ነጃሳ እና የነጃሳ አይነቶች (ጦሀራ – ክፍል 3)

0
9189

ነጃሳ ማለት፦ ሙስሊም ሊጠነቀቀው የሚገባ እና ሰውነቱን፣ አካሉን ወይም የሚሰግድበትን ቦታ ከነካ ሊያፀዳው የሚገባ ቆሻሻ ማለት ነው።

ኢስላም አንዳንድ ነገሮችን ነጃሳ ናቸው ብሎ ፈርጇል። ሙስሊሞችም እንዲጠነቀቋቸው አዟል። አካላቸውን፣ ልብሳቸውን፣ የሚቀመጡበትን ስፍራ፣ ለመብል እና ለመጠጥ የሚጠቀሙበትን ውሃ፣ ከትንሹም ሆነ ከትልቁ ሐደስ የሚፀዳዱበትን፣ ልብሳቸውን የሚያጥቡበትን፣ እቃዎቻቸውን እና መጣቀሚያቸውን የሚያፀዱበትን ውሃ ከእነዚህ ነጃሳዎች እንዲጠብቁም ግዴታ አድርጎ ደንግጓል።

እነዚህን ነጃሳዎች- ለማፅዳት ካልሆነ በስተቀር- መሸከምና መንካትም አይፈቀድም። ውሃ ውስጥ ገብተው ሽታውን፣ ጣዕሙን ወይም ቀለሙን ከለወጡ ውሃው- የፈለገ ቢበዛም- ይነጀሳል። ውሃው ጥቂት ከሆነም- እንደ አብዝሃ ዑለሞች እምነት- ሽታው፣ ጣዕሙ ወይም ቀለሙ ባይለወጥም እንኳ ይነጀሳል።

እነዚህ ነጃሳዎች ከፊሎቹ ከሰዎች አካል የሚወጡ ናቸው። ሽንት፣ ዓይነ-ምድር፣ መዝይ፣ ወድይ፣ የወር አበባ ደም፣ ከሰዎች የሚወጣ ብዛት ያለው ደም፣ ብዛት ያለው ትውከት እዚህ ላይ የሚጠቀሱ ናቸው።

አንዳንዶቹ ህይወት ካላቸው ነገሮች የሚወጡ ናቸው። ስጋቸው የሚበሉ እንስሳት ሽንት፣ ፋንዲያ፣ በህይወት ካለ እንስሳ ላይ የተቆረጠ አካል፣ የውሻ ጭላጭ… ተጠቃሽ ናቸው። አንዳንዶቹ እራሳቸው ህይወት ያላቸው ነገሮች ይሆናሉ። በክት እና የአሳማ ስጋ እዚህ ጋር ይነሳሉ። አንዳንዶቹ ፈሳሽ ነገሮች ናቸው- እንደ ብዙሃን ዑለሞች እምነት- ኸምር ዋነኛው ነው።

ማንኛውም ሰጋጅ ከነጃሳዎች ንፁህ መሆን አለበት። ከነጃሳ መጥራት ለአቅመ አዳም በደረሰ ሰው ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። ህፃናትን በዚህ ማሰልጠንም ግዴታ ነው። ሰባት አመት ሲሆኑ ጀምሮ በንፅህና ይታዘዛሉ። አስር አመት ሲሆናቸውም ይቀጣሉ። ያለ ንፅህና ሶላት ተቀባይነት የለውም።

አላህ እንዲህ ይላል፦

وَثِيَابَكَ فَطَهِّرْ

“ልብስህንም አጥራ።” (አል-ሙደሲር፤ 4)

የአላህ መልእክተኛም እንዲህ ይላሉ፦

الطهور شطر الإيمان

“ንፅህና የኢማን ግማሽ ነው።”

ስለነጃሳ ስናነሳ የምናብራራቸው ብዙ ነጥቦች አሉ። ከነዚህ መሀል ዋናዎቹን እንደሚከተለው እንተነትናለን፦

1. የነጃሳ አይነቶች

 1. በክት

ድንገት (ሳይታረድ) የሞተ ነገር ሁሉ አል-መይታ (ሙት) ይባላል። እንስሳት በህይወት ሳሉ የሚቆረጡ አካላቶቻቸውንም ቃሉ ያካትታቸዋል። ዋቂድ አል-ለይሲይ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል ይላሉ፦

( ما قطع من البهيمة وهي حية فهو ميت ) رواه أبو داود والترمذي وحسنه ، قال : والعمل على هذا عند أهل العلم .

“ከእንስሳ በህይወት እያለ የተቆረጠ አካል በክት ነው።” (አቡዉድ እና ቲርሚዚ ዘግበውታል። ደረጃውንም ሐሰን ብለውታል።) ብዙ የዒልም ሰዎች ጋር በዚህ ሐዲስ ይሠራል።

እዚህ ላይ የምናወጣቸው ፍልቅታዎች (exceptions) ይኖራሉ፦

 • አሳ እና አንበጣ፦

እነዚህ ንፁህ ናቸው። የእነዚህን ሙታን የለየንበት ምክንያት የዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) ሐዲስ ነው፦ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፦

لحديث ابن عمر رضي الله عنهما قال : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : أحل لنا ميتتان ودمان : أما الميتتان فالحوت والجراد ، وأما الدمان فالكبد والطحال ) رواه أحمد والشافعي وابن ماجة والبيهقي والدار قطني.

“ሁለት በክቶች እና ሁለት ደሞች ተፈቀዱልን። በክቶቹ ዓሳ እና አንበጣ ናቸው። ደሞቹ ደግሞ ጉበትና ጣፊያ ናቸው።” (አሕመድ፣ ሻፊዒይ፣ ኢብኑ ማጀህ፣ በይሃቂይ እና ዳረቁጥኒይ ዘግበውታል። ሐዲሱ ደካማ ነው። ኢማም አሕመድ ሐዲሱ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ባልደረቦች ላይ በቆመበት (መውቁፍ በሆነበት) ሁኔታ ሰሒሕ ነው ብለዋል።)

 • ጉንዳን፣ ንብ፣ ዝንብ እና የመሳሰሉ ፈሳሽ ደም የሌላቸው ነፍሳት ሙት አካል፦

ጉንዳን፣ ንብ፣ ዝንብ እና የመሳሰሉ ፈሳሽ ደም የሌላቸው ነፍሳት ሙት አካል ፈሳሽ ነገሮች ውስጥ ቢገባ ንፁህ ነው፤ አይነጅስም። ኢብኑል-ሙንዚር እንዲህ ይላሉ፦ “እነዚህ ነገሮች ንፁህ መሆናቸው ላይ ልዩነቶችን አላውቅም። ከሻፊዒይ ብቻ የተዘገበ ወሬ አልለ። መዝሃባቸው ላይ የሚታወቀው የእነዚህ ነፍሳት ሙት አካል ነጃሳ ነው፤ ፈሳሽ ነገሮች ላይ ከገባ ግን እስካልቀየረው ድረስ ይቅር ይባላል የሚለው አቋማቸው ነው።

 • የሙት አጥንት፣ ቀንዱ፣ ፀጉሩ፣ ጥፍሩ፣ ላባው እና ቆዳው

እነዚህ ሁሉ ንፁህ (ጦሃራ) ናቸው። ምክንያቱም የነዚህ ነገሮች መሠረት ንፁህ መሆናቸው ነው። ነጃሳ ለመሆናቸው መረጃ አስካልመጣ ድረስ ንፁህ መሆናቸውን እንፈርዳለን። አል-ዙህሪይ እንዲህ ይላሉ፦ “ዝሆንን የመሰሉ የሙታንን አጥንት አስመልክቶ “አንዳንድ የሠለፍ ሰዎች ፀጉራቸውን ሲሞሸጡበት እና ቅባት ሲቀባቡበት አይቻለሁ። በዚህም ላይ ችግር አለ ብለው አያምኑም።” ቡኻሪ ዘግበውታል።

ኢብኑ ዐባስ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላሉ፦

وعن ابن عباس رضي الله عنهما قال: تصدق على مولاة لميمونة بشاة فماتت ، فمر بها رسول الله صلى الله عليه وسلم فقال: ( وهلا أخذتم إهابها فدبغتموه فانتفعم به ؟  فقالوا : إنها ميتة ، فقال : (إنما حرم أكلها ) رواه الجماعة

“ለመይሙና ባርያ አንዲት ፍየል ምፅዋት ተሰጣት እና ሞተችባት። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በነርሱ በኩል ሲያልፉ እንዲህ አሉ፦ “ቆዳዋን ወስዳችሁ አርባችሁት አትጠቀሙበትም?!” ሰዎቹም፦ “እርሷኮ የሞተች ናት!” አሉ። “መብላቱ ነው የተከለከለው!” አሉ። (ጀመዓዎቹ ዘግበውታል)

 1. ደም

ከታረደ ከብት እንደሚፈስ ደም- ብዙ ሆኖ የሚፈስም ሆነ- የወር አበባ ደም ሁሉም አይነት ደም ነጃሳ ነው። ነገር ግን ጥቂት ከሆነ ይቅር ይባላል።

ስለዚህ የአላህ ንግግር ማብራሪያ ከኢብኑ ጁረይጅ እንዲህ የሚል ተዘግቧል፦

“አል-መስፉሕ” ማለት የሚያፈሱት ደም ማለት ነው። በጅማት ውስጥ የሚገኘው ደም ችግር የለበትም።” (ኢብኑልሙንዚር ዘግበውታል)

ከአዒሻ እንደተዘገበውም እንዲህ ይላሉ፦ “ድስጣችን ላይ የደም ምልክት እያለው ስጋ እንበላ ነበር።”

አልሐሰን እንዲህ ይላሉ፦ “ሙስሊሞች ከነቁስላቸው መስገዳቸውን አላቆሙም።” (ቡኻሪይ ዘግበውታል)

ዑመር (ረ.ዐ.) ደማቸው እየፈሰሰ እንደሰገዱ የሚያረጋግጥ ዘገባም ተገኝቷል። አል-ሐፊዝ ፈትሕ ላይ እንዲህ ብለዋል። አቡሁረይራ (ረ.ዐ.) ሁለት ወይም ሦስት ጠብታ የሆነ ደም ሶላት ውስጥ ችግር የለውም ብለው ያምናሉ።

 1. የአሳማ ስጋ

قُل لَّا أَجِدُ فِي مَا أُوحِيَ إِلَيَّ مُحَرَّمًا عَلَىٰ طَاعِمٍ يَطْعَمُهُ إِلَّا أَن يَكُونَ مَيْتَةً أَوْ دَمًا مَّسْفُوحًا أَوْ لَحْمَ خِنزِيرٍ فَإِنَّهُ رِجْسٌ أَوْ فِسْقًا أُهِلَّ لِغَيْرِ اللَّهِ بِهِ 

“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፦ «ወደእኔ በተወረደው ውስጥ በክት ወይም ፈሳሽ ደም ወይም የአሳማ ስጋ እርሱ ርኩስ ነውና ወይም በአመጽ ከአላህ ስም ሌላ በእርሱ ላይ የተወሳበት ካልኾነ በስተቀር በሚመገበው ተመጋቢ ላይ እርም የኾነን ነገር አላገኝም።” (ሱረቱል አንዓም፤ 145)

 1. የሠዎች ትውከት፣ ሽንታቸው እና ዓይነምድር

እነዚህ ነገሮች ነጃሳ ስለመሆናቸው የዑለሞች ስምምነት አለ። ትንሽ ትውከት ይቅር ይባላል። ከእናቱ ወተት ውጭ ሌላ ምግብ የማይመገብ የህፃን ወንድ ሽንትም እንደቀላል ነጃሳ ይቆጠራል። እርሱ ከነካን ውሃ እላዩ ላይ በመርጨት ብቻ መብቃቃት ይቻላል። ይህን ያልነው በዓሊይ ሐዲስ ላይ ተመርኩዘን ነው።

وعن علي رضي الله عنه قال : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم ( بول الغلام ينضح عليه ، وبول الجارية يغسل )

ከዓሊይ (ረ.ዐ.) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ አሉ፦ “የወንድ ህፃን ልጅ ሽንት በውሃ ይረጫል። የህፃን ሴት ልጅ ሽንት ይታጠባል።”

ቀታዳ እንዲህ ይላሉ፦ “ይህ ምግብ ያልተመገቡ እንደሆነ ነው። ምግብ መመገብ የጀመሩ ከሆነ ግን ሽንታቸው ይታጠባል።” አሕመድ ዘግበውታል። ይህ የአሕመድ ቃል ነው። ከነሳኢይ በቀር አስሓቡ ሱነኖችም ዘግበውታል።

አል-ሐፊዝ ፈትህ ላይ እንዲህ ይላሉ፦ “ሰነዱ ሶሒሕ ነው።” ምናልባት የወንዱ ከሴቷ ሽንት የተለየው ሰዎች አብዝተው ስለሚሸከሙትና ሽንቱም ሰፊ ቦታ ላይ የመረጨት ባህሪ ስላለው ለሰዎች ለማቅለል ተብሎ ነው። አላህ የተሻለውን ያውቃል!

 1. አል-ወድይ

እንደ ነጭ ውሃ ነው። ሙቅ ነው። ከሽንት በኋላ ይወጣል። ነጃሳ ለመሆኑ በዑለሞች መሀል ምንም አይነት ልዩነት የለም።

قالت عائشة : وأما الودي فإنه يكون بعد البول فيغسل ذكره وأنثييه ويتوضأ ولا يغتسل ، ورواه ابن المنذر.

አዒሻ እንዲህ ይላሉ፦ “ወድይ ከሽንት በኋላ የሚወጣ ፈሳሽ ነው። ነጃሳ ነው። ስለዚህ ብልቱን እና ፍሬዎቹን ያጥባቸዋል። ዉዱእ ማድረግም አለበት። ነገር ግን ሙሉ የገላ ትጥበት ግዴታ አይደለም።” (ኢብኑል ሙንዚር ዘግበውታል)

 1. አል-መዝይ

እንደ ነጭ ውሃ ነው። ለዛዛ ነው፤ እርስ በራሱ ይሳሳባል። ወሲብ በሚታሰብበት ወይም መቅድሙ በሚካሄድበት ጊዜ የሚወጣ ፈሳሽ ነው። በሚወጣበት ጊዜ ሰውየው ልብ ላይለው ይችላል። ይህ ፈሳሽ ከወንድም ከሴትም ይገኛል። ሴቶች ላይ ግን ይበዛል። ዑለሞች ሁሉ ነጃሳ እንደሆነ ተስማምተዋል። ነገር ግን አካልን ከነካ ማጠብ ግዴታ ይሆናል፤ ልብስን ከነካ ደግሞ ውሃ እላዩ ላይ ማፍሰስ ይበቃል። ይህን ያልነው እንዲህ አይነቱን ነጃሳ መጠንቀቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ምክንያቱም ብዙ ላጤ ወንዶች የሚቸገሩበት ልብሳቸው ላይ አብዝቶ የሚከሰት ነው። ስለዚህ ከህፃን ወንድ ልጅ ሽንት በላይ እንደ ቀላል ነጃሳ ሊታሰብ ይገባዋል።

ዓሊይ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላሉ፦ “እኔ መዝይ የሚበዛብኝ ሰው ነበርኩ። ልጃቸው እኔጋር ስለነበረች (ስላገባኋት) አንድን ሰው ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲጠይቅ አዘዝኩት፡: እንዲህ አሉ፦

توضأ واغسل ذكرك

“ዉዱእ አድርግ፤ ብልትህንም እጠብ።” (ቡኻሪና ሌሎችም ዘግበውታል)

 1. መንይ (ፍትወት)

አንዳንድ ዑለሞች ፍትወት ነጃሳ እንደሆነ ያምናሉ። የተሻለው አቋም ግን ንፁህ መሆኑ ነው። ነገርግን እርጥብ ከሆነ ማጠብ ይወደዳል። ደረቅ ከሆነ ደግሞ መፈግፈግ ይመረጣል።

አዒሻ እንዲህ ይላሉ፦ “መንይን ደረቅ ከሆነ እፈገፍገው ነበር። እርጥብ ከሆነ ደግሞ አጥበው ነበር።” (ዳረቁጥኒይ አቡዐዋና እና በዛር ዘግበውታል)

وعن ابن عباس رضي الله عنهما قال : سئل النبي صلى الله عليه وسلم عن المني يصيب الثوب ؟

ኢብኑ ዐባስ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይላሉ፦ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ልብስን ስለሚነካ ፍትወት ተጠየቁ። እንዲህ ብለው መለሱ፦

إنما هو بمنزلة المخاط والبصاق ، وإنما يكفيك أن تمسحه بخرقة أو بإذخرة  رواه الدار قطني والبيهقي والطحاوي ، والحديث قد اختلف في رفعه ووقفه .

“እርሱ እኮ እንደ ንፍጥ እና አክታ ነው። በጨርቅ ወይም በሰንበሌጥ ማበስ ይበቃሃል።” (ዳረቁጥኒይ፣ በይሃቂይ እና ጠሓዊይ ዘግበውታል። ሐዲሱ መርፉዕ ወይም መቅቁፍ መሆኑ ላይ ልዩነት አልለ።)

 1. ስጋቸው የማይበላ እንስሳት ሽንት እና ፋንዲያ

እነዚህ ነጃሳ ናቸው። የዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ሐዲስ ይህን ያረጋግጣል። እንዲህ ይላሉ፦

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ሽንት ቤት ሄዱና ሦስት ድንጋይ እንዳመጣ አዘዙኝ። ሁለት ድንጋዮች አገኘሁኝ፤ ሦስተኛ አጣሁ። ፋንዲያ ያዝኩኝ ይዤ መጣሁ። ሁለቱን ድንጋዮች ያዙና፦

هذا رجس

“ይህ ነጃሳ ነው።” ብለው ፋንዲያውን ጣሉት።” (ቡኻሪይ ኢብኑ ማጀህ እና ኢብኑ ኹዘይማ ዘግበውታል።) በሌላ ዘገባ እንዲህ የሚል ጨምረዋል፦

إنها ركس إنها روثة حمار

“እርሷ ነጃሳ ናት፤ የአህያ ፋንዲያ ናት።” አሉ።

ስጋቸው የማይበላ የእንስሳት ሽንት ጥቂት ከሆነ ይቅር ይባላል። ይቅር የተባለውም ለመጠንቀቅ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። አል-ወሊድ ኢብኑ ሙስሊም አውዛዒይን ጠየቅኳቸው ይሉናል። “ስለ ስጋቸው ስለማይበሉ እንደ በቅሎ፣ አህያ እና ፈረስ ያሉ እንስሳት ጠየኩኝ።” እርሳቸውም እንዲህ አሉኝ “ሰዎቹ በየዘመቻቸው ሁሉ በዚህ ይፈተኑ ነበር። ከልብሳቸውም ይሁን ከአካላቸው አያጥቡትም ነበር።”

ስጋቸው የሚበሉ እንስሳት ሽንትን አስመልክቶ ማሊክ እና አሕመድ እንዲሁም የተወሰኑ ሻፊዒዮች ንፁህ ነው የሚል ብይን ሰጥተዋል። ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ይላሉ፦ “ነጃሳ ነው ብሎ የወሰነ ማንም ሶሓባ የለም። ነጃሳ ነው ብሎ ማሰብ እራሱ አዲስ ንግግር ነው። ከሶሓባ (ንግግር) የቀደመው የለም።”

አነስ (ረ.ዐ.) እንዲህ አሉ፦ “ከዑክል እና ከዑረይና ሠዎች መጡ። ከዚያም መዲና አልተስማማቸውም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ግመሎችን አዘዙላቸው። ወተቶቻቸውንና ሽንቶቻቸውን እንዲጠጡ አዘዙ።” (አሕመድ እና ሁለቱ ሸይኾች፤ ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

 1. አል ጀላላህ (ነጃሳ የተቀለበች እንስሳ)

ሐዲስ ላይ የጀላላህን ስጋ መመገብም ሆነ ወተቷን መጠጣት የሚከለክል ዘገባ መጥቷል።

ከአብዱላህ ቢን አባስ እንደተዘገበው “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የጀላላን ወተት መጠጣት ከልክለዋል” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)። ዐምር ቢን ሹዐይብ ከአባታቸው እና ከአያታቸው እንደዘገቡት “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የቤት አህያን ስጋ ከልክለዋል። ጀላላንም ከመጋለብና ስጋዋን ከመብላት ከልክለዋል።” (አህመድ፣ ነሳዒን እና አቡዳውድ ዘግበውታል) አልጀላላህ ማለት ብዙ ጌዜ ሽታዋ እስከሚቀየር ድረስ ዓይነምድር የምትመገብ እንስሳ ናት። ግመል፣ ከብት፣ ፍየል፣ ዶሮ ወይም ሌላ። ነገር ግን ለተወሰነ ጌዜ ከዓይነምድር አርቀው ካሰሯት፣ ንፁህ ምግብ ከተቀበለች እና ስጋዋን ንፁህ ከሆነ ስጋዋ ሐላል ይሆናል። ምክንያቱም ስጋዋ እርም የሖነበት ምክንያት ተነስቶላታል።

 1. ኸምር (አልኮል)

ብዙ ዑለሞች ጋር አልኮል ነጃሳ ነው። እንደማስረጃ ተከታዩን አንቀፅ ይጠቀማሉ።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّمَا الْخَمْرُ وَالْمَيْسِرُ وَالْأَنصَابُ وَالْأَزْلَامُ رِجْسٌ مِّنْ عَمَلِ الشَّيْطَانِ فَاجْتَنِبُوهُ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው። (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና።” (አል ማኢዳ፤ 90)

 1. ውሻ

ውሻ ነጃሳ ነው። እርሱ የተጎነጨውን ሰባት ጌዜ ማጠብ ግዴታ ነው። ከሰባቱ አንዱ በአፈር መሆኑም የግድ ነው። ምክንያቱም አቡሁረይራ በሐዲሳቸው እንዲህ ብለዋል።

طهور إناء أحدكم إذا ولغ فيه الكلب أن يغسله سبع مرات أولاهن بالتراب

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፦ “የአንዳችሁ እቃ ውሻ ከተጎነጨበት ንፁህ የሚሆነው ሰባት ጊዜ በማጠብ ነው። ከሰባቱ አንዱ በአፈር መሆን አለበት።” (ሙስሊም፣ አሕመድ፣ አቡዳዉድ እና በይሃቂይ ዘግበውታል)

ደረቅ ምግብን የነካ እንደሆነ የነካውን እና ከዙሪያው ያለውን ይጥልና በቀረው ይጠቀምበታል። ምክንያቱም በመሰረቱ ንፁህ በመሆኑ አሁንም ንፁህ እንደሆነ ይታሰባል። የውሻ ፀጉርን አስመልክቶ ትክክለኛው አስተሳሰብ ጦሃራ ነው የሚለው ነው። ነጃሳ መሆኑን የሚያስፈርድ አንድም ማስረጃ የለም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here