የስነ ምግባር ደንብ (አዳብ/Etiquette) ምንነትና አስፈላጊነት
ሁሉም ማህበረሰብ ከሌሎች የሚለየው የራሱ የሆነ የስነምግባር ደንብ አለው። ራሱን የሚያከብር ማህበረሰብ ግለሰቦቹን በራሱ መርሆዎች ላይ ያንፃል። የግለሰቦች የአኗኗር ዘይቤ ለማህበረሰቡ አስተሳሰብ ተግባራዊ ተምሳሌትና መገለጫ ይሆናል። ማህበረሰብ ከርሱ በላይ ጠንካራ በሆነ ሌላ ማህበረሰብ መሸነፍ ማሳያ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል ማህበረሰቡ መርሆዎቹን መዘንጋቱ፣ መርሆዎቹ በግለሰቦቹ አኗኗር ዘይቤ ላይ ያለመንፀባረቁና በዘመኑ አስተሳሰብ መዋጥ ይገኙበታል።
አሜሪካ አንግሎሳክሰን የተባለው ህዝብ አካል ነች። ይህ ከመሆኑም ጋር ከነዚህ ህዝቦች የሚለያትን መንገድ ቀይሳለች። የራሷን የስልጣኔና ባህል መገለጫ አዋቅራለች። የራሷን የአኗኗር ዘይቤና የስነምግባር ደንብ ፈጥራለች። በጋር የሚግባባቡት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሳይቀር በጊዜ ሂደት የራሷን የተለየ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘየ እንዲኖራት አድርጋለች።
አይሁዶች የራሳቸው ሀገር እንዲኖራቸው ሲወስኑ (ሲስማሙ) ከአለም ዙሪያ ተሰባሰቡ። ቋንቋቸው የተለያየ ነበር፤ ባህላቸውም እንደዚሁ። ከዚሁም ጋር ወደ ፍልስጤም የሚሰደድን በሙሉ የአይሁዶችን ቋንቋ (ኢብራይስጥን) እንዲማርና የአይሁዶች መለዮ ቆብ እንዲያደረግ አስገድደዋል።
የራሱ ስነምግባር ደንብና ባህል (ስርዓት) የሌለው ማህበረሰብ የለም። የስነምግባር ደንብ (ዒልመል-ሱሉክ) በዩኒቨርስቲዎች ራሱን ችሎ የሚሰጥ የትምህርት አይነት ነው። ዲፕሎማቶች በስራቸው ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ይህ ስልጠና ይሰጣቸዋል። የአበላል፣ የአጠጣጥ፣ የአለባበስ፣ የንግግር (ውይይት) ደንብ (ስነስርዓት) ይማራሉ። ምክንያቱም ዲፕሎማት ማለት የአገሩና የህዝቡ አምባሳደር ነውና። የህዝቡን ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ ሊያንፀባርቅ ይገባል።
ሙስሊሞች የበላይ በነበሩበት በአባሲድ ስርአት-ዘመን ከሌላ አገር የሚመጡ አምባሳደሮች ኸሊፋውን ከማግኘታቸው በፊት ለአንድ ወር በዋናዋ ከተማ ባግዳድ ይቀመጡ ነበር። አምባሳደሩ በዚህ ወቅት አንዳንድ የአረብኛ ቃላትን እየተማረ፣ የአለባበስ፣ ሰላምታ አሰጣጥና ተመሳሳይ ስርአቶችን እየተለማመደ ይቆያል። ከኸሊፋው ጋር በሚገናኝ ጊዜ እንዴት በመልካም ሁኔታ አቀራረቡን እንደሚያሳምር እርግጠኛ ለመሆን። ያኔ የሙስሊሙ ኡማ ጠንካራ ነበር። ሌሎች ህዝቦች ሙስሊሞችን የሚከተሉበት (የሚመሳሰሉበትና) የስነምግባር ደንቡን የሚያከብሩበት ዘመን ነበር።
የስነምግባር ደንብ ዛሬ ላይ ፕሮቶኮል (Protocol/ አዳብ አስ-ስሉክ) የሚባል መጠሪያ ተሰጥቶታል። ሁሉም ህዝብ የራሱ ፕሮቶኮል አለው። እንዲያውም የፕሮቶኮሉን አፈፃፀም የሚከታተል ራሱን የቻለ ልዩ ባለሙያ ይመደባል። ልዩ በሆነ መንገድ ትበላለህ፣ ትለብሳለህ፣ ሰላምታ ትሰጣለህ፣ ትቀመጣለህ። ይህ ደንብ ከቦታ ቦታ ይለያያል። እያንዳንዱ ኡማ የራሱ የሆነ ደንብና ስብእና አለው። እነዚህ ጉዳዮች ሁለተኛ (ትርፍ) ጉዳዮች ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። እንዲያውም ታላቅና ወሳኝ ከሚባሉ አጀንዳዎች የሚካተት ነው። እነዚህ የፕሮቶኮል ደንቦች በከፍተኛ አመራሮች የሚደነገግና የሚቀመጥ ሌላ አካል መቀየር የማይችላቸው መሆኑ እነዚህ ደንቦች የአንድ ህዝብ የማንነት መገለጫ መሆናቸውን ያጋግጥልናል።
አዳብ በኢስላም
ከዚህ በመነሳት የኢስላም ሸሪዓ የሙስሊሙ ኡማ ማንነቱን በመጠበቅና ልዩነት በማሳወቅ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-
إن اليهود والنصارى لا يصبغون، فخالفوهم
“አይሁዶችና ክርስቲያኖች ፀጉራቸውን አያቀልሙም፤ (እናንተ ፀጉራችሁን በማቅለም) ተፃረሯቸው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)
እንደዚሁም
لا تقوموا كما تقوم الأعاجم يعظم بعضهم بعضا
“ሌሎች ህዝቦች አንዳቸው አንዱን ለማክበር ሲል እንደሚቆመው አትቁሙ” (አቡ ዳውድና ኢብኑ ማጃህ)
لا تطروني كما أطرت النصارى ابن مريم إنما أنا عبدٌ فقولوا: عبد الله ورسوله
“ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ እንዳጋነኑት አታጋኑኝ። እኔ ባሪያ ብቻ ነኝ። የአላህ ባሪያና መልእክተኛ በማለት ጥሩኝ” (ቡኻሪ)
ኢስላም በአለባበስም ሆነ በገፅታ ሌሎች ህዝቦችን መመሳሰልን ከልክሏል። በእንቅስቃሴም ሆነ በአኗኗር ስርአት መመሳሰልን አውግዟል። በአነጋገርም ሆነ ስነምግባር ደንብ እንደዚሁ። ምክንያቱም ከዚህ ሁለ ጀርባ አንዱን ስርአት ከሌላው፣ አንዱን አመለካከት ከሌላው የመለየት ጥልቅ ስሜት በመኖሩ ነው። አንድን ስብስብ ከሌላው የሚለየው ልዩ ባህሪ መኖሩ ነው።
ኢስላም ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ህዝቦች ውስጣዊ ሽንፈት እንዳይሰማን ከልክሏል። አንድን ህዝብ አልቆ መመልከት ያንን ህዝብ በጭፍን እንድትከተል ያመቻችሀል (ያደርገሀል)። የሙስሊሙ ኡማ የተፈጠረችው የሰው ልጅ መሪ ለመሆን ነው። ለመሪነት ካጫት አካል- አላህ- ባህሎቿንና ልማዶቿን ልትወስድ ይገባታል።
ይህ ጭፍን ወገንተኝነት ወይም ምክንያት አልባ አቋም አይደለም። ይልቁንም ከግልብ አመለካከት የራቀ ውስጣዊ እሳቤንና ፍላጎትን የሚዳስስ እይታ እንጂ። እነዚህ እሳቤዎችና ፍላጎቶች ናቸው አንድ ህዝብ ከሌላው የሚለዩት። ይህ ሚዛን ነው አንድን አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ የህይወት እይታ ከሌላው የሚለየው።
ይህን ሀሳብ የሚያመላክቱ በርካታ ሐዲሶች ተነግረዋል።
የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡-
من تشبه بقوم فهو منهم
“ከአንድ ህዝብ ጋር የተመሳሰለ ከነርሱ ነው”
ليس منا من تشبه بغيرنا
“ከሌሎች ህዝቦች ጋር የተመሳሰለ ከኛ (ወገን) አይደለም”።
የዚህ ክልከላ አላማ ሌሎች የሚጠቀሙትን ስልቶችና ዘዴዎች እንዳንጠቀም መከልከል አይደለም። ይልቁንም የሌሎችን በስነምግባር ደንቦችንና አኗኗር ስርዓታቶች በጭፍን እንዳንከታተል መከልከል ነው። ልዩ ማንነታችንና ስብእናችንን እንዲሁም መገለጫዎቹን ጠብቀን እንድንኖር ማስቻል ነው።
በዚህ መግቢያ ላይ ትኩረት ለመስጠት የተፈለገው ዋናው ጉዳይ ስለ አዳብ (ስነ-ስርአት) ስናወራ ቅርፃዊና የላይ ላይ ተግባር ይህን ያህል ትኩረት የሚሻ ነጥብ አይደለም የሚሉ ወገኖች መልስ ለመስጠትና ተራ የጭፍን ወገንተኝነትና ጠባብነት ጉዳይ አለመሆኑን ለመሳየት ነው። ከውስጡ የተሸነፈ ሰው ማንነቱን ያጣል የቀንና የለሊት ሀሳቡ ሌሎችን በጭፍን ስለመከተልና ስለመመሳሰል ብቻ ይሆናል።
ከዚህ በመቀጠል በተከታታይ ክፍሎች አንድ ሙስሊም በንግግሩ ዳእዋ (ወደ ኢስላም ጥሪ) እንደሚያደርገው ሁሉ በተግባሩም ተጣሪ ይሆን ዘንድ የሚያስችሉትን የኢስላም አዳቦች (የስነምግባር ደንቦች) ዋና ዋናዎቹን ለማየት እንሞክራለን።
ምንጭ፡- ደ/ር ሙስተፋ ጣሃን, “አዳበ ሱሉክ ፊል ኢስላም”
Jeza kallah