ትርጓሜው
የአላህን ትእዛዝ በመቀበል፣ ውዴታውን በመፈለግ፣ ጥንታዊውን ቤት ለመዞር፣ በሶፋና መርዋ መሀል ለመሮጥ፣ ዓረፋ ሜዳ ላይ ለመቆም እና ሌሎችንም አምልኮዎች ለመፈፀም መካን ማሰብና ወደርሷ መሄድ ሐጅ ይባላል። ሐጅ ከአምስቱ የኢስላም መሰረቶች አንዱ ነው። ከእስልምና መሆኑ እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቀው የሚገባ የአምልኮ ዘርፍም ነው። ሐጅ ዋጂብ (ግዴታ) አይደለም ያለ ሰው ይከፍራል፤ ከእስልምና ይወጣል። ሐጅ ግዴታ የሆነው- እንደ አብዝሀ ልሂቆች (ጅምሁረል ዑለማ) አስተያየት- ከሒጅራ በኋላ ስድስተኛው አመት ላይ ነው።
ቱሩፋቱ
በብዙ ሐዲሶች ላይ ሐጅ የሚያስገኘውን ትርፍ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አብራርተዋል። ከእነዚህ መሀል ጥቂቱን እንይ፡-
1. አቡ ሁረይራ እንደዘገቡት፡-
سئل رسول اللّه صلى الله عليه وسلم، أي الأعمال أفضل ؟ قال: “إيمان بالله ورسوله”. قيل: ثمَّ ماذا ؟ قال: “ثم جهاد في سبيل الله”. قيل: ثم ماذا ؟ قال: “ثمَّ حَج مَبْرُور
“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘የትኛው ስራ በላጭ ነው?’ ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም ‘በአላህ ማመን!’ ብለው መለሱ። ‘ከዚያስ?’ ተባሉ። ‘በአላህ መንገድ ላይ መታገል (ጂሀድ)’ አሉ። ‘ከዚያስ?’ አሏቸው። ‘መልካም ሐጅ!’ አሉ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
መልካም ሐጅ (ሐጁን መብሩር) ማለት ሐጢያት ያልተቀላቀለው ሐጅ ነው።
2. አሁንም ከአቡ ሁረይራ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
مَنْ حجَّ، فلم يرفثْ، ولم يَفسُق، رجع كيوم ولدته أُمه
“ሐጅ ያደረገና (ሐጁ ላይ) የወሲብ ወሬ ያላወራ እና የፍስቀት ስራ ያልሰራ ሰው እናቱ እንደወለደችው ቀን ሆኖ ይመለሳል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
3. አሁንም አቡ ሁረይራ በዘገቡት ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
الحجاج والعُمّار وفدُ اللّهِ، إن دَعوه أجابَهم، وإن استغفروه غفر لهم
“ሐጅ እና ዑምራ የሚያደርጉ ሰዎች የአላህ እንግዶች ናቸው። ከጠሩት ይሰማቸዋል። ምህረት ከለመኑት ይምራቸዋል።” (ነሳኢይ፣ ኢብኑ ማጀህ እና ሌሎችም ዘግበውታል)
4. ኢብኑ ጀሪር -የሐሰን ደረጃ ባለው ሰነድ- ጃቢርን (ረ.ዐ) ዋቢ በማድረግ እደዘገቡት የአላህ መልእተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
هذا البيتُ دعامة الإسلام، فمن خرج يَؤمُّ هذا البيت من حاجّ أو مُعتمر، كان مضموناً على اللّه إن قبضه أن يُدخله الجنة، وإن ردَّه ردّه بأجر وغنيمة
“ይህ ቤት (ካዕባ) የኢስላም ወጋግራ ነው። እርሱን አስቦ ከቤቱ የወጣ ሐጀኛ እና ዑምራ የሚያደርግ ሰው አላህ ዋሱ ነው። ከገደለው ጀነት ያስገባዋል። ወደ ሀገሩ ከመለሰው አጅር እና ድልብ ምንዳ አግኝቶ ይመልሰዋል።” (ጠበራኒ ዘግበውታል)
5. ከቡረይዳህ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
النفقة في الحج كالنفقة في سبيل اللّه؛ الدرهم بسبعمائة ضعف
“ሐጅ ላይ የሚወጣ ወጪ ልክ በአላህ መንገድ (ጂሃድ) ላይ እንደሚወጣ ገንዘብ ነው። አንድ ዲርሀም በሰባት መቶ ንብብር ነው የሚመነዳው።” (ኢብኑ አቢ ሸይባ፣ አሕመድ፣ ጠበራኒይና በይሀቂይ በሐሰን ሰነድ አውርተውታል)
የሐጅ ግዴታ በእድሜ አንድ ጊዜ ነው
ሐጅ በእድሜ ውስጥ ተደጋጋሚነት የሌለው ግዴታ በመሆኑ ላይ ዑለሞች ሁሉ ይስማማሉ። ስለት ካልተሳለ በስተቀር በእድሜ ልክ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ግዴታ የሚሆነው። ከአንዴ በላይ የሚያደርገው ሐጅ እንደ ትርፍ (ተጠዉዕ) ይቆጠርለታል። አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ.) እንደዘገቡት፡-
“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንድ ቀን ኹጥባ አደረጉልን። ከዚያም ‘እናንተ ሰዎች ሆይ! አላህ በናንተ ላይ ሐጅን ግዴታ አድርጓል ሐጅ አድርጉ።’ አሉ። ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በየአመቱ ነውን?!’ አለ፤ አንድ ሰው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዝም ቢሉም ሦስት ጊዜ ይህን ጥያቄ ደጋገመው። ከዚያም ‘አዎን! ብል ኖሮ ግዴታ ይሆን ነበር። ከዚያም አትችሉም ነበር።’ አሉ። ከዚያም ‘የተውኳችሁን ተዉኝ! ከእናንተ በፊት የነበሩ ሠዎችን ያጠፋቸው ጥያቄ ማብዛታቸውና ነብያቶቻቸውን መንቀፋቸው ነው። አንድን ነገር ሳዛችሁ የቻላችሁትን ያህል ሥሩት። ማንኛውንም ነገር ከከለከልኳችሁ ተዉት።’ አሉ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ሐጅን ማቻኮል ግዴታ ነው?
ኢማም ሻፊዒይ፣ አስ-ሰውሪይ፣ አል-አውዛዒይና ሙሐመድ ኢብኑል-ሐሰን የሐጅ ግዴታነት ወዲያው ሳይሆን በፈለገው ጊዜ እንደሆነ ያምናሉ። ከእድሜው ውስጥ በፈለገው ጊዜ ያደርጋል። ግዴታ የሚያደርጉት መስፈርቶች ተሟልተው በሚቆይበት ጊዜ የሚያሳልፈው ወቅት ኃጢያት አይሆንበትም። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሂጅራ በኋላ እስከ አስረኛው አመት ድረስ ሐጅ ሳያደርጉ ቆይተዋል። ባለቤቶቻቸውና ብዙ ባልደረቦቻቸውም እስከዚህ ጊዜ ድረስ ያለ ሐጅ ቆይተዋል። ከዚህ በላይ እንደጠቀስነው ሐጅ በግዴታነት የተደነገገው ከሂጅራ በኋላ ስድስተኛው አመት ላይ ነው። ሐጅ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ያለውና ሐጅን ግዴታ የሚያደርጉ መስፈርቶች የተሟሉለት ሰው ሐጁን ማቆየቱ ኃጢያት ቢሆን ኖሮ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለአራት አመታት ያህል አያዘገዩም ነበር። ኢማም ሻፊዒይ እንዲህ ይላሉ፡-
فاستدللنا على أن الحج فرضه مرة في العمر، أوله البلوغ، وآخره أن يأتي به قبل موته
“ሐጅ በእድሜ አንድ ጊዜ ብቻ ግዴታ የሚሆን አምልኮ አንደሆነ በማስረጃ አረጋግጠናል። የግዴታ ዘመኑ የሚጀምረው ከጉርምስና ሲሆን ዘመኑ የሚያበቃው ደግሞ በሞት ነው።”
አቡ ሐኒፋ፣ ማሊክ፣ አሕመድ እና አንዳንድ የሻፊዒያ መዝሀብ ዑለሞች ደግሞ ሐጅን ግዴታ የሚያደርጉትን መስፈርቶች ያሟላ ሰው ከተግባሩ መዘግየት አይችልም ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ወዲያው ሐጅ ማድረግ አለበት። ይህን ሃሳብ የሚያጠናክሩት በዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ሐዲስ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ይላል፡-
من أراد الحج، فلْيُعَجِّلْ، فإنه قد يمرض المريض، وتضل الراحلة، وتكون الحاجة
“ሐጅ ማድረግ የፈለገ ያቻኩል። ምናልባት ህመምተኛውም ህመም ሊመጣበት፣ መጓጓዣ ሊያጣ ወይም ችግር ይገጥመው (ድህነት ይመጣበት) ይሆናል።” (አሕመድ፣ አል-በይሀቂይ፣ አል-ጠሓዊይ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል።)
በአቡሁረይራ ዋቢነት በተዘገበው ሌላኛው ዘገባ፡-
تعجّلوا الحَجَّ – يعني الفريضة – فإن أحدكم لا يدري ما يعرض له
“-ግዴታ የሆነውን- ሐጅ አቻኩሉ። ማንኛችሁም ምን እንደሚገጥመው አያውቅም።” የሚል እናገኛለን። አሕመድና አል-በይሀቂይ ዘግበውታል።
የመጀመሪያውን ሐሳብ የሚጋሩት ዑለሞች እነዚህና መሰል ሐዲሶችን በተመራጭነት ተርጉመዋቸዋል። ስለዚህ እንደነርሱ እምነት የሐዲሱ መልእክት እንዲህ ይላል። ማንም ሰው ምን እንደሚገጥመው ስለማያውቅ ሐጅን ግዴታ የሚያደርጉ መስፈርቶች በተሟሉለት ጊዜ ወዲያው ሐጅ ማድረግ ይወደድለታል (ሙስተሃብ)። የሐዲሶቹ መልእክት ይህን ነጥብ አጠናከረ እንጂ በፍጥነት ሐጅ ማድረግ ግዴታ መሆኑን አያስይዝም።
ሐጅ ግዴታ የሚሆንባቸው መስፈርቶች
የፊቅህ ልሂቆች አንድ ግለሰብ ላይ ሐጅ ግዴታ እንዲሆን የሚቆጥሯቸው ስምምነት ያለባቸው ነጥቦች አሉ። እነዚህ
የሚከተሉት ናቸው፡-
- ሙስሊም መሆን
- ለአቅመ-አዳም/ሄዋን መድረስ
- ዓቅል (አእመሮ ጤነኛ መሆን)
- ነፃ /ሁር/ መሆን (ከባርነት)
- አቅም (ችሎታ) መኖር (ኢስቲጣዓ)
እነዚህን መስፈርቶች ያላሟላ ሰው ሐጅ ማድረግ ግዴታ አይሆንበትም። ከእነዚህ መሀል እስልምና፣ ጉርምስና እና ዓቅል ማንኛውም የአምልኮ ተግባር በአንድ ሰው ላይ ግዴታ ነው ለማለት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች እንደሆኑ የሚታወቅ ነው። ሐዲስ ላይ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይሉናል፡-
رُفِع القلم عن ثلاث؛ عن النائم حتى يستيقظ، وعن الصبي حتى يشب، وعن المعتوه حتى يعقل
“ከሦስት ሰዎች መዝገብ ተነስቷል። የተኛ ሰው እስኪነቃ፤ ህፃን እስኪጎረምስ፤ እብድ እስኪነቃ።” እነዚህ ላይ ሐጅ ተጨማሪ ሁለት መስፈርቶችን አክሏል። አንደኛው ጨዋ መሆን (ባርያ አለመሆን) ነው። እንደሚታወቀው ሐጅ ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ የሚያሻው የአምልኮ ዘርፍ ነው። ባርያ ደግሞ የራሱ ገንዘብ የለውም። አቅምና ጊዜውም አሳዳሪውን በማገልገል የሚያሳልፈው ነው። ስለዚህ ባርያ ላይ ሐጅ ግዴታ አይደለም። ሁለተኛው መስፈርት ችሎታ (ኢስቲጣዓ) ነው። አላህ ቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል፡-
ግን ኢስቲጣዓ በምን ይሟላል?
ሐጅን ግዴታ ከሚያደርጉ መስፈርቶች መሀል የሆነውን ኢስቲጣዓን ተሟልቷል የምንልባቸው መስፈርቶች እነዚህ ናቸው፡-
- አካል ጤነኛ መሆን፡- በእርጅና፣ በአካል ጉዳተኝነት ወይም ይድናል ተብሎ በማይታሰብ ህመም ምክንያት አቅም የሌለው ሰው ገንዘብ ካለው ሌላ ሰው ሐጅ እንዲያደርግለት ማድረግ አለበት። ይህን ነጥብ “ሐጅን ለሌላ ሰው ማድረግ” የሚለው የፅሁፋችን ክፍል ውስጥ በስፋት ዳስሰነዋልና ወደሌሎቹ ጉዳዮች እንሂድ።
- መንገዱ አማን (ሰላም) መሆን፡- ሐጅ ለማድረግ ያሰበ ሰው ለነፍሱ እና ለገንዘቡ በማይሰጋበት መልኩ እስከ መካ የሚያደርሰው መንገድ ሰላም መሆን አለበት። ሽፍቶች ካሉና ገንዘቡ ወይም ህይወቱ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ከጠረጠረ (ከፈራ) ወይም ወረርሽኝ እንዳያገኘው ከፈራ ሐጅ ማድረግ ያልቻለ በመሆኑ ሐጅ ማድረግ አይገደድም።
- ስንቅ ያለው መሆን፡- ስንቅ ስንል አካሉ ጤና የሚሆንበት እና ህይወቱን የሚያቆይበት ቀለብ ነው። ይህም ሐጅን ፈፅሞ እስኪመለስ ድረስ ከቤተሰቦቹ ቀለብ እና መሰረታዊ ከሆኑ ወጪዎቻቸው- ከልብስ፣ ከቤት፣ ከመጓጓዣ እና ከማምረቻ መሳሪያዎች- የተረፈ መሆን አለበት።
- መጓጓዣ ያለው መሆን፡- እዚህ ላይ ታሳቢ የምናደርገው መጓጓዣው ለደርሶ መልስ የሚበቃ መሆኑን ነው። ይህም የየብስ፣ የባህር ወይም የአየር መጓጓዣ ሊሆን ይችላል። ልብ እንበል። ይህ በእግሩ መሄድ ለሚርቀው ሰው ነው። በእግሩ ቢሄድ የማይርቀው ሰው መጓጓዣ መኖሩ መስፈርት አይሆንም። ምክንያቱም ቅርብ ስለሆነ በእግሩ መሄድ ይችላል።
በአንዳንድ የሐዲስ ዘገባዎች ላይ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ቁርአን ላይ የተጠቀሰውን ‘ ሰቢላ’ (መኼድ) ማለት ምን እንደሆነ አብራርተዋል።
አነስ ኢብኑ ማሊክ ናቸው ሐዲሱን የዘገቡልን። “ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‘የአላህ መልእተኛ ሆይ! ሰቢል ማለት ምንድን ነው?’ ተብለው ተጠየቁ። ‘ስንቅና መጓጓዣ ነው!’ አሉ።” (ዳረቁጥኒይ ዘግበውታል። ሶሒሕ /ትክክለኛ/ ብለውታል።)
ከዓሊይ (ረ.ዐ) በተገኘው ዘገባ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ወደ የአላህ ቤት የሚያደርሰው ስንቅና ቀለብ ኖሮት ሐጅ ያላደረገ ሰው ከፈለገ አይሁድ ከፈለገ ነሷራ ሆኖ ይሙት! ምክንያቱም አላህ እንዲህ ይላል፡- ’’ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መኼድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው።”
የዚህ ሐዲስ ሰነድ ውስጥ ሂላል ኢብኑ ዓብዲላህ እና አል-ሐሪስ የሚባሉ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች አሉ። አል-ሐሪስን ሸዕቢይ እና ሌሎችም የሐዲስ ምሁራን “ሀሰተኛ” በማለት ፈርጀውታል።
ከላይ የጠቀስናቸው ሐዲሶች ምንም እንኳ ድክመት ያለባቸው ቢሆንም ብዙ ዑለሞች በአንድ ሰው ላይ ሐጅ ግዴታ እንዲሆን ስንቅ እና መጓጓዣን መስፈርት ያደርጋሉ። ስንቅና መጓጓዣ የሌለው ሰው ሐጅ ግዴታ አይሆንበትም።
አልሙሀዘብ የተሰኘው የኢማም አሽ-ሺራዚይ መፅሀፍ ላይ እንዲህ የሚል ማብራሪያ አለ፡- “ስንቅና መጓጓዣ ያገኘ ነገር ግን እዳ ያለበት ሰው- እዳው አስቸኳይ ቢሆንም ባይሆንም- ሐጅ ግዴታ አይሆንበትም። ምክንያቱም ሐጅ (እንደ ኢማሙ ሻፊዒይ እምነት) አጣዳፊ የሆነ የአምልኮ ግዴታ አይደለም። እዳ ግን አጣዳፊ ከሆነ ከሐጁ ይቀድማል። ቀጠሮው ገና ከሆነ ደግሞ ያለውን ገንዘብ ሐጅ ላይ አውሎት የሚከፍለው ሊያጣ ስለሚችል እንዳይጣበብ ያሰጋል። ስለዚህ አሁንም እዳው ከሐጁ ይቀደማል።”
ከዚያም በመቀጠል መፅሀፉ እንዲህ ይላል፡- “ያለውን ገንዘብ ለርሱ ለሚመጥን መኖሪያ ቤት መግዣና ለሚያስፈልገው አሽከር (ኻዲም) ከፈለገው ሐጅ ግዴታ አይሆንበትም። ካላገባ እና ዝሙት የሚፈራ ከሆነ ደግሞ ኒካህን ከሐጅ ያስቀድማል። ምክንያቱም ኒካሁ አጣዳፊ ሲሆን ሐጁ ግን ጊዜ የሚሰጥ የአምልኮ አይነት ነው። ገንዘቡን ለህይወቱ የሚጠቅመውን አስፈላጊ ወጪ ለመሸፈን ያስችለው ዘንድ ለንግድ ሊያውለው ከፈለገስ? አቡል-ዓባስ ቢን ሶሪሕ ‘ሐጅ ግዴታው አይሆንም። ምክንያቱም እርሱ እራሱን ያልቻለ ከገንዘቡ ከጃይ ነው። ንግዱ እራሱ እንደ መኖሪያ ቤት እና እንደ አሽከር አስፈላጊ ስለሆነ ሁለቱን ለይተን አናይም።’ ብለዋል።… እንደ የሻፊዒያ መዝሀብ ዑለሞች እምነት ያለ ምንም የገንዘብ ልውጫ (ኪራይ ወይም ግዢ) አንድ ሰው ለሌላው መጓጓዣ ቢሰጥ መቀበል ግዴታ አይሆንበትም። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ ስጦታ መመፃደቅን ያመጣል። መመፃደቅን መሸከም ደግሞ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ሰጪው ልጅ ከሆነ መቀበል ግዴታ ይሆናል። ምክንያቱም መመፃደቅ የሌለበት ስጦታ ስለሆነና ያለምንም ችግር ሐጅ ማድረግ ስለተመቸው ሐጅ ማድረግ ችሎታ ካላቸው ይመደባል።የሐንበሊያ ዑለሞች ግን ‘ሌላ ሰው በሚሸፍንለት ወጪ ሐጅ ማድረግ ግዴታ አይሆንበትም። ኢስቲጣዓን (ችሎታን) በስጦታው አግኝቶታልም አንልም። ስጦታ ሰጪው ዘመድ ወይም ባዳ ቢሆንም ይህ ብይን አይለወጥም። ስጦታው መጓጓዣ፣ ስንቅ ወይም ገንዘብ ቢሆንም ይኸው ብይን አይቀየርም።’ ብለዋል።”
5. ሰዎችን ከሀጅ የሚያግድ ነገር አለመኖር፡- ለምሳሌ መታሰር፣ ሰዎችን መካ ከመድረስ የሚያግድ በደለኛ ባለስልጣን ወ.ዘ.ተ.
የህፃን እና የባርያ ሐጅ፡-
ህፃናትና ባሪያዎች ሐጅ ግዴታ አይሆንባቸውም። ቢያደርጉት ግን ተቀባይነት አላቸው። ይህ ሐጃቸው ግን ከግዴታው ሐጅ አያብቃቃቸውም። የኢስላም ሐጃቸውም ጫንቃቸው ላይ እንዳለ ይሆናል። ዓብዱላህ ኢብኑ ዓባስ እንዲህ የሚለውን የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ.) ሐዲስ ዘግበውልናል።
أيما صبي حج، ثم بلغ الحِنْث، فعليه أن يحج حجة أخرى، أيما عبد حج، ثم أعتق، فعليه أن يحج حجة أخرى
“ማንኛውም ህፃን ሐጅ ቢያደርግና ከዚያም ቢጎረምስ ሌላ ሐጅ እንዲያደርግ ይገደዳል። ማንኛውም ባርያ ባርነቱ ላይ ሳለ ሐጅ ቢያደርግና ከዚያም ነፃ ቢደረግ በርሱ ላይ ሌላ ሐጅ አለበት።” (አጥ-ጠ-በራኒይ በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።)
አህመድ፣ ቡኻሪና ቲርሚዚ እንደዘገቡት ሳኢብ ኢብኑ የዚድ (ረ.ዐ) “አባቴ (እኔን ይዞ) ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ሐጅ አድርጓል። እኔም ያኔ የሰባት አመት ልጅ ነበርኩ።” ብለዋል።
ስለዚህ ህፃን ልጅ ከመድረሱ በፊት ሐጅ ካደረገ በኋላ ቢጎረምስ አሁንም ሐጅ ግዴታ ይሆንበታል። ባርያም ከነፃነቱ በፊት ሐጅ አድርጎ ከዚያም ነፃ ቢወጣ አቅሙ ካለው ሐጅ ማድረግ ግዴታ ይሆንበታል። ይህ ነጥብ ዑለሞች ያለልዩነት የተስማሙበት ነው።
ዐብዱላህ ኢብኑ ዓባስ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡- “…አንዲት ሴት አንድ ህጻንን ከፍ አድርጋ እያሳየች ‘ለዚህ ህፃን ሐጅ አለውን?’ ስትል ጠየቀች። ‘አዎን! ላንቺ ደግሞ ምንዳ አለሽ!’ አሉ፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)።” (ሙሰሊም፣ ቲርሚዚ፣ አቡ ዳዉድ፣ ኢብኑ ማጃህና አህመድ ዘግበውታል)
ጃቢር ኢብኑ ዓብዲላህ (ረ.ዐ) በዘገቡት ሐዲስ ደግሞ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡- “ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ሐጅ አድርገናል። ከእኛ ጋር ሴቶች እና ህፃናት አብረው ነበሩ። ለህፃናት ‘ለበይክ’ እንልላቸው እና ጠጠር እንወረውርላቸው ነበር።” (አህመድ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)
ልብ እንበል። ህጻን ልጅ የለየ (ሰባት አመት ገደማ የሆነ) ከሆነ ራሱ ይነይታል። የሐጅ ስራዎችንም እራሱን ችሎ ይፈፅማል። እንዲህ ካልሆነ ግን ወልዩ (ኃላፊው) ይነይትለታል። ተልቢያ ያደርግለታል። ጠዋፍ እና ሰዕይ (መሮጥ) የመሳሰሉትን የሐጅ ስራዎችም ያሰራዋል። ዓረፋ ላይም ያስቆመዋል። ጠጠር ይወረውርለታል። ዓረፋ ላይ ከመቆሙ በፊት ወይም ዓረፋ ላይ ቆሞ ሳለ ቢጎረምስም ይህ ሐጁ ከኢስላም ሐጅ (ከግዴታው ሐጅ) ያብቃቃዋል። ባርያም ነፃ ከተደረገ እንደዚያው አይነት ብይን ይኖረዋል። አላህ የተሻለ ያውቃል!!
የሴቶች ሐጅ
እንደ ወንድ ሁሉ ሴት ላይም ሐጅ ግዴታ ይሆናል። ያለፉት የመገደድ መስፈርቶች እስከተሟሉ ድረስ የፆታ ልዩነት የለም። ሴት ላይ ግን የምንጨምረው መስፈርት እንዳለ ይታወቅልን። አብሯት ባል ወይም መህረም (ለጋብቻ እርም የሆነ ዘመድ) ሊኖር ይገባል።
ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ሰማሁኝ ብለው የሚያወሩት ሐዲስን እንታዘብ፡-
لا يَخْلُوَنَّ رجل بامرأة، إلا ومعها ذو محرم، ولا تسافر المرأة، إلا مع ذي محرم”. فقام رجل فقال: يا رسول اللّه، إن امرأتي خرجت حاجّة، وإني اكتتبت في غزوة كذا، وكذا. فقال: “انطلق، فحُجَّ مع امرأتك
“ ‘ማንም ወንድ አብሯት መህረም በሌለበት ሁኔታ ከባዳ ሴት ጋር አይገለል። ማንኛዋም ሴት አብሯት መህረም በሌለበት ጉዞ ብላ አትውጣ።’ ከዚያም አንድ ሰው ብድግ አለና ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ባለቤቴ ሐጅ ላድርግ ብላ ወጥታለች። እኔ ደግሞ ልዘምት ተመዝግቤያለሁ።’ አለ። መልእክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) ‘ሂድና ከሚስትህ ጋር ሐጅ አድርግ።’ አሉ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
የሕያ ኢብኑ ዓባድ እንዲህ ብለዋል፡- “አንዲት አር-ረ-ይ የሚባል ሐገር ሴት ‘እኔ ሐብታም ነኝ። ነገር ግን ግዴታ የሆነብኝን ሐጅ አላደረኩም። መህረም ደግሞ የለኝም።’ ስትል ለኢብራሂም አን-ነ-ኸዒይ ፃፈችላቸው። እርሳቸውም ‘አንቺ አላህ መንገድ ካደረገላቸው (ችሎታ ካላቸው) ሰዎች አይደለሽም።’ ብለው ፃፉላት።” ይህን ነጥብ ሴቶች ላይ ሐጅ ግዴታ እንዲሆን ከሚቀመጡት መስፈርቶች እና እንደ ስንቅና መጓጓዣ የመቻል (ኢስቲጣዓ) መስፈርት የሚቆጥሩት ኢብራሂም አን-ነኸዒይ ብቻ አይደሉም። አቡ ሐኒፋ እና ባልደረቦቻቸው፣ አል-ሐሰን፣ አስ-ሰውሪይ፣ አሕመድ እና ኢስሐቅም ተመሳሳይ አቋም ይጋራሉ።”
አል-ሐፊዝ (ኢብኑ ሐጀር) እንዲህ ይላሉ፡- “የሻፊዒያ መዝሀብ ዑለሞች ጋር ሚታወቀው አቋም ባል ወይም መህረም ወይም ታማኝ ሴቶችን እንደ አማራጭ የሚያቀርበው አቋም ነው። አንዳንድ አስተያየቶች ላይ አንድ ሴትም ትበቃለች የሚል እናገኛለን። አል-ከራቢሲይ ባጣቀሱት በሌላ አመለካከት ደግሞ መንገዱ ሰላም እና ደህንነት ያለው ከሆነ ለብቻዋም መሄድ ትችላለች። ይህ ሁሉ ዋጂብ የሆነውን ሐጅ ወይም ዑምራ ለመፈፀም ሲሆን ነው።”
“ሱቡሉስ-ሰ-ላም” የተሰኘው መፅሀፍ እንዲህ ይላል፡- “አንዳንድ ዑለሞች ባልቴት ያለመህረም ጉዞ መውጣት ትችላለች ይላሉ።”
መንገዱ አማን ከሆነ ወይም ታማኝ የጉዞ ጓደኞች ካገኘች ሴት ያለ መህረም እና ያለባል መጓዝ ትችላለች የሚል አቋም ያላቸው ልሂቆች ቡኻሪይ በዘገቡት የዓዲይ ኢብኑ ሐቲም ሐዲስን መረጃ አድርገዋል። ዓዲይ እንዲህ ይላሉ፡-
بينا أنا عند رسول اللّه صلى الله عليه وسلم، إذ أتاه رجل فشكا إليه الفَاقَةَ، ثم أتاه آخر، فشكا إليه قطع السبيل، فقال: “يا عدي، هل رأيت الحِيرَة؟” قال: قلت: لم أرها، وقد أنبئت عنها. قال: “فإن طالت بك حياة، لترين الظَّعِينَةَ ترتحل من الحيرة، حتى تطوف بالكعبة لا تخاف إلا اللّه
“እኔ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ እያለሁ አንድ ሰው ወደርሳቸው መጣና በድህነት እየተሰቃየ እንዳለ ስሞታ አቀረበ። ሌላኛው ሰው ደግሞ መንገድ ስለመቆረጡ ነገራቸው። እርሳቸውም ‘ዓዲይ ሆይ! ሒራህ የምትባለዋን (የዒራቅ መንደር) ታውቃታለህ?’ አሉ። ‘ስለርሷ ሰምቻለሁ፤ አላየኋትም’ አልኳቸው። ‘ህይወትህ ከረዘመ በአቅማዳ (ሀውደጅ) ውስጥ ሆና የምትሄድ ሴት ከአላህ ውጭ ሌላን ሳትፈራ ከሒራህ ተነስታ በመጓዝ ካዕባን ጠዋፍ ታደርጋለች።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)
የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባለቤቶች ዑመር ባደረጉት የመጨረሻ ሐጅ ላይ ዑመርን (ረ.ዐ.) አስፈቅደው ሐጅ አድርገው ነበር። ብለው ደግሞ ሌላም መረጃ ያጣቅሳሉ። አብረዋቸው እንዲጓዙ የመደቡላቸው ዑስማን ኢብኑ ዐፋን እና ዐብዱር-ረ-ሕማን ኢብኑ ዐውፍን ነበር። ዑስማን “ማንም ሰው ወደነርሱ እንዳይቀርብ! ማንም እንዳያያቸው!” እያሉ አዋጅ ይሉ ነበር። ሴቶቹም ግመል ላይ በተጫነ አቅማዳ (ሀውደጅ) ውስጥ ነበሩ። (ቡኻሪ ዘግበውታል)
በማናቸውም የዑለሞች አመለካከት ብንሄድ አንዲት ሴት ያለ መህረም እና ያለ ባል ሐጅ ብታደርግ ሐጇ ተቀባይነት አለው። “ሱቡሉስ-ሰ-ላም” ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን። “ኢብኑ ተይሚያህ (ረ.ዐ.) እንዲህ አሉ፡- ‘ሴት ያለ መህረም የምታደርገው ሐጅ ተቀባይነት አለው። ሐጅ ለማድረግ ችሎታ (ኢስቲጣዓ) የሌለውም ሰው ሐጁ ተቀባይነት አለው’።”
በጥቅሉ፡- አቅም (ኢስቲጣዓ) የሌለው፣ ህመምተኛ፣ ደሀ፣ ገንዘብ የተቀማ ሰው፣ መንገድ የተቆረጠበት ሰው፣ መህረም የሌላት ሴት እና ሌሎችም ሐጅ ግዴታ ያልሆነባቸው ሰዎች እራሳቸውን በማጨናነቅ ሐጅ ላይ ከተገኙ ሐጃቸው ተቀባይነት አለው። ከዚህ በላይ አንዳንዶቹን በጎ ሰሪዎች ሌሎቹን ደግሞ ስህተተኞች ብለን ልንከፍላቸው እንችል ይሆናል። በጎ ሰራ የምንለው መጓጓዣ ባይኖረውም እራሱን አስጨንቆ በእግሩ የተጓዘን ሰው አምሳያ ነው። ስህተት ሰራ ያልነው ደግሞ ለምኖ ሐጅ ያደረገና ያለመህረም ሐጅ ያደረገችን ሴት አምሳያ ነው።
ሐጃቸው ተቀባይነት አለው ያልነው ለሐጅ ያላቸውን ብቁነት የሚያጓድል ምንም ነገር ስለሌለ ነው። ኃጢያቱን የፈፀሙት በሄዱበት መንገድ እንጂ ሐጁ ላይ አይደለም። ስለዚህ ሐጃቸው አልፎላቸዋል። ተቀባይነት አግኝቶላቸዋል።
ባልን ማስፈቀድ
ወደ ግዴታው ሐጅ የምትሄድ ሴት ባሏን እንድታስፈቅድ ትበረታታለች። ከፈቀደ ትወጣለች። ካልፈቀደላትም ያለፍቃዱ ትሄዳለች። ግዴታ የሆነውን ሐጅ እንዳታደርግ ባል ሚስቱን መከልከል አይችልም። ምክንያቱም እርሷ ላይ ግዴታ ከሆኑት አምልኮዎች መሀል አንዱ ነው። ፈጣሪን በማመፅ ፍጡርን መታዘዝ አይቻልም። በእርግጥ ላታስቸኩለው እና አዘግይታ ልትፈፅመው ትችል ይሆናል። ነገር ግን ጫንቃዋን ንፁህ ለማድረግ ካሰበች እና በፍጥነት ሐጅ ማድረግ ከፈለገች መብት አላት። ልክ ሶላትን በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገድ እንደምትችለው ማለት ነው። በዚህኛው ሐጅ አምሳያ የስለትን ሐጅ መቀየስ እንችላለን። እርሱም ግዴታ ስለሆነ ባሏ ባይፈቅድም መሄድ ትችላለች። ትርፍ ሐጅን ግን ባሏ እንዳትሄድ መከልከል ይችላል። ዳረቁጥኒይ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ይዘው ይህን ሐዲስ ነግውናል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሐብት ያላት እና ለሐጅ ባሏ ያልፈቀደላትን ባለትዳር ሴትን አስመልክቶ “ባሏ ካልፈቀደላት መሄድ አትችልም።” ብለዋል።
አላሁ አዕለም!