የመጨረሻው ቀን (የውሙል ቂያማህ) ክፍል-2

0
5212

ለመጨረሻው ቀን ትልቅ አፅንኦት ለምን ተሠጠ ?

ሊጠቀሱ ከሚችሉ አበይትይ ምክኒያቶች መካከል

  • አንደኛ– የዐረብ መሽሪኮች /በአምልኮ በአላህ ያጋሩ የነበሩና በሱ የካዱ ሰዎች/ ክፉኛ በሆነ መልኩ በመጨረሻው ቀን መኖር ያስተባብሉ ነበር፡፡ ሁኔታቸውንም አላህ ሱ.ወ እንዲህ በማለት አውስቶታል፡፡
وَقَالُوا مَا هِيَ إِلَّا حَيَاتُنَا الدُّنْيَا نَمُوتُ وَنَحْيَا وَمَا يُهْلِكُنَا إِلَّا الدَّهْرُ

እርሷም (ሕይወት) የቅርቢቱ ሕይወታችን እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡ «እንሞታለን፤ ሕያውም እንኾናለን፡፡ ከጊዜም (ማለፍ) በስተቀር ሌላ አያጠፋንም» አሉ፡፡(አል ጃሲያህ፤24)

ይሉ ነበር፡፡

  • ሁለተኛ፡ የመፅሃፉ ባልተቤቶች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) በመጨረሻው ቀን መኖር የሚያምኑ ቢሆንም እንኳ የእምነት አመለካከታቸው ግን መንገድ የሠተና እጅግ የከፋ ሁኔታ ላይ የደረሠ ሆኖ እናገኛለን፡፡ ለምሣሌ ነሣራዎች/ ክርስቲያኖች/ ከዚህ ቀን ጭንቀት ለመገላገል መተማመኛቸው ያደረጉት ‹ለኛ ሲል መስዋእት ሆኗል፤ ከሀጢኣታችን ሊያነፃን መጥቷል› የሚሉትን ነቢዩ ዒሣ ዐ.ሰ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ለዚህ ቀን ዝግጅት ጎድሏቸዋል፡፡  ሂንዱዎችም ሆኑ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች በተመሣሣይ መልኩ የሚሉት አላቸው፡፡ አይሁዶችም ቢሆኑ በመጨረሻው ዓለም ያላቸው የእምነት አመለካከት የጥፋቱ ከፍተኛነት ከክርስቲያኖች፣ ከሂንዱዎችና ከቡድሃዎች የተሻለ አይደለም፡፡
  • ሦስተኛ፡ በመጨረሻው ቀን ማመን ለህይወታችን የላቀ ግብና ከፍ ያለ ዓላማ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ይህም ግብ መልካም መሥራን፣ መጥፎ ነገሮችን መራቅን፣ በበላጭ ሥራዎችና ትላልቅ ነገሮች እራስን ማስዋብና ማስከበርን ፤ ለአካላችንም ሆነ ለሃይማኖታችን፣ ለክብራችን፣ ለህሊናችን እንዲሁም ለሀብት ንብረታችን ጎጂ የሆኑ ርካሽ ነገሮችን መራቅን ያጠቃልላል፡፡ ይህም በምድር ላይ አላህ ሱ.ወ ለሰው ልጅ የሠጠው የተተኪነት ሚና ከሚረጋገጥባቸው ነገሮች መካከል ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ስኬት አንድ ሰው ወደ መልካም ነገር የሚያነሣሣና ከመጥፎ ነገር የሚከለክልን ስሜት የመከተል ግድ ይሆንበታል፡፡ ይህም ሁኔታ ሊጠናከር የሚችለው ነገሮችን ዘወትርና በጥልቀት በማስታወስ፣ በአእምሮ መላልሦ በማስተንተንና የተለያዩ ምሣሌዎችን በማንሣት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሂደት መልካም ነገር የመሥራቱ ባህሪ ሥር ዘልቆና ተፅእኖውም ጎልቶ የታለመው ግብና ዓላማ እስኪሣካ ፤ መጥፎ የሚሠራ ሰው ከመጥፎ ድርጊቱ እስኪመለስ የተሣሳተውም ከስህተቱ እስኪታረምና የሰው ልጅ በተደጋጋሚ ስህተት ላይ እንዳይወድቅና ከመንገድ እንዳይወጣ የሚያግዘውን ትልቅ ዓላማውን በትክክል ወስኖ ለስኬቱ እስኪንቀሣቀስ ድረስ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

የመጨረሻው ቀን መጀመሪያ

ከተከበሩት የቁርኣን አንቀፆች እንደምንረዳው የመጨረሻው ቀን የሚጀምረው በዚህ ዓለም ላይ በሚከሠተው አጠቃላይ የለውጥ ሁኔታ ነው፡፡ ሰማይ ትሠባበራለች፣ ጨረቃ ትሠነጣጠቃለች፣ ከዋክብት ይረግፋሉ፣ መሬት ብትንትኗ ይወጣል፣ ሁሉም ነገር ባዶና አስፈሪ ይሆናል፣ የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ የሚያውቃቸው ነገሮች ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ ይወድማሉ፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

يَوْمَ تُبَدَّلُ الْأَرْضُ غَيْرَ الْأَرْضِ وَالسَّمَاوَاتُ ۖ وَبَرَزُوا لِلَّهِ الْوَاحِدِ الْقَهَّارِ

ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን ሰማያትም (እንደዚሁ) አንድ አሸናፊ ለኾነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለጹበት ቀን (አስታውሱ)፡፡ (ኢብራሂም፤48)

ተፈጥሮአዊ እውቀትና የመጨረሻው ቀን

የዚህ ዓለም የመጥፈያ ጊዜ እሩቅ ሣይሆን ቅርብ ነው፡፡ የፍጥረተዓለሙ ተመራማሪዎች ጭምር ይህ ዓለም ፍፃሜ የሚያገኝበት አንድ ቀን ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡  ይህ ዓለም ከዚህ በፊት ለብዙ ዘመናት እየደረጀ እንደመጣ ሁሉ በቀጣይነትም እስከመጨረሻው ደረጃ ድረስ ያድግና ኋላም ላይ ይጠፋል፡፡ በዚህም ቁርኣን ያወሣው የዚህ ዓለም የመጥፋት እውነታ ከሣይንሳዊው ግኝት እውቀት ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡

የእስልምና ሃይማኖት ከአላህ እና ትክክለኛ ሃይማኖትም ስለመሆኑ ከሚያመለክቱ ትላልቅ ማስረጃዎች መካከል ስለ ዓለም መጥፋት በዚህ መልኩ የተናገረ አንድም አካል አለመኖሩ ነው፡፡ ቀደምት ሃይማኖቶችም ቢሆኑ ቁርኣን በጠቀሠው መልኩ ጉዳዩን አላወሱትም፡፡ ነገሩ የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ ፈጠራና አጓጉል ፍልስፍናም አይደለም፡፡ ባይሆን ለነቢዩ ከተሠጡት ሙዕጂዛዎች/ተዓምራቶች/ መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

ቀኑ መቼ ነው?

የትንሣኤ መከሠቻ ቀን እውቀቱ ያለው አላህ ሱ.ወ. ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ከአላህ ሱ.ወ ውጭ ከርሱ ዘንድ የተላከ መልእክተኛም ይሁን ወደ አላህ ቅርብ የሆነ መልኣክም ጭምር የሚያውቀው አይደለም፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

إِنَّ اللَّهَ عِندَهُ عِلْمُ السَّاعَةِ وَيُنَزِّلُ الْغَيْثَ وَيَعْلَمُ مَا فِي الْأَرْحَامِ

አላህ የሰዓቲቱ ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ዝናብንም ያወርዳል፡፡ በማሕፀኖችም ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃል፡፡(ሉቅማን፤34)

ሰዎች ነቢዩን ሰ.ዐ.ወ በዚህ ዙሪያ ይጠይቁ በጥያቄአቸውም ችክ ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን አላህ የፈጠረውን ዓለም የፍፃሜ ቀን እውቀት ለራሱ ብቻ ነው ያደረገው፡፡

إِلَيْهِ يُرَدُّ عِلْمُ السَّاعَةِ

ጊዜይቱን ማወቅ ወደእርሱ ይመለሳል(ፉሲለት፤47)

ለዚህ ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ሲሠጥ አላህ ሱ.ወ. እንዲህ ብሏል

يَسْأَلُونَكَ عَنِ السَّاعَةِ أَيَّانَ مُرْسَاهَا ۖ قُلْ إِنَّمَا عِلْمُهَا عِندَ رَبِّي ۖ لَا يُجَلِّيهَا لِوَقْتِهَا إِلَّا هُوَ ۚ ثَقُلَتْ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ لَا تَأْتِيكُمْ إِلَّا بَغْتَةً ۗ يَسْأَلُونَكَ كَأَنَّكَ حَفِيٌّ عَنْهَا ۖ قُلْ إِنَّمَا عِلْمُهَا عِندَ اللَّهِ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَاا يَعْلَمُونَ

ከሰዓቲቱ መቼ እንደምትረጋ (እንደምትመጣ) ይጠይቁሃል፡፡ «ዕውቀቷ በጌታዬ ዘንድ ነው፡፡ በጊዜዋ እርሱ እንጂ ሌላ አይገልጣትም፡፡ በሰማያትና በምድርም ከበደች፡፡ በድንገት ቢኾን እንጂ አትመጣችሁም» በላቸው፡፡ ከእርሷ አጥብቀህ እንደ ተረዳህ አድርገው ይጠይቁሃል፡፡ «ዕውቀቷ አላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም» በላቸው፡፡ (አል አዕራፍ፤187)

ከኢብኑ አመር ረ.ዐ እንደተዘገበው የአላህ ነቢይ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ

« مفاتيح الغيب خمس لا يعلمهن إلا الله: إن الله عنده علم الساعة، وينزل الغيث، ويعلم ما فى الأرحام، وما تدرى نفس ماذا تكسب غدًا، وما تدرى نفس بـ أى أرض تموت »

‹አላህ ብቻ እንጂ ማንም የማያውቃቸው የሩቅ እውቀት መክፈቻዎች አምስት ናቸው፡፡ አላህ ዘንድ የሰዓቲቱ /የትንሣኤ ቀን/ እውቀት አለ፣ ዝናብን ያወርዳል፣ በማህፀን ውስጥ ያለን ያውቃል፣ አንዲት ነፍስ ነገ የምትሠራውን አታውቅም፣ አንዲት ነፍስ በየትኛው ምድር እንደምትሞት አታውቅም፡፡›

አል አሉሲ በተፍሲራቸው እንዲህ ይላሉ ‹አላህ የሰዓቲቱን ቀን እውቀት የደበቀበት ምክኒያት ሸሪዓዊ ጥበብን ያዘለ ነው፡፡ ይህ መሆኑ የሰውን ልጅ ወደ መልካም ሥራ ያነሣሣል፤ ከመጥፎ ነገርም ይከለክላል፡፡ የሰው ልጅ የሞት ቀነ ቀጠሮ መደበቁ እንዲሁ ጥበባዊ ምክኒያት እንዳለው ሁሉ፡፡ ፍጥረተዓለማዊ ጥበቦች ሁሉ ይህንኑ ያሣያሉ ብንል ያስኬዳል፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን አንቀፅ የላይ በላይ ሁኔታ ስናይ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ የቂያማን የመከሠቻ ቀን አያውቁም፡፡ ማለትን ይመስላል፡፡ በርግጥም ሁኔታው ትክክል ነው፡፡ ባይሆን ቱርሙዚ በዘገቡት ሀዲስ እርሣቸው ማለትም ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ ለቂያማ ቀን መቃረብ ምልክት እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ. እንዲህ ብለዋልና

« بعثت أنا والساعة كهاتين ( وأشار بالسبابة والوسطى ) »

እኔና ሰዓቲቱ እንዲህ የሆንን ሲሆን ተላክሁኝ› (አመልካች እና የመሃል ጣታቸውን አንድ ላይ በማጣመር እያሣዩ) ፡፡

ነቢዩ በርግጥም ይህን ያሉት ቂያማ እጅግ መቃረቧን ለማመላከት ነው፡፡ቡኻሪና ሙስሊም ከኢብኑ ዑመር በዘገቡት ዘገባ ደግሞ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ.

« وإنما أجلكم فيمن مضى قبلكم من الأمم، من صلاة العصر إلى غروب الشمس »

‹የናንተ እድሜ ከበስተፊታችሁ ካለፉት ህዝቦች እድሜ ጋር ሲነፃፀር ከዐስር ሰላት እስከ ፀሃይ መጥለቅ ያለው ነው፡፡› ብለዋል፡፡

ስለዚህች ዓለም ህይወት ፍፃሜ ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆንልን ትክክለኛ ሀዲስ አልመጣም፡፡በዚሁ ዙሪያ ሲናገሩ ታዋቂው ዓሊም ኢብኑ ሀዝም እንዲህ ይላሉ ‹እኛ ሙስሊሞች ዘንድ በቁጥር የሚታወቅ ነገር የለንም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰባት ሺህ፤ ከዚያ በላይ አሊያም ከዚያ በታች ያለ ሰው ከነቢዩ ሰ.ዐ.ወ ያልተዘገበ ትክክለኛ ባልሆነ ንግግር ነው የተናገረው፡፡  ባይሆን ከነቢዩ የተዘገበው ቢኖር በተቃራኒው ነው፡፡ ይህች ዓለም አላህ ብቻ የሚያውቀው እድሜ ነው ያላት፡፡ የተላቀውና የተከበረው አላህ ሱ.ወ. እንዲህ አለ

مَّا أَشْهَدتُّهُمْ خَلْقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَلَا خَلْقَ أَنفُسِهِمْ

የሰማያትንና የምድርን አፈጣጠር አላሳየኋቸውም፡፡ የነፍሶቻቸውንም አፈጣጠር (እንደዚሁ)፡፡(አል ከህፍ፤51)

የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ በሌላ ሀዲሣቸው እንዲህ ብለዋል

« ما أنتم فى الأمم قبلكم إلا كالشعرة البيضاء فى الثور الأسود، أو الشعرة السوداء فى الثور الأبيض »

‹እናንተ ከቀደሟችሁ ህዝቦች ጋር ስትነፃፀሩ በጥቁር በሬ ውስጥ እንደ ነጭ ፀጉር አለያም በነጭ በሬ ውስጥ እንደ ጥቁር ፀጉር ናችሁ፡፡›

አል በዕስ/መቀስቀስ/

የመጨረሻው ቀን የሚጀምረው በመቀስቀስ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው የሰው ልጅን በዚህች ዓለም ላይ በፊት በነበረበት መልኩ በመንፈስና/ሩህ/ በአካል በመቀስቀስ ነው፡፡ ፡፡ ይህ መቀስቀስና ዳግም ወደ ነፍስ መዝራት የሚሆነው ሙሉ በሙሉ ከጠፉና ከታጡ በኋላ ነው፡፡ የሰው ልጅ ይህን የመጨረሻ ቀን መነሣት እንዴትነት አያውቅም፡፡ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሪያው አፈጣጠርና መነሣት ይለያልና፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

نَحْنُ قَدَّرْنَا بَيْنَكُمُ الْمَوْتَ وَمَا نَحْنُ بِمَسْبُوقِينَ
عَلَىٰ أَن نُّبَدِّلَ أَمْثَالَكُمْ وَنُنشِئَكُمْ فِي مَا لَا تَعْلَمُونَ
وَلَقَدْ عَلِمْتُمُ النَّشْأَةَ الْأُولَىٰ فَلَوْلَا تَذَكَّرُونَ

እኛ ሞትን (ጊዜውን) በመካከላችሁ ወሰንን፡፡ እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም፡፡ ብጤዎቻችሁን በመለወጥና በዚያ በማታውቁትም (ቅርጽ) እናንተን በመፍጠር ላይ (አንሸነፍም)፡፡የፊተኛይቱንም አፈጣጠር በእርግጥ ዐውቃችኋል፡፡ አትገነዘቡምን?(አል ዋቂዓህ፤60-62)

የመቀስቀስ ማስረጃዎች

ቁርኣን በመቀስቀስ ዙሪያ በርካታ ማስረጃዎችን አውርዷል፡፡ ይህም ከመጀመሪያው አፈጣጠር ጋር በማነፃፀርና አላህ ሱ.ወ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ፣ ሁሉንም ነገር አዋቂ መሆኑን በመግለፅ ችምር ነው፡፡ አላህ ችሎታ ማነስ ምክኒያት አካልን ወደነበረበት መመለስ የሚያቅተው አምላክ አይደለም፡፡ ዕውቀቱም ሰፊና ሁሉን ያካበበ ነውና አንድንም ነገር አይዘነጋም፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِن كُنتُمْ فِي رَيْبٍ مِّنَ الْبَعْثِ فَإِنَّا خَلَقْنَاكُم مِّن تُرَابٍ ثُمَّ مِن نُّطْفَةٍ ثُمَّ مِنْ عَلَقَةٍ ثُمَّ مِن مُّضْغَةٍ مُّخَلَّقَةٍ وَغَيْرِ مُخَلَّقَةٍ لِّنُبَيِّنَ لَكُمْ ۚ وَنُقِرُّ فِي الْأَرْحَامِ مَا نَشَاءُ إِلَىٰ أَجَلٍ مُّسَمًّى ثُمَّ نُخْرِجُكُمْ طِفْلًا ثُمَّ لِتَبْلُغُوا أَشُدَّكُمْ ۖ وَمِنكُم مَّن يُتَوَفَّىٰ وَمِنكُم مَّن يُرَدُّ إِلَىٰ أَرْذَلِ الْعُمُرِ لِكَيْلَا يَعْلَمَ مِن بَعْدِ عِلْمٍ شَيْئًا ۚ وَتَرَى الْأَرْضَ هَامِدَةً فَإِذَا أَنزَلْنَا عَلَيْهَا الْمَاءَ اهْتَزَّتْ وَرَبَتْ وَأَنبَتَتْ مِن كُلِّ زَوْجٍ بَهِيجٍ
ذَٰلِكَ بِأَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ وَأَنَّهُ يُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَأَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ
وَأَنَّ السَّاعَةَ آتِيَةٌ لَّا رَيْبَ فِيهَا وَأَنَّ اللَّهَ يَبْعَثُ مَن فِي الْقُبُورِ

እናንተ ሰዎች ሆይ! ከመቀስቀስ በመጠራጠር ውስጥ እንደ ሆናችሁ (አፈጣጠራችሁን ተመልከቱ)፡፡ እኛም ከዐፈር ፈጠርናችሁ፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም፣ ከዚያም ከቁራጭ ሥጋ፣ ፍጥረትዋ ሙሉ ከሆነችና ሙሉ ካልሆነች (ችሎታችንን) ለናንተ ልንገልጽላችሁ ፈጠርናችሁ፡፡ የምንሻውንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በማሕፀን ውስጥ እናረጋዋለን፡፡ ከዚያም ሕፃን ሆናችሁ እናወጣችኋለን፡፡ ከዚያም ሙሉ ጥንካሪያችሁን ትደርሱ ዘንድ (እናሳድጋችኋለን)፡፡ ከእናንተም የሚሞት ሰው አልለ፡፡ ከእናንተም ከዕውቀት በኋላ ምንንም እንዳያውቅ ወደ ወራዳ ዕድሜ የሚመለስ ሰው አልለ፡፡ ምድርንም ደረቅ ሆና ታያታለህ፡፡ በእርሷም ላይ ውሃን ባወረድን ጊዜ ትላወሳለች፡፡ ትነፋፋለችም፡፡ ውበት ካለው ጎሳ ሁሉ ታበቅላለችም፡፡ይህ አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡ሰዓቲቱም መጪ ፣ በእርሷ ፈጽሞ ጥርጣሬ የሌለባት በመሆኗ፣ አላህም በመቃብሮች ውስጥ ያለን ሁሉ የሚቀሰቅስ በመሆኑ ነው፡፡          (አል ሀጅ፤5-7)

አላህ ሱ.ወ ሰማይና ምድርን ከምንም መፍጠር አላቃተውም፡፡ ዛሬም ድረስ እየፈጠረ፣ እየለገሠ፣ እያኖረ፣ እየገደለ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ከምናየው ከምናስተውለው ነገር ሁሉ በኋላ መልሦ መፍጠሩ እንዴት ያቅተዋል!

أَفَعَيِينَا بِالْخَلْقِ الْأَوَّلِ ۚ بَلْ هُمْ فِي لَبْسٍ مِّنْ خَلْقٍ جَدِيدٍ

በፊተኛው መፍጠር ደከምን? በእውነቱ እነርሱ ከአዲስ መፍጠር በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ (ቋፍ፤15)

ከነኚህ በነፍስም ሆነ በአድማስ በሚታዩ ግልፅ ማስረጃዎች ሁሉ በኋላ መቀስቀስንም ሆነ ዳግም ወደ ህይወት መመለስን መካድ ትርጉም የለውም፡፡

መቀስቀስን የሚክዱ ሰዎች የሚያነሷቸው ማምታቻዎች

ከምናውቀውና ከተላመድነው ተጨባጭና ያለፈ ሁነታ ጋር ይጋጫል፡፡› በማለት ከሰዎች ከፊሎቹ የመቀስቀስን እውነታ ክደዋል፡፡ ጉዳዩም ለነሱ የማይዋጥ ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ ሰውነት ከተበጣጠሠና ከተለያየ ከበሰበሰ በኋላ ወደነበረበት የመመለሱን ነገር ህሊናቸው የሚቀበለው አይመስልም፡፡ የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ አፈር ነው የሚሆነው፤ አፈርም ለአትክልቶች ማብቀያ ይሆናል፤ ሰዎችም እነዚያን አትክልቶችና አዝርእቶች ለምግብነት ይጠቀማሉ ከዚያም ይሞታሉ፤ በቃ ያለው ሂደት ይሀው ነው፡፡› በማለት ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡‹ታዲያ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ የሰው ልጅ እንዴት ሊቀሰቀስ ይችላል?› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ውዥንብር ቀድሞም የነበረ ሲሆን ዛሬም ድረስ ከብዙዎች ልቦና ውስጥ አልጠፋም፡፡ ቁርኣንም ይህንኑ ጉዳይ በተደጋጋሚ አንስቶ መልስ ሠጥቶበታል፡፡

وَقَالُوا مَا هِيَ إِلَّا حَيَاتُنَا الدُّنْيَا نَمُوتُ وَنَحْيَا وَمَا يُهْلِكُنَا إِلَّا الدَّهْرُ ۚ وَمَا لَهُم بِذَٰلِكَ مِنْ عِلْمٍ ۖ إِنْ هُمْ إِلَّا يَظُنُّونَ
وَإِذَا تُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ آيَاتُنَا بَيِّنَاتٍ مَّا كَانَ حُجَّتَهُمْ إِلَّا أَن قَالُوا ائْتُوا بِآبَائِنَا إِن كُنتُمْ صَادِقِينَ
قُلِ اللَّهُ يُحْيِيكُمْ ثُمَّ يُمِيتُكُمْ ثُمَّ يَجْمَعُكُمْ إِلَىٰ يَوْمِ الْقِيَامَةِ لَا رَيْبَ فِيهِ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ

እርሷም (ሕይወት) የቅርቢቱ ሕይወታችን እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡ «እንሞታለን፤ ሕያውም እንኾናለን፡፡ ከጊዜም (ማለፍ) በስተቀር ሌላ አያጠፋንም» አሉ፡፡ ለእነርሱም በዚህ (በሚሉት) ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚጠራጠሩ እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡አንቀጾቻችንም ግልጾች ኾነው በእነርሱ ላይ በተነበቡላቸው ጊዜ ክርክራቸው «እውነተኞች እንደ ኾናችሁ አባቶቻችንን አምጡ» ማለት እንጅ ሌላ አልነበረም፡፡«አላህ ሕያው ያደርጋችኋል፤ ከዚያም ይገድላችኋል፣ ከዚያም ወደ ትንሣኤ ቀን ይሰበስባችኋል፡፡ በእርሱ ጥርጥር የለበትም፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም» በላቸው፡፡(አል ጃሲያህ፤24-26)

አላህ ለነዚያ መቀስቀስን ለሚያስተባብሉ ሰዎች ማስተባባላቸው ምንም እንደማይጠቅማቸውና ትርጉም እንደሌለው መለሠባቸው፡፡ ምክኒያቱም እነሱ የአላህን ታላቅነትና ሀያልነት ችሎታውን፣ እውቀቱንና ጥበቡን አልተገነዘቡም፡፡ ወደ ነፍሦቻቸውም አልተመለከቱም፡፡ በነፍሦቻቸቸው ውስጥ ትላልቅ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለሚክዱት ነገርም ማስረገጫ የሆነ ጠንካራ ማሣመኛና ማሣያ እሩቅ ሣይሄዱ በቅርብ አለላቸው፡፡ አላህ ነው መጀመሪያውኑ የፈጠራቸው፡፡ ኋላም እንዲሞቱ ያደረጋቸው እርሱ ነው፡፡ ይህን ያደረገ ጌታ እነሱን ዳግም ቀስቅሶ አንድ ላይ በመሰብሰብ ለጥያቄ ማቅረብ አያቅተውም፡፡ ይህ ፈፅሞ መካድ የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

وَهُوَ الَّذِي يَبْدَأُ الْخَلْقَ ثُمَّ يُعِيدُهُ وَهُوَ أَهْوَنُ عَلَيْهِ ۚ وَلَهُ الْمَثَلُ الْأَعْلَىٰ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ وَهُوَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ

እርሱም ያ መፍጠርን የሚጀምር ከዚያም የሚመልሰው ነው፡፡ እርሱም (መመለሱ) በእርሱ ላይ በጣም ገር ነው፡፡ ለእርሱም በሰማያትም በምድርም ከፍተኛ ባሕርይ (አንድነትና ለእርሱ ብጤ የሌለው መኾን) አልለው፡፡ እርሱም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡(አር ሩም፤27)

በመቀስቀስ ጉዳይ ላይ የሰዎች መለያየት

በመቀስቀስ ዙሪያ የሰው ልጆች እንደየሥራቸው በብዙ መልኩ በሀሣብ ተለያይተዋል፡፡ እነዚያ  እምነታቸውና አመለካከታቸው የተስተካከለው፣ ሥራቸው ያማረው፣ ነፍሣቸውም የጠራው እነሱ ናቸው የተሟላ አካልና መንፈስ ባለቤቶች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥራቸው መጥፎ የሆነው፣ አመለካከታቸውም የተበላሸው የጎደለ አካልና መንፈስ ባለቤቶች እነርሱ ናቸው፡፡

ከአቢ ሁረይራ ረ.ዐ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐወ አንዲህ አሉ

« يحشر الناس يوم القيامة ثلاثة أصناف: صنف مشاة، وصنف ركبان، وصنف على وجوههم » قيل: يا رسول الله كيف يمشون على وجوههم ؟ قال: « إن الذى أمشاهم على أقدامهم قادر على أن يمشيهم على وجوههم، أما إنهم يتقون بوجوههم كل حَدَب وشكوك »

‹የሰው ልጆች በትንሣኤ ቀን በሦስት አይነት ሁኔታ ላይ ይቀሠቀሳሉ፡፡ በእግሮቻቸው የሚሄው፣ በእንሠሳ ተሣፍረው የሚጓዙ እና በፊታቸው ተደፍተው የሚሄዱት ናቸው› አሉ፡፡ ‹በፊቶቻቸው እንዴት ነው የሚሄዱት? የአላህ መልእክተኛ ሆይ!› አሏቸው፡፡ እርሣቸውም በእግራቸው ያስኬዳቸው (አምላክ) በፊታቸውም ሊያስኬዳቸው ቻይ ነው፡፡ በፊቶቻቻው ሁሉንም ኮረብታና እሾህ አይጠነቀቁም፡፡›

በሌላ ሀዲስ ደግሞ የተከበሩት የአላህ ነቢይ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል

« يحشر المتكبرون والمتجبرون يوم القيامة فى صور الذَّرِّ تطؤهم الناس، لهوانهم على الله  »

‹ኩራተኞችና አምባገነኖች የትንሣኤ ቀን አላህ ሱ.ወ ዘንድ ዋጋ የሌላቸው ከመሆኑ የተነሣ (መሬት ላይ በወደቀ) የእህል ዘር ፍሬ ተመስለው ሰዎች ይረጋግጧቸዋል፡፡›

ሙስሊም ከጃቢር ረ.ዐ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው አለ

« يبعث كل عبد على ما مات عليه »

‹እያንዳንዱ (የአላህ ባሪያ) በሞተበት ነገር ላይ ይቀሠቀሣል፡፡›

ይህም ማለት በኼይር ነገር ላይ የሞተ ደስ በሚል ጥሩ ሁኔታ ላይ ይቀሠቀሣል በመጥፎ ነገር ላይ የሞተም በአስቀያሚ ሁኔታ ላይ ይቀሠቀሣል ማለት ነው፡፡ ንም እንኳ የመንፈስ ሀይል በሰውነት ላይ እንደሻት የመሆን ከፍተኛውን ሀይል ቢኖራትም መቀስቀስ የሚሆነው በህይወትና በአካልም ጭምር ነው፡፡ የመንፈስ ሀይል በአጭር ጊዜ ረጅሙን መንገድ ማቋረጥና በጀነትና በእሣት ሰዎች መካከል በንግግር መመላለስም ትችላለች፡፡ ይህም በነገሮች የመመሠልና የምትኖርበትን አካል የመቆጣጠር ሁኔታዋ ከመላኢኮችን ጅኖች ጋር ያመሣስላታል፡፡

ሸፈዓ/ምልጃ/

ምልጃ ማለት በመጨረሻው ቀን አላህ ሱ.ወ ለሰው ልጆች መልካሙን ነገር የሚሻበት ሥርኣት ነው፡፡ ሸፈዓ/ምልጃ/ ምላሽ ካላቸው ዱዓኦች መካከል የምትጠቀስ ናት፡፡

ከነኚህም መካከል ለታላቁ ነቢያችን ብቻ የምትሆነው ታላቋ ምልጃ ትጠቀሣለች፡፡ ያኔ የሰው ልጆች ከቂያማ ቀን አስፈሪ ሁኔታ ፋታ ያገኙ ዘንድ የአላህ መልአክተኛ ሰ.ዐ.ወ አላህ ለሰዎች ፍርድ ይሠጥ ዘንድ ያማልዳሉ፡፡ አላህ ለጥያቄአቸውና ዱዓኣቸውም ምላሽ ይሠጣል፡፡ በተሠጣቸው ላቅ ያለ ክብርም የመጀመሪያዎቹም ሆኑ የመጨረሻዎቹ ህዝቦች ይቀኑባቸዋል፡፡  በዚህም ሥርኣት ነቢያችን ሰ.ዐ.ወ በፍጥረተ ዓለሙ ላይ ታላቁና በላጭ ሰው ስለመሆናቸው ግልፅ ይወጣል፡፡ አላህ ቃል የገባላቸው መቃመል መህሙድ /ምስጉን ቦታ/ የሚባለውም ይሀው ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

وَمِنَ اللَّيْلِ فَتَهَجَّدْ بِهِ نَافِلَةً لَّكَ عَسَىٰ أَن يَبْعَثَكَ رَبُّكَ مَقَامًا مَّحْمُودًا

ከሌሊትም ላንተ ተጨማሪ የኾነችን ሶላት በእርሱ (በቁርኣን) ስገድ፡፡ ጌታህ ምስጉን በኾነ ስፍራ በእርግጥ ያቆምሃል፡፡(አል ኢስራእ፡ 79)

ከኢብኑ ዑመር ረ.ዐ እንደተዘገበው የአላህ ነቢይ ሙሀመድ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ

« إن الشمس تدنو يوم القيامة، حتى يبلغ العَرَق نصف الأذن، فبينما هم كذلك استغاثوا بآدم، فيقول: لست بصاحب ذلك ثم بموسى، فيقول كذلك، ثم بمحمد، فيشفع، ليقضى بين الخلق، فيمشى حتى يـ أخذ بحلْقَة باب الجنة، فيومئذ، يبعثه الله مقامًا محمودًا يحمده أهل الجمع كلهم »

‹የቂያማ ቀን ፀሃይ በጣም የቀረበች ትሆናለች፡፡ ላቡ ከፊል ጆሮው ድረስ የሚያሠጥመው ሰው አለ፡፡ በዚያ ሁኔታ ላይ ሣሉ (ከዚህ ጭንቅ እንዲገላግሏቸው) ለአደም ዐ.ሰ የ(አማልደን) የእርዳታ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ እርሣቸውም ‹እኔ ለዚህ ብቁ አይደለሁም› በማለት ይመልሷቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሙሣ ዐ.ሰ ይሄዳሉ፡፡ ሙሣ አደም እንዳለው ይሏቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሙሀመድ ሰ.ዐ.ወ ይመጣሉ፡፡ እርሣቸውም አላህ ለሰዎች ፍርድ ይሠጥ ዘንድ ያማልዳሉ፡፡ ከዚያ  በጀነት በር ማንጠልጠያ እስኪይዙ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ያኔ አላህ ሰዎች ሁሉ የሚያመሰግኑባቸው የሆነ ምስጉን ቦታ ላይ ያነሣቸዋል፡፡›

ከኡበይ ኢብኑ ከዕብ እንደተዘገበው ደግሞ ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ አሉ

« إذا كان يوم القيامة كنتُ إمام الأنبياء، وخطيبهم، وصاحب شفاعتهم من غير فخر»

‹ቂያማ የተከሠተች እለት እኔ የነቢያት መሪ እና ንግግር አድራጊያቸው እንዲሁም የምልጃቸው ባለቤት እሆናለሁ፡፡ ይሄ ጉራ አይደለም፡፡›

ከዚህ ከላይ ከተጠቀሠው ውጭ ያለው ምልጃ ሁሉ መስፈርት አለው፡፡ እነሱም

  1. ከአላህ ሱ.ወ ፈቃድ የተሠጠው ምልጃ መሆን አለበት፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
مَن ذَا الَّذِي يَشْفَعُ عِندَهُ إِلَّا بِإِذْنِهِ

ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ ማነው?(አል በቀራህ፤255)

  1. አላህ ምልጃ እንዲደረግለት ለወደደው/ለፈቀደው/ ሰው ብቻ መሆን አለበት፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَلَا يَشْفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ارْتَضَىٰ

ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም፡፡(አል አንቢያእ፤28)

አምላካዊ ፍትህን መሠረት ባደረገ መልኩ አላህ ሱ.ወ ይቅር ያላቸው ብቻ ናቸው የምልጃ የሚያገኙት፡፡ ምልጃ የምልጃ ጠያቂውን ክብርና በአላህ ዘንድ ያለውን ቦታ ያመለክታል፡፡ ዱዓእ ባደረገና ከአላህም ምላሹን በፈለገ ጊዜ የአላህ መሻት ይፈፀም ዘንድ፡፡ ምልጃ ጠያቂው በሚያደርገው ዱዓእ ውስጥ የሰው ልጅ ነፍስ የምትጠራበትን ኢማንን እንዲሁም ለሰው ልጅ ስብእና መሟላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለውን መልካም ሥራን መዘንጋት አሊያም ችላ ማለት የለበትም፡፡ ጣኦት አምላኪዎች አምላኮቻችን ይጠቅሙናል በማለት ጣኦቶቻቸውን ይተማመኑ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዳለው

وَيَعْبُدُونَ مِن دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَضُرُّهُمْ وَلَا يَنفَعُهُمْ وَيَقُولُونَ هَٰؤُلَاءِ شُفَعَاؤُنَا عِندَ اللَّهِ

ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ይግገዛሉ፡፡ «እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው» ይላሉ፡፡(ዩኑስ፡ 18)

አላህ ሱ.ወ ግን እንዲህ በማለት ተስፋ አስቆረጣቸው፡፡

كُلُّ نَفْسٍ بِمَا كَسَبَتْ رَهِينَةٌ
إِلَّا أَصْحَابَ الْيَمِينِ
فِي جَنَّاتٍ يَتَسَاءَلُونَ
عَنِ الْمُجْرِمِينَ
مَا سَلَكَكُمْ فِي سَقَرَ
قَالُوا لَمْ نَكُ مِنَ الْمُصَلِّينَ
وَلَمْ نَكُ نُطْعِمُ الْمِسْكِينَ
وَكُنَّا نَخُوضُ مَعَ الْخَائِضِينَ
وَكُنَّا نُكَذِّبُ بِيَوْمِ الدِّينِ
حَتَّىٰ أَتَانَا الْيَقِينُ
فَمَا تَنفَعُهُمْ شَفَاعَةُ الشَّافِعِينَ

ነፍስ ሁሉ በሠራችው ሥራ ተያዥ ናት፡፡የቀኝ ባለቤቶች ብቻ ሲቀሩ፡፡ከአመጸኞቹ ኹነታ፡፡(ይሏቸዋልም) «በሰቀር ውስጥ ምን አገባችሁ?»(እነርሱም) ይላሉ «ከሰጋጆቹ አልነበርንም፡፡ «ለድኾችም የምናበላ አልነበርንም፡፡ «ከዘባራቂዎቹም ጋር እንዘባርቅ ነበርን፡፡ «በፍርዱ ቀንም እናስተባብል ነበርን፡፡ «እርግጠኛው (ሞት) እስከ መጣን ድረስ፡፡» የአማላጆችም ምልጃ አትጠቅማቸውም፡፡             (አል ሙደሲር፤38-48)

አብዛኞቹ ሰዎች በሃይማኖቱ ውስጥ የተዛቡ ትርጉሞችን በማስገባት በመልካም ሰዎች ምልጃ መተማመንን ተስፋቸው አድርገዋል፡፡ በዚህም የተነሣ በተበላሸ አመለካከታቸው በርካቶች ከአላህ ትእዛዛት ርቀዋል፡፡ አላህ ሱ.ወ ማስረጃቸውን ቆራጣ አደረገው፡፡ እንዲህ በማለት

لَّيْسَ بِأَمَانِيِّكُمْ وَلَا أَمَانِيِّ أَهْلِ الْكِتَابِ ۗ مَن يَعْمَلْ سُوءًا يُجْزَ بِهِ وَلَا يَجِدْ لَهُ مِن دُونِ اللَّهِ وَلِيًّا وَلَا نَصِيرًا
وَمَن يَعْمَلْ مِنَ الصَّالِحَاتِ مِن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَأُولَٰئِكَ يَدْخُلُونَ الْجَنَّةَ وَلَا يُظْلَمُونَ نَقِيرًا
وَمَنْ أَحْسَنُ دِينًا مِّمَّنْ أَسْلَمَ وَجْهَهُ لِلَّهِ وَهُوَ مُحْسِنٌ وَاتَّبَعَ مِلَّةَ إِبْرَاهِيمَ حَنِيفًا

(ነገሩ) በምኞታችሁና በመጽሐፉ ሰዎች ምኞት አይደለም፡፡ መጥፎን የሚሠራ ሰው በእርሱ ይቀጣል፡፡ ለእርሱም ከአላህ ሌላ ጠባቂንም ረዳትንም አያገኝም፡፡ ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡ በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳ አይበደሉም፡፡ እርሱ መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ለአላህ ከሰጠና የኢብራሂምንም መንገድ ቀጥተኛ ሲኾን ከተከተለ ሰው ይበልጥ ሃይማኖቱ ያማረ ማን ነው?(አን ኒሣእ፤123-125)

እውነተኛው ሃይማኖት ለአላህ ብሎ እጅ መስጠትና ሥራን ማሣመር ነው፡፡ በኢስላማዊ የህይወት መንፈስ ውስጥመኖር የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ ለልጃቸው ፋጢማ ረ.ዐ ያስተላለፉት አደራ ነው፡፡ እንዲህ ብለዋታል

« اعملى يا فاطمة، فأنى لا أغنى عنك من الله شيئًا »

‹ ፋጢማ ሆይ! በርትተሸ ሥሪ እኔ ከአላህ (ቅጣት) አላድንሽምና፡፡›

አላህ ሱ.ወ የሰውን ልጅ ከመበደልና ጥረቱንም ከማናናቅ የጠራ ጌታ ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያዎቹም ሆነ በኋላኞቹ ትውልዶች ውስጥ የተላለለፈ መንገዱ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

أَمْ لَمْ يُنَبَّأْ بِمَا فِي صُحُفِ مُوسَىٰ
وَإِبْرَاهِيمَ الَّذِي وَفَّىٰ
أَلَّا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ
وَأَن لَّيْسَ لِلْإِنسَانِ إِلَّا مَا سَعَىٰ
وَأَنَّ سَعْيَهُ سَوْفَ يُرَىٰ
ثُمَّ يُجْزَاهُ الْجَزَاءَ الْأَوْفَىٰ

ይልቁንም በዚያ በሙሳ ጽሑፎች ውስጥ ባለው ነገር አልተነገረምን?በዚያም (የታዘዘውን) በፈጸመው በኢብራሂም (ጽሑፎች ውስጥ ባለው አልተነገረምን?) (እርሱም ኃጢያት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም፡፡ ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም፡፡ ሥራውም ሁሉ ወደ ፊት ይታያል፡፡ ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል፡፡ (አን ነጅም፤36-41)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here