ተውሒድ – የኢስላም መገለጫ (ተውሒድ – ክፍል 3)

0
2899

ኢስላም ለተውሒድ የሰጠውን ክብደትና ትኩረት ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ ተውሒድን መገለጫው፣ ከጣኦት አምልኮ፣ ከክርስትና፣ ከአይሁድም ሆነ ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለይበት አብይ ባህሪው ማድረጉ ነው።

እናም የኢስላም አብይ መገለጫ “አሐዳዊ እምነት” (ዲኑ ተውሒድ) የሚለው ቃል ሆነ።

ኢስላም መሠረታዊ መልእክቱ በሁለት ሐረጎች ይገለጻል። እነርሱን የተቀበለ ወደ ኢስላም ይገባል። የመጀመሪያው ሐረግ “ሸሃደቱ አን ላኢላሐ ኢለላህ” (ከአላህ በስተቀር አምልኮት የሚገባው አምላክ እንደሌለ መመስከር) ሲሆን ሁለተኛው “ወአነ ሙሐመደን ረሱሉላህ” (ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን መመስከር) ነው።

የአላህን አንድነትና የነቢዩ ሙሐመድን መልእክተኛነት መመስከር ናቸው።

ከአላህ ሌላ አምላክ የለም ብሎ መመስከር ማለት ከርሱ ውጭ በሰማያትም ሆነ በምድር በእውነት የሚያመልኩት አምላክ እንደሌለና ከርሱ ሌላ ያሉ አማልክት ሁሉ የሐሰት አማልክት መሆናቸውን መመስከር ነው። ይህ ምስክርነት አላህን ብቻ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት ማምለክንና ከርሱ ሌላ ያሉ አማልክትን ሁሉ ፈጽሞ አለማምለክን ያካትታል። ሁለት ነገሮች እስካልተረጋገጠ ድረስም ጠቀሜታ አይኖረውም፡-

  • አንደኛ፡- የአላህን አሐዳዊነት ከልብ አምኖ፣ አውቆ፣ እውነት ብሎና ወዶ መቀበል።
  • ሁለተኛ፡- ከአላህ ሌላ በሚመለኩ ነገሮች ሁሉ መካድ። የአላህን አንድነት በቃሉ መስክሮ ከአላህ ውጭ የሚመለኩ አካላትን ያልካደና ያላስተባበለ ምስክርነቱ አይፈይደውም።

የነቢዩ ሙሐመድን መልእክተኛነት መመስከር ማለት የታዘዙትን መፈጸም፣ ያስተላለፉትን መልእክት እውነት ብሎ መቀበል፣ ከከለከሉት መታቀብ፣ አላህን እርሳቸው ባስተማሩት መንገድ ብቻ ማምለክ፣ እርሳቸው ለሰው ልጆች ባጠቃላይ መላካቸውን ማወቅና ማመን፣ የአላህ አገልጋይ እንደሆኑ፣ እንደማይመለኩ፣ የማይስተባበሉና ሊታዘዟቸው የሚገቡ መልእክተኛ መሆናቸውን፣ የታዘዛቸው ጀነት፣ ያመጸባቸው እሳት እንደተዘጋጀለት ማወቅና ማመን ነው። እንዲሁም በእምነትና አመለካከት፣ በአምልኮ ስርዓት፣ በሕግና አስተዳደር፣ በስነ ምግባር፣ በቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በሐላልና በሐራም አጀንዳዎች ወዘተ የአላህን ሕግ ከርሳቸው እንደምንቀበል ማወቅና ማመን ግድ ነው። ምክንያቱም የአላህን መልእክት ለሰው ልጆች አድራሽ ናቸውና።

ይህን የተውሒድ ቃል መግለጽ ለአንድ ሙስሊም የየእለት ተግባሩ ነው። በቀን ውስጥ በግዴታ ሶላቶች ተሸሁድ ላይ ዘጠኝ ጊዜ፣ በኢቃማው አምስት ጊዜ ደጋግሞ ይናገረዋል። ኢስላም በዚህ ብቻም አላበቃም። በየቀኑ አምስት ጊዜ በሁሉም የዓለማችን ክልሎች በሚገኙ መስጊዶች ውስጥ በከፍተኛ ድምጽ፡-“አሽሐዱ አንላኢላሐ ኢለላህ” ተብሎ እንዲታወጅ አዟል።

ሙስሊም አባት አዲስ የተወለደ ልጁን ሸሪዓዊ በሆነ አዛን (የሶላት ጥሪ) እንዲቀበል ኢስላም ማዘዙም ድንቅ ነገር ነው። እንደተወለደ በቀኝ ጆሮው አዛን ያሰማዋል። እናም በዚህች ዓለም ውስጥ ሕጻኑ የሚሰማው የመጀመሪያው ድምጽ የተውሒድ ድምጽ ይሆናል። ልጁ በዚህች ዓለም ውስጥ አላህ የወሰነለትን ያህል ጊዜ ቆይቶ ሊሞት ሲቃረብ ወዳጅ ዘመዶቹ “ላኢላሐኢለላህ” የሚለውን ቃል ይናገር ዘንድ ከአጠገቡ በመደጋገም ይሉለታል። በዚህ መልኩ ሙስሊም የሕይወትን ብርሃን የሚቀበለው በተውሒድ ሲሆን፣ ሕይወትን የሚሰናበትበት የመጨረሻ ቃልም ተውሒድ ይሆናል። ከሕጻንነት አንቀልባ እና ከሞት አልጋው መካከል ባለው የሕይወት ጊዜውም ተውሒድን ከማጽናት እና ወደርሱ ከመጣራት ውጭ ሌላ ዓላማና ተግባር የለውም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here