የኒያ /ውስጣዊ ውሳኔ/ ስርዓት

0
8402

ኒያ በሙስሊም ህይወት ውስጥ ያለውን ታላቅ ስፍራ፣ በአጠቃላይ ለዱንያም ሆነ ለዲን ስራዎች ያለውን አስፈላጊነት እያንዳንዱ ሙስሊም የሚያምንበት ጉዳይ ነው። ምክኒያቱም ሁሉም ተግባር ይህንኑ መሰረት አድርጎ ነው የሚሰራው፤ የሚጠነክረውና የሚደክመው፤ የሚስተካከለውና የሚበላሸው። የትኛውንም ስራ ስንሰራ ለማንና ለምን እንደምንሰራ መለየት ተገቢ ነው። ለዚህም ኒያችንን ማስተካከል እንዳለብን በዋነኝነት የሚያሳስበን የተከበረው ቁርአን ነው፡-

وَمَا أُمِرُوا إِلَّا لِيَعْبُدُوا اللَّهَ مُخْلِصِينَ لَهُ الدِّينَ حُنَفَاءَ وَيُقِيمُوا الصَّلَاةَ وَيُؤْتُوا الزَّكَاةَ ۚ وَذَٰلِكَ دِينُ الْقَيِّمَةِ

“አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣ ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)። ይህም የቀጥተኛይቱ (ሃይማኖት) ድንጋጌ ነው።” (አል-በይና፤ 5) በሌላ አንቀፅም

قُلْ إِنِّي أُمِرْتُ أَنْ أَعْبُدَ اللَّهَ مُخْلِصًا لَهُ الدِّينَ

“በል “እኔ አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ያጠራሁ ኾኜ እንድግገዛው ታዘዝኩ።” (አል- ዙመር፤ 11 )

ሁለተኛው የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቃል ነው። ለምሳሌ

“ስራ ሲባል የሚለካው በኒያው ነው። ሁሉም ሰው የኒያውን ያገኛል” ብለዋል(ብኻሪ)

በሌላ የሐዲስ ዘገባም መልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

“አላህ ወደ መልካችሁና ወደ ገንዘባችሁ አይመለከትም። የሚመለከተው ወደ ቀልባችሁና ወደ ስራችሁ ነው(ሙስሊም ፤አህመድ የዘገቡት)።

ወደ ቀልባችሁ ይመለከታል ማለት ኒያችሁን ያያል ማለት ነው። በዚህም ኒያ ለማንኛውም ስራ መነሻና መቀስቀሻ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በሌላ ሐዲስ “አንድ ሰው በጎ ነገር ለመስራት አስቦ ባይሰራው እንኳ (የበጎ ስራ) ምንዳ ይፃፍለታል (አህመድ)

በጥሩ ኒያ ምክንያት አንድ ሰው በጎ ነገረ በማሰቡ ብቻ ምንዳ ያገኛል፤ ይህ የኒያን ታላቅ ደረጃን ያሳየናል። በሌላ ሐዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

“ሰዎች አራት አይነት ናቸው። አንዱ አላህ ዕውቀትና ገንዘብ ሰጥቶት በዕውቀቱና በገንዘቡ ይሰራበታል (ይህን ያየ ሌላ ሰው) አላህ ለዚህ ሰው እንደሰጠው ለእኔም ቢሰጠኝ ኖሮ አንደሱ መልካም ነገር እስራበት ነበር ይላል፤ ሁለቱም ሰዎች በምንዳ  እኩል ናቸው። ሌላው ሰው ደግሞ አላህ ገንዘብ ሰጥቶት፤ ዕውቀት ነስቶታል፤ በመሆኑም ገንዘቡን ያለአግባብ ያውላል ታዲያ የዚህን ሰው ተግባር ያየ ሰው ምናል አላህ እንዲህ ሰው ሰጥቶኝ በነበረ እንደሱ አደርግ ነበር ይላል፤ ሁለቱም በመጥፎ ምንዳ እኩል ናቸው ብለዋል። (ቲርሚዚ)

ጥሩ ኒያ ያለው ሰው በጎ ስራ ተሰርቶ የሚገኘውን ምንዳ በኒያው ብቻ አገኘ፤ መጥፎ ኒያ የነበረውም መጥፎ ስራ ሰርቶ የሚገኘውን ዋጋ አገኘ። በሁለቱም ሁኔታ ኒያ ትልቁ ሚና ይጫወታል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተቡክ ዘመቻ ላይ ሆነው እንዲህ አሉ፡-

“መዲና ውስጥ ሰዎች አሉ ሸለቆ ስናቋርጥ፤ ከሀዲያንንም የሚያስቆጭ ቦታንም ስንረግጥ፤ ተራራ ስንወጣ፤ ለዘመቻም ገንዘብ ስናወጣ፤ መከራ ሲደርስብንም እነሱ መዲና ላይ ሆነው ከእኛ ጋር በምንዳ ይጋራሉ” ሰሀቦችም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንቱ የአላህ መልዕክተኛ አሏቸው፤ እሳቸውም “ችግር ከእኛ ጋር እንዳይሳተፉ ከለከላቸው ነገር ግን በሀሳባቸው (ኒያቸው) ተሳትፈዋል” አሏቸው። (ቡኻሪ፣ አቡ ዳውድ)። እንግዲህ ጥሩ ኒያ ዘመቻ ያልወጣውን ሰው ሳይቀር ከወጣው ሰው ጋር በምንዳ እኩል ያደርጋል። በሌላም ሐዲስ የአላህ ነብይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

“ሁለት ሙስሊሞች በሰይፋቸው ለመገዳደል ቢገናኛኙ ገዳዩም ተገዳዩም የእሳት ናቸ” አሉ። ሰሀቦችም አንቱ የአላህ መልዕክተኛ  ገዳዩስ እሺ በመግደሉ ይቀጣ ተገዳዩ እንዴት እሳት ሊያገኘው ይችላል? ብለው ጠየቁ። እሳቸውም “ጓደኛውን ለመግደል ስላሰበ ነው” አሉ (ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ ነሳኢ) እዚህም ጋር መጥፎ ኒያ ገዳዩንም ተገዳይንም እኩል ተቀጪ ሲያደርግ እንመለከታን፤ ተገዳይ መጥፎ ኒያ ባይኖረው ኖሮ ጀነት ይገባ ነበር። በሌላ ንግግራቸው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም 

“አንድ ሰው ሚስት ለማግባት ፈልጎ መኅሯን እንደማይሰጣት አላህ የሚያውቅበት ሆኖ እያለ አታሎ ያገባት እንዲሁም የተገናኛት ሰው በዕለተ-ቂያማ ከአላህ ዘንድ ዝሙተኛ ሆኖ ይቀርባል። ማንም ሰውም ብሩን እንደማይመልስ አላህ የሚያውቅበት ሆኖ እያለ ከሰው ብድር የወሰደ በእለተ-በቂያማ ከአላህ ፊት ሌባ ሆኖ ይቀርባል።” (አህመድ፣ ኢብኑ ማጀህ)

በመጥፎ ኒያ ምክንያት ተፈቅዶ የነበረው ነገር ወደ ክልክልነት፤ ሐላል የነበረው ወደ ሐራምነት ተለወጠ። ይህ የሚያሳየው ኒያ በጣም አስፈላጊና ደረጃውም በጣም ከፍ ያለ ጉዳይ መሆኑ ነው። ስለሆነም ሁሉም ሰራ የሚመሰረተውም ሆነ የስራ ትክክለኝነቱና ተቀባይነቱ የሚረጋገጠው በኒያ ስለሆነ ያለኒያ ወይም በተበላሸ ኒያ ስራዎችን እንዳይሰራ መጠንቀቅ አለበት። ኒያ የስራ ሩህ(ነፍስ) ነው። እሱ ሲስተካከል ስራ ይስተካከላል፤ ሲበላሽ ስራም ይበላሻል።

አንድ ሙስሊም ኒያ የስራዎች ሁሉ ሩክን (ማእዘን) እንደሆነና ለተቀባይነቱ ቅድመ መስፈርት (ሸርጥ) እንደሆነ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሁሉ ኒያ የሚባለው ነገር እንዲሁ በምላስ ብቻ (ጌታዬ ይህን አስቤአለሁ…) በማለት የሚነገር እንዳልሆነም ይገነዘባል። ይልቁንም ኒያ በመልካም አላማ በመነሳሳት ጥቅምን ለማግኘት ወይም ከጉዳት ለመጠበቅ በጎ ነገር ለመስራት ከቀልብ የሚነሳ ግፊት ነው። በዚህም ተግባር አንድ ሰው በስተመጨረሻ ማግኘት የሚመኘው የታላቁ ጌታችንን የአላህን ውዴታ ነው

አንድ ሙእሚን በተለምዶ የሚሰራን የተፈቀደን (ሙባህ) ስራ ሲሰራ ኒያውን በማስተካከል ብቻ ምንዳ ወደሚያስገኝ ስራ (ጧአ)  ሊለወጥ ይችላል። በተቃራኒውም ምንዳ የሚያስገኝ ስራ በኒያ በልሹነት ምክንያት ወደ መጥፎነት የሚቀየርበት ሁኔታ አለ። እዚህ ጋር ሊተኮርበት የሚገባው ነገር አንድ ሰው መጥፎ ነገር ለመስራት ጥሩ ኒያ ቢያሳድር ተግባሩ ወደ መልካም ምንዳ አይቀየርም። ለምሳሌ፡- ሰውን ለማስደሰት ብሎ ሀሜት ውስጥ የሚገባ መልካም ኒያ መኖሩ ብቻ የሚጠቅመው አይሆንም። እንዲሁም በሐራም ገንዘብ መስጂድ ቢሰራ፤ ለመልካም ነገር የገቢ ምንጭ ለማስገኘት ብሎ የዳንስ ምሽቶች ቢያዘጋጅ ወይም ሎተሪ ቢያዘጋጅ፣ ከመልካም ሰዎች ቀብር ላይ እነሱን ወደድኩ ብሎ ህንፃ ቢገነባ ወይም ለነሱ ብሎ እርድ ቢያርድ ይህ ሰው ስራው አላህን የሚወነጀልበት ስለሆነ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ቅጣትም ይጠብቀዋል። በአጠቃላይ መጥፎ ስራ በጥሩ ኒያ ምክንያት ወደ መልካምነት በፍፁም አይቀየርም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here