ተውሒድ – የመልዕክተኞች አብይ ተልእኮ (ተውሒድ – ክፍል 2)

0
4862

ተውሒድ በመለኮታዊ ሃይማኖቶች ሁሉ ከፍተኛ ቦታና ክብር ያለው በመሆኑ ከኑሕ እስከ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ድረስ በአላህ መልእክተኞች ጥሪ ውስጥ አብዩን ስፍራ ሊይዝ በቅቷል። አላህ ለሰው ልጆች መሪ አድርጎ የላካቸው መልእክተኞች ተግባር እርስ በርስ ተያያዥነት ባላቸው ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች ይጠቃለላል፡-

  • አንደኛ፡- አላህን ወደ ማምለክ ጥሪ ያደርጋል።
  • ሁለተኛ፡- ጣኦትን ወደ መከልከል (ወደ መታቀብ) ጥሪ ያደርጋል።

ቁርአን ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡-

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ فَمِنْهُم مَّنْ هَدَى اللَّهُ وَمِنْهُم مَّنْ حَقَّتْ عَلَيْهِ الضَّلَالَةُ فَسِيرُوا فِي الْأَرْضِ فَانظُرُوا كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُكَذِّبِينَ

“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ “አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ” በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል። ከእነሱም ውስጥ አላህ ያቀናው ሰው አልለ። ከእነሱም ውስጥ በእርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አልለ። በምድርም ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።” (አን-ነህል፤ 36)

ነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲል አናግሯቸዋል፡-

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ

“ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (አል-አንቢያእ፤ 25)

ይህም በመሆኑ ሁሉም የአላህ መልእክተኞች ለየሕዝቦቻቸው ያስተላለፉት የመጀመሪያ ጥሪ እንዲህ ሆኗል

يَا قَوْمِ اعْبُدُوا اللَّهَ مَا لَكُم مِّنْ إِلَٰهٍ غَيْرُهُ إِنِّي أَخَافُ عَلَيْكُمْ عَذَابَ يَوْمٍ عَظِيمٍ

“ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ለእናንተ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም። እኔ በእናንተ ላይ የከባድ ቀንን ቅጣት እፈራላችኋለሁ።” (አል-አእራፍ፤ 59)

ኑሕ፣ ሁድ፣ ሷሊህ፣ ሹዓይብና ሌሎች ነብያትም ተመሳሳይ ቃል እንደተናገሩ ቁርአን ዘግቧል።

ወደ ጣኦታውያን በመጀመሪያ የተላኩት ነቢዩ ኑሕ ለወገኖቻቸው እንዲህ ይላል፡-

وَلَقَدْ أَرْسَلْنَا نُوحًا إِلَىٰ قَوْمِهِ إِنِّي لَكُمْ نَذِيرٌ مُّبِينٌ *  أَن لَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ إِنِّي أَخَافُ عَلَيْكُمْ عَذَابَ يَوْمٍ أَلِيمٍ

“ኑሕንም ወደ ሕዝቦቹ በእርግጥ ላክን። (አላቸውም)፡-“እኔ ለእናንተ ግልጽ አስፈራሪ (አስጠንቃቂ) ነኝ።” “አላህን እንጂ ሌላን አትገዙ። እኔ በእናንተ ላይ የአሳማሚን ቀን ቅጣት እፈራላችኋለሁና።” (ሁድ፤ 25-26)

ወገኖቻቸው እርሳቸው ከሞቱ በኋላ አምላክ ያደረጓቸው ዒሳም እንዲህ ብለዋል፡-

لَقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ وَقَالَ الْمَسِيحُ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ إِنَّهُ مَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ اللَّهُ عَلَيْهِ الْجَنَّةَ وَمَأْوَاهُ النَّارُ وَمَا لِلظَّالِمِينَ مِنْ أَنصَارٍ

“እነዚያ “አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው” ያሉ በእርግጥ ካዱ። አልመሲህም አለ፡- “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ።” እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ። መኖሪያውም እሳት ናት። ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።” (አል-ማኢዳህ፤ 72)

የነብያት መቋጫ የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ተውሂድ ያደረጉት ጥሪ ከሌሎች ይበልጥ የጠነከረ፣ ጥልቅ እና ዘልዓለማዊ ነው። ይህ እውነታ በቁርአንና በሱንና በጉልህ ሰፍሯል። የኢስላም አምልኳዊ ክንውኖች፣ ሕግጋትና ሥነ ምግባራዊ ደንቦች ሁሉ ይህ የተውሂድ ጥሪ በጉልህ ይንጸባረቅባቸዋል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here