እውነትን ፈላጊው – ሰልማን አል-ፋሪስ

0
10715

አሁን ደግሞ ሌላውን ጀግና ስብዕና ከፐርሺያ ምድር ልናይ ነው፡፡

ከርሱ በኋላ ከዛች ምድር ኢስላምን ብዙዎች ተቀብለዋል፡፡ በእምነት ፣ ዕውቀትና በምድራዊ ህይወት ጥግም ደርሰው ነበር፡፡ በዚህ ብቻም ሳይገደቡ የኢስላም እንፀብራቂና ጉልህ መታያ ማማም ሆነዋል፡፡ ሙስሊም ፋላስፋዎች፣ የህክምና ጠበብቶች ፣ ህግ አዋቂዎች፣ የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች እና ወዘተ ፈልቀውባታል፡፡ የሰልማን ሐገር…..

የመጀመሪያው የኢስላም ዘመን ልጆች ከብርሀን ፍንጣቂ የሆኑ ስብዕናዎች ስብስብ ነበር፡፡ ከየሀገራቱ ይመጣሉ፡፡ የተለያየ አስተሳሰብ ፣ ባህል ፣ ያሳደጋቸው ቢሆኑም፣ እምነቱ ግን አዋሃዳቸው፡፡ የአንድ መስመር ተሰላፊዎች አደረጋቸው፡፡

መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የእምነታቸውን በረከታማ መስፋፋት በእርግጥ ተንብየዋል፡፡ ኧረ እንደውም ከልዑሉና አዋቂው ጌታቸው እውነተኛ የሆነ ቃል ኪዳን ተገብቶላቸዋል፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ዘመንና ቦታን ቀረብ አድርጎ አሳያቸው፡፡ የኢስላም ሰንደቅ በመሬት ከተሞች ካስማ ላይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በዓይናቸው በብረቱ ተመለከቱ፡፡ ሰልማን አል-ፋሪስ ታዲያ የዓይን ምስክር ነው፡፡ ከነዚህ ክስተቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡

                         የኸንደቅ ዘመቻ ትውስታ 

     በአምስተኛው ዓመተ ሂጅራ የኸንደቅ ዘመቻ ትውስታ . . . መካንና በውስጧ የነበሩትን የአጋሪያን መሪዎች ተገናኝቶ በአዲሱ እምነትና ተከታዮች እንዲሁም በመልዕክተኛው ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድና ለማስቆም የአይሁዳውያን መሪዎች ልዑክ ከመዲና በሚስጥር ተንቀሳቀሰ፡፡ አይሁዳውያኑ አጋሪያኑን ሊረዷቸውና ሊተባበሯቸው ቃልም ገቡ፡፡ ይህች በክህደት የተሸፈነች ዘመቻ ተከሰተች፡፡ መዲናን ከውጭ በኩል የቁረይሽ የገጥፋን ጦር ሊያጣድፏት፤ ከውስጥ ደግሞ የበኑ ቁረይዟ አይሁዶች ከሙስሊሞች ሰልፍ ያሉ መናፍቃን በአንድ ጊዜ ጨርሰው የታሪክ ትውስታ ሊያደርጓቸው ተነሱ፡፡

መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) እና አማኞች ክፉኛ ደነገጡ፡፡ ያላሰቡትና ያልተዘጋጁበት የለሊት ሴራ ከፊታቸው ተደቀነ፡፡ ዝግጅቱን የጨረሰና መሳሪያ ጥግ ድረስ የታጠቀ ወታደር ወደ መዲና እየቀረበ ነው፡፡ ይህን የአማኞችን ሁኔታ ቁርዓን እንዲህ በስዕል መልክ አስቀምጦታል፡፡

إِذْ جَاءُوكُم مِّن فَوْقِكُمْ وَمِنْ أَسْفَلَ مِنكُمْ وَإِذْ زَاغَتِ الْأَبْصَارُ وَبَلَغَتِ الْقُلُوبُ الْحَنَاجِرَ وَتَظُنُّونَ بِاللَّهِ الظُّنُونَا

“ከበላያችሁም ፣ ከናንተ በታችም በመጡባችሁ ጊዜ ፣ ዓይኖም በቃበዙ ፣ ልቦችም ላንቃዎች በደረሱና በአሏህም ጥርጣሬዎችን በጠረጠራችሁ ጊዜ (ያደረገላችሁን አስታውሱ)፡፡”  አል አህዛብ 33፤10

በአቡ ሱፍያንና በዑየይያ ኢብኑ ሂስን መሪነት 24 ሺህ ጦር ወደ መዲና እየቀረበ ነው፡፡ መዲናን በግድያና ጭፍጨፋ ቃጤ አድርገው ሙሐመድን እና ባልደረቦቹንና እምነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገላገሉ ቋምጠው እየገሰገሱ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጦርነት የቁረይሽ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅ ሁሉም ከኢስላም ጋር ጠብ የነበረበት  ፣ ኢስላምን የወደፊት እንቅፋት አድርጎ ያሰበና ምድራዊ ጥቅሙን ብቻ አምላኪ የነበረው ሁሉ ተሰልፎበታል፡፡ የመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጠላቶች እንደ ግለሰብም ፣ ስብስብም አሊያ ደግሞ ብሔር ጭምር ያደረጉት የመጨረሻ ሙከራ ነበር፡፡ ሙስሊሞች ራሳቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታና ውጥረት ተከበው አገኙት፡፡ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦቻቸውን ሊያማከሩ ሰበሰቧቸው፡፡ በርግጥ በመጋደሉና መከላከሉ ላይ ተስማሙ፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው የሚከለከሉት?

በዚህ ጊዜ ነበር ባለ ረጃጅም ባቶችና ባለ ብዙ ፀጉሩ ሠው ብድግ ያለው፡፡ በርግጥ መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ለዚህ ሰው ግዙፍ ፍቅርና ፣ የከበረ እይታ ነበራቸው፡፡ ሠልማን (ረ.ዐ) መዲናን ከተራራ ላይ ሆኖ ቁልቁል ወደታች በጥልቀት አያት፡፡ በተራሮች የታሸገች፣ በትላልቅ ቋጥኞች የተከበበች ሆና አገኛት፡፡ ስለዚህም አለ እየመጣ ያለው ወታደር በቀላሉ መሸሸጊያና አድፍጦ  መዋጊያ ቦታ ሊያገኝ ነው፡፡ ሰልማን ፐርሺያ እያለ የጦርነት ስልትና እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ጥልቅ ግንዛቤን ቋጥሮ ስለነበር በፍጥነት ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሔደ፡፡ ዓረቦች አይተውት የማያውቁትን የመከላከልና መዋጋት ስልት ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይዞ ቀረበ፡፡ ሐሳቡ የምሽግ ቁፋሮ ነበር፡፡ መዲና ዙሪያዋን በጥልቅ ጉድጓድ እንድትከበብ….

በዚህ ዘመቻ ይህ ቁረይሽ አይታ የማታውቀው ምሽግ ባይቆፈርና ባትደናገጥ የጦር ሀይሉ ለወር ያህል ድንኳን ውስጥ ተስፋ ቆርጦ በቁም የሞተ ሬሳ ሆኖ መዲናን ሰብሮ አለመግባቱ ባይከሰት ፤ ከዚያም አላህ (ሱ.ወ) በአንዱ ለሊት ሀይለኛ ንፋስ ልኮ ድንኳናቸውን ባይመነጋግለውና የተስፋቸውን ቋንጃ ባይሰብረው ሙስሊሞች ምን ይጠብቃቸው ነበር ስንል አላህ ይወቀው፡፡

አቡ ሱፍያን ወታደሩን በመጣበት ይመለስ ሲል ትዕዛዝ አሳለፈ፡፡  ይህ ምሽግ ሲቆፈር ታዲያ ሰልማን ከእምነት ወንድሞቹ ጋር ቋጥኝ መፍለጫ ይዞ ሲቆፍር ነበር፡፡ ያ የእዝነት ነብይም (ሰ.ዐ.ወ) እንደ ባልደረቦቻቸው ጎንበስ ቀና እያሉ ሲቆፍሩ ነበር፡፡ ሰልማን እየሰራ በነበረበት ቡድን ላይ ግን መቆፈሪያቸው ከበድ ያለ አይነኬ ቋጥኝ ተቀብሮ አገኛቸው፡፡ ሰልማን የጠንካራ ጡንቻ ባለቤት ነበር፡፡ ሁለት ክንዶቹን ከፍ አድርጎ ቋጥኝን በመፍለጫ ሲኮረኩም፣ ወዲያው ወደ ኮረት የሚቀይር ጉልበት ነበረው፡፡ ነገር ግን ይህች ቋጥኝ  ያን ጉልበቱን አራቀችው፡፡ አደከመችው፡፡ ባልደረቦቹ ጋር ቢታገሉም ብዙ መጓዝ አልቻሉም፡፡ ሰልማን ወደ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በመሄድ የምሽጉን  መስመር ቁፋሮ ለማስቀየር ፍቃድ ጠየቀ፡፡ ምክንያቱም ያቺ ጠንካራ ቋጥኝ ናት፡፡

መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ግን የነ ሰልማንን ቡድን ለማገዝ አብረውት መጡ፡፡ ቋጥኟን ሲያዩዋት መዶሻ ጠየቁ፡፡ ፍንጣሪ እንዳይመታቸው ባልደረቦቻቸውን ትንሽ ራቅ እንዲሉ ጠየቋቸው፡፡ በአላህ ስም አሉ ጠንከር አድርገውና ቆርጠው በተከበሩት እጆቻቸው መዶሻውን ከፍ አድርገው ቋጥኟን መቷት፡፡ ከፍተኛ ብርሀን ቦግ ብሎ በራ፡፡ መዲናን ያሸበረቀ ብርሀን እንደነበረ ሰልማን ተናግሯል፡፡

መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹አሏሁ አክበር የፐርሺያ ቁልፍ ተሠጠኝ ትልልቅ ህንፃዎቿ እየታዩኝ ነው፡፡ የኪስራ ከተሞች ተገለጡልኝ፡፡ ህዝቦቼ ይነግሱበታል፡፡›› አሉ፡፡

አሁንም መፍለጫውን ከፍ አደረጉት ለሁለተኛ ጊዜ መቱት አሁንም ካለፈው የበለጠ ብርሀን በራ፡፡ “ላኢላሀ ኢለሏህ አሏሁ አክበር” የሮምን መክፈቻ ቁልፍ ተሰጠሁ፡፡ ቀያይ ህንፃዎቿ እየተንፀባረቁ እየታዩኝ ነው፡፡ ህዝቦቼ ይነግሱባታል፡፡››

ለሶስተኛ ጊዜ መዶሻውን ከፍ አድርገው መቱት፡፡ ቋጥኟ ተሸፈነች፡፡ ራሷ ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ብርቱ ምት ራሷን ሰጠች፡፡ የተንቦገቦገ ብርቱ ብርሃን ወጣት፡፡ መልእክተኛውም ሙስሊሞችም አንድ ላይ “ላኢላሀ ኢለሏ አላሁ አክበር” አሉ፡፡ ‹‹በዚህች ቅፅበት የሶሪያ ስንደቅና ሌሎች የምድር ከተሞች ላይ ለወደፊት የአላህ ሰንደቅ የሚውለበለብባቸው ቦታዎች እያየሁ ነው፡፡” አሉ

አማኞቹ ከገዘፈ እምነት ደስታ ጮሁ፡፡ ‹‹ይህ አላህና መልእክተኛው የገቡልን ቃል ነው፡፡›› አሉ፡፡ አላህ ከዚያም መልእክተኛው እውነት ተናገሩ፡፡

ሰልማን (ረ.ዐ) የምሽጉ ቁፋሮ ዋና አማካሪ ነበር፡፡ የሩቅ ሚስጥራትና የቀጣይ ሂደት ትንቢት ብርሃን ባለቤት የነበረችው ቋጥኝ ባልደረባ ነበር፡፡ ከውስጧ ብርሃን ሲወጣ አይቷል፡፡ የብስራት ዜናዎቹን ሰምቷል፡፡ አዎ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጎን ቆሞ ነበር እናም ሰልማን በህይወት እያለ የብስራቶቹን ተፈፃሚነት አይቷል፡፡ በእውንም ኖሯቸው የፐርሺያንና ሮምን ከተሞች ተመልክቷል፡፡ የሱዳን ፣ ሶሪያ ፣ ግብፅንና ኢራቅ ከተሞችን አይቷል፡፡ በእነዚህ ከተሞች ላይ የእውነት፣ ቅናቻ እንዲሁም የመልካም ጥሪ ተስተጋብቶ ከከፍተኛ ማማ ላይ ሆኖ ብርሀኑን እየረጨ ብዙ ቦታዎችን አሳምሯል፡፡

እነሆ ጥላዋ የሚያምርና ረዘም ያለች ዛፍ ስር ተቀምጦ ለባልደረቦቹ  እውነትን ፍለጋ ከሀገር ሀገር እንዴት እንደኳተነ እየነገራቸው ነው፡፡ ከህዝቦቹ ከፋርሳውያን እምነት ወደ ክርስትና ከክርትና ደግሞ ወደ ኢስላም እንዴት መጣ ? ከአባቱ ቤት ድልብ ምቾት ወደ ድህነት እቅፍ መንፈስና ህሊናውን እንዴት ማጥራት እንዳለበት የዘዴ ፍለጋ በባሪያ ገበያ ውስጥ እንዴት እንደተሸጠ ፣ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዴት እንደተገናኘ እንዳመነባቸው . . . እየተረከ ነው፡፡

ስለሚያወራው አንፀባራቂ ታሪክ ለመስማት ኑ ከስብስቡ ጠጋ    እንበል  . . .  እነሆ ሰልማን ጀመረ ‹‹ጀይ ከሚባል ጎሳ የተገኘሁ የአስበሃን ሰው ነኝ፡፡ አባቴ የግዛቷ መሪ ነበር፡፡ ከአላህ ፍጡራን በሙሉ እኔ ለአባቴ ተወዳጅ ሰው ነበርኩ፡፡ መጁሲያ ላይ ተግቻለሁ፡፡ የምናቀጣጥላት እሳት አለቃም ሆንኩ፡፡ አባቴ በዓመት ሁለቴ ምርት የሚሰጥ መሬት ነበረው፡፡ አንድ ቀን ወደዛ ላከኝ፣ በመንገዴ ላይ የክርስቲያኖችን ቤተ አምልኮ አየሁ፡፡ ሲፀልዩም ተመለከትኩ፡፡

ምን እንደሚሰሩ ለማየት ገባሁ፡፡ ጳጳሱን ባየሁት ጊዜ ተገረምኩ፡፡ ለራሴም ይህማ እኛ ካለንበት እምነት የተሻለ ነው አልኩ ፀሀይ እስክትገባ አልተለየኋቸውም፡፡ ወደ አባቴ መልእክትም አልሄድኩም መልእክተኛ ልኮ እስኪያስወስደኝ ወደ ቤትም አልተመለስኩም ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹን በጉዳያቸውና በእምነታቸው ስለተመሰጥኩ የእምነታቸው ምንጭ የት እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡ ሻም ውስጥ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ወደ ቤት እንደተመለስኩ ለአባቴ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚያመልኩ ሰዎች በኩል እንዳለፍከሉና ሳያቸው እንደሳበኝ ነገርኩት፡፡ ከኛም እምነት የነርሱ ይሻላል ስለው ተቆጣኝ እኔም ተከራከርኩት እግረ- ሙግ አስገብቶኝ አገተኝ፡፡

ወደ ክርስቲያኖቹ እምነታቸውን እንደተቀላቀልኩና ከሻም የሚመጣ ሲራራ ካለ ከመመለሱ በፊት ከነርሱ ጋር ወደ ሻም አብሬ እንድሄድ እንዲያሳውቁኝ መልእክት ላኩባቸው፡፡ ባልኳቸው መሠረት ላኩልኝ፡፡ ሰንሰለቱን በጥሼ ወጣሁ አብሬያቸው ወደ ሻም ሄድኩ፡፡ እንደደረስኩ ስለ አዋቂያቸው ጠየቅኩ የቤተክርስቲያኑ ዋና ጳጳስ እንድሆነ ነገሩኝ፡፡ ወደርሱ ሄድኩ ስለው ሁኔታዬ ነገርኩት፡፡ እርሱን እያገለገልኩ ማምለክ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን ይህ ጳጳስ በእምነቱ ላይ እኩይ ነበር፡፡ ከሠዎች ለሰዎች መከፋፈል ያለበትን ገንዘብ ሰብስቦ ለራሱ ያደልብ ነበር፡፡ ሞተና በርሱ ቦታ ሌላ ጳጳስ ተኩበት፡፡ እምነታቸው ውስጥ ከርሱ የተሻለ አላየሁም፡፡ የወዲያኛው ዓለም ክጃሎቱ ትልቅ፣ ለምድራዊ ነፀብራቅ ግዴለሽና ከአምልኮ ስንቅ የሚቋጥር ሰው ነበር፡፡ ከርሱ በፊት ማንንም ወድጄ በማላውቅበት ሁኔታ ወደድኩት፡፡ መሞቻው ሲቃረብ ከአላህ የሆነው ጉዳይ (ሞት) እንደምታየው ቀርቦሃል፡፡ በምን ታዘኛለህ ? ምንስ አደራ ትለኛለህ አልኩት፡፡ ሞሱል  ካለ አንድ ሰው በስተቀር እኔ ባለሁበት መንገድ ላይ ያለ ማንንም አላውቅም አለኝ፡፡ ከሞተ በኋላ ሞሱል ወዳለው ሠው መጥቼ ስለ ሁኔታዬ ነገርኩት፡፡ አላህ እስከፈቀደው ጊዜ ድረስ እርሱ ዘንድ ቆየሁ፡፡ ሞት ሲያካበው እሱንም ጠየቅኩት ሮም አሙሪያ ካለ ሰው ጋር እንድገኛኝ አዘዘኝ፡፡ ተጉዤ አገኘሁት ከርሱ ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ ለህይወቴ የቁም ከብቶችና ፍየሎች ማርባት ጀመርኩ፡፡ ይህም ሠው የሞት ጣዕር ያዘው ወደ ማን አደራ ትለኛለህ ? ብዬ ጠየቅኩት ልጄ ሆይ አሁንኳ ትሄድበት ዘንድ የምልክህ ፣እኛ ባለንበት መንገድና ፍኖት ያለ ሰው አላውቅም፡፡

ነገር ግን በኢብራሂም ፍኖት ሆኖ የሚላክ ነብይ የሚመጣበት ዘመን ተቃርቧል፡፡ የተምር ዛፍ የበዛበትና በሁለት ኮረብታዎች መኃል ወዳለች ከተማ ይሰደዳል፡፡ ከቻልክ ወደ እሱ ሂድ አለኝ፡፡

የማይደበቁ ተዓምራት አሉት የሰደቃ (ምፅዋት) ምግብ አይመገብም፣ ስጦታ ይቀበላል፣ በትከሻዎቹ መሀል የነብይነት ማህተም አለው ስታየው ታውቀዋለህ፡፡

አንድ ቀን የሲራራ ነጋዴዎች፡፡ አጋጠሙኝ ስለ ሀገራቸው ጠየኳቸው የዓረቢያ ፔኒንዙላ ሰዎች እንደሆኑ አወቅኩ፡፡ ከብቶቼንና ፍየሎቼን ሰጥቼያቸው ወደ ሀገራችሁ አብሬያችሁ ልሂድ ውሰዱኝ ስላቸው ተስማሙ፡፡ የጉዞ ባልደረባቸው ሆኜ እስከ “ዋዲል ቁራ” የተሰኘ ቦታ ድረስ መጣን፡፡ እዚህ ቦታ ስንደርስ ግን ሸፍጥ ሰሩብኝ፡፡ ለአንድ አይሁዳዊ ሰው ሸጡኝ፡፡

ብዙ የተምር ዛፎችን አየሁ፡፡ የተነገረችኝ ሀገር ይህች እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ ለወደፊቱ ያ ነብይ የሚሰደድባት ቦታ…. ነገር ግን ሳትሆን ቀረች፡፡ ከገዛኝ ሰው ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ አንድ ቀን ከበኒ ቁረይዟ የሆነ አይሁድ መጣና ከሠውየው ገዝቶኝ መዲና ወሰደኝ፡፡ በአላህ ይሁንብኝ ልክ መዲናን እንዳየኋት ያቺ የተነገረችኝ መሬት ላይ እንደደረስኩ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ በኒ ቁረይዟ መንደር ውስጥ በሰውየው የቴምር እርሻ ውስጥ መስራቱን ተያያዝኩት፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) ተሰደው መዲና ቁባዕ አረፉ፡፡

ከእለታት አንድ ቀን የቴምር ዛፍ አናት ላይ ነበርኩ፡፡ አለቃዬ ከስር ተቀምጧል፡፡ አንድ የአጎቱ ልጅ አይሁዳዊ መጣና ‹‹በኒ ቂላዎችን አላህ ይርገማቸው ቁባእ ላይ ከመካ ነብይ ነኝ ብሎ የመጣ ሰው ላይ ይራኮታሉ›› አለ፡፡ ልጁ ንግግሩን እንደጨረሰ የሆነ ነገር ሠውነቴን ወረረኝ፡፡ አሳዳሪዬ ላይ ልወድቅ እድክደርስ ድረስ ዛፊቱ ተርገፈገፈች በፍጥነት ወረድኩና ‹‹አሁን ምን አልክ ? ዜናውስ ምንድን ነው ?›› ስለው አሳዳሪዬ በከባድ ጥፊ ፊቴን አነደደኝ፡፡ ‹‹በማያገባህ ምን ጥልቅ አደረገህ ? በል ወደ ስራህ ሂድ ›› አለኝ፡፡ ወደ ስራዬ ተመለስኩ፡፡ ሲመሽ ያለችኝን ቋጥሬ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ወዳሉበት ቁባእ አቀናሁ፡፡ ወዳሉበት ስገባ የተወሰኑ ባልደረቦቻቸው ጋር ናቸው፡፡ እንግዳ ስለሆናችሁና የሚያስፈልጋችሁ ብዙ ነገር አለ፡፡ እኔ ለምፅዋት (ሰደቃ) የተሳልኩት ምግብ አለ፡፡ ያላችሁበት ሲነገረኝ ይህ ሰደቃ ለናንተ እንደሚገባ አስቤ ይዤው መጣሁ አልኩና ፊታቸው አስቀመጥኩት፡፡ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ባልደረቦቻቸው ዞር አሉና ቢስሚላህ ብላችሁ ተመገቡ አሉ፡፡ እርሳቸው ግን እጃቸውን አልዘረጉም፡፡ በውስጤም በአላህ ይሁንብኝ ይህቺ አንዷ ምልክት ናት፡፡ እርሱ ሰደቃን አይመገብም፡፡

በቀጣይ ቀንም ምግብ ይዤ ወደ መልእክተኛው ተመልሼ መጣሁና ‹‹እንዳየሆት ሰደቃን አይበሉም፡፡ ስጦታ ይዤልዎት መጥቻለሁ›› ብዬ ፊታቸው አደረግኩት፡፡ ባልደረቦቻቸውን በአላህ ስም ተመገቡ አሉና አብረው በሉ፡፡ እኔም ለራሴ በአላህ ይሁንብኝ ይህቺ ሁለተኛዋ ናት አልኩኝ፡፡ አዎ ስጦታን ግን ይመገባሉ፡፡ ተመለስኩና የተወሠኑ ቀናት ቆየሁ፡፡  ወደርሳቸው ስሄድ በቂዕ ጀናዛ ለመሸኘት በሄዱበት ፣ ባልደረቦቻቸው ዙሪያቸውን ከበዋቸው ተቀምጠው አገኘኋቸው፡፡ ሁለት ኩታዎችን አንዱን ከላይ ለብሰው ሌላውን ታጥቀው ነበር፡፡ ሠላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ትከሻቸው መኃል ያለውን የነብይነት ማህተም ለማየት ስንቆራጠጥና ስንጠራራ ነበር፡፡ ይህንንም ስላወቁብኝ ከትከሻቸው ፎጣውን አወረዱት፡፡ ምልክቱን በተነገረኝ ቦታ ላይ አየሁት፡፡ ያ ጳጳስ እንደነገረኝ ማህተሙን ተመለከትኩት፡፡ ዘልዬ ተደፋሁበትበና እያለቀስኩ እስመው ጀመር፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)  አረጋጉኝና ከፊታቸው ቁጭ አልኩ አሁን እንደምነግራቸው ታሪኬን ነገርኳቸው፡፡ ከዛ እስልምናን ተቀበልኩ፡፡ በባርነት ቀንበር መያዜ በድርና እሁድ ጦርነቶችን ከመሣተፍ አገደኝ፡፡

አንድ ቀን ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአሳዳሪዬ ጋር ከባርነት ነፃ እንዲያደርጉኝ የገንዘቡን መጠን እንድደራደር አዘዙኝ፡፡ ተደራደርኩት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦቻቸው እንዲተባበሩኝ አደረጉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከባርነት ነፃ አወጣኝ፡፡ ነፃነቱ የተጠበቀ ሙስሊም ሆኜ ኖርኩ፡፡ ከነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) ጋር አብሬ የኸንደቅን ዘመቻ ተሣተፍኩ፡፡

ሰልማን (ረ.ዐ) ግዙፉንና ምርጥ የሆነውን ስለ እምነት እውነት ፍለጋ መኳተኑን እንዲህ በሚያምር መልኩ ተረከ፡፡ የህይወቱን ግብ ያሠመረለት ፍኖት በእርግጥ ይህ የሞራል ልዕልና ነው፡፡ ከፍታን የተመኘች መንፈሱ፣ ጠንካራ ፈተናዎችን አሸንፎ የበላይ ከሆነ በኋላ ወደ ታች መውረድ አይታሰብም፡፡ ስለ እውነት ለፋ ከአባቱ በፍቅርና እንቅብካቤ ከተከበበ ቤት ምኑንም ወደማያውቀው መንከራተት ገባላት፡፡ ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር በባርነት ቀንበር ታስሮ እስኪደክም ተጓዘላት፡፡ የተለያዩ የህይወት መንገዶችን ቃኘ፡፡ ስለርሷም የሙጥኝ አለ፡፡ መስዋእትነትን ከፈለ፡፡ አላህም ታዲያ በምድር ከመልእክተኛው ጋር በማገናኘት በኢስላም ካሰው፡፡ ረዘም ያለ ዕድሜ ሰጥቶትም የኢስላም ሰንደቅ በምድር ስትውለበለብ መመልከት ቻለ፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) ደጋግ ባሪያዎች የምድርን ጫፎች ሞልተዋት በቅናቻና (ምሪት ፣ ሂዳያ) በፍትህ ሞልተዋት ማየት ቻለ፡፡

የዚህ ሰው ኢስላም ስለምን አማረ፡፡ ስለምንስ በእውነት የታገዘ ሆነ ? በርግጥ የርሱ ኢስላም የትጉሃንና ጥንቁቃኑ ነበር፡፡ ስለ ምድራዊ ህይወት የነበረውን ግዴለሽነት ፣ ቅልጥፍናውንና ጥንቁቅነቱን አይተው ሰዎች ከዑመር ኢብኑል ኸጧብ ጋር ያመሳስሉት ነበር፡፡ ሰልማን (ረ.ዐ) ከአቡ ደርዳዕ (ረ.ዐ) ጋር ለተወሰኑ ቀናት አንድ ቤት አብረው ቆዩ፡፡ አቡደርዳዕ (ረ.ዐ) ቀን ይፆማል ለሊት ይቆማል፡፡ ሰልማን ታዲያ አቡደርዳዕን ከዚህ ጥግ የደረሰ አምልኮ ወደ መካከለኛ ሊመልሰው ከጀል፡፡ አንድ ቀን የሱና ፆምን አስፈሰከው፡፡ አቡ ደርዳዕ ሰልማንን እየወቀሰ “ለጌታዬ እንዳልፆምና እንዳልሰግድ ትከለክለኛለህ?” አለው፡፡ ሰልማንም አይንህና ቤተሰብህ ካንተ መብት አላቸው፡፡ ፁም አፍጥር፣ ስገድ ተኛ ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ዜና ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)  ደረሳቸው ሰልማን እውቀትን ጠገበ ሲሉ አድናቆታቸውን ገለፁ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ከህሊናው ብስለትና የዳበረ እውቀቱ በተጨማሪ ስነ ምግባርና ሀይማኖተኝነቱንም ያዩ ነበር፡፡

በኸንደቅ ዘመቻ እለት አንሷሮች ቆመው “ሰልማን ከኛ ነው” አሉ፡፡ ሙሀጂሮችም ተነሱና “ኧረ ሰልማን ከኛ ነው” ሲሉ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለቱንም ተጣሩና “ሰልማንማ የኛ ነው አህለለል በይት” ብለው ተናገሩ፡፡ በእርግጥ እርሱ ለዚህ ክብር የተገባ ነበር፡፡

ዐሊይ ኢብኑ አቡ ጧሊብ (ረ.ዐ) ሉቅማን አል – ሀኪም ብለው ይጠሩት ነበር፡፡ ሰልማን (ረ.ዐ) ከሞተ በኋላ ስለሱ ሲጠየቁ “እሱማ ከኛ ከአህለል በይት ነው፡፡ ለናንተ ሉቅማነል ሀኪምን አላችሁን ?” ሲሉ መልሰው ነበር፡፡ እርሱ የመጀመሪያዎቹም የመጨረሻዎቹም ትውልድ እውቀት ተሰጥቶታል፡፡ የመጀመሪያዎቹን መፅሀፍት አንብቧል የመጨረሻውንም እንዲሁ፡፡ እርሱ የማይነጥፍ የእውቀት ባህር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ በዑመር (ረ.ዐ) ዘመነ ኺላፋ መዲናን ሊጎበኝ መጣ፡፡ ዑመር (ረ.ዐ) ከዚህ በፊት ለማንም ሰርተውትና አድርገው የማያውቁትን ነገር አደረጉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ባልደረቦቻቸውን ሰበሰቡና “አንድ ላይ ሁነን ሰልማንን ወጥተን እንቀበለው” አሉ፡፡ በመዲና ጎዳናዎች ወተው ተቀበሉት፡፡ ሰልማን (ረ.ዐ) ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከተገናኘ በኋላ ነፃነቱን የተጎናፀፈና ሙስሊም ፣ ታጋይና አምላኪ ሆኖ ኖረ፡፡ በኸሊፋው አቡበክር (ረ.ዐ) ከዛም ዑመር (ረ.ዐ) እንዲሁም አላህን (ሱ.ወ) እስኪገናኝ በነበረበት የኡስማን (ረ.ዐ.) ጊዜ አብረው ኖረዋል፡፡ በነዚህ ወቅቶች የኢስላም ሰንደቅ በየአቅጣጫውና አድማሱ ላይ ይውለበለብ ነበር፡፡ ብዙ ገንዘብና ድልቦች ወደ ኢስላማዊው ኺላፋ መናገሻ መዲና ግምጃ ቤት ይገባ ነበር፡፡ ለተለያዩ ሰዎች ሹመት ይሰጣል፡፡ የተወሰነ የደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያዎችም ነበሩ፡፡ ታዲያ ሰልማን በዚህ ወቅት የት ነበር ?  በዚህ የድሎት ነፀብራቅ በነበረበት ጊዜ በምን ሁኔታ ይኖር ነበር፡፡ አይናችሁን በደንብ ክፈቱና ከዛፉ ስር ቁጭ ብሎ ቅርጫት የሚሰራ ሽማግሌ በአይነ ህሊናችሁ ሳላችሁ ? አዎ እሱ ሰው ሰልማን ነው፡፡ በደንብ እዩት፡፡ ከልብሱ ማጠር የተነሳ ተሰብስቦ ወደ ጉልበቱ ደርሷል፡፡ ከክቡር ሽምግልናውና ሞገሱ ጋር፡፡ ለሰልማን በዓመት ከአራት እስከ ስድስት ሺህ ዲርሃም በቂው ስለነበር ከግምጃ ቤት ይሰጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በሰደቃ ያከፋፍለዋል፡፡ አንዲትም ዲርሃም አይጠቀምም፡፡ እንዲህም ይል ነበር “ዑመር ኢብኑል ኸጧብ እንዳልሰራ ቢከለክለኝም ግን በአንድ ዲርሃም የቴምር ሰበዝ እገዛለሁ፡፡ በርሱም ቅርጫት እሰራለሁ በሶስት ዲርሃም እሸጠዋለሁ፡፡ አንድ ዲርሃም ለስራው እመልሳለሁ፤ አንድ ዲርሃም ለቤተሰቦቼ በቂ ስለሆነ አስቤዛ እሰጣለሁ ሶስተኛውን ዲርሃም ደግሞ ለሰደቃ እሰጣለሁ”፡፡

አዎ ! የሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የዘመናት የኩራት ካባ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንዶቻችን ስለ አቡበከር ዑመርና አቡዘር (ረ.ዐ) እና መሰል ወንድሞቻቸውን ቀለል ያለ ህይወታቸውንና ጥንቃቄያቸውን ስንሰማ፤ የአረቦች የህይወት ዘዴያቸው ነው ልንል እንችላለን፡፡ የአረቢያን ፔኒንዙላ አንድ አረብ ለህይወቱ የሚያስፈልገውን በቀላሉ ስለሚያገኝ ነው ልንልም እንችላለን፡፡ ነገር ግን አሁን ይኸው አንድ ከፐርሺያ ምድር ከተገኘ ፣ ምቾትና ድሎት ካሳደጉት ከድሆች ሳይሆን ከመሪዎች የነበረ ሰው ፊት ነው ያለነው፡፡ ድሎትን ፣ መትረፍረፍንና ፀጋን ችላ ብሏል፡፡ በእጅ ስራ ውጤቱ በአንዲት ዲርሃም ብቻ ተብቃቅቷል፡፡ ስልጣንን በሩቁ ይሸሽ ነበር፡፡ እንዲህም ይል ነበር “በሁለት ሰዎች ላይም ቢሆን እንኳን መሪ ላለመሆን አፈር መመገብ ካለብህ አድርገው”

ወደ ጅሃድ ሜዳ መሪ ከተደረገ እያለቀሰና እየፈራ ይቀበላል፡፡ ስልጣንን ወይም በሰዎች ላይ መሾምን ይጠላል፡፡ በግዴታ ከተሸመ ደግሞ ገንዘብ ተቀብሎ ለምን አይጠቀምም የእጁን ስራ ውጤት ብቻ ለምን ይጠቀማል፡፡

ሒሻም ከሐሰን እንደዘገቡት “ለሰልማን 5000 ዲርሃም ይከፈለው ነበር፡፡ 3000 ሰዎች መሀል ግን አንዲት ካባ፤ ግማሹን አሸርጦ ግማሹን ለብሶ ኹጥባ ያደርግ ነበር” ብለዋል፡፡ደሞዙ ሲወጣ ወደ ሌላ ያሣልፈዋል (በሰደቃ ያከፋፍለዋል) የእጅ ስራ ውጤቱን ነበር የሚመገበው፡፡” የፀጋ ውልድ ፣ የስልጣኔ እንክብክብ ሆኖ ሳለ ይህ ሁሉ ምድራዊ ግዴለሽት ከየት መጣ ያውም ፐርሺያዊ ሆኖ . . .

እስኪ የሞት ፍራሹ ላይ ሆኖ ሊነግረን ነው፡፡ ምላሹን ከርሱ እንስማ ምጡቋ ነፍሷ አዛኙንና ሀያሉን አላህ ለመገናኘት እየተዘጋጀች ነው፡፡ ታሞ በተኛበት ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ (ረ.ዐ) ሊጠይቀው ገባ፡፡ ሰልማን አለቀሰ፡፡ ሰዕድም “አባ ዓብደላህ ሆይ ! ለምን ታለቅሳለህ መልእክተኛው  እኮ ወደውህ ነው የሞቱት” አለው፡፡ ሰልማንም “በአላህ ይሁንብኝ ሞትን ፈርቼና ለህይወት ጓጉቼ አይደለም ያለቀስኩት ነገር ግን የአላህ መልእክተኛ  አንዳችሁ ከዱንያ የጋላቢ ያህል ድርሻ ብቻ ይኑረው ብለውን ነበር፡፡ እኔ ደግሞ እንደምታየኝ በዚህ ሁሉ ቁስ ተከብቤያለሁ” አለ፡፡ ሰዕድ ‹‹ቤቱን አየሁት አንዲት ድስትና የውዱእ ማድረጊያ ዕቃ ነው ያሉት›› ይላል፡፡ ሰዕድም “አባ ዓብደላህ ሆይ ! ካንተ የምንይዘው ምክር ካለ ጣል አድርግልን” አለው፡፡ ሰዕድ ሆይ ! “አንድ ነገር መስራት ስትሻ ስራዋን፣ ስትፈርድ ፍርድህን፣ እጅህ ላይ ያለን ስታከፋፍልም ጭምር አላህ ዘንድ አስታውሳት፡፡”

ከዚህ በፊት ነፍሱን በገንዘብ፣ስልጣንና ዝና የሞላው ዛሬ ደግሞ በመብቃቃት የሞላት ሰው ይህ ነበር፡፡  መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) እርሱንና ሌሎች ባልደረቦቻቸውን በአጠቃላይ ዱንያን እንዳያመልኩ ፣ ባሪያዋ እንዳይሆኑና የጋላቢ ስንቅ ያህል እንዲይዙ መክረዋቸው ነበር፡፡”

በርግጥ ሰልማን ቃሉን ጠብቋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ድንበር አልፌ ይሆን ብሎ ፈርቶ ነፍሱ ለጉዞ በምትዘጋጅበት ወቅት ፊቱ በእንባ ራሰ፡፡ የሚመገብባት ድስት፣የሚጠጣባትና ውዱእ የሚያደርግባት ኮዳ በዱንያ ቁስ የተከበበ አስመሰሉት፡፡ ከዚህ በፊት ዑመርን ይመስላል አላልኳችሁም ?

በተለያዩ ከተሞች መሪ ተደርጎ በተሾመባቸው ጊዜያት እንኳ ሁኔታው ምንም አልተቀየረም ነበረ፡፡ አሚር ስለሆነ የሚከፈለውን ገንዘብ ፍፁም እንዳያገኘው ይጠነቀቅ ነበር፡፡ አለባበሱ ካፖርት ነው፡፡ አንድ ቀን በመንገድ ላይ ሲዘዋወር ከሻም ተምርና ቲን ፍሬ የያዘ አንድ ሠው መጣ፡፡ መሸከሙ የደከመው ይህ ሠው ከፊት ለፊቱ ካሉ ሰዎች መሀል ድሃ የሚመስለውን አሸክሞ የሚፈልገው ቦታ ካደረሰለት በኋላ የልፋቱን ዋጋ ለመስጠት አሰበ፡፡ ሰልማን (ረ.ዐ) ዓይኑ ውስጥ ስለገባበት በምልክት ጠራውና መጣ፡፡ እስቲ ተሸከም ይህን አለው፡፡ ተሸከመና አብረው መሄድ ጀመሩ፡፡ ሰልማን (ረ.ዐ) መንገድ ላይ ሰዎችን ስላገኘ ሰላምታ አቀረበ፡፡ ቆም ብለው “በአሚሩም ላይ ሰላም ይስፈን” ብለው መለሱ፡፡

ሰውየው ደንገጥ ብሎ “በአሚሩም ላይ ሠላም ይስፈን?!” የቱን አሚር ለማለት ፈልገው ነው?” አለ፡፡ በጣም የተገረመው ደግሞ ከነዚህ ሰዎች መሀል ‹‹አሚራችን እኛ እንሸከም” ብለው ሲሽቀዳደሙ ማየቱ ነበር፡፡

ይህ የሻም ሠው ሀገረ – ገዢው ሰልማን አል – ፋሪስ አንደሆነ አወቀ፡፡ ተደናግጦ ይቅርታ ጠየቀው፡፡ ከናፍሮቹ ተንቀጣቀጡ፣ በጣም እንዳዘነ ነገረው፡፡ ያሸከመውን ሊቀበለው ሲጠጋው ሰልማን ግን ራሱን በማወዛወዝ ተቃውሞውን ገለፀ፡፡ ቤትህ እስከማድረስልህ ድረስ አላወርድም፡፡” አለው፡፡ “አንድ ቀን ሹመትን ለምን ትጠላለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ወተቷን ሲጠቧት ጥፍጥናዋን እና ሲያቋርጣት ምሬቷ ከባድ ነው፡፡” ሲል መልሷል፡፡

አንድ ቀን ጓደኛው ቤቱ ሲገባ ሰልማን ሊጥ ያቦካል፡፡ ‹‹አገልጋይህስ?” ሲል ጠየቀው “ለአንድ ጉዳይ ላክናት  ፤ ሁለት ስራ እርሷ ላይ መደራረብን ጠላን፡፡” አለው፡፡ የሰልማን ቤት እያልን ስናወራ ነበር፡፡ ቤቱ ምን ይመስላል እስቲ በደንብ እናወራው፡፡ ሰልማን ቤቱን ማሰራት የፈለገ ጊዜ ግንበኛውን እንዴት ነው የምትገነባው ግን? ሲል ጠየቀው፡፡

ግንበኛውም ቀድሞ የሚረዳና ንቁ ስለነበር እንዲሁም የሰልማንን ምድራዊ ግዴለሽነትና ጥንቁቅነት ስለሚያውቅ ‹‹አታስብ ቤትህን ከፀሀይ ሙቀትና ብርድ የምትጠለልበት ፣ ስትቆም ጭንቅላትህን ስትተኛ እግርህን የሚነካ አድርጌ ነው የምሰራልህ›› አለው፡፡ ሰልማንም ‹‹አበጀህ! እንደርሱ አድርገህ ስራው፡፡›› አለ፡፡

ሰልማን ለአፍታ እንኳ የሚመካበት ምድራዊ ሀብት፣ ነፍሱ የምትንጠለጠልበት አንድም ነገር አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ለባለቤቱ በአደራ እንድታስቀምጥለት ያዘዛት ዕቃ ነበር፡፡ በሞተበት ዕለት ንጋት ላይ እንድትሰጠው ጠየቃት፡፡ “እንድትደብቂልኝ የሰጠሁሸን ዕቃ አምጪልኝ” አላት፡፡ ይዛለት መጣች መካ የተከፈተች ዕለት ያገኘው፣ ስሞት የምቀባው ብሎ ጠብቆ ያስቀመጠው ሚስክ  ነበር፡፡  ውሃ የያዘ ዕቃ እንዲቀርብለት አዘዘ፡፡ ሚስኩን ከውሃው በእጁ ደባለቀው ለባለቤቱም ‹‹ዙሪያዬን እርጪው፡፡ አሁን ምግብ የማይመገቡ የአላህ ፍጡራን ይመጣሉ፡፡ ሽቶ ግን ይወዳሉ፡፡” አላት፡፡

“በሩን ክፈቺውና ቁጭ በይ” አላት ያዘዛትን ፈፀመች፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ስታየው ነፍሱ ከገላውና ዱንያ ተለይታለች፡፡

የላይኛውን ዓለም ተቀላቀለች፡፡ ቀጠሮዋን ለማክበር በናፍቆት ክንፍ ወደ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና ወደ ባልደረቦቻቸው አቡበክርና ዑመር ተጓዘች፡፡ ስለ እውነት ለኳተነው ሰልማን አላህ ይዘንለት፡፡ አሚን!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here