መልካም ስነ-ምግባር

0
12836

ስነ-ምግባር ከነፍሳችን ጋር ጥልቅ ቁርኝትና የፀና መሰረት ያለው ሲሆን ፍላጎታችንና ምርጫችን፤ በጎና መጥፎ እንዲሁም ፀያፍም ሆነ ውብ ስራዎቻችን የሚመነጩበት የህይወታችን ክፍል ነው። ነፍሳችን በባህሪዋ ስለሁሉም ነገረ ምቹ ናት። ይህም ማለት የመጥፎ ወይም የጥሩ ተፅዕኖ ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ ነች። ነፍሳችንን ጥቂት ስልጠና ብንሰጣት ሐቅንና መልካምን የመውደድ፤በጥሩ ነገር መነሳሳት፤ ቆንጆን ነገር ማፍቀር፤ መጥፎን የመጥላት ባህሪን እንድትላበስ ማድረግ ይቻላል። ይህ ባህሪዋ መልካምና ተወዳጅ ተግባራትን ያለ ማንም አስገዳጅነት ወደመተገበር የሸጋግራታል። ይሄኔ ነፍሳችን “የመልካም ስነምግባር” ባለቤት ትሆናለች። ስነ-ምገባር ከሰው የሚመነጭና ካለማንም አስገዳጅነት የሚፈፅመው ተግባሩ መገለጫ ነውም ተብሏል። ለምሳሌ፡- ሆደ ሰፊነትና እርጋታ፤ ታጋሽነትና ቻይነት፤ ቸርነትና ጀግንነት፤ ፍትሀዊነትና በጎነት ወዘተ የመልካም ስነ-ምግባር መገለጫዎች ናቸው።

በተቃራኒው ነፍስ ሊደረግላት የሚገባውን ማስተካከያ አልያም እንክብካቤ ካልተደረገላት ወይም በመጥፎ አስተዳደር ካደገች መጥፎውን ጥሩ፤ ቆንጆውን ደግሞ የሚያስጠላ አድረጋ መመልከት ባህሪዋ ይሆናል። ከዚያም ቆሻሻና ርካሽ ተግባራትንና ንግግሮችን ያለምንም አስገዳጅነት ትተገብራለች፤ ትናገራለች። እንድን መጥፎ ስራ በንግግርም ሆነ በተግባር የምንሰራውና ያለማንም አስገዳጅነት የምንፈፅመው ከሆነ መጥፎ ስነ-ምግባር የሚል ስም እንሰጠዋለን። ከነዚህ ስራዎች መካከል እንደ ሸፈጥ፣ ሐሰትን መናገር፣ ትዕግስት ማጣት፣ ስግብግብነት፤ ድርቅና፤ ፈላጭ ቆራጭ መሆን፤ መጥፎ መናገር፤ ብልግና ወዘተ የመጥፎ ስነ-ምግባር ምሳሌዎች ናቸወ።

ኢስላም ሰዎችን ወደ ጥሩ ስነ-ምግባር ጥሪ ሲያደርግ፤ ሙስሊሞችንም በዚሁ ምግባር እንዲሰለጥኑም ሲያዝ፤ ውስጣቸውም እንዲሰርፅና የማንነታቸው አካል እንዲሆን ሲጠይቅ ይታያል። መልካም ስነ-ምግባርን የኢማን መገለጫና የእስልምና ጤናማነት መለኪያ አድርጎታል። ስለሆነም አላህ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) በጥሩ ስነ-ምግባራቸው እንዲህ ሲል አመስግኗቸዋል።

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

“አንተም በታላቅ ስነምግባር ላይ ነህ::” (አል-ቀለም68፤4)

በጥሩ ስነ-ምግባር እንዲዋቡም

وَلَا تَسْتَوِي الْحَسَنَةُ وَلَا السَّيِّئَةُ ۚ ادْفَعْ بِالَّتِي هِيَ أَحْسَنُ فَإِذَا الَّذِي بَيْنَكَ وَبَيْنَهُ عَدَاوَةٌ كَأَنَّهُ وَلِيٌّ حَمِيمٌ

“መልካሚቱና ክፉይቱም (ጸባይ) አይተካከሉም። በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጸባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር። ያን ጊዜ ያ ባንተና በእርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል።” (ፋሲለት 41፤34) ብሎ አዟቸዋል።

ይህ መልካም ስነ-ምግባር ሁሉም የሚናፍቃት የላቀችዋ የጀነት መግቢያ ምክንያትም መሆኑ እንዲህ ተገልጿል።

وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ

“ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ።”        (አል-ዒምራን 2፤133)

የአላህም መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩበትን ዓላማ ሲናገሩ “እኔ የተላኩት መልካም ስነ-ምግባርን ለሟላ ነው” በማለት ተናግረዋል። (በይሃቂይ)

በሌላ ሀዲሳቸውም የመልካም ስነ-ምግባር ደረጃ እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል “እንደ መልካም ስነምግባር ሚዛን የሚደፋ ነገር የለም” (ቲርሚዚ)::  በተጨማሪ

“መልካም ስራ ማለት ጥሩ ስነምግባር ነው።” (ሙስሊም)

“ኢማናቸው ምሉዕ የሆኑ ሰዎች በስነ ምግባራቸውም በጣም ምርጦች ናቸው።” (አቡዳውድ)

“እኔ ዘንድ  እጅግ በጣም ተወዳጁና በዕለተ-ቂያማ ቅርብ የሚሆነው በጣም ያማረ ስነምግባር ያለው ሰው ነው።” (ቲርሚዚ)

“ከስራዎች ሁሉ በላጩ ምንድን ነው? ተብለው ሲጠየቁ ‘መልካም ስነምግባር ነው።’ ብለው መልሰዋል።”

በተመሳሳይ “አብዛኛው ሰው ጀነት የሚገባው በምንድነው? ተብለው ሲጠየቁ መልካም ስነምግባር ነው።” (ሀይሰሚ)

በሌላም ሐዲስ “አንድ ስው በዒባዳው ደካማ ሆኖ፤ በስነምግባሩ መልካምነት የተነሳ የአኼራን ትልቁን ደረጃ የተከበረ ቦታ ይቸረዋል።” (ጦበራኒ)

በመልካም ስነምግባር ላይ የሰለፎች አስተያየት

ሐሰን አል-በሰሪ እንዲህ ይላሉ፡- “መልካም ሰነ ምግባር መገለጫ የፊትን ገፅታን ፈታ ማድረግ፤ አለመተናኮል ነው።” ዐብደሏህ ኢቡኑ መባረክ ደግሞ፡- “መልካም ስነ ምግባር በሶስት ነገር ይገለፃል ከሐራም ነገር በመራቅ፤ ሀላል ነገር በመፈለግና ቤተሰብን በተገቢው መንገድ መምራት ነው።” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “መልካም ስነምግባር እጅን ከመጥፎ መሰብሰብና የሙዕሚንን ምክንያት መቀበል (ሙዕሚንን ከነችግሩ መቻል ነው።)” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ “መልካም ስነምግባር ከአላህ ውጪ ሌላ ሀሳብ ላይኖርህ ነው።” እነዚህ ገለፃዎች የርዕሱን ከፊል ገፅታ የሚመለክቱ ሲሆኑ ምንነቱን በሚመለከት ግን ያሳለፍነውን ገለፃዎች ማየት በቂ ነው።

የስነምግባር መገለጫዎች ደግሞ ምን እነደሚመስሉ ስንመለከት እንዲህ ተብሏል። መገለጫዎቹ “ብዙ ይሉኝታና ሀፍረት ያለው፣ ሰዎችን ከመተናኮል የራቀ፣ መልካም ጎኑ ዘወትር የሚነሳለት፣ ምላሱ ለእውነት የተገራ፣ ንግግሩ ጥቂትና ስራው ብዙ፣ የምላስ ወለምታ (ስህተቱ) ያነሰ፣ የማያስፈልግ ነገር የማያበዛ (በንግግርም በምግብም ወዘተ)፣ ለበጎ ነገር የቀረበ፣ ክብሩን የሚጠብቅ፣ታጋሽና አመስጋኝ፣ የአላህን ውሳኔ ወዳጅና ሆደ ሰፊ፣ ቃልኪዳኑን ፈፃሚና ጥብቅ የሆነ፣ ተራጋሚና ተሳዳቢ ያልሆነ፣ ነገር አዋሳጅና ሀሜተኛ ያለሆነ፣ ከምቀኝነት ከችኩልነትና ከስስታምነት የፀዳ፣ ፈገግተኛና ዝምተኛ፣ ለአላህ ብሎ የሚወድና የሚቆጣ … ነው።”

ይህ እንግዲህ ከመልካም ስነምግባር ከፊል ገፅታዎች ናቸው።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here