትልቅ ተግባር የኢስላም መንፈሱም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ادْعُ إِلَىٰ سَبِيلِ رَبِّكَ بِالْحِكْمَةِ وَالْمَوْعِظَةِ الْحَسَنَةِ

ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳጼ (በለዘብታ ቃል) ጥራ፡፡ አነህል 16፤125

ويقول رسول الله – صلى الله عليه وسلم : ((فوالله لأنْ يَهدِيَ الله بك رجلاً، خير لك من أن يكون لك حُمْر النَّعَم))

ነብዩ (ሰዐወ) እንዲህ ይላሉ፡ በጌታዬ እምላለሁ አንድን ሰው ወደ እውነተኛው መንገድ መምራት የቀያይ ግመሎች ባለቤት ከመሆን የተሻለ ነው፡፡

እነዚህ የለውጥ ክፍሎች ላይ በፅናት መታገልና መበራታት እንዲሁም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት የአዎንታዊነትን አዲስ ገፅ መክፈት ነው፡፡ ከረመዳን ትምህርት ቤት እነዚህን ሙሉ የለውጥ ክፍሎች ለመሰነቅ እንዘጋጅ!

አላህ በሰላም ያድርሰን…….

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here