ታላቁ የበድር ጦርነት (ክፍል 3)

1
6627

በዐቂዳ እና በርህራሄ መካከል

በበድር በርህራሄና በዐቂዳ መካከል ከፍተኛ ተጋድሎ ነበረ የተካሄደው። ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ጎን ሆነው የተዋጉት ብዙዎቹ የኢስላም ወታደሮች ከሙሽሪኮች ጎራ ተሠልፈው የተዋጉአቸውን በርካታ ዘመዶቻቸው ጋር ነበር የተፋጠጡት።

በዉጊያው ሜዳ አንድ ሰው ወንድሙን፣ አባቱን፣ አጎቱን፣ ወይም የልጁን ሚስት ያገኝ ነበር። በዚህም የተነሣ የመተዛዘን ስሜትና ዐቂዳ ተፋጠጡ። ሆኖም ግን እዝነትና ርህራሄ በጠንካራዋ ዐቂዳ ለመሸነፍ ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም። አማኝ ሁሌም ቢሆን አላህ ባሣወቀው ነገር ላይ ፅኑ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَتَّخِذُوا آبَاءَكُمْ وَإِخْوَانَكُمْ أَوْلِيَاءَ إِنِ اسْتَحَبُّوا الْكُفْرَ عَلَى الْإِيمَانِ ۚ وَمَن يَتَوَلَّهُم مِّنكُمْ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الظَّالِمُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክህደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው። ከእናንተም ውስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው እነዚያ እነሱ በዳዮች ናቸው።” (አት-ተውባ 9፤ 23)

ልጅ አቡ ሁዘይፋ ኢብኑ ዑተይባ በምእመናን ጎራ አባቱ ዑትባህ ኢብኑ ረቢዓህ ደግሞ ከሙሽሪኮች በኩል የተፋጠጡበትን ሁኔታ እናስተውል። ልጅ አባቱን ወደ ሀቅ መንገድ እንዲመለስ ወደ አላህ ይጠራውና አማላጅም ይልክበት ነበር። መሃይም እና ተእቢተኛ የነበረው አባት ግን በጥመቱና በጥፋቱ ቀጠለ። በመጨረሻም ይሀው ጥፋቱና ጥመቱ ፍፃሜውን አበላሸበትና በአማኝ ሙስሊሞች እጅ ተገድሎ ሊወድቅ ቻለ። ጦርነቱ ሲያበቃና ድሉም የሙስሊሞች ሲሆን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተገደሉት ሙሽሪኮች በቦይ ውስጥ እንዲጣሉ አዘዙ። የአቡ ሁዘይፋ አባት ዑትባህ ኢብኑ ረቢዓህ ወደ ጉድጓዱ ሲጎተት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የአቡ ሁዘይፋን ፊት ተመለከቱ፡ ፊቱ ሲቀያየርም አስተዋሉ። እንዲህም አሉት “አቡ ሁዘይፋ ሆይ! ስለ አባትህ የሆነ ነገር የተሠማህ ትመስላለህ።” አሉት። አባ ሁዘይፋም “አይደለም የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ስለ አባቴም ሆነ ስለ መገደሉ ምንም አልተሠማኝም። ነገር ግን አባቴ ታጋሽ ትልቅና አስተዋይ ሰው መሆኑን አውቅ ነበር። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ወደ እስልምና ይመራውም ዘንድ እመኝ ነበር። መጨረሻው ምን እንደሆነና በክህደት ላይ እንደሞተ ባየሁ ጊዜ ግን ስመኝለት የነበረው ባለመሣካቱ ሀዘን ገባኝ።” የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዱዓእ አደረጉለት። በጎ ነገርም ተናገሩት።

ምርኮኞች

በበድር ጦርነት የተገደሉ የሙሽሪኮች ቁጥር ሰባ ሲሆን የተማረኩትም ሰባ ነበሩ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሙስሊሞች ባላቸው የከፋ የጠላትነት ስሜትና በጥፋታቸው እጅግ መብዛት የተነሣ ሁለት ሰዎች እንዲገደሉ አዘዙ። ሰዎቹ ሙስሊሞችን እጅግ በመበደላቸውና ደካሞችንም በማሠቃየታቸው እንዲሁም የአላህ እና የመልእክተኛው ክፉ ጠላት በመሆናቸው እንደ ጦር ወንጀለኞች እንጂ እንደ ምርኮኛ መታየት የሌለባቸው ናቸው። የተቀሩት ስልሣ ስምንት ምርኮኞች ናቸው። በነኚህ ዙሪያ ምን ሊደረግ እንደሚገባ ነቢዩ ከሰሃቦቻቸው ጋር ተማከሩ። ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አስዋሽተውሃል፣ ወግተውሃል፣ ከሀገርህ አስወጥተውሃል። እገሌን ለኔ ይፍቀዱልኝና (የርሱ ዘመድ የሆነውን ሰውዬ ሥም እየጠቀሠ) አንገቱን ልቅላው። ሀምዛን ደግሞ ለወንድሙ ዐባስ ያመቻቹለት ዐሊይን ደግሞ ከዐቂል .. በዚህ መልኩ ሰዎች ከሙሽሪኮች ጋር ምንም ዓይነት ወዳጅነት እንደሌለን ያውቁ ዘንድ።” አለ። ቀጠለ “አንድም አንገቱን የማልለው ምርኮኛ ሊኖርህ የሚገባ አይመስለኝም። እነኚህ ትላልቅ መሪዎቻቸው፣ አለቆቻቸው ናቸው።” በዚህም ሀሳቡ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ እና ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሃ ደገፉት።

አቡበክር ደግሞ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እነኚህ ሰዎች ቤተሰቦችህና ህዝቦችህ ናቸው። አላህ በርግጥ በነርሱ ላይ ድልንና የበላይነትን ሰጥቶሃል። በህይወት አቆይተሃቸው ቤዛ ብትቀበል የሚሻል ይመስለኛል። ከነሱ የምንወስደው ክፍያ ደግሞ ለመጠናከርና ሀይል ለማግኘት ያግዘናል። አላህ መርቷቸውም ኋላ ላይ ደጋፊህ ሊሆኑ ይችላሉ።” አለ።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የአቡበክርን ሀሣብ ተቀበሉ። ስልሣ ስምንቱን ምርኮኞችም ለየሰሃቦቻቸው በመከፋፈል “ለምርኮኞች መልካም ዋሉ።” አሏቸው። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ ከምርኮኞቹ የመቤዣ ክፍያ ተቀበሉ። ከነሱ ውስጥ ሀብታሞቹ ለአንድ ምርኮኛ ከአንድ እስከ አራት ሺህ ድርሃም ይከፍሉ ነበር። ድሆቹ አንዳንዶቹ በነፃ ተለቀቁ። የተማሩት ደግሞ የሙስሊሞችን ልጆች ማንበብና መፃፍ እንዲያስተምሩ ግዴታ ተጣለባቸው። ይህም ለነሱ መቤዣ እንዲደረግ ሆነ።

የእምነት ወንድማማችነት በላጭ ስለመሆኑ

በእናቱና አባቱ በኩል የሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ወንድም የሆነው አቡ ዐዚዝ ዑመይር ኢብኑ ሃሽም ምርኮኞች ውስጥ ነበር። በጦርነቱ ወቅት በአቡል ዩስር አል አንሷሪ ነበር የተማረከው። አቡ ዐዚዝ ወንድሙ ሙስዐብ ባለበት በኩል አለፈ። ሙስዐብ ለአቢል ዩስር እንዲህ አለው። “ምርኮኛህን አጥብቀህ ያዘው እናቱ ሀብታም ስለሆነች ብዙ ገንዘብ ልትከፍልህ ትችላለች።” ወንድሙ አቡ ዐዚዝም “ወንድሜ ሆይ! ይህ አንተ ለኔ ያለህ ምክር ነው?!” ሙስዐብም “ካንተ ይልቅ እሱ ነው ወንድሜ።” አለው።

የመቤዣ ክፍያው ሲጠየቅ እናቱ በቁረይሽ ውስጥ እጅግ ውድ የተባለውን ካሣ ተጠየቀች። አራት ሺህ ተባለች። እሷም አራት ሺ ድርሃሙን በመላክ አስለቀቀችው። በዚህ መልኩ የእምነት ወንድማማችነት ከዘርና ደም ትስስር በላይ መሆኑ ተረጋገጠ። ይህም የሆነው በሀቅ እና በአላህ መንገድ በመሆኑ ነው።

የአላህ መልእክተኛ ልጅ የዘይነብ ባል ከምርኮኞች ውስጥ መገኘቱ

አቡልዓስ ኢብኑ አር-ረቢዕ ኢብኑ ዐብዱልዑዛ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አማች የልጃቸው የዘይነብ ባለቤት ነበር። አቡልዓስ በሀብት፣ በታማኝነት፣ በንግድም በመካ ውስጥ ከሚቆጠሩ ትላልቅ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። እናቱ ሃለህ ቢንት ኹወይልድ ደግሞ የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሚስት የኸዲጃ እህት ናት። የአላህን መልእክተኛ ልጃቸውን ለሱ እንዲድሩም የጠየቀችው እሷ ናት። እንደ ልጇም ታየው ነበር። ይህም እሱ ለሷ ካለው አክብሮት የተነሣ ነው። በአንድም ነገር ላይ አይቃወማትም። ይህ ሁሉ የሆነው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከመላካቸው ማለትም ወህይ ከመውረዱ በፊት ነበር። ነቢዩ መለኮታዊውን ራእይ ሲቀበሉና ከቁረይሾች ጋርም የጠላትነት ሁኔታ ውስጥ ከገቡ በኋላ አቡለሀብ “ሙሀመድ ብቻውን ይቅር በናንተ ሥር ያሉትን የሱን ልጆች ፍቱ።” በማለት መመሪያ አስተላለፈ። መጀመሪያ ልጁን ዑትባን እንዲፈታ አዘዘው። እሱም የአላህን መልእክተኛ ልጅ ፈታ። ወደ አቡልዓስ በመሄድም ዘይነብን እንዲፈታ ጠየቁት። “እኛ በቁረይሽ ውስጥ ካሉ ሴቶች ሁሉ መርጠህ የፈለግከውን እናጋባሃለን ይህችን ፍታት።” አሉት።

አቡልዓስ ግን “ወላሂ ይህችን ሚስቴን አልፈታትም። በሷም ምትክ ከቁረይሽ ሴቶች ሌላ እንዲኖረኝ አልሻም።” ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በዚህን ጊዜ በዚህ አቋሙ ተደሰቱበት። የመካ ሰዎች በካሣ ክፍያ ምርኮኞቻቸውን እንዲወስዱ በላኩባቸው ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ልጅ ዘይነብም ባሏ ይፈታላት ዘንድ የመቤዣ ገንዘብ ላከች። ከገንዘቡም ጋር ያኔ ከአቡልዓስ ጋር ስትጋባ እናቷ ኸዲጃ በስጦታ መልክ የሠጠቻትን ቀላዳህ ጭምር አብራ ሠደደች።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘይነብን ባዩ ጊዜ በእጅጉ አዘኑላት። ለሰሃበቻቸውም “ምርኮኛዋን መልቀቅ ከፈለጋችሁና ያቀረበችውን ንብረት መመለስ ከቻላችሁ አድርጉ።” አሏቸው። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እሺ” አሉ። ምርኮኛ ባሏን አቡልዓስን ፈቱላት ንብረቷንም መለሱላት። በልዋጩም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘይነብ ወደ መዲና ተሠድዳ ትመጣ ዘንድ እንዲለቃት ለአቡልዓስ ሀሣብ አቀረቡለት። አቡልዓስም በሀሣቡ ተስማማ። የአላህ መልእክተኛ የአንዳንድ ምርኮኞችን አቅምና ሁኔታ በማየት ያለ አንዳች የካሣ ክፍያና ልዋጭ በነፃ አሠናብተዋቸዋል።

የበድር ጦርነት ውጤቶች

የበድር ጦርነት በአጠቃላይ በእስልምና እንስቃሴም ሆነ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግልፅ በሆነ መልኩ ትልቅ ትምህርት ሠጥቶ ያለፈ ዘመቻ ነው። ታላቁ ጌታ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እለቱን

يَوْمَ الْفُرْقَانِ

“እውነትና ውሸት በተለየበት ቀን” (አል-አንፋል 8፤ 41) በማለት ሠይሞታል።

ይህ ጦርነት ታላላቅ ውጤቶች የተገኘበት ሲሆን ከነኚህም መካከል፡-

 1. ጦርነቱ ሁለት ጎራዎች የሚለይ ውሸትና እውነትን የሚያሣውቅ ነበር። የሙስሊሞች ሀይል ተጠናከረ። በዐረቢያ ደሴት ሁሉ ተፈሩ። የራሷ ትምህር፣ አመለካከትና መርህ ያላት እውነት ከፍ ብላ ታየች።
 2. ቁረይሾች በዐረቦች ዘንድ የነበራቸው ደረጃ በአንዴ የፈራረሰ ሲሆን ድንገት በደረሠባቸው በዚህ ሽንፈት የመካ ሰዎች ክፉኛ ተደናግጠዋል።
 3. የሙስሊሞች በአካባቢው ላይ አስፈሪ ሀይል ሆኖ መውጣት በመካና መዲና መካከል የሚገኙ በርካታ ጎሣዎችን እውቅና ሠጥተው ከነሱ ጋር ስምምነት እንዲፈፅሙ አስገድዷቸዋል። በዚህም የተነሣ ሙስሊሞች ወሣኝ የሆነውን ይህ የንግድ መስመር በዋናነት ሊቆጣጠሩ ችለዋል።
 4. ሙስሊሞች ከጦርነቱ በፊት ሌላው ቀርቶ በመዲና አብረዋቸው የሚኖሩ ሙስሊም ያልሆኑ ማህበረሰቦችን ጭምር ይፈሩ ነበር። ከበድር ሲመለሱ ግን ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። አብዛኞቹ ሙስሊም ያልነበሩ ሰዎች እስልምናን መቀበላቸውን በይፋ አሣወቁ። እስልምናን ያልወደዱ ደግሞ መናፍቅ (እላዩን የሠለሙ በመምሰል ውስጡን ግን ያልሠለሙ) መሆንን መረጡ። በዚህም የተነሣ መናፍቅነት በመዲና ውስጥ አቆጠቆጠ።
 5. አይሁዶች ለሙስሊሞች ያላቸው ጥላቻ ጨመረ። አንዳንዶቹ አይሁዶችም ጠላትነቱን በግልፅ እስከማሣየት ደረሱ። ከፊሎቹ ደግሞ በመዲና ውስጥ የሙስሊሞችን ሁኔታ በመሠለል ለቁረይሾች ወሬ ያቀብሉና ያነሣሱባቸው ጭምር ነበር።
 6. የቁረይሽ የንግድ መስመር አደጋ ላይ ወደቀ። በዚህም ቁረይሾች ሙስሊሞችን ስለፈሩ የንግድ መንገዳቸውን በነጅድ በኩል በማድረግ የዒራቅን መስመር ለመምረጥ ተገደዱ። ይህም መንገድ ረጅም ነበር።
 7. በበድር ቀን ሸሂድ /መስዋእት/ የሆኑ ሙስሊሞች ቁጥር አሥራ አራት ሲሆን ከነኚህም መካከል ስድስቱ የሙሃጅሮች /ከነቢዩ ጋር በስደት ከመካ ወደ መዲና የገቡ/ እና ስምንቱ ደግሞ ከአንሷር /የመዲና ሙስሊሞች/ ወገን ነበሩ። ከሙሽሪኮቹ ደግሞ ሰባ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሰባ ያህሉ ደግሞ ተማርከዋል። አብዛኞቹም ትላልቅና ዋና ዋና የሚባሉ ሰዎቻቸው ነበሩ።

ከዚህ ጦርነት የምናገኘው ትምህርት

 1. አላህ ጠንካራ አማኞችን አይቀሬ በሆነው ድል ቃል ገብቶላቸዋል። እርሱ የሻውም ነገር መፈፀሙ ግድ ነው። ማንም ከመከሠት አይከለክለውም።
 2. አላህ ሀቅን የሚያፀናውና ውሸትን የሚደመስሰው ጠንካራ ታጋይና ታጋሽ በሆኑ ሰዎች አማካይነት ነው።
 3. እጅ ለእጅ መያያዝ አንድ መሆንና አለመለያየት ለስኬትና ለድል የሚያበቃ መንገድ ነው።
 4. ጦርነቱን ለማሸነፍ ሙስሊሞች የተከተሉት አዲስ የጦርነት ስልት ጠላትን በከፍተኛ ሁኔታ አደናግጧል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በድር ላይ ሙሽሪኮችን ካንበረከኩበት ከዚህ የጦርነት የውጊያ ታክቲክ አማኞች ከፍተኛ የሆነ ልምድ አግኝተውበታል።
 5. ፅኑ ዐቂዳ በራስ መተማንን ያደረጃል። ወኔና ሞራልንም በላቀ ሁኔታ ከፍ ያረጋል። የማይሸነፍ ሠራዊትንም ለመገንባት ያግዛል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

 

كَم مِّن فِئَةٍ قَلِيلَةٍ غَلَبَتْ فِئَةً كَثِيرَةً بِإِذْنِ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ مَعَ الصَّابِرِينَ

“ከጥቂት ጭፍራ በአላህ ፈቃድ ብዙን ጭፍራ ያሸነፈች ብዙ ናት፤ አላህም ከታጋሾች ጋር ነው።” (አል-በቀራህ 2፤ 249)

*****

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here