መልእክተኞች (ክፍል 2)

0
3870

መልእክተኞች የተላኩበት ምክኒያት

አላህ መልእክተኞችን የላከበት ዋና ዓላማ ወደ አላህ አምልኮ መንገድ እንዲጠሩና ሃይማኖቱንም በምድር ላይ ያቆሙ ዘንድ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ

“ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (አል-አንቢያእ 21፤ 25)

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ

“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ ‘አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ’ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል።” (አን-ነህል 16፤ 36)

شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَىٰ ۖ أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ 

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ። ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)።” (አሽ-ሹራ 42፤ 13)

ሃይማኖትን ማቆምና አላህን መገዛት፤ በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመፅሃፎቹ፣ በመልእክተኞቹና በመጨረሻው ቀን የማመኑን ነገር መስመር ያስይዘዋል። መልካም ሥራዎችም እንዲሁ የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ላይ እስካለ ድረስ በቁሣዊም ሆነ በሥነምግባር ሥርኣቱ የመጠቀና የፀና እንዲሆን ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አላቸው። ነፍሱን ያጠራሉ፣ በውስጡም የበጎነትን አስተሣሰብ ይተክላሉ፣ ሕይወቱንም የተስተካከለ እንዲሆን ያደርጋሉ።

ይህን ታላቅ የሆነ መለኮታዊ ትምህርት ሰዎች በአእምሮአቸው ሊደርሱበት አይቻላቸውም። ትምህርቱ የሚገኘው ከአላህ (ሱ.ወ) በሆነ መለኮታዊ ራእይ ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

هُوَ الَّذِي بَعَثَ فِي الْأُمِّيِّينَ رَسُولًا مِّنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِهِ وَيُزَكِّيهِمْ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَإِن كَانُوا مِن قَبْلُ لَفِي ضَلَالٍ مُّبِينٍ

“እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርኣንን) በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከእነርሱው ውስጥ የላከ ነው። እነርሱም ከእርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ።” (አል-ጁሙዓ 62፤ 2)

በዚህም የተነሣ አላህ (ሱ.ወ) ቀልቡን ከዚክሩ ያዘናጋው፣ ስሜቱን የተከተለና ጉዳዩም ድንበር አላፊ የሆነው ሰው ማስረጃ ዋጋ ታጣለች። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

إِنَّا أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ كَمَا أَوْحَيْنَا إِلَىٰ نُوحٍ وَالنَّبِيِّينَ مِن بَعْدِهِ ۚ وَأَوْحَيْنَا إِلَىٰ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ وَإِسْحَاقَ وَيَعْقُوبَ وَالْأَسْبَاطِ وَعِيسَىٰ وَأَيُّوبَ وَيُونُسَ وَهَارُونَ وَسُلَيْمَانَ ۚ وَآتَيْنَا دَاوُودَ زَبُورًا
وَرُسُلًا قَدْ قَصَصْنَاهُمْ عَلَيْكَ مِن قَبْلُ وَرُسُلًا لَّمْ نَقْصُصْهُمْ عَلَيْكَ ۚ وَكَلَّمَ اللَّهُ مُوسَىٰ تَكْلِيمًا
رُّسُلًا مُّبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ لِئَلَّا يَكُونَ لِلنَّاسِ عَلَى اللَّهِ حُجَّةٌ بَعْدَ الرُّسُلِ ۚ وَكَانَ اللَّهُ عَزِيزًا حَكِيمًا

“እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን ወደ አንተም አወረድን። ወደ ኢብራሂምም፣ ወደ ኢስማዒልም፣ ወደ ኢስሓቅም፣ ወደ ያዕቆብም፣ ወደ ነገዶቹም፣ ወደ ዒሳም፣ ወደ አዩብም፣ ወደ ዩኑስም፣ ወደ ሃሩንና፣ ወደ ሱለይማንም አወረድን። ለዳውድም ዘቡርን ሰጠነው። እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን ወደ አንተም አወረድን። ወደ ኢብራሂምም፣ ወደ ኢስማዒልም፣ ወደ ኢስሓቅም፣ ወደ ያዕቆብም፣ ወደ ነገዶቹም፣ ወደ ዒሳም፣ ወደ አዩብም፣ ወደ ዩኑስም፣ ወደ ሃሩንና፣ ወደ ሱለይማንም አወረድን። ለዳውድም ዘቡርን ሰጠነው። ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልክተኞች ባንተ ላይም ያልተረክናቸውን መልክተኞች (እንደላክን ላክንህ)። አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው። ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)። አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።” (አን-ኒሣእ 4፤ 163-165)

በሌላም የቁርኣን አንቀፅ

وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُضِلَّ قَوْمًا بَعْدَ إِذْ هَدَاهُمْ حَتَّىٰ يُبَيِّنَ لَهُم مَّا يَتَّقُونَ ۚ إِنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ

“አላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለእነሱ እስከሚገልጸላቸው (እስከሚተውትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም። አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና።” (አት-ተውባ 9፤ 115)

ታዋቂው የቁርኣን ተንታኝ ኢብኑ ከሲር እንዲህ ይላሉ- ልቅናው ከፍ ያለው አላህ ስለተከበረው ማንነቱና ፍትሃዊ ስለሆነው ጥበቡ በማስመልከት ሲያሣውቅ “አላህ ሰዎችን መልእክት ካልደረሣቸውና ማስረጃም በትክክል እስካልቆመባቸው ድረስ አያጠማቸውም። ይላል።” ብለዋል። ይህንንም በማስመልከት አላህም (ሱ.ወ). እንዲህ ብሏል

وَأَمَّا ثَمُودُ فَهَدَيْنَاهُمْ فَاسْتَحَبُّوا الْعَمَىٰ عَلَى الْهُدَىٰ

“ሰሙዶችማ መራናቸው ዕውርነትንም በቅንነት ላይ መረጡ።” (ፉሲለት 41፤ 17)

ልቅናው ከፍ ያለው አላህ አንድንም ሰው ማስረጃ እስኪያቆምበትና ምክኒያት እስኪያሣጣው ድረስ አይቀጣም። አላህ እንዲህ አለ

وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّىٰ نَبْعَثَ رَسُولًا

“መልዕክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም።” (አል-ኢስራእ 17፤ 15)

የነቢያት መጠበቅ (ዒስማ)

መልእክተኞችን አላህ ነው የመረጣቸውና ያላቃቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَىٰ آدَمَ وَنُوحًا وَآلَ إِبْرَاهِيمَ وَآلَ عِمْرَانَ عَلَى الْعَالَمِينَ

“አላህ አደምን፣ ኑሕንም፣ የኢብራሂምንም ቤተሰብ፣ የዒምራንንም ቤተሰብ በዓለማት ላይ መረጠ።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 33)

ከክፋትም አጠራቸው፤ ከትንሹም ይሁን ከትልቁ ወንጀል ጠበቃቸው። አላህ እንዲህ አለ

وَمَا كَانَ لِنَبِيٍّ أَن يَغُلَّ 

“ለነቢይም ሰለባን መደበቅ አይገባውም።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 161)

በእውነት፣ በአደራ፣ በሀቅ ላይ በመረዳዳት፣ ግዴታን በመወጣትና በመሣሠሉት ትላልቅ ሥነምግባራት አሣመራቸው። ከነኚህ መካከል ስዲቅ /እውነተኛው/ በመባል የሚታወቀው ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሠ) ይገኛል።

وَاذْكُرْ فِي الْكِتَابِ إِبْرَاهِيمَ ۚ إِنَّهُ كَانَ صِدِّيقًا نَّبِيًّا

“በመጽሐፉ ውስጥ ኢብራሂምንም አውሳ። እርሱ በጣም እውነተኛ ነቢይ ነበርና።” (መርየም 19፤ 41)

ከነሱም መካከል አላህ ለራሱ የመረጠውና ያዘጋጀው አለ

وَأَلْقَيْتُ عَلَيْكَ مَحَبَّةً مِّنِّي وَلِتُصْنَعَ عَلَىٰ عَيْنِي

“ባንተ ላይም ከእኔ የኾነን መወደድ ጣልኩብህ። (ልትወደድና) በእኔም ጥበቃ ታድግ ዘንድ።” (ጧሃ 20፤ 39)

በሌላም የቁርኣን አንቀፅ

فَلَبِثْتَ سِنِينَ فِي أَهْلِ مَدْيَنَ ثُمَّ جِئْتَ عَلَىٰ قَدَرٍ يَا مُوسَىٰ
وَاصْطَنَعْتُكَ لِنَفْسِي

“በመድየን ቤተሰቦችም ውስጥ (ብዙ) ዓመታትን ተቀመጥክ። ከዚያም ሙሳ ሆይ! በተወሰነ ጊዜ ላይ መጣህ። ለነፍሴም (በመልእክቴ) መረጥኩህ።” (ጧሃ 20፤ 40-41)

ከነሱም ውስጥ አላህ በዐይኑ የሚከታተለው /ዘወትር በአላህ ጥበቃ ሥር ያለ/ አለ

كَذَٰلِكَ يَجْتَبِيكَ رَبُّكَ وَيُعَلِّمُكَ مِن تَأْوِيلِ الْأَحَادِيثِ وَيُتِمُّ نِعْمَتَهُ عَلَيْكَ وَعَلَىٰ آلِ يَعْقُوبَ كَمَا أَتَمَّهَا عَلَىٰ أَبَوَيْكَ مِن قَبْلُ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْحَاقَ ۚ إِنَّ رَبَّكَ عَلِيمٌ حَكِيمٌ

“እንደዚሁም (እንዳየኸው) ጌታህ ይመርጥሃል። ከንግግሮችም ፍች ያስተምርሃል። ጸጋውንም ከአሁን በፊት በሁለቱ አባቶችህ በኢብራሂምና በኢስሐቅ ላይ እንዳሟላት በአንተ ላይና በያዕቆብ ዘሮችም ላይ ይሞላታል። ጌታህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና።” (ዩሱፍ 12፤ 6)

አላህ (ሱ.ወ) በመርየም ምእራፍ በርካታ ነቢያቶችን ካወሣ በኋላ እንዲህ አለ

أُولَٰئِكَ الَّذِينَ أَنْعَمَ اللَّهُ عَلَيْهِم مِّنَ النَّبِيِّينَ مِن ذُرِّيَّةِ آدَمَ وَمِمَّنْ حَمَلْنَا مَعَ نُوحٍ وَمِن ذُرِّيَّةِ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْرَائِيلَ وَمِمَّنْ هَدَيْنَا وَاجْتَبَيْنَا ۚ إِذَا تُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ آيَاتُ الرَّحْمَٰنِ خَرُّوا سُجَّدًا وَبُكِيًّا

“እነዚህ (ዐሥሩ) እነዚያ አላህ በእነሱ ላይ የለገሰላቸው ከነቢያት ከአዳም ዘር ከኑሕ ጋር (በመርከቢቱ ላይ) ከጫናቸውም (ዘሮች) ከኢብራሂምና ከእስራኤልም ዘሮች ከመራናቸውና ከመረጥናቸውም የኾኑት የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ።” (መርየም 19፤ 58)

የአላህ መልእክተኞች ምንም እንኳ በደረጃ ቢበላለጡም በመንፈሣዊ ንፅህናና ከአላህ ጋር ባላቸው ግንኙነት በኩል ጫፍ የደረሱ ናቸው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

تِلْكَ الرُّسُلُ فَضَّلْنَا بَعْضَهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ ۘ مِّنْهُم مَّن كَلَّمَ اللَّهُ ۖ وَرَفَعَ بَعْضَهُمْ دَرَجَاتٍ ۚ وَآتَيْنَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ الْبَيِّنَاتِ وَأَيَّدْنَاهُ بِرُوحِ الْقُدُسِ

“እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን። ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ። ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ። የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው። በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው።” (አል-በቀራህ 2፤ 253)

በዚህ መልኩ ነቢያትና በአላህ መልእክተኞች ዙሪያ በቁርኣን ውስጥ የወረዱ በርካታ የቁርኣን አንቀፆች በሙሉ የነሱን ፅዳት /ከወንጀል መጠበቅ/፣ ንፅህናና ቅድስና የሚያመለክቱ ሆነው እናገኛለን። ይህም ለሰው ልጅ ዓይነተኛና ህያው የሆነ ምሣሌ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ስብእናው የተሟላ የሰው ልጅ ባህሪም ምን እንደሚመስል ትልቁ ማሣያዎችም እነሱ ናቸው።

ታዲያ እነኚህ ዓይነቶቹ የምጡቅ ስብእና ባለቤቶች በወንጀል ይዘፈቃሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ነቢያት ከሀጢኣት የጠሩ ናቸው። ግዴታ የተደረገባቸውን ነገር አይተውም። ሀራም የሆነ ነገር አይሠሩም፣ ምሣሌያዊ የሆነ መሪ በሚገለፅበት በትላልቅና መልካም ባህሪያት እንጂ አይገለፁም። ይህም ሰዎች ሁሉ የሚቀጣጩበት ከፍተኛና ዓይነተኛ የሆነ ደረጃ ነው። የአላህ መልእክተኞች ዘወትር አላህ ወዳስቀመጠላቸው ምሉዕነት ለመድረስ እንደጣሩ ናቸው።

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እራሱ ነው ትልቅና ሞገስ ያለው የፀና ተራራ እስኪሆኑና መመረጣቸውና በላጭ መሆናቸው ተገቢ እንደሆነ ለማሣየትም ጭምር ነቢያቱን ሥርኣት የማስያዙን፣ የማነፁንና የማስተማሩን ሀላፊነትን የወሰደው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

أُولَٰئِكَ الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ وَالْحُكْمَ وَالنُّبُوَّةَ ۚ فَإِن يَكْفُرْ بِهَا هَٰؤُلَاءِ فَقَدْ وَكَّلْنَا بِهَا قَوْمًا لَّيْسُوا بِهَا بِكَافِرِينَ

أُولَٰئِكَ الَّذِينَ هَدَى اللَّهُ ۖ فَبِهُدَاهُمُ اقْتَدِهْ

“እነዚህ እነዚያ መጻሕፍትንና ጥበብን፣ ነቢይነትንም የሰጠናቸው ናቸው። እነዚህ (የመካ ከሓዲዎች) በእርሷ ቢክዱም በእርሷ የማይክዱን ሕዝቦች ለእርሷ በእርግጥ አዘጋጅተናል። እነዚህ (ነቢያት)፤ እነዚያ አላህ የመራቸው ናቸው። በመንገዳቸውም ተከተል።” (አል-አንዓም 6፤ 89-90)

በሌላም አንቀፅ

وَجَعَلْنَاهُمْ أَئِمَّةً يَهْدُونَ بِأَمْرِنَا وَأَوْحَيْنَا إِلَيْهِمْ فِعْلَ الْخَيْرَاتِ وَإِقَامَ الصَّلَاةِ وَإِيتَاءَ الزَّكَاةِ ۖ وَكَانُوا لَنَا عَابِدِينَ

“በትዕዛዛችንም ወደ በጎ ሥራ የሚመሩ መሪዎች አደረግናቸው። ወደእነሱም መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አወረድን። ለእኛ ተገዢዎችም ነበሩ።” (አል-አንቢያእ 21፤ 73)

እንዲሁ በሌላም አንቀፅ

إِنَّهُمْ كَانُوا يُسَارِعُونَ فِي الْخَيْرَاتِ وَيَدْعُونَنَا رَغَبًا وَرَهَبًا ۖ وَكَانُوا لَنَا خَاشِعِينَ

“እነርሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም ነበሩ። ለእኛ ተዋራጆችም ነበሩ።” (አል-አንቢያእ 21፤ 90)

የተጠቀሱት የቁርኣን አንቀፆች በሙሉ አላህ (ሱ.ወ) በነቢያቶቹና በመልእክተኞቹ ላይ ያፈሠሠው የስብእና ፀጋ ምን ያህል የተሟላ እንደሆነ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው። በዚህ መልኩ አላህ (ሱ.ወ) መልእክተኞቹን ባያሟላቸው ኖሮ ግርማ ሞገሣቸው በሰዎች ዘንድ በወደቀ ነበር። ሰዎች ባነሠ ዓይን የሚመለከቷቸው ከሆነ ደግሞ በነሱ ላይ እምነት ይጠፋል። በመሆኑም ለነሱ የሚመራ አንድም ሰው አይኖርም። ፍጥረትን ሁሉ ወደ ሀቅ ይመሩ ዘንድ የተላኩበት ጥበብም ትርጉም ያጣል። ግዴታ መተውን፣ ሀራም ከሠሩ፣ አሊያም ምርጥ ሥነምግባርን ከተፃረሩና በአጠቃላይም የሰውን ልጅ ምሉእነት የሚያጓድሉ ነገሮችን የፈፀሙ እንደሆነ መጥፎ ምሣሌ በሆኑ ነበር። በዚህም የተነሣ ዓይነተኛ ምሣሌና የብርሃናማው መንገድ አመላካች መሆን በተሣናቸው ነበር።

የአላህ መልእክተኞች ከሌሎች የሰው ልጆች የበለጠ ደረጃቸው እንዳላቸው ያውቃሉ። በመሆኑም ሁሌም የተሟላ ቅድስና ላይ ናቸው። በሁሉም ሁኔታ ውስጥ አላህን በሀሣባቸው ያያሉ። ውበቱንና ታላቅነቱን የሚያመለክቱ ነገሮችን ያስተውላሉ። ችሎታውንና የታላቅነቱን ምልክቶች፣ ጥበቡና እዝነቱን የሚያንፀባርቁ ነገሮችን ይመለከታሉ። ይህን ሁሉ በራሣቸውና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች፣ በሰማይና በምድር፣ በቀንና በለሊት፣ በሕይወትና በሞት ውስጥ ያያሉ። በዚህም የተነሣ ልቦናቸው አላህን በማላቅና ለሱ በመተናነስ ይሞላል። በልባቸው ውስጥ ለሸይጧን መቀመጫ ቦታ የለም፤ ስሜትም ቦታ አይኖረውም፤ ደመነፍስም አይስተናገድም። እውነትን ከመፈለግ፣ ለሱ ከመታገልና በሱ መስመር ከመሠዋት ውጭ ሌላ ዝንባሌ የላቸውም።

በቁርኣን ውስጥ የወረደውና ለሰዎችም ውጭው አሊያም እላይላዩ ሲታይ ሀጢኣት የሠሩ የሚያስመስላቸውና ከሀጢኣት የተጠበቁ መሆናቸውን የሚቃረኑ የሚመስሉ የቁርኣን አንቀፆች አሉ። በርግጥም የነኚህ አንቀፆች ትርጉም እኛ በተረዳነው መልኩ አይደለም። ቀጥሎ በሚቀርበው ማብራሪያ ግልፅ ይሆንልናል።

አደም (ዐ.ሰ)

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَعَصَىٰ آدَمُ رَبَّهُ فَغَوَىٰ

“አደምም የጌታውን ትእዛዝ (ረስቶ) ጣሰ። (ከፈለገው መዘውተር) ተሳሳተም።” (ጧሃ 20፤ 121)

የዚህ አንቀፅ የላይላይ ትርጉሙ /ዟሂር/ አደም (ዐ.ሰ) ለሸይጧን ጥሪ ምላሽ በመስጠት እንደተሞኘ፣ የአላህን ትእዛዝ በመጣሱም እንቢተኛ እንደሆነና ይህም ድልጠቱና ጥፋቱ እንደሆነ ነው የሚያሣየን። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

فَأَزَلَّهُمَا الشَّيْطَانُ عَنْهَا فَأَخْرَجَهُمَا مِمَّا كَانَا فِيهِ 

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው።” (አል-በቀራህ 2፤ 36)

ነገርግን ሁኔታውን በጥልቀት ያየን እንደሆነ አደም (ዐ.ሰ) የዚህ ጥፋት ሰለባ ሊሆን የቻለው ሆን ብሎ አስቦበትና ፈልጎ ሣይሆን ለአላህ ገብቶ የነበረውን ቃሉን በመርሣቱ ብቻ ነው። አደም ይህን ድርጊት የፈፀመው ሆነ ብሎና አስቦበት እስካልሆነ ድረስ ጥፋት የለበትም። አላህ (ሱ.ወ) በስህተት ለተፈፀመ ነገርና በመርሣት በፈፀሙት ስህተት ሰዎችን አይቀጣምና። አሊያ ግን ሰዎችን በማይችሉት ነገር ማስገደድ ነው የሚሆነው። አላህ (ሱ.ወ) ነፍስ ከምትችለው በላይ አያጨናንቃትም። ለዚህም መነሻችንና ማስረጃቸን የአላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው።

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَلَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌ فِيمَا أَخْطَأْتُم بِهِ وَلَٰكِن مَّا تَعَمَّدَتْ قُلُوبُكُمْ

“በእርሱ በተሳሳታችሁበት ነገርም በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም። ግን ልቦቻችሁ ዐውቀው በሠሩት (ኀጢአት አለባችሁ)። አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።” (አል-አህዛብ 33፤ 5)

በሌላም የቁርኣን አንቀፅ

رَبَّنَا لَا تُؤَاخِذْنَا إِن نَّسِينَا أَوْ أَخْطَأْنَا 
“(በሉ)፡- ጌታችን ሆይ! ብንረሳ ወይም ብንስት አትያዘን፤ (አትቅጣን)።” (አል-በቀራህ 2፤ 286)

አደም ይህን ስህተት የፈፀመው ሆነ ብሎ እንዳልሆነም ማስረጃችን የአላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَلَقَدْ عَهِدْنَا إِلَىٰ آدَمَ مِن قَبْلُ فَنَسِيَ وَلَمْ نَجِدْ لَهُ عَزْمًا

“ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን። ረሳም። ለእርሱም ቆራጥነትን አላገኘንለትም።” (ጧሃ 20፤ 115)

አደም የተከለከለውን ዛፍ በበላበት ወቅት አላህ የመከረውንና አደራ ያለውን ቃል ረስቷል። የተከለከለውን ነገር ሲፈፅም ሆነ ብሎና ቆርጦ አልነበረም። በመሆኑም በፈፀመው ስህተት ተጠያቂ አይሆንም።

መርሣቱ በቁርኣን ውስጥ በእንቢተኝነት ቃል የተገለጸው አደም (ዐ.ሰ) አላህ (ሱ.ወ) ዘንድ ያለውን ደረጃ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው። አላህ (ሱ.ወ) በእጁ ፈጥሮታል፣ ከመንፈሱም ነፍቶበታል፣ መላእክቶችን አሰግዶለታል፣ ጀነቱ ውስጥ አኑሮታል፣ ስሞችን ሁሉ አስተምሮታል። ይህ ሁሉ ዉለታና ፀጋ የተደረገለት ሰው ጌታውን እንዳያስከፋና የአላህንም አደራና ቃል ኪዳን ሊረሣ በማይችልበት መልኩ ሁሌም በተጠንቀቅና በንቃት ላይ መገኘት ነበረበት።

ኑህ (ዐ.ሰ)

ኑህ (ዐ.ሰ). ደግሞ ከሱ የታየውና እንደ ጥፋት የተወሰደበት የርሱ የሆነው ልጅ በውሃ መጥለቅለቅ ከጠፉት ህዝቦች ጋር እንዳይጠፋ አላህን መጠየቁ ነበር። አላህ (ሱ.ወ) እሱንና ቤተሰቦቹን ነጃ ሊያወጣላቸው ቃል ገብቶለት ነበርና ነው ኑህ ስለ ልጁ ለመጠየቅ የተገደደው። በቁርኣን ውስጥ በተገለፀው መልኩ እንዲህ በማለት

وَنَادَىٰ نُوحٌ رَّبَّهُ فَقَالَ رَبِّ إِنَّ ابْنِي مِنْ أَهْلِي وَإِنَّ وَعْدَكَ الْحَقُّ وَأَنتَ أَحْكَمُ الْحَاكِمِينَ
قَالَ يَا نُوحُ إِنَّهُ لَيْسَ مِنْ أَهْلِكَ ۖ إِنَّهُ عَمَلٌ غَيْرُ صَالِحٍ ۖ فَلَا تَسْأَلْنِ مَا لَيْسَ لَكَ بِهِ عِلْمٌ ۖ إِنِّي أَعِظُكَ أَن تَكُونَ مِنَ الْجَاهِلِينَ
قَالَ رَبِّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ أَنْ أَسْأَلَكَ مَا لَيْسَ لِي بِهِ عِلْمٌ ۖ وَإِلَّا تَغْفِرْ لِي وَتَرْحَمْنِي أَكُن مِّنَ الْخَاسِرِينَ

“ኑሕም ጌታውን ጠራ። አለም ‘ጌታዬ ሆይ! ልጄ ከቤተሰቤ ነው። ኪዳንህም እውነት ነው። አንተም ከፈራጆች ሁሉ ይበልጥ ዐዋቂ ነህ።’ (አላህም) ‘ኑሕ ሆይ! እርሱ ከቤተሰብህ አይደለም፤ እርሱ መልካም ያልሆነ ሥራ ነው፤ በርሱ ዕውቀት የሌለህንም ነገር አትጠይቀኝ፤ እኔ ከሚሳሳቱት ሰዎች እንዳትሆን እገስጽሀለሁ’ አለ። ‘ጌታዬ ሆይ! በእርሱ ለእኔ ዕውቀት የሌለኝን ነገር የምጠይቅህ ከመሆን እኔ ባንተ እጠበቃለሁ። ለእኔም ባትምረኝና ባታዝንልኝ ከከሳሪዎቹ እሆናለሁ’ አለ።” (ሁድ 11፤ 45-47)

ኑህ (ዐ.ሰ) የልጃቸውና የርሣቸው ዝምድና ልጃቸው አላህን በመካዱና ከጥሪው በማፈንገጡ ምክኒያት መበጠሱን አላወቁም ወይንም አላስተዋሉም ነበር። ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ) ቤተሰቡን ሁሉ ነጃ ሊያወጣላቸው ቃል ገብቶላቸው ሣለ ከቤተሰቡ የሆነውን ልጁን እንዴት ሊያጠፋ እንደቻለ ለመጠየቅ የተነሣሱት። አላህም (ሱ.ወ) ሃይማኖታዊ እና መነፈሣዊ ትስስር ከደም ዝምድና የሚበልጥ መሆኑን ለነቢዩ ኑህ (ዐ.ሰ) አሣወቃቸው። እምነታዊ ትስስር የተቋረጠች እንደሆነ የዝምድናና የደም ትስስር ዋጋ የለውም። በማስተማር መልኩም አላህ ለኑህ እንዲህ አለው

إِنَّهُ لَيْسَ مِنْ أَهْلِكَ

“እሱ ከቤተሰብህ አይደለም።” (ሁድ 11፤ 46)

ምክኒያቱም የኑህ ልጅ ሥራ ጥሩ አልነበረምና ነው። በመሆኑም የዝምድና ትስስር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ከአባቱ ጋር የነበረው ዝምድናም በዚሁ አክትሞለታል። ነጃ ሊወጡ ቃል ከተገባላቸው ውስጥም ሊሆን ያልቻለውም ለዚሁ ነው።

“ለሰው ልጅ ሁለተኛ አባት” በመባል የሚታወቁት ነቢየላህ ኑህ (ዐ.ሰ) ህይወታቸውን በሙሉ ወደ አላህ መንገድ ጥሪ በማድረግ ነው የጨረሱት። በህዝቦቻቸውም መካከል ሆነው ለ950 አመታት ያህል ወደ አላህ ተጣርተዋል፤ በመንገዱም ብዙ ደክመዋል። ይህ ከመሆኑ ጋር የዚህን የአላህን ንግግር ትርጉም መሣት አልነበረባቸውም። ሊገባቸውም ይገባ ነበር። ነገር ግን የአባትነት ርህራሄ አሸነፋቸው። በመሆኑም ይህን ሁኔታቸው አላህ ከሠጣቸው ከፍተኛ ደረጃና ትልቅ ቦታ አንፃር ከርሣቸው የማይጠበቅ ነውና እንደ ጉድለት ታየባቸው። በመጨረሻም ነገሩ በገባቸው ጊዜ ኑህ (ዐ.ሰ) ሽሽታቸውን ወደ አላህ አደረጉ፤ አስበውበት ላላደረጉት ለዚህ ድልጠትም ምህረቱን እንዲለግሣቸው ጠየቁ። አላወቁም ነበርና። እንዲህ በማለት

قَالَ رَبِّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ أَنْ أَسْأَلَكَ مَا لَيْسَ لِي بِهِ عِلْمٌ ۖ وَإِلَّا تَغْفِرْ لِي وَتَرْحَمْنِي أَكُن مِّنَ الْخَاسِرِينَ

“ጌታዬ ሆይ! በእርሱ ለእኔ ዕውቀት የሌለኝን ነገር የምጠይቅህ ከመሆን እኔ ባንተ እጠበቃለሁ። ለእኔም ባትምረኝና ባታዝንልኝ ከከሳሪዎቹ እሆናለሁ አለ።” (ሁድ 11፤ 47)

ኢብራሂም (ዐ.ሰ)

በኢብራሂም ዱዓእ ውስጥ እንዲህ የሚል ወርዷል።

وَالَّذِي أَطْمَعُ أَن يَغْفِرَ لِي خَطِيئَتِي يَوْمَ الدِّينِ

“ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው።” (አሽ-ሹዐራእ 26፤ 82)

በርግጥ እኛ የነቢዩ ኢብራሂም ሀጢኣት ምን እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። የምናውቀው ቢኖር የአላህ ወዳጅ መሆናቸውን ነው። አላህ (ሱ.ወ) ምርጥና የተሟሉ የሆኑ ሥነምግባራትን እንደሠጣቸውም ጭምር እናውቃለን። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَأْكُلُوا الرِّبَا أَضْعَافًا مُّضَاعَفَةً ۖ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“በቅርቢቱም ዓለም በእርግጥ መረጥነው። በመጨረሻይቱም ዓለም እርሱ ከመልካሞቹ ነው።” (አል-በቀራህ 2፤ 130)

إِنَّ إِبْرَاهِيمَ كَانَ أُمَّةً قَانِتًا لِّلَّهِ حَنِيفًا وَلَمْ يَكُ مِنَ الْمُشْرِكِينَ
شَاكِرًا لِّأَنْعُمِهِ ۚ اجْتَبَاهُ وَهَدَاهُ إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ
وَآتَيْنَاهُ فِي الدُّنْيَا حَسَنَةً ۖ وَإِنَّهُ فِي الْآخِرَةِ لَمِنَ الصَّالِحِينَ

“ኢብራሂም ለአላህ ታዛዥ ወደ ቀጥተኛ ሃይማኖት ተዘንባይ ሕዝብ ነበር። ከአጋሪዎቹም አልነበረም። ለጸጋዎቹ አመስጋኝ ነበር፤ መረጠው። ወደ ቀጥተኛውም መንገድ መራው። በቅርቢቱም ዓለም በጎን ነገር ሰጠነው። እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም በእርግጥ ከመልካሞቹ ነው።” (አን-ነህል 16፤ 120-122)

አላህ ይምራቸው ዘንድ መጠየቃቸው እኛ በህሊናችን የሚመጣው ዓይነት ሀጢኣት የሠሩ ሆነው አይደለም። ምናልባትም በልባቸው ውስጥ ደረጃቸው ላቅ ያለ ቦታቸውም ከፍ ያለ ሆኖ ሣለ የአላህን መልእክት ከማድረስ በቂ ጥረት እንዳላደረጉ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።

………. ይቀጥላል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here