ነፃነትን የማይፈልግ ማን አለ? በርግጥ ወንድም ይሁን ሴት በአጠቃላይ የሰው ልጅ ሆኖ ‘ነፃነትን አልፈልግም’ የሚል ማንም የለም። ፍጡር ሁሉ ነፃነትን ይፈልጋል። ያለው ይንከባከባል፤ የሌለው ይናፍቃል። ሌላው ቀርቶ እንሠሣትም እንኳ ነፃነትን ይፈልጋሉ። ለምሣሌ – እስቲ አንዲት በራሪ ወፍ እንያዝና ትንሽ መውጫ ቀዳዳ ብቻ በማበጀት ጠባብ ጎጆ ውስጥ እናድርጋት። ወፏ ወጥታ ለመብረር ስትጣደፍ እናስተውላለን።

በጎጆዋ ውስጥ ታሥራ ለዘላለም መኖርን አትፈልግምና። አንድ ድመት እንውሰድና በሩን በመዝጋት ከአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ እናኑራት- ወዲያውኑ ወደ በሩ በመሄድ መውጫ በሩን ስትጭርና ስትጮህ እንመለከታለን። በተቆለፈ በር ውስጥ ተዘግቶባት ዘወትር መኖርን አትሻምና።

ነፃነት በቅርቡ የመጣ የዘመኑ ሰው ሀሣብ አይደለም። ባለቤቶቹም ምእራባውያን አሊያም ምሥራቃውያን ማህበረሰቦች አይደሉም። ነፃነት ዓለማቀፋዊ የሆነ ሀሣብ ነው። ለራሱም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ ነፃነትን የማይፈልግ ህዝብ አለ ብሎ ማሠብም ስህተት ነው። ሆኖም ግን አንድ እውነታ አለ፤ በምእራቡም ሆነ በምሥራቁ የዓለማችን ክፍል የሚኖሩ አንዳንድ ህዝቦች ነፃነትን ለራሣቸው ብቻ እንጂ ሌሎች እንዲኖራቸው አይፈልጉም። ይህ በርግጥ ትልቅ አፈናና ጭቆና ነው።

freed2እስልምና በነፃነት እንድንኖር፤ ያለ አንዳች ፍራቻ በእኩልነትም እንድናስብና እንድንመኝ ሌሎችም ነፃነት ያገኙ ዘንድ እንድንሠራ ያስተምረናል። ነፃነትና እኩልነት በጥብቅ የተሣሠሩ ነገሮች ናቸው። በእስልምና ዓይን ለአላህ ባላቸው የፍራቻ ደረጃ ካልሆነ በቀር የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ናቸው። በመሆኑም ከነፃነት በፊት በእኩልነት ዙሪያ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። እኩልነትን ሣንተገብር ነፃነትን መተግበር አይታሠብምና። ማስታወስ የሚገባን ሌላው ነጥብ በኢስላም ውስጥ ነፃነት ስንል የምንወዳቸውንና ስሜታችን የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ አሣድዶ መሥራት ሣይሆን ጥሩ ነገሮችን መርጦ የመሥራት ነፃነት መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። በዐረብኛ “ሁር”- ነፃ የሚለው ቃል ነፃነትን ብቻ ሣይሆም ክብርንም ያመለክታል። “የሰው ልጅ ነፃነት ይከበር” ስንልም ለሰብኣዊው ፍጡር ተገቢው ከበሬታ ይሠጠው ማለታችን ነው። በአጠቃላይ መልኩ እስልምና ነፃነትን ያበረታታል፣ ይደግፋል፣ ለነፃነትም ያነሳሳል። እስልምና ለሰው ልጅ መከበር ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጥ የነፃነትና የክብር ሃይማኖት ነው። ሰዎችን አእምሮአቸውንና መንፈሣቸውን ክፍት በማድረግም ላለሙት ግብ እንዲደርሱ ያግዛቸዋል። ነፃነት ትልቅ ክብር ነው። ከጭቆናና ውርደት ተላቆ ክብርን እስካላገኘ ድረስ የሰው ልጅ ነፃ ነው ማለት አይቻልምና።

اللَّهُ وَلِيُّ الَّذِينَ آمَنُوا يُخْرِجُهُم مِّنَ الظُّلُمَاتِ إِلَى النُّورِ وَالَّذِينَ كَفَرُوا أَوْلِيَاؤُهُمُ الطَّاغُوتُ يُخْرِجُونَهُم مِّنَ النُّورِ إِلَى الظُّلُمَاتِ أُولَٰئِكَ أَصْحَابُ النَّارِ هُمْ فِيهَا خَالِدُونَ

“አላህ የነዚያ ያመኑት ሰዎች ረዳት ነው። ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል። እነዚያም የካዱት ረዳቶቻቸው ጣዖታት ናቸው። ከብርሃን ወደ ጨለማዎች ያወጧቸዋል። እነዚያ የእሣት ጓዶች ናቸው፤ እነርሱ በውስጧም ዘውታሪዎች ናቸው።” (አል በቀራህ 2፡ 257)

وَلَقَدْ كَرَّمْنَا بَنِي آدَمَ وَحَمَلْنَاهُمْ فِي الْبَرِّ وَالْبَحْرِ وَرَزَقْنَاهُم مِّنَ الطَّيِّبَاتِ وَفَضَّلْنَاهُمْ عَلَىٰ كَثِيرٍ مِّمَّنْ خَلَقْنَا تَفْضِيلًا

“የአደምን ልጅ በርግጥ አከበርናቸው፤ በየብስና በባህርም አሣፈርናቸው፤ ከመልካም ነገሮችም ለገስናቸው። ከፈጠርናቸው ፍጡሮች በብዙዎች ላይ ማስበለጥን አስበለጥናቸው።” (አል ኢስራእ 17፡ 70)

ነፃነት በቅርቡ የመጣ የዘመኑ ሰው ሀሣብ አይደለም። ባለቤቶቹም ምእራባውያን አሊያም ምሥራቃውያን ማህበረሰቦች አይደሉም። ነፃነት ዓለማቀፋዊ የሆነ ሀሣብ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ ነፃነትና የአላህ ሀይልና እውቀት የሚቃረኑ የሚመስላቸው ብዙዎች አሉ። ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው። ነገሮች እኛ ሙስሊሞች በአላህ ቀዷና ቀደር (ቀድመው የተላለፉ ውሣኔዎችና ፍርዶች) ያለ ጥርጥር እናምናለን። ይህም ማለት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ያለፈውን፣ ያለንበትንና የወደፊቱን ሁሉ ያውቃል፤ በሁሉም ነገር ላይም ሀይልና ሥልጣን አለው ማለት ነው። ቢሆንም ግን በራሱ ፈቃድና ሀይል ነገሮችን የመምረጥ ነፃነትን ሠጠን፤ ነፃ ፈቃድና ፍላጎትም ለገሠን። ይህ ማለት ግን እሱ እኛ የምንሰራውን አያውቅም አሊያም በኛ ላይ ሀይል የለውም ማለት አይደለም። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የምንሠራቸውን ነገሮች ጥሩም ይሁኑ መጥፎ አንዲት ሣትቀር ያውቃል። አላህ እንዲህ አለ

إِنَّا هَدَيْنَاهُ السَّبِيلَ إِمَّا شَاكِرًا وَإِمَّا كَفُورًا

“እኛ መንገድን መራነው ፤ ያመስግንም ይካድም ። ” (አል ኢንሣን 76፤ 3)

የነፃነት ፅንስ ሀሣብ ዑቡዲያህ (አላህን መገዛት) ጋርም አይቃረንም። ኢስላም እራሱ ነፃነትን የሠጠን ሲሆን ፈጣሪያችንን አላህን መታዘዝና ማገልገል እንዳለብንም አስተምሮናል። ኢስላም መሠረቱን ያደረገው ፍፁም በሆነ መልኩ ለአላህ ታዛዠ መሆንን ነው። በመሆኑም የኢስላማዊ ነፃነት ፅንሠ ሀሣብ ማንኛውንም ፍፁም የሆነ ሥልጣን ከግለሰቦች በመንጠቅ ለሚገባው አካል ለፈጣሪያቸው መስጠት ነው። ለምን ከተባለ እነኚህ ሥልጣኖች አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለሰው ልጅ የሠጠውን ይቃረናሉና ነው። ለአላህ ፈቃድና ትእዛዝ ማደር የሰው ልጅ ነፃነትን አይጋፋም። የአምልኮ ተግባራት ወደ ትልቅ ስኬትና ነፃነት የሚያደርሱ መሠላሎች ናቸውና። አላህን መገዛት ውስጥ ውስጡን ሀላፊነትን ከመወጣት ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው ።

ነፃነት በኢስላም ከሞራላዊ ግዴታና ከተጠያቂነት አሊያም ከእውነተኝነት፣ ከፍትሃዊነት፣ ከበጎ ሠሪነትና ትክክለኛነት ከመሆን ማፈንገጥ አይደለም። እነዚህ አይነት ጋጥወጥነቶች ነፃነት ሊባሉ አይችሉም። ተራ ግርግር ወይንም ሙስና ልንላቸው እንችላለን። የኢስላም አስተምህሮ የሰው ልጆች ሁሉ በአእምሮ፣ በመንፈስም ሆነ በአካል ነፃ መሆን እንዳለባቸው ነው።

ኢስላም ለሁሉም ህዝቦች የእምነት ነፃነትንም አረጋግጧል። በእምነትም ማስገደድ እንደሌለ አውጇል። ሱራህ አል በቀራህ ቁ 256 ላይ የተመለከተውም ይሀው ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል

لَا إِكْرَاهَ فِي الدِّينِ قَد تَّبَيَّنَ الرُّشْدُ مِنَ الْغَيِّ

“በሃይማኖት ማስገደድ የለም። ቅኑ መንገድ ከጠማማው በርግጥ ተገለጠ።” (አል-በቀራህ 2፣ 256)

በመሆኑም ሰዎች ሁሉ እምነታቸውን በነፃነት ማራመድና የመተግበር መብት አላቸው። ሆኖም ግን እምነታቸውን በግድ ሌሎች ላይ ለመጫን ሙከራ ማድረግ የለባቸውም። እንዲሁም እስልምና ለሰው ልጆች ሀሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይሠጣል፤ ነገር ግን ሰዎች መሠረተ ቢስ ወሬዎችንና ውሸትን መናገር የለባቸውም። ኢስላም ሰዎች በራሣቸው ፍላጎትና ስምምነት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡና መሪዎቻቸውም ታማኝ ሣይሆኑ ሲቀሩ አሊያም ሀላፊነትን መወጣት ሲያቅታቸው ያወርዱ ዘንድ የፖለቲካ ነፃነትንም ያስተምራል። ኢስላም የኢኮኖሚ ነፃነትንም ይፈቅዳል፤ ሰዎች በነፃነት ሠርተው የማግኘትና የፈለጉትን ያህል የማከማቸት መብት ያላቸው ቢሆንም ያለ አንዳች ርህራሄ በማግበስበስ ለራሣቸው ብቻ የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ለሌላው ባለማሠብና በማጭበርበር መሆን የለበትም የሚል አቋም አለው።

  • እስልምና የነፍስን፣ የእእምሮንና የአካል ነፃነትን ያስተምራል።
  • እስልምና የግለሰብንና የማህበረሰብ ነፃነትን ያስተምራል።
  • እስልምና በዚህኛውም ሆነ በመጭው ዓለም ነፃነትን ያስተምራል።

በቁርዓን ውስጥ የነፃነት ፅንሠ ሀሣብ በተለያዩ ሁኔታዎችና ቃላቶች ተገልጿል። “ሁር” ወይንም “ተህሪር”- ነፃነት አሊያም ባሪያን ነፃ ማድረግ፣ “ነጃት”- የደህንነት ዋስትና ማግኘት፣ “ፈውዝ”- የላቀ ስኬት በማስመዝገብ ከግብ መድረስ፣ “ፈላህ”- አስተማማኝ ደህንነት … የሚሉት ጥቂቶች ሲሆኑ በሀዲስ ደግሞ “ዒትቅ” የሚለው ቃል ነፃ ማውጣት /ነፃ ነህ/ ማለትን ያመለክታል።

የነፃነትን ፅንሠ ሀሣብ ለዓለም ያስተማሩት ሙስሊሞች ከመሆናቸው ጋር ዛሬ ዛሬ የዘመናችን ሙስሊሞች እየተገበሩት ከትግበራው የራቁ መሆናቸውን ስናይ በእጅጉ ያሣዝናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ነፃነት አሉታዊና አዎንታዊ ገፅታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይኖርብናል። ይሀውም አንድን ነገር ለመፈፀም ነፃነትን ማግኘትና ከአንድ ነገር ነፃ መውጣት ሊሆን ይችላል። ኢስላም ነፃነትን የሚፈልገው ለደስተኛና ጤነኛ ህይወት፣ በብልፅግና ለመኖር፣ እንዲሁም ለሞራላዊና ለተከበረ ህይወት ሲባል ነው። ኢስላም የሰው ልጆች በነፃነት የአምልኮ ተግባራቸውን እንዲፈፅሙ፣ ሀሣባቸውን እንዲገልፁ፣ ሰርተው እንዲያገኙ፣ ቤተሰብ እንዲመሠርቱና በምርጫቸውም የራሣቸው የሆነ መንግስት እንዲያቋቁሙ ይፈልጋል። ህዝቦች ሁሉ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ከማህበራዊ ጭቆና ነፃ እንዲወጡ ያበረታታል። ኢስላም ሰዎች ሁሉ ከቁስ አምላኪነትና ከራስ ወዳድነት ነፃ እንዲወጡ ይፈልጋል። ኢስላም ሰዎች አንዳንድ ሃይማኖቶች ከሚያደርሱባቸወ ስቃይ እንዲገላገሉ ይፈልጋል። በመጨረሻም ዋናውና እጅግ አስፈላጊው የሆነው ነገር ኢስላም የሰው ልጆች በመጨረሻውና ዘላለማዊው በሆነው ዓለም ከጀሀነም እሣት ነፃ እንዲወጡና በጀነት ውስጥ በሀሴት በአላህ ዉዴታ ሥር ተጠቃለው እንዲኖሩ ይፈልጋል።

የነፃነትን ፅንሠ ሀሣብ ለዓለም ያስተማሩት ሙስሊሞች ከመሆናቸው ጋር ዛሬ ዛሬ የዘመናችን ሙስሊሞች እየተገበሩት ከትግበራው የራቁ መሆናቸውን ስናይ በእጅጉ ያሣዝናል። በመሆኑም በሙስሊሙ ዓለም የሚገኘው ማህበረሰብ ከጭቆና፣ ከኢፍትሃዊነትና ከእኩልነት እጦት እየተሠቃየ ነው። ሙስሊሞች ለራሣቸውም ሆነ በሌላው ዓለም በሚደረገው የነፃነት እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሣታፊ መሆን ይኖርባቸዋል። ስለ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና እምነት ነፃነት ከመናገር ወደ ኋላ ማለት አይገባቸውም። ስለ ሰብአዊ መብት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ስላላቸው ህዝቦች መብት፣ ስለ ሴቶች መብትም እንዲሁ ማንሣትና መታገል ይኖርባቸዋል። እነኚህ ሁሉ መብቶች በእስልምና ሙሉ እውቅናና ድጋፍ ተሠጥቶአቸዋል። በመሆኑም የቁርኣንንና የሀዲስን መመሪያ እንዲሁም የቀደምት ሠለፎችን ፈለግ በመከተል እነኚህ መብቶችና ነፃነቶች በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ለማስረፅ በከፍተኛ ሁኔታ መጣር ይጠበቅብናል።

4 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here