መበቀል እየቻሉ ይቅር ማለት
በማስከተልም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ ከዕባ ገቡ። በዳርቻዋም ተክቢራ አሠሙ። ከዚያም ወደ መቃም ኢብራሂም /የኢብራሂም መቆሚያ/ በመምጣት ቦታው ላይ ሠገዱ። የዘምዘም ውሃም ጠጡ።
በመስጅድ ውስጥም ቁጭ አሉ። ዐይኖች ሁሉ እርሣቸውንና ሰሃቦቻቸውን ለትልቅ ችግር በዳረጉ፤ ከሀገራቸው ባስወጧቸውና በወጓቸው የመካ ሙሽሪኮች ላይ ምን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ በማሰብ በፍራቻ ወደርሳቸው ትመለከታለች።
የነቢዩ ምላሽ ግን አንድ ሙስሊም ቁጣውም ሆነ ውዴታው ለስሜቱ ሣይሆን ለአላህ ብቻ መሆን እንዳለበት ትልቅ ትምህርት የሚቀሠምበት ሆኖ ተገኘ። የአላህ መልእክተኛ ዐለይህ ሠላም እንዲህ አሏቸው “እናንተ ቁረይሾች ሆይ! ምን የማደርጋችሁ ይመስላችኋል!” አሏቸው። እነርሱም “መልካም ውሣኔ ነው የምንጠብቀው። የተከበርክ ወንድማችን የተከበረው ወንድም ልጅ።” አሉ። እርሣቸውም በአንድ ቃል
اذهبوا فأنتم الطلقاء
“ሂዱ እናንተ ነፃ ናችሁ!” አሏቸው።
ከዚያም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ኹጥባ አደረጉ። በርካታ የእስልምና ህግጋትንም ግልፅ አደረጉ። ከነኚህም መካከል ሙስሊም በካፊር ምትክ እንዳይገደል፣ ሁለት የተለያየ እምነት ላይ የሚገኙ ሰዎች ውርስ እንዳይወራረሱ፣ ሴት ልጅ በእናትም በአባትም አክስቷ በሆነችው ሴት ላይ እንዳታገባ፣ ከሣሽ ማስረጃ ማቅረብ እንዳለበት መሀላም ለተከሣሽና ክሱን ለሚያስተባብል ሰው እንደሆነ፣ አንዲት ሴት ያለ ሙህሪም ከሦስት ቀን በላይ የሚያስኬድ መንገድ ጉዞ ማድረግ እንደሌለባት፣ ከሱብሂ እና ዐሰር ሰላት በኋላ ሠላት እንደሌለ፣ በዒድ አል አድሃ እና በዒድ አልፍጥር ቀን እንደማይፆም የሚሉት ይገኙበታል።
ከዚያም እንዲህ አሉ “እናንተ ቁረይሾች ሆይ! አላህ የጃሂሊያን መሃይምነትን ክፋትና በአባቶች መኮፈስን አስወግዶላችኋል። የሰው ልጆች ሁሉ ከአደም ናቸው። አደም ደግሞ ከአፈር ነው። ይህን ካሉ በኋላም የሚከተለውን የቁርዓን አንቀፅ አነበቡ።
ከዚያም ሰዎች ለአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በእስልምና ላይ ቃል መግባት ጀመሩ። በዚሁ ቀን ከሠለሙት ውስጥ ሙዓዊያ ኢብኑ አቢሱፍያን እና አቡቁሃፋ የአቡበክር አስስዲቅ አባት ይገኙበታል። የአላህ መልእክተኛ የጓደኛቸው የአቡበክር አባት በመስለሙ ምክኒያት በእጅጉ ተደሠቱ።
አንድ ሰው የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በመፍራት እየተንቀጠቀጠ ወደሣቸው መጣ። እርሳቸውም “አንተ ሰው ተረጋጋ እራስህን አታጨናንቅ። እኔ ንጉስ አይደለሁም። እኔ ከቁረይሾች የሆነችና የአንዲት ደረቅ ቂጣ የምትበላ ሴት ልጅ ነኝ።” አሉት።
በተገኙበት እንዲገደሉ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የፈረዱባቸው ሰዎች ምድር ከነስፋቷ ጠበበችባቸው። ከመካከላቸውም የአላህ ውሣኔ ተላልፎበት ቅጣቱ ተፈፃሚ ሆኖበት የተገደለ አለ። የአላህ እዝነትና ጠበቃ ደርሦለትም የሠለመም አለ። ከነሱ መካከል የሆነው ዐብዱላህ ኢብኑ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ሰርህ በጥቢ ወንድሙ ከሆነው ዑስማን ኢብኑ ዐፋን ዘንድ ተጠጋ። ከሰዎች ጋር እርቅ እንዲያወርድለትም ዑስማንን ጠየቀ። ዑስማንም ጊዜ እስኪያልፍና ሰዎችም እስኪረጋጉ ድረስ ደበቀውና ወደነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘንድ ይዞት መጣ። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! የደህንነት ዋስትና ሠጥቸዋለውና ቃልኪዳንም ይስጡት አላቸው።” ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በተደጋጋሚ ፊታቸውን ካዞሩ በኋላ በመጨረሻም ቃልኪዳኑን ተቀበሉ። ዑስማን እና ዐብዱላህ ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘንድ በወጡ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ዐለይህ ሰላም “ዞር ያልኩት እኮ አንዳችሁ ተነስታችሁ አንገቱን እንድትመቱ ነበር።” አሏቸው። እነሱም “አያመላክቱንም ነበር ታዲያ!” አሏቸው። እርሣቸውም “አንድ ነቢይ ሰራቂ ዐይን ሊኖረው አይገባም።” አሏቸው።
ሌላው ተፈላጊ ዒክሪማህ ኢብኑ አቢጀህል ደግሞ ሀገር ጥሎ ሸሸ። የአጎቱ ልጅ የሆነችው ሚስቱ ኡሙ ሀኪም ቢንት አልሃሪስ ቢን ሂሻምም ከኋላው ተከተለቸው። እሷ ከመካ መከፈት አስቀድማ ነበር የሠለመችው። ከአላህ መልእእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የደህንነት ዋስትናን በመቀበል እሱ ወደ ባህር ዳርቻ ርቆ በመጓዝ ላይ እያለ ደረሠችበትና “እጅግ መልካምና በላጭ ከሆነ ሰው ዘንድ ነው ወዳንተ የመጣሁት። ባይሆን እራስህን አታጥፋ። ላንተ የደህንነት ዋስትና ተቀብያለሁ።” አለችው። እሱም ሀሣቡን ሠርዞ ወደኋላው ተመለሠ። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ባዩት ጊዜ ከተቀመጡበት ፈጥነው በመነሣት “ስደተኛና ሙስሊም ሆኖ ወደኛ የመጣሀው ሆይ! እንኳን በደህና መጣህ!” አሉት። ከዚያም ዒክሪማህ እስልምናን ተቀበለ። ለርሳቸው ያሣየውን ጠላትነት ሁሉ እንዲምሩትና ይቅር እንዲሉት የአላህን መልእክተኛ ጠየቀ። እርሣቸውም ምህረት አደረጉለት። ከዚያ በኋላ ከምርጥና ለእስልምና በእጅጉ ከሚቆረቆሩ ሙስሊሞች መካከል ለመሆን ቻለ።
ሀባር ኢብኑ አል-አስወድ ግን ሸሸ። የት እንደገባም አልታወቀም። የአላህ መልእክተኛ ጁዕራነህ ሲደርሱ ግን ሰልሞ ወደርሣቸው መጣ። እንዲህም አላቸው፡- “ከአንቱ ሸሽቼ ወደ ገጠር ነዋሪዎች ልኮበልል ነበር። ነገርግን ሰውን እንደሚያቀርቡ፣ ዝምድናን እንደሚቀጥሉ፣ ያጠፋብዎትን ይቅር እንደሚሉ አስታወስኩኝ። የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በአላህ የምናጋራ ሰዎች ነበርን። በእርስዎ ሰበብ አላህ ቅናቻን ሠጠን። ከጥፋት መንገድምም አዳነን። መልካም ይቅር ማለትን ይቅር ይበሉ።” አላቸው። እርሳቸውም “ይቅር ብዬሃለሁ።” አሉት።
ከመኽዙም ጎሳ የሆኑትን አልሃሪስ ኢብኑ ሂሻምን እና ዙሀይር ኢብኑ አቢ ኡመያን ደግሞ የአቡጧሊብ ልጅ የሆነችው ኡሙ ሃኒዕ አስጠጋቻቸው። የአላህ መልእክተኛም ዐለይህ ሰላም ማስጠጋቷን ተቀበሉ።
የአላህ መልእክተኛ አልሃሪስ ኢብኑ ሂሻምን ሙስሊም ሆኖ ባገኙት ጊዜ “ያንተ ዓይነቱ እስልምናን ለማወቅ መዘግየት አልነበረበትም። ወደ መንገዱ ለመራህ አላህ ምስጋን ይሁን።” አሉ። ከዚያ በኋላ ኢብኑ ሂሻም ከታላላቅ ሰሃቦች ለመሆን በቃ።
ሰፍዋን ኢብኑ ኡመያ ደግሞ ከሰው ዐይን ጠፋ። ወደ ባህር ሄዶ ነፍሱን ለማጥፋትም አሠበ። የአጎቱ ልጅ ዑመር ኢብኑ ወህብ አል-ጁመሂ መጣና “የአላህ ነቢይ ሆይ! ሰፍዋን የጎሣው አለቃ ነው። እራሱን ባህር ውስጥ ለመጣል ሸሽቷል። እርስዎ ለቀዩም ለነጩም የደህንነት ዋስትና ሠጥተዋልና ለሱም የደህንነት ዋስትና ይስጡት።” አላቸው። እርሣቸውም “የአጎትህን ልጅ ድረስበት እሱ ዋስትና ተሠጥቶታል።” አሉት። እሱም “ምልክት ይስጡኝ” አላቸው። እርሣቸውም ጥምጣማቸውን ሠጡት።
ዑመይርም ጥምጣሙን ይዞ ሄደ። ሰፍዋንንም ደርሦበት “በእናት አባቴ ይሁንብህ! የላቀ፣ እጅግ መልካም እና በላጭ ከሆነ ሰው ዘንድ ነው ወዳንተ የመጣሁት። እሱም የአጎትህ ልጅ የሆነውና የበላይነቱ የበላይነትህ፣ ክብሩ ክብርህ፣ ንግስናው ንግስናህ የሆነው ነው።” አለው። ሰፍዋንም “እኔ ለነፍሴ እፈራለሁኝ።” አለው። ዑመይርም “እሱ አንተ ከምታስበው በላይ ታጋሽ እና የተከበረ ሰው ነው።” በማለት የደህንነት ጥምጣሙን አሣየው። እሱም ወደ አላህ መልእክተኛ ሠለላሁ ዐለይህ ወሠለም ተመለሠ። “እርስዎ የደህንነት ዋስትና እንደሠጡኝ ይህ ሰው ነገረኝ” አላቸው። እርሣቸውም “እውነት ብሏል” አሉት። እሱም “ለመወሠን እንዲያስችለኝ ሁለት ወር ይስጡኝ።” አላቸው። እርሣቸውም “አራት ወር ይሁንልህ” አሉት። በመጨረሻም ሠለመ። እስልምናውም ያማረ ሆነ።
ከተፈረደባቸው መካከል ብቸኛ ሴት የሆነችው ሂንድ ቢንት ዑትባህ ደግሞ ተደበቀች። ቆይታ ግን ሠለመች።
ከዕብ ኢብኑ ዙሀይር ደግሞ ምድር ከነስፋቷ በጠበበችበትና የሚያስጠጋው አጣ። የአላህ መልእክተኛ ከመካ ወደ መዲና በተመለሱበት ወቅት ሠለመና የአላህን መልእክተኛን በማወደስም እንዲህ አለ፡- “መልእክተኛው የሚያበሩ ሰይፍ ናቸው። ከተመዘዘው የአላህ ሰይፍ የሆኑ ናቸው።”
ሃምዛን የገደለው ወህሽይ ደግሞ ሠለመና እስልምናውም ያማረ ሆነ። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ተቀበሉት። ዑትባህ እና ሙዕተብ የሚባሉ የአቡ ለሀባ ሁለት ልጆችም ወደርሣቸው በመምጣት ሠለሙ። ነቢዩም በእጅጉ ተደሠቱባቸው።
ሌላውና ከተደበቁት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሱሀይል ኢብኑ ዐምር አንዱ ሲሆን ልጁ ዐብዱላህ የደህንነት ዋስትና እንዲሠጠው ጠየቀና ነቢዩም ተቀበሉት። እንዲህም አሉ “ሱሀይል ብልህ አዕምሮ ያለው የተከበረ ሰው ነው። የሱ ዓይነቱ ሰው እስልምናን ሊያውቅ ይገባል።” አሉ። ይህ የነቢዩ ንግግር ሱሀይል ዘንድ በደረሠ ጊዜም ወላሂ ይህ ሰው ትንሽም ሆኖ ትልቅም ሆኖ ደግ ነበር። አለ። ከዚያም ሠለመ።
ለሴቶች ቃልኪዳን
ለወንዶች ቃል ኪዳን መስጠቱ ባለቀ ጊዜ ሴቶች ነቢዩን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሙባየዓ አደረጉ /በእስልምና ላይ ቃልኪዳን/ ገቡላቸው። ቃል የሚጋቡትም በአላህ ሱብሃኑ ወተዓላ ላያጋሩ፣ ላይሰርቁ፣ ዝሙት ላይፈፅሙ፣ ልጆቻቸውን ላይገድሉ፣ በእጆቻቸውም ሆነ በእግሮቻቸው ቅጥፈትን ይዘው ላይመጡ በመልካም ነገርም ባዘዟቸው ጊዜ የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሊታዘዙ ነበር።
ከዚያም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ቢላል የከዕባ ጀርባ ላይ ወጥቶ አዛን እንዲያወጣ አዘዙት። በዚህ መልኩ እስልምና በታላቁ የአላህ ቤት ጀርባ ላይ በተደረገው ታላቅ ጥሪ ከፍ አለ። ሙስሊሞች ይህን ቀን ለዚህ ለታላቅ ፀጋና ድል ያበቃቸውን አላህን የሚያመሰግኑበት የበዓል ቀን ቢያደርጉ ሊገርም አይገባም። መካን ከከፈቱ በኋላ የአላህ መልእክተኛ ዐለይህ ሠላም አሥራ ዘጠኝ ቀን ቆዩባት። ኋላም ወደ መዲና ተመለሱ። በመካ በቆዩበት ወቅትም ሠላትን አሳጥረው ይሠግዱ ነበር። በመጨረሻም ዒታብ ኢብኑ ኡሰይድን አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም የእለት ደሞዙንም አንድ ድርሃም በማሰብ ወደ መካ ተመለሱ።
የዑዛ መፍረስ
መካ በገቡ በአምስተኛው ቀን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድን ከሠላሣ ፈረሠኞች ጋር የቁረይሾች ትልቁ ጣኦት የሆነውን የዑዛን ማረፊያ ያፈርስ ዘንድ ላኩት። የዑዛ መቀመጫ በተምር ዛፍ በተከበበ አካባቢ ላይ የነበረ ሲሆን ኻሊድም እቦታው ድረስ በመሄድ አፈራረሠው።
የሱዋዕ መፍረስ
ዐምር ኢብኑ አልዓስንም የሁዘይል ጎሣ ትልቁ ጣኦት የሆነውንና ከመካ በሦስት ማይል ርቀት ላይ የሚገኘውን የሱዋዕን መናገሻ እንዲያፈርስ ላኩት። እሱም ሄዶ አፈረሠው።
የመናት መፍረስ
ሰዕድ ኢብኑ ዘይድ አል አሽሀሊንም ከሀያ ፈረሠኞች ጋር የኩለብ እና የኩዛዓ ጎሣዎች ጣኦት የሆነውንና መቀመጫው በባህር ዳርቻ አካባቢ የሚገኝ ተራራ ላይ የሆነውን መናትን ያፈርስ ዘንድ ላኩዋቸው። እነርሱም ሄደው አፈራረሱት።
የታላቁ የመካ መከፈት ዘመቻ ውጤቶች
1- ቁረይሾች ተንኮታኮቱ። ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜም ተሸነፉ። ሀይላቸውም ሙሉ በሙሉ ከሠመ። ጣኦት አምልኮ ዳግመኛ ወደ ዐረቢያ ምድር ላይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተመታ። ጦሮች ሙስሊሞችን ይወጉ ዘንድ መነሻ በማድረግ የሚጠቀሙባትና የጣኦት አምልኮ ማዕከል ሆና ስታገለግል የነበረችው መካ መከፈቷ የባዕድ አምልኮን ከሥር መመንገሉ ግልፅ ነው። በዚህም ከመካ ከሃዲያንና ባለሥልጣኖቻቸው በኩል በሙስሊሞች ላይ ይደርስ የነበረው የአመታት ጭቆናና እንግልት አከተመ። በርግጥም ረጅሙ እጃቸው ጣኦት አምልኮን ይቃወም በነበረ ሰው ላይ ሁሉ የተለቀቀ ነበር። ለዚህም ነው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “ከመካ መከፈት በኋላ ስደት የለም። ነገርግን ጅሃድ (ትግል) እና ኒያ ነው። ለጅሃድ ተነሱ በተባላችሁ ጊዜ ተነሱ።” በማለት የተናሩት። መካ እንደ መዲና ሁሉ የእስልምና ማዕከል ሆነች። ለጅሃድ እና የአላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ ቃል ከፍ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ከሷ ወጥቶ መሠደድ ክልክል ሆነ።
2- የመካ መከፈት በጃሂሊያው የጣኦት አምልኮ ዘመን ትልቅ ተፅእኖ በነበራቸው ወገኖች ላይ የቅስፈት ያህል ነበር የሆነባቸው። በመሆኑም ይመስላል ወዲያውኑ ለአዲሱ እምነት ካላቸው ጉጉት የተነሣ በራሣቸው ፈቃድ ለእስልምና እጅ ሠጡ። ለእስልምናም ረዳት፣ ጠባቂና ተጣሪ ሆነውም ቆሙ። የሙስሊሞች ሀይልና ጥንካሬ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረና እየጎለበተ መጣ።
3- የመካ መከፈት የዐረቢያን ደሴት አንድ ለማድረግም አይነተኛ ሚና ነበረው። በርካታ ሰዎችም የቁረይሾችንና የአለቆቻቸውን ፈለግ በመከተል ወደ እስልምና ለመግባት ተጣደፉ። የደካሞችና የእውነት ወዳጆች ፍራቻም ተወገደ። እየተቻኮሉ ወደ ዲኑ ከያቅጣጫው ተመሙ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ይህንኑ በማስመልከት እንዲህ አለ
“የአላህ እርዳታና (መካን) መክፈት በመጣ ጊዜ፤ ሰዎችንም ጭፍሮች እየኾኑ፤ በአላህ ሃይማኖት ውስጥ ሲገቡ ባየህ ጊዜ፤ ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው። ምሕረትንም ለምነው። እርሱ ጸጸትን በጣም ተቀባይ ነውና።” (አን-ናስ 110፤ 1-3)
የመካ መከፈት የእስልምናን መንግስት በወቅቱ በጦር ዝግጅትም ሆነ በጥንካሬ ምድር ላይ ይገኙ ከነበሩ ሀይሎች መካከል በአንድ ጊዜ ታላቅ መንግሰት እንዲሆን አደረገው። የሙስሊሙ ጦር በቁርጠኝነት በጀግንነትና ወደፊት በመገስገስ ተጋድሎው ማንም የሚዳፈረው አልነበረም። ከመካ መከፈትና እስልምናን መቀበል በኋላ ዐረቦች ከስሜትና ከጎሠኝነት የመበታተን አደጋ ተላቀው ወደ ታላቅ አንድነት መጡ። በአንድ ፍትሃዊ አመራርና እውነት በጎነትንና ፍፁም ፍትሃዊነትን በያዘው አምላካዊ መመሪያ ሥር በመሆን ወደ ልቅናና ክብር ተሸጋገሩ።
ከመካ መከፈት የምናገኛቸው አስተምህሮቶች
1- ክህደት እና ቃል ማፍረስ መጨረሻው ውርደት መሆኑን
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እና ሙስሊሞች ቃልኪዳናቸውን ጠብቀው ኖረዋል። የሚጠበቅባቸውንም ሁሉ አድርገዋል። በዚህም ያዘዛቸው ሃይማኖታቸው ነው። አላህ ሱብህነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“ቃል ኪዳንም በገባችሁ ጊዜ በአላህ ቃል ኪዳን ሙሉ።” (አን-ነህል 16፤ 91)
ከሃዲያኑ ግን ቃላቸውን አፈረሱ። አሴሩም። የተንኮልም መጨረሻ እዳው ለባለቤቱ ነውና መልሦ ቀጣቸው። ይህም የሆነው ከሙስሊሞች ጋር የገቡትን ቃልኪዳን በማፍረሣቸውና እነሱንም በመውጋታቸው ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“አላህ ከዳተኛን ውለታቢስን ሁሉ አይወድም።” (አል-ሃጅ 22፤ 38)
2- ማዘናጋትና ነገሮችን በሚስትር ማስኬድ ለድል ዓይነተኛ መሣሪያዎች ናቸው
የአላህ መልእክተኛ ሰለለሁ ዐለይህ ወሠለም ሙሽሪኮችን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከተው ለዝግጅትም ጊዜ እንዲያጡ ለማድረግ ብለው ስለ ዘመቻው ምንም እንዳይተነፍስ አሣስበው ነበር። ይህም በጠላቶችቻው ላይ ድል ያገኙ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ረድቷቸዋል።
3- ሙስሊሞች ከሁደይቢያው ስምምነት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ላይ ነበሩ
በዚህም ጦራቸው ሊበዛ ችሏል። ሀይላቸውም ሆነ ዝግጅታቸው ጠንካራ ሆኗል። በመጨረሻም ዘመቻው ቀላል ሆነላቸው። ድልንም ተጎናፀፉ። በሌላ በኩል ግን የሙሽሪኮቹ ቁጥር ቀንሦ ወደ ስሜቶቻቸው ተመልሠው ተዳክመው ነበር። በዚህም ከፍተኛ የሆነ ሽንፈት ሊደርስባቸው ችሏል።
4- ማቀድ እና መደራጀት በጠላት ልቦና ውስጥ ፍራቻ ይከታል ሀይሉንም ሽባ ያደርጋል
የአላህ መልእክተኛን ጦር የአደረጃጀትና የዝግጅት ሁኔታ ባየ ጊዜ ይህ ጦር ፈፅሞ ሊሸነፍ እንደማይችል በመገመት የመካ ሰዎች አለቃ የነበረው አቡሱፍያን ተስፋ ቆርጦ እጅ ለመስጠት ተገደደ። ይህንንም ሄዶ ለህዝቦቹ ነገራቸው። በነሱም ልቦና ውስጥ የሱ ዓይነት ስሜት ተከሠተ።
5- ሥነልቦናዊ ጥንካሬ ከድል ምሠሦዎች መካከል አንዱ ነው
ከመካ ለቀው ወደ መዲና ተሠደው የነበሩ መሃጂሮች ወደ መካ በመመለሣቸውና በአላህ ድል በእጅጉ ደስተኞች ነበሩ። ለዚህ ታላቅ ቀን ለመድረስ በእጅጉ ጓጉተዋል ተመኝተዋል። አንሷሮችም ቢሆኑ በደስታ ደረጃ ከነሱ የተናነሱ አልነበሩም። ምክኒያቱም መካ የሰዎች ሁሉ ቀልብ የምትጓጋላትና ነፍሦች ሁሉ የምትመኛት የተከበረው የአላህ ቤት የሚገኝባት ከተማ ናትና።
የቁረይሾች ሥነልቦና ግን በአንፃሩ እጅግ የተዳከመና የፈራረሠ ነበር። ዋና ዋናዎቹ መሪዎቻቸውም ሀገር ጥለው ለመኮብለልና ለነቢዩ ጦር እጅ ለመስጠት ተገደዋል። በህይወት ለመዳን ሲሉ ወደቤቶቻቸው በመግባት በሮቻቸውን ዘግተው የተቀመጡም በርካቶች ናቸው።
6- እዝነትና ርህራሄ የተዘጉ ልቦናዎችን ይከፍታሉ
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እዝነት፣ ለወንጀለኞችና አጥፊዎችም ይቅር ባይነታቸው እንዲሁም ለጠላቶቻቸው ምህረት ማድረጋቸው በተቃራኒ አቅጣጫ የሚገኙትን ሰዎች የሙሀመድን እምነት ይወዱና ይቀበሉ ዘንድ ከፍተኛ ተፅእኖ አሣድሮባቸዋል። ለዚህም ነው በርካቶች በቡድን በቡድን በመሆን ወደ አላህ ሃይማኖት በጥድፊያ ሊገቡ የቻሉት።
7- መተናነስና ከጉራ ነፃ መሆን የታላላቅ ሰዎች ባህሪ ነው
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በድል ወደ መካ ሲገቡ የታዩበት ሁኔታ የሙስሊሞችን ልብ በእጅጉ ነበር የነካው። የአላህን ምንዳ የሚፈልጉ ፍራቻው ያደረባቸውና እርሱንም ከሁሉም ነገር በላይ አስበልጠው የሚወዱ ሰዎችም ከዚህ ድርጊታቸው ታላቅ ትምህርት ቀስመዋል።
ሌላው ከነቢዩ የታየው ነገር ደግሞ አደራን ለባለቤቷ መመለሣቸው ነበር። ከዕባን ከጣኦታት እና እርኩስ ነገሮች ሁሉ ካፀዱ በኋላ የከዕባን ቁልፍ ለዑስማን ኢብኑ ጦልሃ መልሰዋል። ይህም በሰዎች ልቦና ውስጥ ያሣደረው ተፅእኖ ቀላለል አልነበረም። ጠላቶቻቸውም ከወዳጆቻቸው ለምስክርነት በመቅደም እንዲህ ለማለት እስኪበቁ ድረስ “እሱ /ሙሀመድ/ በርግጥም ዝምድናን የሚቀጥል፣ በእጅጉ ለሰው የሚያዝን፣ እጅግ የተከበረ ደግ እና ቃሉን የሚሞላ ነው።”
8- መጋረጃው ሲገለጥ ውሸት እርቃኑን ይቀራል
ጣኦታት ተሠባበሩ፡ እውነት ይፋ ሆነ፤ ውሸትም ኮሠመነ። እጅግ አደገኛ ከነበሩት ሙሽሪኮች መካከል አንዷ የነበረችው የአቡሱፍያን ሚስት ታመልክ የነበረውን ጣኦት ስትሠባብር እንዲህ እስከማለት ደርሳለች “ለዘመናት ባንተ ማጃጃልና ክፋት ውስጥ ኖረናል።”
*****