በ 8ተኛው አመተ ሂጅራ ረመዳን 20 መካ ተከፈተች፤ ከጣኦት አምልኮ ነፃ ወጥታ የኢስላም ብርሃን ፈነጠቀባት… እነሆ መካን የመክፈት ታላቁ ዘመቻ..
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ቁረይሾች እጅ እስካልሠጡ ድረስ መላው ዐረቦችም እጅ ሊሠጡ እንደማይችሉ፤ መካ ወደ እስልምና ገብታ በአላህ ሃይማኖት እስካልተዳደረች ድረስ ሌሎች ሀገራትም ሊስተካከሉና ሊገሩ እንደማይችሉ አሣምረው ያውቁ ነበር። በመሆኑም ይመስላል መዲና ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ መካን ለመክፈት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። ነገርግን ከቁረይሾች ጋር በሁደይቢያ ስምምነት ወቅት የገቡትን ቃል ኪዳን ለማክበር ሲሉ ከሀሣባቸው ታቀቡ። እርሣቸው ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ሁሉ ዓይነታ ናቸውና። ሆኖም ግን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አንድ ነገር እንዲከሠት የሻ እንደሆነ መንገዶችን ያመቻቻል፤ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችም ያስወግዳል። በመጨረሻም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ መካ ለመዝመት ምክኒያት ተፈጠረላቸው።
ነገሩ እንዲህ ነው- የኹዛዓ ጎሣዎች ከነቢዩ ጋር የበክር ጎሳዎች ደግሞ ከቁረይሾች ጋር ያጠቃቸውን ሁሉ አብረው ሊከላከሉ አሊያም ሊያጠቁ የአንደኛው ጠላት የሌላኛውን ጠላት ጠላቱ አድርጎ እንደሚስወድ፤ በዚሁ ላይም ለመተባበር የስምምነት ቃል ኪዳን ነበራቸው። በጃሂሊያ (ከእስልምና በፊት በነበረው ዘመን) በኹዛዓ እና በበክር ጎሣዎች መካከል የደም ግጭት የነበረ ሲሆን ይሀው ጉዳይ እስልምና የበላይነትን እያገኘ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ እየተባባሠ መጣ። የተኩስ ቁም ስምምነትም በመካከላቸው ተደርጎ ሣለ ከበክር ጎሳ የሆነ አንድ ሰው ከኹዛዓ ጎሣ የሆነ አንድ ሌላ ሰው በሚሰማበት ሁኔታ የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እያዜመ ያብጠለጥል ጀመር። የሚወዳቸው ታላቁ ነቢይ የተነኩበት ይህ ሰሃባ በንዴት ጡዞ ተነስቶ ሰውዬውን ደበደበው። በዚህም በሁለቱ ጎሣዎች መካከል የነበረው ውስጥ ለውስጥ ሲብሠለሠል የኖረው ጥላቻ ዳግም ክፉኛ ተቀሠቀሠ። የበክር ጎሣዎችም የከረመ ቁስላቸውን አስታወሱ። ባላንጣዎቻቸው የሆኑትን ጎሣዎች ለመውጋት ወዳጆቻቸው ከሆኑት የመካ ቁረይሾች እገዛ ፈለጉ። ቁረይሾችም በሚስጢር በስልጠና እና በሰው ሀይል ድጋፍ አደረጉላቸው። ከዚያም በክሮች ወደ ኹዛዓ ምድር አቀኑ። እነሱ በሠላም እያሉና ፈፅሞ ለጠብ ባልተዘጋጁበት ሁኔታ ደርሠውም ከሀያ በላይ ሰዎችን ገደሉባቸው።
ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ጋር የቃልኪዳን ስምምነት የነበራቸው የኹዛዓ ሰዎች የበክር ጎሳዎች እና ቁረይሾች የፈፀሙባቸውን ጥቃት ለአላህ መልእክተኛ እንዲነግር በዐምር ኢብኑ ሳሊም አልኹዛዒ የተመራ ልዑክ ላኩ። ዐምር ልዑኩን ይዞ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘንድ በደረሠና ጉዳዩንም በዝርዝር በነገሯቸው ጊዜ የአላህ መልእክተኛ “ወላሂ እራሴን ከምከላከልበት ነገር ሁሉ እናንተንም እከላከላለሁ።” በማለት ቃል ገቡ።
ቁረይሾች በበኩላቸው የፈፀሙት ድርጊት ቃልኪዳንን ማፍረስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ባደረጉት ነገር እጅጉን ተፀፀቱ። ይህንንም ጥፋታቸውን ለመካስም መሯሯጥ ጀመሩ። ስለሆነም መሪያቸውን አቡሱፍንን ቃልኪዳኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ጊዜውም እንዲራዘም በሚል ወደ መዲና ላኩት። አቡሱፍያንም አንድም ሰው እንዳልቀደመው በማሰብ መዲና ደረሠና የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ባለቤት በሆነችው ልጁ የምእመናን እናት ኡሙ ሀቢባ ዘንድ አረፈ። በአላህ መልእክተኛ ፍራሽ ላይ ለመቀመጥ በሚንደረደርበት ጊዜም የገዛ ልጁ ፍራሹን ጠቀለለችበት። “ልጄ ሆይ! ከኔ መራቅሽ ነው ወይንስ ከኔ ማራቅሽ ነው?” አላት አቡሱፍያን። እሷም “አንተ ሙሽሪክ ነጅስ ሆነህ የአላህ መልእክተኛ ፍራሽ ላይ መቀመጥ አትችልም።” አለችው። እሱም “ከኔ ዘንድ ከሄድሽ በኋላ በርግጥም መጥፎ ነገር አግኝቶሻል።” አላት።
አቡሱፍያን ፊት ከነሣችው ልጁ ዘንድ በመውጣትም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መስጅድ ውስጥ እያሉ መጣ። የመጣበትንም ጉዳይ ነገራቸው። የአላህ መልእክተኛም ዐለይህ ወሠለም “አዲስ የተፈጠረ ነገር አለን እንዴ!” አሉት።እሱም “የለም” አላቸው። የአላህ መልእክተኛም ዐለይህ ሠላም “እንግዲያውስ እኛ በስምምነታችን እና በጊዜያች ቀጠሮአችን ላይ ነን። ከዚህ የሚጨምር ነገር አይኖርም።” አሉት።
አቡሱፍያን ተነስቶ በሀሣቡ ላይ ይደግፉት ዘንድ ወደ ታላላቅ የቁረይሽ ሙሃጅሮች (ከመካ ተሰደው የመጡ ሰሃቦች) ዘንድ ሄደ። ነገርግን አንድም አጋዥ ሊያገኝ አልቻለም። ሁሉም በአንድ ደምፅ “የምናስጠጋው የአላህ መልእክተኛ ያስጠጉትን ነው።” አሉት። አቡሱፍያን አማራጭ አልነበረውም። ምንም ነገር ሣይሠራና ሣይዝ ወደ ህዝቦቹ ወደ መካ ተመለሠ። እነሱም በበኩላቸው እንደካዳቸውና እስልምናን እንደተቀበለ አስወሩበት። እሱም ይህን ወሬ ለማስተባበል ወደ ጣኦታት ፊት በመሄድ ተናዘዘ ንስሃ ገባም።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለጉዙ መሠናዳት ጀመሩ። ሰሃቦቻቸውንም እንዲዘጋጁ አዘዙ። ወዴት እንደሚሄዱ ግን ለአስስዲቅ (አቡበክር) ብቻ ነበር የነገሩት። እሱም `የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ባንተና በቁረይሾች መካከል የቃል ኪዳን ስምምነት የለምን?” በማለት ጠየቃቸው። እርሣቸውም “ነበረ ነገርግን እነርሱ ካዱ፤ ቃላቸውንም አፈረሱ።” አሉት።
በመቀጠልም የአላህ መልእክተኛ በመዲና ዙሪያ የሚገኙ የገጠር ሰዎችን ለጦርነት እንዲዘጋጁ ቀሰቀሱ። “በአላህ እና በመልእክተኛ የሚያምን ማንኛውም ሰው ረመዷንን መዲና ይምጣ።” በማለትም ጠንከር ያለ አዋጅ አስተላለፉ። ከአስለም፣ ጊፋር፣ ሙዘየናህ፣ አስጀዕ እና ጁሀይናህ ጎሣ የሆኑ በርካታ ሰዎች ወደ መዲና ተመሙ። ወሬው እንዳይሠራጭና ቁረይሾችም ሠምተው ለጦርነት እንዳይዘጋጁ በማሰብ ነቢዩ ዐለይህ ሠላም እንቅስቃሴው ሁሉ ድብቅ እንዲሆን አደረጉ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሀሳባቸው በመካ ላይ ጦርነት ማካሄድ ሳይሆን ክብሯን በማይነካ መልኩ ነዋሪዎቿ ወደ እስልምና ይገቡ ዘንድ መጣር ነው። እንዲህ በማለትም ዱዓእ አደረጉ “አላህ ሆይ! በሀገሯ እንዳለች ድንገት እስክንደርስባት ድረስ ከቁረይሾች ስለሁኔታችንና እንቅስቃሴያችን ወሬያችን ደብቅ።”
በበድር ዘመቻ ላይ ተገኝተው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሃጢብ ኢብኑ አቢ በልተዓህ በመዲና የአላህ መልእክተኛ ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልፅ አንድ ደብዳቤ በመፃፍ በአንዲት ሴት አማካይነት በፍጥነት እንዲደርስ ለመካ ቁረይሾች ላከ። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠም ይህን ሁኔታ ደረሱበት። ዐሊን፣ ዙበይርን እና ሚቅዳድን መልእክተኛዋን ሴትዮ ይፈልጉ ዘንድ ላኩ። “ረውደተ ኻኽ ምትባል ቦታ እስክትደርሱ ድረስ ሂዱ። እዚያም ስትደርሱ አንዲት ደብዳቤ የያዘች ሴት ታገኛላችሁ። እናም ተቀበሏት።” አሏቸው። ሦስቱ ሰዎች ከረግረጋማው ቦታ እስኪደርሱ ድረስ ተጓዙ። ሴቴዮዋንም አገኙና “ደብዳቤውን አውጪ!” አሏት። እሷ ግን ካደች። እነሱም “ታወጪያለሽ አለበለዚያ ልብስሽን ታወልቂያለሽ” በማለት አስፈራሯት። እሷም ወዲያውኑ ከሹሩባዋ ውስጥ አወጣች።
የአላህ መልእክተኛ መልእክተኞች ደብዳቤውን ይዘው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘንድ መጡ። ሃጢብንም አስጠርተው “ምን ሆነህ ነው ምን ነካህ ሃጢብ ሆይ!” አሉት። እሱም “የአላህ መልእተኛ ሆይ! ለመፍረድ አይቸኩሉብኝ እኔ በርግጥ ከነርሱ ባልሆንም ከቁረይሾች ጋር ስምምነት አለኝ። እዚህ ያሉና ከአንቱ ጋር ያሉ ሙሃጅሮች መካ ላይ ንብረቶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚጠብቁላቸው የቅርብ ዘመዶች አሏቸው። እኔ ግን የለኝም። ስለዚህም ይህን እንደ ውለታ ቆጥረውልኝ ዝምድናዬን እንዳይቆርጡ በማሰብ ነው እንጂ ለሌላ አይደለም። ይህን ያደረግኩት ከሃይማኖቴ ወጥቼ አለያም ከእስልምና በኋላ ኩፍርን ክህደትን ወድጄ አይደለም።” አለ። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “እውነት ነግሯችኋል።” አሉ።
ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁ ግን አላስቻለውም። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! የዚህን ሙናፊቅ አንገት ልምታ ይተውኝ!።” አለ። የአላህ መልእክተኛም “እሱ እኮ በድር ላይ የተገኘ ሰው ነው። አላህ እኮ በድር ጦርነት ላይ ለነበሩ ሰዎች ‘የሻችሁን ሥሩ እኔ ምሬያችኋለሁ’ ማለቱን አታውቅም እንዴ!” አሉት።
ይህንኑ ክስተት አስመልክቶ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የቁርኣን አንቀፅ አወረደ።
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጠላቶቼንና ጠላቶቻችሁን ወዳጆች አድርገችሁ አትያዙ። ከእውነቱ የመጣላችሁን ሃይማኖት በእርግጥ የካዱ ሲኾኑ ውዴታን ወደእነርሱ ታደርሳላችሁ። መልክተኛውንና እናንተን በአላህ በጌታችሁ ስላመናችሁ (ከመካ) ያወጣሉ። በመንገዴ ለመታገልና ውዴታዬን ለመፈለግ የወጣችሁ እንደኾናችሁ (ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው)። እኔ የምትደብቁትንና የምትገልጹትን ሁሉ የማውቅ ስኾን ወደእነርሱ በፍቅር ትመሳጠራላችሁ። ከእናንተም (ይህንን) የሚሠራ ሰው ቀጥተኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ።” (አል-ሙምተሃና 60፤ 1)
ወቅቱ የረመዷን ወር አጋማሽ ላይ ነበር። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ኢብኑ ኡም መክቱምን በመዲና ላይ አስተዳዳሪ አድርገው ከሌላው ጊዜ ሁሉ በቁጥር ግዙፍ የሆነውን ጦር በመምራት ወደ መካ ተንቀሳቀሱ። የጦሩ ብዛት አሥር ሺህ ታጋይ ነበር። አብዋእ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ እጅግ ጠላታቸው ከሆኑ ሰዎች መካከል ሁለቱን ማለትም የአጎታቸውን ልጅና የበድር ዘማቹ የዑበይዳ ኢብኑ አልሃሪስ ወንድም የሆነውን አቡሱፍያን ኢብኑ አልሃሪስን እና አማቻቸውንና የሚስታቸው የኡሙ ሠለማ ወንድም የሆነውን ዐብዱላህ ኢብኑ ኡመያ ኢብኑ አልሙጊራን አገኙ። ሰዎቹ ለመስለም ነበር የሚሄዱት። የአላህ መልክተኛም ተቀበሏቸው። በእጅጉም ተደሠቱባቸው። እንዲህም አሏቸው
“ዛሬ በናንተ ላይ ወቀሳ የለባችሁም። አላህ ለእናንተ ይምራል። እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው አላቸው።” (ዩሱፍ 12፤ 92)
ከዲድ ከሚባል ቦታ ሲደርሱ ፆሙ በሙስሊሞች ላይ መክበዱን አስተዋሉ። በመሆኑም እንዲያፈጥሩ አዘዟቸው። እርሣቸውም አፈጠሩ። እንዲሁም በጉዞአቸው መንገድ ላይ ዐባስ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ አጠቃላይ ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ መዲና ሲሠደድ አገኙት። እርሣቸውም ወደ መካ እንዲመለስና ቤተሰቦቹን ግን ወደ መዲና እንዲልክ አዘዙት። መረ ዘህራን የሚባል ቦታ ሲደርሱ በምሽቱ አሥር ሺህ እሣት እንዲቀጣጠል አዘዙ።
ቁረይሾች ሙሀመድ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጦር ይዞ ወዳልታወቀ አቅጣጫ እየተንቀሣቀሠ መሆኑን ወሬ ደረሣቸው። ስለሆነም አቡሱፍያን ኢብኑ ሀርብን፣ ሀኪም ኢብኑ ሂዛምን እና በዲል ኢብኑ ወረቃእን ወሬውን ያጣሩ ዘንድ ላኳቸው። እነሱም መረ ዘህራን በደረሱ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው እሣት ተቀጣጥሎ አዩ። አቡሱፍያንም በብዛቱ ተገርሞ “ይህ የዐረፋን እሣት ነው የሚመስለው።” አለ። በዲል ደግሞ “የበኒ ዐምር ጎሣ እሣት ያህል ነው።” አለ። “በኑ ዐምርማ በቁጥር ከዚህ ያነሱ ናቸው።” አለ አቡሱፍያን።
እነ አቡሱፍያንን የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሆኑ ሰዎች አዩኣቸውና ደረሱባቸው። ይዘውም ወደ አላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አመጧቸው። አቡ ሱፍያን ሠለመ። ሲሄዱም ለዐባስ እንዲህ አሉት። “ሙስሊሞች ሁሉ ያዩት ዘንድ አቡሱፍያንን ተራራው ጫፍ ላይ እሠረው።” ዐባስም ወስዶ አሠረው። የተለያዩ ጎሣዎችም በቡድን በቡድን እየሆኑ በአቡሱፍያን በኩል ያልፉ ጀመር። እሱም የትኛዋ ጎሣ እንደሆነች ይጠይቃል። ሲመልሱለትም “እኔና እርሷን ምን አገናኘን!።” ይላል። በመጨረሻም ከአንሷሮች የሆነችውና ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳ ባንዲራዋን የሚሸከመው ጎሣ ስታልፍ ሰዕድ ለአቡሱፍያን “አቡሱፍያን ሆይ! ዛሬ የእርድ ቀን ነው። ከዕባም ሀላል ትደረጋለች። (በውስጧ ሰው አለመግደሉ ይቀራል)” አለው። አቡሱፍያንም “ዐባስ ሆይ! ምንኛ የጥፋት ቀን ነው!” አለ።
በመጨረሻም አንዲት ከሁሉም አነስ ያለችና ሰሃቦች እና የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሚገኙባት ቡድን መጣች። ባንዲራ ተሸካሚዋ ዙበይር ኢብኑ አልዐዋም ሲሆን እሱም ሰዕድ ያለውን ነገር ለአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ነገራቸው። እርሣቸውም “ሰዕድ ዋሸ። ዛሬ አላህ ለከዕባ ታላቅ ክብር የሚሰጥበትና ከዕባ የምትለብስበት ቀን ነው።” አሉ። ከዚያም ባንዲራቸው ሁጁን (የተራራ) ላይ እንድትተከል አደረጉ።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድን በታችኛው የመካ ክፍል በከድይ ኮረብታ በኩል እንዲገባ አዘዙና እርሣቸው ደግሞ በላይኛው ማለትም በከዳእ በኩል ገቡ። የርሣቸው ወገን የሆነ ተጣሪም እንዲህ በማለት ተጣራ። “ወደቤቱ የገባና ቤቱን የዘጋ ሰው እርሱ ሰላም ነው አይነካም። ወደ መስጊድ የገባ እርሱም ሰላም ነው አይነካም። ወደ አቡሱፍያን ቤት የገባም እርሱ ሰላም ነው አይነካም።” አለ።
ይህ በርግጥም ከአላህ መልእክተኛ የሆነ ትልቅ ስጦታ ነው። ከመካ ሰዎች መካከል ግን በሙስሊሞች ላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ ወንጀል የፈፀሙትንና እስልምናን እና ማህበረሰቡን ትልቅ ችግር ውስጥ የከቱትን ጥቂት ሰዎች ለዩ። እነኚህ ሰዎች በከዕባ ሥር ተደብቀው የተገኙ ቢሆንም እንኳ ደማቸው እንዲፈስ አዘዙ። ከነኚህ ሰዎች መካከል ዐብዱላህ ኢብኑ ሰዕድ ኢብኑ አቢ አስሰርህ ሰልሞ በነበረበት ወቅት ለአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የወሕይ መልአክቶችን ሲፅፍ የነበረና ኋላ ላይ ከእስልምና በመውጣት በነቢዩ ላይ ውሸትን ሲቀጣጥፍ የነበረ ሰው ነው። በወቅቱ እንዲህ እያለ ያላግጥ ነበር። “ሙሀመድ ‘ዐሊሙን ሀኪም’ ብዬ እንድፅፍ ሲነግረኝ እኔ ደግሞ ‘ገፉሩን ረሂም’ ብዬ እፅፍ ነበር።”
ሌሎቹ ደግሞ ዒክሪማህ ኢብኑ አቢጀህል፣ ሰፍዋን ኢብኑ ኡመያ፣ ሀባር ኢብኑ አል አስወድ፣ አልሃሪስ ኢብኑ ሂሻም፣ ዙሀይር ኢብኑ አቢ ኡመያ፣ ከዕብ ኢብኑ ዙበይር፣ እና የሃምዛ ገዳይ የነበረው ወህሽይ ኢብኑ ሀርብ ሲሆኑ እንዲሁም ሃምዛን ያሰገድለችውን የአቡ ሱፍያን ባለቤት ሂንድ ቢንት አቢ ሱፍያንና ሌሎችም ጥቂቶች ነበሩ። ከነኚህ በቀር ሌላ ማንም ሰው እንዳይገደል በጥብቅ አሳሰቡ።
የኻሊድ ኢብኑ አል ወሊድ ጦር ወደ መካ ሲገባ ከቁረይሽ የተወሠነ የመከላከል ተቃውሞ ገጠመው። ኻሊድም ተዋጋቸውና ከነርሱ ሀያ አራት ያህሉን ሲገድል ከርሱ ወገን ደግሞ ሁለት ሙስሊሞች ሞቱበት። በመጨረሻም በዚሁ አቅጣጫ ድል አድርጎ ገባ።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሚመሩት ጦር ደግሞ ይህ ነው የሚባል መከላከል አላጋጠመውም። ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በግመላቸው ላይ ሆነው ግንባራቸው ከኮርቻው ጋር የተጣበቀ በሚመስል መልኩ እጅግ በመተናነስና በዚህ ታላቅ ፀጋ አላህን በማመስገን አጎንብሰው መካ ገቡ። ኡሣማ ኢብኑ ዘይድ ከኋላቸው ተፈናጦ የነበረ ሲሆን ቀኑም ጁሙዓ ጠዋት ረመዷን ሀያኛው ቀን ላይ ያመለክት ነበር። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በዚሁ የመተናነስ ሁኔታ ላይ ሆነው ባንዲራቸው እስከተተከለችበት ጀሁን ድረስ ተጓዙ። ቦታውም ላይ የምእመናን እናት ኡሙ ሰለማ እና መይሙና ያረፉበት ጎጆ ተጣለላቸው። ጥቂት ካረፉ በኋላም ወጡ። ከጎናቸው አቡበክር እያወራቸው እርሣቸው ደግሞ ሱረቱ አል-ፈትህን እያነበቡ ከዕባ ዘንድ ደረሱ። በግመላቸው ላይ ሆነውም ሰባት ጊዜ ከዕባን ዞሩ። በአንካሴያቸውም ሀጀር አልአስወድን ተሣለሙ። በዚያን ወቅት በከዕባ ዙሪያ ሦስት መቶ ስልሣ ስድስት ጣኦታት ነበሩ። ነቢዩ በእጃቸው በነበረው ከዘራ /አንካሴ/ እነኚሁኑ ጣኦታት ወጋ እያደረጉ
جاء الحق وزهق الباطل ، وما يبدئ الباطل وما يعيد
“እውነት መጣ ውሸት ከሰመ። ከአሁን በኋላ ውሸት አይፈጠርም አይመለስም።” ይሉ ነበር።
ከዚም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ትእዛዝ አስተላለፉና በከዕባ ውስጥ የነበሩ ጣኦታት ሁሉ እንዲወጡና እንዲወገዱ ተደረገ። በውስጧ የኢስማዒል እና የኢብራሂም ምስል አዝላም /ለጥንቆላ የሚውል ዘንግ መሠል ነገር/ በእጃቸው ይዘው የሚያሣይ ምስል ነበር። የአላህ መልእክተኛም ይህንንኑ በማየት “የአላህ ቁጣ ይውረድባቸው! እነሱ ፈፅሞ የጥንቆላ እጣ እንዳልተጣጣሉ ያውቁ ነበር።” አሉ።
እለቱ የአላህ ቤት ከዕባ ከብዙ ዘመናት በኋላ ከውሽት አምልኮ የጠራበት የመጀመሪያው ቀን ነበር። በሁሉም ዐረቦች የገጠሩም ሆነ የከተማው ነዋሪ ዘንድ እጅግ ቅዱስ ሆና የምትታየው ከዕባ ከዚህ እርኩስ ነገር በመጥራቷም ምክኒያት የጣኦት አምልኮ ጥቂት አካባቢ ላይ ብቻ ሲቀር ከሁሉም የዐረቢያ ምድር ምንም ማየት በማይቻል መልኩ ተጠራርጎ እንዲጠፋ ሆነ።