ነጃሳን ማስወገድ (ጦሀራ – ክፍል 4)

0
5542

 1. አካልን እና ልብስን ንፁህ ማድረግ

ልብስ እና አካል ነጃሳ ከነካቸው የሚታይ ነጃሳ ከሆነ እስከሚለቅ ድረስ ማጠብ ግዴታ ይሆናል። ነጃሳን በማስለቀቅ ሂደት ውስጥ ዋናው መርህ ነጃሳው መኖሩን የሚጠቁሙ ቅሪቶችን፣ ጣዕምን፣ ቀለምን እና ሽታን ማስወገድ ነው። ነገርግን በሚገባ ከታጠበ በኋላ የማይለቅ ፋና ካለው ይቅር ይባላል። የሚታይ ካልሆነ (ሽንትን ይመስል) አንድ ጊዜ በማጠብም ቢሆን ንፁህ ይሆናል።

አስማእ ቢንት አቢበክር (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፦ አንዲት ሴት ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መጣች እና እንዲህ አለች፤ “አንዳችን ልብሷን የወር አበባ ይነካዋል። ምን ታድርገው?” የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ አሉ፦

تحته ثم تقرضه بالماء ، ثم تنضحه ثم تصلي فيه

“ትፈቅፍቀው፤ ከዚያም በውሃ ትሸው፤ ከዚያም ትስገድበት።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ነጃሳ የሴቶች ልብስን የእግር ጫፍ ከነካው መሬቱ ራሱ ንፁህ ያደርገዋል። ምክንያቱም አንዲት ሴት ኡሙ ሰለማን እንዲህ ብላ ጠየቀች፦

أن امرأة قالت لام سلمة رضي الله عنهما :  إني أطيل ذيلي وأمشي في المكان القذر ؟ فقالت لها : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : يطهره ما بعده (رواه أحمد وأبو داود) .

“እኔ የልብሴ የእግር ጫፍ ረዥም ሆኖ በቆሻሻ ስፍራ እራመዳለሁ (እንዴት ላድርግ)?” ኡሙ ሰለማም እንዲህ አሏት “የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘ከርሱ በኋላ ባለው ስፍራ ይፀዳል።’ ብለዋል።” (አሕመድ እና አቡዳውድ ዘግበውታል)

2. መሬትን ንፁህ ስለማድረግ

አንድን መሬት ነጃሳ ከነካው በርሱ ላይ ውሃ በማፍሰስ ይፀዳል።

በአቢሁረይራ ሐዲስ እንደተዘገበው አንድ ባላገር ተነሳና መስጂድ ውስጥ ሸና። ሰዎች ወደርሱ ተነሱና እላዩላይ ሊወድቁ ደረሱ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፦

دعوه وأريقوا على بوله سجلا من ماء أو ذنوبا من ماء ، فإنما بعثتم ميسرين ولم تبعثوا معسرين

“ተዉት በሽንቱ ላይ በባልዲ ውሃ ሞልታችሁ አፍሱበት። እናንተ አግራሪዎች ሆናችሁ ነው የተላካችሁት። አካባጅ ሆናችሁ አልተላካችሁም።” (ከሙስሊም ውጪ ያሉት ጀመዓዎች ዘግበውታል)

በተጨማሪም ከመሬት ጋር ዘውታሪ የሆኑ ነገሮች (ለምሳሌ፦ ዛፍ እና ግንብ) እላያቸው ላይ ያለው ነጃሳ በመድረቁ ጦሃራ ይሆናሉ አቡ ቂላባ እንዲህ ብለዋል፦ “መሬት መድረቁ ንፅህናው ነው።”

3. የቅቤ እና መሰል ነገሮች ንፅህና

ኢብኑ ዓባስ ከመይሙና እንደዘገቡት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቅቤ ላይ ስለወደቀች አይጥ ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል፦

ألقوها، وما حولها فاطرحوه وكلوا سمنكم

“እርሷን እና ከዙሪያዋ ያለውን ጣሉ። ከዚያም ቅቤያችሁን ብሉ።” (ቡኻሪይ ዘግበውታል)

4. የበክት ቆዳ ንፅህና

የበክት ቆዳ ውስጡም ሆነ ውጪው በመታረብ ይፀዳል። ምክንያቱም በኢብኑ አባስ ሀዲስ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦

إذا دبغ الاهاب فقد طهر

“ቆዳ የታረበ ጊዜ በእርግጥ ንጹህ ሆነ” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

5. የመስታወትን እና የመሰል ነገሮች ንፅህና

መስታወት፣ ቢላዋ፣ ሰይፍ፣ ጥፍር፣ አጥንት፣ ብርጭቆ እና ቅባት ያላቸው እና ውሃ የማይመጡ ለስላሳ እቃዎች በሙሉ የነጃሳውን ፋና በሚያስወግድ ነገር በማበስ ንፁህ ይሆናሉ። ሶሓባዎች ሰይፋቸውን ደም ከነካው በኋላ ተሸክመው ይሰግዱ ነበር። ደሙን በማበስ ይጠርጉትና በዚሁ ይብቃቁ ነበር።

6. የጫማ ንፅህና

ጫማ ሽፍንም ይሁን ክፍት የነጃሳው ፋና ከሌለበት መሬት ላይ በመታሸት ንፁህ ይሆናል። ምክንያቱም በአቡ ሁረይራ ሀዲስ ውስጥ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፦

إذا وطئ أحدكم بنعله الاذى فإن التراب له طهور

“አንዳችሁ በጫማው ቆሻሻ የረገጠ ከሆነ አፈር ንፁህ ያደርግለታል።” (አቡዳውድ ዘግበውታል)

ተጨማሪ ምክንያት ማንሳት ካለብንም እንዲህ እንላለን። ጫማ በነጃሳ በተደጋጋሚ የሚነካ ስፍራ ነው። ስለዚህ በደረቅ ነገር ማሸት ይበቃዋል። ልክ የኢስቲንጃ ቦታን ይመስላል። እንደውም ከእስቲንጃ ቦታም የበለጠ በተደጋጋሚ በነጃሳ ይነካል። ምክንያቱም የኢስቲንጃ ቦታዎች በነጃሳ የሚነኩት በቀን ሁለቴ ወይም ሶስቴ ብቻ ሊሆን ይችላል። ጫማ ግን ብዙ ጊዜ በነጃሳ የሚነካ ስፍራ ነው። ስለዚህ ንፅህናውን ማግራራት ተገቢ ይሆናል።

7. እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች

  1. የልብስ ማድረቂያ ገመድ ነጃሳ ልብስ ተሰጥቶበት ከዚያም በፀሀይ ወይም በንፋስ ከደረቀ በኋላ በርሱ ላይ ሌላ ንፁህ ልብስ ቢሰጣበት ችግር የለውም።
  2. አንዳች ነገር በሰውየው ላይ ከወደቀበት እና እርሱ ደግሞ ንፁህ ነገር ይሁን ሽንት መለየት ካልቻለ በላዩ ላይ የወደቀበት ነገር ምን እንደሆነ መጠየቅ ግዴታ አይሆንበትም። እርሱ ይህንን ተላልፎ ሰዎችን ቢጠይቅ እንኳን ተጠያቂዎቹ ነጃሳ እንዳረፈበት ቢያውቁም እንኳን መመለስ ግዴታ አይሆንበቸውም። ሰውየውም ያንን ቦታ ማጠብ ግዴታ አይሆንበትም።
  3. በለሊት እግር ወይም የልብስን የእግር ጫፍ ውሃ ይሁን ሽንት ያልተለየ እርጥብ ነገር ቢነካው ማሽተት እና ምን እንደነካው ለማወቅ መፈተሽ ግዴታ አይሆንበትም። ምክንያቱም ከዑመር እንደተዘገበው እርሳቸው (ኡመር) አንድ ቀን በመንገድ እያለፉ እንዳለ ከአሸንዳ የወረደ ነገር ፈሰሰባቸው። አብሯቸው የነበረ አንድ ባልደረባቸው ነበርና “አንተ ባለ አሸንዳ ውሃህ ንፁህ ነው ወይስ ነጃሳ?” አለ። ዑመርም “አንተ ባለ አሸንዳ አትንገረን።” ብለው ዝም አሰኝተውት አለፉ።
  4. የመንገድ ጭቃ የነካውን ነገር ማጠብ ግዴታ አይደለም። ኩሙይል ኢብኑ ዚያድ እንዲህ ይላሉ፦ “ዐሊይን በዝናብ ጭቃ ውስጥ ሲገቡ አየኋቸው። ከዚያም ወደ መስጂድ ገቡና ሰገዱ። እገራቸውምን አላጠቡትም።”
  5. ሰውየው ሶላቱን ካጠናቀቀ በኋላ ልብስ ወይም አካሉ ላይ ከዚህ ቀደም አይቶት የነበረ ነጃሳ ከተመለከተ፣ ወይም ነጃሳውን ያውቀው የነበረ ሆኖ ረስቶ ከሰገደበት፣ ወይም አልረሳትም፤ ነገርግን እርሷን ማስወገድ ካቃተው ሶላቱ ትክክል ነው። ምክንያቱም አላህ እንዲህ ይላል፦

وَلَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌ فِيمَا أَخْطَأْتُم بِهِ وَلَٰكِن مَّا تَعَمَّدَتْ قُلُوبُكُمْ  وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَّحِيمًا

“በእርሱ በተሳሳታችሁበት ነገርም በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም። ግን ልቦቻችሁ ዐውቀው በሠሩት (ኀጢአት አለባችሁ) አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።” (አል አህዛብ፤ 5)

  1. በተጨማሪም ይህ ብይን ሶሓባዎች እና ታቢዒዮች ፈትዋ የሰጡበት አቋም ነው።
  2. ከልብሱ ነጃሳ የነካው ስፍራ የተሰወረበት ሰው ሁሉንም ማጠብ ግዴታ ይሆንበታል። ምክንያቱም ልብሱን በሙሉ በማጠብ እንጂ የልብሱን ንፅህና ማረጋገጥ አይችልም። ስለዚህ “ግዴታ ነገር ያለርሱ የማይሟላበት ነገር እራሱም ዋጂብ (ግዴታ) ነው።” የሚለው የፊቅህ መርህ ውስጥ ይካተታል።
  3. ንፁህ ልብሶችን ከነጃሳ ልብስ ጋር ቢቀላቀሉ እና መለየት ካልተቻለ በእያንዳንዱ ልብስ አንዳንድ ጌዜ ይሰግዳል። ልክ እንደቂብላ ማለት ነው። የቂብላ አቅጣጫ የጠፋው ሰው በሁሉም አቅጣጫዎች አንድ አንድ ጊዜ ይሰግዳል። እንደተጨማሪ አማራጭም አንዱን ልብስ አጥቦ በርሱ መስገድም ይችላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here