የማስፈቀድና የጉብኝት /ዚያራ/ ደንብ (አዳብ- ክፍል 2)

0
3847

የጉብኝትና የማስፈቀድ አዳብ ፅንሰ ሀሳብ

ሰዎችን ከማግኘት በፊት የቅድሚያ ፈቃድ የመጠየቅ ስርዓት በሙስሊም ህይወት ውስጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳይ ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ ረገድ የሚስተዋለው ቸልተኝነት የግለሰቦችንና የማህበረሰቡን ህይወት ያቃውሳል። ጊዜውን በአግባቡ ለሚጠቀምና በፕሮግራም ለሚመራ ሙስሊም ይህ ስርአት ወሳኝ ነው። ለጊዜው (እድሜው) ትልቅ ቦታ ለሚሰጥና ሌሎችን በመርዳትና ታላላቅ ተልእኮዎችን በማሳካት ለተጠመደ ሰው ይህ ደንብ እጅግ ያስፈልገዋል።

እንዲህ አይነቱ በፕሮግራምና በስርዓት የሚመራ ሰው ጊዜን ሊያከብርና ሰዎችን ቅድሚያ የማስፈቀድ ደንብ ተገዢ ሊሆንም ይገባል።

አንዳች ወሳኝ ተግባር በመፈፀም ላይ ሳለህ አንድ ሰው ቀድም ሳያሳውቅህ (ሳያስፈቅድህ) በድንገት በርህን ቢያንኳኳና ቢገባ  ከስራህ ቢያናጥብህ፣ ወይም የሆነ መፅሀፍ ማንበብ ጀምረህ፣ በሆነ ርዕሰ ጉዳይ እየፃፍክ ሳለህ፣ ወይም ከሆነ የስራ ባልደረባህ ጋር የስራ ጉዳይ እየተወያየህ ወይም ከናፈቅከው ወዳጅህ ጋር ወይም ከምትወዳቸው ቤተሰቦችህ (ሚስትህና ልጆችህ ጋር እየተጫወትክ) ሳለህ ቀጠሮ ያላስያዝከው ሰው በድንገት መጥቶ ቢያቋርጥህ፣ ሁሉን ነገርህን ቢያናጥብህ የሚሰማህን አስብ-

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል:-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَدْخُلُوا بُيُوتًا غَيْرَ بُيُوتِكُمْ حَتَّىٰ تَسْتَأْنِسُوا وَتُسَلِّمُوا عَلَىٰ أَهْلِهَا ذَٰلِكُمْ خَيْرٌ لَّكُمْ لَعَلَّكُمْ تَذَكَّرُونَ * فَإِن لَّمْ تَجِدُوا فِيهَا أَحَدًا فَلَا تَدْخُلُوهَا حَتَّىٰ يُؤْذَنَ لَكُمْ وَإِن قِيلَ لَكُمُ ارْجِعُوا فَارْجِعُوا هُوَ أَزْكَىٰ لَكُمْ وَاللَّهُ بِمَا تَعْمَلُونَ عَلِيمٌ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እስከምታስፈቅዱና በባለቤቶቿ ላይ ሰላምታን እስከምታቀርቡ ድረስ ከቤቶቻችሁ ሌላ የኾኑን ቤቶች አትግቡ። ይህ ለእናንተ መልካም ነው። እናንተ ትገነዘቡ ዘንድ (በዚህ ታዘዛችሁ)። በውስጧም አንድንም ሰው ባታገኙ ለእናንተ እስከሚፈቀድላችሁ ድረስ አትግቧት። ለእናንተ ተመለሱ ብትባሉም ተመለሱ። እርሱ ለእናንተ የተሻለ ነው። አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው።” (አን-ኑር 24፤ 27-28)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ

لا تأتوا البيوت من أبوابها ولكن ائتوها من جوانبها، فاستأذنوا، فإن أذن لكم فادخلوها، وإلا فارجعوا

“ቤቶችን ቀጥታ በበር ጋር ሁናችሁ አትግቡ ይልቁንም በጎን በኩል ሁኑ፣ አስፈቅዱም፣ መግባት ከከተፈቀደላችሁ ግቡ፣ ካልተፈቀደላችሁ ግን ተመለሱ” (ጠበራኒ ዘግበውታል)

ይህ ነው እንግዲህ ኢስላም ለተከታዮቹ የሚያስተምረው የመጠቀ ስነስርአት።  የልብ በሺታ ያለበት ሰው ያልተፈቀደለትን ነገር ለማየት ወይም የሌሎች የግል የሆነ ጉዳይ ለማየት እንዳይችል ኢስላም ይህን እኩይ ተግባር ከለከለ።  ለሁሉም ወደ ሰው ቤት ስትገቡ አስፈቅዳችሁ ይሁን ሲል አወጀ። ባለቤቱ በሙሉፈቃደኝነት መስማማቱን እስከሚገልፅ ድረስ አትግቡ በማለት ደንቡን አስቀመጠ።

“እስቲእናስ”-الاستئناس -የሚለው የአረብኛ ቃል “ማስፈቀድ” ከሚለው ቃል በላይ የሆነ መልእክት አለው። አንድ ሰው ሊፈቅድልህ ይችላል። ነገር ግን አንተን ለማግኘት ፈልጎ ሳይሆን ሀያእ ይዞት (አንተን ላላመመለስ አፍሮ) ሊሆን ይችላል።  ሙስሊም በሙሉ ፈቃደኝነት (በመፈለግ) መስማማትና በሀያእ እሺ ማለት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲረዳ ይጠበቃል።  ስለተፈቀደለት ብቻ መግባት ሳይሆን በርግጥ እሺታውን የገለፀው በሙሉ ፈቃድ በመስማማት መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

ተግባራዊ እርምጃዎች

ይህን አደብ ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወንህን አረጋግጥ

 1. ልትጎበኘው ያሰብከውን ሰው ጋር ቀድመህ ቀጠሮ አስይዝ
 2. ለጉብኝትህ አላማ ያለህ መሆንህን እርግጠኛ ሁን
 3. ጉዳይህን ከፈፀምክ ከሰው ቤት አትቆይ
 4. በስልክ ወይም በሌላ መንገድ መፈፀም የምትችለውን ጉዳይ ለመፈፀም ስትል ሰዎች ቤት አትሂድ
 5. ሶስት ጊዜ በሩን አንኳኳ፣ ካልተከፈተልህ ተመለስ
 6. ከበሩ በጎን በኩል ሁን፣ ወደ ሰዎች ቤት ውስጥ አታጮልቅ (አትመልከት)
 7. ስለማንነትህ ከጠየቀህ (ማነው ስትባል )፣ራስህን በአግባቡ ግለፅ (ስምህን ተናገር)፣ “እኔ ነኝ” አትበል
 8. የቤቱ ባለቤት አሁን ላገኝህ አልችልም ካለህ፣ በንፁህ ልብ ተረዳው (ተቀበለው)
 9. ጉዳይህን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ሞክር
 10. ሰዎችን ለመዘየር ምቹ የሆኑ ወቅቶችን ተጠቀም፣ በተጠሉ ወቅቶች ሰዎችን አትዘይር
 11. የቤቱ ባለቤት በእውነት አንተን ለማግኘት ፈልጎ የፈቀደልህ መሆኑን እርግጠኛ ሁን
 12. ባለቤቱ ተቀመጥ ያለህ ቦታ ተቀመጥ
 13. የራስህንም ሆነ የባለቤቱን ጊዜ መቆጠበህን እርግጠኛ ሁን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here