መልእክተኞች (ክፍል 4)

0
3029

ከመልእክተኞች እጅግ ፅኑዎቹ /ኡሉል ዐዝም/

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

فَاصْبِرْ كَمَا صَبَرَ أُولُو الْعَزْمِ مِنَ الرُّسُلِ

“ከመልክተኞችም የቆራጥነት ባለቤቶች የኾኑት እንደ ታገሱ ሁሉ ታገስ።” (አል አህቃፍ 46፤ 35)

“ኡሉል ዐዝም” ማለት ሁሉም የአላህ መልእክተኞች ናቸው ያሉ አሉ።

ሆኖም ግን ስለ ኡሉል ዐዝም ከተባሉት ሁሉ ሚዛን የሚደፋው እነሱ ሙሀመድ፣ ኑህ፣ ኢብራሂም፣ ሙሣና ዒሣ መሆናቸውን ነው፤ በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትና ሠላም ይውረድ።

ኡሉል ዐዝሞችን አላህ (ሱ.ወ) ከሌሎች መልእክተኞች ለይቶ በሁለት የቁርኣን አንቀፆች ላይ ሥማቸውን ጠቅሷል።

አንደኛው

وَإِذْ أَخَذْنَا مِنَ النَّبِيِّينَ مِيثَاقَهُمْ وَمِنكَ وَمِن نُّوحٍ وَإِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَى ابْنِ مَرْيَمَ ۖ وَأَخَذْنَا مِنْهُم مِّيثَاقًا غَلِيظًا

“ከነቢዮችም የጠበቀ ኪዳናቸውን ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሒምም፣ ከሙሳም ከመርየም ልጅ ዒሳም በያዝን ጊዜ (አስታወስ)። ከእነርሱም የከበደን ቃል ኪዳን ያዝን።” (አል-አህዛብ 33፤ 7)

የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ

شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَىٰ ۖ أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ። ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)።” (አሽ-ሹራ 42፤ 13)

ከመልእክተኞች በላጩ

ከመልእክተኞች ሁሉ በላጩ ታላቁና የመጨረሻው ነቢይ የሆኑት ነቢያችን ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

تِلْكَ الرُّسُلُ فَضَّلْنَا بَعْضَهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ ۘ مِّنْهُم مَّن كَلَّمَ اللَّهُ ۖ وَرَفَعَ بَعْضَهُمْ دَرَجَاتٍ ۚ وَآتَيْنَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ الْبَيِّنَاتِ وَأَيَّدْنَاهُ بِرُوحِ الْقُدُسِ

“እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን። ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ። ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ። የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው። በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው።” (አል-በቀራህ 2፤ 253)

አላህ ደረጃቸውን ከፍ ያደረገው ሰይዳችን /አለቃችን/ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው።

ለዚህም ትልቁ ማስረጃ በኣሊ ዒምራን ምእራፍ ላይ የተጠቀሰው ነቢያትን በሱ መምጣት የሚያበስረውና መላካቸውን የደረሱበት እንደሆነ በሱ ያምኑና ይረዱትም ዘንድ ከነሱ ቃል ኪዳን መወሰዱ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُم مِّن كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ ثُمَّ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مُّصَدِّقٌ لِّمَا مَعَكُمْ لَتُؤْمِنُنَّ بِهِ وَلَتَنصُرُنَّهُ ۚ قَالَ أَأَقْرَرْتُمْ وَأَخَذْتُمْ عَلَىٰ ذَٰلِكُمْ إِصْرِي ۖ قَالُوا أَقْرَرْنَا ۚ قَالَ فَاشْهَدُوا وَأَنَا مَعَكُم مِّنَ الشَّاهِدِينَ

“አላህ የነቢያትን ቃል ኪዳን ከመጽሐፍና ከጥበብ ሰጥቻችሁ ከዚያም ‘ከእናንተ ጋር ላለው (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ መልክተኛ ቢመጣላችሁ በርሱ በእርግጥ እንደምታምኑበት በእርግጥም እንድትረዱት ሲል በያዘ ጊዜ (አስታውስ)። አረጋገጣችሁን? በዚህም ላይ ኪዳኔን ያዛችሁምን?’ አላቸው። ‘አረጋገጥን’ አሉ። ‘እንግዲያስ መስክሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከመስካሪዎቹ ነኝ’ አላቸው።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 81)

ከጃቢር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

والله لو كان موسى حيًا بين أظهركم ما حل له إلا أن يتبعنى

“ወላሂ ሙሣ በመካከላችሁ በህይወት ያለ ቢሆን እኔን ከመከተል ውጭ አማራጭ አይኖረውም።” ብለዋል

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) “በአላህ ነቢያት መካከል አታበላልጡ” የማለታቸው አንደኛው ትርጉሙ- እነሱን በማክበር ደረጃ ድንበር አትለፉ ማለት ሲሆን ሁለተኛው ትርጉም ደግሞ ሙስሊሞች ወንድማማች የሆኑትን ነቢያት አንዱን ከሌላኛው ያነሠ አድርገው እንዳይመለከቱና ደረጃቸውን ዝቅ እንዳያደርጉ ለማሣሰብ ነው።

የነቢይነትና የመልእክተኛነት መቋጨት

የነቢያት ሁሉ ዓላማ የሰው ልጆችን ከጥፋት ሁሉ ማዳንና ከጨለማዎችም ወደ ብርሃን መንገድ ማምጣት ነው። ነቢያት የሁልጊዜም ሥራቸው ወደ መልካም ነገር መጥራት ነበር። የቅን መንገድ መሪዎችና በጨለማዋ ምድርም የብርሃን ተሸካሚዎች እነሱ ናቸው። ከአንደኛው ማለፍ በኋላ ሌላኛው ነቢይ ተከትሎት የሚመጣበት ሚስጢር ወንድሙ የጀመረውን የሰው ልጆችን የማስተካከል ግንባታ ለመቀጠልና ይበልጥ በማሣመርም ግንባታውን ለማጠናቀቅ ነው። በመጨረሻም ግንባታው በመጨረሻው ነቢይ ነቢያችን ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) አማካኝነት ፍፃሜ አገኘ። የርሣቸው ሃይማኖት የቀደሙትን ሃይማኖቶች ሁሉ የያዘ ጥቅል የሆነ መልእክት ነው። ጥሪያቸውም የሰው ልጅ የህይወት ክፍልን ሁሉ የሚያካትት ሲሆን የለውጥና የህዳሴ መሰረቶችን ያዘለ ዘላለማዊ ጥሪ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا 

“ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ። ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ።”          (አል-ማኢዳህ 5፤ 3)

እውነተኛውን የአላህን ዲን በማሟላት ውጤቱ መስተካከል የሆነው የአላህ ፀጋ በሰዎች ላይ ተሟላ። ከዚህ በኋላ የማስተካከል ሥራ አይኖርም። በዚህም የነቢይነት ሂደቱ ተቋረጠ መልእክቱም መቋጫ አገኘ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِّن رِّجَالِكُمْ وَلَٰكِن رَّسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ

“ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም። ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው።” (አል-አህዛብ 33፤ 40)

ነቢይነት በመቋረጡ ምክኒያት የሰማይ የወህይ /የራእይ/ መልእክቱም ተቋረጠ። ነቢይነትም መልእክተኝነትም ከርሣቸው በኋላ አይኖርም። እርሣቸውም ይህንኑ በማስመልከት እንዲህ ብለዋል

مثلى ومثل الأنبياء كمثل رجل بنى دارًا، فأكملها وأحسنها إلا موضع لبنة، فكان من دخلها، فنظر إليها قال: ما أحسنها إلا موضع هذه اللبنة، فـأنا موضع اللبنة، خُتم بى الأنبياء عليهم الصلاة والسلام

“የኔና የነቢያት አምሣያ እንደ አንድ ቤት የሠራ ሰው ነው፤ አንዲት ክፍተት ብቻ ስትቀር ቤቱን ሰርቶና አሣምሮ አጠናነቀቀ። ወደዚህች ቤት የገባ ሰውም ወደቤቱ በመመልከት ‘ይህች ክፍተት ባትቀር ኖሮ እንዴት ያምር ነበር!’ ይላል። እኔ የዚያች ክፍተት መዝጊያ ነኝ። በኔ ነቢያት (መላካቸው) አከተመ። በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትና ሠላም ይውረድና”

የነቢያችንን ስኬት የሚያመለክቱ ታላላቅ ስራዎቻቸው

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ወደ አላህ መንገድ ባደረጉት ጥሪ እጅግ የተሣካላቸው ነቢይ ስለመሆናቸው የሚመሰክሩ ግዙፍ የሆኑ ሥራዎች አሏቸው። እነኚህን በርካታ ተግባራት በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።

  • አንደኛ– በጣኦት አምልኮ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዐረቡ ዓለም ተነቅሎ እንዲጠፋ አድርገዋል። በምትካቸውም በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ማመንን ተክለዋል።
  • ሁለተኛ– በጃሂሊያ ከንቱ አስተሣሰብና በአስነዋሪ ልማዶች ላይ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ በምትኩ በላጭ ሥነምግባራትንና ምርጥ ሥርኣቶችን አኑረዋል።
  • ሦስተኛ– የሰውን ልጅ ወደ ምሉእነት የሚያቃርበውን እውነተኛ ሃይማኖት በምድር ላይ ተክለዋል።
  • አራተኛ– ትልቅ አብዮት በማካሄድ ነባራዊ ሁኔታዎችን፣ አስተሣሰቦችን፣ አመለካከቶችን፣ የጃሂሊያ ሰዎች የኖሩበትን፣ ያደጉበትንና ያረጁበትን የህይወት መስመር ሙሉ ለሙሉ ለውጠዋል።
  • አምስተኛ– የአረብ ህዝቦችን አንድ በማድረግ በቁርኣን ጥላ ሥር ታላቅ መንግስት መሥርተዋል።

እነኚህ በጥቂቱ የመልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ስኬት የሚያመላክቱ ሥራዎቻቸው ሲሆኑ እነኚህ ሁሉ ለማሣካትም ሆነ ለመከወን አስቸጋሪ የሆኑ ትላልቅ ጉዳዮች ናቸው። በተለይ የነበሩበትን ተጨበጭ ሁኔታ አደገኛነት አንፃር ስናይ አንዱን እንኳን ማሣካት በእጅጉ የሚከብድበት ሁኔታ ነው የነበረው። አንድ ሰው ነገሮች ሁሉ የተመቻቹለት ቢሆን እንኳ ከነኚህ ነገሮች ከፊሉን እንኳን ማሣካት ይከብደዋል።

በነኚህ ሥራዎች ተንቀሣቅሦ በዚህ መልኩ ስኬትን ማግኘት ከታላቁ ነቢይ ታላላቅ ተዓምራቶች መካከል ነው። ዒሣ (ዐ.ሠ) የሞተ ሰውን የመቀስቀስ፣ ሙሣ (ዐ.ሠ) ደግሞ ወደ እባብነት የምትቀየር ዱላ እንደ ተዓምር ከአላህ ዘንድ ተሠጥቶኣቸው የነበረ ቢሆንም እነኚህ ሁለቱ ተዓምራቶች ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ድል አንፃር የሚስተካከሉ አሊያም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም።

ስለ እውነትነታቸው የሚያመላክቱ ማስረጃዎች

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከአላህ (ሱ.ወ) መላካቸው እውነት መሆኑን ከሚያመላክቱ ማስረጃዎች መካከል፡-

አንደኛ፡- በምድር ላይ ኑሮአቸው ወቅት ለዚህች ዓለም ጥቅም ሲበዛ ግዴለሽ /ዛሂድ/ ነበሩ። በሥራቸው ከሌሎች ምንዳ የሚጠይቁ አልነበሩም። ስለ ገንዘብም ሆነ ስለ ሌሎች ቁሳዊ ነገሮች ግድ አልነበራቸውም። ለሥልጣንም ሆነ ስለ ክብራቸው የሚጨነቁ አልነበሩም።

ስለ ገንዘብ ግየለሽ መሆናቸውን ከኑሮ ሁኔታቸው መረዳት እንችላለን። አንድም ቀን ለስላሣ ሀር ላይ ተኝተው አያውቁም። የሱፍ ልብስም አልለበሱም። በወርቅ ጌጥም ተጊጠው አያውቁም። ቤታቸው ከቤቶች ሁሉ እጅግ ቀለል ያለና የተናነሠ ነው። በቤታቸውም ውስጥ ለምግብ ማብሠያ እሣት ሣይቀጣጠል ድፍን ሁለት ወራቶች ያልፉ ነበር። ዑርዋህ ከአክስቱ ዓኢሻ ስታወራ ሰምቶ እንደዘገበው “አክስቴ ሆይ! በምንድነው የምትኖሩት? አላት። እሷም ‘በሁለት ጥቋቁር ነገሮች- በውሃና በተምር’ አለችው።”

አንድ ቀን ዑመር ኢብኑልኸጧብ (ረ.ዐ) የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በተቀዳደደ አሮጌ ሠሌን ልይ ሲተኙ አገኛቸው፤ የሰሌኑም ቅርፅ ጀርባቸው ላይ ቀርቶ ነበር። ዑመር ይህን በማየት አለቀሱ። የአላህ መልእከተኛም (ሰ.ዐ.ወ)

ما يبكيك ؟ فقال: ما بال كسرى وقيصر ينامان على الديباج والحرير، وأنت رسول الله يؤثر فى جنبك الحصير، فقال صلى الله عليه وسلم: يا عمر، أما ترضى أن تكون لهم الدنيا ولنا الآخرة ؟

“ ‘ምን ያስለቅስሃል?’ አሉት። ዑመርም ‘ኪስራና ቀይሰር የፋርስና የሩም ነገስታት በሱፍ እና በሀር ላይ ይተኛሉ፤ አንቱ ግን የተከበሩ የአላህ መልእክተኛ ሆነው የሰሌን ቅርፅ በጀርባዎ ላይ ያታያል!’ አላቸው። እርሣቸውም ‘ዑመር ሆይ! ለነሱ ይህች የቅርቢቱ ዓለም ለኛ ደግሞ ያ የመጨረሻው ዓለም እንዲሆን አትወድምን!’ አሉት።”

በአንድ ወቅት ሙስሊሞች በጦርነት ድል ካደረጉ በኋላ የምርኮ ንብረት ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣ። ሚስቶቻቸው ከዚህ ከመጣው ሀብት የተወሰነውን ቢያቋድሷቸውና ለነሱም የተወሰነ ድርሻ እንዲሠጣቸው ጠየቁ። ለነኚህ ሴቶች ጥያቄ መልስ የተሠጠው ቀጥሎ ባለው የቁርኣን አንቀፅ ነበር። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ إِن كُنتُنَّ تُرِدْنَ الْحَيَاةَ الدُّنْيَا وَزِينَتَهَا فَتَعَالَيْنَ أُمَتِّعْكُنَّ وَأُسَرِّحْكُنَّ سَرَاحًا جَمِيلًا
وَإِن كُنتُنَّ تُرِدْنَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَالدَّارَ الْآخِرَةَ فَإِنَّ اللَّهَ أَعَدَّ لِلْمُحْسِنَاتِ مِنكُنَّ أَجْرًا عَظِيمًا

“አንተ ነቢይ ሆይ! ለሚስቶችህ (እንዲህ) በላቸው- ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጧን የምትፈልጉ እንደ ሆናችሁ ኑ፤ አጣቅማችኋለሁና። መልካምንም ማሰማራት (በመፍታት) አሰማራችኋለሁና። አላህንና መልክተኛውን የመጨረሻይቱን አገርም የምትፈልጉ ብትሆኑም፤ እነሆ አላህ ከእናንተ ለመልካም ሠሪዎቹ ትልቅን ምንዳ አዘጋጅቷል።” (አል-አህዛብ 33፤ 28-29)

ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶቻቸውን ሰበሰቡና እንዲህ አሏቸው

هل تردن الله ورسوله والدار الآخرة؟ أم تردن الدنيا وشهواتها؟

“አላህን መልእክተኛውንና የመጨረሻውን አገር ትፈልጋላችሁ ወይንስ ይህችን የቅርቢቱን ዓለምና ስሜቶቿን?” አሏቸው።

ሁሉም ሴቶች በአንድ ድምጽ አላህን መልእክተኛውንና የመጨረሻውን አገር መረጡ። በዚህም አድራጎታቸው ተወደሱ። ለጠየቁትም ጥያቄ ቁርኣን በሚከተለው መልኩ መልስ ሠጠ።

يَا نِسَاءَ النَّبِيِّ لَسْتُنَّ كَأَحَدٍ مِّنَ النِّسَاءِ ۚ إِنِ اتَّقَيْتُنَّ فَلَا تَخْضَعْنَ بِالْقَوْلِ فَيَطْمَعَ الَّذِي فِي قَلْبِهِ مَرَضٌ وَقُلْنَ قَوْلًا مَّعْرُوفًا

“የነቢዩ ሴቶች ሆይ! ከሴቶች እንደማናቸው አይደላችሁም። አላህን ብትፈሩ (ትበልጣላችሁ)። ያ በልቡ ውስጥ በሽታ ያለበት እንዳይከጅል በንግግር አትለስልሱም። መልካምንም ንግግር ተናገሩ።” (አል-አህዛብ 33፤ 32)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህችን ዓለም ሲሠናበቱ የጦር ልብሣቸው (ጠሩራቸው) አንድ ይሁዲ ዘንድ ተይዞ ነበር። ህይወታቸውን በሙሉ አንድም ቀን የገብስ ቂጣ እንኳን በልተው ጠግበው አያውቁም ነበር።

ክብርን አለመፈለጋቸው የሁልጊዜም ባህሪያቸው ነበር። ሰሃቦች ሊያወድሷቸውና ሊያጠሯቸው ሲፈልጉ እርሣቸው ግን

لا تطرونى كما أطرت النصارى المسيح بن مريم

“ክርስቲያኖች የመርየም ልጅ አል-መሲህን /ዒሣን/ እንዳጠሩት አታጥራሩኝ።” አሏቸው።

አል-ወሊድ ኢብኑ አልሙጊራ በአንድ ወቅት የመካ ሙሽሪኮችን በመወከል ለድርድር እርሣቸው ዘንድ መጣ። የዚህችን ዓለም ጥቅም ሁሉ ሊሰጣቸው ቃል ገባላቸው። እርሣቸው ግን ከቁርኣን የፉሲለት ምእራፍ የመጀመሪዎቹን አንቀፆች አነበቡለት። ስለ ዓለማዊ ጥቅም ግድየለሽነታቸው ይህን ይመስል ነበር።

ሁለተኛ – የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የማይፅፉ የማያነቡ /ኡምሚይ/ ነቢይ ነበሩ። እነኚህን ትላልቅ ስኬቶች ያስመዘገቡት ነቢይ መፃፍ ማንበብ የማይችሉ፣ ት/ቤት ያልገቡ፣ አስተማሪ ያልነበራቸው ቢሆንም እጅግ ተሳክቶላቸዋል። ከርሣቸው በፊትም ሆነ በኋላ ማንም ያልደረሠበት ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሠዋል።

ቁርኣንም ለእውነተኛነታቸውና ለታማኝነታቸው ማስረጃ ይሆን ዘንድ ይህንን እውነታ መዝግቦታል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَكَذَٰلِكَ أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ رُوحًا مِّنْ أَمْرِنَا ۚ مَا كُنتَ تَدْرِي مَا الْكِتَابُ وَلَا الْإِيمَانُ وَلَٰكِن جَعَلْنَاهُ نُورًا نَّهْدِي بِهِ مَن نَّشَاءُ مِنْ عِبَادِنَا ۚ وَإِنَّكَ لَتَهْدِي إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ
صِرَاطِ اللَّهِ الَّذِي لَهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ ۗ أَلَا إِلَى اللَّهِ تَصِيرُ الْأُمُورُ

“እንደዚሁም ወደ አንተ ከትእዛዛችን ሲኾን መንፈስን (ቁርኣንን) አወረድን። መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደኾነ የምታውቅ አልነበርክም። ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በእርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው። አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ትመራለህ። ወደዚያ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ወደ ኾነው አላህ መንገድ (ትመራለህ)። ንቁ! ነገሮቹ ሁሉ ወደ አላህ ይመለሳሉ።”        (አሽ-ሹራ 42፤ 52-53)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከመላካቸው በፊት ነቢይነት እራሱ ምን እንደሆነ መረጃ የሌላቸው፤ ከላይኛው የዓለም ክፍል ጋርም ግንኙነት ያልነበራቸው ነበሩ። ይህ ሆኖ ሣለ እነኚህ ድርጊቶች ሁሉ በእጃቸው ላይ መፈፀማቸው ታላቅ ግርምትን የሚያጭር ነው። ሆነ ብለው ለትምህርትና ለምርምር ብቻ ጊዜቸውን የሰው ሰዎች እንኳን ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያስመዘገቡትን ዓይነት ስኬት ማስመዝገብ ፈፅሞ አይቻላቸውም።

ይህ በርግጥም ልቅናው ከፍ ያለ ጌታ የአላህ (ሱ.ወ) እገዛና ተውፊቅ ያለበት ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ቁርኣን እንዲህ ይላል

وَمَا كُنتَ تَتْلُو مِن قَبْلِهِ مِن كِتَابٍ وَلَا تَخُطُّهُ بِيَمِينِكَ ۖ إِذًا لَّارْتَابَ الْمُبْطِلُونَ

“ከእርሱ በፊትም መጽሐፍን የምታነብ በቀኝህም የምትጽፈው አልነበርክም። ያን ጊዜ አጥፊዎቹ በእርግጥ በተጠራጠሩ ነበር።”            (አል-ዐንከቡት 29፤ 48)

ይህንን ጉዳይ ባላንጣዎቻቸው ጭምር ያውቁ እርሣቸው በነኚህ በተሠጣቸው ተኣምራቶች ይሟገቷቸው ነበር። ታዲያ ይህን ግልፅ እውነት የሚጠራጠር አንድም ሰው አልነበረም። ከማመን የከለከላቸውም ኩራት እንጂ ሌላ አይደለም። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَإِذَا تُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ آيَاتُنَا بَيِّنَاتٍ ۙ قَالَ الَّذِينَ لَا يَرْجُونَ لِقَاءَنَا ائْتِ بِقُرْآنٍ غَيْرِ هَٰذَا أَوْ بَدِّلْهُ ۚ قُلْ مَا يَكُونُ لِي أَنْ أُبَدِّلَهُ مِن تِلْقَاءِ نَفْسِي ۖ إِنْ أَتَّبِعُ إِلَّا مَا يُوحَىٰ إِلَيَّ ۖ إِنِّي أَخَافُ إِنْ عَصَيْتُ رَبِّي عَذَابَ يَوْمٍ عَظِيمٍ
قُل لَّوْ شَاءَ اللَّهُ مَا تَلَوْتُهُ عَلَيْكُمْ وَلَا أَدْرَاكُم بِهِ ۖ فَقَدْ لَبِثْتُ فِيكُمْ عُمُرًا مِّن قَبْلِهِ ۚ أَفَلَا تَعْقِلُونَ

“አንቀጾቻችንም ግልጽ ኾነው በእነርሱ ላይ በተነበቡላቸው ጊዜ እነዚያ መገናኘታችንን የማይፈሩት ከዚህ ሌላ የሆነን ቁርኣን አምጣልን ወይም ለውጠው ይላሉ። እኔ ከራሴ በኩል ልለውጠው አይገባኝም። ወደእኔ የሚወርደውን እንጂ አልከተልም። እኔ ከጌታዬ ባምጽ የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ በላቸው። አላህ በሻ ኖሮ በእናንተ ላይ ባለነበብኩትም (አላህ) እርሱን ባላሳወቃችሁም ነበር። በእናንተም ውስጥ ከእርሱ በፊት (ምንም ሳልል) ብዙን ዕድሜ በእርግጥ ኖሬአለሁ፤ አታውቁምን?” (ዩኑስ 10፤ 15-16)

ሦስተኛ– ሁሌም እውነትን መናገራቸው።

ከመላካቸው በፊትም ሆነ በኋላ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንድም ቀን ዋሽተው አያውቁም። መለኮታዊው ራእይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣባቸው ለነገሩ እንግዳ በመሆናቸው ተደናግጠው ወደ ባለቤታቸው ኸዲጃ ዘንድ በመምጣት “በነፍሴ ላይ ፈርቻለሁ” አሏት። እሷም “አይሆንም! አላህ ፈፅሞ አያዋርድህም አንተ እውነት ተናጋሪ ነህ፣ ዝምድናን ትቀጥላለህ፣ አደራን ትሸከማለህ፣ እንግዳን ታሣርፋለህ፣ ለሌለው ትሠጣለህ፣ ጊዜ በሚያመጣው ችግር ላይ ታግዛለህ።” በማለት አረጋጋቻቸው።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በኢስላም የነቢይነትን ተልእኮ እንደጀመሩ ለአቡበከር ነበር እንዲያምንባቸውና እንዲቀበላቸው የነገሩት። አቡበክርም ወዲያው በመጀመሪያው ጥሪያቸው ነበር ያመናቸው። ከዚያ በኋላም ላይ ቢሆን በሚናገሩት ሁሉ ከማመን ወደ ኋላ አላለም። እውነተኛ መሆናቸውንና ታማኝነታቸውን ያውቅ ነበርና። በአንድ ወቅት ስለ ሃይማኖት ጉዳይ ምንም የማያውቅ አንድ የገጠር ሰው እርሣቸው ወዳሉበት ገባ። እንዳያቸውም የእውነት ድባብ አነበባቸው። ወዲያውም “ይህ የውሸታም ፊት አይደለም” በማለትም መሠከረ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here