እውነተኝነትና ትዕግስት የአላህ ባሪያዎች ባህሪያት

0
6908

ምስጋና ለአላህ ይሁን፡፡ ሶላትና ሰላም በተወዳጁና ምርጡ በሆኑት ነብዩ ሙሐመድ ፣ በቤተሰባቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና በተወደጃቸው ላይ ይሁን፡፡

አንድ የአላህ ባርያ ከሌሎች የሰው ልጆች በተለየ መልኩ፣ እሱ እንጂ ሌላው ሊመሰልበት የማይችል ባህሪ ባለቤት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በማህበረሰቡ መካከል ሰዎችን ወደቀጥተኛ መንገድ የመምራት እድል ይኖረዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በምንመለከተው ርእስ በአላህ ፈቃድ የእንደዚህ አይነት ባህሪ ባለቤት ለመሆን እንጥራለን፡፡

የመጀመሪያው ባህሪይ

  • እውነተኛነት

እውነተኛነት ሁሉንም አይነት የህይወት ዘርፍ ያካትታል፡፡ ከነፍስ ጋር፣ ከሠዎች ጋር እንዲሁም ከአላህ ጋር፡፡ እውነተኛ ሠው ራሱን አይዋሽም፡፡ የማይሰራውን የሚናገር አይደለም፡፡ቁርአን እንዲህ ሲል የገልፃል፡፡

أَتَأْمُرُونَ النَّاسَ بِالْبِرِّ وَتَنسَوْنَ أَنفُسَكُمْ وَأَنتُمْ تَتْلُونَ الْكِتَابَ ۚ أَفَلَا تَعْقِلُونَ
እናንተ መጽሐፉን የምታነቡ ሆናችሁ ሰዎችን በበጎ ሥራ ታዛላችሁን? ነፍሶቻችሁንም ትረሳላችሁን? (የሥራችሁን መጥፎነት) አታውቁምን? አል-በቀራ፤  44
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لِمَ تَقُولُونَ مَا لَا تَفْعَلُونَ
كَبُرَ مَقْتًا عِندَ اللَّهِ أَن تَقُولُوا مَا لَا تَفْعَلُونَ
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የማትሠሩትን ነገር ለምን ትናገራላችሁ? የማትሠሩን ነገር መናገራችሁ አላህ ዘንድ መጠላቱ ተለቀ፡፡ አል-ሶፍ፤ 2-3

እውነተኛ ሰው ከሰዎች ጋርም እውነተኛ ነው፡፡ ሙናፊቅና ሸፍጠኛ አይደለም፡፡ ቁርአን እንዲህ ይመሰክርበታል፡፡

وَمِنَ النَّاسِ مَن يَقُولُ آمَنَّا بِاللَّهِ وَبِالْيَوْمِ الْآخِرِ وَمَا هُم بِمُؤْمِنِينَ
يُخَادِعُونَ اللَّهَ وَالَّذِينَ آمَنُوا وَمَا يَخْدَعُونَ إِلَّا أَنفُسَهُمْ وَمَا يَشْعُرُونَ
فِي قُلُوبِهِم مَّرَضٌ فَزَادَهُمُ اللَّهُ مَرَضًا ۖ وَلَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ بِمَا كَانُوا يَكْذِبُونَ
ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡ አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡ በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ አለባቸው፡፡ አላህም በሽታን ጨመረባቸው፡፡ ለነርሱም ይዋሹ በነበሩት ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡ አል-በቀራ፤8-10
وَمِنَ النَّاسِ مَن يُعْجِبُكَ قَوْلُهُ فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَيُشْهِدُ اللَّهَ عَلَىٰ مَا فِي قَلْبِهِ وَهُوَ أَلَدُّ الْخِصَامِ
وَإِذَا تَوَلَّىٰ سَعَىٰ فِي الْأَرْضِ لِيُفْسِدَ فِيهَا وَيُهْلِكَ الْحَرْثَ وَالنَّسْلَ ۗ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ الْفَسَادَ

وَإِذَا قِيلَ لَهُ اتَّقِ اللَّهَ أَخَذَتْهُ الْعِزَّةُ بِالْإِثْمِ ۚ فَحَسْبُهُ جَهَنَّمُ ۚ وَلَبِئْسَ الْمِهَادُ

ከሰዎችም ውስጥ እርሱ ክርክረ ብርቱ ሲኾን በቅርቢቱ ሕይወት ንግግሩ የሚደንቅህና በልቡ ውስጥ ባለው ነገር ላይ አላህን የሚያስመሰክር ሰው አልለ፡፡ (ካንተ) በዞረም ጊዜ በምድር ላይ በውስጧ ሊያበላሽና አዝመራንና እንስሳዎችን ሊያጠፋ ይሮጣል፡፡ አላህም ማበላሸትን አይወድም ለእርሱ «አላህን ፍራ» በተባለም ጊዜ፤ ትዕቢቱ በኃጢኣት (ሥራ) ላይ ትገፈፋዋለች፡፡ ገሀነምም በቂው ናት፤ (እርሷም) በእርግጥ የከፋች ምንጣፍ ናት፡፡ አል-በቀራ፤ 204-206

እውነተኛ ሰው በአላህም ላይ አይዋሽም፡፡ የሚዋሽ ከሆነ አላህ እንዲህ ይመሰክርበታል፡፡

فَمَنْ أَظْلَمُ مِمَّن كَذَبَ عَلَى اللَّهِ وَكَذَّبَ بِالصِّدْقِ إِذْ جَاءَهُ ۚ أَلَيْسَ فِي جَهَنَّمَ مَثْوًى لِّلْكَافِرِينَ

በአላህም ላይ ከዋሸ እውነቱንም በመጣለት ጊዜ ከአስተባበለ ሰው ይበልጥ በዳይ ማን ነው? በገሀነም ውስጥ ለከሓዲዎች መኖሪያ የለምን? (አለ እንጅ)፡፡ አል-ዙመር፤ 32

የአላህ ባሪያ ራሱን፣ ሠዎችን እንዲሁም አላህን የማያታል ነው፡፡ በዚህም እውነተኛነት የጀነትን መንገድ ያጎናጽፋል፡፡ ረሡል/ሰ.ዐ.ወ/ እንዳሉት

 عَلَيْكُمْ بِالصِّدْقِ، فَإِنَّ الصِّدْقَ يَهْدِي إِلَى الْبِرِّ، وَإِنَّ الْبِرَّ يَهْدِي إِلَى الْجَنَّةِ، وَمَا يَزَالُ الرَّجُلُ يَصْدُقُ وَيَتَحَرَّى الصِّدْقَ حَتَّى يُكْتَبَ عِنْدَ اللَّهِ صِدِّيقًا، وَإِيَّاكُمْ وَالْكَذِبَ، فَإِنَّ الْكَذِبَ يَهْدِي إِلَى الْفُجُورِ، وَإِنَّ الْفُجُورَ يَهْدِي إِلَى النَّارِ، وَمَا يَزَالُ الرَّجُلُ يَكْذِبُ، وَيَتَحَرَّى الْكَذِبَ حَتَّى يُكْتَبَ عِنْدَ اللَّهِ كَذَّابًا 

“እውነት ላይ አደራችሁን፡፡ እውነት ወደ በጎ ነገር ይመራል፡፡ በጎ ነገር ደግሞ ወደ ጀነት ይመራል፡፡ አንድ ሠው እውነትን የሙጥኝ ካለ አላህ ዘንድ እውነተኛ ተብሎ ይፃፋል፡፡ ውሸትን አደራችሁን፡፡ ውሸት ወደ ብልግናና ጋጠወጥነት ይመራል፡፡ ጋጠወጥነት ደግሞ ወደ ጀሀነም ይመራል፡፡ አንድ ሠው ውሸት ላይ ከዘወተረ፣ አላህ ዘንድ ውሸታም ተብሎ ይመዘገባል፡፡ /ቡኻሪና ሙስሊም/

በሌላ የሙስሊም ዘገባ ደግሞ “እውነት በጎ ነገር ነው፡፡ በጎ ነገር ደግሞ ወደጀነት ይመራል፡፡ ውሸት ወደ ብልግና ይመራል፡፡ ብልግና ደግሞ ወደ እሳት ይመራል” ብለዋል፡፡

እውነት ባለቤቱን ልቅናን ያወርሳል፡፡ እውነተኛ ፈጣሪውን እንጂ ፍጡርን አይፈራም፡፡ የሆነን ስራ ለፍጡራን ብሎ አይሰራም፡፡ ምስጋናን ወይም ውዳሴን ከፍጡራን አይጠብቅም፡፡ ይህን ደረጃ የአላህ ምርጥ ባሪያዎች እንጂ ሌላው አይደርስበትም! አንዳንድ ሊቃውንት እንዳሉት፡- “በአስመሳይነት የሚኖር ሠው የእውነት ሽታ ከቶም አያሸትም“ ብለዋል፡፡ ኢብራሂም ኸዋስ የተባሉ ሠው ደግሞ “እውነተኛ ሠው ግዴታ የሆነውን ሲሰራ እንጂ ለሌላ ቦታ አታየውም ወይም ሱና የሆኑ ስራዎችን ሲሰራ እንጂ አታገኘውም”፡፡ ጁነይድ የተባሉት ሊቅ ደግሞ “ትክክለኛው እውነተኝነት ማለት ካልዋሸህ በቀር ከማትድንበት /ከማትወጣበት/ አጋጣሚ፣ እውነት መናገር ነው”፡፡                   እንዲሁም ተብሏል፡- ሶስት ነገሮች እውነተኛን አያሳስቱትም፣

  1. ጣፋጭ ነገር
  2. ቁንጅና        
  3. ክብር /ግርማ ሞገስ/   

ኢብኑልቀይም ስለእውነት ሲናገሩ፣ “እውነተኝነት የታላቆች ደረጃ ነው፡፡ በእውነት መንገድ ያልተጓዘ ከጉዞ ተቋራጭና ጠፊ የሚያደርግ፤ የኒፋቅና የኢማን ሠዎች መለያ፤ የጀነት ሠዎች ከእሳት ሠዎች የሚለዩበት፤ በምድር ላይም የአላህ ሠይፍ ነው፡፡ በሱ የተከራከረ ድምጽ ከፍ ይላል፤ የሥራ አስኳል፤ የሁኔታዎች ማጠንጠኛ፤ የስጋትን ጥሰት ተከላካይ ነው፡፡ በበራፉ የገቡበት ወደ ላቀው ፈጣሪ አላህ ያደርሳቸዋል፤ የዲኑ መሰረት መገንቢያ፤ እርግጠኝነት መሰረት መቋጠሪያ /ማሰሪያ/ ነው፡፡ ከነብይነት ደረጃ ቀጥሎ የሚቀመጥ ደረጃ ነው፡፡ እውነተኛ ሰዎች መቀመጫቸው ወንዞች ምንጮችና የሚፈሱበት የጀነት ቤቶች ናቸው፤ በዚህ ቤት/ጀነት/ ቀልባቸው የተያያዘና የአላህ እርዳታ ያልተለያቸው ናቸው”፡፡

እውነተኛ ሰው ለሐቅ እንጅ ህይወትን አይመኝም፡፡ በራሱ ላይ ጉደለትን እንጂ አይመሰክርም፤ የሚወደውን አላህን ውዴታ ለማጣጣምና በዒባዳ ለመቆም እንጂ መኖርን አይወድም፡፡ ወደ አላህ የሚያቀርበውንና ዲን እንዲኖረው የሚያደርጉትን ሰበቦች የሚያበዛ፤ ለዱንያ ብሎ ወደ ዲን እና ወደ አላህ የማይጠጋ፤ ለስሜቱም ብሎ አላህን የማያመልክ ነው፡፡ ዑመር ኢብኑልኸጣብ(ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ

“ሶስት ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ ዱንያ ላይ መቆየት አልመኝም ነበር፡፡“

  1. በጀሃድ ፈረስን አዘጋጅቼ መዝመት
  2. የሌሊት ሶላት እና
  3. ልክ ተምር እንደሚጣፍጠው ንግግራቸው ከሚጠፍጥ ሠዎች ጋር መቀማመጥ 

ዑመር ለማለት የፈለጉት፣ ጂሃድ፣ ሶላትና ጠቃሚ ዕውቀት እነዚህ የታላቆች ደረጃዎች መገለጫ  ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ቤት ጀነትና ደረጃቸውም ከፍ ያለ ነው፡፡

ሙዓዝ ኢብኑልጀበል ጣእረሞት ላይ እያሉ እንዲህ አሉ፡- “አንተ ጌታዬ ሆይ! እኔ ዱንያ ላይ መቆት የምመኘው የውሃ ቦይ ለመስራት፣ አትክልት ለመትከልና ሴት ለማግባት አይደለም፡፡ ነገር ግን ዱንያ ላይ መቆየት የምመኘው የተጠማን ለማጠጣት፣ የሌሊት ሶላትን ለመስገድና ዑለሞች ባሉበት የዕውቀት ማድ ላይ በጉልበቴ ለመዳህ ነው”፡፡

እውነተኛው ሠው ከዚህ አንፃር ነፍሱ ብዙ እንዳጎደለች ይሰማዋል፡፡ ይህን የመሰለ ስሜት የሚያድርበትም ከዚህ የተሸለ ትልቅ ስራ መስራት ስለሚፈልግና ራሱንም ስለሚያሳንስ ነው፡፡ የነፍሱን ነውር ጠንቅቆ ስለሚያውቅና የራሱ ስንቅ ቀላል መሆኑን ስለሚገነዘብ ነው፡፡ አላህን ያወቀ ሰው ራሱን ያውቃል፡፡ ራሱን ያወቀ ደግሞ የነፍሱን ጉድለት ማየት ይችላል፡፡

እውነተኛ ሰው የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መከተልን፣ በውጪም በውስጥም ለሳቸው ጥሪ ምላሽ መስጠትን፤ መንገዳቸውን አጥብቆ መያዝ፣ በትዕግስትና ኢኽላስ በተሞላበት በሁሉም እንቅስቃሴው አላህን ማምለክን አይቀሬ ጉዳይ አድርጎ ይመለከታል፡፡ በርግጥ አላህም ከባሪያው ይህንኑ እንጂ ሌላ አይወድም፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ነገር አካላዊ ፍላጎትን የማሟላት ወይም የነፍስን ስሜት የማዳመጥ  ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ስራ አላህ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ስራው ተወዳጅ የሆንና የአላህ መልእክተኛ ባመጡት መልኩ ሲሆን እንዲሁም በጉዳዩ አላህ ብቻ ታስቦ ሲሰራ ነው፡፡

እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን እውነተኛ ሠው በዒባዳ ከሚጣጣሩ ሠዎች ይለያል፡፡ ከመንገዱም የሚደርስበት የለም፡፡ ምክንያቱም በዚህ መስመር ተጓዦቹ አናሳ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ መንገደኞች ስሜታቸውን እያጣጣሙ ተሳፋሪዎች ናቸውና ነው፡፡ ራሳቸውን ለራሳቸው ስሜት እርቃን ያስቀሩም ናቸው፡፡ ስለሆነም እውነተኛ ሰውና እነዚህ ሠዎች አራምባና ቆቦ ናቸው፡፡

ሁለተኛው ባህሪይ

  • ትዕግስት ፡- በመከራና በአላህ መንገድ በሚደርስ ችግር መታገስ

የአላህ ባርያ ቁርአንን በሚቀራበት ጊዜ መከራ የዚህ አለም አንዱ አካል እንደሆነ ከዚህም መከራ ፈፅሞ መራቅ እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ መከራ የእውነተኛ የአላህ ባርያ የሚጓዙበት መራራ መንገድ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ቀጣዩ የአላህ ቃል ያረጋግጥልናል

الم
أَحَسِبَ النَّاسُ أَن يُتْرَكُوا أَن يَقُولُوا آمَنَّا وَهُمْ لَا يُفْتَنُونَ
وَلَقَدْ فَتَنَّا الَّذِينَ مِن قَبْلِهِمْ ۖ فَلَيَعْلَمَنَّ اللَّهُ الَّذِينَ صَدَقُوا وَلَيَعْلَمَنَّ الْكَاذِبِينَ

አ.ለ.መ (አሊፍ ላም ሚም)፤ ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚተው መኾናቸውን ጠረጠሩን፤እነዚያንም ከእነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፡፡ እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል፡፡ ውሸታሞቹንም ያውቃል፡፡ አል-ዐንከቡት፤1-3

በሌላም የቁርአን አንቀፅ፣

لَتُبْلَوُنَّ فِي أَمْوَالِكُمْ وَأَنفُسِكُمْ وَلَتَسْمَعُنَّ مِنَ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ مِن قَبْلِكُمْ وَمِنَ الَّذِينَ أَشْرَكُوا أَذًى كَثِيرًا ۚ وَإِن تَصْبِرُوا وَتَتَّقُوا فَإِنَّ ذَٰلِكَ مِنْ عَزْمِ الْأُمُورِ

በገንዘቦቻችሁና በነፍሶቻችሁ በእርግጥ ትፈተናላችሁ፡፡ ከእነዚያም ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡትና ከእነዚያም ከአጋሩት ብዙን ማሰቃየት ትሰማላችሁ፡፡ ብትታገሱና ብትጠነቀቁ ይህ ከጥብቅ ነገሮች ነው፡፡ አል-ዒምራን፤186

እንዲሁም

وَلَنَبْلُوَنَّكُم بِشَيْءٍ مِّنَ الْخَوْفِ وَالْجُوعِ وَنَقْصٍ مِّنَ الْأَمْوَالِ وَالْأَنفُسِ وَالثَّمَرَاتِ ۗ وَبَشِّرِ الصَّابِرِينَ

الَّذِينَ إِذَا أَصَابَتْهُم مُّصِيبَةٌ قَالُوا إِنَّا لِلَّهِ وَإِنَّا إِلَيْهِ رَاجِعُونَ

أُولَٰئِكَ عَلَيْهِمْ صَلَوَاتٌ مِّن رَّبِّهِمْ وَرَحْمَةٌ ۖ وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُهْتَدُونَ

ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ታጋሾችንም (በገነት) አብስር፡፡እነዚያን መከራ፤ በነካቻቸው ጊዜ «እኛ ለአላህ፤ ነን እኛም ወደርሱ ተመላሾች» ነን የሚሉትን (አብስር)፡፡እነዚያ በእነርሱ ላይ ከጌታቸው የኾኑ ምሕረቶች ችሮታም አልሉ፡፡ እነርሱም (ወደ እውነት) ተመሪዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ አል-በቀራ፤155-157

وَلَنَبْلُوَنَّكُمْ حَتَّىٰ نَعْلَمَ الْمُجَاهِدِينَ مِنكُمْ وَالصَّابِرِينَ وَنَبْلُوَ أَخْبَارَكُمْ

ከእናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ፣ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልጽ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ሙሐመድ፤ 31

አላህ ባሪያውን ሲወደው ይፈትነዋል፡፡ የወንጀል ቅሪት ካለበት እዚሁ ዱንያ ላይ በቅጣት ያወራርድለታል፡፡ ወንጀል ከሌለበት ደግሞ ምንዳ እንዲያገኝና ደረጃውን ከፍ እንዲያደርግ ይረዳዋል፡፡ በመከራ ወንጀል ሲታበስ ደረጃም ከፍ ይላል፡፡ እዚህ ላይ ነቢያት ከምንም በላይ እጅግ በጣም መከራን ተሸካሚዎችና ታጋሽ ነበሩ፡፡

“አቢሰዒድ አንድ ጊዜ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ገቡ፡፡ ረሡል (ሰ.ዐ.ወ) በትኩሳት ሰውነታቸው ሙቆ ወፍራም ልብስ ጣል አድርገውባቸዋል፡፡ አቢሰዒድም እጁን ከልብሱ ላይ አሳርፎ አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ምን የበረታ በሽታ ነው የያዘዎት? አላቸው፡፡ ረሡልም እኛ እንደዚሁ ነን መከራ ይበረታብናል፡፡ ምንዳም ይደራረብልናል አሉት፡፡ ከዚያም አንቱ የአላህ ምልዕክተኛ ከሠዎች መካከል መከራ የሚበረታበት ማን ነው? ሲል እሳቸውም ነብያት ናቸው አሉት፡፡ ከዚያስ እነማን ናቸው? ሲላቸው ዑለሞች ናቸው፡፡ ከዚያስ ሲላቸው ደጋግሰዎች አሉት፡፡ ከመካከላቸው አንዱ በቅማል ተሰቃይቶ ለሞት እስኪበቃ ድረስ መከራ ይደርስበታል፡፡ ሌላው ደግሞ ከደረበው ልብስ በቀር የሚለብሰው አጥቶ በድህነት ይፈተናል፡፡ ከመካከላችሁ በስጦታ እንደሚደሰት እነሡ ደግሞ መከራ ሲደርስባቸው በጣም ደስ ይላቸዋል”፡፡ በሌላ የሐዲስ ዘገባ “እጅግ በጣም የበረታ መከራ የሚደርስባቸው ነብያት ናቸው፡፡ ከዚያም እያለ ይቀጥላል፡፡ አንድ ሠው በእምነቱ ልክ ይፈተናል፡፡ በዲኑ በጣም ጠንካራ ከሆነ መከራው በጣም ይበረታበታል፡፡ በዲኑ እንደነገሩ ከሆነ ደግሞ መከራ እንደአቅሙ ይሆናል፡፡ መከራ አንድን ሠው ምድር ላይ እየተንቀሳቀሰ አይተወውም ወንጀሉን የሚጠርግለት ቢሆን እንጅ”፡፡

የመከራ ምንዳ ጥፍጥናና የመከራውን ብርታት መርሳት

ኢብኑልቀይም እንዲህ ይላሉ፡- “አንድ ሠው በበዳይ ሰው ከሚያደርስበት መከራና ከዚህ ውጪ በሚደርስ ችግር ለመታገስ በሶት መንገዶች ነገሩን መቋቋም ይቻላል፡-

  1. በመከራው የሚገኘውን ጥሩ ምንዳ ማስታወስ፡- አንድ ሠው በችግር ምክንያት ስለሚደርስ መከራና ስለሚያስከትለው ምንዳ ያለው ግንዛቤና እርግጠኝነት መከራውን ያቃልለታል፡፡ ምክንያቱም ማካካሻ የሚሆነው ነገር አግኝቷልና፡፡ አንድ ሠው ትልቅ መከራ ደርሶበት ከቻለውም መከራውን ማቃለል ይቻላል፡፡ነፍስ ከችኩልነቷ የተነሳ የሁሉንም ነገር ውጤት በቅርብ ማየትን ትሻለች፤ አዕምሮ ደግሞ የወደፊቱና የመጨረሻው ግብ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

ምሁራን አስተያየቶች እንደሚስማሙበት ተድላ እንዲሁ በፀጋ አይገኝም፡፡ አንድ ሠው በመከራ ጊዜ ትዕግስት ካደረገ የዕረፍትን ሀገር ይጎናፀፋል፡፡ እንደ ችግሩ መጠን እረፍት ይገኛል፡፡

ጭንቀትም ይመጣል እንደተሸካሚው፣

ቸርነት ይታያል ቸር እንደሚሆነው፡፡

ትልቅ በትንሽ አይን አንሶ እነደሚታየው

በትልቅ አይንማ ትንሹም ትልቅ ነው፡፡

ቁምነገር ምንድን ነው፤ የአንዱን መከራ የመጨረሻ ውጤት ያሰበ ሰው፤ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የደረሰበትን ችግር በቀላሉ መወጣት እገዛ ያገኛል፡፡ መከራን ቀለል አድርጎ በመመልከት ትእግስትን ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በፈቃድህ ነው ወይስ በነገሮች አስገዳጅነት የሚለው ይወስነዋል፡፡

2. ነገ ድል (ከመከራ ነጻ መውጣት) እንደሚመጣ ማሰብና መጠባበቅ፡- ይህም ሲባል ይህን መከራ ታገሶ በማሳለፍ የሚመጣውን ጣእም በማስታወስ አሁን እየደረሰ ያለውን መከራ ቸል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ከያንዳንዱ መከራ ጀርባ ድል አለ፡፡

3. አላህ ለሡ የዋለለተትን ፀጋዎች ማስታወስ /መቁጠር/፡፡ ፀጋዎቹን በማስታወስ መቁጠር ካቃተው ወይም ከብዛታቸው ተነሳ መቁጠር ከተሳነው መከራው ይቀልለታል፡፡ ከዚህም አንፃር አላህ ከዋለለት ውለታ አንጻር የሱ መከራ ከባህር ላይ ጠብ እንዳለ የውሃ ጠብታ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የኖርካቸውን የአላህ ጸጋዎች ማስታወስ ማለት ከችግሩ በፊት የነበርክበትን ሁኔታ ማሰብ ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ወደፊት የሚመጣውን ጸጋና ጥሩ ምንዳን ማሰብን መጠበቅ ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያው ዱንያ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአኺራ ነው፡፡ ከታሪክ እንደሚነገረው አላህን በጣም ከሚገዙ ሴቶች የሆነች አንዲት ሴት፤ ጣት በመቆረጥ አደጋ ሲገጥባት ሳቀች፡፡ በዙሪያዋ ካሉት ሠዎች አንዱ እንዴት ትስቂያለሽ? ብሎ ጠየቃት፡፡ እኔ በአዕምሮህ ልክ እነግርሃለሁ፡፡ የምንዳው ጥፍጥና የመከራውን መራራነት አስረሳኝ አለችው፡፡ የሰውዬው አዕምሮ መከራ ተሸካሚዋ የደረሰባትን መከራ የመጨረሻው አደጋ አድርጎ ያስብ ነበር፡፡ አሷ የመከራውን መልካም ጎን መምረጧ፣ በምስጋናና በውዴታ ነገሩን ማጣጣሟና ከወደፊቱ አንፃር ጉዳዩን በምስጋና ማሳለፍን መምረጧ ነበር ለሰውየው የሚከብደው፡፡

ውድ ወዳጄ ሆይ! የአላህ ወዳጅ የሚሆነው እውነተኛና ታጋሽ ነው፡፡ መታገስና እውነተኛነት የነብያት ስነምግባር መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች የደጋጎች ስንቅና የአመስጋኞች መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም አላህ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَعِينُوا بِالصَّبْرِ وَالصَّلَاةِ ۚ إِنَّ اللَّهَ مَعَ الصَّابِرِينَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስና በሶላት ተረዱ፡፡ አላህ (በእርዳታው) ከታጋሾች ጋር ነውና፡፡ አል-በቀራ፤153

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here