የስድስቱ ቀን የሸዋል ፆም- ድንጋጌዎች እና ትምህርቶች

0
8063

ከረመዷን በኋላ የስድስቱ ቀን የሸዋል ፆም ሱና ሙአከዳ (ወደ ግዴታ የሚጠጋ ጠንከር ያለ ሱና) ነው። ስለዚህ ስለ ፆም በሚያነሳሳው ንግግራቸው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከረመዷን በኋላ እነኚህን ስድስት የሸዋል ቀናት የፆመ ሰው አመቱን ሙሉ እንደፆመ እንደሚቆጠርለት ተናግረዋል።

ከዚህም በመነሣት ረመዷንን አስከትሎ እነኚህን ስድስት ቀናት በየአመቱ መፆምን ያዘወተረ ሰው እድሜውን በሙሉ እንደፆመ ነው ማለት አንችላለን። ከአቡ አዩብ አል-አንሷሪ በተላለፈው ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

من صام رمضان ثم أتبعه ستًا من شوال فكأنما صام الدهر كله

“ረመዷንን የፆመና ከሸዋልም ስድስቱን ያስከተለ ሰው አመቱን በሙሉ እንደፆመ ነው።” ብለዋል (ሙስሊም፣ አቡ ዳውድ፣ ቲርሚዚና ኢብኑ ማጃ ዘግበውታል)።

“ደህር” ማለት አመት ማለት ሲሆን አመቱን በሙሉ እንደፆመ ነው ማለት ነው። በየአመቱ ይህንን ፆም የፆመ እድሜውን በሙሉ አንደፆመ ስንልም ለማብራሪያ የሚከተለውን ሀዲስ በመጠቀም ነው፡-

صيام شهر بعشرة أشهر وصيام ستة أيام بشهرين، فذلك صيام العام

“አንድ ወር መፆም እንደ አሥር ወር የሚቆጠር ሲሆን ስድስቱን ቀን መፆም ደግሞ እንደ ሁለት ወር ናቸው። ይህም በአጠቃላይ የዓመት ፆም ማለት ነው።” (ኢማም አህመድና ኢብኑ ሂባን ዘግበውታል)

ከረመዷን በኋላ ፆምን መላመድና ለፆም መነሣሣት ላለፈው ረመዷን ፆም ተቀባይነት ማግኘት ምልክት ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከአንድ ባሪያው ሥራውን የተቀበለ እንደሆነ ከዚያ በኋላም ቢሆን ለሌላ መልካም ሥራ ያነሣሣዋል፤ እንዲፀናም ያደርገዋል። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሸዋልን ስድሰት ቀን ፆም እንድንፆም መክረውናል። ይህም ታላቅ ምንዳን እንደሚያስገኝልን ጠቁመውናል። ምንዳው ለመግለፅ የሚከብድ ነው። ይህም ለኛ ለሙሀመድ ህዝቦች ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሆነ ችሮታና ልግስና ነው። ምንም እንኳን በምድር ላይ የተሠጠን እድሜ አጭር ቢሆንም እነኚህንና የመሳሰሉትን ምንዳቸው ተነባብሮ የሚከፈልባቸውን ሥራዎች በመሥራት በተዘዋዋሪ የረጅም እድሜ ባለቤት የሆነ ሰው የሚያገኘውን ጥቅም ልናገኝ እንችላለለን። የታደለና አላህ ያደለው ሰው ማለት ይህን እድል በአግባቡ የተጠቀመና እነኚህ ጥቂት ቀናት ሳያልፉም የተጠቀመባቸው ነው። ኢማም ነወዊ ረሂመሁሏሁ ዑማኦች እንዲህ ብለዋል ይላሉ “አንድ አመት ፆም ሊሆን የቻለበት ምክኒያት መልካም ሥራ በአሥር ስለሚባዛ ረመዷን በአሥር ወር ስድስቱ የሸዋል ቀናት ደግም በሁለት ወር ማለትም ስልሣ ቀናት ስለሚታሰቡ ነው።” ብለዋል።

ስድስቱን ቀናት አከታትሎ ስለመፆም

እነኚህን የሸዋል ቀናት ልክ ረመዷን እንዳለቀ በዒድ ማግስት አከታትለን መፆም ይኖርብናል ወይንስ በሸዋል ውስጥ በማንኛውም ቀን ስድስት ቀን መፆም ይገባናል በሚለው ላይ ዑለማኦች ተወዛግበዋል። ሐነፊዬች እና ሻፊዒዬች ማከታተሉ በላጭ መሆኑን ሲያስረዱ ኢማም አህመድ ግን በሁለቱም መልክ ፆሙን መፈጸም እንደሚቻልና አንዱ ከሌላኛው ተመራጭ እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ (ሰይድ ሳቢቅ፡- ፊቅህ አስ-ሱና )። ሁሌም ቢሆን ሸዋል የረመዷንን ወር ተከትሎ የሚመጣ ነውና ከዚህ ወር ስድስት ቀናትን አከታትሎ ቢፆም ወይም ነጣጥሎ ቢፆም መፆሙ አጅሩን (ምንዳውን) ሊያስገኝ መቻሉንና ችግርም እንደማይኖረው ዶ/ር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ በፈትዋቸው ገልጸዋል።

ጠቃሚ ነጥቦች

1. አንዳንድ ሰዎች የሸዋል ስድስቱን ቀን የፆመና አንዴ የጀመረ ሰው በየአመቱ መፆሙ ግድ ይሆንበታል ብለው የሚያስቡ አሉ። ይህ ትክክለኛ አመለካከት አይደለም። አንድ ሰው ቢፈልግ መፆም ቢሻው ደግሞ መተው ይችላል። ይህን አመት ቢያፈጥርና ቀጥሎ ያለውን አመት ቢፆም ችግር የለውም። በየአመቱ መፆም ግድ አይደለም።

2. አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አንድ ሰው ከረመዷን በኋላ የሸዋልን ፆም በቀጥታ የጀመረ እንደሆነ ስድስቱን መሙላቱ የግድ ነው፤ ለችግር እንኳን ቢሆን ማቋረጥ የለበትም ይላሉ። ይህም ትክክል አይደለም። የሱና ፆሞችን የሚፆም ሰው ምርጫው በራሱ እጅ ነው። ፆሙን በየትኛውም ሁኔታና ጊዜ ባሻው ሰዓት ማቋረጥ ይችላል። ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል፡-

الصائم المتطوع أمير نفسه إن شاء صام وإن شاء أفطر

“የሱና ፆም የሚፆም ሰው የራሱ አዛዥ ነው። ቢፈልግ መፆም ቢፈልግ ደግሞ ማፍጠር ይችላል።” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)

3. የሸዋልን ፆም መፆም የፈለገ ሰው ከለሊቱ ኒያውን /ለመፆም ሀሣቡን/ ማሣደር ይኖርበታል። ለተወሠነ ጊዜ የሚፈፀም የተወሠኑ ቀናት የተለየ ምንዳ ያለው ፆም ነውና እንደሌሎች የሱና ፆሞች መታየት የለበትም።

4. የረመዷን ፆም ቀዷ ያለበት ሰው መጀመሪያ እነኚህን ቀዷውን ከፆመ በኋላ ነው ስድስቱን የሸዋል ቀን ፆም መፆም ያለበት። የረመዷን ወር ፆም ግዴታ የሸዋል ፆም ደግሞ ሱና በመሆኑ ግዴታው ከሱና መቀደም አለበት። ሆኖም ግን ጥያቄው በዑለማኦች መካከል ልዩነት ማስነሣቱ አልቀረም።

5. ስድስቱን የሸዋል ቀናት ለመፆም መፍጠኑ ተወዳጅ ነገር ነው። የሸዋል ቀን ፆም የሚጀምረው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ነው። የመጀመሪያው ቀን ዒድ ነውና። ወደ መሃል አሊያም መጨረሻ አካባቢ አድርጎ መፆምም ችግር የለውም።

የሸወል ፆም ሚስጢርና የተደነገገለት ዓላማ

1. አንድ ሰው ስድስቱን የሸዋል ቀን ፆም መፆሙ የአመት ፆም እንዲሆንለት ያግዘዋል። እሷ ማሟያ ናትና።

2. የሸዋልን እና የሸዕባንን ፆም ከሰላት በፊት እና በኋላ እንደሚሰገዱ ሱና ሰላቶች አድርገን መውሰድ እንችላለን። ይህም በግዴታው ላይ ክፍተት እና ጉድለት ካለ ለሟሟያነት ይጠቅማል። የቂያማ ቀን አንድ ሰው መልካም ሥራ የጎደለው እንደሆነ ከሱናዎቹ ነው የሚሟላለት። አብዛኞቻችን በፆማችን ክፍተት እና የጉድለት ችግር አያጣንም። ስለዚህም ይህን ለመጠገን እና ለማሟላት የሚጠቅሙን ሥራዎች ያስፈልጉናል።

3. የረመዷን ወር ፆም ያለፈውን ሀጢኣታችንን ያስምርልናል /እንዲማርልን ምክንያት ይሆናል/። ከረመዷን ፍፃሜ በኋላ ደግሞ ፆምን መቀጠል እነኚህን ከአላህ የተቸሩንን ታላላቅ ፀጋዎች እንደማመስገን ይቆጠራል። ወንጀልን ከመማር በላይ ምን ፀጋ አለና!

4. አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ባሮቹ እሱን በማውሣትና ሥሙን ግልፅ እና ከፍ በማድረግ በመሣሰሉት ፀጋውን እናመስግን ዘንድ አዟል። እንዲህ በማለት

وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّهَ عَلَىٰ مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ

“ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)።” (አል-በቀራ 2፤ 185)

ለረመዷን አድርሦ እንድንፆም ስላቻልን፣ ለምህረት ወርም ስላበቃን አላህን በእጅጉ ልናመሰግነው ይገባል። ስለዚህ የረመዷንን ወር ፆም ስንጨርስ ለዚህ ችሮታው ውለታ ፆም በመፆም አላህ ማመስገን ይኖርብናል።

5. አንድ የአላህ ባሪያ በረመዷን ውስጥ ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ይቃረብባቸው የነበሩ የአምልኮ ሥራዎች በረመዷን መውጣት የሚቋረጡ አይደሉም። ባሪያው በህይወት እስካለ ድረስ ይኖራሉ። ከፆም ካፈጠረ በኋላ ወደ ፆም የሚመለስ ሰው አሁንም አላህ ወደሚወደው ነገር መመለስ የሚችልና የማይሠለች መሆኑን እንዲሁም ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አድርግ ተብሎ ትእዛዝ የተሠጠው እንደሆነ ሁሌም ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያመላክታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here