የመጨረሻው ቀን (የውሙል ቂያማህ) ክፍል-1

0
5603

በመጨረሻው ቀን ማመን ከእምነት ማእዘናት አንዱ ስለመሆኑ

በመጨረሻው ቀን ማመን ከእምነት ማእዘናት መካከል አንዱ ሲሆን ከትክክለኛው የእምነት አመለካከት/ዐቂዳ/ ክፍልም ይመደባል፡፡ እንዲያውም በአላህ ማመንን ተከትሎ የሚመጣ እጅግ ወሣኝና ዋናው የእምነት ቅርንጫፍ ነው ማለትም ይቻላል፡፡

ለምን ከተባለ በአላህ ማመን የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ የመጀመሪያ ምንጭ የሆነውን ፈጣሪ ለማወቅ ያግዛል፡፡ በመጨረሻው ቀን ማመን ደግሞ የዚህን ፍጥረተዓለም መጨረሻ ለማወቅ ወደሚያግዝ እውቀት ይመራል፡፡

መነሻና መመለሻውን በትክክል ያወቀ እንደሆነ የሰው ልጅ ዓላማውን ይወስናል፣ ግቡንም መንደፍና ወደዚህ ግብና ዓላማ የሚያደርሱትንም አስፈላጊ ግብኣቶች ሁሉ መያዝ ያስችለዋል፡፡ የሰው ልጅ ስለ መጨረሻው አገር መኖር እውቀት ያጣ እንደሆነ ግን ህይወቱ ዓላማ አልባ ትሆናለች ግቡም ባዶና ዋጋቢስ ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ መሄጃውን እንኳ የማያውቅ ተጓዥ እንደሆነ መንፈሣዊ ብልፅግናውንና ላቅ ያለ ክብሩን ያጣል፤ እንሠሳት እንደሚኖሩትም ይኖራል፡፡ የሚመራው አእምሮው ሣይሆን የተፈጠረበት ስሜቱ ብቻ ነው፡፡ ይህም አካሄድ የሰውን ልጅ ስብእና ለአስከፊ ውድቀት የሚዳርግ ግልጽ የሆነ መንፈሣዊ ክስረት ነው፡፡

የሰው ልጅ ለቀልድ አልተፈጠረም

በተከበረው ቁርኣኑ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እኛን የሰው ልጆችን ለትልቅ ዓላማና ክቡር ለሆነ ግብ እንደፈጠረን ነግሮናል፡፡ ይህም ከፈጣሪያችን የተሟላ ከሆነ ቅድስናውና ከላቀ ጥበቡ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ. አንድን ነገር ሲሠራ አሊያም ሲፈጥር የራሱ የሆነ ዓላማና ጥበብ አለውና፡፡

አላህ ሱ.ወ የሰውን ልጅ በእጁ የፈጠረው፣ ከመንፈሱም የነፋበት፣ በመላእክቶችም ላይ ያስበለጠው፣ በሰማይና በምድር መካከል ያሉትን ነገሮች ሁሉ ያገራለትና የፍጥረተዓለሙ ሁሉ ንጉስም ያደረገው ያለ ዓላማና ግብ አይደለም፡፡  ይህ በርግጥም ለአላህ ሱ.ወ የማይገባ የሆነ ተራ ቀልድ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

لَوْ أَرَدْنَا أَن نَّتَّخِذَ لَهْوًا لَّاتَّخَذْنَاهُ مِن لَّدُنَّا إِن كُنَّا فَاعِلِينَ

 ‹‹ሰማይንና ምድርን በመካከላቸው ያለውን ሁሉ ቀላጆች ሆነን አልፈጠርንም›› (አል አንቢያእ፤16)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅም

أَفَحَسِبْتُمْ أَنَّمَا خَلَقْنَاكُمْ عَبَثًا وَأَنَّكُمْ إِلَيْنَا لَا تُرْجَعُونَ
فَتَعَالَى اللَّهُ الْمَلِكُ الْحَقُّ ۖ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ رَبُّ الْعَرْشِ الْكَرِيمِ

«የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን?» (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?) የእውነቱም ንጉስ አላህ ከፍተኛነት ተገባው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ የሚያምረው ዐርሽ ጌታ ነው፡፡ (አል ሙእሚኑን፤115-116)

የሰው ልጅ ከአላህ ሱ.ወ ትልቅ ተልእኮ ተሠጥቶታል፡፡  ይህም በምድር ላይ ተተኪ ይሆን ዘንድ ከአላህ ሱ.ወ የተሾመ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ሀላፊነቱ ግዴታዎች ተጥለውበታል፡፡ በዚህ ዙሪያም ነገ አላህ ሱ.ወ ፊት ጥያቄ አለበት፡፡ የመፈጠር ዓላማ ይህ ነውና ከዚህ ውጭ ማሰብ ከእውነት መዞርና ጥመትን መምረጥ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

أَيَحْسَبُ الْإِنسَانُ أَن يُتْرَكَ سُدًى
أَلَمْ يَكُ نُطْفَةً مِّن مَّنِيٍّ يُمْنَىٰ
ثُمَّ كَانَ عَلَقَةً فَخَلَقَ فَسَوَّىٰ
فَجَعَلَ مِنْهُ الزَّوْجَيْنِ الذَّكَرَ وَالْأُنثَىٰ
أَلَيْسَ ذَٰلِكَ بِقَادِرٍ عَلَىٰ أَن يُحْيِيَ الْمَوْتَىٰ

ሰው ስድ ኾኖ መትተውን ይጠረጥራልን? የሚፈሰስ ከኾነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን? ከዚያም የረጋ ደም ኾነ (አላህ ሰው አድርጎ) ፈጠረውም፡፡ አስተካከለውም፡፡ ከእርሱም ሁለት ዓይነቶችን ወንድና ሴትን አደረገ፡፡ ይህ (ጌታ) ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ አይደለምን?(አል ቂያማህ፤36-40)

የመጨረሻው ቀን ምንነት

ይህ ያለንበት ዓለም ህይወት ጊዜያዊ ነው፡፡ እውነተኛውና ዘላለማዊ የሆነው የመጨረሻው ዓለም የሚጀመረው የዚህን ዓለም መፈራረስ ተከትሎ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ማብቂያ ላይ ማንኛውም ህይወት ያለው ነገር ሁሉ ይወድማል፡፡ በፍጥረተ ዓለሙም ውስጥ እንግዳና አዳዲስ ነገሮች ይከሠታሉ፤ ሰማይና ምድር እንዳልነበሩ ይሆናሉ ፡፡ በመጨረሻም አላህ ሱ.ወ. የአኺራን ህይወት በአዲስ መልክ ያስጀምራል፡፡ ሁሉንም የሰው ልጆች ዳግም ነፍስ ይዘራባቸውና ከመቃብራቸው ይቀሰቅሣቸዋል፡፡ ከመቀስቀስም በኋላ አላህ ሱ.ወ እያንዳንዱን ሰው በምድር ላይ ባሳለፈው መልካምና መጥፎ ሥራ ላይ ይመረምረዋል፡፡ ከመጥፎ ሥራው ይልቅ መልካምነቱ ሚዛን የደፋውን ጀነት ያስገባዋል፡፡ በተቃራኒው የሆነውን ደግሞ ከጥፋቱ ጋር በሚመጣጠን መልኩ በእሣት ይቀጣዋል፡፡

ቁርኣን በመጨረሻው ቀን ስለማመን የሠጠው አፅንኦት

ቁርኣን በመጨረሻው ቀን የማመኑን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሠጥቶታል፡፡ ይህንንም በሚከተሉት ሁኔታዎች ላይ እናስተውላለለን፡፡

 • አንደኛ፡ በአላህ ከማመን ጋር አስተሣስሮታል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَلَٰكِنَّ الْبِرَّ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ

‹‹ነገር ግን መልካምነት በአላህ ማመን በመጨረሻው ቀን ማመን…›› (አል በቀራህ፤177)

إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَالَّذِينَ هَادُوا وَالنَّصَارَىٰ وَالصَّابِئِينَ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَعَمِلَ صَالِحًا فَلَهُمْ أَجْرُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ وَلَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ

እነዚያ ያመኑ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ክርስቲያኖችም፣ ሳቢያኖችም (ከእነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡ (አል በቀራህ፤62)

 • ሁለተኛ፡ በእያንዳንዱ የቁርኣን ምእራፍ ውስጥ የተጠቀሠ እስኪመስል ድረስ ቁርኣን የመጨረሻ ቀንን  በብዛት አውስቶታል፡፡ አንዴ በመረጃና በማስረጃ ሌላ ጊዜ ደግሞ በምሣሌ የቀረበበት ሁኔታ ደግሞ ይበልጥ ለልቦና ቀርቦ እንዲታይ አድርጎታል፡፡
 • ሦስተኛ፡ የቁርኣንን አንቀፆች በአንክሮ የሚከታተል ሰው ለዚህ ታላቅ ቀን የተለያዩ ስያሜዎች እንደተሰጡት ይገነዘባል፡፡ እያንዳንዱ ስምም በዚያ ቀን ውስጥ የሚከሠተውን አስፈሪ ሁኔታ በሚገልፅ መልኩ ነው የተቀመጠው፡፡

ለቂያማ ቀን ከተሠጡ ስያሜዎች መካከል ከፊሎቹን እንቃኝ

 • የውሙል በዕስ / የመቀስቀስ ቀን/ በመባል ይታወቃል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَقَالَ الَّذِينَ أُوتُوا الْعِلْمَ وَالْإِيمَانَ لَقَدْ لَبِثْتُمْ فِي كِتَابِ اللَّهِ إِلَىٰ يَوْمِ الْبَعْثِ ۖ فَهَٰذَا يَوْمُ الْبَعْثِ وَلَٰكِنَّكُمْ كُنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ

እነዚያንም ዕውቀትንና እምነትን የተሰጡት «በአላህ መጽሐፍ (ፍርድ) እስከ ትንሣኤ ቀን በእርግጥ ቆያችሁ፡፡ ይህም (የካዳችሁት) የትንሣኤ ቀን ነው፡፡ ግን እናንተ የማታውቁ ነበራችሁ» ይሏቸዋል፡፡ (አር ሩም፤56)

 • የውሙል ቂያማህ /የትንሣኤ ቀን/ም ተብሏል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَيَوْمَ الْقِيَامَةِ تَرَى الَّذِينَ كَذَبُوا عَلَى اللَّهِ وُجُوهُهُم مُّسْوَدَّةٌ

በትንሣኤ ቀንም እነዚያን በአላህ ላይ የዋሹትን ፊቶቻቸው የጠቆሩ ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ በገሀነም ውስጥ ለትዕቢተኞች መኖሪያ የለምን?     (አዝ ዙመር፤60)

 • ሣኣህ /ወቅት/ ወይንም ጊዜም ይባላል፡፡ አላህ ሱ.ወ. እንዲህ አለ
اقْتَرَبَتِ السَّاعَةُ وَانشَقَّ الْقَمَرُ

ሰዓቲቱ (የትንሣኤ ቀን) ተቃረበች፤ ጨረቃም ተገመሰ፡፡ (አል ቀመር፤1)

 • አል ኣኺራህ /የመጨረሻው ቀን/ም ይባላል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

بَلْ تُؤْثِرُونَ الْحَيَاةَ الدُّنْيَا
وَالْآخِرَةُ خَيْرٌ وَأَبْقَىٰ

ይልቁንም ቅርቢቱን ሕይወት ትመርጣላችሁ፡፡ መጨረሻይቱ (ሕይወት) በላጭ ሁል ጊዜ ዘውታሪም ስትኾን፡፡ (አል አዕላ፤16-17)

 • የውመ ዲን /የፍርዱ ቀን/ ም ይባላል ፡፡አላህ ሱ.ወ እንዳለው
مَالِكِ يَوْمِ الدِّينِ

የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነው፡፡ (አል ፋቲሃ፤4)

 • የውመል ሂሳብ /የምርመራ ቀን/ በመባልም ይታወቃል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَقَالَ مُوسَىٰ إِنِّي عُذْتُ بِرَبِّي وَرَبِّكُم مِّن كُلِّ مُتَكَبِّرٍ لَّا يُؤْمِنُ بِيَوْمِ الْحِسَابِ

ሙሳም «እኔ በምርመራው ቀን ከማያምን ትዕቢተኛ ሁሉ በጌታዬና በጌታችሁ ተጠበቅሁ» አለ፡፡ (ጋፍር፤27)

 • የውመል ፈትህ/የድል ቀን /
قُلْ يَوْمَ الْفَتْحِ لَا يَنفَعُ الَّذِينَ كَفَرُوا إِيمَانُهُمْ وَلَا هُمْ يُنظَرُونَ

«በፍርድ ቀን እነዚያን የካዱትን ሰዎች እምነታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ እነርሱም ጊዜን አይሰጡም፤» በላቸው፡፡ (አስ ሰጅዳህ፤29)

 • የውመ ተላቅ/የመገናኛ ቀን / ይባላል፡፡ አላህ ሱ.ወ እዲህ አለ
رَفِيعُ الدَّرَجَاتِ ذُو الْعَرْشِ يُلْقِي الرُّوحَ مِنْ أَمْرِهِ عَلَىٰ مَن يَشَاءُ مِنْ عِبَادِهِ لِيُنذِرَ يَوْمَ التَّلَاقِ

(እርሱ) ደረጃዎችን ከፍ አድራጊ የዐርሹ ባለቤት ነው፡፡ የመገናኛውን ቀን ያስፈራራ ዘንድ ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ ከትዕዛዙ መንፈስን (ራእይን) ያወርዳል፡፡ እነርሱ (ከመቃብር) በሚወጡበት ቀን (ጋፍር፤15-16)

 • ‹የውመል ጀምዕ ወተጋቡን /የመሰብሰብ እና ቀን የመጎዳዳት/ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

يَوْمَ يَجْمَعُكُمْ لِيَوْمِ الْجَمْعِ ۖ ذَٰلِكَ يَوْمُ التَّغَابُنِ

ለመሰብሰቢያ ቀን የሚሰበስብባችሁን ቀን (አስታውሱ)፤ ይህ የመጎዳዳት (መግለጫ) ቀን ነው፡፡ (አት ተጋቡን፤9)

 • የውመል ኹሉድ/ የመዘውተሪያ ቀን/ስያሜው ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
ادْخُلُوهَا بِسَلَامٍ ۖ ذَٰلِكَ يَوْمُ الْخُلُودِ

«በሰላም ግቧት ይህ የመዘውተሪያ ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡ (ቋፍ፤34)

 • የውመል ኹሩጅ /የመውጫ ቀን/ ተብሏል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
يَوْمَ يَسْمَعُونَ الصَّيْحَةَ بِالْحَقِّ ۚ ذَٰلِكَ يَوْمُ الْخُرُوجِ

ጩኸቲቱን በእውነት የሚሰሙበት ቀን ያ (ከመቃብር) የመውጫው ቀን ነው፡፡ (ቋፍ፤42)

 • የውመል ሀስረህ /የቁጭት ቀን/ ተብሏል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
وَأَنذِرْهُمْ يَوْمَ الْحَسْرَةِ إِذْ قُضِيَ الْأَمْرُ وَهُمْ فِي غَفْلَةٍ وَهُمْ لَا يُؤْمِنُونَ

እነሱም (አሁን) በዝንጋቴ ላይ ኾነው ሳሉ እነሱም የማያምኑ ሲኾኑ ነገሩ በሚፈረድበት ጊዜ የቁልጭቱን ቀን አስፈራራቸው፡፡ (መርየም፤39)

 • የውመ ተናድ/የመጠራራት ቀን/ ፡፡ አላህ ሱወ. እንዲህ አለ
وَيَا قَوْمِ إِنِّي أَخَافُ عَلَيْكُمْ يَوْمَ التَّنَادِ

«ወገኖቼ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ የመጠራሪያን ቀን እፈራለሁ፡፡» (ጋፍር፤ 32)

 • አል ኣዚፋህ/ ቀራቢይቱ /
أَزِفَتِ الْآزِفَةُ
لَيْسَ لَهَا مِن دُونِ اللَّهِ كَاشِفَةٌ

ቀራቢይቱ (ኅልፈተ ዓለም) ቀረበች፡፡ ለእርሷ ከአላህ ሌላ ገላጭ የላትም፡፡ (አን ነጅም፤57-58)

 • አጥ ጧመህ / መዓት/ ትባላለች፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ

فَإِذَا جَاءَتِ الطَّامَّةُ الْكُبْرَىٰ
يَوْمَ يَتَذَكَّرُ الْإِنسَانُ مَا سَعَىٰ

ታላቂቱም መዐት በመጣች ጊዜ፣ሰው ሁሉ የሠራውን በሚያስታውስበት ቀን (አን ናዚዓት፤ 34-35 )
 • አስ ሷኸህ / አደንቋሪቱ / ተብላለች፡፡

فَإِذَا جَاءَتِ الصَّاخَّةُ
يَوْمَ يَفِرُّ الْمَرْءُ مِنْ أَخِيهِ
وَأُمِّهِ وَأَبِيهِ
وَصَاحِبَتِهِ وَبَنِيهِ
لِكُلِّ امْرِئٍ مِّنْهُمْ يَوْمَئِذٍ شَأْنٌ يُغْنِيهِ

አደንቋሪይቱም (መከራ) በመጣች ጊዜ፤ ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፤ ከናቱም ካባቱም፤ ከሚስቱም ከልጁም፤ ከእነርሱ ለየሰው ሁሉ በዚያ ቀን (ከሌላው) የሚያብቃቃው ኹነታ አልለው፡፡ (ዐበስ፤33-37)

 • አል ሃቅቀህ /እውነትን አረጋጋጪቱ / ተብላለች፡፡ አላ ሱ.ወ እንዲህ አለ
الْحَاقَّةُ
مَا الْحَاقَّةُ

እውነትን አረጋጋጪቱ (ትንሣኤ)፡፡አረጋጋጪቱም (እርሷ) ምንድን ናት! (አል ሃቀህ፤ 1-2)

 • አል ጋሺያህ / ሸፋኚቱ/ ሌላ ስሟ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
هَلْ أَتَاكَ حَدِيثُ الْغَاشِيَةِ

የሸፋኝቱ (ትንሣኤ) ወሬ መጣህን?(አል ጋሺያህ፤1)

 • አል ዋቂዓህ /የመከሠቻዋ ቀንም/ ተብሏል፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ አለ
إِذَا وَقَعَتِ الْوَاقِعَةُ

መከራይቱ በወደቀች ጊዜ፡፡ ለመውደቋ አስተባባይ (ነፍስ) የለችም፡፡ ዝቅ አድራጊና ከፍ አድራጊ ናት፡፡ (አል ዋቂዓህ፤1-3)

 ……..(ይቀጥላል)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here