የመፀዳጃ ቤት ስርዓት (ጦሀራ – ክፍል 5)

0
7831

ከሽንት እና ከዓይነምድር የሚፀዳዳ ሰው የሚከተላቸው ስነስርአቶች እንደሚከተለው አሳጥረን አቅርበናቸዋል፦

 1. የአላህ ስም ያለበትን ነገር አለመያዝ

ይህም ስሙ የተፃፈበት ነገር ውድመት ወይም አደጋ ይገጥመዋል ብሎ ካልፈራ ወይም ሒርዝ (አንገት ላይ የሚንጠለጠል መድሃኒት) ካልሆነ ነው። ምክንያቱም አነስ እንደዘገቡት፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሙሐመዱንረሱሉሏህ (ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ) የሚል ፅሁፍ የተቀረፀበት ቀለበት ለበሱ። ከዚያም ሽንት ቤት ሲገቡ ያወልቁት ነበር።” አራቱ ዘግበውታል። አል ሃፊዝ ይህን ሀዲስ “ነውር ያለበት (ማዕሉል) ነው” ብለዋል። አቡዳዉድ ደግሞ “ሙንከር (የተነቀፈ ሐዲስ) ነው” ነገር ግን የሐዲሱ የመጀመሪያ ክፍል ሶሒህ ነው ብለውታል።

 1. ከሰዎች መራቅ እና መሸፈን

በተለይም በዓይነምድር ወቅት ሰዎች ድምፅ እንዳይሰሙ እና ሽታው እንዳይሸታቸው። ምክንያቱም ከጃቢር እንደተዘገበው፦

“ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር መንገድ ወጣን። ለሽንት መውጣት በፈለጉ ጊዜ ከሰዎች ይርቁ ነበር።” (ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

አሁንም በአቡዳውድ ሌላኛው ዘገባ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሽንት ለመሽናት ከተነሱ ከሰዎች ርቀው ይሄዱ ነበር።”

 1. ቢስሚላህ ብሎ ወደ መፀዳጃ ይገባል። አዑዙቢላህ ማለት። ሁለቱንም ጮክ ብሎ ማለት

ሜዳ ላይ ከሆነ የሚፀዳዳው ልብሱን ለማውለቅ ሲሰናዳ ሁለቱንም ጮክ ብሎ ይላል። ምክንያቱም አነስ የዘገቡት ሐዲስ እንዲህ ይላል።

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ.) ሽንት ቤት መግባት ሲፈልጉ፦

بسم الله ، اللهم إني أعوذ بك من الخبث والخبائث

አነባነቡ፦ “ቢስሚላሂ አላሁመ ኢኒ አዑዙቢከ ሚነል ኹቡሲ ወል ኸባኢስ”

“በአላህ ስም፤ አላህ ሆይ እኔ ከወንድ ሰይጣኖች እና ከሴት ሰይጣናት ባንተ እጠበቃለሁ።” ይሉ ነበር።” (ጀመዐዎቹ ዘግበውታል)

 1. ከማንኛውም – ዚክርም ይሁን ሌላ – ንግግር መቆጠብ

ስለዚህ ሰላምታ አይመልስም። ለአዛን አድራጊ መልስ አይሰጥም። የግድ የሆነ ንግግር ግን ይፈቀዳል። ለምሳሌ፦ ጉድጓድ ውስጥ ይገባል ብሎ ከሰጋ ዓይነ ስውርን ይመራል። ካስነጠሰ በልቡ አላህን ያመሰግናል። ምላሱን አያንቀሳቅስም።

አቢሰዒድ በሐዲሳቸው ላይ የአላህን ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሰምቻቸዋለሁ ብለው እንደዘገቡት፦

لا يخرج الرجلان يضربان الغائط كاشفين عن عورتيهما يتحدثان فإن الله يمقت على ذلك

“ሁለት ሰዎች ወደ መፀዳጃ ሄደው ሀፍረተ ገላቸውን ገልጠው ወሬ እንዳያወሩ። አላህ በዚህ ድርጊት ይቆጣል።” ብለዋል” (አህመድ፣ አቡዳዉድ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

 1. የቂብላን አቅጣጫ ማክበር አለበት

ስለዚህ ወደ ቂብላ ፊቱን ማዞርም ይሁን ለርሱ ጀርባውን መስጠት የለበትም። ምክንያቱም በአቢ ሁረይራ ሐዲስ እንደተዘገበው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

إذا جلس أحدكم لحاجته فلا يستقبل القبلة ولا يستدبرها

“አንዳችሁ ለመፀዳዳት ከተቀመጠ ወደ ቂብላ ፊቱን አያዙር። ጀርባውንም አይስጥ።” (አህመድ እና ሙስሊም ዘግበውታል)

ወደ ቂብላ መዞር እና ጀርባን መስጠት ሐራም የሚሆነው ሜዳ ላይ ሲሆን ነው። በግንብ ውስጥ ከሆነ ግን ይፈቀዳል።

ከመርዋን አል-አስፈር እንዲህ የሚል ተዘግቧል፦ “ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) ግመላቸውን ወደ ቂብላ አቅጣጫ አንበርክከው ወደርሷ ሲሸኑ ተመልክቻቸዋለሁ። ከዚያም “አንቱ የአብዱራህማን አባት ይህ ድርጊት ተከልክሎ የለም አንዴ?” ብዬ ጠየኳቸው። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፦ “አዎን! ነገርግን የተከለከለው በሜዳ ላይ ሲሆን ነው። ባንተ እና በቂብላ መካከል የሚሸፍንህ አንዳች ነገር ካለ ችግር የለውም።” አቡዳውድ፣ ኢብኑ ኹዘይማ እና አል-ሐኪም ዘግበውታል። ሰነዱ አል-ፈትህ የተሰኘው መፅሃፍ ላይ እንዳለው ከሆነ በሐሰን ደረጃ ላይ አለ።

 1. ነጃሳው እንዳይነካው ለመጠንቀቅ ዝቅ ያለ እና ለስላሳ ቦታን መፈለግ

ምክንያቱም አቡ ሙሳ (ረ.ዐ) በሐዲሳቸው እንደዘገቡት፦

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከአንድ አጥር አጠገብ ወደ ለስላሳ ስፍራ መጡና ሽንት ሸኑ። እንዲህም አሉ፦

إذا بال أحدكم فليرتد لبوله

“አንዳችሁ ሽንቱን ሲሸና ለሽንቱ ቦታ ይፈልግለት።” (አቡዳዉድ እና አህመድ ዘግበውታል) ሐዲሱ በሰነዱ ውስጥ ማንነቱን ያልታወቀ ሰው ቢኖረውም ትርጉሙና መልእክቱ ግን ሶሒህ ነው።

 1. ስንጥቅ መሬት ላይ ከመፀዳዳት መጠንቀቅ

ምክንያቱም ስንጥቅ መሬት ውስጥ እርሱን የሚያስቸግሩ ነፍሳት ሊኖሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ቀታዳ ከዐብደላህ ኢብኑ ሰርጂስ ይዘው በዘገቡት ሐዲስ ላይ እንዲህ የሚል አለ፦

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ስንጥቅ መሬት ላይ ከመሽናት ከልክለዋል። ቀታዳን “ስንጥቅ መሬት ላይ መሽናት ምን አስጠላው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “እርሷ የጅኖች መኖሪያ ናት! አለ።” አህመድ፣ ነሳዒይ፣ አቡዳውድ፣ አል-ሐኪም እና አል-በይሃቂይ ዘግበውታል። ኢብኑ ኹዘይማ እና ኢብኑ ሰከን ሐዲሱን ሶሒህ ነው ብለውታል።

 1. የሰዎች መጠለያ፣ መንገዳቸው እና የሚያወሩበት ቦታ ላይ መፀዳዳት የለበትም

ምክንያቱም በአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ) ሐዲስ እንደተዘገበው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፦

اتقوا اللاعنين

“እርግማን የሚያመጡ ሁለት ነገሮችን ተጠንቀቁ!” “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ምንድን ናቸው እነርሱ?” ብለው ጠየቋቸው።

الذي يتخلى في طريق الناس أو ظلتهم

“የሰዎች መንገድ እና ጥላቸው ላይ መሽናት ነው” አሉ።” (አሕመድ፣ሙስሊምና አቡዳዉድ ዘግበውታል)

 1. የገላ መታጠቢያ ውሃ ላይ መሽናት የለበትም። ወራጅ ውሃ ላይም መሽናት የለበትም

በአብደላህ ኢብኑ ሙገፈል ሐዲስ ውስጥ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

 لا يبولن أحدكم في مستحمه ثم يتوضأ فيه ، فإن عامة الوسواس منه

“አንዳችሁም በውስጡ ውዱ ሊያደርግበት በገላ መታጠቢያው ውስጥ መሽናት የለበትም። ውስዋሴ በሙሉ ከርሱ ነው።” (አምስቱ ዘግበውታል) ነገርግን “በውስጡ ውዱእ ሊያደርግት” የሚለው ንግግር የአሕመድ እና የአቡዳውድ ዘገባ ላይ ብቻ የተገኘ ነው።

አሁንም ከርሳቸው እነደተዘገበው፦ “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ወራጅ ውሃ ውስጥ መሽናት ከልክለዋል።” ሙጅመዑዝ-ዘዋኢድ የተሰኘው መፅሃፍ ላይ “ጦበራኒይ ዘግበውታል፤ ዘጋቢዎቹም ታማኞች ናቸው።” የሚል ሰፍሯል።

የገላ መታጠቢያ ስፍራው ላይ ውሃን የሚያሳልፍ ቱቦ ካለ በርሱ ላይ መሽናት አይጠላም።

 1. ቆሞ አይሸናም

ምክንያቱም ቆሞ መሽናት ከክቡር ስብእና እና ከመልካም ልማድ የወጣ ተግባር ነው። በተጨማሪም ሽንቱ መረጫጨቱ አያስቸግረኝም ብሎ ካመነ ግን ቆሞ መሽናት ይችላል። ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፦

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ቆመው ሸንተዋል ብሎ የነገራችሁን ሰው አትመኑት። እርሳቸው ተቀምጠው እንጂ አይሸኑም ነበር።” ከአቡዳዉድ በስተቀር አምስቱ ዘግበውታል። ቲርሙዚ እንደሚሉት፦ “ይህ (ሐዲሱ) በዚህ ጉዳይ ውስጥ ከተዘገቡት ሐዲሶች በሙሉ መልካሙ እና እጅግ የተሻለው ሶሒሁ ነው።”

የዓኢሻ ንግግርን የምንይዘው እስከ የእውቀታቸው ወሰን ነው። ማለትም እርሳቸው ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ካላቸው ጥቡቅ ትስስር እና አብሮነት ጋር ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ቆመው ሲሸኑ አልተመለከቷቸውም በማለት ነው የምንረዳው። ስለዚህ ሑዘይፋ ከዘገቡት ሐዲስ ጋር አይጋጭም። የሑዘይፋው ሐዲስ እንዲህ ይላል፦

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሰዎች ቆሻሻ ወደ ሚጥሉበት ስፍራ ጠጋ ብለው ቆመው ሸኑ። እኔም ከርሳቸው ኋላ ቆምኩኝ። ከዚያም ውዱእ አደረጉና በኹፍ (በጫማ) ላይ አበሱ።” (ጀመዓዎች ዘግበውታል)

 1. በሁለቱ መንገዶች (በመቀመጫ እና በብልት ቀዳዳዎች) ላይ ያለውን ነጃሳ ማስወገድ አለበት

ከፈለገ በድንጋይ እና እንደ ድንጋይ ባሉ ደረቅ፣ ንፁህ፣ ነጃሳን በሚመጡ እና ክብር በሌላቸው ነገሮች ማስለቀቅ ይችላል። ከፈለገም በውሃ ብቻ ማስለቀቅ ይችላል። ከፈለገም በሁለቱም ነጃሳውን ማስለቀቅ ይችላል። ምክንያቱም በዓኢሻ (ረ.ዐ) ሐዲስ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

إذا ذهب أحدكم إلى الغائط فليستطب بثلاثة أحجار فإنها تجزئ عنه

“አንዳችሁ ወደ መፀዳጃ ሲሄድ በሦስት ድንጋይ ኢስቲንጃ ያድርግ (ነጃሳውን ያስለቅቅ)። እርሷ (ሦስቷ ድንጋይ) ታብቃቃዋለች።” (አሕመድ፣ ነሳኢይ አቡዳውድ እና ዳረቁጥኒይ ዘግበውታል)

 1. በቀኝ እጁ ኢስቲንጃ ማድረግ የለበትም

ዘይድ በሐዲሳቸው እንዲህ ብለዋል፦

“ሰልማን እንዲህ ተብለው ተጠየቁ፦ “ነብያችሁ ስለ መፀዳዳት ሳይቀር ሁሉን ነገር አስተማሯችኋል?” ሱለይማንም እንዲህ አሉ፦ “አዎን!” ከዓይነ-ምድርም ሆነ ከሽንት ስንፀዳዳ ወደ ቂብላ እንዳንዞር፣ በቀኝ እጃችን ኢስቲንጃ እንዳናደርግ፣ አንዳችንም ከሦስት ድንጋዮች ባነሰ እንዳንጠቀም፣ በፋንዲያ ወይም በአጥንት እንዳንጠቀም ከልክለውናል።” (ሙስሊም፣ አቡዳዉድ እና ቲርሙዚይ ዘግበውታል)

 1. ከኢቲንጃ በኋላ እጁን በመሬት ላይ ማሸት ወይም በሳሙና ማጠብ

ምክንያቱም እንዲህ ሲያደርግ እጁ ላይ የሚኖሩት አስፀያፊ ሽታዎች ይለቃሉ። በተጨማሪም አቡሁረይራ በዘገቡት ሀዲስ፦

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ መፀዳጃ ሲሄዱ በእቃ – በነሃስ እቃ ወይም በቆዳ እቃ- ውሃ ይዤ እከተላቸዋለሁ። ከዚያም ኢቲንጃ ያደርጋሉ። ከዚያም እጃቸውን በመሬት ላይ ያብሳሉ።”  (አቡዳውድ፣ ነሳኢይ፣ አል-በይሀቂይ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

 1. ብልቱን እና ሱሪውን በውሃ መርጨት

ይህን የሚያደርገው ውስዋሴን ለመገፍተር ነው። ከዚህ በኋላ እርጥበት ቢሰማውም እንኳ ይህ ሱሪዬ ላይ ወይም ብልቴ ላይ የረጨሁት ውሃ ነው በማለት ውስዋሴውን ያስወግደዋል። ምክንያቱም በሱፍያን ቢን አል-ሀከም ሐዲስ ውስጥ፦

“የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሽንት የሸኑ ጊዜ ውዱእ ያደርጋሉ። ውሃም ይረጫሉ።” የሚል እናገኛለን። በሌላ ዘገባ፦ “የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሸንተው ብልታቸውን በውሃ ሲረጩ ተመልክቻቸዋለሁ።” ይላሉ። ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) ሱሪያቸው እስከሚረጥብ ድረስ ብልታቸውን በውሃ ይረጩት ነበር።

 1. ወደ መፀዳጃ ሲገባ ግራ እግሩን ማስቀደም ሲወጣ ደግሞ ቀኝ እግሩን ማስቀደም። ከዚያም “ምህረትህን” (ጉፍራነከ) ማለት

ከአኢሻ (ረ.ዐ.) እንደተዘገበው፦ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሲወጡ፦

غفرانك

“ጉፍራነከ (ምህረትህን እለምንሃለሁ) ይሉ ነበር።” ከነሳኢይ በስተቀር አምስቱ ዘግበውታል። አቡሐቲም እንዳሉት “የዐኢሻ ሐዲስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመጡት ሐዲሶች በሙሉ የበለጠ ሶሒህ ነው።”

 1. ከሽንቱ መጥራቱን እና ሽንቱ መቆሙን ማረጋገጥ

ይህ እንደ ልማዱ ይታያል። የመጨረሻዋ የሽንት ጠብታ መውጣቷን ለማረጋገጥ መቆም እና መራመድ ወይም ሽንት ቤት ውስጥ በመቆየት ቁጭ ብድግ ማለት ካለበት ባስለመደው እና በሚመቸው መልኩ ሽንቱ ወጥቶ ማለቁን ያረጋግጣል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here