ኢዕቲካፍ – ህግጋቱና ሥርዓቶቹ

1
8598

ኢዕቲካፍ ማለት በተለያዩ አምልኮ ሥራዎች ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መቃረብን በማሰብ መስጅድ ውስጥ በተወሠነ መልኩ ለተወሠነ ጊዜ መቆየት ነው። ኢዕቲካፍ በእስልምና ያለ ስለመሆኑ በቁርዓን ውስጥ ተመልክቷል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በኢዕቲካፍ ወቅት ከሴቶች ጋር ሊኖረን የሚገባንን ግንኙነት ሲገልፅ እንዲህ ብሏል

وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ 
“እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ (ሴቶቻችሁን በወሲብ) አትገናኙዋቸው፡፡” (አል-በቀራህ 2፤187) (ኢብኑ ቁዳማ፣ አል-ሙግኒ)

የኢዕቲካፍ ሸሪዓዊ ድንጋጌው

ኢዕቲካፍ ሱና (ቢሰሩት የሚመነዱበት ቢተውት ደግሞ የማይቀጡበት) የአምልኮ ዓይነት ስለመሆኑ የኢስላም ሊቃውንት ተስማምተውበታል። በስለት መልክ እራሱ ላይ ግዴታ ያደረገ ሰው ሲቀር። ይህ ሰው ግን በራሱ ላይ ቃል የገባውን መሙላት ስላለበት ግዴታ (ዋጂብ) ይሆንበታል። (ነወዊ፣ አል-መጅሙዕ)

ከአቢ ሁረይራ ረዲየሏሁ ዐንሁ እንደተዘገበው፡-

كَانَ النَّبِيُّ يَعْتَكِفُ فِي كُلِّ رَمَضَانٍ عَشْرَةَ أَيَّامٍ فَلَمَّا كَانَ الْعَامُ الَّذِي قُبِضَ فِيهِ اعْتَكَفَ عِشْرِينَ يَوْمًا

“ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በያንዳንዱ የረመዷን ወር አሥር ቀን ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር። ወደ አኺራው ዓለም በሄዱበት ዓመት ደግሞ ሀያ ቀን ኢዕቲካፍ አድርገዋል።” (ቡኻሪ)

የኢዕቲካፍ የተደነገበበት ሚስጢር

ኢማም ኢብኑልቀይም ረሂመሁሏህ እንዲህ ይላሉ፡- “ቀልብ መስተካከልና ፅናት የሚያገኘው ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሎና ወደርሱ ፊቱን አዙሮ ሲጓዝ ነው። የቀልብን ደህንነት ወደ አላህ መመለስ እንጂ ሌላ ነገር አያረጋጋውም። ትርፍ ምግብ፣ መጠጥ፣ አላስፈላጊ የሆነ የበዛ የወንድ ሴት ቅልቅል፣ ትርፍ ንግግርና ትርፍ እንቅልፍ ለቀልብ ግርጠትን እንጂ አይጨምሩለትም። እነኚህ ነገሮች ቀልብን በየሸለቆው ይበታትኑታል፤ ወደ አላህ መንገድ እንዳይመጣም ያግዱታል፤ ያዳክሙታል፤ እንቅፋት ይሆኑበታል፤ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለባሮቹ ከሚያደርገው ረህመትም እንዳያገኝ ይጋርዱታል። ፆም የመደንገጉ ሚስጢርም ይህንኑ ትርፍ ንግግርና መጠጥን ለማስወገድ ነው። ከቀልብም ወደ አላህ እንዳይደርስ መሠናክል ሊሆን የሚችልበትን የስሜት እክል እንዲያነሣለት ነው።

የመደንገጉ ሚስጥር ጥቅሙ ለሰው ልጅ ነው። በዚህም አንድ የአላህ ባሪያ በዚህኛውም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ተጠቃሚ ይሆናል። አንዳችም የሚጎዳውም ሆነ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ጥቅሙ የሚያቆራርጠው ነገር አይኖርም። ቀልብ ተረጋግታና ሰክና በአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ጉዳይ እንድትቀመጥ፣ በሱ እንድትሰበሰብ፣ ከፍጥረታት ሁሉ ርቃ ወደርሱ እንድትነጠልና እንድትገነጠል በርሱም እንድትደሠት ዓላማው ያደረገው ኢዕቲካፍም መንገድ የሆነው ለዚሁ ነው። ይህም ቀልብ አላህን በማውሣትና ወደሱ ፊትን በማዞር የምታገኘውን ህያውነት ትጎናፀፍ ዘንድ ያግዛታል። አላህን በማውሣት ጭንቀቶች ሁሉ ይወገዳሉ፤ ሀሣቦች በሙሉ ይርቃሉ። እርሱ የሚወደውን ነገር በማስተንተንም ከፍጥረት ይልቅ የርሱ ወዳጅነት ይገኛል። ይህም በብቸኝነቱ የቀብር ህይወት ውስጥ አጫዋች እንዲደረግለት ይሆናል።”

ኢብኑልቀይም በጥቅሉ የኢዕቲካፍን ዓላማ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ አስቀምጠውታል።

የኢዕቲካፍ ዓይነቶች

ኢዕቲካፍ ሁለት ዓይነት አለው፡- ሱና የሆነ ኢዕቲካፍ እና ግዴታ የሆነ ኢዕቲካፍ ናቸው።

አንደኛ – ሱና ነው የሚባለው ኢዕቲካፍ አንድ ሙስሊም ወደ አላህ ለመቃረብ ምንዳውን ለመፈለግና የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ ለመከተል ብሎ በራሱ ፈቃድ የሚያደርገው ሲሆን ይህም በዋናነት በረመዷን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ የሚደረገው ነው።

ሁለተኛ – ግዴታ የሆነው ኢዕቲካፍ አንድ ሙስሊም በራሱ ላይ ግዴታ የሚያደርገው ሲሆን ይህም ጥቅል በሆነ ስለት ሊሆን ይችላል። ለምሣሌ ወላሂ ለአላህ ብዬ ኢዕቲካፍ ማድረግ አለብኝ ያለ ሰው እና አሊያም ደግሞ በስለት መልኩ ለምሣሌ አላህ በሽተኛዬን ካዳነልኝ ይህን ያህል ኢዕቲካፍ አደርጋለሁ ብሎ ቃል የገባ ሰው ኢዕቲካፍ ማድረጉ ግዴታ ሆኖበታል ማለት ነው። የዚህ ዓይነቱ ሰው ስለቱን ኢዕቲካፍ በማድረግ ቃሉን የመሙላት ግዴታ አለበት። (ሰይድ ሳቢቅ፣ ፊቅህ አስ-ሱና)

የኢዕቲካፍ መስፈርቶች (ሹሩጥ)

እስልምና፣ የትክክለኛ አዕምሮ መኖር፣ ሀይድና ኒፋስ (የወሊድ ደም) ጠሃራ መሆን የኢዕቲካፍ መስፈርቶች ናቸው።

አንደኛ- እስልምና

ኢዕቲካፍ ለማድረግ ሙስሊም መሆንን አንዱ መስፈርት ነው። ምክኒያቱም ኢዕቲካፍ እንደ ፆም ሁሉ የእምነት ቅርንጫፍ በመሆኑ ነው። ካፍር /ሙስሊም ያልሆነ ሰው/ ኢዕቲካፍ ማድረግ አይጠበቅበትም፤ ቢያደርግም እንኳን ተቀባይነት አይኖረውም።

ሁለተኛ – በአዕምሮ ጤናማ መሆን

ኢዕቲካፍ የሚያደርግ ሰው በአዕምሮ ጤነኛ መሆን አለበት። የአዕምሮ በሽተኛ ኢዕቲካፉ ትክክል አይደለም። በዚህ ሁኔታ ላይ ዒባዳ ማድረግ አይጠበቅበትምና። አእምሮ አንድን ነገር ለመሸከም መሰረታዊ ነገር ነው። ከዐሊ ኢብኑ አቢጧሊብ እንደተዘገበው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል፡-

رُفِعَ الْقَلَمُ عَنْ ثَلاَثَةٍ عَنْ النَّائِمِ حَتَّى يَسْتَيْقِظَ وَعَنْ الصَّبِيِّ حَتَّى يَحْتَلِمَ وَعَنْ الْمَجْنُونِ حَتَّى يَعْقِلَ

“ሦስት ዓይነት ሰዎች አይፃፍባቸውም። የተኛ ሰው ከእንቅልፉ እስኪነቃ፣ ህፃን ልጅ ለአቅመአደም እስኪደርስ፣ የአዕምሮ በሽተኛ ወደ ጤናማ አዕምሮ ስኪመለስ ድረስ።” (አቡ ዳውድ)
ሦስተኛ – ከሀይድና ከኒፋስ መፅዳት
ኢዕቲካፍ ማድረግ ለፈለገች እንስት ሌላው መስፈርት ከሀይድ (የወር አበባ) እና ከኒፋስ (ከወሊድ ደም) መፅዳት አለባት። (ሰይድ ሳቢቅ፣ፊቅህ አስ-ሱና)

የኢዕቲካፍ ማዕዘናት (አርካን)

ኢዕቲካፍ ሁለት ዋና ዋና ማዕዘናት አሉት። እነርሱም፡-

 • ለአላህ በመታዘዝ ወደ አላህ መቃረብን በማሰብ ኒያ ማድረግ እና
 • መስጊድ ውስጥ መቆየት ናቸው።

ኒያ (ሥራን ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ብቻ ጥርት አድርጎ ለመሥራት ማሰብ) ግዴታ ስለመሆኑ ማስረጃው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَمَا أُمِرُوا إِلَّا لِيَعْبُدُوا اللَّهَ مُخْلِصِينَ لَهُ الدِّينَ

“ሃይማኖትን ለሱ ብቻ አጥርተው አላህን ሊገዙ እንጂ አልታዘዙም።” (አል-በይነህ 98፤ 5)

ከዑመር ኢብኑ አል-ኸጧብ ረዲየሏሁ ዐንሁ በተዘገበው ሀዲስ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

إِنَّمَا الأَعْمَالُ بِالنِّيَّاتِ وَإِنَّمَا لِكُلِّ امْرِئٍ مَا نَوَى

“ስራ የተባለ ሁሉ በኒይያህ ነው። እያንዳንዱ ሰው የኒይያውን ያገኛል።” ብለዋል። (ቡኻሪ ዘግበውታል)

በመስጅድ ውስጥ መቆየት ግዴታ ስለመሆኑ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ 

“እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ (ሴቶቻችሁን በወሲብ) አትገናኙዋቸው፡፡” (አል-በቀራህ 2፤187)

ኢዕቲካፍ ከመስጅድ ውጭ የሚቻል ቢሆን ኖሮ አላህ ሴቶችን አለመቅረብን በመስጅድ ውስጥ ብቻ አይከለክልም ነበር። ስለዚህም ለኢዕቲካፍ ተገቢዎቹ ቦታዎች መስጅዶች መሆናቸውን እንረዳለን። የቁርዓን አንቀፁም ኢዕቲካፍ መስጅድ ውስጥ መሆን እንዳለበት ይገልፅናል። (ሰይድ ሳቢቅ፣ ፊቅህ አስ-ሱና)

የኢዕቲካፍ ቦታ

ኢዕቲካፍ አምስቱ የግዴታ የጀመዓ ሰላት በሚሰገድበት መስጅድ እንጂ አይበቃም። በመስጅዱ የጁሙዓ ሰላት መቆሙ ግን መስፈርት አሊያም ግዴታ አይደለም። ይህም የሆነው አላህ በአጠቃለይ መልኩ መስጅድ በመጥቀሱና ለየት ተብሎ የተጠቀሠ ሌላ ነገር ስለሌለ ነው። ሆኖም ግን ኢዕቲካፍ ጁሙዓ በሚቆምበት መስጅድ ውስጥ ቢሆን ይወደዳል። ምክኒያቱም ለኢዕቲካፍ መስጅድ የገባ ሰው ለጁሙዓ ሰላት ብሎ ወደሌላ መስጅድ መውጣት መግባት እንዳያበዛ ነው። (አል-ሙምቲዕ ሸርሁል ሙግኒ)

ኢዕቲካፍ ለሴቶች

ሴቶች በየትኛውም መስጊድ ኢዕቲካፍ ቢያደርጉ ይበቃላቸዋል። በመስጅዱ የጀማዓም ሆነ የጁምዓ ሰላት መሠገዱ መስፈርት አይደለም። ቀድሞውኑ በነሱ ላይ የጀመዓ ሰላት ግዴታ አይደለምና። በሌላ በኩል ግን ሴት ልጅ ቤቷ ኢዕቲካፍ ማድረጓ አይበቃላትም። ምክኒያቱም የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሚስቶች በመስጅድ ኢዕቲካፍ ለማድረግ ፈልገው ነቢዩ ፈቅደውላቸዋልና። ለኢዕቲካፍ የመረጡት ቦታ መስጅድ ባይሆን ኖሮ ባልፈቀዱላቸው ነበር። ከመስጊድ ይልቅ በቤት ኢዕቲካፍ ማድረጋቸው በላጭ ቢሆን ኖሮም ባመላከቷቸው ነበር። (ሻፊዒይ፡- አል-ኡም ፤ በገዊ፡- ሸርሁ ሱና ፤ ነወዊ፡- አል-መጅሙዕ)

የኢዕቲካፍ ወቅት እና የጊዜ እርዝመቱ

ኢዕቲካፍ በየትኛውም ጊዜ በቀንም ሆነ በለሊት የተፈቀደ ነው። በላጩ ኢዕቲካፍም በረመዷን የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ውስጥ የሚደረገው ሲሆን ለኢዕቲካፍ የአጭርም ሆነ የረጅም የጊዜ ገደብ የተቀመጠ ነገር የለውም። ከአንድ ለሊት ላነሠ ጊዜም ቢሆን ይቻላል። ወይንም ከቀንም ሆነ ከለሊት ጥቂት ጊዜ መስጊድ ውስጥ ኢዕቲካፍ ነይቶ መቀመጥ ይቻላል። (ኢብኑ ሩሽድ፡- አል-ሙጅተሂድ ፤ ነወዊ፡-አል-መጅሙዕ )

በረመዷን የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት የኢዕቲካፍ ሚጀምርበትና የሚያበቃበት ጊዜ

የረመዷን የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ኢዕቲካፍ የሚጀምረው የሀያኛው ቀን ረመዷን ፀሃይ ሣትጠልቅ ማለትም በረመዷን ሀያ አንደኛው ለሊት ነው። የሚያበቃውም የረመዷን ወር የመጨረሻ ቀን ፀሃይ ስትጠልቅ ነው። (ነወዊ፡- አል-መጅሙዕ )

ፆም ከኢዕቲካፍ ጋር

ኢዕቲካፍ ለማድረግ መፆም መስፈርቱ አይደለም። ያለ ፆምም ኢዕቲካፍ ይበቃል። ከኢብኑ ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁ እንደተዘገበው ዑመር የአላህን ነቢይ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ጠየቀ። በጃሂሊያ ጊዜ በመካው መስጅድ አንድ ለሊት ኢዕቲካፍ ለማድረግ ተሣልኩኝ። ነቢዩም ስለትህን ሙላ አሉት። ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል።

ለኢዕቲካፍ ፆም መስፈርት ቢሆን ኖሮ የለሊት ኢዕቲካፍ ባልበቃ ነበር። ምክኒያቱም ለሊት የሚፆም ፆም የለምና። ኢዕቲካፍ ግን በለሊትም ይቻላል። እንደ ሠላት ሁሉ ፆም ለሱ መስፈርት አይደለም። ይህ ጉዳይ በሸሪዓ የተደነገገም ነገር አይደለም። ከዑላማኦችም አልተገኘም። (ኢብን ሀጀር አል-ስቀላኒ፡- ፈትሁል ባሪ፤ ነወዊ፡- አል-መጅሙዕ)

የሴቶች ኢዕቲካፍ

ከላይ እንደጠቀስነው ሴቶች ኢዕቲካፍ ማድረግ ይበቃላቸዋል። መስፈርቱም የባሏን ፈቃድ አሊያም የወኪሏን ፈቃድ ማግኘት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢዕቲካፍ ማድረጓ ሌሎችንም ሆነ እራሷን በማይፈትን መልኩ ሲሆን ነው። ፊትና የሚፈራ ከሆነ ኢዕቲካፍ ለሷ የተከለከለ ነው። (ነወዊ፡- አል-መጅሙዕ ፤ በገዊ፡- ሸርሁ አስ-ሱና )

ከዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በመጨረሻዎቹ አሥር የረመዷን ቀናት ኢዕቲካፍ ለማድረግ ፈለጉ። ዓኢሻም አስፈቀደቻቸው። እርሣቸውም ፈቀዱላት። (ቡኻሪ)

በሌላ የዓኢሻ ዘገባ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የመጨረሻዎቹን አስር የረመዷን ቀናት እስከሞቱበት እለት ድረስ ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር። ሚስቶቻቸውም ከርሣቸው ህልፈት በኋላ ኢዕቲካፍ አደረጉ። (ቡኻሪን ሙስሊም)

የበሽታ ደም የሚፈሣት (አል-ኢስቲሃዷ) ሴት ኢዕቲካፍ

ከተለመደው ጊዜዋ በተለየ መልኩ አዘውትሮና ለረጅም ጊዜ ደም የሚፈሣት ሴት ደሟን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በመቆጣጠር ኢዕቲካፍ ማድረግ ይኖርባታል። (ሸውካኒ፡- ነይሉል አውጣር )

ከዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ እንደተዘገበው የበሽታ ደም የሚፈሣት የሆነች አንዲት ሚስታቸው ከነቢዩ ጋር ኢዕቲካፍ አደረገች። ሁምራ እና ሱፍራ (ከሀይድ ደም ውጭ የሆነ ደም) ታያለች። ጥስት ከሥሯ በማድረግ ትሰግድ ነበር ብላለች። (ቡኻሪን ሙስሊም)

በኢዕቲካፍ ወቅት ሀይድ ያጋጠማት ሴት

ሴት ልጅ በሱና ኢዕቲካፍ ላይ እያለች ሀይድ (የወር አበባ) ቢመጣባት ከመስጅድ መውጣት ግዴታ ይሆንባታል። ከጠራች በኋላ ወደ መስጅድ ባትመለስም እንኳ ምንም የለባትም። የሱና ኢዕቲካፍ ነበርና። (ማወርዲይ፡- አልሃዊ ፤ በገዊ፡- ሸርሁ አስ-ሱና )

ሴት ልጅ በሀይድ ወቅት መስጅድ በመግባቷ ጉዳይ ላይ የእስልምና ዑለማኦች በሦስት መዝሀቦች (መንገዶች) ተለያይተዋል።

 • አንደኛው መዝሀብ ሀይድ ላይ ላለች ሴት መስጊድ መግባት ፈፅሞ አይፈቀድላትም የሚለው ሲሆን ይህም አቋም በኢማም ማሊክ፣ ሻፊዒይ፣ እና አህሉል-ረኢ መዝሀብ ነው። ለዚህም ማስረጃቸው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

 إني لا أحل المسجد لحائض ولا جنب

“ሀይድ ላይ ላለች፣ እና ጀናባ ለሆነ ሰው መስጅድ አልፈቅድም።” ብለዋል የሚለው ሀዲስ ነው።

ሌላው ሀዲስ ደግሞ ለዓኢሻ ያስተላለፉት ሲሆን በዚህም ሀዲሣቸው ዓኢሻ ሀጅ ላይ እያለች ነቢዩን ሀይድ ስለመጣባት ምን ማድረግ እንዳለባት ስትጠይቃቸው

 افعلي ما يفعل الحاج غير أن لا تطوفي بالبيت

“አንድ ሀጃጅ ሰው የሚፈፅመውን ሁሉ ፈፅሚ በከዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረጉ ሲቀር” ያሏት ነው። ሀዲሱን ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

ሌላው ማስረጃ ደግሞ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሀይድ ላይ ያለች ሴት ለዒድ ሰላት እንዳትገኝ መከልከላቸው ነው። ይህንንም ሀዲስ ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

 • ሁለተኛው መዝሀብ ደግሞ ሀይድ ላይ ያለች ሴት ግድ የሆነ ጉዳይ ካላት መስጅድ መግባት ትችላለች የሚለው ሲሆን ይህንንም መንገድ ሼኽ ኢብኑ ተይሚያ ተቀብለውታል። ማስረጃውም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለጥቁሯ ሴት በመስጅድ ውስጥ ድንኳን /ግርዶ/ የተከሉበትን ሁኔታ በመጥቀስ ነው። ይህን ሀዲስ ቡኻሪ ዘግበውታል።

ይህንንም ሀዲስ ሲተነትኑ – ይህች ሴት እንደ ማንኛዋም ሴት ሁሉ ሀይድ እንደሚመጣባት ግልፅ ነው። ይህ ከመሆኑ ጋር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ግን በመስጊድ ውስጥ ድንኳን እንዲጣልላት ፈቀዱ። ይላሉ። ከዚህም በመነሳት አንዲት ሀይድ ላይ ያለች ሴት ለሙሃደራ እና ለሌላ ጠቃሚ ትምህርት ወደ መስጅድ ብትመጣ ችግር የለውም ብለዋል።

 • ሦስተኛው መዝሃብ መስጂዱን በሚፈሣት ደም የማታበላሽ ከሆነ ጥንቃቄ በማድረግ መግባት ትችላለች የሚለው ሲሆን ይህም የኢማም ማሊክ መዝሀብ እንደሆነ ተዘግቧል። ከኢማም ሻፊዒይ መዝሀብም ከሁለት አንዱ እና የኢማም አህመድ አቋም ነው። ዟሂሪያዎችም (ግልፅና የላይ በላይ ትርጉምን የሚከተሉ ሰዎች)ም ይህንኑ አቋም ተከትለዋል። ኢብኑ ሀዝምም የተቀበሉት ሲሆን ጠንካራ መስረጃቸውም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ

ناوليني الخمرة من المسجد فقالت: إني حائض قال إن حيضتك ليست في يدك

“ከመስጅድ ውስጥ ጉፍታ አቀብይኝ ሲሏት እሷም ሀይድ ላይ ነኝ አለቻቸው፡፡ እርሣቸውም ሀይድሽ ያለው በእጅሽ ላይ አይደለም አሏት።” ሀዲሱን ኢማሙ ሙስሊም ዘግበውታል።

በሌላ በኩል ደግሞ መስጅድን ሀይድ ላይ ላለች ሴትና ጀናባ ላይ ላለ ሰው አልፈቅድም የሚለው ሀዲስ ትክክለኛ ዘገባ እንዳልሆነ የሚናገሩም አሉ። የዓኢሻ ሀዲስም ቢሆን ከጠዋፍ ጉዳይ ጋር የተያያዘ እንጂ ከሰላት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለው ነው። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሀይድ ላይ ያሉ ሴቶች ከሙስሊሞች የመስገጃ ቦታ ራቅ ይበሉ ማለታቸው የዒድ ሰላት የሚሰገድበት ቦታ እንጂ መስጅድ ተፈልጎበት አይደለም ብለዋል። ሀይድ ላይ ላለች ሴት ከመስገጃ ቦታውም መራቅ አለባት የተባለው እሷ ስለማትሰግድ ሰጋጆችን እንዳታጨናንቅ ነውም ተብሏል። ወሏሁ አዕለም

ረስቶ ከመስጅድ መውጣት

አንድ ለኢዕቲካፍ ብሎ መስጅድ የገባ ሰው ረስቶ አሊም በስህተት አሊያም ተገዶ የወጣ እንደሆነ ኢዕቲካፉ ሱና ይሁን ግዴታ አይበላሽም። በጠበራኒ ዘገባ ከሰውባን ረዲየሏሁ ዐንሁ እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም፡-

رفع عن أمتي الخطأ والنسيان وما استكرهوا عليه

“ከህዝቦቼ ስህተት፣ መርሣትና፣ የተገደዱበት ነገር ተነስቷል (አይያዙበትም)።” ብለዋል። (አልባኒ- ሰሂሁል ጃሚዕ )

የሱና ኢዕቲካፍን ማቋረጥ

አንድ ሙስሊም ሱና የሆነ ኢዕቲካፍ ጀምሮ ያቋረጠ እንደሆነ ቀዷ ምትኩን መክፈል አይጠበቅበትም። እራሱ ፈልጎ ያደረገው ካልሆነ በቀር። ኢማሙ ሻፊዒይ ረሂመሁሏህ እንዲህ ይላሉ፡-

كل عمل لك أن تدخل فيه، فإذا خرجت منه فلا قضاء عليك إلا الحج والعمرة

“ሀጅና ዑምራ ሲቀር ጀምረህ የተውከው ነገር ሁሉ ምትክ መክፈል አይጠበቅብህም።” (በገዊ፡- ሸርሁ አስ-ሱና)

የኢዕቲካፍ ሥርዓቶች (አዳብ)

 1. ኢዕቲካፍ ያደረገ ሰው የሱና ሰላቶችን እና የለሊት ሰላትን፣ ቁርዓን ደጋግሞ መቅራትን ከአንድ ጊዜ በላይ ለማክተም ቢጓጋ ቢያበዛ መልካም ነው።
 2. አላህን ማውሣት ዚክር ማብዛት፣ ኢስቲግፋር ከአላህ ምህረት መጠየቅንና ዱዓእን ሰላት ዐለ ነቢን ማብዛት። ለዚህም ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የወረዱ ሀዲሦችን መጠቀም።
 3. ኢዕቲካፍ ያደረገ ሰው ከድርጊትም ሆነ ከንግግር የማይመለከተውን ነገር መራቅ ይኖርበታል።
 4. ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው ወሬ አለማብዛት ይገባዋል። ንግግሩ የበዛ ሰው ስህተቱ ይበዛልና።
 5. ከአጉል ክርክርና ከታይታ መራቅ ይኖርበታል።
 6. በመስጊድ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሰዎች ማገዝ ይኖርበታል።
 7. የተረጋጋ መሆን፣ ፀባዩን ማሣመር፣ ደምፅን ከፍ በማድረግም ሆነ በሌላ ከእንቅልፍም ሆነ ከሠላትና ከሌላ ነገር ለኢዕቲካፍ መስጊድ የገቡትን በሚረብሽ መልኩ ማስደንገጥ የለበትም።
 8. ኢዕቲካፍ ያደረገ ሰው ቦታውን መስጅድን ከጓደኞቹ ጋር ማረፊያ መነጋገሪያና መጫወቻ እንዲሁም መዘያየሪያ ማድረግ የለበትም። በወሬ ረጅም ጊዜ ማጥፋትም ሆነ ሌላ ከዒባዳ ጋር ያልተያያዘ አላስፈላጊ ድርጊት ኢዕቲካፍ የተደነገገበትን ዓላማ የሚቃረን ነው።

በኢዕቲካፍ የሚበቁ (ሙባህ) ነገሮች

ዑለማኦች ለአንድ ኢዕቲካፍ ላደረገ ሰው የሚበቁ ነገሮችን ዘርዝረዋል ፤ ከነኚህም መካከል፡-

 1. ለዒባዳ የሚነጠልበት ጎጆ ነገር መትከል ይችላል። ከዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ በረመዷን አሥሩ የመጨረሻ ቀናቶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር። ግርዶ ነገርም እጋርድላቸው ነበር። ሱብሂ ይሰግዱና ወደዚያ ይገባሉ። ብላለች። (ቡኻሪ)
 2. ለጉዳይ ከመስጅድ መውጣት፣ ምግብና ውሃ ለማምጣት አሊያም ለሽንት ቤት እና ለውዱእ ለትጥበት ብሎ መውጣት ይቻላል። የሚፈልገው ነገር መስጊድ ውስጥ የማይገኝ እንደሆነ።
 3. ኢዕቲካፍ የሚያደርግ ሰው ሚስቱን ተቀብሎ በመጋረጃው ውስጥ አብሮ ቢሆን አሊያም ሊዘይሩት የመጡትን ሰዎች ቢቀበል ችግር የለውም። ይህም ፊትና በማይቀሰቅስ መልኩ መሆን አለበት። ከዐለይ ኢብኑ ሁሴን ረዲየሏሁ ዐንሁማ እንደተዘገበው የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ባለቤት የሆነችው ሰፊያ እርሣቸው በረመዷን የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት መስጅድ ውስጥ ኢዕቲካፍ ላይ እያሉ ልትዘይራቸው እንደመጣችና ጥቂትም እንዳወራቻቸው ከዚያም ወደቤቷ እንደተመለሠች ነቢዩም ሊሸኟት እንደተነሱ ነግራዋለች። (ቡኻሪና ሙስሊም)
 4. ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው ሚስት ለማግባት ቢጠይቅ፣ ኒካህ ቢያስር አሊም መስጅድ ውስጥ በሚደረግ የኒካህ ሥነሥርዓት ላይ ቢገኝ ኢዕቲካፉ አይበላሽም። ኢዕቲካፍ መልካም ነገር የማይከለከልበት አምልኮ ነው። ጋብቻም ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከምንታዘዝባቸው ነገሮች አንዱ ዒባዳ ነው። ነገርግን ጊዜው ረዝሞ ከዋና ዓላማ ከኢዕቲካፍ የሚያዘናጋበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም። ሠላምታ መመለስም ሆነ አስነጥሦት አልሀምዱሊላህ ያለን ሰው የርሀሙከላህ ማለትም ኢዕቲካፉን የሚሸራርፍ አይደለም።
 5. ኢዕቲካፍ ያደረገ ሰው የግል ንፅህናውን መጠበቅ፣ ሽቶ መቀባትም ሆነ ጥሩ ልብስ መልበስ እንዲሁም ፀጉሩን ማበጠርና ጥፍሩን መቆረጥ ይበቃለታል። ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ እንዳለቸው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሀ ወሠለም መስጊድ ውስጥ በመሆን እራሣቸውን ወደኔ ያወጡና እኔ ሀይድ ላይ እያለሁ አበጥርላቸው ነበር። ብላለች። (ቡኻሪ)
 6. ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው የቁርዓን ትምህርት ቢያስተምር አሊያም ትምህርቱ በሚሠጥበት ቦታ ላይ ቢገኝ አሊያም ሌሎች እውቀት የሚገኝባቸውን ኪታቦች ቢያነብ በዑለማኦች ጋር ቢቀማመጥና ከነርሱ ጋር ቢማማር በአጠቃላይም ለሌሎች በሚተርፍ ዒባዳዎች ላይ ቢሠማራ አይከለከልም።
 7. ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው መስጅዱ ጣሪያ ላይ ቢወጣ ከመስጅዱ ወጥቷል አይባልም። ጣሪያው የመስጅዱ አካል ነውና።

ኢዕቲካፍን የሚያበላሹ ነገሮች

1. ያለ አንዳች ምክኒያት ከመስጊድ መውጣት

ከእናታችን ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ እንደተዘገበው

السُّنَّةُ عَلَى الْمُعْتَكِفِ أَنْ لاَ يَعُودَ مَرِيضًا وَلاَ يَشْهَدَ جَنَازَةً وَلاَ يَمَسَّ امْرَأَةً وَلاَ يُبَاشِرَهَا وَلاَ يَخْرُجَ لِحَاجَةٍ إِلاَّ لِمَا لاَ بُدَّ مِنْهُ وَلاَ اعْتِكَافَ إِلاَّ بِصَوْمٍ وَلاَ اعْتِكَافَ إِلاَّ فِي مَسْجِدٍ جَامِعٍ

“ኢዕቲካፍ ላደረገ ሰው ሱናው በሽተኛን አለመዘየር፣ ጀናዛ ሽኝት ላይ አለመገኘት፣ ሴት ልጅን አለመንካትና አለመገናኘት፣ የግድ ለሆነ ነገር እንጂ ከመስጊድ አለመውጣት ነው። በፆም እና በመስጅድ እንጂ ኢዕቲካፍ የለም።” ሀዲሱን አቡዳውድ ዘግበውት አልባኒ ሰሂህ ብለውታል።

2. የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም

ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው ሆነ ብሎ ሚስቱን በወሲብ ቢገናኝ ኢዕቲካፉ እንደሚበላሽ ዑለማኦች ተስማምተውበታል። ኢዕቲካፉም የግዴታ ኢዕቲካፍ ካልሆነ በስተቀር ቀዷ የለበትም። ከላይ የጠቀስነው የቁርዓን አንቀፅ (አል-በቀራህ 2፤ 187) ይህንኑ ያመለክታል።

3. ከእስልምና መውጣት

ኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው ከእስልምና ወጥቶ ወደ ሌላ ሃይማኖት ቢገባ አሊያም ጨርሦውኑ አላህን የካደ እንደሆነ ኢዕቲካፉ ይበላሻል። ለዚህም ማስረጃው

وَلَقَدْ أُوحِيَ إِلَيْكَ وَإِلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكَ لَئِنْ أَشْرَكْتَ لَيَحْبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ الْخَاسِرِينَ

“ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፡፡ በእርግጥም ከከሓዲዎቹ ትኾናለህ ማለት ወደ አንተም ወደእነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል፡፡” (ዙመር 39፤ 65) የሚለው የቁርዓን አንቀፅ ነው።

4. አዕምሮ መበላሸት

ኸምር በመጠጣት፣ በአእምሮ በሽታ እና እራስን በመሣትም ኢዕቲካፍ ሊበላሽ ይችላል። ጤናማ አዕምሮ ለኢዕቲካፍ አንዱ መስፈርት ነውና።

5. ሀይድና ኒፋስ

በሀይድ እና በወሊድ ደም ምክኒያትም ኢዕቲካፍ ይፈርሳል። (ኢብኑ ቁዳማ፡- አል-ሙግኒ)

በመጨረሻም አላህ ለኢዕቲካፍ ወፍቆን እንዲቀበለን እንማጸነዋለን፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here