በእስልምና የጊዜ አቆጣጠር ሙሀረም የአዲሱ አመት የመጀመሪያው ወር ነው። ሙሀረም ወር እጅግ ከተከበሩ ወራቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህንኑ በማስመልከት በዚህ አጭር መጣጥፍ የሂጅራ አቆጣጠር እንዴት እንደተጀመረ መለስ ብለን በጥቂቱ ለመቃኘት እንሞክራለን። እስልምና ታሪክ ብዙ ክስተቶችን ያዘለ ነው። ክስተቶቹን መስማቱ ነፍስን ያጓጓል። ስሜትን ይይዛል።

የሚገርመውና የሚያሣዝነው ግን አብዛኞቻችን እነኚህ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የሆኑ ክስተቶች “መቼና የት ተከሠቱ?” ቢባል ብዙ የምናውቅ አይደለንም።

በሂጅራ አቆጣጠር መሥራት መቼ ተጀመረ?

በሂጅራ አቆጣጠር መሥራት የተጀመረው በ 16ኛው አሊያም በ 17ኛው አመት በዑመር ኢብኑ አልኻጧብ (ረ.ዐ) የኸሊፋነት ዘመን ነው።

አስ-ሱሀይሊ አር-ረውድ አል-አንፍ በተባለው መፅሃፋቸው “ሰሃቦች የሂጅራን አቆጣጠር ፅንሠ ሀሣብ የወሰዱት

لَّمَسْجِدٌ أُسِّسَ عَلَى التَّقْوَىٰ مِنْ أَوَّلِ يَوْمٍ [٩:١٠٨]

“ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው (የቁባ) መስጊድ…” (አት-ተውባ 9፤ 108)

ከሚለው የቁርዓን አንቀፅ ነው። ይህ ሲባል ግን ያ ቀን ባጠቃላይ የቀናት ሁሉ የመጀመሪያው ቀን ነው ማለት አይደለም። ነገርግን ያ ቀን አላህ (ሱ.ወ) እስልምናን ከፍ ያደረገበት የመጀመሪያው ቀን መሆኑን ያመላክታል። የአላህ ነቢይም (ሰ.ዐ.ወ) አምላካቸውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ያመለኩበት ቀን ነው። መስጅድም የተጀመረው በዚሁ ቀን ሲሆን ሰሃቦችም ኢስላማዊው አቆጣጣር ከዚያ ቀን እንዲጀምር በሀሣብ ተግባብተውበታል።” (አር-ረውድ አል-አንፍ ቅጽ 4፣ ገጽ 255)

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የሂጅራ አቆጣጠርን ለማስቀመጥ አቢይ ክስተቶች ያሏቸው ነገሮች ነበሩ። ከነኚህም ምክኒያቶች መካከል የታሪክ አጥኚዎች የተስማሙበትን አራቱን ማስቀመጥ ይቻላል። ውልደታቸው፣ በነቢይነት መላካቸው፣ ስደታቸው እና ሞታቸው።

ብዙዎች ያስበለጡት ከስደታቸው ቀን ይጀመር የሚለውን ነው። ምክኒያቱም የተወለዱበት እና የተላኩበት ትክክለኛው ቀን ከውዝግብ የፀዳ አይደለም። ሞት ደግሞ የያዘው ዜና ብሥራትን ሣይሆን ሀዘንን ነውና ይህን ቀን ለማስታወስ ባለመፈለግ ሰሃቦቹ በስደት ቀናቸው ይሆን ዘንድ ተስማሙ። ወሩንም ከረቢዕ አል-አወል ወደ ሙሀረም የወሰዱበት ምክንያት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስደትን ለማድረግ የቆረጡት በሙሀረም ወር በመሆኑ ነው። ከመዲና የአንሷር ሰዎች ጋር የቃልኪዳኑን ስምምነት የፈፀሙት በዚልሂጃ ወር ለሙሀረም መግቢያ ነው። ከመዲና ሰዎች ጋር ቃልኪዳን ተጋብተው ለስደት ከቆረጡ በኋላ መጀመሪያ ያዩት ጨረቃ የሙሀረም ወር ጨረቃ ነበር። ይህም ለሂጅራው አቆጣጠር የሚጀመሪያው ወር እንዲሆን አድርጎታል። ይህንንም ትንተና አብዛኞቹ የታሪክ አጥኚዎች ተስማምተውበታል።

ዑመር አቆጣጠሩን ለማስቀመጥ የፈለጉበት ምክኒያቶች ናቸው ብለው ኢብኑ ሀጀር በፈትሁል-ባሪ ላይ ካስቀመጡት መካከልም፡-

“አባ ሙሣ ለዑመር (ረ.ዐ) ‘ካንተ መቼ እንደተፃፈ የማይታወቅ ደብዳቤ ወደኛ ይመጣል።’ በማለት ፃፈላቸው። ዑመርም በዚሁ ዙሪያ ለመወያየት ሰዎችን ሰበሰቡ። ከፊሎቹ ‘ነቢዩ ከተላኩበት ቀን ጀምሮ ይሁን’ አሉ ሌሎቹ ደግሞ ‘ከስደታቸው ቀን ጀምሮ ይሁን’ አሉ። ዑመር (ረ.ዐ) ግን ‘እውነትና ሀሠት መካከል መለያ ያደረገችው ሂጅራ /የስደቷ ቀን/ ነችና በሷ ፃፉ።’ አሏቸው። ይህም 17ኛው አመት ነበር። በዚህ ከተስማሙ በኋላ ከፊሎቹ ‘በረመዷን ወር ይጀመር’ አሉ። ዑመር (ረ.ዐ) ግን ‘በሙሀረም ወር ጀምሩ። ሰዎች ከሀጃቸው የሚመለሱበት ጊዜ ነውና።’ አሏቸው። እነሱም በዚሁ ተስማሙ።” (ፈትሁል-ባሪ ቅጽ 7፣ ገጽ 315)

አህመድ እና ዐሩባ በአዋኢል፣ ቡኻሪ በ አል-አደብ እንዲሁም አልሃኪም ከመይሙን ኢብኑ መህራን እንደዘገቡት ደግሞ፡-

“ለዑመር ክስተቱ የሸዕባን ወር የሆነ ጉዳይ ተነሣላቸው። በዚህን ጊዜ ‘የትኛው ሸዕባን? ያለፈው ያለንበት ወይንስ የሚመጣው?’ በማለት ከጠየቁ በኋላ ‘ሰዎች የዘመናትን ጊዜ የሚያውቁበት ነገር አስቀምጡላቸው።’ አሉ። በዚህን ጊዜ የተወሰኑ ሰዎች የፋርስ ሰዎች አንድ ንጉስ ከሞተ በኋላ ሌላው ሲሾም አዲሱ ንጉስ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ዘመናትን እንደሚቆጥሩ ሁሉ እንደዚያ መጠቀም ፈለጉ። ይህን ማድረግ ግን አልወደዱም። ከፊሎቹ ደግሞ በሮማውያን አቆጣጠር ከእስክንደር ዘመን ጀምሮ ይደረግ አሉ። ይህንንም ጠሉ። ሌሎች ደግሞ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የውልደት ጊዜ ጀምሮ ይሁን አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከመላካቸው ጊዜ ጀምሮ ይሁን አሉ። ዐሊ ኢብኑ ጧሊብ እና ሌሎች ‘ከመካ ወደ መዲና ከተሰደዱበት ቀን ጀምሮ ይሁን። የተወለዱበትና ተላኩበት ቀናት እንደተሰደዱበት ቀን ሁሉም ሰው በይፋ የሚያውቋቸው አይደሉምና።’ በማለት ሀሣብ ሠጡ። ዑመርና ሌሎች ሰሃቦች ሀሣቡ መልካም እንደሆነ ተስማሙ። ዑመር አቆጣጠሩ ከአላህ መልእክተኛ የስደት ቀን እንዲጀምር አዘዙ። በዚያው አመት መጀመሪያው ወር ከሆነው ሙሀረም ወርም አቆጣጠሩ እንዲደረግ ሆነ።”

ኢብኑ አቢ ኸይሠማህ ከኢብኑ ሲሪን እንደዘገበው ደግሞ፡-

“አንድ ሰው ከየመን መጣና ‘የቀን አቆጣጠር የሚሉት ነገር አየሁኝ ይህ ቀን ይህ አመት በማለት ይፅፋሉ።’ አለ። ዑመርም ‘ይህ መልካም ነገር ነው እናንተም የቀን አቆጣጠር አስቀምጡ።’ አሉ። በሀሣቡ ከተስማሙ በኋላ አንዳንድ ሰዎች ከውልደታቸው ሌሎች ከመላካቸው ሌሎች በስደት ከወጡበት ቀን ሌሎች ደግሞ ከሞቱበት ቀን ጀምሮ ይሁን አሉ። ዑመር ግን ‘ከመካ ወደ መዲና ከወጡበት ቀን ጀምሮ አቆጣጠሩን አስቀምጡ።’ አሏቸው። ‘ከየትኛው ወር እንጀምር’ በሚለውም ተነጋገሩ። ከፊሎች በረጀብ እንጀምር አሉ። ሌሎች ደግሞ በረመዷን አሉ። ዑስማን (ረ.ዐ) አቆጣጠሩን ‘ከሙሀረም ወር ጀምሮ አድርጉት። እሱ የተከበረ ወር የአመቱ መጀመሪያና ሰዎችም ከሀጅ የሚመለሱበት ነውና።’ አላቸው። ይህ የሆነው በ17ኛው አሊያም በ16ኛው አመት በረቢዕ አል አወል ወር ነው። ተብሏል።”

አልሃኪም በአል-ሙሰተድረክ መፅሃፋቸው (ቅጽ 3፣ ገጽ 14) ውስጥ ከሰዒድ ቢን አል-ሙሰየብ እንደዘገቡት፡-

“ዑመር አቆጣጠር የሚጀመርበት የመጀመሪያው ቀን የትኛው ይሁን በሚለው ላይ ሰዎችን ሰበሰቡ። ዐሊም (ረ.ዐ) ‘የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሽርክ ምድርን በመተው ከተሠደዱበት ቀን ጀምሮ ይሁን።’ አለ። ዑመርም ይህንኑ አደረጉ።”

ከነኚህ ከወረዱት ዘገባዎች ላይ እንዳየነው “በሙሀረም ወር ይጀመር” የሚለውን ሀሣብ የሰነዘሩት ዑመር ዑስማን እና ዐሊ መሆናቸውን ነው። ዐሊ ከዚህም በተጨማሪ አቆጣጠሩ ከሂጅራ ቀን እንዲጀምር ሀሣብ ሰጥተዋል።

የሂጅራ አቆጣጠርን በማስቀመጡ ላይ ታሪክ አጥ-ጦበሪ (ቅጽ 4፣ ገጽ 38)፣ የኢብኑ ከሲርን አል-ቢዳያ ወን-ኒሃያ (ቅጽ 3፣ ገጽ 206)፣ የኢማም አስ-ሰኻዊን አል-ኢዕላን ቢተውቢኽ ሊመን ዘመ ታሪክ (ገጽ 78) እንዲሁም የኢማም ሱዩጢን አሽ-ሸማሪኽ ፊ ዒልም አት-ታሪኽን ኪታቦች ማየት ይቻላል።

4 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here