ወላጆችህ ባንተ ደስ እንዲሠኙ ለማድረግ የሚያግዙ 10 ነጥቦች

2
29259

ልጅ ሆነን ሣለ ወላጆቻችን የሚሰሩት ነገር አይመቸንም። እንዲያውም አብዛኞቻችን ድርጊታቸውንና ሁኔታቸውን እንተችና እናጣጥል ነበር። አድገን የነርሱ ቦታ ላይ ስንድርስ ግን ያኔ እነርሱ ሲሠሩ የነበረው ነገር ትክክል መሆኑ ይገለፅልናል። በጊዜው በነርሱ በኩል ይደርስብን የነበረው ጫና ያላግባብ መስሎ ቢታየንም ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ ግን ያደርጉት የነበረው ነገር ትክክልና ለኛው ብለው ስለመሆኑ ይገባናል። በኛ ላይ የወላጆቻችን ውለታ እጅግ ብዙ ስለመሆኑ በጥቂቱም ቢሆን የሚገባን ልጅ ያገኘን እንደሆነ ነው።

“ቢር አልዋሊደይን” (ለወላጅ መልካም መዋልን) እስልምና ትልቅ ዋጋ ሠጥቶታል። ለወላጅ መልካም መዋል የቀደምት የአላህ ነቢያትም መንገድ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዳለው ነቢዩ ዒሣ ዐለይህ ሠላም ገና በእናታቸው አንቀልባ ውስጥ ሆነው ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር።

وَبَرًّا بِوَالِدَتِي وَلَمْ يَجْعَلْنِي جَبَّارًا شَقِيًّا
 

“ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)። ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም።” (መርየም 19፤ 32)

ቀጥሎ ወላጆቻችን በኛ ደስ እንዲሠኙ ለማድረግ ሊያግዙን የሚችሉ 10 ውብ ነጥቦችን እንዘርዝር

  1. ትዝታ – ልጅ ሆነን ሣለ እንዴት ያጨናንቁንና ይጫኑን እንደነበረ እናስታውሣቸው። በማዝናናት መልኩም እንተርክላቸው። አሁን ላይ ሆነን ሁኔታውን ስናጤን ግን ያኔ እነርሱ በርግጥም በድርጊታቸው ትክክል የነበሩ መሆኑንም እንንገራቸው።
  2. ውስጣዊ ስሜት – ወላጆቻችን የሆነ ነገር አሊያም ስጦታ የሠጡን እንደሆነ ደስታችንና ውስጣዊ ስሜታችንን አውጥተን እናሣያቸው። አጋጣሚውንም በመጠቀም ይህ የሠጡን ስጦታ በጣም ጠቃሚና እጅግ ያስፈልገን እንደነበረም እንግለፅላቸው።
  3. ስጦታ – ለነርሱ ያለንን ውዴታና ከበሬታ የምንገልፅበት ስጦታ ገዝተን እንስጣቸው። ስጦታው የግድ ውድ ነገር መሆን የለበትም። ባይሆን በተቻለን አቅም ሁሉ ደጋግመን እንስጣቸው። የሠጠናቸውን ስጦታ ለሌላ ሰው አሣልፈው ቢሰጡ እንኳ አንቀየማቸው። ያደረግነው ሁሉ ለነርሱ ያለንን ውዴታ ለመግለፅና ውዴታቸውን ለማግኘት ነውና።
  4. ወግ – ከነርሱ ጋር ጊዜ ወስደን እናውራቸው። ወላጆቻቸው (አያቶቻችን)፤ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በህይወት ካሉ ባሉበት ሄደን እንዘይራቸው። በጉብኝታችን ወቅት ያየነውንና የሠማነውንም ነገር እነርሱን ደስ በሚያሠኝ መልኩ መልሠን እንንገራቸው።
  5. ማማከር – ማግባት ስንፈልግ፣ ቤት አለያም መኪና ለመግዛት ስናቅድ፣ እሩቅ መንገድ ለመሄድ ስንወጥንና ሌሎችም ከባባድ ውሳኔዎች ማድረግ ስንፈልግ እናማክራቸው። ቀለል ያሉ ነገሮችን ለምሳሌ ለጓደኛችን ልብስ መግዛት፣ ምግብ ማድረስ፣ አሊያም ስጦታ ነገር መስጠት ስንፈልግም ሀሣባችንን እናማክራቸው። ማማከራችን ለነርሱ ያለንን ግምት ያሳያቸዋልና።
  6. ጨዋታ – በልጅነታችን ወቅት ከነርሱ፣ ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያሣለፍናቸውን አዝናኝ ገጠመኞችና ትዝታዎችን ሌሎችንም በማንሣት እናጫውታቸው። ጨዋታ በመፍጠርና በመቀለድም እናስፈግጋቸው።
  7. ቴክኖሎጂን መጠቀም – በፌስቡክ፣ በትዊተርና በመሣሰሉት ገፆች የነርሱን አባባል በመለጠፍ ለነርሱ ያለንን አክብሮት እናሣይ። እናታችን የሠራችውን ምግብ፤ አባታችን የለፋበትን የእርሻ ማሳ አሊያም ሌላ ነገር ፎቶ በማንሣት ለጓደኞቻችን፣ ለወዳጆቻችንና እነርሱንም ለሚያውቅ ሁሉ እናሠራጭ። ይህንንም ድርጊታችንን መልሠን እንንገራቸው። ከሌሎች ሰዎች በሚደርሣቸው መልእክት በመነሣት ልጃቸው በሠራው ሥራ ውስጣቸው ደስ ይሠኛልና።
  8. መጎብኘትና ማስተናገድ – እነርሱን ለመጎብኘት፣ ወደ ቤት ጠርተን ለመጋበዝና አብሮ ተመቀማምጦ ለመብላትና ለማውራት ጊዜ ይኑረን። መንገድ የሚሄዱ ከሆነም በቤታቸው ተገኝተን እንሸኛቸው። አቅሙ ካለንም ወጭያቸውንም እንቻል።
  9. ርህራሄና እዝነት – በተለይ ዕድሜያቸው የገፋ እንደሆነ እዝነትና ርህራሄ እናሣያቸው። ባልተገባ መልኩ አስቆጥተናቸው ከሆነም ቶሎ ብለን ይቅርታቸውንና ውዴታቸውን እንፈልግ።
  10. ጓደኞች – መልካም ጓደኞቻችንና ወዳጆቻችንን እቤታቸው ድረስ በመውሰድ እናስተዋውቃቸው። በዚህ ድርጊታችን ደስ ይሠኛሉና።

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) አባታቸው ገና ሳይወለዱ፤ እናታቸው ደግሞ ገና የስድስት አመት አካባቢ ልጅ ሆነው ሣሉ ነው የሞቱባቸው። በመሆኑም የቲም /ወላጅ አልባ/ ሆነው ነው ያደጉት። ምናልባት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እርሣቸው እስኪያድጉ ድረስ ወላጆቻቸው በህይወት ቆይተው ቢሆን ኖሮ እኛ ፈፅሞ በማንወጣው መልኩ ለወላጆች መልካም መዋልን ባሣዩን ነበር። ለወላጅ መልካም መዋል ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በቃል እንጂ በተግባር አልደረሠንም። በተግባር ቢደርሰን ኖሮ የወላጅ ሀቅ ከመክበዱ የተነሣ ትግበራው ኢማናችን ይፈታተን ነበር። ያም ሆነ ይህ ወላጆቻችን በህይወት ያሉ እንደሆነ በተቻለን መጠን እነሱን በሚያስደስት መልኩ መልካም ነገር ልናደርግላቸው ይገባል። በህይወት የሌሉ እንደሆነም ለነርሱ ዱዓእ በማድረግ፣ ምህረትን በመለመን፣ ዘመዶቻቸውን በመቀጠል፣ ጓደኞቻቸው በመጠየቅና ሌሎች መልካም ሥራዎችን በነርሱ ሥም በመስራት ማስደሠት ይቻላል።

ለወላጅ መልካም መዋል ሁሌም መደረግ ያለበት ነገር ነው። ምንዳውም እጅግ ትልቅ ተፅእኖውም ከባድ ነው። ለወላጅ መልካም መዋል እጅግ አስፈላጊ ነገር በመሆኑ አላህ (ሱ.ወ) ቁርዓኑ ውስጥ ከአምልኮው ቀጥሎ አውስቶታል። አዞበታልም። እንዲህ በማለት

وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا إِمَّا يَبْلُغَنَّ عِندَكَ الْكِبَرَ أَحَدُهُمَا أَوْ كِلَاهُمَا فَلَا تَقُل لَّهُمَا أُفٍّ وَلَا تَنْهَرْهُمَا وَقُل لَّهُمَا قَوْلًا كَرِيمًا
 

“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው።” (አል-ኢስራእ 17፤፡ 23)

ኢማም ሀሠን ልበስሪ “አንድ ሰው የሱና ፆም በመፆም ላይ እያለ ወላጆቹ ፆሙን እንዲፈታ ጠይቀውት የታዘዛቸው እንደሆነ ሁለት ምንዳ ማለትም ለወላጅ የመታዘዝንና የፆም ምንዳን ያገኛል።” ይላሉ።

بروا آباءكم يبركم أبناؤكم

“ለወላጆቻችሁ መልካም ዋሉ ልጆቻችሁ መልካም ይውሉላችኋል። /ለእናት አባት ጥሩ ሁኑ ልጆቻችሁ ጥሩ ይሆኑላችኋል።/”

2 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here