አሕመድ ዲዳት – ዓለማቀፉ ዳዒ

4
16304

አሕመድ ዲዳት (1918-2005 ዓ.ል)

ይህ ታላቅ ሰው በልጅነታቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማሯቸው የግድ አስፈላጊ ከሆኑ ትምህርቶች በስተቀር ብዙ ትምህርት አላገኙም። ደህና ከሚባል ትምህርት ቤት ገብተውም በምቹ ድባቧና በሰፊው ግቢዋ ዉስጥ አልተንሸራሸሩም። እንደነዚያ ነገሮች ሁሉ ገር እንደሆኑላቸውና ጠዋት ማታ ቦርሣቸውን ተሸክመው ወደ ትምህርት ቤት እንደሚመላለሱት ልጆችም በተረጋጋ ሁኔታ አላደጉም። ቤተሰባቸውን ባጋጠማቸው ከባድ ድህነት ምክንያት ገና በልጅነታቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እና ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት የተገደዱ ናቸው።

ሁሉም ልጆች በዚያ የልጅነት ዕድሜ ከጎናቸው ሊያጧት የማይፈልጉትንና የሚወደውን ምግብ የምታዘጋጅለት፣ የምታጫውት፣ በደስታም ሆነ በሐዘን ወቅት ከጎን የምትሆን እናት ከአጠገባቸው ባለመኖሯ ምክንያት በዉስጣቸው አስከፊ እና ትልቅ የብቸኝነት ስሜት ተሰምቷቸው አድገዋል… አሕመድ። አባታቸው የቤተሰቡን የዕለት ወጭ ለመሸፈንና የአባትነት ኃለፊነታቸውን ለመወጣት ሌት ተቀን ይታትሩ ነበር።

ታሪካቸውን የምናወሳላቸው አሕመድ ዲዳት፣ ምንም እንኳ በርካታ ችግሮች የተጋረጡባቸው ቢሆንም በልጅነታቸው ከትምህርት ባልንጀሮቻቸው መካከል እጅግ ጎበዝ እና ቀዳሚ፣ ብልህ ልጅ ነበሩ። ዕድሜያቸው አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን እርሣቸውንና ቤተሰባቸውን የከበበውን የድህነት ማቅ ለመግፈፍ ሲሉ በራሣቸው ሥራ ጀመሩ። ሱቅ ዉስጥ ሰዎች ዘንድ ተቀጥረው ሻጭ ሆኑ።

ዛሬ ላይ ሆነን ከተወለዱና ወደዚህች ምድር ከመጡ ድፍን መቶ ዓመት ሊሞላቸው አንድ ዓመት ብቻ የቀራቸውንና በሕይወት ካለፉ ደግሞ 12 ዓመት የሆናቸው ታላቁን የኢስላም ፈርጥ አሕመድ ዲዳትን ስናስብ ትክክለኛውን የእስልምናን ጥሪና አስተምህሮ ለማድረስ የተጉ ጎበዝ ፈረሠኛ ብቻ ሆነው አይደሉም የምናገኛቸው። በምላስም ሆነ በብዕራቸው እስልምናን ከምዕራባውያን ጥቃትና የሥም ማጥፋት ዘመቻ በመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ የሙስሊም ዓለማቀፍ ስብእናዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን እንረዳለን።

ዲዳት የጽሑፍም የመድረክም አንበሳ  ናቸው። መድረክ አያያዛቸው፣ ሞገሳቸውና የንግግራቸው ሁኔታ ሁሉ ሀሳብን ይሰርቃል፣ ልብን ይገዛል። መድረክ ላይ የትኛውም ርቱዕ ተናጋሪ አይረታቸውም። በንግግራቸውና በክርክራቸውም የገጠሟቸውን ብዙዎችን መሳቂያ መሳለቂያ አድርገዋል። አንዲት ቃል የተናገሩ እንደሆን ያች ቃል በዓለም ዙሪያ አሉ በተባሉ ጳጳሶች ጉያ በመግባት ታሸብራቸዋለች፣ ዕረፍትም ትነሳቸዋለች።

በርግጥም አሕመድ ዲዳት ለየት እና ወጣ ያሉ ዳዒ ናቸው። በደዕዋ ሥራ ላይ የሚያህላቸው ማንም የለም። በዚህ ዘርፍ ከሀያ አንደኛው ክፍለዘመን ጋር ሊሄድ በሚችል መልኩ ተክነው ወጥተዋል።

አሕመድ ሑሴን ቃሲም ዲዳት የተወለዱት በ1918 ዓ.ል በህንድ ሱራት ነው። አባታቸው ሑሴን ቃሲም ዲዳት በደቡብ አፍሪካ ዉስጥ በልብስ ሰፊነት ይሠሩ ነበር።

አሕመድ ዲዳት በ1927 ዓ.ል አባታቸው ወደሚገኙበት ። በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ታዳጊ ነበሩ። ህንድን ከለቀቁ በኋላ እናታቸው ሞተች። አላህ ይዘንላት። አሕመድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ከዚያ በኋላ ድህነት አላፈናፍን አላቸው። የትምህርት ክፍያቸውን እንኳን መክፈል እስኪሳናቸው ሲደርሱ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።

አባታቸው ልጃቸው ያቋረጠውን ትምህርቱን ይቀጥል ዘንድ ከብዙ ነጋዴዎች ጋር ቢነጋገሩም ምንም መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም። ስለዚህም ሌላ አማራጭ መፈለግ ያዙ።

አሕመድ ዲዳት በተለያዩ ሙያዎች ላይ በመሥራት ዕድላቸውን ሞክረዋል። በብዙ የንግድ ቦታዎች ላይ ሠርተዋል። ከዚያም ቤተሰባቸው የሚኖርበትን ደርባን ከተማን በመልቀቅ ከአንድ የተከበረ ሙስሊም ሱቅ ዉስጥ ለመሥራት ከደርባን ሀያ አምስት ማይል ርቀው ተጓዙ። እዚያም ተቀጥረው ሻጭ ሆነው ቆዩ። ቀጥሎም ትላልቅ መኪናዎችን ከሚያመርት አንድ ፋብሪካ ዉስጥ ሹፌር ሆነው ተቀጠሩ። ቀጥሎም የገቢና ወጭ ምርቶች መዝጋቢ ሆነው ሠሩ። ከዚያም የፋብሪካው ኃላፊ ሆኑ።

በ1936 በናታል ደቡባዊ ዳርቻ በቢሮ ዕቃዎች ሻጭነት ተቀጥረው በመሥራት ላይ እያሉ በክርስቲያኖች ሴሚናር ላይ ሙስሊሞችን ወደ ክርስትና ለመለወጥ የተሰማሩ የተወሰኑ ሚሽነሪዎችን አገኙ። ሰዎቹ የእስልምና ሃይማኖት መልዕክተኛ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እስልምናን ያስፋፉት በሰይፍ ኃይል እንደሆነም ይናገሩ ነበር። የዚህ ዓይነቱ ውንጀላ ሸይኽ አሕመድ ዲዳትን ይበልጥ እንዲነሳሱና ወደሃይማኖት ንፅፅር ጥናት እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ስለኢስላም ማጥናት የጀመሩትም ሚስተር ፋየርፋክስ የሚባል ወደ እስልምና የገባ ሰው በሚሰጠው ትምህርት ላይ በመገኘት ነበር። ትምህርቱ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ፋየርፋክስ ክፍለጊዜውን በማራዘም ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና እስልምናን ለክርስቲያኖች እንዴት መስበክ እንደሚቻልም በተጨማሪ አስተማራቸው። በጊዜ ሂደት ፋይርፋክስ ማስተማሩን ሲያቆም ስለመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ዕውቀት የነበራቸው አሕመድ ዲዳት በቦታው ተተክተው ለሶስት ዓመታት ያህል አስተማሩ። ዲዳት መደበኛ በሆነ መልኩ እንደሙስሊም ምሁራን ጊዜ ወስደው ኪታቦችን አልተማሩም።

ሸይኽ አሕመድ ዲዳት በ1937 ዓ.ል ደግሞ ሐዋእ ገንገት የምትባል እንስት አገቡና አንዲት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆችን ከሷ አገኙ።

በ1949 ዓ.ል ወደ ፓኪስታን በመጓዝ በአንድ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ዉስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

በ1996 ዓ.ል እዚያ ከሚገኙ ትላልቅ ጳጳሶች ጋር የተሳካ ክርክር አድርገው ከአውስትራሊያ ሲመለሱ አንገታቸው ሥር ባገኛቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ፓራላይዝድ በመሆን ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ፍራሽ ላይ ወድቀው ቆዩ።

በታመሙበት ጊዜ ሁሉ ከተለያዩ የዐረብ ሀገራት መንግሥታት እና መሪዎቻቸው ትልቅ እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር። ስለሆነም በተሻለ ሁኔታ እንዲታከሙና በዘርፉ በተካኑ ሐኪሞች እንዲታዩ ተብሎ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሪያድ ሆስፒታል ተዛወሩ።

አሕመድ ዲዳት በመጨረሻም ወደማይቀረው ሞት እና ወደ አላህ ጉርብትና የሄዱት በ2005 ዓ.ል በሰማኒያ ሰባት ዓመት ዕድሜአቸው በእጅጉ የሚወዱትን የአላህን (ሱ.ወ) ቃል ቁርኣንን በማዳመጥ ላይ እያሉ ነበር።

ለአሕመድ ዲዳት የተቸሩ የአላህ ጥበቃዎችን እንክብካቤዎች

በአሕመድ ዲዳት ሕይወት ዉስጥ ያልተጠበቁ የአላህ ጥበቃዎችና እንክብካቤዎች ታይተዋል። አላህ (ሱ.ወ.) ነገሮችን አስተካክሎላቸዋል፣ ሰበቦችንም አሟልቶላቸዋል። የመጀመሪያው – ለንባብ ያላቸው ጉጉት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው። በብቸኝነታቸው ጊዜያት ሁሉ መጽሐፎች መልካም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በዚህም የመጽሐፎች ጥብቅ ጓደኛ ሆነው ኖሩ። መጽሐፍ፣ መጽሄት ይሁን ጋዜጣ አሊያም ሌላ ነገር በእጃቸው የገባውን ሁሉ በጥልቅ የመረዳት ስሜት ሳያነቡ አያልፉም ነበር። በቤተመጽሐፋቸው ዉስጥ ያላነበቧቸው አንድም መጽሐፍ የለም። ከዚህም ጎን ለጎን አላህ ጥልቅ የመረዳት ተሰጥኦ እና የመጠቀ እይታን፣ አንደበተ ርቱእነትን፣ በነገሮች ስኬትና ድልን፣ ትግልና ብርታትን አላህ ለግሷቸዋል።

ለማንበብ ያላቸው ከፍተኛ ጉጉት ከባበድ መሠናክሎች ሁሉ እንዲገሩላቸው እገዛ አድርጎላቸዋል። ከእስልምና መከላከል እና ጠበቃው መሆን ትልቁ ዓላማቸውና ጭንቀታቸው ነበር። እስልምና የሚነካውን ሰው ሁሉ ባገኙበት በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ይከራከሩ ነበር። በዚህም በአዕምሮ ምጥቀትም ሆነ በክርክር ችሎታ ዘወትር ይረቷቸው ነበር። ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ የሆነ የቋንቋ ንግግር ችሎታ ነበራቸው።

ሌላው አላህ ያሳካላቸው ነገር ደግሞ ። “ኢዝሃሩል ሐቅ /እውነትን መግለጽ” የተሠኘውን የረሕመቱላህ  አልሂንዲን መጽሐፍ ማግኘታቸው ነበር። ይህም የሆነው በአንድ ወቅት የሚነበብ ነገር ፍለጋ በአንድ መጋዘን ዉስጥ የተከማቹ መጽሐፎችን ሲያገላብጡ ነበር። ይህን ጥንታዊ የሆነ መጽሐፍ በማግኘታቸው እጅጉን ተገረሙ፣ ማመንም አቃታቸው። መጽሐፉ የታተመው በ1915 ዓ.ል ሲሆን መጽሐፉን አንስተው በእንግሊዝኛ ፊደል የተፃፈውን ርዕሱን ማየት ጀመሩ። “HAKK IZARUL” ይላል። ሆኖም ግን የዚህን ቃል ትርጉም ማወቅ አልቻሉም። ምክንያቱም ዐረብኛ ቃል ነውና።  ሆኖምግን ዝቅ ሲሉ የእንግሊዝኛ ትርጉሙን ተመለከቱ “TRUTH REVEALED” ይላል።

ረሕመቱላህ ይህንን መጽሐፍ ያዘጋጁት ለክርስቲያኖች መልስ እንዲሆናቸው ነበር። በዋናነትም በመበረዝና መከለስ፣ በሥላሴ ምንነት፣ በቁርኣን እውነትነትና በነቢይነት ዙሪያ አምስት ጥናቶች የተካተቱበት ነበር። በወቅቱ የክርስትና ሚሽነሪዎች በሙስሊም ህንዶች መካከል ገብተው በሰፊው ይንቀሳቀሱ ነበር።

አሕመድ ዲዳት ሃይማኖታዊ ንጽጽር ጉዳዮች በሚገባ ካነበቡና በጥልቀት ከተረዱ በኋላ በማስረጃዎች እና መረጃዎች በእጅጉ ታጥቀው በአዳራሽ ዉስጥ ትምህርት መስጠት ጀመሩ። ትምህርቱንም የሚሠጡት በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ዕውቀት ላላቸውና ለሌሎችም ወገኖች ነበር። ትምህርታቸው እጅግ ሳቢ እና ፋይዳውም የጎላ ነበር። የአዳራሹን ኪራይም ሆነ የተለያዩ ወጭዎችንም የሚችሉት ራሣቸው ነበሩ።

ይህ ወጣት ተናጋሪ የከተማውን ህዝብ ለመሳብና ትኩረት ለማግኘት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ዕውቀት እና መረጃ፣ በቁርኣን እና በመልዕክተኛው ላይ ያለው ጠንካራ እምነት እጅግ አስደናቂ ነበር።

ከዕለታት በአንዱ ቀን በደርባን ንግግራቸውና ትምህርታቸው ላይ የነበሩ የጆሃንስበርግ ሰዎች ወደርሣቸው በመምጣት የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ ምክንያት በማድረግ ንግግር እንዲያደርጉላቸውና ትምህርት እንዲሠጧቸው ጋበዟቸው። ትንሽ ካመነቱ በኋላ ሀሳቡን ሳይቀበሏቸው ቀሩ። ለዚህም ምክንያት ነበራቸው። ዲዳት ከዝቅተኛ ገቢ የማኅበረሰብ ክፍል ዉስጥ የሚመደቡ ናቸው። የጉዞ  ወጭያቸውን እንኳን ለመሸፈን አቅም የላቸውም። ሆኖምግን ሰዎቹ የመሄጃውንም ሆነ የመልስ ጉዞውን ወጭ ለመሸፈን ቃል ገቡላቸው። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን ለመሄድ ዕድል አገኙ። በጆሃንስበርግ አዳራሽም እጅግ አነጋጋሪና አስደማሚ የሆነ ንግግራቸውን አደረጉ። ሆኖምግን መልዕክታቸው በንግግርነቱ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በዉስጣቸው ትልቅ የራስ መተማመን ስሜት ተተከለ። በዚህም የተነሳ በደዕዋው ዘርፍ በሠፊው ለመሥራት አሰቡ። በእንዴትነቱ ዙሪያም አዳዲስ ሀሳቦችን በማከል ስለትግበራው ብዙ አሠላሠሉ።

አሕመድ ዲዳት የደዕዋ ትምህርት መስጠቱን በጆሃንስበርግ ቢጀምሩ ትልቅ አቀባበል ሊኖረው እንደሚችል አሰቡና በ1958 ዓ.ል በደርባን ከተማ አዳራሽ የደዕዋ ትምህርታቸውን መስጠት ጀመሩ። እዚያ የሚገኘውን ትልቁን መስጂድም ለደዕዋ ሥራው ማዕከል አደረጉት። እጅግ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች በማድረጋቸውም ሰዎች በብዛት እስልምናን መቀበል ጀመሩ። አሕመድ ዲዳት በእውነት መንገድ ላይ አንዳችም ነገር አይፈሩም ነበር። በፓኪስታን ያሉበት ድረስ ሄደው ሦስት ቄሶችን በመከራከር አጣብቂኝ ዉስጥ ሲያስገቧቸው ከርሣቸው የሚወጡ ቃላቶች በሙሉ በጀግንነትና በወኔ የተሞሉ ነበሩ።

የመድረክ ላይ አንበሳ

ልጃቸው ዩሱፍ ዲዳት አባታቸውን “የመድረክ አንበሳ’ ሲሉ ይገልጿቸዋል። በርግጥም ሸይኽ አሕመድ ዲዳት በዋናነት በክርክር ስልታቸውና በማራኪ የመድረክ አቀራረባቸው ነው የሚታወቁት። ከዚህም በተጨማሪ የተዋጣለት ፀሐፊም ናቸው። ከሀያ በላይ መጽሐፎችን የፃፉ ሲሆን በርካታ በራሪ ወረቀቶችንም አዘጋጅተው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎች በዓለም ዙሪያ ተበትነዋል። እነኚህ የህትመት ዉጤቶችም ብዙዎቹ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ተተርጉመው ተሠራጭተዋል።

ልጃቸው ዩሱፍ ዲዳት የቀድሞው የደቡብ አፍረካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በ1994 ዓ.ል ሳውዲ ዐረቢያን ሲጎበኙ ያሉትን ያስታውሳሉ። ማንዴላ እንዳሉት በሄዱበት ሁሉ ሰዎች በተለይም ወጣቶች ስለታላቁ የሙስሊም ምሁር ስለ ዲዳት ሁኔታ ይጠይቋቸዋል። ለቴሌቭዥን ቃለምልልስ ሲቀርቡም የጋዜጠኛው ቀዳሚ ጥያቄ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ሸይኽ ዲዳት  እንዴት ናቸው የሚል ነው።

ሸይኽ አሕመድ ዲዳት በዓለማቀፍ ደረጃ ከታዋቂ ሰዎች ጋር ያደረጓቸው በርካታ ክርክሮችን አድርገዋል። ጎልተው ከሚጠቀሱት መካከል፡-

 1. ከጆን ጊልኽረስት ጋር ያደረጉት ክርክር – ጊልኽረስት ከቤኖኒ ደቡብ አፍሪካ ሲሆን በሃይማኖቱ ክርስቲያን የሆነ ጠበቃ ነው። በ1975 ዓ.ል በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅላት ዙሪያ ከዲዳት ጋር ክርክር አድርገዋል።
 2. ከጆሽ ማክዶዌል ጋር ያደረጉት ክርክር – አሕመድ ዲዳት በዓለማቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትና ሰፊ እውቅናም ያስገኘላቸው ክርክር ሲሆን በኦገስት 1981 በደርባን ደቡብ አፍሪካ ነበር ያደረጉት። ጆሽ ማክዶዌል ታዋቂ የክርስቲያን ሰባኪ ነው።
 3. ከአኒስ ሾሮሽ ጋር ያደረጉት ክርክር – አሕመድ ዲዳት ከፍልስጤማዊው አኒስ ሾሮሽ ጋር በተደጋጋሚ ክርክር አድርገዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በሴፕተምበር 8ቀን 1977 ዓ.ል በበርሚንግሃም ክርክር አደረጉ። ክርክሩንም ያደረጉት በቁርኣንና መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃልነት ዙሪያ ነበር። በ1980ዎቹ ዉስጥ ደግሞ ዲዳት እና ሾሮስ ለሁለት ጊዜ ያህል ክርክር አድርገዋል። የመጀመሪያውን ክርክር ያደረጉት በ1985 ዓ.ል በለንደን ሮያል አልበርት አዳራሽ ሲሆን የክርክሩ ርዕስ የነበረውም “የሱስ አምላክ ነውን?” የሚል ነበር። ሁለተኛው ክርክር ደግሞ በተሻለ ቅንጅትና ደማቅ ዝግጅት በኦገስት 7 ቀን 1988 ዓ.ል በበርሚንግሃም የተካሄደው ሲሆን ከቁርኣንና ከመጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል የትኛው ነው? በሚል ርዕስ ሥር  ነበር።
 4. ከጂሚ ሰዋጋርት ጋር ያደረጉት ክርክር – አሕመድ ዲዳት በኖቨምበር 1986 ዓ.ል ከክርስቲያን የቴሌቭዝን ሰባኪው ጂሚ ስዋጋርት ጋር ክርክር አድርገዋል።
 5. ሌሎች ተጠቃሽ ክርክሮች – ሸይኽ አሕመድ ዲዳት በኦክቶበር 1991 ዓ.ል ወደ ስካንዴኔቭያን አገራት በመጓዝ ሶስት ክርክሮችንና በርካታ ንግግሮች አድርገዋል። ሁለቱ ክርክሮች የተደረጉት በተከታታይ ምሽቶች በስቶክሆልም ስዊድን ከፓስተር ስታንሊ ጆበርግ ጋር ነበር። የመጀመሪያው ክርክር የተደረገው “መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የአምላክ ቃል ነውን?” በሚል ርዕስ ሥር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “እውን ኢየሱስ አምላክ ነውን?” የሚል ነበር።

ዲዳት እና ጳጳሱ

የሮማው የካቶሊክ ጳጳስ ጆን ፖል በሙስሊሞች ጋር የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ መከባበርና መነጋገር እንዲኖር ጥሪ ካደረጉ በኋላ በ1984 ዓ.ል  ዲዳት በቫቲካን አደባባይ ለህዝብ ክፍት በሆነ መልኩ ከጳጳሱ ጋር ለመከራከር ሀሳብ አቀረቡ። ሆኖምግን ጳጳሱ ሀሳቡን አልተቀበሉም። የጳጳሱ ቢሮ መልስ ሊሠጣቸው ባለመቻሉም በጥር ወር 1985 ዓ.ል አሕመድ ዲዳት ብፁዕነታቸው ከሙስሊሞች ጋር ድርድር ይደረግ የሚል የድብብቆሽ ጨዋታ ይዘዋል የሚል አርዕስት የያዘ በራሪ ወረቀት አሠራጩ።

መጽሐፎቻቸው እና ንግግሮቻቸው

አሕመድ ዲዳት ከደርዘን በላይ የሆኑና በብዛት የተሠራጩ አነስተኛ መጠን ያላቸው መጽሐፎችን አዘጋጅተው አሳትመዋል። ዲዳት የሠጧቸው ትምህርቶችና ያደረጓቸው ንግግሮችም በዋናነት የሚያተኩሩት በኢስላም ክርስቲያን ሃይማኖት ንጽጽር ዙሪያ ነው። መጽሐፎቻቸውም የተዘጋጁት  በመድረክ ላይ ያቀረቧቸውን ትምህርቶችና ንግግሮች መሠረት አድርገው ነው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል-

 • Is the Bible God’s Word? – መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነውን?
 • What the Bible says about Muhammad – መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነብዩ ሙሐመድ ምን ይላል?
 • Crucifixion or Cruci-Fiction? – እውነተኛ ስቅላት ወይስ ልቦለድ
 • Muhammad: The Natural Successor to Christ – ሙሐመድ ትክክለኛው የክርስቶስ ወራሽ
 • Christ in Islam – ክርስቶስ በኢስላም
 • Muhammad the Greatest – ሙሐመድ የታላቆች ታላቅ
 • Al-Qur’an the Miracle of Miracles – ቁርኣን የተዓምራት ሁሉ ተዓምር

ዲዳት አራት አነስተኛ እውቅ መጽሐፎቻቸውን በአንድ ላይ በመጠረዝ ያሳተሙ ሲሆን 10,000 ኮፒ የሚሆኑ መጽሐፎችን “The Choice” በሚል ስያሜ ነበር የታተሙት። የመጀመሪያው መጽሐፋቸው በአፕሪል 1993 ዓ.ል የታተመው Islam and Christianity የተሠኘው ነው። ይህ መጽሐፍ በ1990ዎቹ ዉስጥ ከፍተኛ እውቅናን የተጎናፀፈ ነበር። በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ በርካታ ሚሽነሪዎችም በነፃ ታድሏል። መጽሐፉን በርካታ ማተሚያ ቤቶች በተደጋጋሚ ያሳተሙት ሲሆን በሁለት ዓመት ዉስጥ ብቻ 250ሺህ ያህል ኮፒ በመካከለኛው ምሥራቅ ሊታተም ችሏል።

ቀጥሎ ደግሞ ሁለተኛው ጥራዝ “The Choice” ስድስት አነስተኛ መጽሐፎችን በማካተት ታተመ። ዲዳት በዐብደላህ ዩሱፍ ዐሊ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተተረጎመው የቅዱስ ቁርኣን በሰፊው እንዲተዋወቅና እንዲሠራጭ እገዛ  አድርገዋል። በንግግራቸውም ዉስጥ በተደጋጋሚ ይጠቅሱት ነበር።

ዘመናት  በሰዎቻቸው ይዘከራሉ

አሕመድ ዲዳት አላህ ይዘንላቸውና በደዕዋው ዘርፍ ለሙስሊሞች አዲስ መንገድ ያሳዩ ታላቅ ሰው ነበሩ። ሕይወታቸውን በሙሉ በእስልምና እና በቁርኣን ላይ አንፀው ኖረዋል። በአላህ እና በመልዕክተኛው ማመን ብቻውን በቂ እንዳልሆነና መልዕክታቸውን ትክክለኛው ጥሪ ካልደረሣቸው ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች መካከል በማሠራጨትና በማስተማር ስለዚህች ዓለምም ሆነ ስለመጨረሻው ዓለም እንዲሁም ለዘመናት ስለ እስልምና እና ቁርኣን የተሳሳተ ግንዛቤ የያዙ ሰዎችን አመለካከት አደገኛነት በማስተማር የሚገባቸውን ሐቅ ለነርሱ መስጠት እንደሚገባ በልቦናቸው ዉስጥ የሰረፀ አቋም ሆኗል።

በርግጥም ማንኛውም ስለ እስልምና የሚያሳስበው ሙስሊም ሁሉ እኚህ አንጋፋ ሸይኽ ከእስልምና ለመከላከል ሲሉ በቁርጠኝነት እና በፅናት ትላልቅ ቄሶችን ሲሞግቱ ሲያይ ዐይኑ በእንባ የሚሞላ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ዲዳት ቄሶቹ ንግግራቸውን እስኪጨርሱ ተራቸውን ሲጠብቁ የተመለከታቸው ሁሉ በፊታቸው ላይ አንድም ዓይነት ጥርጣሬ፣ መረበሽም እና ወደኋላ የማለት ስሜት አያይም። ፍጹም በሆነ መልኩ እርጋታ ይነበብባቸዋል። ነጭ ፂማቸው፣ ሞገሳቸውና ሳቢ ፈገግታቸው ሕይወታቸውን በሙሉ ተለይቷቸው አያውቅም። ባጠረ ጸጉራቸው ላይ የተደፋችውና በመጠኑ ወደ ግንባራቸው ወጣ ያለችው ትንሿ ኮፊያቸው ከብዙዎች ህሊና የምትጠፋ አይደለችም። በቂ እና አሳማኝ የሆነ መረጃ ታጥቀው ከነሞገሳቸው በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ ይቀመጣሉ። ጉያቸው በሰሉ ቀስቶች የተሞላ ነው። ግዳያቸውን ለመጣል በዝምታና በተረጋጋ መንፈስ ተራቸውን የሚጠባበቁ ይመስላሉ። …

ምናልባት በተደጋጋሚ ሲወያዩና ሲከራከሩ በምታዩዋቸው ጊዜ ቁርኣንን አንስተው ከፍ ባለ ድምጽ “ይህ ከአላህ ዘንድ ነው!” የሚሉበት ሁኔታ አይረሣችሁም። የአላህ ቃል ከፍ ብሎ ለዘላለሙ ይኖር ዘንድ በርግጥም ብዙ ጥረዋል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጻፏቸው መጽሐፎችና ባሰሟቸው ዲስኩሮችና ክርክሮች ዓለማቀፍ ዝናን ያተረፉት ሸይኽ አሕመድ ዲዳት በ1986 ዓ.ል ሃምሳ ዓመት ሙሉ እስልምናን ለማገልገል ስላበረከቱት አስተዋጽኦ የንጉስ ፈሀድን ዓለማቀፍ ሽልማት አግኝተዋል።

አላህ አሕመድ ዲዳትን ይዘንላቸው። ከሰፊው የእዝነት ጀነቱም ያስገባቸው። ስለ ኢስላም ላደረጉት አስተዋጽኦ ሁሉ መልካሙን ይመንዳቸው።

4 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here