ልዩ የረመዳን መገለጫዎች

0
6501

የወሮች ቁንጮ የሆነውና ታላላቅ ችሮታዎችን ጠቅልሎ የያዘው የረመዳን ወር ከነሙሉ ስጦታው ገብቷል። ታላላቅ ትሩፋቶችን አዝሎ በአላህ ፀጋዎች ደምቆ ልቦቻችንን በብርሀኑ እየሞላ ይገኛል…፤ በመሰረቱ የረመዳን ወር በሙስሊሞች ልብ ውስጥ ምን ያህል ታላቅ ቦታ እንዳለው ለማንም ድብቅ አይደለም፤ አዎ! ረመዳን የእዝነት፣ የምህረትና ከእሳት ነፃ መውጫ ወር ነው፤ በዚህ ወር ብዙ ስጦታዎችና ልግስናዎች ከአላህ (ሱ.ወ) ዘንድ ወደ ባሮቹ ይንቧቧሉ። ከዚህ ቀጥለን ይህ ወር ከሌሎች ወራት የሚለይባቸውን መሰረታዊ ነጥቦች እንመለከታለን።

የረመዳን ወር መለያዎች

1. የኢስላም ማዕዘን፡- የረመዳን ወር ከኢስላም ማዕዘናት አንዱ የሆነውን ግዴታ የተደረገብንን ፆም የምንተገብርበት ወር ነው። የማንኛውም ሰው እስልምና ሊሟላ የሚችለው ረመዳንን ሲፆም ነው፤ የረመዳንን ግዴታነት የሚክድ ሰው ካፊር ይሆናል (ከኢስላም ይወጣል)፤ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ
 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።” (አል-በቀራ 2፤ 183)

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- “ኢስላም በአምስት ነገሮች ላይ ተገነባ፤ የአላህን ብቸኛ አምላክነትና የሙሀመድን የአላህ መልክተኝነት መመስከር፤ ሶላትን መስገድ፤ ዘካን መስጠት፤ ረመዳንን መፆም፤ የተከበረውን ቤት መጎብኘት (ሐጅ ማድረግ)።” (ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል)።

2. የቁርአን መውረድ፡- ከረመዳን ወር መለያዎች አንዱ አላህ (ሱ.ወ) ቁርአንን በሱ ውስጥ ማውረዱ ነው፤ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِّنَ الْهُدَىٰ وَالْفُرْقَانِ
 

“(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው።” (አል-በቀራ 2፤ 185)

ቁርዐን የዚህች ኡማ የህይዎት መመሪያ ነው፤ እሱ ግልጽ የሆነ መፅሐፍና ቀጥተኛ መንገድ ነው፤ በሱ ውስጥ ቃል ኪዳን፣ ዛቻና ማስፈራሪያ አለበት፤ ቁርዐን ለያዘውና ለተገበረው የቅናቻ መንገድ ነው፤ ለሠራበትና ሐላሉን (የተፈቀደውን) ተጠቅሞ ሐራሙን (ክልከላውን) ለራቀ ብርሃን ነው፤ በእውነትና ውሸት መካከል የሚለየው እሱ ነው፤ እሱ ቧልት ሳይሆን ጥብቅ (ምር) ቃል ነው፤ ስለዚህ እኛ ሙስሊሞች ይህን የጌታችንን መጽሐፍ በማንበብ፣ በመሀፈዝ /በቃል በመሸምደድ/፣ ትርጉሙን በመረዳት፣ በማስተንተንና በተግባር ላይ በማዋል ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል።

3. የሰይጣን መታሰር፡- በረመዳን ወር የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ የገሀነም በሮች ይዘጋሉ፤ አመፀኛ ሰይጣናትም ይታሰራሉ፤ በፊት ይደርሱበት የነበረው ቦታ መድረስ አይችሉም፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إذا دخل رمضان فتحت أبواب السماء، وغلقت أبواب جهنم، وسلسلت الشياطين وفي روايةإذا جاء رمضان فتحت أبواب الجنة

“ረመዳን ሲገባ የሰማይ በሮች ይከፈታሉ፤ የገሀነም በሮች ይዘጋሉ፤ ሰይጣናትም ይቀፈደዳሉ።” በሌላ ዘገባም “ረመዳን ሲመጣ የጀነት በሮች ይከፈታሉ” ብለዋል (ቡኻሪ ዘግበውታል)

4. የስራዎች ምንዳ መደራረብ፡- በረመዳን ወር የሐሰናት (የመልካም ሥራዎች) ምንዳ እጥፍ ድርብ ይሆናል፤ በረመዳን የሚሰሩ ኸይር ስራዎች ከሌላው ጊዜ የበለጠ ምንዳ ይኖራቸዋል፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ከሰደቃ በላጩ የትኛው ነው ተብሎ ሲጠየቁ “በረመዳን የሚደረግ” ሲሉ መልሰዋል (ቲርሚዚይ ዘግበውታል)።

5. ፆመኛ ማስፈጠር፡- በረመዳን ወር ፆመኛ ያስፈጠረ (ፆም ያስፈታ) ከጿሚው ምንዳ ምንም ሳይጎድል እሱ የሚያገኘውን የሚያክል ምንዳ ያገኛል፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ:-

من فطر صائماً فله مثل أجره من غير أن ينقص من أجر الصائم شيء

“ፆመኛን ያስፈጠረ ሰው የፆመኛው ምንዳ ምንም ሳይነካ የፆመኛውን ያክል ምንዳ አለው።” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)።

6. ከአንድ ሺህ ሌሊቶች በላጭ የሆነቸው “የለይለተል-ቀድር” በውስጥ መገኘት፡- ይህች ሌሊት አላህ (ሱ.ወ) በአመቱ የሚከሰቱ ጉዳዮችን የሚጽፍባት የተባረከች ሌሊት ናት። ከአንድ ሺህ ሌሊቶችም በላጭ ናት

لَيْلَةُ الْقَدْرِ خَيْرٌ مِّنْ أَلْفِ شَهْرٍ
 

“መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺሕ ወር በላጭ ናት።” (አል-ቀድር 97፤ 3)

የሷን አጅር (ምንዳ) የተከለከለ ሰው በዙ ኸይር (ትሩፋት) ነገር አልፎታል፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

فيه ليلة خير من ألف شهر، من حرم خيرها فقد حرم

“በሱ (በረመዳን) ከአንድ ሺህ ሌሊቶች የምትበልጥ ሌሊት አለች፤ የሷን ትሩፋት የተከለከለ (ያላገኘ) ሰው በእርግጥም ተከልክሏል” (ሰሂህ- አህመድና ነሳኢይ ዘግበውታል)።

በዛች ለሊት በሙሉ እምነትና ምንዳዋን አስቦ የቆመ (ሌሊቱን በኢባዳ ያሳለፈ) ሰው ያለፈውን ወንጀሉን አላህ (ሱ.ወ) ይምርለታል፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من قام ليلة القدر إيماناً واحتساباً غفر له ما تقدم من ذنبه

“ለይለተል ቀድርን ሙሉ እምነት አሳድሮና ምንዳዋን አስቦ የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።

በሌላ አህመድ በዘገቡት ሐዲስም:-

من قامها إبتغاءها، ثم وقعت له، غفر له ما تقدم من ذنبه وما تأخر

“እሷን ፈልጎ የቆመና ያጋጠመችው ሰው ያለፈውና የሚመጣው ወንጀሉ ይማርለታል” ተብሏል።

ይህ በትንሽ ስራ ብዙና ግዙፍ ምንዳ ማግኘት የሰማዩም የመሬቱም ካዝና በጁ የሆነው ጌታ ትሩፋት ነው፤ ምስጋናና መመፃደቅ ለአላህ ብቻ ናቸው።

7. መላአክት በብዛት ወደ መሬት መውረድ፡-አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

تَنَزَّلُ الْمَلَائِكَةُ وَالرُّوحُ فِيهَا بِإِذْنِ رَبِّهِم مِّن كُلِّ أَمْرٍ
 

“በርሷ ውስጥ መላእክትና መንፈሱ በጌታቸው ፈቃድ በነገሩ ሁሉ ይወርዳሉ።” (አል-ቀድር 97፤ 4)

8. የሱሁር (የሌሊት ምግብ)፡- ሱሁር መብላት የዚህችን ኡማ የፆም ሥርዓት ካለፉት ህዝቦች የሚለይ ሲሆን በውስጡ ብዙ ኸይር ነገር ይዟል፤ ይህንንም ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ በማለት ገልፀውልናል፡- “በኛና በመጽሐፍት ባልተቤቶች ፆም መካከል ያለው ልዩነት ሱሁር መብላት ነው” (ሙስሊም ዘግበውታል)። በሌላ ቡኻሪና ሙስሊም በተስማሙበት ሐዲስ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ)

تسحروا فإن في السحور بركة

“ሱሁር ብሉ፤ ስሁር መብላት በረካ አለውና” ሲሉ ተናግረዋል (ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል)።

9. የዑምራ ትሩፋት፡- በረመዳን ወር የሚሰራ ዑምራ ከነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ሐጅ ማድረግ ጋር ይስተካከላል፤ ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ)

عمرة في رمضان تعدل حجة أو قال حجة معي

“በረመዳን የሚደረግ ዑምራ ከሐጅ ጋር እኩል ነው፤ ወይም ከኔ ጋር ከሚሰራ ሐጅ ጋር እኩል ነው” ብለዋል።

10. ወንጀል ማበሻ፡- ረመዳን ወንጀል እንዲታበስ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች አንዱና መሰረታዊው ነው፤ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

الصلوات الخمس، والجمعة إلى الجمعة، ورمضان الى رمضان مكفرات لما بينهن إذا اجتنبت الكبائر

“ታላላቅ ወንጀሎች ከተራቁ፤ አምስት ወቅት ሶላቶች፣ ከጁምዓ እስከ ጁምዓ፣ ከረመዳን እሰከ ረመዳን በመካከላቸው ያለውን ወንጀል ያብሳሉ” (ሙስሊም ዘግበውታል)።

11. የተራዊህ ሰላት፡- በረመዳን ወር ብቻ በጀመዓ የሚሰገደው የ“ተራዊህ” ሶላት አንዱ የረመዳን መለያ ነው፤ ተራዊህ ሶላትን ለመስገድ ሙስሊምች ወንዶችም ሴቶችም በአላህ ቤት መስጂድ ይሰባሰባሉ፤ ከረመዳን ውጭ ግን ይህን ሶላት ተሰባስበው በአንድነት አይሰግዱም።

12. ቸርነት፡- ሰዎች በረመዳን ወር የበለጥ ቸርነታቸው ይጭምራል፤ ይህ በተጨባጭ የሚታይ ጉዳይ ነው፤ ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት:-

كان النبي أجود الناس، وكان أجود ما يكون في رمضان

“ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ለጋስ ነበሩ፤ በጣም የሚለግሱት ደግሞ በረመዳን ወር ነበር።”

13. የመስጊዶች መሙላት፡- በረመዳን ወር መስጊዶች በአማኞች ይጣበባሉ፣ በተለያዩ የኢባዳ አይነቶች ህያው ይደረጋሉ፤ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሰዎች በጀማዐም በግልም መስጊድን ያዘወትራሉ።

14. የበድር ድል፡- ሌላው የረመዳንን ወር ለየት የሚያደርገው ጉዳይ ታለቁ የበድር ዘመቻ በረመዳን ውስጥ መደረጉ ነው፤ የበድር ዘመቻ መላኢኮች ከሙእሚኖች ጎን ተሰልፈው ካፊሮችን ለመዋጋት የወረዱበትና ሙእሚኖች ታላቅ ድል የተቀናጁበት ሙሽሪኮች (የመካ አጋሪዎች) ደግሞ ክፉኛ የተሸነፉበት ታላቅ ቀን ነው፤ አምላካችን አላህ የጠንካራ ሐይል ባለቤት ነው።

15. የመካ መከፈት፡- ቅዱሷን ከተማ መካ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ከሙሽሪኮች እጅና ከጣዖት አምልኮት ነፃ ያወጡበትና የኢስላም ብርሃን ወደ ምስራቅም ምዕራብም እንዲፈነጥቅ ሁኔታዎችን ያመቻቸው ትልቁ ድል “የመካ መከፈት” (ፈትሁ መካ) በዚሁ በረመዳን ወር ነበር የተገኘው። ከመካ መከፈት በኋላ አላህ (ሱ.ወ) ለመልክተኛው ድል ስለሰጣቸው ሰዎች በፍቃዳቸው በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ አላህ ሀይማኖት ኢስላም ይገቡ ጀመር፤ ነቢያችንም (ሰ.ዐ.ወ) በመካ የነበረውን ጣዖት አምላኪነት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠፉት፤ መካም የኢስላም ሀገር ሆነች፤ ከዚህ በኋላ ኢስላም በሁሉም አካባቢዎች ተሰራጨ።

ይህን የተለየና በረከቱና ስጦታው የበዛ ወር እኛ ሙስሊሞች ጊዜያቱን በሞላ በሚጠቅመን ነገር ላይ ማሳለፍ ይገባናል፤ በዚህም መሰረት በዚህ ወር ትኩረት ሰጥተን ልንቀሳቀስባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነጥቦች እንደሚከተለው ተዘርዝሯል:-

የረመዳን ወር የትኩረት አቅጣጫዎች

  1. ልቦናዎች የሚደብቁትን ሁሉ የሚያየውና የሚያውቀው አላህ (ሱ.ወ) የኢማናችንን ጥንካሬ በዚህ ፆም ሊፈትነን እንደፈለገ በመገንዘብ ከፍተኝ ትኩረት መስጠት፤
  2. ረመዳንን ስንፆም በኒያ (አስበንና ወስነን) መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ያለ ኒያ የፆመ ሰው ምንዳ የለውምና።
  3. ቀኑን በሙሉ በመኝታ ከማሳለፍ መቆጠብ አለበን።
  4. ቁርኣንን ከሌላው ጊዜ በተሻለ በብዛት መቅራት አለብን።
  5. ከፈጣሪያችን ጋር ተውባ (ወደሱ መመለስ) ማደስ ያስፈልጋል።
  6. የረመዳንን ሌሊቶች በጫወታና ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች ከማሳለፍ መቆጠብ አለብን።
  7. በረመዳን ወር ዱዓ፣ ከአላህ ማህርታ መጠየቅና ወደሱ መዋደቅ ማብዛት አለብን።
  8. አምስት ወቅት ሶላቶችን በመስጂድ ጀመዐ ጠብቀን መስገድ ያስፈልጋል።
  9. ሙሉ አካላችን አላህ (ሱ.ወ) ከከለከላቸው ነገሮች በመቆጠብ መፆም ይኖርባታል።

ቁርኣን የወረደበት የረመዳን ወር ይህ ነው፤ ይህ ወር ከጀነት የሚቀረብበትና ከእሳት የሚራቅበት ጊዜ ነው። እድሜህን ሁሉ ያለ ኢባዳ ያባከንክ፣ በረመዳንና በሌላውም ጊዜ ከኢባዳ ወደ ኋላ የቀረህ፣ ዛሬ ነገ እያልክ በቀጠሮ ወደ አላህ መመለስን ያዘገየህ፣ ረመዳንንና ቁርኣንን በቸልተኝነት እያለፍክ ያለህ ሰው ሆይ! እስኪ በአላህ ይሁንብህ ንገረኛ እስከመቼ በንዲህ አይነት ህይወት ትቀጥላለህ? አይቀሬው ሞት ድንገት ከተፍ ቢል ጌታህ ፊት ምን ይዘህ ትቀርባለህ?… ከወዲሁ ቆም ብለህ ልታስብበት ይገባል!

በተከበረው ረመዳን ከምግብ ብቻ ተከልክለህ አይንህን፣ አንደበትህንና አጠቃላይ ውሎህን ያልገራሀው ወንድሜ ሆይ! ድካምህ በከንቱ እንዳይቀር እያሰብክበት ነውን? ስንት ፆመኛ አለ ከፆሙ ራሀብንና ጥምን እንጅ የማያተርፍ! ስንት ሰጋጅ አለ ከሶላቱ እንቅልፍ ማጣትና ድካምን እንጅ ሌላ የማያተርፍ! ማንኛውም ከመጥፎ ተግባርና ከወንጅል የማይከለክል ቂያም (የሌሊት ሶላት) ለባለቤቱ ከአላህ መራቅ እንጂ ሌላን አይጨምረውም፤ እንደዚሁም ማንኛውም ከሐራም የማይከለክል ፆም ለባለቤቱ መጠላትንና መከልከልን እንጂ አይጨምረውም።

ሰዎች ሆይ! የአላህን ተጣሪ ሲሰሙ ፈጣን ምላሽ ከሚሰጡ፣ የአላህ አንቀፆች ሲነበቡላቸው ልባቸው ጥርት ከሚል ሰዎች፣ ሲፆሙ ደግሞ ምላሳቸው፣ ጆሯቸውና አይኖቻቻው ከሚፆሙ ሰዎች አኳያ እኛ የት ነው ያለነው? በነሱ ፈለግ ልንከተል አይገባምን? ያአላህ! ሁኔታችንን ወደ አንተ አቤት እንላለን፤ ያአላህ! እዝነትህን አደራ! ንግግሮች እያማሩ በሄዱ ቁጥር ስራዎች እየከፉ ሄዱ፤ ያ አላህ አንተ በቂያችንና መጠጊያችን ነህ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here