ኢማም አን-ነወዊ

0
7830

የዘር ሀረጋቸውና ዕድገታቸው

አቡ ዘከሪያ ሙሕይዲን ኢብኑ ሸረፍ አን-ነወዊ ይባላሉ። የተወለዱት በሶሪያ ከሐውራን መንደር አንዷ በሆነችው በነዋ ነው። ጊዜውም በ631 ዓ.ሂ ሲሆን ከደጋግ ወላጆች ነው የተወለዱት። ዕድሜአቸው አሥር ዓመት ገደማ ሲሆን ቁርኣንን በቃላቸው ማጥናት እና ፊቅሂን በአንዳንድ ዑለማኦች እጅ መማር ጀመሩ። በ649 ዓ.ሂ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ብለው ከአባታቸው ጋር በመሆን ደማስቆ ወደሚገኘው የሐዲሥ ማዕከል አቀኑ። እዚያም የረዋሒያ መድረሳን ተቀላቀሉ። መድረሳው ከታላቁ የኡመዉያ መስጂድ ጋር ተያይዞ የተሠራ ነበር። በ651 ዓ.ሂ ከአባታቸው ጋር በመሆን ሐጅ አደረጉ። ከዚያም ወደ ዲመሽቅ (ደማስቆ) ተመለሱ። እዚያም ሆነው ሙሉ ሀሳባቸውንና ፊታቸውን ወደ ዑለማኦች ማዕድ በማዞር ዕውቀት መቅሰም ጀመሩ።

የኢማም ነወዊ ሥነምግባር  እና ባህሪያቸው

ኢማም ነወዊ ሞገስ ያላቸው ሰው ነበሩ። ሲስቁ እምብዛም አይታዩም። ከጨዋታና ላግጣም የራቁ ናቸው። የቱን ያህል መራራ ቢሆንም እውነትን ከመናገር ወደኋላ ባለማለት አቋማቸው ይታወቃሉ። በአላህ ጉዳይም የየትኛውንም ወቃሽ ወቀሳን አይፈሩም። ለዓለማዊነት ከማደር እጅግ የራቁ በአላህ ፍራቻም የሚታወቁ የታላቅ ስብእና ባለቤት ናቸው። ስለርሣቸው የፃፉ ሁሉ በርግጥም ከዚህች ዓለም እጅግ ቁጥብ እና የተብቃቁ ስለመሆናቸው መስክረዋል።

ኢማም ነው ለአላህ ያላቸው ፍራቻ  በእጅጉ ይለያል። ለመሪዎችና አስተዳዳሪዎች መልካም ምክራቸውን ያቀብላሉ። በጥሩ ያዛሉ፣ ከመጥፎ ነገርም ይከለክላሉ። ለኢማም አንነወዊ አላህ ይዘንላቸው – በሀያ አራት ሰዓታት ዉስጥ አንድ ጊዙ ብቻ ማለትም ከዒሻ በኋላ ነበር የሚመገቡት። ከማንም ምንም ፈልገው አያውቁም። ብዙን ጊዜ ለመሪዎች እና ለሚኒስቴሮቻቸው ይጽፉ፤ ለህዝቡም ሆነ ለሀገራቸው በሚጠቅም ነገር ላይ ያመላክቱና ይመክሩ ነበር።

የዕውቀት ሕይወታቸው

ዲመሽቅ ከደረሱ በኋላ ያለው የዕውቀት ሕይወታቸው ሶስት የተለያየ ክፍል ነበረው።

የመጀመሪያው –  ገና በልጅነትና በወጣትነት ሕይወታቸው ዕውቀት ፍለጋ መጣር እና ለማግኘት የተጉበት ነው።

ሁለተኛው – ዕውቀታቸውን የበለጠ ለማስፋት፣ በጥልቀትም ለማወቅ የጣሩበት ነው። በዚህም የተለያዩ ዕውቀቶችን ፍለጋ አብዝተው ደክመዋል። በየቀኑ በተለያዩ ሸይኾች ላይ አሥራ ሁለት ያህል ትምህርቶችን ይማሩ ነበር።

ሦስተኛው – ዕውቀትን መጠቀም፣ ማስተማርና ማሠራጨት። ይህንን የጀመሩት በ660 ዓ.ሂ ገና በሰላሳ ዓመታቸው ነበር። አላህም (ሱ.ወ) ጊዜያቸውን ባርኮላቸዋል። በርግጥም ረድቷቸዋል። ጊዜያቸውን እጅግ የሚገራርሙና የማይታመኑ ትላልቅ የሆኑ መጽሐፍት በመፃፍ ተጠቅመውበታል። በመጽሐፍቶቻቸው ዉስጥ የሚጠቀሙት ገለፃ  የለሰለሰና ገር፣ ማስረጃቸው ግልጽ፣ እይታቸው የተብራራ ነበር። ድርሰቶቻቸው ዘመናትን ተሻግረው ዛሬም ድረስ በያንዳንዱ ሙስሊም ቤት ዉስጥ ይገኛሉ።

ኢማም አንነወዊ – በቀንም ይሁን በሌሊት አንድም የሚያባክኑት ጊዜ አልነበራቸውም። ሙሉ ጊዜያቸውን በዕውቀት ጉዳዮች ላይ ያውሉታል። መንገድ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ በማንበብ እና ትምህርቶቻቸውን በማጥናት የተጠመዱ ነበሩ። በዚህ መልኩ ዕውቀትን ሲገበዩ ለስድስተ ዓመታት ዘለቁ። ከዚያም ወደ መፃህፍት ዝግጅትና ለሙስሊሞችና ለመሪዎቻቸው ምክሮቻቸውን ወደማካፈል ፊታቸውን አዞሩ። ራሣቸውንም በእምነት ለማጠንከር በብርቱ ይታገሉ ነበር። ረቂቅ የሆኑ የፈቅሂ ዕውቀቶችን በማስተንተን ከዑለማኦች መንገድ ላለመውጣት ይመራመሩ ነበር። በቀልብ ሥራዎች ዙሪያም የራሣቸውን ሁኔታ ይገምግሙ፤ ቀልባቸውንም ከመጥፎ ነገር ለማንፃት ይጥሩ ነበር። ኢማሙ በጣም ትናንሽ በሆኑ ነገሮች ላይ ጭምር ራሣቸውን ይገመግሙ ነበር። በዕውቀታቸውና በዕውቀት ፍለጋ ስልታቸው የማይደክሙ ነበሩ። የአላህን መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲሦችንም በአግባቡ ያውቃሉ። ዓይነቶቻቸውንም ሁሉ እንዲሁ። ትክክለኛውንና ያልሆነውን፣ ውድቅ የሆነውንና እና ተቀባይነት ያለውን የሌለውን ይለያሉ። ትርጉሙን እና መልዕክቱንም ይገነዘባሉ።

ኢማም ነወወዊ ጊዜያቸውን በሙሉ በዕውቀትና በትግበራው ላይ ያዋሉ ታላቅ ዓሊም ናቸው። ከፊሉን ድርሰት ያዘጋጁበታል፣ ከፊሉን ይማሩበታል፣ ከፊሉን ደግሞ ይሰግዱበታል፣ ሌላውን ቁርኣን ለማንበብ፣ በጥሩ ነገር ለማዘዝና ከመጥፎ ለመከልከል ይጠቀሙበታል።

በቃል በማጥናት ሁኔታቸው (በሒፍዛቸው) ሲበዛ ፈጣን ናቸው። በአጭር ጊዜ ዉስጥ በርካታ መጽሐፎችን ሐፍዘዋል። በዚህም የኡስታዛቸውን አቢ ኢብራሂም ኢስሓቅ ኢብኑ አሕመድ አልመግሪቢን ዉዴታና አድናቆት ማትረፍ ችለዋል። በትምህርት ማዕዳቸውም ላይ የየዕለቱን ትምህርት መልሰው ለታዳሚዎች እንዲያስተምሩ አድርገዋቸው ነበር። ከዚያም በአል-አሽረፊያ የሐዲሥ ማዕከል እና በሌሎችም ተምረዋል።

ተማሪያቸው የነበረው ዐላአዲን ኢብኑ አልዐጣር ስለ ትምህርት አቀሳሰማቸው ኢማም ነወዊ የነገሩትን ሲናገር – በየቀኑ በተለያዩ ሸይኾች እጅ አሥራ ሁለት ትምህርቶችን ከነማብራሪያውና ትክክለኛ መልዕክቱ ይማሩ ነበር። በአል-ወሲጥ ዙሪያ ሁለት ትምህርት፣ በሙሀዘብ አንድ ትምህርት፣ በአል-ጀምዕ በይነ ሶሒሐይን ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በሶሒሕ ሙስሊም ዙሪያ አምስት ትምህርት፣ በለምዕ ኢብኑ ጀኒይ ነሕው ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በኢብኑ ሰኪት ኢስጢላሕ አልመንጢቅ የቋንቋ ትምህርት ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በሶርፍ ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በኡሱል አልፊቅህ ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በአስማእ ሪጃል ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ በኡሱለዲን ዙሪያ አንድ ትምህርት፣ የሚማሩ ሲሆን ከነኚህ ትምህርቶች ጋር የተያያዘውን ሁሉ ከነማብራሪያው፣ ጥያቄ ከሚያስነሳው ጉዳይና ከቋንቋ አንጻር እና ከመሳሰሉት ሁሉ አስፈላጊውን ነገር  ይፅፉ ነበር።

ከርሣቸውም እጅ በርካታ ዑለማኦች ተምረዋል። ዕውቀታቸውም በተለያዩ አገራት ተበትኗል፣ ስለ እስልምና ጥያቄዎች መልስ የሠጡባቸው ትምህርቶችም በሰፊው ተሠራጭተዋል። በድርሠቶቻቸውም በበርካታ ሙስሊም አገራት የሚገኙ ሙስሊሞች ተጠቃሚ ሆነዋል። መጽሐፍቶቻቸው ዛሬም ድረስ ዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊዎች ናቸው።

የኢማም አንነወዊ ሸይኾች

ኢማም ነወዊ በአባ አልፈረጅ ዐብዱረሕማን ኢብኑ አቢ ዑመር እና በዋና ሸይኻቸው ሙሐመድ ኢብኑ አሕመድ አልመቅዲሲ እጅ ተምረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከአባ ኢስማዒል ኢብን አቢ አስሓቅ ኢብራሂም ኢብኑ አቢ አልዩስር፣ ከአባል ዐባስ አሕመድ ኢብኑ ዐብዱ ዳኢም፣ ከአቡልበቃእ ኻሊድ አንናቡሊሲ ፣ ከአባ ሙሐመድ ዐብዱልዐዚዝ ኢብኑ ዐብደላህ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልሙሕሲን አልአንሷሪይ፣ ከዲያእ ኢብኑ ቲማም አልሒሲ፣ ከአልሓፊዝ አባልፈድል ሙሐመድ ኢብኑ ሙሐመድ አልበክሪይ፣ ከአባልፈዳኢል ዐብዱልከሪም ኢብኑ ዐብዱሶመድ (የዳመስቆ ኸጢብ)፣ ከአባ ሙሐመድ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ሳሊም ኢብኑ የሕያ አልአብናሪ፣ ከአባ ዘከሪያ የሕያ ኢብኑ አልፈትሕ አሲራፊ አልሐራኒ፣ ከአባ ኢስሐቅ ኢብራሂም ኢብኑ ዐሊ ኢብኑ አሕመድ ኢብኑ ፋዲል አልዋሲጢ እና ከሌሎችም እጅ ተምረዋል።

ኢማም ነወዊ ለዕውቀት ያበረከቱት አስተዋጽኦ

በፊቅሂ ዙሪያ

ኢብኑ አልዐጣር እንዲህ ይላል – “ነወዊ የሻፊዒ መዝሀብ ጥልቅ አዋቂ ናቸው። መርሆቹን፣ መሠረቶቹን እና ቅርንጫፎቹን ሁሉ አሳምረው ያውቃሉ። እንዲሁም ስለ ሶሓቦች እና ታቢዒዮች መዝሀብም፣ ሙስሊም ዑለማኦች ስለተለያዩባቸውና ስለተስማሙባቸው ነጥቦች፣ ይበልጥ ዕውቅና ስላገኘውና ስለተተወው እይታ ሁሉ ያውቃሉ። በዚህ ሁሉ አቋማቸው ቀደምት ደጋግ ሙስሊሞችን መንገድ ይከተሉ ነበር።›

በሐዲሥ ዙሪያ

አንድ ዘመን በመጣ ቁጥር በዚያ ዘመን ዉስጥ አላህ የሐዲሥ ሰዎችን ያስነሳል። እነርሱም በሐዲሥ ዕውቀት ዙሪያ  በማብራራት፣ አዲስ አቅጣጫ በማሳየትም ሆነ በማረም በኩል ሌላ አብዮት ያስነሳሉ። በመካከለኛው ዘመን ከተነሱ ትላልቅ ስብእናዎች መካከል ኢብኑ ሶላሕ፣ ኢማም ነወዊ፣ አልሚዚይ እንዲሁም ኢማም ዘሀቢ ይጠቀሳሉ። ኢማም ነወዊ ከነርሱ ባላቸው የጠለቀ ዕውቀት ይለያሉ። በፊቅሂም ሆነ በሐዲሥ ዕውቀት እርሣቸውን የሚስተካከል አልነበረም ማለት ይቻላል።[1]

ኢብኑ አልዐጣር እንደዘገቡት ኢማም ነወዊ ቡኻሪና ሙስሊምን፣ የአቢ ዳዉድን፣ የቲርሚዚን እና የነሳኢን የሒዲሥ ጥንቅሮችን፣ የኢማም ማሊክን አልሙወጦእ፣ የሻፊዒን እና የኢማም አሕመድን ሙስነድ፣ የዳሪሚን፣ የአቢ ዐዋናን፣ የአቢ የዕላ አልመውሱሊን፣ የኢብኑ ማጀህ ሱነንን፣ የዳር ቁጥኒን፣ የበይሀቂን፣ የበገዊ ሸርሑ ሱናን እና የተፍሲር ኪታባቸውን መዓሊሙ ተንዚልን፣ የዙበይር ኢብኑ በካር አልአንሳብን፣ የነባቲያ አልኹጠብን፣ የአልቁሸይሪ ሪሳላን፣ የኢብኑ ሱንኒን ዐመል አልየውም ወልለይላን፣ የአልኸጢብን ኣዳቡ ሳሚዕ ወርራዊን እና ሌሎችንም በርካቶችን ተምረዋል። እነኚህ ሁሉ በሸይኹ የእጅ ጽሑፍ የተጠቀሱ ናቸው።

ኢማም ነወዊ እና የሐዲሥ ዕውቀታቸው

ኢማም ነወዊ እንደ በርካታ ሙሐዲሶች ጥረታቸውን በሐዲሱ ዘገባ ሰንሰለት (ሰነድ) ዙሪያ ብቻ ትኩረት አያደርጉም ነበር። የሐዲሡን መልዕክት ለማወቅ ትልቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህንኑ በሶሒሕ ሙስሊም ማብራሪያቸው መቅድም ላይ ጠቅሰውታል። ከዚያም ወደዕውቀታዊ ጭብጡ ያተኩራሉ። ከርሣቸውም በርካታ ሰዎች ተምረዋል። አቡልፈትሕ፣ አልሚዚይ እና ኢብኑል ዐጣር ጥቂቶቹ ናቸው።

ኢማም ነወዊ እና የቋንቋ ትምህርት

አንድ ሰው ቁርኣንንም ሆነ ሐዲሥን መረዳትና ትርጉማቸውንም ሊገነዘብ የሚችለው፣ የቀደሙትንም ሆነ ኋላ ላይ የመጡትን የዕውቀት ሰዎች አባባል በአግባቡ የሚገነዘበው የዐረቢኛ ቋንቋን ጠንቅቆ ሲያውቅ ነው። ይህም ነሕው እና ሶርፉን ያጠቃልላል (ስለ ዐረብኛ ቋንቋ ሰዋስዎና ህግጋት ጥናት)። የቃላትንም ትርጓሜ ሊያውቅ ግድ ይላል። ይህ የኢማም ነወዊ አቋም ሲሆን ሌሎችንም የሚመክሩበት ጉዳይ ነው። ተህዚብ አልአስማእ ወል-ሉጋት በተሠኘውና የቋንቋ አስፈላጊነት ላይ አተኩረው ባዘጋጁት መጽሐፋቸው መቅድም ላይ እንዲህ ብለዋል –  “አስፈላጊ ስለመሆኑ ብዙ ማብራራት አያስፈልግም። ሁሉም ዑለሞች ተስማምተውበታልና። እንዲያውም ሙፍቲ፣ ኢማምም ሆነ ቃዲ የሆነ ሰው ማወቁ መስፈርት ነው። መማሩም የወል ግዴታ ነው። ከፊሉ ካልተማረ ግዴታነቱ ከሌላው ላይ አይወድቅም።”[2]

ሌሎች ሁለቱ የነወዊ መጽሐፎች “ተሕሪር አት-ተንቢህ” እና “ተህዚብ አልአስማእ ወልሉጋት” ኢማም ነወዊ በቋንቋ ዕውቀት ዙሪያ በዘመናቸው አቻ እንዳልነበራቸው የሚያመላክቱ ናቸው።

ኢማም ነወዊ በሕክምና ሥራ ለመሠማራት ስለመሞከራቸው

ኢማም ነወዊ እንዲህ ይላሉ – “በሕክምና ሥራ ለመሠማራት በዉስጤ አስቤ ነበር። ለዚህም ሲባል የኢብኑ ሲናን ‘አልቃኑን’ መጽሐፍ ገዛሁኝ። በዚሁ ዙሪያ ለመሥራትም ቆርጬና አቋም ይዤ ተነሳሁኝ። ሆኖምግን ልቤ ላይ ተጋረደ። ለበርካታ ቀናትም ምንም ሳልሠራ ቆየሁኝ። ጉዳዩን መልሼ አሰብኩበት። እንዴት ነው ይህን ነገር ላስብ የቻልኩት አልኩኝ። ስለህክምና አብዝቼ ማሰቤ እንደሆነ አላህም ሰበቡን አሳወቀኝ። ወዲያውኑ የገዛሁትን የኢብኑ ሲናን መጽሐፍ አውጥቼ ሸጥኩኝ። ከህክምና ጋር የተያያዙ ነገሮችንም ከቤቴ አስወጣሁኝ። ቀልቤ እንደገና ሲበራ ታወቀኝ። መጀመሪያ ወደነበርኩበት ሁኔታ ተመለስኩኝ።”[3]

ምናልባት ያ ኢማሙን ያገኛቸው የቀልብ ጨለማ በሕክምና ዙሪያ እንዳይጽፉ አግዷቸው ይሆናል። ስለ ሕክምናም ነገሮች እንዲከብዱ አድርጎባቸው ይሆናል። ኢማም ነወዊ ወደ ሕክምና ትምህርት ሊያዘነብሉ የቻሉት ምናልባት “ከሐላል እና ከሐራም ዕውቀት ቀጥሎ ከሕክምና ትምህርት በላይ ምርጥ የሆነ ትምህርት አላውቅም” ያሉትን የኢማማቸውን የኢማም አሽ-ሻፊዒን አባባል ተከትለው ሊሆን ይችላል።[4]

ኢማም ነወዊ የሠሩባቸው ኃላፊነቶች

ኢማም ነወዊ የኢብኑ ኸልካን ምክትል በመሆን በኢቅባሊያ መድረሳ እስከ 669 ዓ.ሂ መጨረሻ ድረስ ሠርተዋል።[5] እንዲሁም በአል-ፈለኪያ እና ሩክኒያ መድረሳዎችም ምክትል ሆነው አገልግለዋል።[6]

ኢማም ነወዊ ከ665-676 ዓ.ሂ ባለው ጊዜ ዉስጥ የአል-አሽረፊያን ሐዲሥ ማዕከል በዋና ኃላፊነት መርተዋል። በወቅቱ ይህ ማዕከል በሐዲሥ ትምህርት በሻም ምድር እጅግ ይታወቅ ነበር። እዚያ የገባ ሰው ሙሉ ጊዜውን ዕውቀት በመቅሰም ላይ ነው የሚያሳልፈው። በተለይ የሐዲሥ ዕውቀትን። “የሐዲሥ ማዕከሉ ሸይኽ” የተባለ ሰው በዕውቀት ደረጃ ከፍተኛውን ማዕረግ እንደተጎናፀፈ ነው የሚቆጠረው። ከኢማም ነወዊ በፊት የማዕከሉ ኃላፊ የነበሩት ተቂየዲን ኢብኑ ሶላሕ እና ሺሃቡዲን አቡ ሻማህ አልመቅዲሲ ነበሩ።

ታጅ አስ-ሱብኪ እንዲህ ይላል “አባቴ እንዲህ አሉኝ .. ከኢማም ነወዊ እና ኢብኑ ሶላሕ በላይ ሓፊዝ እና አላህን ፈሪ የሆነ ከአል-አሽረፊያ የሐዲሥ ማዕከል አንድም ሰው አልገባም።”[7]

የኢማም ነወዊ ድርሠቶች

ኢማም ነወዊ በዚህች ምድር ላይ የኖሩት ለ46 ዓመታት ብቻ ነበር። ይህ ከመሆኑ ጋር ትተው ያለፉት የድርሰት ክምችት ለዕድሜያቸው ቢካፈል በየቀኑ ሁለት ቀለል ያሉ መጽሐፍትን የመፃፍ ያህል ነው።[8] ወደ ዕውቀቱ ዓለም የገቡት በ18 ዓመታቸው መሆኑን ስናስተውል ደግሞ በርግጥም አላህ ዕድሜያቸውን እንደባረከላቸውና እርሣቸውም የቱን ያህል ብርቱ ጥረት ያደርጉ እንደነበር እንረዳለን።

እጅግ ከሚታወቁ ድርሰቶቻቸው መካከል

  • ሸርሑ ሙስሊም ፡- የኢማም ሙስሊምን መጽሐፍ መሠረት ያደረገ ዳጎስ ያለ ማብራሪያ ሲሆን የዘገባ ሰንሰለቶችን፣ ስለ ቋንቋዊ ትርጓሜዎች፣ ስለ ሐዲሡ አጠቃላይ ትርጉሞች፣ ከየሐዲሡ ስለሚገኙ ጠቃሚ ትምህርቶች፣ የየሐዲሡ ጥንካሬና ድክመት ዙሪያ ስለተባሉ ጉዳዮች እና ስለ ሌሎችም ጠቃሚ ሀሳቦች በዝርዝር ይዳስሳል።
  • ረውዳ ወይም ረውደቱ ጣሊቢን – በኢማም ሻፊዒ መዝሀብ ዙሪያ ወሳኝና ትላልቅ ከሚባሉ መጽሐፎች መካከል አንዱ ነው። ነወዊ ይህን መጽሐፍ ያዘጋጁት “ሸርሕ አል-ከቢር” የተሠኘውን የኢማም ራፊዒን መጽሐፍ አሳጥረው ነው። መጽሐፉ ብዙ ሙገሳ ተችሮታል።
  • አልሚንሃጅ – በብዛት ተሠራጭተው ከሚገኙ የኢማም ነወዊ መጽሐፎች መካከል አንዱ ነው። የራፊዒን “ሙሐረር” የተሠኘውን መጽሐፍ አሳጥረው ያቀረቡት ነው። መጽሐፉ ታርሟል። የተለያዩ አማራጮችም አሉት።
  • ሪያዱ ሷሊሒን – የሐዲሥና የምክር መጽሐፍ ነው። ልዩ የሚያደርገው እንደዚህ መጽሐፍ እምነት የተጣለበትና በዓለም ላይ የተሠራጨ መጽሐፍ አለመኖሩ ነው። ታላቁ ዓሊም ሙሐመድ ኢብኑ ዐሊ አስ-ሲዲቂ አሽሻፊዒ “ደሊሉል ፋሊሒን ሊጠሪቅ ሪያዱ ሷሊሒን” በሚል ሥያሜ ለመጽሐፉ ማብራሪያ ሠርተውለታል። ሪያዱ ሷሊሒን ሌሎች ማብራሪያዎችም በተለያዩ ዑለሞች ተዘጋጅቶለታል።
  • አልአዝካር – በዚህ መጽሐፍ አንድ ሙስሊም የቀንና የሌሊት ሥራዎች ተዳሰውበታል። የየአጋጣሚዎች ዚክሮች (ዉዳሴዎች)ንና ድንጋጌዎቻቸውን ይዟል።

ሌሎች መጽሐፎች

አት-ቲብያን፣ ተሕሪር አት-ተንቢህ፣ አልኢዳሕ ፊልመናሲክ፣ አልኢርሻድ፣ አት-ተቅሪብ፣ አል-አርበዒን አን-ነወዊያ፣ ቡስታን አል-ዓሪፊን፣ መናቂብ አሽ-ሻፊዒ፣ ሙኽተሶር አሰድ አልጋባ፣ አልፈታዋ፣ አደብ አልሙፍቲ ወልሙስተፍቲ፣ ሙኽተሶር ኣዳብ አልኢስቲስቃእ፣ ሩኡስ አልመሳኢል፣ ቱሕፈት ጡላብ አልፈዷኢል፣ አት-ተርኺስ ፊልኢክራም ወልቂያም፣ መስአለቱ ተኽሚስ አልገናኢም፣ ሙኽተሶት አት-ተዝኒብ፣ መስአለቱ ኒየቱል ኢግቲራፍ፣ ደቃኢቅ አልሚንሃጅ፣ ረውዳ፣ አት-ተቅሪብ ወት-ተይሲር ይገኙበታል።

ህልፈታቸው

ኢማም ነወዊ የሞቱት በ676 ዓ.ሂ ወደ ነዋ ከተመለሱ በኋላ ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ ለወቅፍ የተሠጡና የተዋሷቸውን መጽሐፎችን ለየባለቤቶቻቸው መልሰዋል። የሸይኾቻቸውን መቃብሮች ጎብኝተውም አልቅሰዋል። እንዲሁም በሕይወት ያሉትን ወዳጆቻቸውን ጎብኝተው ተሰናብተዋልም። አባታቸውንም እንዲሁም በይት አልመቅዲስ (ኢየሩሳሌምን) እና አልኸሊልን (ቤተልሄምን) ጎብኝተዋል። ከዚያም ወደ ነዋ ተመለሱ። እዚያም ታመሙ። በረጀብ 24 ቀን እዚያው ሞቱ።

አላህ ኢማም ነወዊን በሰፊ እዝነቱ ዉስጥ ያስገባቸው። ለኢስላምና ለሙስሊሞች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሉ በመልካም ይመንዳቸው።

[1] عبد الغني الدقر: الإمام النووي ص55

[2]  النووي: تهذيب الأسماء واللغات، 1/ 3

[3]  السخاوي: فتح المغيث شرح ألفية الحديث، ص6- 7، والتذكرة 4/1470

[4]  : عبد الغني الدقر: الإمام الشافعي ص273

[5] ابن كثير: البداية والنهاية 13/ 279

[6] ابن كثير: البداية والنهاية 13/ 279

[7] النعيمي، عبد القادر: الدارس في تاريخ المدارس، دار الكتب العلمية – بيروت 1990م، 6/ 36

[8] አንዱ መጽሐፍ የአርባ ገጽ ያህል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here