በአላህ አሀዳዊነት ማመን (ተውሒድ – ክፍል 1)

0
6386

በመላው ዩኒቨረስ ራሱን ያስተዋወቀው አምላክ አላህ አንድ ነው። አጋር የለውም። በማንነቱም ሆነ በባህሪው አምሳያ የለውም።

قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ اللَّهُ الصَّمَدُ لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ

“በል ‘እርሱ አላህ አንድ ነው። አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። አልወለደም፤ አልተወለደምም። ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም’።” (አል-ኢክላስ 1-4)

وَإِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ لَّا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ الرَّحْمَٰنُ الرَّحِيمُ 

“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው።” (አል-በቀራ 163)

በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ የሚገኝ ነገር ሁሉ ፈጣሪውም አስተናባሪውም አንድ መሆኑን ያመለክታል። ዩኒቨርሱን የሚመራው አካል ከአንድ በላይ ቢሆን ኖሮ ስርዓቱ በተፋለሰ ነበር። አላህ እንዲህ ሲል እውነትን ተናግሯል፡-

لَوْ كَانَ فِيهِمَا آلِهَةٌ إِلَّا اللَّهُ لَفَسَدَتَا فَسُبْحَانَ اللَّهِ رَبِّ الْعَرْشِ عَمَّا يَصِفُونَ

“በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር። የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ።” (አል-አንቢያእ 22)

مَا اتَّخَذَ اللَّهُ مِن وَلَدٍ وَمَا كَانَ مَعَهُ مِنْ إِلَٰهٍ إِذًا لَّذَهَبَ كُلُّ إِلَٰهٍ بِمَا خَلَقَ وَلَعَلَا بَعْضُهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ سُبْحَانَ اللَّهِ عَمَّا يَصِفُونَ

“አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)። ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም። ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር። ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር። አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ።” (አል-ሙእሚኑን 91)

አላህ በፈጣሪነቱ አንድ ነው። የሰማያትና የምድር እንዲሁም በመካከልም ሆነ በውስጣቸው ያሉ ፍጡራን አምላክ። ሁሉንም ነገር ፈጠረ። መጠኑን አስተካከለ። መራም። ከፍጡራኑ መካከል አንዱም በሰማይ ወይም በምድር ውስጥ ያለችን ቅንጣት ፈጥሬያለሁ፣ አስተዳድራለሁ ወይም እመግባለሁ የሚል ክርክር አያነሳም። ይህን ሊል አይገባውም። አይችልምም።

አላህ በአምላክነቱም አንድ ነው። ከርሱ ሌላ ለአምልኮ ተገቢ የሆነ አካል የለም። በፍርሃትና በተስፋ የሚያድሩለት፣ የሚተናነሱለት፣ እዝነቱን የሚከጅሉት፣ የሚመኩበት፣ ትእዛዙንም ያለ ተቃውሞ የሚፈጽምለት እርሱ ብቻ ነው። የሰው ልጆች ባጠቃላይ- ነቢያትን፣ የአላህ እውነተኛ ባለሟሎችን፣ ባለስልጣናትንና ንጉሳንን ጨምሮ- የአላህ ባሮች ናቸው። ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን መጥቀምም ሆነ መጉዳት፣ ሕይወትን መስጠትም ሆነ መንሳት አይችሉም። ከነርሱ ውስጥ አንዱን አምላክ ያደረገ፣ በፍርሃት የራደለት ወይም የሰገደለት ከሚገባው በላይ ከፍ አደረገው። የራሱንም ክብር አዋረደ።

ስለሆነም ኢስላም ለሰው ልጆች ባጠቃላይ፣ ለክርስቲያኖችና ለአይሁዶች በተለይ እንዲህ የሚል ጥሪ አስተላለፈ፡-

قُلْ يَا أَهْلَ الْكِتَابِ تَعَالَوْا إِلَىٰ كَلِمَةٍ سَوَاءٍ بَيْنَنَا وَبَيْنَكُمْ أَلَّا نَعْبُدَ إِلَّا اللَّهَ وَلَا نُشْرِكَ بِهِ شَيْئًا وَلَا يَتَّخِذَ بَعْضُنَا بَعْضًا أَرْبَابًا مِّن دُونِ اللَّهِ فَإِن تَوَلَّوْا فَقُولُوا اشْهَدُوا بِأَنَّا مُسْلِمُونَ

“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በእኛና በእናንተ መካከል ትክክል ወደ ኾነች ቃል ኑ። (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ፣ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጎ ላይይዝ ነው፤ በላቸው። እምቢ ቢሉም፡- እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክሩ በሏቸው።” (አሊ ኢምራን 64)

ኢስላማዊው እምነት “የተውሂድ” “የኢኸላስ” ወይም “የተቅዋ” ቃል በመባል በሙስሊሞቹ ዘንድ በምትታወቀው ሃረግ ይጠቃለላል። እርሷም ላኢላሀ ኢለሏህ (لا إله إلا الله) ናት- (ከአላህ ውጭ ሌላ አምላክ የለም።)

ይህች ሐረግ በምድራዊ አምባገነኖችና በጃሂልያ ጣኦታት ላይ የታወጀች አብዮት ነበረች።  ከኢስላማዊ መርሆዎችና እሴቶች ያፈነገጠ ማንኛውም ከኢስላም ውጭ ያለ ስርአትና የህይወት ዘይቤ ጃሂሊያ ይባላል። ተውሂድ በምድራዊ የሐሰት አማልክት ላይ ዛፍም ሆነ ድንጋይ ወይም ሰው የታወጀች ነበረች። “ላኢላሃ ኢለሏህ” የሰውን ልጅ ከፍጡራን ባርነት ነፃ ለማውጣት የተላለፈች አለማቀፋዊ ጥሪ ናት። የአዲስ ጎዳናና ሕይወት መገለጫም ናት። ይህ ጎዳና ንጉሳን ወይም አዋቂዎች የፈለሰፉት አይደለም። ፊቶች የሚዋደቁለት፣ ልቦች ለትእዛዙ የሚያድሩለት፣ ለስልጣኑ የሚርዱለት አምላክ ፍኖት እንጅ።

ላኢላሀ ኢለሏህ ከተለመደው የጃሂልያ ሕብረተሰብ የተለየ አዲስ ሕብረተሰብ መወለዱ የታወጀባት ቃል ነበረች። በእምነቱ፣ በአመለካከቱና ሕይወቱን በሚመራበት ስርዓት ፍጹም የተለየ ሕብረተሰብ። የዘር፣ የቦታና የመደብ ልዩነት የሌለበት ሕብረተሰብ። ለአንድ አምላክ ብቻ ያደረ፣ የርሱ ብቻ ፍጹም ተገዥና ታማኝ አገልጋይ የሆነ ሕብረተሰብ።

በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን የነበሩ የጃሂልያ መሪዎች በዚህች ቃል ውስጥ የተካተተውን መልእክት ተረድተዋል። የስልጣን ዙፋናቸውን የምታናጋ፣ አምባገነንነታቸውን የምትሰባብር፣ ደካሞችን በነርሱ ላይ የምታስነሳ ቃል መሆኗ ገብቷቸዋል። እናም ያላቸውን ኃይል ሁሉ ተጠቅመው ጦርነት ከፈቱባት። ሰዎች እንዳይቀበሏት ለማድረግ መንገዶችን ሁሉ ዘጉ። ያመኑትን ከእምነታቸው ለመመለስ የአቅማቸውን ያህል ጣሩ።

የሰው ልጅ ትልቁ ችግር ከመካከሉ ከፊሎቹ ራሳቸውን በምድር ላይ አምላክ ወይም ከፊል አምላክ ማድረጋቸው ወይም ደግሞ ሌሎች እነርሱን እንዲህ አድርገው መያዛቸው ነው። ሰዎች ለነርሱ ይሰግዳሉ፣ በፍርሃት ይርዱላቸዋል፣ ይዋደቁላቸዋል፣ ያለ ተቃውሞም ይታዘዟቸዋል።

ኢስላማዊው አሃዳዊ እምነት ግን የአማኞችን ነፍስ ከዚህ ርክሰት አጸዳ። ግማሽ ወይም 1/3ኛ ሰብአዊ አምላክ የላቸውም። የአምላክ ልጅ ወይም አምላክ ያረፈበት የሚባል ሰው አያውቁም። ሰው ለሰው አይሰግድም። ሰው ለሰው መሬት አይስምም። ይህ ነው የእውነተኛ የሰው ልጆች ወንድማማችነት፣ የእውነተኛ ነፃነት፣ የእውነተኛ ክብር መሠረት። በባሪያና በሎሌ መካከል ወንድምነት የለም። ሰውን አምላክ አድርገው በያዙበት ሁኔታ ነፃነት የለም። ለመሰሉ ፍጡር የሚሰግድና የሚያጎበድድ ወይም ከአላህ ውጭ ሌላ ገዥን የያዘ ሰው ሰብአዊ ክብርን ተነፍጓል። አቡ ሙሰል አሽአሪ እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡-

ወደ ነጃሺ በገባን ጊዜ እርሱ ከዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር። አምር ኢብኑል አስ በስተቀኙ፣ አማራህ በስተግራው ነበሩ። ቀሳውስቱ በስርዓት ተሰድረው ተቀምጠዋል። በወቅቱ ከቁረይሽ አጋሪዎች ዘንድ ወደ ነጃሺ በልዑክነት የተላኩት አምርና አማራህ “ለንጉሱ እነዚህ ሰዎች ለአንተ አይሰግዱልህም” ብለውት ኖሯል። ወዲያው እንደገባን ቀሳውስቱ “ለንጉሱ ስገዱ” ሲሉ አጣደፉን። ጃእፈር ኢብኑ አቢ ጣሊብም  “ከአላህ ውጭ ለማንም አንሰግድም” ሲል መለሰ።

ሃገራቸውን በችግር ምክንያት የለቀቁ ስደተኞች፣ የሰው አገር ጥገኞች፣ በንጉሱ ሃገርና ፈቃድ ስር በሆኑበት ሁኔታ እንኳ እምነታቸውን ለቅጽበት ለድርድር አላቀረቡም። ከአላህ ውጭ ለፍጡር ሊሰግዱ አልፈቀዱም። ይህች የጃእፈር ቃል የሙስሊሞች የዘወትር መፈክር ናት!

“ኢላህ” ማለት ምንድን ነው?

ኢላህ (አምላክ) ማለት በእውነት ሊመለክ የሚገባ ማለት ነው። ፍጹም ፍቅርና ፍጹም ታዛዥነት ሊለግሱት የሚገባ ማለት ነው። ይህም የሆነው ለፍጹም ፍቅርና ለፍጹም ታዛዥነት ተገቢ በሚያደርጉት ምሉእ ባህሪያት የተገለጸ በመሆኑ ነው።

አምላክ ሸይኹል ኢስላም ቢን ተይሚያህ እንዳሉት ቀልቦች የሚወዱት፣ የሚናፍቁት፣ የሚያድሩለትና የሚተናነሱለት፣ የሚፈሩት እና ተስፋ የሚያደርጉት፣ መከራ ሲያገኛቸው የሚመለሱበት፣ አንዳች ሃሳብ ሲይዛቸው የሚጠሩት፣ ለበጎ ነገር የሚመኩበት፣ ወደርሱ የሚመለሱበት እና የሚረጉበት፣ በፍቅሩ የሚሰክኑበት አካል ማለት ነው። ይህ አካል ደግሞ አላህ እንጅ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።

ይህም በመሆኑ “ላኢላሐኢለላህ” (ከአላህ ውጭ ሌላ አምላክ የለም) ከንግግሮች ሁሉ ይበልጥ እውነት እና በላጭ ሆነች። የነገሮች ሁሉ ፈርጥ፣ የበጎ ሥራዎች ሁሉ አስኳል ለመሆን በቃች። በሶሒሕ የሐዲስ ዘገባ እንደተወሳው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

أفضل ما قلته أنا والنبيون قبلي: لا إله إلا الله

“እኔና ሌሎች ነብያት ከተናገርናቸው ንግግሮች ሁሉ በላጯ ላኢላሐኢለላህ ናት።”

እውነተኛው አምላክ አላህ ብቻ መሆኑንና ከርሱ ሌላ አምላክ እንደሌለ በእርግጠኝነት ማመን፣ አምልኮዎችንም ለርሱ ብቻ ማዋል ነው።


ምንጭ፡- ዶክተር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ, “ሀቂቀቱ-ተውሒድ”።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here