ለምንድን ነው ሁኔታችን መጥፎ የሚሆነው? መስጂዶቻችን በሺዎች የሚቆጠሩ፤ የሰጋጆቹ ቁጥር በሚሊዩን የሚቆጠር ነው?! እዚህ ጋር አንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡ መልሱም እንዲሁ ግልፅና ቀድሞም የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የመልሱን እውነታ ለማወቅ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል፡፡ ያቀረብነውን ጥያቄም ምላሽ ለመስጠት የቁርአን መረጃዎችን በማጣቀስ እንመልሳለን፡፡ በዚህም በሰላት ላይ ያለንን አቋም እናውቃለን፡፡
አላህ በምዕራፍ መርየም ወዳጁ ስለሆኑ ነቢዩ ኢብራሂመ እና ዝርያዎቻቸውመ እንዲህ ይላል፡-
እነዚህ (ዐሥሩ) እነዚያ አላህ በእነሱ ላይ የለገሰላቸው ከነቢያት ከአዳም ዘር ከኑሕ ጋር (በመርከቢቱ ላይ) ከጫናቸውም (ዘሮች) ከኢብራሂምና ከእስራኤልም ዘሮች ከመራናቸውና ከመረጥናቸውም የኾኑት የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ፡፡ ከእነሱም በኋላ ሶላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ፡፡ (መርየም፤58-59)
የቁርአን አንቀፅ መሰረት ፤በነብዩ ያዕቁብ (በኒኢስራኢል) እና ኢስማዒል ዘሮች (አረቦች) ሰላትን በተገቢው መንገድ አንዳላልሰገዱት ያለመለክታል፡፡
ከዚህ የምንረዳው ሶላት ከነ ሙሉ ስርዓቷና ውበቷ ካለተሰገደች ሙሉ የሰላትን ዋጋ አታስገኝም፡፡ ፋቲሀ መቅራት ፤ ሩኩዕ ፤ሱጁድ፤ መቆምና መቀመጥ የሰላት ሩክን ቢሆኑም በተገቢው መንገድ ካልተፈፀሙ ሰላት መስገድ አያስኙም፡፡
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ሶላትን መስገድና ሶላትን ማቋቋም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ሶላትምን ወቅቱን ጠብቆ አለመስገድም ሌላው የሶላት መጥፋት ምልክት ነው፡፡ ለመሆኑ “ኋላ የመጣው” ትውልድ ሰላቱን እንዳጠፋ እናስ አጥፍተነዋልን? በርግጥ ሶላትን ማጥፋት ማለት ሙሉ በሙሉ መተው ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን “ማጥፋት” ማለት “እየፈፀሙት አለመጠቀም” ማለት ነው፡፡ የ“ሶላት መጥፋት” ትርጉሙ ከሰላት ሊገኝ የሚገባውን መሰረታዊ የሆነው “ተቅዋን ” ማጣት ማለት ነው፡፡
ሶላት መዳረሻ ወይስ ዓላማ?
ሶላትም ሆነ ሌሎች ዒባዳዎች በራሳቸው በራሳቸው ግቦች አይደሉም ፡፡ አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ (አል-በቀራ፤21)
የመጨረሻ ግቡ “ተቅዋ” ማስገኘት ነው፡፡ ሌሎቹም ዒባዳዎች ተቅዋን (አላህ መፍራት) ማስገኘተ ነው አላማቸው፡፡ ሶላት እንዲሁ ሰጋጁን ከመጥፎ ነገር ሲያቅበው ሰውየው አላህ ፈርቷል ማለት ይቻላል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
ከመጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፡፡ ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡ አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል፡፡ (አል-አንከቡት፤45)
ሶላቱን በአግባቡ አለመስገድ በራሱ ወነጀል የሆነ ተግባር ነው፡፡ ምናልባት እሱ አማኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ነፃ ከሚወጡት ሰዎች ደግሞ መሆን አይችልም፡፡ ቀጣዩን አንቀፅ እናንብብ
እነዚያም እነሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የኸኑት (አገኙ)፡፡ እነዚያ ወራሾቹ እነርሱ ናቸው፡፡ እነዚያ ፊርደውስን (ላዕላይ ገነትን)፤ የሚወርሱ ናቸው፡፡ እነርሱ በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ (አል-ሙዕሚኑን፤9-11)
ሶላትን ስርዓቷን ጠብቆ በመፈፀም፤ በፍርሀት (ኹሹዕ) መስገድና ከሰላት በኃላ ወንጀል አለመፈፀም ጥብቅ ትስስር ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ (ኹሹዕ) ለአንድ ሙዕሚን ኢኽላስ ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው፡፡ ምክንያቱም በየረከዓው አላህን “ትክክለኛውን መንገድ ምራን” የሚለው አንቀፅ ስለሚያነብ፡፡ በሰላት ውስጥ የሚኖር ኹሹዕና መጥፎ ስራን መስራት አብረው አይኖረም ፡፡ ከሰላት በኃላም ወንጀልም መስራት አብሮ አይገኝም፡፡ ምክንያቱም ያ ከሆነ የአላህ ንግግር “ትክክለኛውን መንገድ ምራን” ሚለው አንቀፅ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ሶላታችን ለሰው እይታ የሚሰገድ ራስን ማታለያ ነው የሚሆነው፡፡
በቁርአን አገላለፅ መሰረት ሶላት መስገድ ማለት ፤ ኹሹዕና ጊዜዋን ጠብቆ በአንድ ላይ አጣምሮ መፈፅም ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ፡፡ እነዚያ እነርሱ በስግደታቸው ላይ ዘውታሪዎች የኾኑት፡፡(አል-መዓሪጅ፤22-23)፡፡
በቁርአን ውስጥ “አቃመ” የሚለው ግስና የግሱ እርባታዎች ከሶላት በተያያዘ መልኩ አርባ ጊዜ ያህል ተወስተዋል፡፡ በአረብኛ ቋንቋም በቁርአን አገባብ መሰረትም በአንድ ነገረ ላይ ቆመ ማለት በነገሩ ዘወተረበት፣ ጠበቀው ማለት ነው፡፡ አላህም ከመልካም ሰሞቹ መካከል “አል-ቀዩም” አንዱ ነው፡፡
በመሐላዎቻችሁ በውድቁ (ሳታስቡ በምትምሉት) አላህ አይዛችሁም፡፡ ግን ልቦቻችሁ ባሰቡት ይይዛችኋል፡፡ አላህም በጣም መሐሪ ታጋሽ ነው፡፡ (አል-በቀራ፤225)
አንቀፅ “አል-ቀዩም” የሚለውን ስም ሲብራራ « በሁሉም ነገር ላይ አስተናባሪ ፤ ለአንድም ነገር ዝንጉ ያልሆነ »በሚል ነው፡፡ ከዚህ ትርጓሜ አንፃር አላህ ፍትህን ፤ሚዛናዊነትነ ጠባቂ አንድንሆን ያዘናል፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቀዋሚዎች በነፈሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ (አል-ኒሳእ፤135)
ከዚህ አንፃርም ሶላትን በተገቢው መንገድ የማይሰግድ ሰው የትኛው እንደሆነ ማወቅ እንችላለን፡፡ ሁሉም ወንጀልን፤ ብልሹነትንና በደልን የሚፈፅሙና የሚያስፋፋ ሰዎች ሶላትን በትክክል የሚፈፅሙ አይደሉም፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች የሰላት ጉዳይ በሚገባ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሲሆኑ ይችላሉ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
ለከሓዲዎች በነፍሶቻቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲኾኑ የአላህን መስጊዶች ሊሠሩ አይገባቸውም፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው ተበላሹ፡፡ እነሱም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ የአላህን መስጊዶች የሚሠራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣ ሶላትንም በደንቡ የሰገደ፣ ግዴታ ምጽዋትንም የሰጠ ከአላህም ሌላ (ማንንም) ያልፈራ ሰው ብቻ ነው፡፡ እነዚያም ከተመሩት ጭምር መኾናቸው ተረጋገጠ፡፡ አል-ተውባ፤17-18)
መልእክተኛው በነበሩበት ዘመን እንኳን ሙናፊቆች ሶላት ይሰግዱ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚፈለገውን ሶላት አልነበረም የሚሰግዱት ፡፡ ሶላታቸው የይዩልኝ ሶላት ነበር ፡፡ ሶላታቸው ማታለያ ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ጊዜ ጠበቂያ ነበር፡፡ በርግጥ ራሳቸውን ነው ያታለሉት ፡-
መናፍቃን አላህን ያታልላሉ፡፡ እርሱም አታላያቸው ነው፡፡ (ይቀጣቸዋል)፡፡ ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾች ስዎችን የሚያሳዩ ኾነው ይቆማሉ፡፡ አላህንም ጥቂትን እንጅ አያወሱም፡፡ (አል-ኒሳእ፤142)
የሰላት ፍሬ
በቁርአናዊው የቃላት ብያኔ መሰረት ሶላትን ማቋቋም ማለት በውስጧ “በኹሹዕ” መስገድ ፤ በተቅዋ መታነፅና በሶላቶች መካከል በስነ ምግባር መዋብ ማለት ነው፡፡ ሶላትን ማቋቋም በእኛ አረዳድ ሰዎች መስጅድ እንዲመጡ የምናደርገው ኢቃም ማለት ነው፡፡ በርግጥ “ቀድቃመቲ -አል-ሶላት”(ሰላት ቆመች) የሚለው ቃል የሶላት ስርዓት በአግባቡ ለመፈፀም ቁሙ ማለት ሲሆን የሰላት በአግባቡ መቋቋም በበጎ ነገር ከሌሎች ጋር መተባበር፣ በመልካም ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል የሚል ትርጉምም ይኖረዋል፡፡
ሰዎች የሚያውቋቸው በጎ ስነምግባራት ለምሳሌ፡- እውነተኛነት ፤ለሰዎች መልካም መዋል፤ፍትሀዊነት ፤አደራን መጠበቅ፤ ቸርነት፤ሰላምታ ፤ ሆደ ሰፊነትና (መቻቻል)ና ሌሎችም ከመልካም ነገሮች ይመደባሉ፡፡ ከመጥፎ መከልከል ሲባል ለምሳሌ፡- በደል፤ ድንበርን ማለፍ ፤ስግብግብነት፤ አጉል እኔነት፣ መንበጣረርና ሌሎችም መጥፎ ምግባሮች ይካተታሉ፡፡ ይህ አይነቱ በመልካም የሚያዝና ከመጥፎ የሚከለክል ህብረተሰብ በረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ጊዜ ተከሰቶ የነበረውን የመዲና ህብረተሰብ ያሰታውሰናል፡፡ በዚህ ህብረተሰብ ውስጥ የሶላት ሚና በግልፅ ይታይ ነበር፡፡
ሶላት እየሰገደ ሽርክ ውስጥ የሚዘፈቅና ወንጀል ውስጠ የሚንከባለል ሶላቱ ትርጉም የለሽና ዋጋ ቢስ ነው፡፡ አንዳንዶቸ ሶላትን የአካል አንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ የሚፈፅሙ ስህተት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሶላቻቸው ወንጀል ለመስራት ምንክያት ይሆናልና ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ሶላት በሰገደ ቁጥር የሰራውን ቢሰራ ወንጅሉ የሚማርለት ይመስለዋል፡፡ ይህ በራሱ ስህተት ላይ ይጥለዋል፡፡ በዲኑም እንዲያሰተባብል በር ይከፍትለታል፡፡
ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) (አል-ማዑን፤1)
ከዚያ ቀጠል በማድረግ
ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው፡፡ ወዮላቸው ለሰጋጆች፡፡ ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)፡፡ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለኾኑት፡፡ የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለኾኑት (ወዮላቸው)፡፡ (አል-ማዑን፤4-7)
በዚህ አንቀፅ የሚገርመው ነገር ዲኑን እያስተባበለ፤ የቲሞችን እያንገላታ፤ ደሀዎችን ለማብላት የማያስብ ሰው፤ ከነዚህ መጥፎ ሰራዎች በተጨማሪ ሶላትነ ሰጋጅ ነው፡፡ ነገር ግን ሶለቱንም የረሳና ወንጀሉንም ችላ ያለ ነው፡፡ እንዲያውም በሶላቱ የሰዎችን እይታ ይሻል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይቆም የሰውን ገንዘብ ያለአግባብ መብላትና ግልፅም ድብቅም ንፍቅናንም በግልጽ ያሳያል፡፡
የአላህን ቁርአናዊ አንቀፅ በመጥቀስ ሀሳባችንን እንቋጭ፡-
መልካም ሥራ ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም፡፡ ግን መልካም ሥራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነቢያትም፣ ያመነ ሰው ገንዘብንም ከመውደዱ ጋር ለዝምድና ባለቤቶችና ለየቲሞች ለምስኪኖችም፣ ለመንገደኞችም፣ ለለማኞችም፣ ለጫንቃዎችም (ማስለቀቅ) የሰጠ ሰውና ሶላትንም ደንቡን ጠብቆ የሰገደ፣ ዘካንም የሰጠ፣ ቃል ኪዳንም በገቡ ጊዜ በኪዳናቸው የሞሉ (ሰዎች ሥራ) ነው፡፡ በችግር በበሽታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)፡፡ እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው፡፡ እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ (አል-በቀራ፤177)
በዚህ አጋጣሚ ማንኛውም ሰው ከሰላት አንፃር ያለውነ ቦታ (አሰጋገዱን ውጤቱን) ማየትና መገምገም ይኖርበታል፡፡ ይህን ሲያደርግ ፤ ከአላህ ዘንድ ያለውን ቦታ ማወቅ ያስችለዋል ፡፡ አላሀ ሁላችንንም ትክክለኛውን መንገድ እንዲመራን እንጠይቀዋለን፡፡