ታላቁ የበድር ጦርነት (ክፍል 2)

0
7027

የጦሩ ዋና አዛዥ ከወታደሮቻቸው ጋር ስለ መመካከራቸው

ሙስሊሞችና ነቢያቸው አስበውት የነበረው ነገር አልተሣካም። ነገሩ ሣይታሰብ አላህ በሻው ነገር ተቀየረ። በመሆኑም ለዚህ ለተጣደው አስቸኳይ ጉዳይ አዲስ ስልት መቀየሱ ግድ ሆነ። በሚከተሉት ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ነገሮችን በጥልቀት ማጤን ግድ ነው።

  • ሙስሊሞች ለጦርነት ሣይሆን ከሻም የምትመለሰውን የመካን የንግድ ቅፍለት አስበው መውጣታቸው
  • የሙስሊሞች በቁጥርም ሆነ በዝግጅት ከሙሽሪኮቹ ማነስ
  • የአንሷር ሰሃቦች ነቢዩን ለመጠበቅ የገቡት ቃልኪዳን በመዲና ውስጥ እያሉ እንጂ ከመዲና ውጭ አለመሆኑ

ለዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የጦሩ መሪ ነቢዩ ከወታደሮቻቸው ሀሳብ መፈለጉ ግድ ነበር። በመሆኑም የአላህ መልእክተኛ ሰሃቦቻቸውን ለምክክር ሰበሰቡ።

ከዚያም “ሰዎች ሆይ! አመላክቱኝ።” አሏቸው።
አቡበክር ተነሣና ጥሩ ንግግር ተናገረ። እሱን ተከትሎም ዑመር በመነሣት ቆንጆ ንግግር ተናገረ። ሚቅዳድ ኢብኑ ዐምር ደግሞ ተነሣና እንዲህ አለ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኛ በአንቱ አምነናል። አላህ ባዘዘዎት ነገር ይምሩን እኛ ከአንቱ ጋር ነን። ወላሂ እኛ የሙሣ ህዝቦች ለሙሳ ‘አንተና አምላክህ ሂዱና ተዋጉ እኛ እዚሁ እንቀመጣለን።’ እንዳሉት አንልዎትም። ነገርግን እንላለን ‘አንተና ጌታህ ሄዱና ተጋደሉ እኛም ከናንተ ጋር እንጋደላለን።’ በእውነት በላከህ ይሁንብኝ ጊማድ (ሩቅ የመን) ድረስ ይዘሀን ብትሄድ ከአንቱ ጋር እንሄዳለን እስክትደርስ ድረስም አንለይህም።”

የአላህ መልእክተኛ የሚቅዳድን ንግግር አወደሱ ዱዓእም አደረጉለት።

ከዚያም የአላህ መልእክተኛ አሁንም “አመላክቱኝ እናንተ ሰዎች ሆይ!” አሉ። ከአንሷሮችም የሆነ ነገር ለመስማት የሚፈልጉ በመምሠል ወደነሱ ዞሩ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ተነሣና “ወላሂ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በንግግርዎ እኛ እንድንናገር ያሰቡ መሠለኝ።” አለ። እሳቸውም “አዎ” አሉት። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝም ልብ በሚነካ አንደበት፡-

فقد آمنا بك وصدقناك وشهدنا أن ما جئت به هو الحق ، وأعطيناك على ذلك عهودنا ومواثيقنا على السمع والطاعة ، فامض يا رسول الله لما أردت فنحن معك ، فوالذي بعثك بالحق لو استعرضت بنا البحر لخضناه معك ما تخلف منا رجل واحد ، وما نكره أن تلقى بنا عدونا غداً ، إنا لصبرٌ في الحرب صدقٌ عند اللقاء لعل الله يريك منا ما تقرَّ به عينك ، فسر على بركة الله

“በርግጥም በአንቱ አምነናል። እውነት ነውም ብለናል። ይዘውት የመጡት ነገር እውነት መሆኑን መስክረናል። በዚህም ላይ እርስዎን በመታዘዝና በመስማት ላይ ለእርስዎ ቃልኪዳንና ቃል ገብተናል። ወደፊት ይቀጥሉ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኛ ከእርስዎ ጋር ነን። በእውነት በላከዎ እምላለሁ! ባህርን እንድንሻገር ቢያዙን ወላሂ ከርስዎ ጋር አንድም ሰው ሣይቀር እንገባበታለን። ነገም ጠላታችን ጋር ቢያገናኙን የምንጠላ አይደለንም። እኛ በጦርነት ላይ ታጋሾች በፍልሚያ ወቅት እውነተኞች ነን። በርግጥም አላህ ዐይንዎን የሚያሣርፍ ነገር ከኛ ያሣይዎታል። ይሂዱ በአላህ በረከት።” በማለት የሚያስደንቅ ንግር ተናገረ።

የአላህ መልእክተኛ ደስ አላቸው። ከዚያም እንዲህ አሉ “በአላህ በረከት ተጓዙ። አብሽሩ አላህ ከሁለት አንዱን ጭፍሮች ቃል ገብቶልኛል። ወላሂ የነኚህ ሰዎች እያንዳንዱ መውደቂያቸው ይታየኛል።”

በቦታ መረጣ ላይ ምክክር

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ ሙሽሪኮች ጦር መገስገስ እና ከፊት ለፊታቸውም ለጦራቸው ቦታ በመያዝ ለጦርነት መሠናዳት ባሰቡ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰሃቦቻቸው አስተያየትና ምክር ጆሮ ሠጡ። ኸባብ ኢብኑ አልሙንዚር ኢብኑ አልጀሙህ እንዲህ አለ “ይህ ቦታ ወደፊትም እንዳንሄድ ወደኋላም እንዳንቀር አላህ ያሣረፎት ቦታ ነው ወይንስ የጦርነት ሥልትና ሴራ ነው?” በማለት ጠየቃቸው። እርሣቸውም “በርግጥ የጦርነት ሥልትና ሴራ ነው።” አሉት።

እርሱም “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እንግዲያውስ ትክክለኛ ማረፊያ ይሄ መሆን የለበትም ከሰዎች በታች ወዳለው ዝቅተኛ የውሃ ቦታ እስክንደርስ ድረስ ሰዎችን ይዘው ይሂዱ። ከዚያም ከውሃ ጉድጓድ ኋላ ያለውን አንይዛለን። ከዚያም ሀውድ /ገንዳ/ እንሠራና ውሃ እንሞላዋለን። ከዚያም ጠላቶቻችን እንዋጋለን። እንጠጣለን እነሱ አይጠጡም።” አላቸው።

የአላህ መልእክተኛም “ትክክለኛ ነገር አመላክተሃል።” አሉት።

የአላህ መልእክተኛ እና አብረዋቸው ያሉ ሰዎች በመነሣት ለጠላቶቻቸው ወደ ሚቀርብ የውሃ ቦታ ቀረቡና ማረፊያቸው አደረጉ። ሌሎች የውሃ ጉድጓዶች ሁሉ እንዲደፈኑ ተደረገ። ባረፉበት የውሃ ጉድጓድ ላይም አጠሩና ውሃ ሞሉ። የውሃ እቃዎቻቸውንም ወደዚያ በመወርወር መቅዳት ጀመሩ። በዚህም እነሱ ውሃ ሲያገኙ ሙሽሪኮች ግን ውሃ በሌለበት ቦታ ላይ እንዲሠፍሩ ሆነ። ጥም የበረታባቸው የቁረይሽ የተወሰኑ ሰዎች የውሃውን አካል ለመያዝ ወደዚያ ተሽቀዳደሙ። ለመጠጣት የሄዱ ሁሉ ግን በበድር እለት እዚያው ተገደሉ። ከዚያ በኋላ የሠለመው ሀኪም ኢብኑ ሂዛም ሲቀር። እሱም በክህደት ላይ የመሞትን ሁኔታ በመፍራት የበድር ቀን ባለመገደሉ ዘወትር አላህን ያመሰግን ነበር።

እውነት መንገስ የአላህ መሻት ሆነ

በሙስሊሞች እና በሙሽሪኮች መካከል የሚደረገው ፍልሚያ ወሣኝ ስለመሆኑ የማያጠራጥር ነበር። ለምን ከተባለ ቁረይሾች በጦርነቱ የአላህን መልእክተኛ እና ሰሃቦቻቸውን ለአነዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ትልቁ እድላቸው ስለሆነ በጥብቅ ይፈልጉታል። ይህም የጣኦት አምልኮን በብቸኝነት ለማንገስ ይጠቅማቸዋል። በመዲና የሙስሊም መንግስት የመሠረቱትና በወጣት ጦር የተደራጁት ሙስሊሞች ደግሞ በነሱ ላይ የደረሰው የበደልና የጭቆና ዘመን አብቅቶ ትክክለኛው አመለካከትና መለኮታዊው ጥሪ እንዲነግስ የአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መሻት ይፈልጋሉ። ስለሆነም ፍልሚያው የሞት ሽረት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ፈተናው ከባድ መሆኑና መራር ነገር መጎንጨቱ አይቀሬ ነው።

ከሁሉም በላይ የአላህ መሻት ውሸትንና ባለቤቶቹን ማጥፋት እውነትን የያዘውን ሁሉ የበላይ ማድረግ መሆኑ የታወቀ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَإِذْ يَعِدُكُمُ اللَّهُ إِحْدَى الطَّائِفَتَيْنِ أَنَّهَا لَكُمْ وَتَوَدُّونَ أَنَّ غَيْرَ ذَاتِ الشَّوْكَةِ تَكُونُ لَكُمْ وَيُرِيدُ اللَّهُ أَن يُحِقَّ الْحَقَّ بِكَلِمَاتِهِ وَيَقْطَعَ دَابِرَ الْكَافِرِينَ
“አላህም ከሁለቱ ጭፍሮች አንደኛዋን እርሷ ለናንተ ናት ሲል ተስፋ በሰጣችሁ ጊዜ፣ የሀይል ባለቤት ያልኾነችውም (ነጋዴይቱ) ለናንተ ልትኾን በወደዳችሁ ጊዜ፣ አላህም በተስፋ ቃላቱ እውነትን ማረጋገጡን ሊገልጽና የከሓዲዎችንም መጨረሻ ሊቆርጥ በሻ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)።” (አል-አንፋል 8፤ 7)

በሌላ የቁርዓን አንቀፅም

إِذْ أَنتُم بِالْعُدْوَةِ الدُّنْيَا وَهُم بِالْعُدْوَةِ الْقُصْوَىٰ وَالرَّكْبُ أَسْفَلَ مِنكُمْ ۚ وَلَوْ تَوَاعَدتُّمْ لَاخْتَلَفْتُمْ فِي الْمِيعَادِ ۙ وَلَٰكِن لِّيَقْضِيَ اللَّهُ أَمْرًا كَانَ مَفْعُولًا لِّيَهْلِكَ مَنْ هَلَكَ عَن بَيِّنَةٍ وَيَحْيَىٰ مَنْ حَيَّ عَن بَيِّنَةٍ ۗ وَإِنَّ اللَّهَ لَسَمِيعٌ عَلِيمٌ
“እናንተ በቅርቢቱ ዳርቻ ኾናችሁ እነርሱም በሩቂቱ ዳርቻ ኾነው የነጋዴዎቹም ጭፍራ ከናንተ በታች ሲኾኑ በሰፈራችሁ ጊዜ (ያደረግንላችሁን አስታውሱ)። በተቃጠራችሁም ኖሮ በቀጠሮው በተለያያችሁ ነበር። ግን አላህ ሊሠራው የሚገባውን ነገር ሊፈጽም የሚጠፋ ሰው ከአስረጅ በኋላ እንዲጠፋ ሕያው የሚኾንም ሰው ከአስረጅ በኋላ ሕያው እንዲኾን (ያለቀጠሮ አጋጠማችሁ)። አላህም በእርግጥ ሰሚ ዐዋቂ ነው።” (አል-አንፋል 8፤ 42)

በመሆኑም አላህ እንዲሆን የፈቀደው የተቀጠረለት ፍልሚያ እስኪገኝ ድረስ ሁሉም ነገር በፍጥነት ወደፊት መቀጠሉ ግድ ሆነ። የአላህ ጥበቃም ለሙስሊሞቹ ቅርብ እንዲሆን ሆነ።

إِذْ يُرِيكَهُمُ اللَّهُ فِي مَنَامِكَ قَلِيلًا ۖ وَلَوْ أَرَاكَهُمْ كَثِيرًا لَّفَشِلْتُمْ وَلَتَنَازَعْتُمْ فِي الْأَمْرِ وَلَٰكِنَّ اللَّهَ سَلَّمَ ۗ إِنَّهُ عَلِيمٌ بِذَاتِ الصُّدُورِ

وَإِذْ يُرِيكُمُوهُمْ إِذِ الْتَقَيْتُمْ فِي أَعْيُنِكُمْ قَلِيلًا وَيُقَلِّلُكُمْ فِي أَعْيُنِهِمْ لِيَقْضِيَ اللَّهُ أَمْرًا كَانَ مَفْعُولًا ۗ وَإِلَى اللَّهِ تُرْجَعُ الْأُمُورُ

“አላህ በሕልምህ እነሱን ጥቂት አድርጎ ባሳየህ ጊዜ (አስታውስ)። እነሱን ብዙ አድርጎ ባሳየህም ኖሮ በፈራችሁና በነገሩ በተጨቃጨቃችሁ ነበር። ግን አላህ አዳናችሁ። እርሱ በደረቶች ውስጥ ያለን ሁሉ ዐዋቂ ነውና። አላህም ሊሠራው የሚገባን ነገር ይፈጽም ዘንድ በተጋጠማችሁ ጊዜ እነርሱን በዓይኖቻችሁ ጥቂት አድርጎ ያሳያችሁንና በዓይኖቻቸውም ላይ ያሳነሳችሁን (አስታውሱ)። ነገሮቹም ሁሉ ወደ አላህ ብቻ ይመለሳሉ።” (አል-አንፋል 8፤ 43-44)

ከጦርነቱ በፊት

የአላህ መልእክተኛ እና ሰሃቦቻቸው ሞራል ከፍ አለ። በፍልሚያው ቦታ ላይ ከፍ ያለውን አካባቢ ለጦራቸው መረጡ። ለቦታውም አስተማማኝ ጥበቃ አደረጉለት። ከዚም ተዋጊዎቹን መስመር የማስያዝና የማሠለፍ ሥራ ተከናወነ። በጦርነቱ ጊዜ ነገሮች ሲደበላለቁ በስህተት አንዱ ሌላኛውን ወንድሙን የመግደል ሁኔታ እንዳይፈጠር አንድ በአንድም እንዲተዋወቁ ተደረገ። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ እስካለዘዟቸው ድረስ ጥቃት እንዳይከፍቱ ማሣሰቢያ ተሠጣቸው። ይህም ሙሽሪኮች ወዳልታሰበው የጦርነት አቅጣጫ ጎትተው እንዳይወስዷቸው ለመጠንቀቅ ተብሎ የታሰበ ነው።

እንዲህም አሏቸው “ጠላቶቻችሁ ጥቃት ቢከፍቱባችሁ በቀስት መልሷቸው። እኔ እስካዛችሁ ድረስ ከባድ ጥቃት እንዳትከፍቱ።”

በዚህ መልኩ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሁሉም ነገር በወጉ ተዘጋጁ። እያንዳንዱን ጉዳይም በተገቢው ቦታና ሁኔታ ላይ አስቀመጡ። ለግጭት እና ለልዩነት የሚሆን አንድም ነገር ሣያስቀሩ ቦታ ቦታውን አስያዙ። በራሣቸው በኩል የቻሉትን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ጉዳያቸውን ሁሉ ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አስረከቡ።

የአንድ ለአንድ ፍልሚያ

ወሣኟ ሰዓት ደረሠች። ሁለቱ ወገኖች በግልፅ ሜዳ ላይ ተገናኙ። ፊት ለፊትም ተፋጠጡ። ሙሽሪኮች በጃሂሊያ ጉራቸውና ስሜታቸው ሥር ወደቁ። ሁሉም የራሱን ቦታና ደረጃ ማሣየት ይፈልጋል። ጀግንነቱን ማሣየት። እጅግ ሀይለኛና መጥፎ ሰው የሆነው አልአስወድ ኢብኑ ዐብዱልአሠድ አልመኽዙሚይ ወጣና ከፍ ባለ ድምፅ ተጣራ። ከሙስሊሞች የውሃ ኩሬ እንደሚጠጣ አሊያም እንደማፈርሰው ለአላህ ቃል እገባለሁ ወይንም እሞታለሁ። አለ። ሙስሊሞች የከለሉትን የውሃ ኩሬ እያሠበ። ከዚያም ቦታውን ለማጥቃት ተንቀሣቀሰ። ነገርግን ሃምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ ወጣና በሰይፍ ከውሃው ሣይደርስ ከጉልበቱ በታች ያለው እግሩን አበረረለት። ሰውዬው አሁንም መሀላውን ለመሙላት ወደ የውሃ ኩሬው ሮጠ አሁንም ሃምዛ ኩሬው መሃል ደረሠበትና ገደለው። በዚህን ጊዜ የሙሽሪኮቹ ዐትባህ ኢብኑ ረቢዓህ ጀግንነቱን ለማሣየት ፈለገና በወንድሙ ሸይባህ እና በልጁ ወሊድ መካከል ሆኖ ለአንድ ለአንደ ፍልሚያው /ሙባረዛ/ ተጣራ። ወዲያውኑ ከአንሷር የሆኑ ወጣቶች በጥድፊያ ወጡ። የአላህ መልእክተኛ ግን መለሷቸው። ዑበይዳ ኢብኑ አልሃሪስ፣ ሃምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ እና ዐሊ ኢብኑ አቢጧሊብ እንዲወጡ አደረጉ። እነሱም የርሣቸው ቤተሰብ ሲሆኑ ከሌሎቹ በላይ ለአደጋ ጊዜ ይመርጧቸዋል። ጀግንነታቸውንም ሆነ የጦር ልምዳቸውን አሣምረው ያውቃሉ። በአላህ ፈቃድ እነሱ በቁረይሽ ሰዎች ላይ የተሣካላቸው እንደሆነ ደግሞ የሙስሊሞች ሞራል በእጅጉ ይነሣሣል። የሙሽሪኮቹ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ይወድቃል። መርዛማ እሾሃቸውም ይነቀላል።

በዚህም በእድሜ ትልቃቸው የሆነው ዑበይዳ ከዑትባህ ጋር፤ ሃምዛ ደግሞ ከሸይባህ ጋር፤ ዐሊ ደግሞ ከወሊድ የዑትባ ልጅ ጋር ለመፋለም ዝግጁ ሆኑ። ሃምዛም ሆነ ዐሊ ተፋላሚዎቻቸውን ለመጣል ብዙ አልቆዩም። ዑበይዳህ እና ዑትባህ ግን ሁለቱም ክፉኛ ተቆሣሰሉ። ወዲያውኑ ግን ዐሊና ሃምዛ በመረባረብ በሰይፋቸው ዑትባህን ጨረሱት። የቆሰለውን ጓደኛቸውን ዑበይዳን በመሸከምም ለህክምና ወደ ሙስሊሞቹ ካምፕ ወሰዱት።

ይህ የጦርነቱ መክፈቻ ለሙስሊሞች መልካም ለሙሽሪኮቹ ደግሞ ክፉ ዜና ነበር። በመሆኑም ሙሽሪኮቹ እጅጉን ተበሣጩ። በንዴትም ጦዙ። ይህን ክፉ አጀማመር ለመካስም ይመስላል ከፍተኛ ጥቃት ለመሠንዘር ተንቀሣቀሱ። ነገርግን ሙስሊሞች በቦታቸው ላይ በመሆን መለሷቸው። የአላህ መልእክተኛ እስኪያዟቸውም ድረስ ጥቃት አልጀመሩም።

መልእክተኛው አምላካቸውን መማጸናቸው

በዚህ ዓይነቱ ቀውጢ ሰዓት ላይ የሰው ልጅ ፊቱን ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መመለሱ ግድ ነው። አላህ ጭንቀቱን እስኪያነሣለት ድረስም ሀሣቦች ሁሉ ለአላህ መጥራት፣ ኢኽላስም መረጋገጥ ልቦናዎችም በከፍተኛ ሁኔታ ለአላህ መተናነስ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም የአላህ መልእክተኛ በማዘዣ ጎጆአቸው ውስጥ በመሆን ፊታቸውን ወደ ቂብላ በማዞር እጃቸውን ከፍ በማድረግ ጌታቸውን መመሣጠርና መለመን ጀመሩ

اللهم هذه قريش قد أتت يخيلائها تحاول أن تُكذب رسولك اللهم أنشدك عهدك ووعدك . اللهم أنجز لي ما وعدتني اللهم آتني ما وعدتني ، اللهم إن تَهلك هذه العصابة ، من أهل الإسلام اليوم لا تُعبد في الأرض

  

“አላህ ሆይ! ይህች ቁረይሽ ናት ያንተን መልእክተኛ ለማስዋሸት ከጉራዋና ኩራቷ ጋር መጥታለች። አላህ ሆይ! ቃልህንና ቃልኪዳንህን እንድትሞላልኝ እማፀንሃለሁ። አላህ ሆይ! የገባህልኝን ቃል ፈፅምልኝ! የገባህልኝን ቃል ስጠኝ። አላህ ሆይ! ይህች ከኢስላም የሆነችው ትንሽ ስብስብ ዛሬ የምትጠፋ ከሆነ በምድር ላይ አንተን የሚያመልክ አይኖርም።” በማለት።

የአላህ መልእክተኛ እጃቸውን በመዘርጋት ችክ በማለት ጌታቸውን መለመኑን ቀጠሉበት። የለበሱት ኩታ ከትከሻቸው ላይ እስኪወድቅ ድረስ። አቡበክር ወደርሣቸው መጣና ኩታቸውን ወደ ትከሻቸው በመመለስ ከኋላቸው ቀርቦ እንዲህ አላቸው “የአላህ ነቢይ ሆይ! ጌታዎን መማፀኑ ይብቃዎት። ጌታዎ ቃል የገባልዎትን ነገር ይሞላሎታል።” የአላህ መልእክተኛ ግን የአላህ ፈረጅ እስኪመጣ ድረስ ዱዓዓቸውን አላቆሙም። እንዲህ የሚል የቁርዓን አንቀፅ ወረደ

إِذْ تَسْتَغِيثُونَ رَبَّكُمْ فَاسْتَجَابَ لَكُمْ أَنِّي مُمِدُّكُم بِأَلْفٍ مِّنَ الْمَلَائِكَةِ مُرْدِفِينَ

وَمَا جَعَلَهُ اللَّهُ إِلَّا بُشْرَىٰ وَلِتَطْمَئِنَّ بِهِ قُلُوبُكُمْ ۚ وَمَا النَّصْرُ إِلَّا مِنْ عِندِ اللَّهِ ۚ إِنَّ اللَّهَ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“ከጌታችሁ ርዳታን በፈለጋችሁ ጊዜ ‘እኔ በሺህ መላእክት ተከታታዮች ሲኾኑ እረዳችኋለሁ’ ሲል ለናንተ የተቀበላችሁን (አስታውሱ)። አላህም (ይኽንን ርዳታ) ለብስራትና ልቦቻችሁ በርሱ ሊረኩበት እንጂ ለሌላ አላደረገውም። ድልም መንሳት ከአላህ ዘንድ እንጂ ከሌላ አይደለም። አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።” (አል-አንፋል 8፤ 9-10)

ከዚህ በኋላ የአላህ መልእክተኛ “አቡበክር ሆይ! አብሽር ሁሉም ይሸነፋሉ ወደኋላም ይሸሻሉ። አብሽር የአላህ እርዳታና ድል መጥቶልሃል። ይህ የፈረሱን ልጓም የያዘው ጅብሪል ነው። እየመራውም ነው።” አሉ።

የአላህ መልእክተኛ አማኞችን በውጊያ ላይ ሲያነሣሱ

አላህ ሱብሃነሁ ወተኣላ በድል ቢያበስራቸውም መልእክተኛው ድል የሚመጣው የአላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ ትእዛዛት በመከተል፣ በመዘጋጀት፣ በእውነተኝነት መሆኑን ያውቃሉና አርፈው አልተቀመጡም። አላህ የአንድን ህዝቦች የመልካም ሁኔታ አይቀይርም እነሱ እስካልተቀየሩ ድረስ። በመሆኑም ሙስሊሞች ድልንና ስኬትን እስኪጨብጡ ድረስ የቻሉትን ሁሉ ማድረግ፣ በእጅጉ መበርታትና መጠናከራቸው አስፈላጊ ነበር።

ስለሆነም የአላህ መልእክተኛ ወደ ሙስሊሞቹ ሰልፍ በመግባት ወታደራዊ ንግግራቸውን አደረጉ። ሀሳብ ጭንቀትን ለማስወገድና ፅናትን ለማጠናከር።

والذي نفسي بيده لا يقاتلهم اليوم رجل فيقتل صابراً محتسباً مقبلاً غير مدبر إلا أدخله الله الجنة : قوموا إلى جنة عرضها السموات والأرض

“ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታዬ እምላለሁ። አንድም ሰው ዛሬ ታጋሽ ሆኖ ምንዳውን በአላህ ላይ ተሣስቦ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ሳይመለስ እነሱን አይጋደልም አላህ ጀነትን ያስገባው ቢሆን እንጂ። ተነሱ ስፋቷ ሰማያትንና ምድርን የሚልቀው ወደሆነው ጀነት!” አሏቸው።

ዑመይር ኢብኑ አል ሀማም አል አንሷሪይ ተነሣና “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ስፋቷ ‘የሰማያትና የምድር ያህል ስፋት ያላት ጀነት!’” አላቸው። እርሣቸውም “አዎን” አሉት።

ዑመይር በኽ በኽ! /ውዴታ መግለጫ ቃል/ አለ። የአላሀ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “በኽ በኽ! ለማለት ምን አነሣሣህ” አሉት። ወላሂ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ሌላ ነገር አይደለም እሷን ከሚገቡ ሰዎች መካከል ለመሆን ፈልጌ እንጂ አላቸው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “አንተ ከነሱ ነህ” አሉት። ከስልቻው ጥቂት ተምሮች አወጣና መብላት ያዘ። ከዚያም “እነኚህን ተምሮች እስከምበላ የምቆይ ከሆነ ጊዜው ረጅም ነው የሚሆነው።” አለና በእጁ ያሉትን ተምሮች ወረወረና ሄደ።

የጦርነቱ መጀመር

ከዝግጅት፣ ከአደረጃጀት፣ ከሥነልቦናዊ ጦርነትና እስከሌላም ድረስ የዘለቀ የድል መሠረት የሆኑት ዋና ዋና ነገሮች ሙስሊሞች ዘንድ ተሟሉ። ሙሽሪኮቹ ግን ይህን ጉዳይ አልተገነዘቡም። ከዚህም በተጨማሪ ሙስሊሞች ይዘው የመጡትን አዲስ የጦርነት ስልት አላስተዋሉም ነበር። ሙሽሪኮቹ ግን በድሮው የውጊያ ስልታቸው ጦርነቱን ከፈቱ። ይህም አጥቅቶ የመሸሽ ስልት ነበር። ያለ አንዳች የመደራጀት ሥርዓት በስሜት በመነሣሣትና በሀይል በከፍተኛ ሁኔታ ሙስሊሞችን ያጠቁና ይሸሻሉ። ሙስሊሞች ግን አይከተሏቸውም። በቦታቸው ላይ በመሆን በቀስት ብቻ ይለቅሟቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ በመሆን የአላህን መልእክተኛ ትእዛዝ ይጠባበቃሉ። ሙስሊሞች በሚልኩት ዒላማቸውን የጠበቁ ቀስቶች ዝናብ የሙሽሪኮቹ ዋና ዋና የሚባሉ ሰዎች እንደ ቅጠል መርገፍ ጀመሩ። በሚያዩት አስደናቂ ትእይንት የሙስሊሞቹ ወኔ እየተሞላ እያንሠራራና መሬት እየያዘ መጣ። በዚህን ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ ሙስሊሞች ጦር ሰልፍ መሃል ገቡና ጥቃቱን እራሣቸው ለመምራት በማሰብ ሙስሊሞቹ ለጥቃት ስለመዘጋጀታቸው የመጨረሻ ሁኔታቸውን ያስተውሉ ጀመር። ከዚያም ወደ ሙሽሪኮቹ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲፈጥኑና እንዲያጠቁ አዘዟቸዉ። የሙስሊሞች ሰይፎች የከሃዲያን አመፀኞችን አንገት መቅላት፤ ጭንቅላቶቻውንም መልቀም ጀመሩ።

ሙስሊሞች በዚህ ጦርነት ላይ ታላቅ የብስለት እና የጀግንነት ውጊያ አሣዩ። ጦርነቱ ሲፋፋምም የአላህ መልእክተኛ ወደ ጦሩ ፊት መቅደም ያዙ። ዐሊ ኢብኑ አቢጧሊብ እንዲህ ይላል “ጦርነቱ ሲፋፋም እና ሲግል የአላህ መልእክተኛ ሥር እንደበቅ ነበር። ከርሣቸው በላይ ወደ ጠላት ጦር የሚቀርብ ማንም አልነበረም።”

በጦርነቱ ውስጥ የታየው ጀግንነት

ጀግንነቱ በታላላቅ ሰሃቦች እና የጦሩ መሪ ላይ ብቻ የተወሠነ አልነበረም። ከዚያን በፊት ስለ ውጊያም ሆነ ጦርነት የማያውቁ ትናንሽ ልጆች ጭምር ጀግንነታቸውን አሣይተውበታል። ጀግንነታቸውም የቁረይሾች የጦር መሪ ከሆነው እኩይ ግለሰብ ላይ ነበር። በቁረይሾች ውስጥ ትልቅ አለት ነው ከሚባለው ከፍተኛ የሆነ የጦር ልምድ ካለውና የጦሩ መሪም ከሆነው ከአቡ ጀህል ጋር። አቡጀህል በበድር እለት በሙሽሪኮቹ ሰልፍ መካከል በመዘዋወር “የዑትባህ፣ የሸይባህ እና የወሊድ መገደል አያስፈራችሁ። እነሱ ቸኩለው ነው። በላት እና በዑዛ እምላለሁ በተራራው መካከል እስክንበታትናቸው ድረስ አንመለስም።” ይል ነበር። “አንዳችሁ አንድን ሰው ስትገድሉም ከናንተ በመለየቱ ከላት እና ከዑዛ በመራቁ ያጋጠመውን መጥፎ ሥራ ያናገራችሁት ቢሆን እንጂ።”

ከዚያም አቡ ጀህል ለራሱ እንዲህ በማለት ፎከረ “ለዚህ ዓይነቱ ቀን ነው እናቴ የወለደችኝ!”

የአቡጀህል መገደል

ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ እንዲህ ይላል “በበድር ቀን በሰልፍ ላይ እያለሁ ዞር ስል በግራና በቀኜ ታዳጊ ወጣቶችን አየሁኝ። ትናንሽ ከመሆናቸው የተነሣ ያሉበትን ሁኔታ ፈራሁላቸው። በነሱ መካከልም ሆኜ ልከላከልላቸውም ተመኘሁ። አንደኛው ጓደኛው እንዳይሠማ ብሎ ድምፁን ዝቅ በማድረግ “አጎቴ ሆይ! አቡ ጀህልን ያሣዩኝ።” አለኝ። “የአጎቴ ልጅ ሆይ! ምን ያረግልሃል” አልኩት። እሱም “የአላህን መልእክተኛ እንደሚሳደብ ተነግሮኛል። እሱን ያየሁ እንደሆን ልገድለው አሊያም ልሞት ለአላህ ቃል ገብቻለሁኝ።” አለኝ። በዚህ በመገረም ላይ ሣለሁ አንደኛውም ቆነጠጠኝ። የመጀመሪያው ልጅ የጠየቀኝንም ጥያቄ ጠየቀኝ። ወዲያውኑ አቡ ጀህልን በጦሩ መካከል ሲዘዋወር አየሁት። “አያችሁት! ይህ እናንተ የምትጠይቁት ሰውዬያችሁ ነው።” አልኳቸው። በሰይፋቸው ተሸቀዳደሙና እስኪሞት ድረስ ደበደቡት። በሌላ የዐብዱረህማን ዘገባ ደግሞ “በመሃላቸው መሆኔ እጅግ አስደሠተኝ። አሣየኋቸውም። በሰይፋቸውም እንደ ጭልፊት ተረባረቡበት። ልጆቹ የዐፍራእ ልጆች ነበሩ።” ብሏል።

ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ አቡጀህልን ወድቆ በማጣጣር ላይ እያለ አገኘው። እዚያም ጨረሠው። አነስ ኢብኑ ማሊክ እንዳለው የአላህ መልእክተኛ “አቡጀህል ምን እንደሆነ ማነው የሚነግረኝ” አሉ። ኢብኑ መስዑድም “እኔ ነኝ።” አለ። በወደቀበት ሄደና ጺሙን በመያዝ “አንተ አቡጀህል ነህን” አለው። አቡጀህልም “ከሱ በላይ ሰው ገድላችኋል!” በማለት አፌዘበት። ከዚያም ጨረሠውና ስለ ሁኔታው ለነቢዩ ነገራቸው።

የቁረይሽ መሪዎችና ትላልቅ ሰዎች መገደላቸው

የበድር ጦርነት ትላልቅ የቁረይሽ ሰዎች ተገድለዋል። ከነኚህም መካል ዑትባህ፣ ሸይባህ እና ልጁ ወሊድ፣ አቡጀህል፣ ዘመዓህ ኢብኑ አልአስወድ፣ ነቢህ ኢብኑ ሙነበህ፣ ኡመያህ ኢብኑ ኸለፍ እና አቡል በህተራ ይገኙበታል።

የኡመያ ኢብኑ ኸለፍ መገደል

ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ የቁረይሾች አለቃ ነው። በእስልምና መባቻ አካባቢ የሀበሻችንን ቢላልን እና ሌሎች ደካማ ምእመናን በመካ እያሉ በእጅጉ ያሠቃይ ነበር። የበድር ጦርነት ግለት ኡመያን ዐቅል እስከማሣጣት የደረሠ ነበር። እሱም የሚማርከው አሊያም ከዚህ ከተፋፋመው የጦርነት ረመጥ መካከል የሚወስደው እንዳለ ይጠይቅ ነበር።

ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ እንዲህ ይላል “ድንጋጤ በተሞላበት ሁኔታ ከልጁ ጋር ቆሞ ሣለ በኡመያህ ኢብኑ ኸለፍ ዘንድ አለፍኩኝ። የጦር መከላከያ ጥሩሬን አውልቄ ተሸክሜ ነበር። ባየኝም ጊዜ ‘የዐብዱልኢላህ አባት ሆይ!’ አለኝ። እኔም ‘አቤት’ አልኩት። ‘እባክህን እኔንና ልጄን ምርኮኛ አድርገህ ውሰደኝ። ከዚህች ከያዝከው የጦር ጥሩር ይልቅ እኔ እሻልሃለሁ። ምርኮኛ አድርጎ ለወሠደኝ ሰው ለመቤዣ ብዙ ወተት ያላቸውን ግመሎችን እሠጠዋለሁ።’ አለኝ።” ጥሩሩን ወዲያ ወረወርኩና እጁንና የልጁን እጅ ያዝኩኝ። “የዚህ ዓይነት ቀን ፈፅሞ አይቼ አላውቅም።” አለ። “ዐብዱላህ ሆይ! የአሞራ ላባ በደረቱ ላይ ሰክቶ የሚዋጋው ማነው” አለኝ። ዐብዱረህማንም “እሱማ ሀምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ ነው።” በማለት መለሰላቸው። “እሱ ነው ጉድ ሥራ የሠራን።” አለ ኡመያ። ዐብዱረህማን እንዲህ ይላል “እኔ አስሬ ጎትቼያቸው በመሄድ ላይ ሣለሁ ቢላል በሩቁ አያቸው። በጃሂሊያው ጊዜ በመካ በነበሩበት ወቅት ኡመያ የቢላል ጌታ የነበረ ሲሆን በእጅጉ ሲያሠቃየው የነበረ ሰው ነው። ቢላልም ኡመያን ባየ ጊዜ ‘ይህ የክህደት አለቃ ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ አይደል’ አለ። ‘ደህና የሆነ እንደሆነ እኔም ደህና አልሁን!’ አለ። ‘ቢላል ሆይ! ምርኮኛዬ እኮ ነው!’ አልኩት። ደጋግሞ ‘ደህና ከሆነ ደህና አልሁን!’ በማለት ዛተ። ከዚያም ‘ይሀው የከሀዲያን አለቃ የአሏህ አንሷሮች ሆይ!’ በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮሀ። ‘ደህና ከሆነ ደህና አልሁን /ከወጣ አልውጣ!/’ አለ። ሰዎችም ወዲያኑ ከበቡት። እኔ እከላከል ነበር። አንድ ሰው የልጁን እግር በሰይፍ ሲመታው ወደቀ። ኡመያም ከዚህ በፊት ሰምቼ በማላውቀው ድምፅ ጮሀ። እኔም ነገሩ ከአቅም በላይ ሲሆንብኝ ‘ኡመያ ሆይ! ነፍስህን አድን’ አልኩት። ‘የምትድን አይመስለኝም ወላሂ እኔም ምንም የማደርግልህ ነገር ያለ አይመስለኝም።’ ሰዎች ተሰባሰቡና በሰይፍ ደበደቧቸው። በመጨረሻም እስኪጨርሷቸው ድረስ።”

ዐብዱረህማን ከዚያ በኋላ እንዲህ ይል ነበር። “አላህ ለቢላል ይዘንለት ጥሩሬንና ምርኮኛዬን አስጣለኝ! ትእይንቱ ከአላህ ጋር ትግል ውስጥ የሚገባ ሰው የሚሸነፍ አላህን ጠላት የሆነ ሰው ደግሞ የሚዋረድ መሆኑን እና በአላህ አምልኮ የሚያሾፍ ሰው አላህ በመጨረሻም ብርቱ አያያዝ እንደሚይዘውና ለሌሎችም ማስተማሪያ የሚያደርገው መሆኑን ፍንትው ባለ ሁኔታ ያሣየናል። የመጨረሻው ዓለም የአኺራ ቅጣት ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው።

وَاللَّهُ غَالِبٌ عَلَىٰ أَمْرِهِ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ
“አላህም በነገሩ ላይ አሸናፊ ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።” (ዩኑስ 12፤ 21)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here