ባለ ትቢያው ሰማዕት_ ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር

0
9106

የህይወት ታሪኩ ለሰው ልጅ ክብር ነው፡፡ የመስዋዕትነትና ፅኑ እምነት ተምሳሌት ነው፡፡ የሙስዓብ ኢብኑ ዑመይር የኢሥላም ጉዞ …….

ዑመይር በባህረ ሰላጤዋ እምብርት መካ፣  የሁሉ ማረፊያ በሆነው  በኢብራሂም የተገነባውን ቤት ካዕባን ከበው ከሚኖሩ ከበርቴዎቿ መሃል አንዱ ነው፡፡ ስልጣንና ሀብት ነበረው፡፡ ታዲያ ደስታና ጫወታ በከበባት በአንዷ ለሊት የመካ ከበርቴዎች ሳቅና ፌሽታ ወደሚንጣት ቤት ተፋጠኑ፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ዑመይርንና ኸናስ ቢንት ማሊክ የተባለችውን ባለቤቱን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ነበር፡፡ አላህ አዲስ ልጅ በመስጠት ከችሮታው ዋለላቸው፡፡ ሙስዐብን መልከ መልካሙን፣ ሙሰዐብን የቁረይሽን ህያው ጌጥን……                                          ወራት ተፈተለኩ፡፡ዓመታት ነጎዱ፡፡ ሙስዐብ ተከፈነሰ፡፡ ታዲያ በእያንዳንዱ የህይወቱ እርከኖች ላይ ምቾትና ተድላ አብረውት ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ በኩል የእንክብካቤው ብዛት ምንም እስከማይቀር ድረስ ነበር፡፡ በተለይ እናቱ ከሌሎች ከበርቴ ባልንጀሮቿ  ልጆች ጎልቶ እንዲታይ ለውጫዊ ገፅታው ከፍተኛ መዋለ-ንዋይ ታፈስ ነበር፡፡                                                                                        መካ ላይ የወንድ ውበት ሲነሳ ግንባር ቀደሙ ነበር፡፡ ገፅታው ለእይታ ማራኪና ቆንጆ ነበር፡፡ ሙስዐብ በመካ ጎዳናዎችና መንገድ ጠርዞች ካለፈ እርሱን ለማየት የቆነጃጅትና ውበት አድናቂዎች አንገት ይመዘዛል፡፡ ሙስዓብ ሁሌ ደስተኛና ፈገግታ የማይለየው ለጋ ወጣት ነበር፡፡ ከእድሜው ለጋነትና ውብ ገፅታው የተነሳ የስበሰባዎችና ጥሪዎች ጌጥ ነበር፡፡ ውበቱና የአዕምሮው ብስለት የሸፈቱ ልቦችን የተዘጉ በሮችን ይከፍቱ ነበር፡፡

ወራት ጉዟቸውን ቀጥለዋል አመታትም ቅብብሎሹን አጡፈውታል፡፡ የሙስዓብም የህይወት እሽክርክሪት ቀጥሏል፡፡ ህመም፣ጭንቀትና ችግርን ፍጹም አያውቃቸውም፡፡ ነገር ግን የሙስዐብ እናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሌም የጥልቅ አስተሳሰብን ፋና ታያለች፡፡ከብሩህ ፊቱ ላይ ጥንካሬንና ቆራጥነትን ታነባለች፡፡ ቢሆንም ግን የዚህ ጥንካሬ ምንጩ ርቋታል፡፡ እናት የልጇን ውስጥ የማንበብ ችሎታ ቢኖራትም ይህ ግን ተሳናት፡፡ ቀናት ወደፊት አንድ ሲሉ የሙስዓብም ጥንካሬ ይፈረጥማል፡፡ ዛሬ ያለበት ላይ ሆኖ ያለፉ ቀናቱን ሲያስባቸው አሰልቺ ህልሞችና ቅዠት ሆኑበት፡፡

ከእለታት በአንዱ ቀን ይህ ወጣት ሰዎች ከታማኙ ሙሃመድ ሰምተው የሚያወሩትን ይሰማል፡፡ ነብዩ(ሰዐወ)  አላህ እርሳቸውን አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርጎ እንደላካቸው፣ ወደ ብቸኛው ተመላኪ አንድነት ተጣሪ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡                                                መካ ከተማ ነግቶ በመሸ ቁጥር ጭንቀትና ጉዳይዋ ሙሐመድና ኢስላም ከሆኑ ሰንብቷል፡፡ ታዲያ ይህ በምቾት ክልል ውስጥ ያለው መልካሙ ሙስዓብ የዚህን ወሬ ዱካ ከሌሎች በተለየ መልኩ አፈንፍኖ ነበር የሚሰማው፡፡                                                              ነብዩ(ሰዐወ) ካመኑ ተከታዮቻቸው ጋር በመሆን ከቁረይሽ ረብሻና ማደናቆር ራቅ ብለው ሶፋ ተራራ ስር በሚገኘው አርቀም ቤት ውስጥ እንደሚሠበሠቡ ሠማ፡፡ አላቅማማም፡፡ የማየትና እርጋታ ናፍቆት እየቀደመው ወደ አርቀም ቤት አመራ፡፡ ነብዩ(ሰዐወ) ለባልደረቦቻቸው ቁርአንን ያነቡላቸዋል፡፡ ቀጥሎም ለታላቁ አላህ ይሰግዳሉ፡፡ ኢማን በሙስዓብ ልብ ውስጥ ቦታውን ሲይዝ አልቆየም፡፡ ከነብዩ(ሰዐወ) ልቦና ተንቆርቁሮ በከናፍሮቻቸው መሃል የሚወጣው የቁርአን ብርሃናማ መልዕክት ወደሚሰሙ ጆሮዎችና ወደሚያስተነትኑ ህሊናዎች ይፈሳሉ፡፡ በዚህች ምሽት ታዲያ የሙስዓብ ልቦና ተረታ፡፡ አንዳች ነገር ከቆመበት ቦታ ፍንቅል አደረገው፡፡ ያላሰበው የደስታ ስሜት ሊያበረው ቀረበ፡፡ ድንገት ነብዩ(ሰዐወ) ዘንድ ተጠጋ፡፡ ነብዩ(ሰዐወ)በቀኝ እጃቸው የሙስዓብን ደረት ዳበሱት፡፡ እርግጥ የርሱ እርጋታ ጥልቅ ነበር፡፡ በዓይን እርግብግብታ ቅፅበት የጥበብን ጥግ ከዕድሜው በላይ ተላበሰ፡፡ የዘመናትን የጉዞ መስመር ሊቀይር ታጨ፡፡

እናት ልጇን በሃሳብ ዱካ ትከተለው ጀመር፡፡ ተፈታተነችውም፡፡ ልጅ ግን እርጋታው ይጨምራል፡፡ ዑስማን ኢብኑ ጦልሐ አል ሂንዲ ለእናቱ ኢስላምን እንደተቀበለ ሲነግራት ብዙም አልቆየም፡፡ በእርግጥ ዑስማን ሙስዓብ የነብዩን(ሰዐወ) ዓይነት ስግደት ሲሰግድ አይቶት ነበር፡፡ ሙስዓብ ጥቅልል ብሎ ዳሩል አርቀም(ነብዩ መካ ውስጥ ኢስላምን በድብቅ ያስተማሩበት የመጀመሪያው ቤት ነው)ገባ፡፡ በኢስላማዊ ጥሪ ታሪክና ህይወት ውስጥ ህያው ቅርስ ወደሆነችው ቤት፡፡ በወቅቱ በሙስሊሞች ጉልበት ላይ ተጨማሪ ኃይል ሆነ፡፡የነብዩ(ሰዐወ) ኢስላማዊ ጥሪ ከደሙ ተዋሃደች፡፡ እምነቱን በማንነቱ ላይ ከታች ወደ ላይ ካበው፡፡ ከማመኑ በፊት የነበረበትን ህሊናዊ ጨለማ የኋሊት ቃኘው፡፡ አሁን ስላለበት ኢስላማዊ ብርሃንና ጠንካራ፣ ነፃ ተከታዮቹ አስተነተነ፡፡ የሙስዓብ ኢስላምን መቀበል ትልቅ ስደት ነበር፡፡ ሙስዓብ የመጀመሪያውን ስደት ያደረገው ከምድራዊ ብልጭልጮችና ጌጧ ወደ አላህና መልዕክተኛው ነበር፡፡ የጥልቅ ለውጡ ሚስጥሩም ይኸው ነበር፡፡ መካ ውስጥ የኢስላም ሕንፃ ግንባታ አንድ ጡብ ለመሆን በቃ፡፡ ሙስዓብ ኢስላምን ከመቀበሉ ጋር ተያይዞ ከእናቱ በስተቀር ምድር ላይ የሚፈራው ኃይል አልነበረም፡፡ የእናቱ ነገር ግን አሳሰበው፡፡ አላህ በጉዳዩ ላይ ፍርዱን እስኪያመጣ ድረስ ኢስላምን መቀበሉን መደበቅ እንዳለበት ወሰነ፡፡ ነገር ግን መካ በዚያ ወቅት ምንም ሚስጥር የላትም፡፡ የቁረይሽ ዓይንና ጆሮ በየመንገዱ ላይ መረጃን ይፈልጋል፣ያሰራጫልም፡፡ በእያንዳንዷ የእግር ፋና ላይ ትንታኔ ይሰጣል፡፡ ሙስዓብ እናቱ፣ ቤተሰቦቹና ቅርብ ዘመዶቹ በሙሉ ኢስላምን እንደተቀበለ አወቁበት፡፡ ነገርግን በመኃላቸው ቆሞ በፅናት ነብዩ(ሰዐወ) የተከታዮቻቸውን ልቦና የሚያፀዱበትን፣ ጥበብንና ከፍታን የሚሞሉበትን፣ፍትህንና ጥንቃቄን የሚያስተምሩበትን ቁርአንን ያነብላቸው ገባ፡፡ እናቱ በአንድ ጥፊ ልታሰቆመው አሰበች፡፡ ግን በሙስዓብ ፊት ላይ ላይጠፋ የበራው የእምነት ብርሃን የተዘረጋችውን ጥፊ ከምንም አልቆጠራትም፡፡ ከእምነቱ ፍንክች እንደማይልና እንደማይመለስ እርግጠኛ ሆኑ፣ ተስፋም ቆረጡ፡፡ ከቤቱ አንዱ ጥግ ላይ አሰረችው፡፡ ተዘጋበት፡፡ እስረኛ ሆነ፡፡ የቅጣትን ዓይነት ከየቀለማቱ አቀመሱት፡፡ እንዳይንቀሳቀስም አገቱት፡፡ በሰንሰለትም ጠፈሩት፡፡ ያላወቁት ነገር ግን ይህ ሁሉ የስቃይ ዶፍ በእምነት በከበረች ነፍስ ፊት ደቃቃና ከንቱ ልፋት መሆኑን ነበር፡፡

ወደ ሐበሻ(አቢሲኒያ) በተደረገው የመጀመሪያው ስደት፣ ከአማኝ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ወደ አላህና መልዕክተኛው ሁለተኛው ስደቱን በነጃሺ አፈር ላይ አደረገ፡፡ እዚሁ ሐበሻ ላይ የኑሮ ድርቆሽ ሙስዓብን ክፉኛ አገኘው፡፡ በችግር ሰበብ ወደ መካ ከተመለሱት አንዱም ሆነ፡፡ ከአድቃቂ ድህነት ጋር መኖር ያዘ፡፡ በዐቂዳ ጥላ ስር በውዴታ የሚገኝን ደስታ፣ የመጪውን ዓለም ማብቂያ የለሽ ደስታ እያሰበ፣  የነብዩ ባልደረባ መሆንን እያሰበ ኑሮን ገፋ፡፡ ወራት ያልፋሉ፣አመታት ይነጉዳሉ፡፡ የዚህ ወጣት ችግርና ድህነትም ይጨምራል፡፡ ትእግስትና ፅናትን ጨበጠ፡፡ በአንድ ወቅት ነብዩ(ሰዐወ) ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ተቀምጠዋል፡፡ ሙስዓብ የተቀደደች ብትን ልብስ አጠላልፎ ለብሶ መጣ፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ሀፍረተ ገላውን ለመሸፈን ሲል በእሾህ ቀጣጥሎታል፡፡ ከብርድና ቅዝቃዜ የተነሳ ሰውነቱ ልክ እባብ ከሞተ በኋላ ክሽ ብሎ እንደሚደርቀው ደርቋል፡፡ የነብዩ(ሰዐወ) ባልደረቦች ሲያዩት በማዘንና መራራት አንገታቸውን ደፉ፡፡ ከእነርሱ ውስጥም እርሱ ያለበትን ችግር ሊቀርፍ የሚችል አቅም ያለው አልነበረም፡፡ ሙስኣብ ሰላምታ አቀረበ፡፡ ነብዩም(ሰዐወ) ሰላምታውን ከመለሱ በኋላ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ መካ ውስጥ ከቁረይሽ ልጆች ውስጥ ከወላጆቻቸው ዘንድ በፀጋና ምቾት እንዲትረፈረፍ የተደረገ ከሙሰዓብ በቀር አላየሁም፡፡ የአላህና መልእክተኛው ፍቅር ግን ከዛ ውስጥ አወጣው፡፡››

ሙስዓብ ኢብኑ ዑመይር ወደ መዲና የመጀመሪያው የአላህ ነብይ ልኡክ

የመጀመሪያው የዐቀባ ቃል ኪዳን ላይ የተሳተፉ ከ12 በላይ የመዲና ሰዎች መካን ለቀው ሲሄዱ ከእነርሱ ጋር ሙስዓብን አብረው ላኩት፡፡ ቁርአንን ያስተምራቸዋል፡፡ የእምነቱን መሰረታዊ ይዘቶች በልቦናቸው ያፀናል በሚል ሀሳብ ማለት ነው፡፡ መዲና እንደደረሱም ሰዒድ ኢብኑ ዙራራ ዘንድ አረፈ፡፡ ወደ አንሷሮች(የመዲና ነዋሪዎች) ዘንድ በመሄድ ወደ አላህና መልዕክተኛው ይጠራቸዋል፡፡ አንድ ሁለት እያለ ብዙ ሰው ወደ ኢስላም ገባ፡፡ አንሷሮች ወደ ኢስላም በገፍ ገቡ፡፡ ሰዒድ ኢብኑ ሙዐዝና ኡሰይድ ኢብኑ ሁዶይር በሙስዓብ እጅ ኢስላምን ተቀበሉ፡፡ ከነርሱ ጀርባ ደግሞ አውስና ኸዝረጅ(መዲና የነበሩ ሁለት ታዋቂ ብሄሮች ናቸው) ሌሎችም ወደ ኢስላም ከተሙ፡፡ ያ ማለት ግን ፈተናዎች አልገጠሙትም ማለት አይደለም፡፡ አንድ ቀን ሰዎችን እያስተማረ ነበር፡፡ ከመዲና ጎሳ አለቆች አንዱ የሆነው ኡሰይድ ኢብኑ ሁዶይር ኢስላምን ሳይቀበል በፊት መጣ፡፡ ኡሰይድ እነዚህን ሰዎች ከዚህ በፊት ስለማያውቁት አንድ አምላክ እየነገረ በእምነታቸው ላይ ጥርጣሬን እያሳደረና እየፈተናቸው ነው በሚል በቁጣ ገንፍሎ እልህ እየገፋው ወደ ሙስዓብ ቀረበ፡፡ ሙስዓብን ከበው ሲማሩ የነበሩ አማኞች መምጣቱን ሲያዩ ርዕደት ያዛቸው፡፡ ፍርሃት ዋጣቸው፡፡ ሙስዓብ ግን የፊቱ ገፅታ እንኳ አልተቀየረም፡፡ አስዓድ ኢብኑ ዙራራ አብሮት ነበር፡፡ ኡሰይድ ተጠጋና   ‹‹ ህይወታችሁን ማጣት የማትሹ ከሆነ ደካሞቻችንን ከማጃጃል ታቅባችሁ ከዚህ አካባቢ ጥፉ፡፡›› ብሎ በቁጣ ተናገራቸው፡፡ ከሃይሉ ጋር እንደረጋ ባህር፣ እንደንጋት ወጋገን ስንብት በሚመስል መልኩ የሙስዓብ ከናፍሮች ቃላትን አሳምረው ማውጣት ጀመሩ፡፡‹‹ቅድሚያ ተቀምጠህ ብትሰማንና ጉዳያችንን ከወደድከው ትቀበለዋለህ፣ከጠላኸው ደግሞ እንሄዳለን፡፡›› አለው፡፡

ኡሰይድ የምሉእ አስተሳሰብና አስተውሎት ባለቤት ነበርና ‹‹ልክ ብለሃል›› ብሎ የያዘውን ጦር መሳሪያ መሬት ላይ ጥሎ ተቀመጠ፡፡     ሙስዓብ ቁርአንን ያነባል፡፡ ሙሀመድ ኢብኑ ዓብዲላህ(ሰዐወ) የመጡበትን ጥሪ ይዘት ያብራራል፡፡ የኡሰይድ ግንባር የንጋት ፀሐይ እንዳገኘው መስታወት ያንፀባርቅ ጀመረ፡፡ ከወጣቱ አንደበት የሚወጡት ቃላት ተቆጣጠሩት፡፡ ሙስዓብ ንግገሩን እንደጨረሰ ኡሰይድና አብረው የነበሩት ሰዎች ‹‹ይህ ንግግር ምንኛ ያመረና እውነታ ነው›› አሉ፡፡ ‹‹ወደዚህ እምነት ለመግባ የሚከጅል ሰው ምንድን ነው ማድረግ ያለበት›› አሉም፡፡ሙስዓብም ‹‹ልብስና አካሉን ያፀዳል፡፡ የአላህን አንድነት ይመሰክራል፡፡›› ሲል መለሰ፡፡                                             ኡሰይድ ትንሽ ቆይቶ ከፀጉሩ ላይ ውሃ እየተንጠባጠበ መጣና ‹‹ላኢላሃ ኢለሏህ፣ሙሀመደን ረሱሉሏህ›› በማለት መሰከረ፡፡ ዜናው በአንዴ ተዳረሰ፡፡ ሰዒድ ኢብኑ ሙዓዝም መጣ፡፡ ሙስዓብ ዘንድ ጥቂት ተቀመጠ፡፡ ሰምቶት ልቡ ተማረከ፡፡ ኢስላምን ተቀበለ፡፡ ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳ ተከተለው፡፡  በነርሱ ኢስላምን መቀበል ፀጋዎች ሞሉ፡፡ የመዲና ነዋሪዎች እርስበርሳቸው ይጠያየቁ ገቡ፡፡                                  ‹‹ ኡሰይድ ኢብኑ ሁይዶይር፣ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳና ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ኢስላምን ከተቀበሉ የኛ ወደኋላ ማለት ምንድነው›› አሉ፡፡ ሁሉም ወደ ሙስዓብ ጎረፉ፡፡ ከአንደበታቸው እውነት እንጂ አይወጣም፣እንመን ብለው ኢስላምን ተቀበሉ፡፡ የመጀመሪያው የመልእክተኛው አምባሳደር ተልእኮውን በሚገባ ተወጣ፡፡ ውጤታማም ሆነ፡፡

ሙስዓብ ሰዎችን ጁምዓ ቀን ልሰብስብና ላስተምር፣ላሰግድ የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለነብዩ(ሰዐወ) ፃፈ፡፡ ተፈቀደለት፡፡ ሰኢድ ኢብኑ ኸይሰማህ ቤት ሰበሰባቸው፡፡ ይህ እንግዲህ በኢስላም ታሪክ ውስጥ በይፋ ሰውን ሰብስቦ ማስተማር የተጀመረበት አግባብ ነበር፡፡  ሙስዓብ ተልዕኮውን በዚህኛው ሶስተኛው ስደቱ ላይ ሞላ፡፡ ዓመታት ነጎዱ ፣የአውስና ኸዝረጅ ሓጃጆች(የሀጅ ተጓዦች) የሁለተኛውን የዐቀባ ቃልኪዳን ለመፈፀም ወደ መካ መጡ፡፡ ሙስኣብም አብሯቸው መጣ፡፡ የነብዩ(ሰዐወ) ናፍቆት እየገፋው፣ እንባ እያነቀው መካ ገባ፡፡ ወደ ነብዩ (ሰዐወ) ቤት ሮጠ፡፡ አገኛቸው፡፡ የናፍቆት ግንኙነት ነበር…….የአንሷሮችን ሁኔታና እውነታቸውን የሚገልፅ የብስራት ዜና ሪፖርታዥ አቀረበላቸው፡፡ ነብዩም(ሰዐወ) ወደ ካዕባ ተቅጣጭተው ለሁሉም መልካም ነገር እንዲገጥም ዱዓ አደረጉ፡፡ የደስታ ላብም ግንባራቸው ላይ ግጥም አለ፡፡

የሙስኣብ እናት ከመዲና የመምጣቱ  ዜና ደረሳት፡፡ ቅድሚያ ታዲያ በጣም ወደናፈቁት ነብይ ቤት እንደሄደም ሰማች፡፡ ‹‹ አንተ ወላጅን አማፂ ቅድሚያ በኔ አትጀምርም እንዴ›› ብላ  መልእክት ላከችበት፡፡ ሙስኣብም እንዲህ በማለት በመልእክተኛዋ መልእክትን ላከባት፡፡‹‹ ከአላህ መልዕክተኛ በፊት በማንም አልጀምርም፡፡› የእናት ፍቅሩ ጎተተው፡፡ ሊያያትም ሄደ፡፡ የኑሮ መራር በትር ያረፈበትን ገፅታውን ስታይ አዘነች፡፡ እንዲህም አለች‹‹ ይህ ሁሉ ነገር የደረሰብህኮ ካለህበት ስለሸፈትክ ነው፡፡›› አለችው፡፡ በፍጥነትም ‹‹እኔ ያለሁት በአላህ መልእክተኛ እምነት ኢስላም ላይ ነው፡፡ ይህን እምነት አላህ ለመልእክተናውና አማኞች ወዶታል፡፡›› ሲል መለሰላት፡፡ ከድንጋጤዋ የተነሳ ክፉ ተናገረችው፡፡ ‹‹እሺ አንዴ ሐበሻ፣ሌላ ጊዜ መዲና እያልክ ምን አመጣህ!›› አለችው፡፡ ራሱን እያወዛወዘ ‹‹በእምነቴ ከምትፈትኑኝ እሸሻችኋለሁ…..››አለ፡፡ እናቱ ዳግም አግታ የልጇን ወደርሷ መመለስ አሰበች፡፡ ይህንንም ሙስዓብ አወቀባት፡፡ ‹‹እናቴ ልታግቺኝ ብትሞክሪ የሚቀርበኝን ሁሉ ገድላለሁ፡፡››  አላት፡፡

የሙስዓብ ህልፈተ ዜና

ቀናት ነጎዱ፣ዓመታት ዙራቸው ከረረ፡፡ ነብዩ(ሠዐወ) ወደ መዲና ተሰደዱ፡፡ ሙስዓብ በንፁህ ልቦናና አንደበት ያመቻቻት የስሪብ(የመዲና ሌላ ስሟ ነው) ተቀበለቻቸው፡፡ መስተንግዶዋንም ጓዳዋን ሁሉ በመስጠት አሳመረች፡፡ የመካ ቁረይሾች ግን ለነብዩ(ሰዐወ) አልተኙም፡፡ መዲና ለምን ትመቻቸው በሚል የጥላቻ ዓይናቸው ቀላ፡፡ ብዙ የግድያ ሙከራ አደረጉ፡፡ የበድር ዘመቻ ተከሰተ፡፡ ብዙ አስተምህሮት ጥሎ በድል አለፈ፡፡ የኡሁድ ዘመቻ መጣ፡፡ ሙስሊሙ ሠራዊት ራሱን ማዘጋጀት ይዟል፡፡ የነብዩ(ሰዐወ) በመሃል ቆመው የእምነት ነፀብራቅ በጥልቅ የሚነበብበትን ፊት እየፈለጉ ነው፡፡ ይህ ፊት እንደተገኘም የኢስላምን ባንዲራ ተሸካሚ አድርገው ሊመርጡት ነው፡፡ ድንገት ሙስዓብን ጠሩት፡፡ መጣ፡፡ ከተከበረው እጃቸው ላይ ትልቅ አደራን ተቀበለ፡፡ አሁን ጦር መስክ ላይ ናቸው፡፡ ፍልሚያው ተጋጋመ፡፡ ተራራን ይጠብቁ ዘንድ የታዘዙት ቀስተኛ ሶሃቦች ትእዛዝ ጣሱ፡፡ አጋሪያን ወደ ኋላ ሲሸሹ ስላዩ ጦርነቱ የተቋጨ መሰላቸው፡፡ ወደ ምርኮ ተጣደፉ፡፡ ጥለውት ከመጡት ተራራ ጀርባ በኩል የኻሊድ ፈረሰኛ ጦር ድንገተኛና ስትራቴጂያዊ ከበባ በማድረግ ሙስሊሙ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፀመ፡፡ የሙስሊሙን ጦር በተኑት፡፡ ሰልፎቹን በጥሰው ውስጥ ገቡ፡፡ የኢስላምን ቋንጃ ሰብረው መገላገል ቋምጠዋል፡፡ ነብዩ(ሰዐወ) ላይ ተሯሯጡ፡፡ በቀስት ወጓቸው፡፡ ከዙሪያቸው ጥቂት ባልደረቦቻቸቸው ሲከላከሉ ነበር፡፡ ሶሃቦች እዚህም እዚያም ተዋደቁ፡፡

ሙስዓብ የአጋሪያንን ትኩረት ከነብዩ(ሰዐወ) ለመሳብ አደራውን ከፍ አድርጎ አሏሁ አክበር ሲልም ራሱን አንድ አስፈሪ የጦር ብርጌድ አደረገ፡፡ ጥረትና ጭንቀቱ ሁሉ ሙሽሪኮቹን ከነብዩ እይታ ወደርሱ መሳብ ነውና ተሳክቶለት ራሱን ለከፋ አደጋ አጋለጠ፡፡ ህይወት ከነብዩ(ሰዐወ) ውጭ ምን ታደርግና!! አንድ እጁ ባንዲራ ይዞ ታክቢራ ይላል፡፡ ሌላኛው እጁ ደግሞ ሰይፍ ይዞ ይመታል፡፡ ተረባረቡበት፡፡

እስቲ የአይን እማኝ ለነበረው ሹረህቢል አብደሪ እንተወው፡፡                                                                      ሙስዓብ የኡሁድ ዘመቻ እለት ባንዲራ ተሸከመ፡፡ ሰራዊቱ ሲርድ እርሱ ግን ፀና፡፡ ኢብኑ ቀሚዓህ የሚባል ፈረሰኛ መጣና ቀኝ እጁን ቆረጠው፡፡ ሙስዓብም ‹‹ሙሃመድ እንዳለፉት መልእክተኞች መልእክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም››ይል ነበር፡፡ ባንዲራውን በግራ እጁ ያዘ፡፡ ግራውንም ቆረጠው፡፡ ነገርግን ባንዲራውን በሁለት የተቆረጡ ክንዶቹ መሃል ያዘው(የነቢ አደራ አይደል!)፡፡ ‹‹ሙሃመድ እንዳለፉት መልእክተኞች መልእክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም››ማለቱን ቀጥሏል፡፡ በስተመጨረሻም በአንካሴ ወጋው፡ ሙስዓብ ወደቀ፡ ባንድራውንም ለቀቀው፡ የሰማዕታ አንፀባራቂ ፈርጥና ኮከብ ወደቀ፡ አይኔ እያየ ነብዩ(ሰዐወ) ቀድመውኝ ሲሞቱ ማየት አልሻም ይመስል ነበር፡፡ ለርሳቸው የነበረውን ፍቅር ጥልቀት፣የስስቱን መጠን ያሳያል፡፡                                                                                 አላህም ዝንተዓለም የሚነበብ ቁርአን ይሆን ዘንድ የቁርአን አንቀፅ ይሆን ዘንድ አሟላው፡፡ ‹‹ሙሃመድ እንዳለፉት መልእክተኞች መልእክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም….››

መራራው ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ የቅኑ ሰማዕት አስክሬን ፊት በደም ተለውሶ አፈር ውስጥ ድብቅ ብሎ ተገኘ፡፡ አወዳደቁ ነብዩ(ሰዐወ) የከበቧቸው አጋርያን ገድለዋቸው አስክሬናቸውን ላለማየት ፊቱን በሀዘን ድፍት ያደረገ ይመስል ነበር፡፡ የነብዩን(ሰዐወ) መትረፍ ሳያይ ሰማዕት ሆኖ ወደቀ፡፡ ነብዩ(ሰዐወ) ወደ ጦር ሜዳው በመውረድ ሰማዕታትን ተሰናበቱ፡፡ ሙስዓብ ዘንድ ሲደርሱ ግን እምባቸውን መቆጣጠር አቃታቸው፡፡ አለቀሱ……..

ለመስዓብ አስክሬን መከፈኛ ታጣ

ኸባብ ኢብኑ አል አረት(ረዐ) እንዲህ ይተርክልናል፡-‹‹ የአላህን ውዴታ ከጅለን በርሱ መንገድ ወደ መዲና ተሰደድን፡፡ ምንዳችን አላህ ዘንድ ተፅፏል፡፡ ከኛ ውስጥ ምድራዊ ድርሻውን ሳይጠቀም ያለፈ እንደ ሙስዓብ ያለም አለ፡፡ ኡሁድ ቀን ሲገደል መገነዣ ከአንዲት ቁራጭ ፎጣ በቀር ታጣ፡፡ በተገኘቺው ጭንቅላቱን ስንሸፍን እግሩ ይጋለጣል፡፡ እግሩን ስናለብስ ጭንቅላቱ ይታያል፡፡››

ነብዩ(ሰዐወ) ‹‹ከላይ በኩል አልብሱትና ጥሩ ሽታ ባለው ብቃይ እግሩን ሸፍኑት›› አሉ፡፡ ነብዩ(ሰዐወ) የአጎታቸው ሓምዛ መገደልና ሙሽሪኮቹ ገላቸውን መቆራረጣቸው ተደማምሮ ልባቸው በሐዘን ደማ፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ውስጣቸውን ሐዘን እየበላው የመጀመሪያውን አምባሳደራቸውን አስክሬን  ሊሰናበቱት መጡ፡፡ ከአይናቸው እምባ እየረገፈ ‹‹ከአማኞችም ለአላህ ቃል የገቡትን እውን ያደረጉ አሉ፡፡›› ሲሉ ተሰሙ፡፡ የተገነዘባትን ሸካራ ቁራጭ ልብስ እያዩ ‹‹መካ ውስጥ ለስላሳና በጌጥ የተሸቆጠቆጠ ልብስ ለብሰህ አይቼሃለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ፀጉርህ በአቧራ ተሸፍኖ መገነዣ አጣህ!›› ብለው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡

ነብዩ(ሰዐወ) ከፍ ባለ ድምፅ አዋጅ ነገሩ፡፡ ‹‹የአላህ መልዕክተኛ እናንተ ሰማዕታት መሆናችሁን አላህ ፊት የምፅዐት ቀን ይመሰክራሉ፡፡›› አሉ፡፡ ወደተቀሩት ባልደረቦቻቸው ዘወር ብለው‹‹ ሰዎች ሆይ ጎብኟቸው፣ሰላምታም አቅርቡላቸው፡፡ ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታዬ እምላለሁ ማንኛውም ሙስሊም እስከ እለተ ቂያማ ድረስ ሰላምታ አያቀርብላቸውም እነርሱም የሚመልሱ ቢሆን እንጂ፡፡››አሉ፡፡

ሙስዓብ ሆይ! አሰላሙአለይኩም

ሰማዕታት ሆይ! አሰላሙ አለይኩም……

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here