ዘካቱልፊጥር

1
28428

ብዙ ሙስሊሞች ስለሚሰሯቸው የአምልኮ ተግባራት በቂ ግንዛቤ የላቸውም። በተለይም ዘካቱልፊጥርን የመሠሉ በአመት አንዴ የሚከሠቱ አምልኮዎች በአግባቡ ሲተገበሩ አይስተዋልም። በመሆኑም ይችን ትንሽ ፅሁፍ ትጠቅማለች ብለን ፅፈናታል።

ዘካቱልፊጥር ምንድን ነው?

ዘካቱልፊጥር የረመዳን ፆም መገባደጃ ላይ የሚሠጥ ሶደቃ (ምፅዋት) ነው። በነፍስ ወከፍ እያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። “ሰደቀቱል-ፊጥር”፣ “ሰደቀቱ ረመዳን” እና “ዘካቱል-በደን” ተብሎም ይጠራል- ዘካቱልፊጥር።

መች ተደነገገ? አስፈላጊነቱስ?

ዘካቱልፊጥር ከሒጅራ በኋላ ሁለተኛው አመት ላይ ተደነገገ። እንደ አብዝሀ ዑለሞች እምነት ዘካቱልፊጥር ግዴታ (ዋጂብ) ነው። ጥቂቶች የጠበቀ ሱና (ሱና ሙአከዳ) እንጂ ግዴታ አይደለም የሚል አቋም አላቸው። ግዴታ ለመሆኑ የሚቀርቡ መረጃዎች በርካታ ናቸው። ከነርሱ መሀል ጥቂቶቹን እናንሳ። በቅድሚያ ከቁርአን፡-

وَالَّذِينَ فِي أَمْوَالِهِمْ حَقٌّ مَّعْلُومٌ

لِّلسَّائِلِ وَالْمَحْرُومِ

“እነዚያም በገንዘቦቻቸው ላይ የታወቀ መብት ያለባቸው የኾኑት። ለለማኝ ከልመና ለሚከለከልም (መብት ያለባቸው የኾኑት)።” (አል-መዓሪጅ 70፤ 24-25)

ከሐዲስ ደግሞ ይኸኛውን እንይ፡- ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ እንደተዘገበው

فَرَضَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم زَكَاةَ الْفِطْرِ؛ طُهْرَةً لِلصَّائِمِ مِنَ اللَّغْوِ وَالرَّفَثِ، وَطُعْمَةً لِلْمَسَاكِينِ، مَنْ أَدَّاهَا قَبْلَ الصَّلاةِ فَهِيَ زَكَاةٌ مَقْبُولَةٌ، وَمَنْ أَدَّاهَا بَعْدَ الصَّلاةِ فَهِيَ صَدَقَةٌ مِنَ الصَّدَقَاتِ

“ዘካቱልፊጥር ፆመኛ ከአልባሌ ንግግርና ከረፈስ (የወሲብ ወሬዎች) እንዲፀዳበትና ለድሆች ምግብ እንዲሆን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ደንግገውታል። ከሰላት በፊት የሠጠ ሰው ተቀባይነት አለው። ከሰላት በኋላ የሠጠ ሰው ግን እንደማንኛውም ሰደቃ ትሆንለታለች።” (አቡ ዳዉድና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል፤ ሃኪም ሀዲሱን በቡኻሪ መስፈርት ሶሂህ ብለውታል)

የፊጥር ዘካ የፆመኞችን ፆም ይጠግናል። በሠላሳው የፆም ቀናት ወቅት ከተናገራቸው መጥፎ ንግግሮች፣ ከአጓጉል ቀልዶች ማበሻ በመሆን ፆሙን እንደማሟያና መጠገኛ ሆኖ ፅዱ እና ንፁህ ያደርገዋል። ከዚህም ሌላ ዘካተልፊጥር በውስጡ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ጥቅም ይዟል። ድሆችና ችግረኞች በተባረከው የዒድ ቀን ለልመና እንዳይሠማሩና የሰውን እጅ ከማየት ተብቃቅተው ተደስተው እንዲውሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ማን ላይ ነው ግዴታ የሚሆነው? ምን ያህል ነው መጠኑ?

ከኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው፡-

فَرَضَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم زَكَاةَ الْفِطْرِ صَاعًا مِنْ تَمْرٍ أَوْ صَاعًا مِنْ شَعِيرٍ، عَلَى الْعَبْدِ وَالْحُرِّ، وَالذَّكَرِ وَالأُنْثَى، وَالصَّغِيرِ وَالْكَبِيرِ، مِنْ الْمُسْلِمِينَ، وَأَمَرَ بِهَا أَنْ تُؤَدَّى قَبْلَ خُرُوجِ النَّاسِ إِلَى الصَّلاةِ

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) -ባሪያና ጨዋን፣ ወንድና ሴትን፣ ህፃንና አዋቂን ሳይለዩ- ዘካቱል-ፊጥርን በማንኛውም ሙስሊም ላይ ግዴታ አድርገዋል። ዘካው የሚሠጠው አንድ ቁና ተምር ወይም አንድ ቁና ገብስ ነው። ሰዎች ለሰላት ወደ መስገጃ ቦታ ከመውጣታቸው በፊት ዘካው እንዲሰጥም አዘዋል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህ ሐዲስ የረመዳንን ፆም ያጠናቀቀ ሙስሊም በዒዱ ቀን ምን እንደሚጠበቅበት ያስተምራል። ፆሙን በትጋት የጨረሰና የአላህን ሽልማት የሚጠባበቅ ሙስሊም ዘካውን እስካላወጣ ድረስ ፆሙ በሠማይና በምድር መሀል ተንጠልጥሏል። ስለዚህ ለራሱና ሊቀልባቸው ግዴታ ለሚሆንበት ሠዎች (ሚስት፣ ልጅ፣ ወላጆች…) እድሜና ፆታ ሳይለይ ዘካቱልፊጥር ሊያወጣላቸው ይገባል። ዘካውን ልቡ ዘና ብሎና ነፍሱ ተደስታ ማውጣት አለበት።

የዘካው መጠን ትንሽ ነው። አንድ ቁና (ሷዕ) ለአንድ ሰው ብቻ። አንድ ሷዕ ግምቱ 2.25 ኪ.ግ. (ሁለት ኪሎ ግራም ከሩብ) ተብሏል። እህሉ አብዝሀ የሀገሩ ሰዎች እንደቀለብነት ከሚጠቀሙበት አይነት ይሁን። ሙስሊም ሆኖ የረመዳን አንዲት አፍታን ያገኘ ሠው ሁሉ እዚህ ግዴታ ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ ከዒድ ለሊት (ሠላሳኛው ቀን ፀሀይ ከመጥለቁ) በፊት ለተወለደ ህፃን ሳይቀር ዘካቱልፊጥር ሊወጣለት ይገባል። ዘካው ወንድና ሴትን ጨዋና ባሪያንም አይለይም። ግዴታውን የሚሸከመው የራሱንና ወጪያቸውን ሸፍኖ ሊያስተዳድራቸው ግዴታ የሚሆንበትን ሠዎች የሃያ አራት ሠዐት ቀለብ ችሎ ትርፍ ያለው ሰው ብቻ ነው። ሃብት የሌለው ደሃ ሳይቀር ለራሱና ለቤተሰቡ የዒድ ለሊትና ቀኑን የሚበላው ቀለብ ካለው ዘካቱልፊጥር እንዲያወጣ ይገደዳል። በዚህ የአምልኮ ተግባር ኡመቱ ሁሉ የመስጠት ባህሉን ያዳብራል። የቸርነት ባህሪን ያካብታል። የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህሉም በሚያምርና በሚያስደንቅ ሁኔታ ይፋ ይሆናል።

ዘካተልፊጥር የሚሠጠው መች ነው?

ከላይ በተጠቀሰው ሀዲስ እንደተገለፀው የዘካተልፊጥር የማውጫ ጊዜ በኢድ ቀን ሰዎች ለሰላት ወደ መስገጃ ቦታ ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ነው። ይህ ነቢያዊ ፈለግ በመሆኑ በታዘዝነው መሠረት መሥራቱ ተገቢ ነው። ከሰላት በኋላ እስካለው ጊዜ ድረስ ያዘገየ ሰው ወንጀለኛ ነው። ቢያወጣም አጅሩ እንደ ዘካትልፊጥር አይመዘገብለትም። አለፈኝ ብሎ ቀዷ አለማውጣትም የተውበቱን ምሉእነት ስለሚያጓድል ከኃጢያተኝነት አያድንም። ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ የተዘገበው ሀዲስ እንዲህ ይላል፡-

فَرَضَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم زَكَاةَ الْفِطْرِ؛ طُهْرَةً لِلصَّائِمِ مِنَ اللَّغْوِ وَالرَّفَثِ، وَطُعْمَةً لِلْمَسَاكِينِ، مَنْ أَدَّاهَا قَبْلَ الصَّلاةِ فَهِيَ زَكَاةٌ مَقْبُولَةٌ، وَمَنْ أَدَّاهَا بَعْدَ الصَّلاةِ فَهِيَ صَدَقَةٌ مِنَ الصَّدَقَاتِ

“ዘካቱልፊጥርን ፆመኛ ከአልባሌ ንግግርና ከረፈስ (የወሲብ ወሬዎች) እንዲፀዳበትና ለድሆች ምግብ እንዲሆን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ደንግገውታል። ከሰላት በፊት የሠጠ ሰው ተቀባይነት አለው። ከሰላት በኋላ የሠጠ ሰው ግን እንደማንኛውም ሰደቃ ይሆንለታል።” (አቡ ዳዉድና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል፤ ሃኪም ሀዲሱን በቡኻሪ መስፈርት ሶሂህ ብለውታል)

የዚህን ሀዲስ የወል ትርጉም የያዙ አንዳንድ ዑለሞች የሶላት ሰዓት ያለፈበት ሠው የዘካቱልፊጥር ጊዜው ስላለፈ ቀዷ ማውጣት አያስፈልገውም ይላሉ። ሌሎች አብዝሀ ዑለሞች ግን ቀዷ ማውጣት ግዴታ መሆኑን ያምናሉ። ከሶላት ማዘግየት ኃጢያት ነው። ስለዚህ ቀዷ ማውጣቱ ከኃጢያቱ ተውበት ሲያደርግ ማሟላት ከሚገባው መስፈርቶች አንዱ ነው። ይላሉ።

ከዚህ የምንረዳው የዘካተልፊጥር ግዴታ በተወሠነ ጊዜ ውስጥ መሆኑን ነው። ከተጠቀሰው ጊዜ ማሳለፍ ዓላማውን ያጎደለ ተግባር ነውና መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ዘካቱልፊጥር ግዴታ የሚሆነው የዒዱ ቀን ፈጅር ላይ ነው ተብሏል። የኢብኑ ዑመር ሐዲስ ለዚህ እንደመረጃ ይቀርባል።

كُنَّا نُؤْمَرُ أَنْ نُخْرِجَهَا قَبْلَ أَنْ نَخْرُجَ إِلَى الصَّلاةِ، ثُمَّ يَقْسِمُهُ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ صلى الله عليه وسلم بَيْنَ الْمَسَاكِينِ إِذَا انْصَرَفَ، وَقَالَ: أَغْنُوهُمْ عَنِ الطَّوَافِ فِي هَذَا الْيَوْمِ

“ወደ ሰላት ከመውጣታችን በፊት እንድናወጣ እንታዘዝ ነበር። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከሶላት ሲመለሱ ለድሆች ያከፋፍሉታል። እንዲህም ይሉ ነበር ‘(ድሆች) በዚህ ቀን ውስጥ ሰዎች መሀል (ለልመና) እንዳይዞሩ አብቃቋቸው’።” (አቡ ዳዉድ ዘግበውታል፣ ኢብኑ ኹዜይማህ ሶሂህ ብለውታል።)

የዘካተልፊጥር ግዴታነት የሚፀናው የረመዷን ወር የመጨረሻው ቀን ፀሀይ ከጠለቀችበት ጀምሮ ነው ያሉም ሠዎች አሉ። ይህንንም ያሉ ዑለሞች “ለፆመኞች ማጥሪያ ትሆናለች” ከሚለው ነቢያዊ ሀዲስ በመነሣት ነው።

ለዒድ ሰላት ከመውጣት በፊት ዘካተልፊጥርን የምናወጣበት ዓላማ ችግረኞችና ድሆች ለልመና እንዳይዞሩ ለማድረግና በዚያ ቀን ተብቃቅተውና በቤታቸው ተወስነው ትኩረታቸውን በዓሉ ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ነው። ለዚህም ሲባል ቶሎ መስጠቱ ተመራጭ ሆኗል።

ዘካችንን ለማን እንስጥ?

ፉቀሃዎች ዘካቱልፊጥር የሚሠጠው የገንዘብ ዘካ (ዘካቱል-ማል) ለሚሠጣቸው ሠዎች ነው ብለው ያምናሉ። አላህም በቁርአን ውስጥ የነርሱን ማንነት ጠቅሷል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

إِنَّمَا الصَّدَقَاتُ لِلْفُقَرَاءِ وَالْمَسَاكِينِ وَالْعَامِلِينَ عَلَيْهَا وَالْمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمْ وَفِي الرِّقَابِ وَالْغَارِمِينَ وَفِي سَبِيلِ اللَّهِ وَابْنِ السَّبِيلِ ۖ فَرِيضَةً مِّنَ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌ

“ግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በእስልምና) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው። ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት። አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው።” (አት-ተውባ 9፤ 60)

በዚህ አመለካከት ላይ በመመሥረት ዘካቱልፊጥር የሚገባቸው ሠዎች ለህይወታቸው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ያልተሟሉላቸው አል-ፉቀራእ (ድሆች) እና ሚስኪኖችን፤ ልባቸው የተንጠለጠሉ ሠለምቴዎችን፤ ገንዘብ ከፍሎ ነፃ ለመሆን የተደራደረ ባርያን፤ ምርኮዎችን ለማስለቀቅ… ልንል እችላለን። እንደ ኢማሙ ሻፊዒይ ባሉ ዑለሞች እምነት ይህ አንቀፅ ላይ ለተጠቀሱት ስምንቱ ሠዎች ሁሉ ማዳረስ ያስፈልጋል።

እንደ ኢማሙ ማሊክ እና ኢማም ኢብኑ ተይሚያ አመለካከት ደግሞ ዘካቱልፊጥርን ለድሆችና ለሚስኪኖች ብቻ መስጠት ይቻላል።“ለሚስኪኖች ምግብ ናት” የሚለው ነብያዊ ንግግር የዚህን አመለካከት መሠረት አደላድሏልና እኛም ድሆችና ሚስኪኖችን ብቻ ለይቶ መሥጠት ይቻላል ብለን እምናለን።

ዘካቱልፊጥር የት ይሠጥ?

በላጩና የተሻለው ዘካን ዘካ አውጪው የኖረበትና የፆመበት ሀገር ላይ መስጠት ነው። ጉዞ ላይ በመሆኑ ረመዳንን ያለ ሀገሩ የፆመ እንደሆነ የፆመበት ቦታ ላይ መስጠት ይገባዋል (እንደ ሻፊዒያና ሐንበሊያ መዝሀብ ዑለሞች አመለካከት)። ይህን አመለካከት የሚመሠርቱት ዘካቱልፊጥር ከፆመኛው አካል ጋር እንጂ ከገንዘቡ ጋር የማይያዝ የዘካ አይነት መሆኑን በማመላከት ነው።

ዘካ አውጪው ሀገር ላይ ዘካ ሊሠጠው የሚገባው ሠው ከሌለ ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መውሰድ እንደሚቻል የሚያምኑ ብዙ የዚህ ዘመን ዑለሞችም አሉ። እንደመረጃ የሚጠቅሱት የኢማም ሰህኑንን ንግግር ነው። እንዲህ ይላሉ፡-

“ኢማም በሌላ ሀገር ላይ ችግር እንዳለ መረጃ ያለው ከሆነ የሀገሩን ዘካ ወደሌላ ሀገር መውሰድ ይችላል። ችግር ሲከሰት ችግርተኞችን ማስቀደም ግዴታ ነው። ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው። አሳልፎ አይስጠው። አይበድለው።” ይህ አመለካከት ተመራጭ መሆኑ በመረጃ ሲረጋገጥ የተሻለ መንገድ እንደሆነ እኛም እናምናለን።

በተለይም ኃብታም ሀገራት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች በሚኖሩበት ቦታ ላይ ዘካ የሚገባው ሙስሊም ካጡ ባሉበት ቦታ ያወጡት የነበረውን ዘካ ወደ ሀገራቸው እንዲልኩት እንመክራል።

ዘካተልፊጥርን አስቀድሞ ማውጣት ይቻላል?

አስቀድሞ ስለማውጣት ሁለት ፊቅህያዊ አመለካከቶች አሉ።

  • አንደኛው ዘካተልፊጥርን ከመደበኛ ዘካ ጋር በማመሳሰል ከሁለት አመት በፊትም ቢሆን እንኳ አስቀድሞ ማውጣት ይበቃል ያሉ ዑለሞች አሉ።
  • ሌሎች ዑለሞች ደግሞ በረመዳን ውስጥ ብቻ እንጂ ከረመዳን በፊት ማውጣት አይቻልም ብለው ያምናሉ። ምክኒያቱም ዘካቱልፊጥር ፆምን ከመፆምና ከመፍታት ጋር ተያያዥነት ያለው ዘካ ነው። ስለዚህ ከፆም ቀድሞ መስጠት አይፈቀድም።

ግዴታ ይሆንበታል ካልንበት ወቅት (ከዒድ ለሊት) ብዙ መቅደም የለበትም የሚል አቋም ያላቸው ዑለሞችም አሉ። አንድ ወይም ሁለት ቀን ተቀድሞ ቢሠጥ ግን ችግር የለም። የተጋነኑ የቀናት ልዩነቶች ግን አይፈቀድም። ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን አስቀድመው ዘካቸውን ሰጥተዋል። “ዘካቱልፊጥርን ወደ ሰላት መስገጃ ቦታ ከመውጣታችን በፊት እንድናወጣ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ያዙን ነበር።” ይሉናል። ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) ከዒድ ዕለት አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀናት አስቀድመው ይሠጡ ነበር የሚል ዘገባም አለ። እኛም ድሆች በዘካው ለመጠቀም እና ዒዳቸውን ያማረ ለማድግ በቅድሚያ ይዘጋጁበታል ብለን በማሰብ በዚህ ዘመን ከረመዳን አጋማሽ በፊት አስቀድሞ መስጠቱ የተሻለ ነው እንላለን።

ዘካቱልፊጥርን በገንዘብ ተምኖ ማውጣት እንዴት ይታያል?

ዘካቱልፊጥር ከእህል እንደሚወጣ ከዚህ በፊት አስቀድመን ተናግረናል።

በገንዘብ ተምኖ ማውጣት ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ዑለማኦችን በእጅጉ አወዛግቧል። ሁለት አብይ አመለካከቶችን ማንሳት ይቻላል።

  • ከፊል አሊሞች ዘካቱልፊጥርን በገንዘብ ተምኖ ማውጣት አይፈቀድም ባዮች ናቸው። ዘካቱልፊጥር ሐዲስ ላይ ከተዘገቡት የእህል አይነቶች ብቻ ነው ማውጣት የሚገባው የሚል አቋምም ወስደዋል። ስለዚህ ዘካቱልፊጥር የሚወጣባቸው የምግብ አይነቶች አምስት ናቸው። እነርሱም ተምር፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ዘቢብና አቂጥ (ደረቅ ወተት) ናቸው። እነዚህ አምስቱ ሐዲስ ላይ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህን ከሚመስሉ የዘካ አውጪው ሃገር ላይ ለቀለብነት ከሚውል ማንኛውም ምግብ ዘካ ማውጣት ይቻላል። እዚህ አቋም ላይ የደረሱ ዑለሞች ዘካቱልፊጥር አምልኮ ነው ስለዚህ በመለኮታዊ መረጃዎች በተጠቀሰው መልኩ ብቻ መሠራት ይኖርበታል፤ ብለው ይከራከራሉ። በመሆኑም -እንደነሱ እምነት- ሎጂካዊ ማመሳሰሎች (ቂያስ)፣ ጥቅም (መስለሐ) እና መሰል ምርምሮች አይጠቅሙንም። በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘመንም ሌሎች የገንዘብ አይነቶች ነበሩ። ነብያዊ ብይኑ ግን እህል ላይ ብቻ አተኩሯል። በመሆኑም በነኚህ ሐዲሶች ላይ በተጠቀሱት አምስቱና መሠሎቻቸው ላይ ብቻ መወሠን ግዴታ ነው ይላሉ። ስለዚህ ዘካን በእህል እንጂ በዋጋ (በገንዘብ) መስጠት አይፈቀድም ብለው ይደመድማሉ።
  • ከአምስተኛው ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ፣ ከኢማም አቡሀኒፋ እና አንዳንድ ከኢማም አህመድ እና ኢብኑ መዒን እና ሌሎችም የተነገሩ ዘገባዎች ላይ ደግሞ ዘካተልፊጥርን በዋጋ (በገንዘብ) መስጠት ይፈቀዳል የሚል ሀሳብ እናገኛለን። የዚህ ሃሳብ ባለቤቶች “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የእህል ዓይነቶቹን የጠቀሱት በወቅቱ ከምንም ነገር በላይ ለማግኘት ቅርብ ስለነበሩና ለማንኛውም ሰው ለማውጣት የማይከብዱ በመሆናቸው ነው” ብለው ይከራከራሉ። በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወቅት የእህል እጥረት ስለነበረ እህል ላይ ትኩረት ሠጥተው በመናገራቸው ሊሆን እንደሚችልም ያስረዳሉ።

ኢማም ኢብኑ አልቀይም -አላህ ይዘንላቸውና- በነቢያዊ ሀዲስ የተጠቀሱት የእህል ዓይነቶች የማይገኙበት አካባቢ የሚኖር ሰው በአካባቢው ሰዎች ለምግብነት ከሚጠቀሙት ምንም ይሁን ምን ማውጣት ይችላል የሚል አቋም አንፀባርቀዋል። ይህ አቋም የአብዛኞቹ ዑለማኦች (ጁምሁረል ዑለማ) ስምምነት ነው። ከዚህም በመነሣት የሚወጣው ጥሬ እህል ብቻ ሣይሆን ዱቄትም ሊሆን ይቻላል። ዘካተልፊጥር የተደነገገበት ዓላማ ድሆችና ችግረኞች በዒድ ቀን ውስጥ ጠግበው እንዲውሉ መሆኑ እንዳይዘነጋም አሳስበዋል። (ኢዕላሙል ሙወቂዒን)

ኢብኑልቀይም በማስከተልም፡-

وإنما نص على الأنواع المخرجة؛ لأن القوم لم يكونوا يعتادون اتخاذ الأطعمة يوم العيد، بل كان قوتهم يوم العيد كقوتهم سائر السنة، ولهذا لما كان قوتهم يوم عيد النحر من لحوم الأضاحي أمروا أن يطعموا منها القانع والمعتر، فإذا كان أهل بلد أو محلة عادتهم اتخاذ الأطعمة يوم العيد جاز لهم، بل يشرع لهم أن يواسوا المسكين من جنس أطعمتهم، فهذا محتملٌ يسوغ القول به، والله أعلم

“እነኚህ (አምስት) ነገሮች ብቻ የተነገሩት በወቅቱ ሰዎች ዓመቱን ሙሉ ያደርጉት ከነበረው ልምድ ውጭ ለዒድ አልፊጥር ቀን ብለው የሚያዘጋጁት ልዩ ምግብ ስላልነበረ ነው። የኢድ አልአድሃ ቀን የታረደውን ሥጋ ለድሃና ችግረኛ ሰዎች እንዲያበሉና እንዲያከፋፍሉ እንደታዘዘው ሁሉ በዒድ አልፊጥር ቀን ደግሞ በቅርብ ያላቸውንና በእጃቸው የሚገኘውን ነገር እንዲሠጡ ታዘዙ።” ብለዋል።

የኢብኑልቀይም ንግግር ጠንካራና አሳማኝ ነው። ማብራሪያቸውም ዘካተልፊጥር በዋናነት የተደነገገችው ድሆችን ለመርዳት መሆኑን ያመለክታል። ስለሆነም ከተጠቀሱት የእህል ዓይነቶች ውጭ (በገንዘብም ቢሆን) በሌላ ነገር ልኩን ማውጣት ይቻላል የሚል አቋም ያስይዛል። ዘካውን በገንዘብ ተምኖ የሚያወጣ ሰው ለድሀው ተጨማሪ ውለታ አድርጓል። ምክኒያቱም ገንዘብ ከምግብ ዓይነቶች የፈለገውንና ነፍሱ የሻችውን መርጦ ለመግዛት ያስችለዋል።

ከዚህም ሌላ ጥሬ እህል ብንሠጣቸው በእለቱ አስቸኳይ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እህሉን ለማስፈጨት የሚያዩትን ውጣ ውረድና ወጭም ጭምር መገመት ይኖርብናል። ከተጠቀሱት የእህል ዓይነቶች ውጭ ዘካተልፊጥርን ማውጣት አይቻልም አሊያም ፈፅሞ ሀራም ነው የምንል ከሆነ የተጠቀሱት የእህል ዓይነቶች በማይገኙባቸው ሀገራት የሚገኙ ሙስሊሞች ምን ማድረግ እንደሚገባቸውም መፍትሄ መጠቆም ይኖርብናል። ይህን ካልተቀበልን ተጨናንቆ ማጨናነቅና የሸሪዓውን ጥበብና ዓላማ አለመረዳት ነው የሚሆነው።

“ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በዘመናቸው ድርሃም እና ዲናር (የብርና የወርቅ ሳንቲሞች) ከመኖራቸው ጋር ሰዎች ዘካተልፊጥር ከነሱ እንዲያወጡ አልመከሩም።” በሚል ለሚነሳው መከራከሪያ- በወቅቱ እነዚህ ገንዘቦች ውድ እና በቁጥርም እጅግ አናሳ ስለሆኑ ዘካ አውጪዎቹ እንዳይቸገሩ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ የመከላከያ መልስ ያቀርባሉ።

እንደሚታወቀው በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን እህሎችን ሰዎች በብዛት እንደመለዋወጫ ገንዘብ ይጠቀሙ ነበር። በወቅቱ ዘካተልፊጥር በገንዘብ ማለትም በወርቅ እና ብር ሣንቲሞች ይሠጥ ተብሎ ቢወሠን እንኳ የገንዘብ የዋጋ ተመን በየጊዜው ስለሚለዋወጥ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስተውል ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሣቱ አይቀርም ነበር። ነገርግን ዘካቱልፊጥር የሰው ልጅ በእጅጉ ከሚፈልጋቸው ምግቦች ጋር መተሣሰሩ ሁኔታውን ለውዝግብ ዝግ እንዲሆን አድርጎታል። እህል እንደ ገንዘብ በዋጋ ከፍም ሆነ ዝቅ ማለት ተፅኖ የለበትም። አንድ ቁና ገብስ ሁሌም ያው አንድ ቁና ነው። አንድ ድርሃም አሊያም ዲናር ግን የዋጋ ተመኑ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ይላል። ስለዚህ መጠኑን መለካት ያዳግታል።

“ዘካቱልፊጥር አምልኮ ነው ስለዚህ በመለኮታዊ መረጃዎች በተጠቀሰው መልኩ ብቻ መሠራት ይኖርበታል።” በሚል ለሚነሳው ነጥብ- ልንዘነጋው የማይገባው ነገር ዘካቱልፊጥር እንደ ዘካቱል-ማል በመሰረቱ ምክንያታዊ (ሙዐለል) መሆኑ ነው፤ ይሀውም ድሆችን ማብቃቃትና መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት። ዘካቱልፊጥር ለምሳሌ እንደ ሰላት ረከዓዎች የአእምሮ ጣልጋ ገብነት የማይፈቀድበት የአምልኮት ተግባር አይደለም። አንድ ሰው ግዴታ ማውጣት ካለበት መጠን በላይ ጨምሮ ዘካተልፊጥርን ቢያወጣ ተቀባይነት ያገኛል ነገርግን የአንድን ፈርድ ሰላት ረከዓዎች ከተደነገገው በላይ ቢጨምር ሰላቱ ትበላሻለች።

ኢማም ኢብኑልቀዪም እንዲህ ይላሉ፡-

الزكاة تابعة لمصلحة المُعطي صاحب المال ومصلحة الفقير ونفعه، ولا يكلف أحدهما فوق طاقته حتى لا تنتفي السهولة واليسر عن الشريعة

“ዘካ የሰጪውን እና የደሀውን ጥቅም (መስለሐ) ይከተላል። ሸሪዓችን ገራገርና ቀላል ስለሆነ አንዱ ሌላውን ከአቅሙ በላይ ሊጫን አይችልም።…”

ዘካ ዓላማውን የሚያሳካና ጠቃሚ የሚሆነው በተገቢው ቦታ ላይ ሲወድቅና የሠዎችን ችግር መቅረፍ ሲችል ነው። ድሆችን የሚጠቅመው በእህል መስጠቱ ከሆነ የተሻለው እህሉን መስጠት ነው። በገንዘብ ተምኖ ገንዘቡን መስጠት ከሆነ የሚጠቅማቸው በገንዘብ መስጠቱ የተሻለ ነው።

ምንጊዜም ቢሆን ዘካ ላይ የድሆችን ፍላጎት የሚያሟሉና ጥቅማቸውን ይበልጥ በሚያስጠብቁ መንገዶች መጓዝ የተሻለ ነው። አላህ የተሻለ ያውቃል!!

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here