የመጨረሻዬ ፆም

0
7569

የሩቅ ሚስጢር ተገልጦልን የመሞቻ ቀናችን በመቃረቡ ምክኒያት የዘንድሮ የረመዷን ወር ፆም በህይወት ዘመናችን የመጨረሻችን ሊሆን እንደሚችል ቢነገረን.. … በጎ ሥራዎችንና መልካም ነገሮችን እንዴት እናበዛ ይሆን!? ቀንና ለሊቱን አሟጠን ለመጠቀም ሩጫችን ምን ይመስል ይሆን? ሥራችንን ለአላህ ብቻ ጥርት አድርገን ለመሥራትና እውነተኛ ለመሆንስ እንዴት እንተጋ ይሆን!? መልካም ሥራዎቻችንን ለማብዛት ምን ያህል ልንስገበገብ እንደምንችል እስቲ ለአፍታ ያህል በሀሣባችን እናምጣ።

አንድን ነገር “የመጨረሻዬ ሊሆን ይችላል” ብሎ በማሰብ መሥራት ነፍስ ለዚያ ነገር ይበልጥ ትኩረት ሠጥታ ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደዚያ እንድታዞርና በርትታ እንድትሠራ ያግዛታል።

በአንድ ወቅት አንድ ሰው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና “አሣጥረው ያስተምሩኝ።” አላቸው። እርሣቸውም እንዲህ በማለት መከሩት

إذا قمت في صلاتك، فصلِّ صلاة مودع

“ለሰላት ስትቆም የመሠናበቻ (የመጨረሻ) ሠላትህን እንደምትሰግድ ሁን።” (ኢብኑ ማጃህ)

እስቲ ላንዳፍታ የምንሰግደው ሰላት የመጨረሻችን ልትሆን እንደምትችልና ከሰላቷ በኋላ እንደምንሞት አድርገን እናስተንትን። ምን ያህል ተናንሰንና ረጋ ብለን በህያው ልቦና እንሰግዳለን?። ምን ያህል ለውበቷ እንጨነቃለን! እንዴትስ አሟልተንና አሣምረን የአላህን ፊት ብቻ ፈልገንበት እንደምንሰግድ ልብ እንበል።

ለምንድነው ታዲያ በያንዳንዱ የአምልኮ ሥራችን ውስጥ “የመጨረሻዬ ሊሆን ይችላል” የሚል መንፈስ ወደራሣችን የማናመጣው?.. አሏህ (ሱ.ወ) ዛሬም የተከበረው ረመዷን ወር ላይ አድርሦናል። ይህ ረመዷን የመጨረሻችን ሊሆን እንደሚችልና ዳግም ከታላቁ ወር ልንገናኝ እንደማንችል በውስጣችን ብናስብ ለበለጠ ሥራ እንነሣሣለን፤ የበለጠ ውጤትም እናገኝበታለን። ሞት እስካለ ድረስ ለሰው ልጅ ዛሬ እንጂ ነገ ሀብቱ አይደለችም።

ከምናውቃቸውም ይሁኑ ከማናውቃቸው ሰዎች፣ ጓደኞች፣ ቤተሰብም ይሁን ጎረቤቶች…. አምና ከኛ ጋር የፆሙ ዘንድሮ በረመዷን በር ላይ የሌሉ ብዙ ናቸው። አይደለም ሌላው ቀርቶ የዛሬን ቀን አብሮን የተቀበለ ነገርግን ያላጠናቀቀ ስንት አለ! ነገን ያሠበ ያቀደ ነገርግን ያልደረሰበት ብዙ ነው።

በነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሀዲስ እንደተዘገበው እንዲህ ብለዋል፡-

افعلوا الخير دهركم وتعرضوا لنفحات رحمة الله؛ فإن لله نفحات من رحمته، يصيب بها من يشاء من عباده

“ዛሬውኑ መልካም ነገር ሥሩ። ለአላህን የእዝነት መንፈስ እራሣችሁን አዘጋጁ። ለአላህ የእዝነት መንፈሦች አሉት። ከባሮቹም ለሻው ሰው ይሠጣል።”

ስለሆነም ኑ እስቲ አብረን የመሠናበትን ስሜት ወደራሣችን እናምጣ። በዒባዳዎቻችን ውስጥ የመሠናበቻ ስሜትን በውስጣችን በማምጣት ያላግባብ የጠፉ ያለፉ ጊዜያቶቻችንን እንተካ። የስንፍና ቀናቶቻችንን እናካክስ። የባከነ ኢማናችንን እንበቀል። ኑ ይህን ወር የመጨረሻውን ፆም እንደሚፆም ሰው ሆነን እንፁም። ከለመድነው ባህላችንና የኑሮ ሂደታችን ወጣ በማለት ወደ ጥሩና ብሩህ የአምልኮ መንፈስ ውስጥ እንግባ። አላህ ይረዳናል ያግዘናልም።

 • በርግጥ በየአመቱ ረመዷንን እንፆማለን። ነገርግን እውነት ለመናገር የአብዛኞቻችን ፆም ለመገላገልና ግዴታን ለመወጣት ብቻ ነበር። ዘንድሮን ግን ከዚያ መንፈስ መውጣት አለብን። ለየት ያለ ሀሣብ መያዝ አለብን። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) እንዳመላከቱን ፆምን “በኢማን እና አላህ ዘንድ ምንዳውን በመተሣሠብ” እንፁም። አላህ (ሱ.ወ) ያለፈ ወንጀላችንን ይምርልናል። አቤት የወንጀላችን አበዛዙ!
 • በየዓመቱ በረመዷን ወር ቁርዓንን በተደጋጋሚ ለማክተም እንሽቀዳማለን። በርግጥም እጅግ አስደሣች ሩጫ ነው። ዘንድሮን ግን ቁጥር ማብዛትን ዓላማችን አናድርግ። የቁርዓን ኺትሚያችን ጥራት ላይ ያተኮረ ይሁን። ጥሩ ኒያ በማኖርና በጥልቀት በማስተንተን ቁርዓንን እናንብብ። ከማነብነቡም በላይ ትግበራው ላይ ትኩረታችንን እናድርግ።
 • በየዓመቱ ረመዷን መስጊዶችን እንመርጣለን። ቁርዓንን በጥሩ ደምፅ የሚያነብ ጥሩ ስሜት የሚያመጣ ኢማም ፍለጋ በየመስጊዶች እንዞራለን። የዘንድሮ ድካማችን ግን መተናነስና መዋደቅ የሠፈነባት የአላህ (ሱ.ወ) ፊት ብቻ የተፈለገባት ጥሩ ሰላት ፍለጋ ይሁን።
 • በየዓመቱ ረመዷን ከቤተሰባችን ጋር ረመዷንን በጥሩ ሁኔታ ለማሣለፍ በቤት ውስጥ ሁሉን ነገር ለማሟላት እንጥራለን፤ እንተጋለን። በዘንድሮው ረመዷን ግን ሀሣባችን በዚህ ብቻ አይወሰን፤ ጥረታችንን እናስፋው። ነፍሣችንንም ሆነ መንፈሣችንን እናስደስት። ሌላም ሌላም ነገር እናክል.. የኢማን ድባብ ያላቸው አቀማመጦችን ወደ ቤታችን እናምጣቸው። በቤታችን ደስታ እና እርካታ ይሞላ ዘንድ።
 • ቤተሰቦቻችንን በማሰደሠቱ ረገድ የተሣካልን እንደሆነ ደግሞ ለመልካም ሥራዎቻችን ገደብ አናድርግ። ከቤታችን ክልል በመውጣት ከጎረቤትም ይሁን ከቤተሰብ የተቸገሩትን እናግዝ እንርዳ።
 • በየዓመቱ ረመዷን ችግረኞችን ለመርዳት አስበን እንመፀውታለን፤ ለድሆች የአቅማችንን እንሠጣለን። የዘንድሮውን ሰደቃችንን ግን ከፍ ያለ ነገር አስበንበት (ኒያ አድርገን) እንለግስ። ነፍሣችን ከወንጀል እሣት ነፃ ለማውጣት እንለግሰ። ሰደቃ የአላህን ቁጣ ታበርዳለችና።
 • ረመዷን ውስጥ ዑምራ ማድረግ ከሀጅ የሚስተካከል ደረጃ ያለው መሆኑን ስለምናውቅ በየዓመቱ ለማድረግ እንሽቀዳደማለን። የዘንድሮውን ዑምራችንን ግን እስቲ ሌላ ነገር እንነይትበት። በህይወት ዘመናችን የሠራነውን ወንጀሎች ሁሉ ያጥብልን ዘንድ ለህይወታችን ቤዛ እናርገው።
 • በየዓመቱ ረመዷን ሲመጣ በጠቃሚ ሥራዎች ላይ እንበረታለን። በዘንድሮ ረመዷናችን ግን ይህ ጥቅም መስጠታችን ከበፊቱ ከፍ ይበል። ጥሩ መፅሃፍ ገዝተን እንስጥ። መልካም ምክሮችን እናበርክት። የተጣሉትን እናስታርቅ። ሌላም ሌላም….
 • ሰዎች ዱዓእ ከማድረግ በመስነፍ በራሣቸው ላይ ሲሠስቱ ማየት ይገርማል። ዘንድሮ ግን ከዚህ ዓይነቱ ስስት እንላቀቅ። በዚህ በተከበረው ወር ውስጥ ጠንክረን ለራሣችንም ሆነ ለሌሎች ዱዓእ እናድርግ። ሚሊዮን ሙስሊሞች ዱዓኣችንን ፈላጊዎች ናቸው። በሌሉበትና ባላወቁበት ሁኔታ ዱዓእ ስናደርግላቸው ደግሞ “አሚን ላንተም ተመሣሣዩ ይሁን” የሚሉ ተቀባይ መላኢኮች ተመድበዋል። ለሌላ የሚደረግ ዱዓእ ከራስ ድርሻ አንዳች አይቀንስም።
 • በረመዷን ውስጥ ልግስና እጅግ የተወደደ ሥራ ነው። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ወር በመለገሱ ረገድ ይብስባቸዋል። እኛም የርሣቸውን ፈለግ እንከተል። መፍታታችን ይብዛ። ልግስናችንም በገንዘብ ብቻ ሣይሆን በሌላ መልኩም ይሁን.. ላጠፋብን መልካም እናድርግ፤ የቆረጠንን እንቀጥል፤ ለበደለን ይቅር እንበል። አንድ ባሪያ ይቅር ባለ ቁጥር አላህ ከፍታን እንጂ አይጨምርለትም።
 • ኢዕቲካፍ ማለት አምልኮን በማሰብ ለተወሰነ ጊዜ መስጊድ ውስጥ ተገልሎ መቆየት ነው። በፊት የምንገለለው አልባሌ ወሬና ሀሜት ሽሽት ሊሆን ይችላል። ዘንድሮን ግን ከራሣችን ጋር ለማውራትና ለመቀማመጥ ብለን መስጊድ እንታሠር፤ በቆይታችንም እራሣችንንም እንገምግም፤ ስለሁኔታችን እንመርምር። እራሣችንን ከመገምገማችንና ከመመርመራችን በፊት ድንገት ሞት መጥቶብን ቀብር ውስጥ ምርመራ ሊበዛብን ይችላልና።
أَن تَقُولَ نَفْسٌ يَا حَسْرَتَا عَلَىٰ مَا فَرَّطتُ فِي جَنبِ اللَّهِ وَإِن كُنتُ لَمِنَ السَّاخِرِينَ
“(የካደች) ነፍስ ‘እኔ ከሚሳለቁት የነበርኩ ስኾን በአላህ በኩል ባጓደልኩት ዋ ጸጸቴ’ ማለቷን (ለመፍራት)” (አዝ-ዙመር 39፤ 56)
 • ረመዷን ውስጥ ፆመኞችን በማስፈጠር ወደ አላህ (ሱ.ወ) ለመወደድ ጥረት እናደርጋለን። ይህን የምናደርገው ሰው ስላደረገ አሊያም ከሰው እይታ ለመግባት አስበን ሊሆን ይችላል። በዚህ ረመዷን ግን ስናስፈጥር የሰውን ሙገሣ ከመፈለግም ሆነ ከትችቱ ለመራቅ እንዳይሆን እንጠንቀቅ። ለይዩልኝ መሥራት ከአላህ ዘንድ ምንም ምንዳ አያስገኝምና።
 • ጾመኛን ማስፈጠርና የተራበን ሆድ ማጥገብ የሚወደድ እና ነቢያዊ ሱና ነው። ነገርግን ከዚህ በላይ የተራበን የሰው ልጅ ቀልብ ማጥገብ የሚፈለግ ግዴታ ነው። በዚህ በኩል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እኛ ልብ ያላልነው ስንት ምክር የተጠማ ሰው አለ! እኛ ያላስተዋልነው ስንት በስሜት ውስጥ የሚዋኝ አዳኝ የሚፈልግ ፍጡር አለ!
 • ከሰጋጆች ጋር ጎን ለጎን ስንቆም ከሁሉም ጋር የምንተዋወቅ ሆነን አይደለንም። ነገርግን ቀልባችንን እንዲተዋወቅና አንድነታችን እንዲጠናከር አንድ ነገር ማወቅ ይገባናል። ከኢማሙ በኋላ ለሰላት ስንሠለፍ ሰልፍን ማስተካከል የአማኞችን ልብ ያስተሣስራል፤ አንድነታቸውንም ያጠናክራል።
 • ለኛም ሆነ ለዲናችን አደገኛ ጠላቶች አሉ። ከሃዲያን ከሆኑ ዱዓእ በማብዛት በነርሱ ላይ ድልን እንቀዳጅ። ሙስሊሞች ከሆኑ አላህ ሀቁን እንዲያሣያቸው። ዱዓእ ጠላትን ወደ ወዳጅ ይለውጣል። አላህ መልካም አገልጋዮቹን ያግዛል።
 • በረመዷን ውስጥ የሙስሊሞች እጅ እንደሚፍታታ ያውቃሉና በየጎዳናዎችም ሆነ በመስጅድ በር ላይ ችግረኞች ያጋጥሙናል። ነገርግን እኛ የማናያቸውና የማናውቃቸው ብዙ ችግረኞች አሉ። የሰው ዓይን የማየት እፍረት፣ በሽታ፣ አካለ ስንኩልነትም ሆነ ሌላ ነገር ወጥተው ከመጠየቅ ያገዳቸው። እነሱን እናስታውሣቸው። ባሉበትም ሄደን እንርዳቸው።
 • በየዓመቱ የረመዷን ወር ደረጃና ትሩፋት ይዘከራል። እኛም የሚባለውን ሁሉ በተደጋጋሚ ስለሠማን ተላምደን መለወጥ አቅቶናል። በዘንድሮ ረመዷንን ግን የታላቁን ወር ደረጃ ከልብ እናጢን። የግምቱንም ያህል ዋጋ እንስጠው።
 • ለይለቱልቀድር የረመዷን ዋጋ ከፍ ከሚያረጉ ነገሮች አንዷ ናት። እኛም ብዙ ረመዷንን ፆመናል። ለይለቱልቀድርን ስለማግኘታችን ግን አላህ ብቻ ያውቃል። ዘንድሮን ግን ሆነ ብለን ይህችን ታላቅ ለሊት ተግተን እንፈልጋት። እስከዛሬ አላገኘናት ይሆናልና።
 • ረመዷንን ስንሠናበት አሊያም ሲሠናበተን አላህ ለሚቀጥለው ያደርሰን ዘንድ ለጌታችን አደራ እንበለው። ሥራችንንም ይቀበለን ዘንድ እንዲሁ። የምንሰናበት ነገር ካጣን ያ በርግጥም ትልቅ ጥፋት ነው፤ ለእድሜያችንም ትልቅ ኪሣራ ነው። የተከለከለ ማለት አላህ የከለከለው ነው።

ይህ በጥቂቱ ከላይ የጠቃቀስነው በታላቁ ወርሀ ረመዷን በር ላይ ሆነን ውስጣችን የሚመላለስ ስሜት ነው። ይህ ወር የኛ እንዲሆንልን በርግጥ ቆርጠን ተነስተን ይሆን! የወንጀላችንን ቆሻሻ የምናጥብበት ከምክሮቹም ቀልባችንን ህያው የምናረግበት ወር ይሆንልን ይሆን! ወይስ እሱም እንደቀደሙት ረመዷኖች ሁሉ ሣንጠቀምበት ያልፋል..…

ረመዷንን ለአዲስ ህይወት ውጥን እናርገው። ወደ ጌታችን ለመመለስ እውነተኛ መንደርደሪያ ይሁነን። ተሸቀዳድመን ከገበታው መቋደሱ ለሁላችንም ግድ ይላል።

ሙስሊሞችን ያዘናጋሽ ስንፍና ሆይ ከቀልቦቻቸው ላይ ተነሺ.. የሙስሊሞች ሀሳብ ሆይ ለመልካም ነገር ሁሉ ፍጠኚ እሩጪ። ለመልካም ጥሪ ፈጣን ምላሽ የሠጠ ሰው ምንኛ ታደለ! ከበሩ የተባረረና የተመለሠ ምንኛ ከሠረ! አላህ ሆይ! ወደ ስኬት መንገድ ምራን። ወዳንተ ለመመለስና እጅ ለመስጠት አግዘን። ለፀሎታችንም ምላሽ አትንፈገን።

አላህ ሆይ! ረመዷንን ባርክልን። ለፆሙና ለተራዊሁ በተደጋጋሚ ከሚታደሉት አድርገን። ከጀሀነም እሣት ነፃ ከሚሆኑትም አድርገን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here