ታላቁ የበድር ጦርነት በአምስተኛው አመተ ሂጅራ በተቀደሰው ወርሃ ረመዳን 17 ላይ የተካሄደ እውነት ከሐሰት የተለየበት ታላቅ ክስተት ነው። ታሪኩን እነሆ…
የመካ ቁረይሾችንና በተግባር መሠሎቻቸው የሆኑትን ያካተተው የጣኦት አምላኪው ማህበረሰብ ሙስሊሞችን እና ጉዳያቸውን ሁሉ ከመካና ዙሪያዋ ከሚገኙ አካባቢዎች ካባረሩ በኋላ በየስሪብ (መዲና)ም ቢሆን እምነታቸውን በነፃነት ያስፋፉና ይተገብሩ ዘንድ እንደማይተውዋቸው የአላህ መልእክተኛ እና ሙስሊሞች ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። በመሆኑም ለክፉ ነገር ሁሉ እራሣቸውን ማዘጋጀት እና መጠንቀቅ ጀመሩ።
መዲና ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ ድንገት ሊጠቁ እንደሚችሉ በማሰብ ለሙሽሪኮችና በአጠቃላይ በሙስሊሞች ላይ ሊያሴሩ ለሚችሉ ጎሣዎችም የሙስሊሞችን ሀይልና ጥንካሬ ለማሣየት በከፍተኛ ሁኔታ ስልጠናውን አጧጧፉ። ስልጠናው ከየትኛውም ወገን በመዲና ላይ በሙስሊሞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ድንገተኛ ጥቃት ለመመከት እንዲያስችላቸው ነው። እነዚያ ከቁረይሾች ግፍና ጭቆና የሸሹ ሙስሊሞች በርግጥም ብዙዎች እንደሚገምቱት ደካሞች እና አቅም የሌላቸው ሣይሆኑ ባሻ ጊዜ እጅግ አስፈሪ ሀይል እና እሾህ ሊሆኑ ይችላሉና እነሱን ከማጥቃት በፊት ሺህ ጊዜ መላልሦ ማሰብ ተገቢ ነው።
የሥልጠና ቅኝትና ዝግጅት
የአላህ መልእክተኛ ሰላሁ ዐለይህ ወሠለም ሰሃቦቻቸውን ማሠልጠን ያዙ። ሥልጠናውንም ወደ ተግበር ለመለወጥ በመዲና ዙሪያም ተዋጊ፣ ቃኚና አሣሽ ቡድን ላኩ። ከነኚህም መካከል እራሣቸው የመሯቸው ቡድኖች ሲኖሩ አንዳንዶቹንም ከሰሃቦቻቸው መካከል መርጠው እንዲመሩ አድርገዋል። ከቡድኖቹም መካከል
- በሀምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ የምትመራና ሠላሣ የሙሃጅር /ከመካ የተሠደዱ/ ፈረሠኞችን በመያዝ ወደ ዒስ የባህር ዳርቻ የተላከ ቡድን
- በዑበይዳ ኢብኑ አል-ሃሪስ የምትመራና ስልሣ የሙሃጅር ፈረሠኞችን በመያዝ ወደ ራብግ የተላከች
- በሰዕድ ኢብኑ አቢወቃስ መሪነት በመካና መዲና መንገድ ለቅኝት ተልእኮ የተላከች ሰማኒያ ሰዎችን የያዘች ቡድን
- የወዳን ዘመቻ (ገዝዋ)፡- በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተመራችና ሁለት መቶ ፈረሠኞችንና እግረኞችን በመያዝ ለውጊያ ተልእኮ ወደ ውዳን የሄደች ጦር። የአላህ መልእክተኛ በዚህ ዘመቻ ከበኒ ደምረህ ጋር ስምምነት የፈጠሩ ሲሆን የዚህ ዘመቻ ዋና ዓላማ የነበረውም የመካ- ሻም /ሶሪያ/ መንገድን ይቆጣጠሩ ከነበሩ ጎሣዎች ጋር ስምምነትና ግንባር ለመፍጠር ነበር።
- የዑሺራ ዘመቻ፡- የውጊያ ተልእኮ የነበራት ሲሆን ሁለት መቶ ፈረሠኞችና እግረኞች የተካተቱባት በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የምትመራ ጠንካራ ሀይል ነበረች። ዋና ዓላማዋ የነበረውም ለሙሽሪኮች የሙስሊሙን ሀይል ለማሣየትና በየንቡዕ አካባቢ በቁረይሽ የንግድ መንገድ ላይ በመካና መዲና መካከል ከሚገኙ ጎሣዎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ነበር።
- የቡዋጥ ዘመቻ፡- የመዋጋት ተልእኮ የተሠጣት ሁለት መቶ ፈረሠኞችና እግረኞች የተካተቱባት በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የምትመራ ሀይል ነበረች። ዓላማውም በረድዋ ተራራ በኩል አድርጎ ቡዋጥ በመድረስ በመካና መዲና መካከል የቁረይሾች የንግድ መስመር የሆነውን ጎዳና ለመቆጣጠርና ቁረይሾችን ስጋት ላይ ለመጣል ነበር።
- በዐብደላህ ኢብኑ ጀህሽ የተመራች እና ሰማኒያ ጠንካራ ሙሃጂሮች የተካተቱበት የቅኝት ተልእኮ የተሠጣት ሀይል ስትሆን መሪዋም ከሁለት ቀን ጉዞ በኋላ እንጂ ደብዳቤውን እንዳይከፍት ነቢዩ ያዘዙት የተፃፈ መልእክት የያዘ ነበር። የጦሩ መሪ ከሁለት ቀን በኋላ ደብዳቤውን ሲከፍት “ይህን መልእክት እንዳየህ በአንዲት በመካና ጧኢፍ መካከል ከምትገኝ የተምር ዛፍ እስክትደርስ ድረስ ተጓዝ። እዚያም ሁንና የቁረይሾችን ሁኔታ ተከታተል ስለሁኔታቸውም ለማወቅ ሞክር።” ዐብዱላህ ከተምር ዛፏ እስኪደርስ ድረስ ተጓዘ። የቁረይሽ ቅፍለት በዚያ በኩል ስታልፍም ሙስሊሞቹ ጥቃት ከፈቱባት። ከሙሽሪኮችም ወገን ዐምር ኢብኑ አል-ሀድረሚ ተገደለ። ሁለት የቁረይሽ ሰዎችም የተማረኩ ሲሆን አራተኛው ሸሽቶ አመለጠ።
የመጀመሪያው የበድር ዘመቻ
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እና ሰሃቦቻቸው ከሙሽሪኮች አንፃር የጠበቁትና የገመቱት ነገር መከሠቱ እውን ሆነ። ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መዲና ገብተው ብዙም ሣይረጋጉ በከርዝ ኢብኑ ጃቢር አል-ፍህሪይ የተመራ የሙሽሪኮች ጦር በመዲና ዳርቻ በሚገኙ የግጦሽ ማሣዎች ላይ ወረራ በማካሄድ የሙስሊሞች የሆኑ የተወሰኑ ግመሎችንና ፍየሎችን ነድቶ ወሰደ።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተዘረፉ የሙስሊም ግመሎችንና ፍየሎችን ለማስመለስ ሙሽሪኮቹን ለማሣደድ ወጡ። በአላህ መልእክተኛ የተመራው የሙስሊሙ ጦር ለበድር ቅርብ ከሆነው የሰፍዋን ሸለቆ ድረስ ተጓዘ። ነገርግን የሙሽሪኮቹ ሀይል ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ያለ አንዳች ውጊያ ወደኋላ ተመለሱ።
የታላቁ የበድር ጦርነት ምክኒያቶች
1.በመካ ይኖሩ የነበሩ ሙስሊሞች ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈው ከአገራቸው እንዲወጡ በመደረጋቸው።
የመካ ቁረይሾች በሙስሊሞች ላይ ጦርነት ያወጁት የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ኢስላማዊ ጥሪያቸውን በይፋ ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግፉ ቀጠለ። የሙስሊሞችን ደም ማፍሠስ በድብቅም ይሁን በይፋ ያመኑትን የመካ ሙስሊሞች ቤቶቻቸውን መቀማትና ሀብት ንብረቶቻቸውን በሀይል የግላቸው ማድረግ ጀመሩ። ሙስሊሞችም የአላህን ውዴታ አስበልጠው ከተወለዱባትና ካደጉባት ቀዬ ነፍሦቻቸውን ይዘው ኮበለሉ። ጥለው የኮበለሉት ሀብት ንብረትም በቁረይሾች ቁጥጥር ሥር ዋለ። በስደታቸው ወቅትም ሱሀይብን የመሣሰሉ ሰሃቦች ወደ መዲና መሠደድ ፈልገው በመታገዳቸው ሙሉ ንብረታቸውን አሣልፈው በመስጠት እንዲለቋቸው እስከመደራደር ደርሰዋል።
2.ሙሽሪኮች መዲና ድረስ በመምጣት ሙስሊሞችን ማሣደዳቸው
ቁረይሾች መካ ሣሉ በሙስሊሞች ላይ ባደረሱት ግፍና ጭቆና ብቻ በቃን አላሉም። ከስደት በኋላም ቢሆን በነሱ ላይ ማሴርና ማነሣሣትን ሥራዬ ብለው ተያያዙ። በመዲና የሚገኙ ሙስሊሞችን በማጥቃት ንብረቶቻቸውን እንዲዘርፉ እንዲያሸብሯቸውም ጭምር ከሌሎች ሙሽሪኮች ጋር በመተባበር በኩረዝ ኢብኑ ሀባብ አል-ፍህሪ የሚመራ ጦር ላኩ። ይህ ጥቃት የመጀመሪው የበድር ጦርነት በመባል ይታወቃል። ስለሆነም ቁረይሾች ለሙስሊሞች ላሣዩት የከፋ ጥላቻና ሙስሊሞችንና ኢስላምን ለማጥቃት ባደረጉት እንቀስቃሴ ምክኒያት የእጃቸውን ዋጋ ማግኘትና መራራ ውጤቱንም መጎንጨት ነበረባቸው። ጥቅሞቻቸውንና የንግድ መስመሮቻቸውን ሙስሊሞች አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ማሣወቁ የሚያስፈልግበት ጊዜ ደረሠ። እስልምና መጠናከሩን፤ መንግስት ያለው መሆኑን እና ጥቃትንና ክፋትን ሁሉ መመለስ እንደሚችል እንዲሁም ሀቅን የማስፈን ውሸትን የመደምሰስ ሀይል ያለው እጅ እንዳለው ማሣየቱ ግድ ሆነ።
3.ቁረይሾችን ሥርዓት ማስያዝና የሙስሊሞችን ሀብት ንብረት ማስመለስ
በሺህ ግመሎች የምትገመትና አርባ ሰዎችን የያዘች በአቡ ሱፍያን ኢብኑ ሀርብ እና ዐምር ኢብኑ አል-ዓስ የምትመራ የቁረይሾች ቅፍለት የንግድ እቃዎች ይዛ ከሻም ሀገር ወደ መካ መንቀሣቀሷን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በሰሙ ጊዜ ሙስሊሞች ለመውጣት አሰቡ። ነቢዩም “ይህች የቁረይሾች የንግድ ቅፍለት እንዳታመልጣችሁ።” አሏቸው። የተወሰኑ ሰዎች በፍጠነት ለጥሪው ምላሽ ተዘጋጁ። ከፊሎቹ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ለጦርነት አላዘዙንም በሚል መልኩ ተረዱ። ነቢዩ በማስከተል “የሚሣፈር እንሠሣ በቅርብ ያለው ሰው ይሣፈርና አብረን እንሂድ።” አሉ። ወዲያውም የሚሳፈሩትን እንሰሣ በቅርብ የሌላቸውን ሰዎች ሣይጠብቁ በአፋጣኝ ቅፍለቷን አስበው ወጡ።
በወቅቱ የሙስሊሞች ቁጥር ሦስት መቶ አሥራ ሦስት ሰዎች ነበር። መቶ አርባ ምናምን የሚሆኑ ሰዎች ከአንሷር /የመዲና ሰዎች/ ነበሩ፤ የተቀረው ቁጥር ከሙሃጅሮች /ከመካ ወደ መዲና የተሠደዱ ሰዎች/ ነበር። ሙስሊሞቹ ሁለት ፈረስ እና ሰባ ግመሎች ነበሯቸው።
የጦርነቱ ታሪክ
ኢብኑ ኢስሃቅ እንዳለው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተወሰኑ የረመዷን ወር ቀናት ካለፉ ነበር ለዚህ ተልእኮ የወጡት። ሰኞ ቀን ስምንት የረመዷን ወር ቀናት ካለፉ በኋላ ነበር። ዐብዱላህ ኢብኑ ኡም መክቱምን በመዲና ሰላት ላይ አቡ ሉባባን ደግሞ የመዲናን ሁኔታ እንዲቆጣጠርን እንዲያስተዳደር ሀላፊነት ሰጥተው ወጡ።
በወቅቱ የሙስሊሞች ቁጥር ሦስት መቶ አሥራ ሦስት ሰዎች ነበር። መቶ አርባ ምናምን የሚሆኑ ሰዎች ከአንሷር /የመዲና ሰዎች/ ነበሩ፤ የተቀረው ቁጥር ከሙሃጅሮች /ከመካ ወደ መዲና የተሠደዱ ሰዎች/ ነበር። ሙስሊሞቹ ሁለት ፈረስ እና ሰባ ግመሎች ነበሯቸው። የባንዲራቸው ተሸካሚ የነበረው ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ሲሆን የበድር ጦርነት የዋለው ጁሙዓ ጠዋት ረመዷን አሥራ ሰባተኛው ቀን ነበር።
አቡ ሱፍያን የሙስሊሞችን መውጣት አወቀ
አቡሱፍያን እጅግ ንቁ እና ጠንቃቃ ሰው ነው። ነገሮች ይዘው የሚመጡትን መጨረሻ ይገምታል። ቁረይሾች በሙስሊሞች ላይ የሠሩትን ግፍ ጠንቅቆ ያውቃል። እያደገ ያለውን የሙስሊሞች ሀይል ሁኔታም በቅርብ ይከታተላል። ከሻም ግዛት ወጥቶ ሂጃዝ ዋናው የዐረቢያ ምድር አካባቢ እንደደረሠ የመዲና ሙስሊሞችን ሁኔታ መሠለል ያዘ። ለንግድ ቅፍለቱም ፈርቶ በነሱ አካባቢ የሚያልፈውን መንገደኛ ሁሉ የአካባቢውን ሁኔታ ያጠያይቅ ነበር። በመጨረሻም የተወሰኑ መንገደኞች ሙሀመድ እና ባልደረቦቹ የንግድ ቅፍለት የሆነችውን የመካን ግመሎች ለመከታተል የወጡ ስለመሆናቸው ወሬ ደረሠው። በዚህን ጊዜ የጥንቃቄ እርምጃ ወሠደ። መንገድ ከመቀየሩም ባሻገር በመካ ላሉ ቁረይሾችም የድረሱልኝ መልእክት ላከ።
የቁረይሾች መውጣት
አቡ ሱፍያን ወሬውን እንዲነግርለት ደምደም ኢብኑ ዐምር አል-ጊፋሪን ቀጠረ። እሱም አፍንጫው በተቆረጠ ግመል ላይ ሆኖ ኮርቻውን አዙሮ ቀሚሱን ቀዳዶ እንዲህ በማለት እየጮሀ መካ ደረሠ “እናንተ ቁረይሾች ሆይ! እናንተ ቁረይሾች ሆይ! ከአቡሱፍያን ጋር ያለ ሀብት ንብረታችሁን ሙሀመድ እና ባልደረቦቹ ሊዘርፉ ወጥተዋል። ልትደርሱለት ግድ ነው። ድረሱላቸው! ድረሱላቸው!።” ቁረይሾች ይህን ባወቁ ጊዜ ለንግዳቸው ፈሩ። በፍጥነትም ተሰባሰቡና ቅፍለታቸውን ለማዳን ወጡ። ከነሱ ጋርም ዋና አለቆቻቸውና መሪዎቻቸው ነበሩ። ቀንደኛ የኢስላም ጠላት ከነበረው ከአቡ ለሀብ ኢብኑ ዐብዱልሙጦሊብ /የነቢዩ አጎት/ በስተቀር ማንም የቀረ አልነበረም። እሱም ቢሆን በምትኩ አል-ዓስ ኢብኑ ሂሻም ኢብኑ አል-ሙጊራህን ልኮ ነበር። በዚሁ ቁረይሾች ለመውጣት ከስምምነት ደረሱ። ሙስሊሞችን እንደሚያዋርዱና በደሞቻቸው እንደሚጫወቱ በማሰብ ደስ እያላቸውና እየፎከሩ ወጡ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“ሰይጣንም ሥራዎቻቸውን ለእነርሱ ባሳመረላቸውና ‘ዛሬ ለእናንተ ከሰዎች አሸናፊ የላችሁም እኔም ለእናንተ ረዳት ነኝ’ ባለ ጊዜም (አስታውስ)፡፡” (አል-አንፋል 8፤48)
የቁረይሾች የንግድ ቅፍለት ማምለጥ
አቡ ሱፍያን በበኩሉ ተከላካይ የቁረይሽ ጦር ከመካ እስኪመጣለት ድረስ በቦታው ላይ ቆይቶ አልጠበቀም። በራሱ በኩል የቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ ማምለጫ ዘዴዎችን አፈላለገ። በደረሰበት ሁሉ የሙስሊሞችን ሁኔታ ይጠይቃል፤ ወሬዎችን ያነፈንፋል፤ ይተነትናልም። መጅዲ ኢብኑ ዐምር የተባለ ሰው ባገኘ ጊዜ በዚህ ሰሞን “አዲስ ያስተዋልከው ነገር አለን?” በማለት ጠየቀው። እሱም “የማስታውሰው ብዙም ነገር የለኝም። ነገርግን ሁለት መንገደኞች መጡና ግመሎቻቸውን እዚህ በማሰር ከያዙት ስልቻ ውስጥም ውሃ በመጠጣት ከዚያም ተመልሰው ሄዱ።” አለው
አቡሱፍያንም ግመሎቻቸውን አስረው ወደነበረበት በመምጣት ከእንሠሦቹ የቀረውን በጠጥ በማንሣት ሲበትን እውሰጡ ደረቅ ፍሬ አገኘ። ከዚያም “ወላሂ ይሄ የየስሪብ መኖ ነው።” አለ። ሁለቱ ሰዎችም የሙሀመድ ወገኖች መሆናቸውን ገመተ። የሙስሊሙ ጦርም እዚህ አካባቢ መሆን አለበት ሲልም አሠበ።
ወደ ግመሎቹ ቅፍለትም በመመለስ ወደ ኋላ እንዲመለሱ ካደረገ በኋላ መንገድ በማስቀየር በድርን በግራ በኩል በመተው የባህር ሰርጡን ተከትሎ በመጓዘ ቅፍለቱን ይዞ አመለጠ።
የሙሽሪኮች ትእቢት እና በጦርነት አቋም ስለመፅናታቸው
የሙሽሪኮች ጦር በሰፊው በረሃ ላይ እንዲሁም በመካና መዲና መንገድ በሚገኙ ተበታትነው በሠፈሩ ጎሣዎች መካከል እየፎከረና እያቅራራ የጦር ሀይሉንም እያሞጋገሠ አቡሱፍያንን ከሙስሊሞች እጅ ለማስጣል በማሰብ ወደፊት ገሠገሠ። የአቡሱፍያን ቅፍለት ግን ጥቃት ሣያገኛት አመለጠች። አቡሱፍያን ሰላማዊ ሜዳ ላይ መውጣቱንና ከሙስሊሞች ከበባ ማምለጡን በተረዳ ጊዜ ወታደሮቿን አሰባስባ እርሱን ለማዳን እየመጣች ላለችው የቁረይሽ ጦር መልእክት ላከ። “አምልጠናልና ተመለሱ።” በማለት። የአቡሱፍያን መልእክተኛም የሙሽሪኮችን ጦር መንገድ ላይ አገኛቸው። የንግድ ቅፍለቶቹ በሰላም ያመለጡ መሆኑንም ነገራቸው። ነገርግን አቡ ጀህል በትእቢት እና በጉራ እንዲህ አለ “ወላሂ በድር ሣንደርስና ሦስት ቀን እዚያ ሳንቆይ አንመለስም። ግመሎቻችንን እናርዳለን። ምግብ እናበላለን። መጠጥ እንጠጣለን። እውቅ ሴቶችም ይዘፍኑልናል። ዐረቦች ሁሉ ስለኛ መሄድና መሰብሰብ መስማት አለባቸው። ይህንንም በመስማት እስከመጨረሻው ይፈሩናል።” ቁረይሾች የአቡጀህልን ሀሣብ በመቀበል ተጓዙ። የጎሣዎች አለቆችም ሰዎች “ፈሪዎችና ቦቅቧቆች” ይሉናል ብለው በመፍራት ተከተሏቸው። መሹረት አል-አክነስ ኢብኑ ሸሪቅን የተከተሉ የበኑ ዙህራ ሰዎች ሲቀሩ ሌላ ማንም አልተመለሠም ነበር። እሱም በነሱ ውስጥ ተሰሚነት ያለው አለቃ ነበርና ተመለሱ ባላቸው ጊዜ ተመለሱ።
የበድር ጦርነት ክስተቶች
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የወጡት የቁረይሽን የንግድ ግመሎች ለማግኘት ነበር። ወደርሣቸው መንቀሣቀስ ላይ ስለነበረው የቁረይሽ ጦር ግን ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ከመዲና ውጭ ለጦር ዝግጅት ካምፕ ጣሉ። አማኙን የሙስሊም ጦርም አሰባሰቡ። ለመዋጋት አቅማቸው ያልደረሰውንም መለሱ።
የሁለቱ ወገኖች ሀይል
የሙስሊሞች ሀይል
በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተመራው የሙስሊሙ ጦር ቁጥር ሦስት መቶ አሥራ ሦስት ሰው ነበር። ከነኚህም መካከል ሁለት ፈረሰኞች የዙበይር ኢብኑ አል-ዐዋም እና የሚቅዳድ ኢብኑ ዐምር ፈረሦች ሲሆኑ ሰባ ግመልም ተራ በተራ ይፈናጠጡ ነበር።
አብዱላህ ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ይላል “በበድር ቀን ሦስት ሆነን በአንድ ግመል ላይ ተራ በተራ እንሣፈር ነበር:: አቡ ሉባባ፣ የአላህ መልእክተኛ እና ዐሊ አንድ ግመል ይቀያየሩ ነበር። የነቢዩ በእግር የመሄድ ተራ በደረሠ ጊዜ ‘እኛ የርስዎን ፈንታ እንሄዳለን የአላህ መልእክተኛ ሆይ!’ አሏቸው። እርሣቸውም ‘እናንተ በጥንካሬ ከኔ የተሻላችሁ አይደላችሁም። እኔ ደግሞ ከናንተ በተሻለ መልኩ ከአጅር የተብቃቃሁ አይደለሁም።’ በማለት መለሱላቸው።”
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሙስሊሞችን ባንዲራ ለሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ሰጡት። ነጭ ባንዲራ ነበር። በአላህ መልእክተኛ እጅም ሁለት ባንዲራዎች ነበሩ። የአላህ መልእክተኛ ዙበይር ኢብኑ አል-ዐዋምን መዲና ላይ አስተዳዳሪ በማድረግ በግራ በኩል ሚቅዳድ ኢብኑ አስወድን ከታች ደግሞ ቀይስ ኢብኑ አቢ ሰዕሰዓን አደረጉ።
የሙሽሪኮች ጦር
ሙሽሪኮች ዘጠኝ መቶ ሃምሣ ሰዎችን በጦራቸው ውስጥ ለማሰባሰብ ቻሉ። አብዛኛው ሰው ከቁረይሽ ነበር። ሁለት መቶ ፈረስ እና የሚሣፈሯቸውና ጓዞቻቸውንና ስንቆቻቸውን የጫኑባቸው በርካታ ግመሎችም ነበሩ። ለሙሽሪኮች አጠቃላይ የሆነ መሪ አልነበራቸውም። ባይሆን ጎልተው የሚታዩ ሁለት ዋና ዋና ሰዎች ነበሩ። ኡትባህ ኢብኑ ረቢዓ እና አቡጅህል ሲሆኑ ሌሎች በርካታ ታዋቂ የቁረይሽ ሰዎችም ተካተውበታል።
የቅኝት ሥራዎች
የሙስሊሙ የጦር ሀይሎች በመዲና እና በበድር መካከል ያለውን የቅፍለቱን መንገድ ተከተሉ። ርዝመቱ መቶ ስልሣ ኪሎ ሜትር ያህል ነው። የአላህ መልእከተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከድንገተኛ ጥቃት ለመጠንቀቅ እና ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ መረጃ ለማግኘት ሲሉ ከፊት ለፊታቸው ባለው መንገድ በርካታ ቃኚ ሰዎችን ላኩ።
የመጀመሪያው ቃኚ ቡድን ሰበስ ኢብኑ ዐምርን እና ዐዲይ ኢብኑ አቢ ዘዕባእን የያዘ ሲሆን እነሱም በድር እስኪደርሱ ድረስ ተጓዙ። እዚያም ከውሃው ምንጭ ቅርብ ከሆነው የተምር ዛፍ ግመሎቻቸውን አሰሩ። ከዚያም ስልቻዎቻቸውን በማውጣት ከውስጡ ውሃ መጠጣት ጀመሩ። እግረመንገዳቸውንም ወሬ ማዳመጥ ያዙ። ዐዲይ እና ሰበስ ከአካባቢው ሰዎች የሆኑ ሁለት ልጃገረዶች በውሃ ላይ እየተጣሉ አንደኛዋ ለሌላኛዋ “ቅፍለቶቹ የሚመጡት ነገ ስለሆነ ለነሱ መሥራት አለብኝ። ከዚያ በኋላ ያንችን እሠጥሻለሁ” ስትላት ሰሙ። ሁለቱ ሰዎች በሰሙት መረጃ ላይ ትንታኔ ያደርጉ መረጃውን ወስደው ለነቢዩና ሰሃቦቻቸው አቀበሉ።
ሁለተኛው ቃኚ ቡድን
ከዚያ በኋላ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መረጃ ያሰባስቡ ዘንድ ዐሊ ኢብኑ አቢጧሊብን፣ ዙበይር ኢብኑ አለዐዋምን እና ሰዕድ ኢብኑ አቢወቃስን ከተወሰኑ ሰሃቦች ጋር ወደ በድር ምንጭ /የጉድጓድ ውሃ/ ላኳቸው። እነሱም ስለ ቁረይሽ የተወሠነ መረጃ አገኙ። ከበኒ ሀጃጅ የሆነ አገልጋይ እና የበኒልዓስ ኢብኑ ሰዕድ አገልጋይ የነበረው ዐሪድ አቢ የሣርም ሰለሙ። እነ ዓሊ ወጣቶቹን ይዘው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘንድ አመጧቸው- ለጥያቄ። የአላህ መልእክተኛም ጠየቋቸው። እነሱም “እኛ ከቁረይሽ ጦር ወገን ነው የመጣነው ስለ አቡሱፍያን የምናውቀው ምንም ነገር የለም።” አሏቸው። “ስንት ናቸው” በማለት ስለ ቁረይሾች በጠየቋቸውም ጊዜ “በጣም ብዙ ናቸው በቁጥር ስንት እንደሆኑ ግን አናውቅም።” “ለምግባቸው በአንድ ጊዜ ስንት ግመል ነው የሚያርዱት” በማለት ጠየቋቸው። “አንድ ቀን ዘጠኝ ሌላ ቀን ደግሞ አሥር” በማለት መለሱላቸው።
የአላህ መልእክተኛ ከመረጃው በመነሣት “የቁረይሽ ጦር ቁጥር በዘጠኝ መቶ እና አንድ ሺህ መካከል ሊሆን ይችላል” አሉ። ከዚያም ከታላላቅ የቁረይሽ ሰዎች መካከል እነሱ ውስጥ ማን ማን እንዳለ ጠየቋቸው። ወጣቶቹም ዑትባህ ኢብኑ አቢ ረቢዐህን፣ ሸይባህን፣ አቡል በህተራ ኢብኑ ሂሻምን፣ ሀኪም ኢብኑ ሂዛምን እና የተወሰኑ የቁረይሽ ዋና ዋና የተባሉትን ሰዎች ጠሩ። ከዚያም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “ይህች መካ ናት በርግጥም የማህፀኗን ፍሬ ዘርግፋላችኋለች።” አሉ።
የጦሩ መሪ ለቅኝት ስለመውጣታቸው
የአላህ መልእክተኛ መረጃ ፍለጋ ከአቡበክር ጋር በመሆን ወጡ። አንድ የዐረብ ሽማግሌ አገኙና ስለ ቁረይሾች ስለ ሙሀመድ እና ሰሃቦቹ ወሬ እንዳለው ጠየቁት። ሰውየውም ስለማንነታችሁ ካልነገራችሁኝ አልነግራችሁም አላቸው። እርሣቸውም “ከነገርከን እንነግርሃለን” አሉት። ሰውየውም “የኔ በናንት መሆኑ ነው!” ሲላቸው እርሣቸውም “አዎን” አሉ።
ሰውየውም እንዲህ አለ- ሙሀመድ እና ሰሃቦቹ በዚህ በዚህ ቀን የመውጣታቸው ወሬ ደርሦኛል። የነገረኝ ሰው እውነቱን ከሆነ እነሱ በዚህ ቀን እዚህ እዚህ ቦታ ላይ ናቸው ማለት ነው።” አለ ነቢዩና ሰሃቦቹ አሁን የደረሱበትን ቦታ እየጠቀሠ። ቁረይሾች ደግሞ በዚህ በዚህ ቀን ስለመውጣታቸው ወሬ ደርሦኛል። የነገረኝ ሰው እውነቱን ከሆነ እነሱ ዛሬ እዚህ እዚህ ቦታ ላይ ናቸው። በማለት አሁን የቁረይሽ ጦር የሠፈረበትን ቦታ ጠቀሠ። ወሬውን ሲጨርስም “በሉ እናንተ እነማናችሁ ንገሩኝ” በማለት ጠየቃቸው። የአላህ መልአክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “እኛ ከውሃ ነን።” በማለት መልሰውለት ዞር ብለው ሄዱ። ሰውየውም “ከዒራቅ ውሃ ነው” በማለት እየጠየቀ ነበር።
የሙስሊሞቹ አመራሮች መረጃዎችን በመተንተን እውነታው ላይ ስለመድረሣቸው
የቃኚዎቹ ቡድኖች ያመጧቸው መረጃዎች አንድ ላይ ተሰባሰቡ። የወጡላት የቁረይሾች ቅፍለት ማምለጧን ተገነዘቡ። የሙሽሪኮቹ ጦርም ከሙስሊሙ ጦር ፊት ለፊት እንዳለ ተረዱ። የጠላት ጦር ብዛትም ከዘጠኝ መቶ እስከ አንድ ሺህ ሊሆን እንደሚችል ከነሱም መካከል ትላልቅ የቁረይሽ ሰዎች እንዳሉ ዝግጅታቸውም የማይናቅ እንደሆነ ደረሱበት። ለመሆኑ ሙስሊሞች እነኚህን መረጃዎች ይዘው ምን ያደርጉ ይሆን!
በዚህ መልኩ ሁለቱ ወገኖች አንደኛው ስለሌላው ሣያውቅ ሊገናኙ ተቃረቡ። ከዚህ አስፈሪ መገናኘት በኋላ ምን ሊከሰት ይችል ይሆን!። በዚህ መልኩ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው ትልቁ ጦርነት ሊስተናገድ ሰበቦች ተፈጠሩ። መንገዶች ተጠረጉ። ጦርነቱ በሀቅ እና በውሸት መካከል ነበር። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“አላህም ከሁለቱ ጭፍሮች አንደኛዋን እርሷ ለናንተ ናት ሲል ተስፋ በሰጣችሁ ጊዜ፣ የሀይል ባለቤት ያልኾነችውም (ነጋዴይቱ) ለናንተ ልትኾን በወደዳችሁ ጊዜ፣ አላህም በተስፋ ቃላቱ እውነትን ማረጋገጡን ሊገልጽና የከሓዲዎችንም መጨረሻ ሊቆርጥ በሻ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡” (አል-አንፋል 8፤ 48)