ኢስላማዊ ሥነ-ምግባር (ክፍል 2)

0
5514

የነብዩ ሱና የስነ-ምግባር እይታ፡-

ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ የሚያስመሠግን ስነ-ምግባርን አበረታተውታል። አነስ አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና በዘገቡት ሀዲስ፡-

كان النبي صلى الله عليه وسلم أحسن الناس خُلُقاً

(متفق عليه)

“ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ከሁሉም የላቀ ስነ-ምግባር የነበራቸው ነበሩ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሃያልና አሸናፊው አላህ ነብዩን /ሶ.ዐ.ወ/ ሲያሞካሻቸው፡-

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

“አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ” (አል-ቀለም 68፤4) ይላቸዋል።

አዒሻም አላህ ሥራዋን ይውደድላትና ስለ ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ሥነ-ምግባር ስትነግረን፡-

كان خلقه القرآن

(رواه مسلم)

“የነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ስነ-ምግባራቸው ቁርኣን ነበር” (ሙስሊም) ትለናለች።

ኢማሙ ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ደግሞ ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ባልደረቦቻቸውን በመልካም ስነ-ምግባር እንዲታነፁ ጥሪ ሲያቀርቡላቸው ከመጥፎ ሥነ-ምግባር ደግሞ እንዲርቁም አስጠንቅዋቸዋል። የላቀ ሥነ-ምግባርን የተላበሡ ለሆኑት የላቀ ምንዳና በርካታ ትሩፋት እንደሚያገኙም ቃል ገብተውላቸዋል።

ቲርሚዚ ሀሠኑን ሠሂህ በሆነ ሀዲስ እንደዘገቡት ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ፡-

ما من شيء أثقل في ميزان المؤمن يوم القيامة من حسن الخلق، وإن الله يبغض الفاحش البذيَّ

(رواه الترمذي)

“የቂያማ ቀን ምንም ነገር ሚዛን ላይ ከሥነ-ምግባር የበለጠ የሚከብድ የለም፣ አላህ አፀያፊንና ብልግናን ይጠላል” ይሉናል። (ቲርሚዚይ)::

ረሡል በአብዛኛው ሠዎችን ጀነት የሚያስገባ ተግባር ምን መሆኑን ተጠይቀው ሲመልሱ፡-

تقوى الله وحسن الخلق

(رواه الترمذي)

“የአላህ ፍራቻና መልካም ስነ-ምግባር ነው” ብለዋል። (ቲርሚዚይ)።

ከመልካም ሥነ-ምግባሮች፡-

  1. ሃያእ (ይሉኝታ)

ሃያእ (ይሉኝታ) አስቀያሚ ነገሮችን እንድንተው የሚገፋፉና የባለመብቶችን መብት እንዳናጓድል የሚከለክል ሥነ-ምግባር ነው። ይሉኝታ መልካም በሆነ ነገር ባህሪያችንን እንድናንፅ ከሚያደርጉ ጠንካራ መልካም ሥነ-ምግባሮች መካከል አንዱ ሲሆን አስቀያሚ የሆኑ ነገሮችን እንድንርቅ የሚገፋፉም ነው። አንድ ሰው በዚህ ባህሪይ የታነጸ ከሆነ ሌሎቹ መልካም ሥነ-ምግባሮች ገር ይሆኑለታል። ከወራዳ ባህሪያት የራቀ፤ አካሄዱ የፀዳና የጠራ ይሆናል። ትርፍ ንግግር አይናገርም፤ ነፍሡም ወንጀልን ለመዳፈር አትታዘዘውም። ይሉኝታ ከዚህ ትርጓሜውና እይታው አንጻር ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ በሀዲሳቸው ያስገነዘቡትና የተከበሩ ባልደረቦቻቸውን ያበረታቱበትም ነው። ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ /ሶ.ዐ.ወ/፡-

الحياء لا يأتي إلا بخير 

(رواه البخاري ومسلم)

“ይሉኝታ ከመልካም አንጻር ካልሆነ በስተቀር አይከሰትም” ብለዋል። (ቡኻሪና ሙስሊም)

 መልእክተኛው /ሶ.ዐ.ወ/ አንድ የመዲና ሱው ወንድሙን “ይሉኝታ ጎድቶሃል” በሚል አይነት ስሜት ሲገስፀው ረሡል በአጠገባቸው ያልፉ ነበርና ሠሙት። እሳቸውም “ተወው ይሉኝታ የኢማን አንድ ክፍል ነው” ብለውታል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

  1. ቁጥብነት (ዒፋ)

ቁጥብነት እርም ከተደረጉ ነገሮች እራስን መግታትና ሠዎችን ከመጠየቅ መቆጠብ ነው። እውነተኛ ሙስሊም ቁጥብ፤ በራሡ የተብቃቃ፤ አይኑን ወደ ሠው የማያንጋጥጥ፤ ክብሩን የሚጠብቅ ነው።ምንም እንኳን አንዳንድ ሁኔታ ቢያስገድደው፣ እጁን ወደ ሰው ለመዘርጋት አይዳዳውም። የገጠመውን የኑሮ ውጣ ውረድ ወይም የኑሮ መጣበብ በትዕግስት የሚጋፈጥ ነው። ቁርኣን እንደሚያስተምረው መመኪያውን በአላህ ላይ ያደረገ ሰው አላህ መውጫ ቀዳዳ ያደርግለታል። ባልጠበቀውም አቅጣጫ ሲሳዩን ይሠጠዋል።

ነብዩ /ሶ.ዐ.ወ/ ከችግሩ ጋር ቁጥብ ለሆነ ሰው አላህ እንደሚያከብረውና እንደሚያብቃቃው ቃልኪዳን ገብተውለታል። ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ /ሶ.ዐ.ወ/፡-

من يستعف يعفّه الله، ومن يستغن يغنه الله

رواه البخاري ومسلم)‏)

“እራሡን የቆጠበ አላህ ቁጥብ ያደርገዋል። የተብቃቃን አላህ ያብቃቃዋል (ያከብረዋል)” ብለዋል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

  1. ቸርነት (ከረም)

ቸርነት፡- ለጋስነት፣ በእጅ ያለን ነገር ለሌላ ማካፈል ሲሆን ኢስላም በእጅ ያለን ነገር ለሌላ በማካፈል ወይም በመስጠት ላይ የቆመ ሃይማኖት ነው። ስለሆነም ሙስሊሞች ቅን እጆቻቸው ለጋሽ በመሆኑ ተወዳጅ አድርጓቸዋል።

ሃያልና አሸናፊው አላህ፡-

وَمَا تُنفِقُوا مِنْ خَيْرٍ يُوَفَّ إِلَيْكُمْ وَأَنتُمْ لَا تُظْلَمُو

“ከገንዘብም የምትለግሡት ሁሉ (ምንዳው) ወደናንተ ይሞላል። እናንተም አትበደሉም” (አል-በቀራህ1፤272) ይላል።

ቡኻሪና ሙስሊም ከዐብደላህ ኢብን ዐምር እንደዘገቡት አንድ ሰው ረሱልን /ሶ.ዐ.ወ/ በኢስላም ውስጥ በላጩ የቱ ነው? ብሎ ይጠይቃቸዋል። ረሱልም

تطعم الطعام، وتقرأ السلام على من عرفت ومن لم تعرف

(متفق عليه)

“ምግብን ማብላት፤ ለምታውቀውም ሆነ ለማታውቀው ሠላምታን ማቅረብ ነው” ብለው መልሰውለታል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

ቸርነት የቸርን ሰው ሀብት አይቀንስበትም ወደድህነትም አያቀርበውም። ይልቁንም የሃብት መስፊያ መጨመሪያ የመደለቢያም ሠበብ ነው የሚሆነው:: ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሡል /ሰ.ዐ.ወ/

ما من يوم يصبح العباد فيه إلا ملكان ينزلان، فيقول أحدهما: اللهم أعط منفقاً خلفاً، ويقول الآخر: اللهم أعط ممسكاً تلفا 

(رواه مسلم)

“ማንኛውም ባርያው የሚያነጋበት ቀን የለም ሁለት መላኢካዎች የሚወርዱበትና አንደኛው አንተ አላህ ሆይ! ለሠው ለለጋስ ምትክ የሚሆንለትን ሥጠው ሲል ሌላኛው ደግሞ አንተ አላህ ሁይ! ለሚይዝ (ለማይለግስ) ንብረቱን የሚያጠፋበትን ነገር ስጠው እያሉ አላህን የሚጠይቁ ቢሆን እንጂ” ይሉናል (ሙስሊም)።

ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ከነሱ ያስጠነቀቁን ከሆኑት የተጠሉ ባህሪት መካከል፡-

  1. ኩራት (ኪብር )

ኩራት፡- የሃቅ ንግግርን ከመቀበል እራስን ከፍ ማድረግ፣ በፍጡራን ላይ እራስን መስቀል ነው። ኩራት ከላቀ ስነ-ምግባርጋ ይቃረናል፣ በሰዎች መሀል መለያየትንና ጥላቻን ይተክላል፣ አላህ እንዲቀጥል ያዘዘውን ዝምድናን ይቆርጣል። በዚያም ምክንያት እስልምና መንፈስና ልቦና ከዚያ እስኪፀዱ ድረስ ኩራት እንዲጠፋ ጦርነት አውጆበታል። ነብዩም /ሰ.ዐ.ወ/ ይህ አጥፊ በሽታን አስጠንቅቀውናል። የኩራት ባለቤትን ቅጣትና ውርደት የሚጠብቀው መሆኑን ዝተውበታል ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/

لا يدخل الجنة من كان في قلبه مثقال ذرة من كبر، فقال رجل: إن الرجل يحب أن يكون ثوبه حسناً ونعله حسنة. قال: إن الله جميل يحب الجمال، الكبر بطر الحق، وغمط الناس

(رواه مسلم)

“በልቦናው ውስጥ ቅንጣት ታህል ኩራት ያለበት ሰው ጀነት አይገባም ሲሉ አንዱ ሰሃባ ‘አንድ ሰው ልብሱ ጥሩ ጫማው ጥሩ እንዲሆንለት ይወዳል’ ሲላቸው ረሱል /ሰ.ዐ.ወ/ አላህ ቆንጆ ነው ቁንጅና ይወዳል ኩራት ከሃቅ በላይ ሆነ በሃቅ ላይ መንጠባረርና ሰውን ንቆ በትንሽ አይን ማየት ነው” ብለው ተናግረዋል (ሙስሊም)። በሌላም ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሱል/ሰ.ዐ.ወ/

ألا أخبركم بأهل النار: كل عُتُلّ جواظ مستكبر

(رواه البخاري ومسلم)

“የእሳት ሰውን ልንገራችሁ ብለው ሁሉም ጨካኝ ስግብግብና እሚኮራ ሰው ነው” ብለው ተናግረዋል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

ጨካኝ ደረቅና ጭካኔ ያለበት ሲሆን ስግብግብ ደግሞ የሚያግበሠብስና ከመስጠት ንፉግ የሆነ ወይንም ግዙፍ የሖነና በአካሄዱ የሚንጎማለል ሰውም ነው ተብለዋል። ኩራተኞች በመጨረሻው አገር ውርደትና ቅሌት የሚጠብቃቸው ለመሆኑ አላህ ወደነሱ የእዝነትና ርህራሄ እይታን አለማድረጉ ብቻ ይበቃዋል።

ረሱል /ሰ.ዐ.ወ/ ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ፡-

لا ينظر الله يوم القيامة إلى من جرّ ثوبه خيلاء

(رواه البخاري ومسلم)

“አላህ የቂያማ ቀን ለኩራት (ለመንጎማለል ሲል) ልብሱን ወደ ጎታታ ሰው በእዝነትና ርህራሄ አይን አይመለከትም” ይሉናል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

  1. ምቀኝነት (ሀሰድ)

ምቀኝነት፡- አላህ ፀጋን ከዋለለት ሰው ፀጋው የዲን ፀጋም ሆነ አለማዊ ፀጋ እንዲፈለበምበት (ከባለፀጋው ፀጋው እንዲወገድ) መመኘት ነው።

እስልምና ምቀኝነት እርም አድርጎዋል። አላህ ረሱልን /ሰ.ዐ.ወ/ ከምቀኝነት ተንኮልና ክፋት እንዲጠበቁ አዞአቸዋል። ምክንያቱም ምቀኝነት ልብ ውስጥ የሚነድ እሳት ነውና ሰውየውንም ሌሎች ሰዎችንም ያውካል።

ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ከምቀኝነት ጠንከር አድርገው ነው ያስጠነቀቁት። አቡዳውድ በዘገቡት ሱጡጢይና አልባኒይ ሀዲሱን ደካማ ነው ባሉትና የባግዳድ ታሪክ በሚለው ኪታባቸው ውስጥ በሌላ የሀዲስ መንገድ ሃፊዝ ዒራቂይ ሀዲሱን ሃሰን ባደረጉት ሀዲስ ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/

إياكم والحسد، فإن الحسد يأكل الحسنات كما تأكل النار الحطب

(رواه أبو داود)

“ከምቀኝነት አደራችሁን ተጠንቀቁ ምክንያቱም ምቀኝነት እሳት እንጨትን እንደሚበላው መልካም ተግባርን ደግሞ ምቀኝነት ይበላዋል” ብለዋል (አቡዳውድ)።

ከዚያም ባሻገር ምቀኛ በአቋሙ ላይ ደካማ ቁርጠኝነት ያለበት፣ በጌታው ላይ መሃይም የሆነ፣ በፈጣሪው በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች አላዋቂ የሆነ፣ ወደ የፀጋ ፊቱን መልሶ ከችሮታው ሊጠይቀው የሚገባውና የጠራው የሆነው የአላህ የፀጋ ካዝና እራሱ በራስ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ አለመሆኑን ሊያውቅ የሚገባው ሰው ነው።

  1. ሐሜት

ሐሜት፡- ጓደኛህ ያለበት ሆኖ ሳለ አንተ ስለጉዳይ ማውራትህን የሚጠላው ነገር ነው። እስልምና እርም ያደረገውን የሃሜት አይነት በሃይል መራቅን እንድንርቀው ምንነቱን ሲያሳውቀን፣ ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሱል /ሰ.ዐ.ወ/

أتدرون ما الغيبة ؟ قالوا: الله ورسوله أعلم . قال: ذكرك أخاك بما يكره . قال رجل: أرأيت إن كان في أخي ما أقول ؟ قال: إن كان فيه ما تقول فقد اغتبته، وإن لم يكن فيه ما تقول فقد بهته

(رواه مسلم)

 “ሃሜት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ብለው ሰሃቦቻቸውን ሲጠይቁ ሰሃባዎችም አላህና መልዕክተኛው የበለጠ ያውቃሉ ሲሏቸው ረሱልም     /ሰ.ዐ.ወ/ ወንድምህን በሚጠላው ነገር ማውሳትህ ነው ሲሉ ከሰሃባዎች አንዱ በወንድሜ ላይ የማወሳው ነገር ቢኖርበትስ ብለው ሲጠይቅ  ረሱልም /ሰ.ዐ.ወ/ በወንድም ላይ የምትለው ነገር ያለበት ከሆነ በእርግጥም አማህው የምትለው ነገር የሌለበት ከሆነ ደግሞ በሱ ላይ  ቀጠፍክበት” ብለዋል (ሙስሊም)፤ ቅጥፊቱ በሱ ላይ የሌለበትን መዋሸትና በሱ ላይ ቅጥፊት ማድረግ ነው።

በዚያ መሠረት ሌላን ሰው በሚጠላው ጉድለትና ነውር (ጉድለትና ነውሩ ከአካሉ ጋር በተያያዘ መልክም ይሁን ከስነ-ምግባር ጋር የተያያዘም ይሁን ወይንም ከዘሩና ከጎሳው ጋር የተያያዘ ይሁን ልዩነት ሳያደርግበት) ማውሳት የተከለከለ ሲሆን ያ ደግሞ ፈተናን የሚቀሰቅስ፣ ትስስርን የሚቆርጥ፣ ግንኙነቶችን የሚበጣጥስ ሲሆን ሃሜት በአንደበት የሌላን ሰው ጉድለትና ነውርን በማውሳት ላይ ብቻ የተገታ ሳይሆን ሁሉንም ማሳነስ መናቅን ሊገልፁ የሚችሉ ነገራትን በምልክት ወይንም በጥቅሻ ወይንም በማንኛውም መልኩ ቢሆን ያንን ሊያስዝ የሚችልን ነገር በጥቅሉ ሲመለከት ሃያልና አሸናፊው አላህ በሡረቱ አል-ሁመዛህ ቁ.1 ላይ

وَيْلٌ لِّكُلِّ هُمَزَةٍ لُّمَزَةٍ
“ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት” (አል-ሁመዛህ104፤1) ይላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here