ተውሒድ – የአላህ መብት ነው (ተውሒድ – ክፍል 4)

0
4858

ተውሒድ አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት መሆኑና ከርሱ መዘናጋትና ችላ ማለት እንደማይገባ የአላህ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) መግለጻቸው ከላይ ለሰፈረው ሃሳብ የበለጠ ጥንካሬ ይሰጠዋል። ቡኻሪና ሙስሊም ባሰፈሩት ዘገባ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡-

ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በአንዲት አህያ ላይ ነበርን። “ሙዓዝ ሆይ፣ አላህ በባሮቹ ላይ ያለውን መብት፣ ባሮቹም በርሱ ላይ ያላቸውን መብት ታውቃለህን?” አሉኝ። “አላህና መልእክተኛው ያውቃሉ” አልኳቸው። “አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት በርሱ ላይ ምንንም ነገር ሳያጋሩ በብቸኝነት ሊያመልኩት ሲሆን፣ ባሮቹ በርሱ ላይ ያላቸው መብት ደግሞ በርሱ ላይ ምንንም ነገር ያላጋራን ሰው ላይቀጣ ነው።” አሉ። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ ለሰዎች ብስራት ልንገራቸውን?” አልኳቸው። “አታብስራቸው። እንዳይሳነፉ።” አሉ ።

የዚህ መብት ምስጢር አላህ የሰውን ልጅ ካልነበረበት አስገኘው። ተቆጥረው ሊዘለቁ የማይችሉ ጸጋዎችንም ሰጠው። ፀሐይንና ጨረቃን፣ ቀንና ሌሊትን ለርሱ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ገራለት። አእምሮ ሰጠው። ሃሳብን የመግለጽ ችሎታን አስተማረው። እናም ሲሳይን የለገሰ፣ ጸጋዎችን የሰጠ፣ አዛኝና ሩህሩህ አምላክ ሊመሰገን እንጅ ውለታው ሊካድ አይገባም። ሊታወስ እንጅ ሊረሳ አይገባም። ሊታዘዙት እንጅ ሊያምጹት አይገባም።

የቁርአን የመጀመሪያው ኑዛዜ ይህን መብት መግለጽ ሆኗል። የአስር መብቶች አንቀጽ በመባል የሚታወቀው የቁርአን አንቀጽ የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነው፡-

وَاعْبُدُوا اللَّهَ وَلَا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَبِذِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينِ وَالْجَارِ ذِي الْقُرْبَىٰ وَالْجَارِ الْجُنُبِ وَالصَّاحِبِ بِالْجَنبِ وَابْنِ السَّبِيلِ وَمَا مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ مَن كَانَ مُخْتَالًا فَخُورًا

“አላህንም ተገዙ። በእርሱም ምንንም አታጋሩ። በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው (ባሮች)፣ መልካምን (ሥሩ)፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም።” (አን-ኒሳእ 36)

በአል-አንዓም ምእራፍ ውስጥም የሰፈሩት አስሩ ኑዛዜዎች በዚህ መልእክት ተወጥነዋል፡-

قُلْ تَعَالَوْا أَتْلُ مَا حَرَّمَ رَبُّكُمْ عَلَيْكُمْ أَلَّا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَلَا تَقْتُلُوا أَوْلَادَكُم مِّنْ إِمْلَاقٍ نَّحْنُ نَرْزُقُكُمْ وَإِيَّاهُمْ وَلَا تَقْرَبُوا الْفَوَاحِشَ مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَمَا بَطَنَ وَلَا تَقْتُلُوا النَّفْسَ الَّتِي حَرَّمَ اللَّهُ إِلَّا بِالْحَقِّ ذَٰلِكُمْ وَصَّاكُم بِهِ لَعَلَّكُمْ تَعْقِلُونَ

“ኑ፤ ጌታችሁ በእናንተ ላይ እርም ያደርገውን ነገር (በእርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ” በላቸው። “በእርሱ (በአላህ) ምንንም ነገር አታጋሩ። ለወላጆችም በጎን ሥራ (ሥሩ)። ልጆቻችሁንም ከድህንት (ፍራቻ) አትግደሉ። እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና። መጥፎ ሥራዎችንም ከእርሷ የተገለጸውንም የተደበቀውንም ሁሉ አትቅረቡ። ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ በሕግ ቢኾን እንጅ አትግደሉ። ይህን ታውቁ ዘንድ (አላህ) በእርሱ አዘዛችሁ።” (አል-አንአም 151)

በአል-ኢስራእ ምእራፍ ውስጥ የተካተቱት ኑዛዜዎችም እንደዚሁ ይህን መብት በመግለጽ ተወጥነዋል፡-

لَّا تَجْعَلْ مَعَ اللَّهِ إِلَٰهًا آخَرَ فَتَقْعُدَ مَذْمُومًا مَّخْذُولًا وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا إِمَّا يَبْلُغَنَّ عِندَكَ الْكِبَرَ أَحَدُهُمَا أَوْ كِلَاهُمَا فَلَا تَقُل لَّهُمَا أُفٍّ وَلَا تَنْهَرْهُمَا وَقُل لَّهُمَا قَوْلًا كَرِيمًا

“ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ የተወቀስክ ረዳት የሌለህ ትኾናለህና፤ ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው።” (አል-ኢስራእ 22-23)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here