በመልካም ተግባር ላይ መዘውተር

0
8732

ስራችን ተቀባይነት አግኝቷልን?

አንድ ሰው የሰራው ስራ ተቀባይነት የማግኘቱ ምልክት በዚያ በሰራው ዒባዳ ላይ መዘውተሩ ሲሆን በተቃራኒው ተቀባይነት የማጣቱ ምልክት ደግሞ በዒባዳው ወረተኛ መሆኑ ነው።

ስራው ተቀባይነት ያገኘ ሰው አላህ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲታሰር ይቀራል። የዒባዳን በርን አይዘጋም ግንኙነቱን ቁርአን በመቅራት፤ ጀመዓና ጁመዓ በመሳተፍ ይቀጥላል።

ስራው ተመላሽ የሆነበት ሰው፤ ከተወሰነ የዒባዳ ሽርጉድ በኃላ ከቦታው ይጠፋል፤ በዚህም ከፈጣሪው ጋር በዒባዳ ይቆራረጣል። ቁርአን መቅራትና መስጂድ መሄድ እንኳ ቀርቶ ግዴታ ሶላቶችን መስገድ ጥያቄም መልክት ወስጥ ይገባል።

የዒባዳ ተቀባይነት ማግኘት ሌላው ምልክት ለምሳሌ ከረመዷን በኃላ ለዒባዳ ሁሌም በራችን ክፍት መሆኑ ነው። ይህ መሆኑ ይህ ሰው በሰራው ስራ ምንዳ ማግኘቱና በዱንያ ብስራት ማገኘቱን ያረጋግጣል። ምንዳ ማግኘት በአኼራ ብቻ የሚወሰን አይደለም። እንደውም በዱንያም የምንዳ ማግኘት አንዱ መገለጫ ለዒባዳ ዝግጁ መሆንና ዘውታሪ ሆኖ መቀጠል እንዲሁም ለሌላ በጎ ስራ መነሳሳት ነው። በዚህ የተነሳ ለሌላ ቅንነት አንዲበቃ በር ከፋች ይሆናል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَيَزِيدُ اللَّهُ الَّذِينَ اهْتَدَوْا هُدًى

“እነዚያንም የቀኑትን ሰዎች አላህ ቅንነትን ይጨምርላቸዋል፡፡” (መርየም፤ 76)።

وَالَّذِينَ اهْتَدَوْا زَادَهُمْ هُدًى وَآتَاهُمْ تَقْوَاهُمْ

“እነዚያም የተመሩት (አላህ) መመራትን ጨመረላቸው፡፡ (ከእሳት) መጥጠበቂያቸውንም ሰጣቸው፡፡”  (ሙሀመድ፤ 17)

ወንጀልና መጨረሻው

የወንጀል ትርፉ ሌላ ወንጀል ማስከተል ነው። የወንጀል መጠን እየተደራረብ የቀልቡን መጨለም ይጨምርራል። ቀልቡም ቀስ በቀስ በወንጀል ጨለማ ይጠቀጠቃል። ይህን “ዝገት” ነው አላህ በቁርአኑ እንዲህ ሲል የጠቀሰው።

كَلَّا ۖ بَلْ ۜ رَانَ عَلَىٰ قُلُوبِهِم مَّا كَانُوا يَكْسِبُونَ

“ይከልከል፤ ይልቁንም በልቦቻቸው ላይ ይሠሩት የነበሩት (ኀጢአት) ደገደገባቸው፡፡”  (አል-ሙጠፊፊን፤ 14)

በመልካም ስራ መዘውተር

በመልካም ስራ የመዘውተር ልምድ የሙዕሚኖች አርማ ነው። እንዲሁም እጅግ በጣም ተወዳጅና ወደ አላህ መቃረቢያ መንገዳቸው በመልካም ስራ ላይ ዘውታሪነታቸው ነው። ዓኢሻ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ እንደተዘገበው ረሱል (ሰ.ዐ.ወ)

اكْلفوا من العمل ما تطيقون؛ فإن الله لا يمل حتى تملوا، وإن أحب العمل إلى الله أدومه وإن قل

“በአቅማችሁ ልክ ስራ ስሩ፤ እናንተ ትሰለቻላችሁ እንጅ አላህ አይሰለችም። ከስራ ሁሉ እጅግ በጣም ተወዳጅ፤ ጥቂትም ቢሆን ዘውታሪነት ያለው ነው” (ሶሂህ)

ሙዕሚን ስራ ሲሰራ በቋሚነት ነው። ማለትም ሁልጊዜ በስራው ላይ ይዘወትራል ማለት ነው። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በስራ የመዘውተራቸው ማሳያ የሚሆነን የተሐጁድ ሶላት (የሌሊት ሶላት) ነው። በእንቅልፍ ወይም በህመም ምክንያት መስገድ ካልቻሉ ቀን ላይ አስራሁለት ረከዓ ሶላቶችን በመስገድ ያካክሱ ነበር።

በመልካም ስራ ላይ የመዘውተር ትሩፋቱ፡-

  1. ቀልብን ከንፍቅና ማፅዳትና ከጌታው ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከ፡-

ቀልብ እንደሚታወቀው የአካላችን መሰረት ነው። አቡሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳሉት

القلب ملك الأعضاء, والأعضاء جنوده, فإذا طاب الملك طابت جنوده, فبعلاج القلب يصلح البدن كله، وبفساده يفسد البدن كله، كما جاء في الصحيح: ” ألا وإن في الجسد مضغة، إذا صلحت صلح الجسد كله، وإذا فسدت فسد الجسد كله، ألا وهي القلب”.

“ቀልበ የአካል ንጉስ ነው። አካላት የቀልብ ወታደሮች ናቸው። ንጉስ ካማረ ወታደሮችም ያምርባቸዋል። የቀልብ ደህነት የቀሪው አካል ደህንቱ ነው። የቀልብ መላላት የሌላ አካል መበላሸት ነው።” በሐዲስ አንደተረጋገጠው «ንቁ! አካል ውስጥ የተላመጠ ስጋ የመሰለች ነገር አለች ። እሷም ጥሩ ከሆነች፤ ሁሉም አካል ጥሩ ይሆናል። እሷ ከተበላሸች ደግሞ ቀሪው አካል ይበላሻል። እሷም ቀልብ ነች” ብለዋል።

ኢማሙ ኒብኑልቀይም እንዳሉት “አላህ ዘንድ የሚበላለጠው ስራ መብዛቱ ሳይሆን ቀልብ ውስጥ በተቀመጠው ነገር ነው።” ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إن الله لا ينظر إلى صوركم وأموالكم ولكن ينظر إلى قلوبكم وأعمالكم

“አላህ የላይ ገጽታችሁ እና ገንዘባችሁን አይመለከትም። ነገር ግን ቀልቦቻችሁንና ስራዎቻችሁን ይመለከታል።”

አንድ ሰው ቀልቡ በኢማን ሲያበራ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መልካም ነገሮች ሁሉ ወደሱ ይጎርፋሉ። በዚህም ከአንድ በጎ ነገር ወደ ሌላ በጎ ነገር ይሸጋገራል። የአንድ ሰው የቀልብ ጤነኛነቱ ትልቁ መገለጫው በሰራው ስራ ላይ ጉድለት እየተሰማው ተቀባይነት አገኝ ይሆን በማለት በመልካም ስራ ላይ መዘውተር መቻሉ ነው። አላህ እንዳለው፡-

وَالَّذِينَ يُؤْتُونَ مَا آتَوا وَّقُلُوبُهُمْ وَجِلَةٌ أَنَّهُمْ إِلَىٰ رَبِّهِمْ رَاجِعُونَ

“እነዚያም የሚሰጡትን ነገር እነርሱ ወደ ጌታቸው ተመላሾች መኾናቸውን ልቦቻቸው የሚፈሩ ኾነው የሚሰጡት፡፡” (አል-ሙዕሚኑን፤ 60)

2. የአላህን ውዴታ ያስገኛል

ግዴታ በሆኑና ሱና በሆኑ መልካም ስራዎች ላይ መዘውተር የአላህን ውዴታ ያስገኛሉ። በሐዲስ አል-ቁድሰይ እንዲህ ይላል:-

من عادى لي وليًّا فقد آذنته بالحرب، وما تقرب إليَّ عبدي بشيء أحبَّ إليَّ من أداء ما افترضته عليه, ولا يزال عبدي يتقرَّب إليَّ بالنوافل حتى أحبَّه, فإذا أحببتُه كنت سمعه الذي يسمع به، وبصره الذي يبصر به, ويده التي يبطش بها, ورجله التي يمشي بها، وإن سألني أعطيته، وإن استعاذ بي أعذته

“ወዳጆቼን በላንጣ የሆነ፤ ከኔ ጋር ጦርነት እንደከፈተ ነው። አንድ ሰው ወደ አላህ ከሚቃረብባቸው ሰራዎች መካከል የበለጠ ተወዳጁ ግዴታዎችን ሲወጣ ነው። ሱና ሰራዎችንም ከመስራት አይወገድም እኔ እስክወደው። እኔ ስወደው መሰሚያ ጆሮው፤መመልከቻ አይኑ፤ የሚሰራበት እጁ እንዲሁም የሚጓዝበት እግሩ እሆነዋለሁ። ሲጠይቀኝ እሰጠዋለሁ። ጥበቃ ሲያሻው እጥብቀዋለሁ (ከመጥፎ ነገር)።”

3.ከመከራና ከችግር ለመዳን ምክንያት ነው፡-

በበጎ ስራ የመዘውተር ትልቁ ትሩፋት ከመከራና ከችግራ መዳን መቻል ነው። አንድ በድሎት ወይም በፍስሐ ወቅት ወደ አላህ ለመቃረብ የተጋ፤ በችግር ጊዜ አላህ አይተወውም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለኢብኑ ዓባስ (ረ.ዐ) እንዲህ የሚል (አደራ) አስተላልፈዋለወ።

يا غلام، ألا أعلمك كلمات ينفعك الله بهن” فقال: بلى، فقال: “احفظ الله يحفظك، احفظ الله تجده تجاهك، أو قال: أمامك، تعرف إلى الله في الرخاء يعرفك في الشدة, إذا سألت فاسأل الله، وإذا استعنت فاستعن بالله؛ فإن العباد لو اجتمعوا على أن يضروك بشيء لم يكتبه الله عليك لم يقدروا على ذلك, جفت الأقلام, وطويت الصح 

(حسن)

“አንተ ልጅ ሆይ! የሚጠቅምህ የሆኑ ቃላትን አላስተምርህምን? አሉት። እሱም አስተምሩኝ አላቸው። እሳቸውም አላህን ጠብቀው እሱም ይጠብቅሀል፤ አላህን ጠብቅ ፊት ለፊት ላይ ታገኘዋለህ። አላህን በፍስሐ ጊዜ እወቀው፤ በመከራ ጊዜ ያውቅሀል፤ ስትጠይቅ አላህን ጠይቅ፤ መታገዝ ስትፈልግ በሱ ታገዝ፤ ሰዎች በሙሉ ተሰባስበው አንተን ለመጉዳት ቢሞክሩም በመጎዳትህ አላህ አስካልወሰነው ድረስ በፍፁም አይጎዱህም። ቀለሞች ደርቀዋል። መፅሀፉም ተጠቅልሏል።” (ሐሰን የሆነ ሐዲስ)

 4.ለመጨረሻ (ኻቲማ) ማማርና ጀነትን ለማግኘት ምክንያት ነው

አል-ሐፊዝ ኢብኑ ከሲር “ቸር ሰው በቸርነት ልምዱ ይቀላል። በአንድ ነገር ላይ ፀንቶ የኖረ ሰው በዚያው ይሞታል። በልምዱ የሞተ ሰው ደግሞ በዚያው ይቀሰቀሳል። አንዱ ሙዕሚን አጨራረሱ እስኪያምር ድረስ አላህ ከመገዛት አይቦዝንም።” ይላሉ:: አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ جَاهَدُوا فِينَا لَنَهْدِيَنَّهُمْ سُبُلَنَا ۚ وَإِنَّ اللَّهَ لَمَعَ الْمُحْسِنِينَ

“እነዚያም በእኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፡፡ አላህም በእርግጥ ከበጎ ሠሪዎች ጋር ነው፡፡”  (አል-አንከቡት፤ 69)።

يُثَبِّتُ اللَّهُ الَّذِينَ آمَنُوا بِالْقَوْلِ الثَّابِتِ فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَفِي الْآخِرَةِ ۖ وَيُضِلُّ اللَّهُ الظَّالِمِينَ ۚ وَيَفْعَلُ اللَّهُ مَا يَشَاءُ

“አላህ እነዚያን ያመኑትን በቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱም (በመቃብር) በተረጋገጠው ቃል ላይ ያረጋቸዋል፡፡ ከሓዲዎችንም አላህ ያሳስታቸዋል፡፡ አላህም የሚሻውን ይሠራል፡፡” (ኢብራሂም፤ 27)።

ከሀዲስ ደግሞ፤ አነስ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

أن النبي- صلى الله عليه وسلم- قال: “إذا أراد الله بعبد خيرًا استعمله”، قيل: وكيف يستعمله؟ قال: “يوفقه إلى عمل صالح ثم يقبضه عليه

أحمد والترمذي)

“አላህ አንድ ሰው ላይ በጎን ሲሻለት ያሰራዋል።” ሲሉ እንዴት ነው የሚያሰራው ተብለው ተጠየቁ ። እሳቸውም “መልካም ስራን እንዲሰራ ያደርገዋል በዚያው ሞት ይመጣበታል” አሏቸው። (አህመድና ቲርሚዚ የዘገቡት)

አላህ ለመልካም ስራ መትጋትንና ዘውታሪነት ከሰጠን እንዲሁም በዚያው ሞት ከመጣብን በአላህ ፍቃድ በመልክም ስራችን እንቀሰቀሳለን።

5.ሞት ሲመጣ የመላኢካን ብስራት ማገኘት

አላህ እንዲህ ይላል፡-

إِنَّ الَّذِينَ قَالُوا رَبُّنَا اللَّهُ ثُمَّ اسْتَقَامُوا تَتَنَزَّلُ عَلَيْهِمُ الْمَلَائِكَةُ أَلَّا تَخَافُوا وَلَا تَحْزَنُوا وَأَبْشِرُوا بِالْجَنَّةِ الَّتِي كُنتُمْ تُوعَدُونَ
نَحْنُ أَوْلِيَاؤُكُمْ فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَفِي الْآخِرَةِ ۖ وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَشْتَهِي أَنفُسُكُمْ وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَدَّعُونَ
نُزُلًا مِّنْ غَفُورٍ رَّحِيمٍ

እነዚያ ‘ጌታችን አላህ ነው’ ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ ‘አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ’ በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ፡፡(30) እኛ በቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱም ረዳቶቻችሁ ነን! ለእናንተም በእርሷ ውስጥ ነፍሶቻችሁ የሚሹት ሁሉ አልላችሁ፡፡ ለእናንተም በእርሷ ውስጥ የምትፈልጉት ሁሉ አልላችሁ፡፡ (31) መሓሪ አዛኝ ከኾነው አላህ መስተንግዶ ሲኾን (ይባላሉ)፡፡” (ፉሲለት፤ 30-32)።

ይህ አንቀፅ በመልካም ለሚያዙና ለአላህ ለተወዳጅ ሰዎች ብስራት ነው። እነዚህ ሰዎች “ጌታችን አላህ ነው።” ብለው በእምነትና በበጎ ሰራዎቻቸው በሱ ጎዳና ላይ ቀጥ ብለው የቆሙ ናቸው። ስለሆነም አላህ መላኢካን በማዘዝ ቀልባቸው ላይ የደህንነትንና የመረጋጋር መንፈስ እንዲያሳድሩባቸው ያደርጋል። በጀነትም ያበስራቸዋል። የዱንያንና የአኼራን ጉዳዩቻቸውንም አንደሚሰናዱላቸውም ቃል ያስግባል። “ጌታችን አላህ ነው” በሚለው ነገር ላይ ቀጥ ማለት ስንል ቃሉ የሚፈልገውን የቃሉን መልዕክት ተገንዝበን ቀጥ ማለት የሚጠይቅ ነው። ማለትም በውስጥ እሱን ማሰብ፤ በሕይወት ጎዳና እሱን መተግበር፤ ቃሉ የሚጠይቀውን ትልቅና መራራ ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ቁርጠኛ መሆን (መታገስ) ነው። ታዲያ በዚህ ምክንያት ነው አንድ ሰው የመላኢካን ጓደኝነትና የወዳጅነታቸውን ፀጋ ማግኘት የሚገባው።

ለመልካም ስራ አጋዥ ነገሮች

  1. በአላህ መታገዝ

አላህ ያገዘው ሰው ትክክለኛው እገዛ አገኘ። እሱ ያራቀው ደግሞ መድረሻ ቢስ ነው። ስለሆነም እሱ የሚወደው የሆነ በጎ ስራን ያመላክተንና ይገጥመን ዘንድ ከእሱ እገዛን መጠየቅ ይኖርብናል። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሙዓዝን (ረ.ዐ) እጁን ይዘው እንዲህ አሉት፡-

يا معاذ، إني والله لأٌحبك؛ فلا تدعن في دبر كل صلاة أن تقول: اللهم أعني على ذكرك وشكرك وحسن عبادتك

“ሙዓዝ ሆይ! እኔ በአላ ይሁንብኝ በትክክል እወድሀለሁ በሶላት የመጨረሻ ከፍለ ላይ ‘አላህ ሆይ አንተን በማስታወስና በማመስገን እንዲሁም በጥሩ ዒባዳህ ላይ እገዘኝ’ የሚለውን ዱዓ አትተው” (ሰሒህ ሀዲስ)።

ስለዚህ ከአላህ እገዛን መጠየቅ አለብን ይህን ካደረግን እሱ በመልካም ስራዎች ላይ ያግዘናል።

  1. ሚዛናዊ መሆን

በመልካም ስራዎች ላይ ለመዘውተር ሌላው አጋዥ ነገር፤ በዒባዳ ላይ ሚዛናዊ መሆን ነው። በዒባዳ ላይ ከሚገባው በታች መውረድም ሆነ ከሚፈለገው በላይ መውጣት አያስፈልግም። የነገሮች ሁሉ መልካሙ መካከለኛው ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጽንፈኛነትን አስጠንቅቀዋል። ምክንያቱም ይህ ባሕሪይ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) አቡሁረይራ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ

إن الدين يسر، ولن يشاد الدين أحد إلا غلبه، فسددوا وقاربوا وأبشروا، واستعينوا بالغدوة والروحة وشيء من الدلجة

“ይህ ዲን ገር ነው ዲኑን ከሚገባው በላይ ያጠባበቀው ሰው ዲኑ ያሸንፈዋል። ትክክለኛውን መንገድ ያዙ፣ ተቃረቡም አንዲሁም በበጎ ነገር ተበራቱ፤ በቀኑም በጧቱ፤ በረፋዱ እና በማለዳው ጊዜ በአላህ ታገዙ”። (ሶሂህ ሐዲስ)

በሌላ ሶሂህ በሆነ የሀዲስ ዘገባ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ)

وفي الصحيح أنه صلى الله عليه وسلم دخل المسجد مرةً فرأى حبلاً ممدودًا بين ساريتين، فقال : “ما هذا الحبل؟ قالوا: هذا حبل لزينب، فإذا فترت تعلَّقت به، فقال النبي- صلى الله عليه وسلم-: “لا.. حلُّوه، ليصل أحدكم نشاطه، فإذا فتر فليقعد”

“አንድ ጊዜ መስጅድ ሲገቡ ከሁለት ወጋግራ እንጨቶች ላይ የታሰረ ገመድ ተመልክተው ‘ምንድን ነው ይህ ገመድ’ ብለው ጠየቁ። ሰዎችም ይህ ገመድ የዘይነብ ነው፤ ከሰላት ስትደክም የምትይዘው ነው ብለው ነገሯቸው።፡ እሳቸውም ‘ይህ አይሆንም.ገመዱን ፍቱት አንደኛችሁ በተነቃቃበት ጊዜ ሶላት ይስገድ፤ ሲደክም (ሲታክት) ይቀመጥ (ይተኛ)’ አሉ።” (ሶሂህ ሐዲስ)

  1. መልካም ጓደኛ

መልካም ጓገኛ በመልካም ስራ ላይ ለመዘውተር ሌላው አጋዥ ሐይል ነው። ሰው ጓደኞቹ የሚሰሩት መልካም ስራ ሲመለከት እሱም ያን ስራ ለመስራት ይነሳሳል። እነሱ ለመልካም ስራ ሲተጉ እያየ እሱ አለመስራቱ የሀፍረት ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል። ስለሆነም ሲመለከቷቸው አላህን የሚያስታውሱ፤ ንፁህ፣ ደረጃቸው ከፍ ያለና መልካሞች ጋር ጓደኝነት መመስረት ያስፈልጋል። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት

إن من الناس مفاتيح للخير مغاليق للشر

“ከሰዎች መካከል የበጎ ነገር ቁልፍ በእጃቸው የተዳረገላቸውና የመጥፎ ነገር መዝጊያም በእጃቸው የተደረገላውቸው ሰዎቸ አሉ” (ሐሰን ሐዲስ)

ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ለበጎ ነገር ቁልፍ የሆኑ ሰዎችን መጎዳኘን ይገባናል። ቀልባችንን ለውዴታውና እሱን ለማስታውስ ይከፍትልን ዘንድ አላህን እንጠይቀዋለን።

ምርጥ ተምሳሌት፡-

ከዚህ በመቀጠል እስኪ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች መካከል በዱንያ ላይ በህይወት እያሉ የጀነት ሰዎች የተባሉትን እንተዋወቅ። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) አቡሁረይራ በዘገቡት ሐዲስ ስለ አቡበከር እንዲህ አሉ፤

أن النبي صلى الله عليه وسلم قال يومًا من أصبح منكم اليوم صائمًا؟ قال أبو بكر: أنا، قال: مَن اتبع منكم اليوم جنازة؟ قال: أبو بكر: أنا، فقال: من عاد منكم اليوم مريضًا؟ قال أبو بكر: أنا، قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: ما اجتمعن في رجل إلا ودخل الجنة

(صحيح)

“ከእናንተ መካከል ዛሬ ጾመኛ ማነው? አቡበከር እኔ አሉ። ዛሬ ከእናንተ መካከል ጀናዛ (ሬሳ) የሸኘ ማነው? አሉ አቡበከር እኔ አሉ። ከእናንተ መካከል ዛሬ በሽተኛን የጠየቀ ማነው? ሲሉ አቡበከር እኔ አሉ። ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) እነዚህ ነገሮችን በአንድ ላያ ያስገኘ ሰው ጀነት ገባ አሉ።” (ሶሂህ)

ቀጣዩ ደግሞ ቢላል ኢብኑ ረሃሕ ነው። የሐበሻ ባሪያ የነበረው ቢላል ኢስላም ደረጃውን ከፍ አደረገው። በአንድ ወቅት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ)

يا بلال، حدثني بأرجى عمل عملته في الإسلام؛ فإني سمعت دُفَّ نعليك بين يديَّ في الجنة، فقال ما عملت عملاً أرجى عندي من أني لم أتطهَّر طهورًا في ساعة بالليل أو النهار إلا صليتُ بذلك الطهور، ما كُتِبَ لي أن أصل

“ጀነት ውስጥ የጫማህን ኮቴ ሰምቻለሁ። ቢላል ሆይ! ኢስላም ውስጥ ሆነህ በጣም ጥሩ የሆነ የሰራኸውን ስራ አስኪ ንገረኝ አሉት። ቢላልም ውዱእ ካደረኩ በኋላ በቀንም ይሁን በማታ አላህ የፃፈልኝን ያህል ሰላት እሰግዳለሁ። ከዚያ ውጪ ሰራሁት የምለው ስራ የለኝም አላቸው።”

ስለሆነም አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም ወደ አላህ ዒባዳ በመስራት መቃረብን ልናበዛ፤ ይህንንም የመጀመሪያም የመጨረሻም ልናደርገው ይገባል። በሱም በመታገዝ መፈክራችንን

وَعَجِلْتُ إِلَيْكَ رَبِّ لِتَرْضَىٰ

 “አንተ ትወደኝ ዘንድ ወደ አንተ ተቻኮልኩ” የሚለው ቁርአን አንቀፅ ይሁን።

ይህ ነው አላህ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ዘውታሪ መልካም ስራ። አላህ ሁላችንንም መልካሞችና በበጎ ስራ ቀጥ ብለው ከሚቆሙት ያድርግን። ሞት ሲመጣባቸውም በጀነት ከተበሰሩትና እሱ ካልተቆጣቸው አላህ ያድርገን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here