ሰላም ትርጉሙ የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። ይልቁንም ህዝቦች የጋራ ፍላጎት እና ጥቅሞቻቸዉን ለማስከበር በጋራ የሚቆሙለት የዚህ አለም ታላቅ ድልብ እና የአላህ ስጦታ ነዉ። ዜጎች ተሳስበዉ፤ ተረዳድተዉ፤ እና ተዛዝነዉ የሚፈጥሩት ምቹ እና የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ ማለት ነዉ ሰላም። አንድ ማህበረሰብ የታላቅነት ተምሳሌት ሆኖ ሊታይ የሚገባዉ ባሰፈናቸዉ የሰላም ጊዜያት እንጂ ባሸነፋቸዉ ጦርነቶች፤ በገደላቸዉ፤ ባሰራቸዉ እና ከሀገር ባሳደዳቸዉ ዜጎቹ ቁጥር ሊሆን አይችልም።

የአለም ስልጣኔዎች የስኬት ጫፍ የደረሱባቸዉ ዘመናትን ብንቆጥር ሰላም ማስፈን በቻሉባቸዉ አመታት እነደሆነ ታሪክን የኃሊት መመልከት በቂ ማስረጃ ነዉ። ከጎረቤታችን ሜርዌ ስልጣኔ፤ እስከ አክሱም፤ የሩቁን የሮማን፤ የፐርሽያን እና ሌሎችንም ስልጣኔዎች ብንመለከት ከዉስጥ ከህዝባቸዉ ከዉጭ ደግሞ ከአቻ ስልጣኔዎች ጋር ባላቸዉ የሰላም ርቀትና ቅርበት የእድሜ ዘመናቸዉን ቆጥረዉ የታሪክ ገፆቻቸዉን አድምቀዉ ወይም አጉድፈዉ አልፈዋል።

የሰላም መደፍረስን አስከፊነት የሰዉ ልጅ ከረዥም ዘመናት ልምዱ ሊማር ካልቻላቸዉ ወይም በፍጥነት ከሚዘነጋቸዉ (unlearn) መራራ የህይወት እዉነታዎች በዋናነት የሚጠቀስ ነዉ። የሰላምን ዋጋ ሰላም ያጡ ብቻ ይረዱታል እንዲሉ አንድን መራራ የታሪክ ምእራፍ ዘግተዉ ለመራመድ በሚያደርጉት ጥረት የመሪዎች መቀያየር የታለፉትን መራራ ጊዜያት እንደዋዛ ረስተዉ ለከፋ እልቂት ህዝቦቻቸዉን ያዘጋጃሉ። ዜጎቻቸዉን በክፉ ፕሮፓጋንዳ (Horrendous propaganda) ሸንግለዉ ለእልቂት ያሰልፉታል።

አንድ ማህበረሰብ የታላቅነት ተምሳሌት ሆኖ ሊታይ የሚገባዉ ባሰፈናቸዉ የሰላም ጊዜያት እንጂ ባሸነፋቸዉ ጦርነቶች፤ በገደላቸዉ፤ ባሰራቸዉ እና ከሀገር ባሳደዳቸዉ ዜጎቹ ቁጥር ሊሆን አይችልም።

እልፍ የሙስሊሙ አለም ልሂቃን ኢስላም የሰላም ሀይማኖት ነዉ ሲሉ ፅፈዋል፤ በተግባርም ያሳዩባቸዉን አጋጣሚዎች ቆጥሮ ማስረዳት ይቻላል። ብዙዎቹም በግለሰብ፤ በማህበረሰብ ብሎም በአለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን በዋጋ ሊተመን የማይችል መስዋእትነትን የከፈሉ እልፍ ስብእናዎች በሰዉ ልጅ ታሪክ ዉስጥ አልፈዋል። አሁንም ይህን ከባድ ዋጋ ለመክፈል ፍቃደኛ የሆኑ እልፍ አእላፍ ነፍሶች ይገኛሉ። ከነዚህ ብርቅዬ ስብእናዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ነብያት ናቸዉ። ብዙዎች የተገደሉለት፤የተሰደዱለት፤ የተገረፉለትን ሰላም ዋጋዉን የሚረዱት ጥቂቶች ናቸዉ። ለህዝቦቻቸዉ ሰላም የተዘረጉ እጆቻቸዉን በትእቢት እና ጥላቻ ሊጠመዝዙት ተሸቀዳደሙ፤ ለህዝባቸዉ ስኬት የተፈጠረ ህይወታቸዉን በጭካኔ ለመቅጠፍ ተቻኮሉ። የሰላም አምባሳደሮቻቸዉን የሀዘን እና የዉርደት ካባ ለማልበስ እንቅልፍ አጥተዉ አነጉ፤ ለዚሁ የጥፋት ተልእኮ ያልተባረከ (unholy) ህብረት ፈጠረዋል፤ ያለስስት ሀብትና ንብረታቸዉን አፍሰዋል። ይህ ለእኩይ ተግባር የባከነ ጊዜና ጉልበት፤ ሀብትና ንብረት ለሰዉ ልጆች ክብር፤ እኩልነትና ነፃነት ቢዉል አለም አሁን ካለችበት የተሻለ ልትሆን በታደለች ነበር።

የሰላም መሰረቱ ፍትህ፤ ለፍትህ መስፈን ደግሞ ቀናኢ መሪ መኖሩ የግድ ይሆናል። የአለምን ታሪክ የኃሊት ለተመለከተ የመሪዎች ስብእና ለማህበረሰባዊ ብሎም ለታላላቅ ስልጣኔዎች ማበብና መክሰም ቀዳሚዉን ስፍራ ይዘዉ እናገኛለን። ያላቸዉን የመንግስትነት መዋቅር (State Machine) ተጠቅመዉ የፈለጉትን ደባ ሲሻቸዉ በአገር ፍቅር ስም፤ አልያም በመጤ ርእዮተ-አለም (imported Ideologies) የአብራካቸዉ ክፋይ የሆኑ ዜጎቻቸዉን ያለርህራሄ ፈጅተዋል፤አስፈጅተዋል።

በጣም የሚያሳዝነዉ አሁን በኛ ዘመን ከላይ የጠቀስናቸዉ ሁሉ ባህሪያት ይበልጥ ተወሳስበዉና በፕሮፓጋንዳ ተኳኩለዉ መገኘታቸዉ ነዉ። ይህም የሰዉ ልጅ እስከ አሁኑ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን የንቃተ ህሊናዉ እስከዚህ ጣራ ያላሳደገ መሆኑን ያመላከተ ነዉ።

ኢስላም ሙሉ የህይወት ዘዬ ነዉ። ከልዩ ብህሪያቱ ሁለቱ ምሉእነት እና ቅድመ-አድራጊነት (ፕሮ-አክቲቭ) ይገኙበታል። ኢስላም ሰላምን የሚመለከትበት መነፅር ከነዚህ ሁለት መርሆች አንፃር ለመመልከት እንሞክር።

የሰላም መሰረቱ ፍትህ፤ ለፍትህ መስፈን ደግሞ ቀናኢ መሪ መኖሩ የግድ ይሆናል።

ምሉእነት /Wholistic/

ሰላምን በቁንፅል (የጦርነት አለመኖር) ትርጉሙ መረዳት አደጋ አለዉ። የዜጎች ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ነፃነትና ደህንነት ባልተከበረበትና ባልተረጋገጠበት የሀገር ሰላም ሰፍኗል ማለት አይቻልም። ዜጎች ባኮረፉባት እና ከልባዊ ተሳትፎ በተቆጠቡበት ሁኔታ ሁለንተናዊ ልማት ማምጣት የሚታሰብ አይሆንም። የሰላም መስፈን ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ፍትህን በግለሰብ፤ ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ደረጃ ማስፈን ነዉ። የፍትህ እጦት፤ ወገንተኝነት፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ያለመተማመንን እና ያለመረጋጋትን ይፈጥራሉ። ይህም ለሰላም መደፍረስ በር ከፋች ይሆናል። ኢስላም ከላይ ከዘረዘርናቸዉ ችግሮች ያስቀመጣቸዉ መልስና መፍትሄዎች አሉት። የነዚህ መልስና መፍትሄዎች በአግባቡ መተግበር ሁለንተናዊ ሰላምን ያሰፍናል። የችግሮች መፍትሄ ተደርገዉ የሚወሰዱ ማናቸዉም እርምጃዎች በቅድሚያ የተቀናጁ፤ ምሉእ የሆኑ እና ቀጣይነት ያላቸዉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ኢስላም እንደ ስርአት (system) ችግሮችን የሚረዳበት እና መፍትሄ ብሎ የሚያቀርባቸዉ ተግባራት ሁሌም እነዚህን ሶስቱን ባህሪያት ያቀፉ ሆነዉ እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ የጋብቻና ፍቺ ጉዳችን ብንመለከት ኢስላም ከተጋዳኝ መረጣ መስፈርት ይጀምራል። ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዳሉት ሴት ልጅ በብዙ መስፈርት ልትመረጥ ትችላለች የበለጠዉ ዋጋ የሚሰጠዉ መስፈርት ግን ሀይማኖታዊ እሴቶቿ መሆን እንዳለበት ይነግሩናል። ከዚያም ኢስላም የሚስት እና ባልን አብሮ የመኖር ደንብና ስርአት ያስቀምጣል። በተለይ ለሴት ልጅ ፍቅርና ርህራሄን ለወንዱ ክብርና ኃላፊነቱን አፅእኖት ሰጥቶ ይሰብካል። የከረረ ያለመግባባት ቢፈጠር  በማስከተል ፍችን የተጠላ ግን የተፈቀደ ሲል ያስተምራል። ከዚህ አልፎ የሚፈርስ ትዳር ካለ ሰፊ የፍቺ ቀኖናዎችን አስቀምጧል። ብዙዎቹ ከተቻለ ትዳሩን ከመፍረስ አደጋ የመጠበቅ አልያም በመልካም ሳይበድሉና ሳይበደሉ እንዲለያዩ በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ በቁርአን እና በሀዲስ አስደግፎ ያስተምራል። ጋብቻን እንደምሳሌ ወሰድን እንጂ ሁሉም የኢስላም ህግጋት በችግር አረዳድም ይሁን በመፍትሄ አሰጣጥ ምሉእነትን የተላበሱ ሆነዉ እናገኛቸዋለን። ሰላም በግለሰብ፤ በቤተሰብ ብሎም በማህበረሰቡና በአለም ላይ ይሰፍን ዘንድ ችግሮቻችንን የምናይበት /የምንለይበትና መፍትሄ የምንፈልግበት መንገድ ፍጹም ምሉእነትን የተላበሰ መሆን ይጠበቅበታል። ኢስላም ከዚህ አንፃር ሰላምን ለማስፈን የሚከተላቸዉ መንገዶች ምሉእነትን የተላበሱ ናቸዉ።

አዎንታዊነት /Proactiveness/

ኢስላም በብዙ መንገድ ከሚስተምራቸዉ እና የመሪነት እድሉን ባገኘባቸዉ ዘመናት ሲተገብራቸዉ ከነበሩት ተግባራት አንዱ አዎንታዊነት ነዉ። በየደረጃዉና በየዘርፉ የምንወስዳቸዉ ሰላም የማስፈን ተግባራት ከችግሮች መፈጠር በፊት ከሆኑ ቀላል፤ዋጋዉ ዝቅተኛ፤ አዋጭ እና ስኬታማ ይሆናሉ። ጦርነቶች በከፊል የአዎንታዊነት እጦት ዉጤቶች ናቸዉ ቢባል ሀሰት አይሆንም። የሀገር መሪዎች ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን ወይም አካላትን ጠንቅቀዉ መለየትና ቀድመዉ መፍተሄ መሻታቸዉ ለህዝባቸዉ ደህንነትና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ይህም በሀገር እድገት ላይ የሚያመጣዉ ልዩነት ቀላል አይደለም። በግለሰብ ደረጃ እንኳ ብናየዉ አዎንታዊነት /ቅድመ-አድራጊነት/ ያለዉ ጥቅም ከፍተኛ እደሆነ እንረዳለን።

ለሰላም መስፈን ቅን ልቦና፤ ምሉእነት ያለዉ የችግሮች አረዳድና መፍትሄ አሰጣጥ፤ ቅድመ አድራጊነትን የተላበሰ አፈጻጸም እጅግ ወሳኝ ግብአቶች ናቸዉ።

ኢስላም ሰላምን ለማስፈን ከሚሰብካቸዉ እና ከሚጠቀምባቸዉ መንገዶች የተወሰኑትን እንጥቀስ፦

1) የግለሰብ ስብእናን ማሳደግ፡ ኢስላም ለግለሰብ የሚሰጠዉ ቦታ እጅግ የላቀ ነዉ። እንደ መርህም ዳእዋ/ጥሪ/ ከግለሰብ ይጀምራል። የግለሰቦች መስተካከል ለሰላም ማበብና ለልማት ከፍተኛ ድርሻ አለዉ።

2) የቤተሰብ አስፈላጊነት እና ሰላም፡ ቤተሰብ የማህበረሰብ መሰረት ነዉ። ቤተሰብ ላይ ያልተዘራ መልካም ነገር ማህበረሰብ ላይ መፈለግ ላም ባልዋለበት ይሆናል። ኢስላም የቤተሰብን ሚና ከፍተኛ ዋጋ ሰጥቶታል።

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ከእሳት ጠብቁ… (አል ቁርአን)

3) የማህበረሰብን ጤናማነት እና ሰላም፡ ነብያት የሚላኩት ማህበረሰቡ ከፈጣሪዉ ጋር ያለዉን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ነዉ። እሺ ብሎ ነብያትን ቢከተል የሁለቱን አለም ድልቦች ያገኛል። እምቢና አሻፈረኝ ካለም የዚህችን እና የቀጣዩን አለም እድሉን ያበላሻል። የማህበረሰብ ግንዛቤ ለሰላም መስፈን ወይም መደፍረስ ከፍተኛ ሚና አላቸዉ።

4) የየዘመናቱን የሰዉ ልጅ የግንዛቤ አና ሰላም፡ ኢስላም በየዘመናቱ የነበሩትን ኢፍትሀዊ አሰራሮች እና አመራሮች ከፍ ባለ ድምጽ ተቃዉማል፤ ጎጂ የሆኑ በርካታ ወግና ልማዶችን በማረቅ /በማረም/ የሰዉ ልጆችን ወደተሻለ ክብር እና ስልጣኔ አሳድጓል። በግንዛቤ ለዉጥ ማህበረሰቦች ከከብት ጭራ ጎታችነት ወደ አለም መሪነት ተራምደዋል፤ ከደመ ቀዝቃዛ ጭካኔ ወደ የእዝነት ተምሳሌትነት ደርሰዋል፤ ከጠባብ ጎሰኝነት ወደ ኢስላም አለማቀፋዊነት አድገዋል። በነዚህ ሁሉ ጊዜያት ኢስላም አመለካከትን በመግራት ያደረጋቸዉ ተምሳሌታዊ ተግባራት አስካሁን በአንጸባራቂነታቸዉ አቻ ያልተገኘላቸዉን የሰላም ቅርሶች ጥሎ አልፉል። ሙስሊሞች በእየሩሳሌም የሚገኘዉን የአቅሳ መስጅድ ከተቆጣጠሩ በኃል በጊዜዉ ይዘዉት የነበሩት የክርስትና እምነት ተከታይ ቄሶች የአቅሳ መስጂድን ቁልፍ ለመሪያችሁ እንጂ አንሰጥም ባሉ ጊዜ ሁለተኛዉ የኢስላም መሪ /ከሊፋ/ ተብለው የሚታወቁት ኢመር ኢብኑል ከጣብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከመዲና እስከ እየሩሳሌም በመጓዝ ነበር የተቀበሏቸዉ። ሊቀበሏቸዉ በሄዱበት አጋጣሚ እንኳ እዚህ እኛ ማምለኪያ ቦታ (ቤተመቅደስ) ገብተው ስገዱ ብለዉ ሲጋብዟቸው ኡመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸው እዚህ ዉጭ ብሰግድ ይሻላል ከኔ በኃላ የሚመጡ ኡመር ሰግዶበታል እና እንስገድበት ባለመብቶች ነን እንዳይሉ እሰጋለሁና ብለው ነበር የመለሱላቸዉ። በጦርነት ያሸነፈ ጦር ቁልፍ ለመረከብ ሲደራደር በአለም ታሪክ የመጀመሪያዉ ይሆናል። በማስከተልም የኡመር ዘመን ተሻጋሪ አመለካከት ታሪክ ዝንተ አለም ሲያስታዉሰዉ ይኖራል። ይህን የዑመርን የአስተዳደር ዘመን አስመልክቶ የህንድ ነጻነት የጀርባ አጥንት የነበሩት ማህተመ ጋንዲ እንዲ ይላሉ፦ “አለም መመራት ያለባት እንደ ዑመር ባሉ ስብእናዎች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።”

ሰላም ቀጥተኛዉን መንገድ ለተከተሉ ብሉም ለሰዉ ልጆች ሁሉ ይስፈን! አሚን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here