በረመዳን ምን ይጠበቅብናል? (ክፍል 2)

0
5386

ከአላህ ጋር…

ረመዳን እያንዳንዱ ሙስሊም ልቡን ህያው የሚያደርግባቸው እና ከጌታው ጋር ያለውን አብሮነትና ግንኙነት የሚያዳብርባቸው ብዙ አማካዮችን (ወሳኢል/means) ይፈጥራል። ከእነዚህ ጥቂቶቹን እነሆ፡-

1. ፆም

ይህ ነፍስን ለመቆጣጠር የሚረዳ ምርጥ መንገድ ነው። እንዲህ የምንለው ለምን መሰላችሁ? ነፍስ የአላህን ባሮች ከአላህ መንገድ የምታሰናክል ክፉ ነገር ናት። ተፈጥሮዋ ደስታን እንድትፈልግና ከግዴታዎቿ እንድትሸሽ ያደርጋታል። እርሷን የሚያርቅ (የሚያርም) ምርጥ መንገድ ደግሞ ፆም ነው። እርሱ የስሜቷን በር የሚያጣብብ ነገር አለው። ስለዚህ በፆማችን ይህን መጠቀም ከፈለግን የቀኑን አብዝሀ-ክፍል በእንቅልፍ ማሳለፍ የለብንም። ኢፍጣር ላይ ምግብና መጠጥ ስንጠቀምም መሀከለኛ መሆን አለብን። የምግብ አይነቶችን ማብዛት የለብንም። አንድ አይነት ምግብ በቂያችን ነው።

አል-ሐሊሚይ እንዲህ ይላሉ፡-

“…ሐላል የሆኑ ምግቦችን ማብዛት ጥሩ አይደለም። ምናልባት ሰውነቱን ያከብደውና እንቅልፍ እንቅልፍ ያሰኘዋል። ከዒባዳና ከዚክር ያግደዋል። ስለዚህ ረሐቡን የሚቆርጥበት ያህል ከተበላ በቂ ነው። ምግብ የሚበላበት አላማም በዒባዳ ለመጠንከር ይሁን።”

ከምግብና መጠጥ ከመፆም ጋር በቻልነው ያህል ከክፉ ንግግሮችና ሳቅ ራሳችንን ማፆም ይገባናል። “ምላስህን ያዝ!” ይሁን ለራሳችን የምናነሳው መፈክር። ከአልባሌ ጨዋታዎችና ከሌሎችም የምላስ ጣጣዎች እራሳችንን እንጠብቅ።

2. ከመስጊድ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር

መስጊድ ልብን የሚያበራ ታላቅ ሚና አለው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

اللَّهُ نُورُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ 
“አላህ የሰማያትና የምድር አብሪ ነው።” (አን-ኑር 24፤ 35)
ከዚያም ቀጥሎ ያለውን አንቀፅ ደግሞ እንመልከት።

فِي بُيُوتٍ أَذِنَ اللَّهُ أَن تُرْفَعَ وَيُذْكَرَ فِيهَا اسْمُهُ يُسَبِّحُ لَهُ فِيهَا بِالْغُدُوِّ وَالْآصَالِ
“አላህ እንድትከበርና ስሙ በውስጧ እንዲወሳ ባዘዘው ቤቶች ውስጥ (አወድሱት)። በውስጧ በጧትና በማታ ለእርሱ ያጠራሉ።” (አን-ኑር 24፤ 36)
የእነዚህ ሁለት አንቀፆች ትርጉም እንዲህ ሊለን ፈልጓል።

መስጊድ ውስጥ ልብህ ከአላህ ጋር ይተሳሰራል። ነፍስህም ከኃጢያት ይጠበቃል።

ألا أدلكم على ما يمحو الله به الخطايا ويرفع به الدرجات، قالوا بلى يا رسول الله، قال: إسباغ الوضوء على المكارة وكثرة الخطى إلى المساجد وانتظار الصلاة بعد الصلاة، فذلكم الرباط فذلكم الرباط

“አላህ ኃጢያት የሚምርበት ደረጃ ከፍ የሚያደርግበትን ነገር አልነግራችሁም?!” አሉ የአላህ መልእክተኛ። “አዎን! የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” አሉ፤ ባልደረቦቻቸው። “ቅዝቃዜ በሚኖር ጊዜ ዉዱእ አዳርሶ ማድረግ፣ ወደ መስጊድ እርምጃ ማብዛትና ከሶላት በኋላ ሶላትን መጠበቅ። ይኻችሁ ነው ዒባዳን በዒባዳ ላይ ማነባበር (ሪባጥ) ማለት።”

የሙእሚን ቀልብ ከአንድ ሁኔታ ወደሌላ ይገላበጣል። ውስጡ የሚደረጉ የኢማንና የስሜት ጥሪዎች መሀል የሚደረግ ጦርነት አለ። በኢማን ጥላ ስር እንዲቆይ ማድረግና ማረጋጋት ይገባል። ይህን ጊዜ የመስጊድ ሚና ጎልቶ ይታያል። ሰይዲና አባሁረይራህ (ረ.ዐ) ተከታዩን አንቀፅ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اصْبِرُوا وَصَابِرُوا وَرَابِطُوا وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ታገሱ ተበራቱም (በጦር ሜዳ ኬላ ላይ) ተሰለፉም ትድኑም ዘንድ አላህን ፍሩ።” (አሊ ዒምራን 3፤ 200)

“በነብዩ ዘመን ሪባጥ (በጦር ሜዳ ኬላ ላይ የሚደረግ ሰልፍ) የሚደረግበት ዘመቻ አልነበረም። ይህ አንቀፅ ለመንገር የፈለገው ዋና ነጥብ ከሶላት በኋላ ሶላት መጠበቅን ነው።”

መስጊድ በጧት እንግባ። ከሰገድን በኋላም ቦታችንን አንተውም። ምክንያቱም መላኢካዎች ዱዐ ያደርጉልናል። በሃዲስ እንደተዘገበው“እያንዳንዳችሁ በሰገዳችሁበት ስፍራ ከተቀመጠ ዉዱእ እስካልፈታ ድረስ ‘አላህ ሆይ! ማረው። አላህ ሆይ! እዘንለት እያሉ’ መላኢካዎች ዱዓ ያደርጉለታል።”

ይህ ቱሩፋት አብዝሀኛው ሰላቷን ቤቷ ውስጥ የምትሰግድ እህታችን አታጣውም። ቤቷ ውስጥ አንዲት ስፍራ መስጊድ ብላ ብትወስን፣ ወደዚያው ስፍራ በጊዜ ብትሄድ፣ ከሶላት በኋላም ሶላት ብትጠብቅ፣ እዚያው ሶላቱን ብትደጋግምበትና የችሎታዋን ያህል እዚያው ብትቀመጥ ታገኘዋለች።

3. ቁርአን ህይወት ነው

ረመዳን የቁርአን ወር ነው። የነብዩ ተግባር የሚጠቁመው ረመዳን ውስጥ ቁርአንን አብዝቶ ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ቁርአን ልብን ህያው ለማድረግ ፍቱን መድሀኒት ነው፤ መንፈስን በብርሀን ለማሸብረቅ መልካም መንገድ ነው።

يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَتْكُم مَّوْعِظَةٌ مِّن رَّبِّكُمْ وَشِفَاءٌ لِّمَا فِي الصُّدُورِ وَهُدًى وَرَحْمَةٌ لِّلْمُؤْمِنِينَ

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ግሳጼ በደረቶች ውስጥም ላለው (የመጠራጠር በሽታ) መድኃኒት ለምእምናንም ብርሃንና እዝነት በእርግጥ መጣችላችሁ።” (ዩኑስ 10፤ 57)

ሙስሊም ለቁርአን ባለው ቅርበት ያህል ለአላህ ይቀርባል። የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይላሉ፡-

أبشروا!! فإن هذا القرآن طرفه بيد الله وطرفه بأيديكم فتمسكوا به فإنكم لن تهلكوا ولن تضلوا بعده أبداً

“አይዟችሁ! ይህ ቁርአን ጫፉ በአላህ እጅ ነው። ጫፉ ደግሞ እናንተ እጅ ላይ ነው። ከርሱ በኋላ አትጠፉም። አትጠሙምም።”

ይህ መድኃኒት ፍቱን የሚሆነው እና የልባችንን ህመም የሚፈውስልን አላህ እንደሚፈልገው ስንጠቀምበት ነው። ቁርአን የወረደው እንድናስተነትነው ነው። ከውስጡም ለህይወታችን የሚበጁ ትምህርቶችን እንድንቀስም ታዘናል። በምላሳችን እንድናነበው ብቻ አይደለም ወደኛ የመጣው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

كِتَابٌ أَنزَلْنَاهُ إِلَيْكَ مُبَارَكٌ لِّيَدَّبَّرُوا آيَاتِهِ وَلِيَتَذَكَّرَ أُولُو الْأَلْبَابِ

“(ይህ) ወዳንተ ያወረድነው ብሩክ መጽሐፍ ነው። አንቀጾቹን እንዲያስተነትኑና የአእምሮዎች ባለቤቶችም እንዲገሰጹ (አወረድነው)።” (ሷድ 38፤ 29)

አንዳንድ የሠለፍ ሰዎች እንዲህ አሉ፡-

ማንም ሠው ከቁርአን ጋር ተቀምጦ ሳያተርፍ ወይም ሳይከስር አይነሳም። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَنُنَزِّلُ مِنَ الْقُرْآنِ مَا هُوَ شِفَاءٌ وَرَحْمَةٌ لِّلْمُؤْمِنِينَ ۙ وَلَا يَزِيدُ الظَّالِمِينَ إِلَّا خَسَارًا

“ከቁርኣንም ለምእመናን መድኀኒትና እዝነት የኾነን እናወርዳለን። በዳዮችንም ከሳራን እንጂ ሌላ አይጨምርላቸውም።” (አል-ኢስራእ 17፤ 82)

በምላሳችን ቁርአንን ደግመን ደጋግመን አንብበነው ይሆናል። ብዙ ጊዜ ምኞታችን ከማኽተም (አንብቦ ከመጨረስ) አይዘልም። እንደውም አንዳንዴ ደጋግሞ የማኽተም ውድድር ውስጥ ብዙዎቻችን እንገባለን። በተለይም በረመዳን ይህ ውድድር ይበረታል። ከዚህ ውድድር ግን ለልባችን የሚሆን ጥቅም አናገኝም።

ንባባችን በምላሳችን ብቻ ሆኖ ቁርአን ህይወታችንን ሊቀይር አይችልም። ልክ እንደ ገለባ ነው የኛ ውሎ። ትልቅ ነው። ግን ጥቅም የለውም። ይህ ደጋግ ሠዎች ሁሉ አበክረው የመከሩት አብይ ጉዳይ ነው። ሰይዲና ዓሊይ እንዲህ ይላሉ፡-

لا خير في قراءة ليس فيها تدبر

“ማስተንተን የሌለው የቁርአን ንባብ መልካም ፋና የለውም።”

ሐሠን አል-በስሪይም የህንኑ ያብራሩታል፡-

كيف يرق قلبك وإنما همك أخر السورة؟

“ጭንቀትህ የሱራውን መጨረሻ መድረስ ሆኖ እንዴት ልብህ ይቅጠን?!” ይላሉ።

ኢብኑል ቀዪምም የበኩላቸውን ያክላሉ፡-

لا شيء أنفع للقلب من قراءة القرآن بالتدبر والتفكر، فإنه جامع لجميع منازل السائرين، وأحوال العالمين، ومقامات العارفين .. فلو علم الناس ما في قراءة القرآن بالتدبر لاشتغلوا بها عن كل ما سواه، فقراءة آية بتفكر خير من ختمة بغير تدبر وتفهم

“በእስትንታኔና በማስተዋል ቁርአንን እንደመቅራት ለልብ የሚረባ ነገር የለም። ቁርአን ወደ አላህ የሚጓዙ ሠዎችን ማረፊያዎች (መናዚል)፣ የዓለማትን ሁኔታዎች (አሕዋሎች) እና የዓሪፎችን ደረጃዎች (መቃማት) ሁሉ አሟልቶ ይዟል።…ሠዎች ቁርአንን አስተንተኖ በማንበብ የሚገኘውን ጥቅም ቢያውቁ ሌሎችን ሥራዎች በሙሉ ትተው በርሱ ይጠመዱ ነበር። አንድ አንቀፅን በማስተንተን እና በግንዛቤ ማንበብ በግርድፍ ከሚነበነቡ ኺትሚያዎች ይሻላል።”

ረመዳን ከቁርአን ጋር ያለንን ትስስር ብቻ ሳይሆን ትድድር የምናስተካክልበት ምርጥ አጋጣሚ ነው።

በቁርአን እንዴት እንጠቀም?!

ቁርአን ቀልብን የማለስለሻ ምርጥ መንገድ ነው። ዉሀይብ ኢብኑል-ወርድ እንዲህ ይላሉ፡- “ብዙ ተግሳፆችን፣ በርካታ ምክሮችን ተመልክተናል። ነገርግን ልብን የሚያለሰልስና ትካዜን የሚፈጥር ቁርአንን እንደማንበብና እንደማስተንተን ያለ ነገር አላየሁም።”

ቁርአንን በሚገባው መልኩ ማንበብ- አቡሐሚድ አል-ገዛሊይ ዝንደሚሉት- አእምሮ፣ ምላስና ልብ (ቀልብ) በአንድነት የሚተገብሩት ሥራ ነው። የምላስ ተግባሩ ፊደላቱን አሳምሮ በምላስ ማውጣት ነው። የአእምሮ ተግባር ቃላቱን መተርጎም ነው። የልብ ድርሻ በመልእክቱ መነካትና ተግሳፁን ማስተዋል ነው። ምላስ አንባቢ፣ አእምሮ ተርጓሚ፣ ልብ ደግሞ የተግሳፁ አድማጭ ናቸው።

እነሆ በቁርአን እንድንጠቀም የሚረዱ ተግባራዊ ዘዴዎችን እንጠቁማለን። አላህ የምንጠቀም ሠዎች ያድርገን!

i. ከመቅራታችን በፊት፡- ቁርአን መቅራት ከመጀመራችን በፊት ዱዐ እናድርግ። አላህ ልባችንን እንዲከፍትልን፣ የቁርአኑን ብርሀን እንዲለግሰን እንማፀን። በቁርአን ልባችን እንዲነካና እንድናስተነትነው እንዲያግዘን እንለምነው። ይህ ዱዓ ልብ ቁርአኑን እንዲቀበል በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ ሚና አለው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا يَتَذَكَّرُ إِلَّا مَن يُنِيبُ

“ወደእርሱም የሚመለስ ሰው ቢኾን እንጂ ሌላው አይገሰጽም።” (ጋፊር 40፤ 13)

ii. ቁርአን ማንበብ ማብዛት፡- ከቁርአን ጋር ያለንን ቆይታ ማርዘም እና ቁርአንን አብዝቶ ማንበብ ከቁርአን እንድንጠቀም ይረዳናል። ከቁርአን ጋር ያለን ቆይታ በሰከነ ስፍራ ላይ ቢሆን መልካም ነው። ከጫጫታ የራቀ ስፍራ ቢሆንም ተመራጭ ነው። ይህ ዘዴ ቁርአን ላይ ትኩረት እንዲኖረን ያደርጋል። ልብን ይሰበስባል። ቂርአት ከመጀመራችን በፊትም ሲዋክና ዉዱእ ማድረግ አንርሳ።

iii. ከሙስሐፍ ላይ፣ በሚሰማ ድምፅና በዝግታ ማንበብ፡- እነዚህ ነጥቦች ቁርአን ከልባችን እንዲሰርግ ከሚረዱ ነገሮች መሀል ናቸው። በዝግታ ማንበብ (ተርቲል) ስሜትን የሚያንኳኳ የሆነ ነገር አለው። ስሜት ከተቆረቆረ ከግንዛቤያችን ጋር ይጣመራል። ከዚያም ማስተንተን (ተደብ-ቡር) ይወለዳል። ከዚያም ኢማን ይጨምራል።

iv. ያማረ አነባበብ እና ትካዜ፡- ቁርአንን ስናነብ ለእያንዳንዱ ፊደል፣ መሳቢያ (መድ-ድ) እና ድምፅ የድርሻውን እየሰጠን መሆን አለበት። በዚህ መልኩ ካነበብነው የቁርአኑን ውበት ይበልጥ እናገኘዋለን። ከአናቅፆቹ ጋር ያለንን ቆይታም ጣፋጭ ያደርግልናል። ቁርአንን ስናነብ በትካዜ ድምፅ ብናነበውም በመልእክቱ እንድንነካ ያግዘናል።

v. የአናቅፁ ጠቅላላ ትርጉም፡- ዓቅላችንን የቁርአኑን ትርጉም እንዲረዳ ስናደርግ ከንባባችን ጋር እንድንኖርና ትኩረታችን እንዳይሰረቅ ይረዳናል። ዓቅላችንን እናሰራ ስንል እያንዳንዱ ቃል የያዘውን ምስጢር ለመረዳት እንዳክር ማለታችን አይደለም። አናቅፆቹ የሚያስተምሩትን ጥቅል ትርጉም ለመረዳት መሞከር ይበቃል። ከዚህ የጀመረው የእስትንታኔ አቅማችን ቀስ በቀስ ያድግና ለትርጓሜዎቹ ያለን መነሳሳትና መነካት ፈጣን እና ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል።

vi. ቁርአን እያናገረህ ነው፡- ቁርአንን ስታነብ እራስህ ላይ እንደወረደና አንተን እንደሚያናግር እያሰብክ አንብብ። ለዚህ እንዲረዳህ አንዳንድ አናቅፆች ጥያቄ አዘል ንግግሮችን ሲያነሱ ለነርሱ መልስ ስጥ። የዱዓ ቦታዎች ላይ አሚን በል። ስለ ጀነት የሚያወሩ አንቀፆች ላይ ጀነትን ከልብህ ተመኝተህ ለምን። ስለ ጀሀነም ሲነግርህ አላህ እንዲጠብቅህ ተማፀን። አንዲህ ስታደርግ ከቁርአን ጋር ያለህ መግባባት ይጨምራል።

vii. ልብህን የነኩ አናቅፆችን መደጋገም፡- ልብህ ውስጥ የሚገባውን የብርሀን መጠን ለማሳደግና ኢማንህን ለመጨመር አንዳንድ ልብህን የነኩህን አናቅፅ ደጋግመህ አንብባቸው።

viii. ከጎንህ አጠር ያሉ የቁርአን ትርጉም መፅሀፍት ቢኖሩ፡- ትርጉማቸውን መረዳት ይረዳህ ዘንድ የቁርአን ትርጉምና ትንታኔ የያዙ መፅሀፍት ከጎንህ ቢኖሩህ መልካም ነው። ነገርግን አንብበህ ሳትጨርስ እነርሱን እንዳትከፍት። ምክንያቱም ከቁርአን አየር ያወጣሀል። ከምትኖርበት የመንፈስ እርካታና ተመስጦም ይመልስሀል። የከበዱህን ቃላት ያዛቸውና ከቂርአትህ በኋላ ትርጓሜያቸውን ፈልግ/ጠይቅ።

4. የለሊቱ እርጋታና የኢማን ዑደት

የለሊት ሶላት ልብን ህያው የሚያደርግ መልካም መንገድ ነው። የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይላሉ፡-

عليكم بقيام الليل فإنه دأب الصالحين قبلكم، وقربة إلى الله تعالى، ومنهاة عن الإثم وتكفير للسيئات ومطردة للداء عن الجسد

“ለሊት እንድትሰግዱ አደራ ብያችኋለሁ። እርሱ ከናንተ በፊት የነበሩ ደጋግ ሰዎች ቀለብ ነው። ወደ አላህ መቃረቢያ ነው። ከኃጢያት ያግዳችኋል። ከአካልም በሽታን ያስወግዳል።”

የለሊቱን የልግስና ድግስ መታደም፣ የሚታደለውን ስጦታ ለማግኘት ከሙተሀጂዶቹ ጋር መሰለፍ ኢማን ከሚገኝባቸው መንገዶች አንዱ ነው። አምስቱ ሶላቶች ግድ ከመደረጋቸው በፊት የለሊት ሶላት በመልእክተኛውና ባልደረቦቻቸው ላይ ግዴታ ሆኖ ነበር። ምክንያቱም ሰው የለሊቱ መሀል ላይ ወደ ጌታው ሲገለል፣ ልቡ ከርሱ ጋር ሲቀጠል ይበልጥ ይፀዳል። ብዙ የፈጣሪ ስጦታዎች ይዘንቡለታል።

ይህ መንገድ ለሊቱን ለብዙ አገልግሎት እንድንጠቀምበት ይረዳናል። በቁርአን እንድናስተነትን፣ ሩኩዕና ሱጁድ ላይ ያሉትን ድልብ በረከቶች እንድንዘርፍ፣ እራስን ለጌታ በማዋረድ የሚገኘው ምርጥ ስሜትና አላህን በማውሳት የሚገኝ የልብ መረጋጋት… እነዚህ ልብን ወደ ፈጣሪው የሚቃርቡ ምርጥ መንገዶች ናቸው። ስለዚህ የረመዳን አንዲት ለሊትም ብትሆን ያለ ተሀጁድ ሶላት ማለፍ የለባትም። ስለዚህ የተሻለው አማራጭ ተራዊሕ መስጊድ ውስጥ ከመስገዳችን ባሻገር ከፈጅር ሶላት በፊት ለሶላትና ለኢስቲግፋር የሚበቃ ጊዜ እያለ መነሳት ነው።

እስኪ ይህን እንሞክረው! ወላሂ እውነተኛው ህይወትን እዚያው እናገኛለን። የንጋትን ውበት ከጌታችን ጋር እያወጋን ስናገኘው! እንዴት ይማርካል!!

አንዳንድ ሷሊሆች እንዲህ ብለዋል፡-

ليس في الدنيا وقت يشبه نعيم أهل الجنة إلا ما يجده أهل التملق في قلوبهم بالليل من حلاوة المناجاة

“ዱንያ ውስጥ የጀነት ሰዎች የሚያገኙት አይነት ፀጋ የለም። ነገርግን ተቅዋ ያላቸውና ጌታቸውን የናፈቁ ሰዎች ለሊት ላይ ከጌታቸው ጋር ሲያወጉ የሚያሳልፉት ጣፋጭ ጊዜ የጀነቱን ፀጋ ይመሳሰላል።”

ኢቅባል እንዲህ ይላሉ፡-

“ምንም አይነት ሰው ሁን። የፈለገውን ያህል እውቀትና ጥበብ ይኑርህ። በለሊት የምትረጋበት ጊዜ ከሌለህ ጠብ የሚል፣ ዋጋ ያለው ሥራ የለህም።”

ይህን ንግግር ላብራራው። እንዲህ ማለት ነው። ምርጥ ዳዒ፣ አንደበተ-ርቱዕ መካሪ፣ አንጋፋ መምህር… ወይም የሻኸውን ሁሉ ሁን። ለሊት ላይ ከአላህ ጋር የምታሳልፈው፣ የስሜት ልብስህን የምታወልቅበት፣ የክብር ካባህን የምትገፍበት… ጊዜ ከሌለህ ነፍስህን መርዳት አትችልም። ለሊት ላይ ከንቱ ማዕረጎችህን አውልቀህ የጌታውን ቁጣ የሚፈራና ምህረቱን የሚመኝ ባሪያን ምስኪንነት ልበስ። ፍላጎትህን ጠቅልለህ አዘጋጅ። ዓላማህን ወስን። እንቅልፍ ቀንስ። ከውዱ ጌታህ ጋር ለምታደርገው ግንኙነት እራስህን አዘጋጅ። ሰከንዶቹን ሁሉ እየቆጠርክ የሚከፈትልህን በር ጠብቅ። ከዚያህም ጉዳይህን ሁሉ ይዘህ ግባ። የምትሻውን ሁሉ ይቸርሀል።

  • የለሊት ሶላት ፊቅሆች

አላህ ለግሶልን ከፈጅር በፊት ከተነሳን መቆማችንን ብቻ ሳይሆን ሩኩዕና ሱጁዳችንንም ማርዘም አለብን። “ባርያ ሁሉ ለጌታው ይበልጥ የሚቀርበው ሱጁድ ላይ ሆኖ ነው።” ሱጁድ ላይ ንግስና ሁሉ በእጁ ለሆነው አምላክ ያለንን መተናነስ፣ ፍላጎት፣ ውርደትና ምስኪንነት እናሳይበታለን።

እዚህ ጋር የምናነሳው ምርጥ ግንዛቤ አለ። ዶክተር ዐብዱስ-ሰታር ፈትሑላህ የነገሩንን ነው። እንዲህ ይላሉ። በሱረቱል ሙዝ-ዘሚል ውስጥ አላህ በነብዩ ላይ የለሊት ሶላት ግዴታ አደረገባቸው። ሱረቱል ሙዝ-ዘሚል መጀመሪያ ከወረዱት የቁርአን ሱራዎች መሀል አንዱ ነው። በዚህ ጊዜ በወረዱት ጥቂት አንቀፆች ከግማሽ ለሊት በኋላ እንዲያነጉ እንዴት ታዘዙ!? ይህ የሚያሳየው ከቂያሙ ጋር ሱጁድና ሩኩዕ መርዘማቸውም ተፈላጊ ነበር ማለት ነው።

ሱጁድ አላህን የማዋየት፣ ወደርሱ የመጠጋትና ወደርሱ የመሸሽ ምርጥ ማሳያ ነው። ውዴታውን የምንለምንበት፣ ይቅርታውን የምንጠይቅበት፣ መዋረዳችንን እና ለርሱ መተናነሳችንን የምናሳይበት ምርጥ ሁኔታ ነው። እርሱ ላይ ጉዳያችንን ሁሉ ለአላህ ማቅረብና ችግራችንን መመስሞት እንችላለን።

  • ስገድም (ወደ አላህ) ተቃረብም

የሱጁድን አላማ ማሳካት እና ወደርሱ መቃረቢያ ማድረግ ከፈለክ ሱጁድህን የሞቀ አድርገው። ወደ ጌታህ እንዲደርስልህ የምትሻውን መልእክት በእምባህ ጎርፍ አሻግረው። በለቅሶህ ክተበው።

ዐብዱላህ ኢብኑ ሙባረክ እንዲህ ብለዋል፡-

“ለሊቱ ሲጨልም ይታገሉበታል

እስኪወግግ ድረስ በሶላት ይነጋል

ፍርሀት አብርሮት እንቅልፋቸውን

ጎናቸው ራቀ መንጋለያውን

ፍርሀተ-ቢሶች ከአላህ የራቁ

ለሊቱን ሲገፉ እንቅልፍ ሲደልቁ

ጨለማ ዋጣቸው ደጋግ ሰዎችን

እየተማፀኑ ታላቅ ጌታቸውን

የጨለማን ውበት

በጌታ አብርተውት

መስገጃቸውንም በምባ አርጥበውት

ንጋቱ ይመጣል እየነፈረቁ በለቅሶ አጅበውት”

  • የለሊት ሶላት ከተነፈግን ምን እናድርግ?!

ለሊት ተሀጁድ ላይ ለመንቃት የሚረዱንን ነገሮች ሁሉ አድርገናል። ነገርግን የሚቀሰቅሰን የፈጅር አዛን ነው። ምን እናድርግ? የሚል ጥያቄ ቢከሰት እንዲህ ብለን እንመልስ።

ይህ መነፈግ የአላህ መልእክት ነው። ለባሪያው ትምህርትና ተግሳፅ የያዘ መልእክት። መልእክቱ በተለያየ መልኩ ሊተረጎም ይቻላል። ለምሳሌ በሰራነው ኃጢያት እየተቀጣን ሊሆን ይችላል። ከአላህ መብቶች መሀል ያላሟላናቸው አሉ ማለትን ሊጠቁመን ይሆናል። ለሊት ለመስገድ ያለን ፍላጎት ደካማ ስለሆነም ሊሆን ይችላል። ወይም ምን እንደምንሠራ ለማወቅ አላህ ሊፈትነን ይሆናል።….

እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲገጥሙ ወደ አላህ መሸሽ ይገባል። ሶላት ሰግደን፣ ምህረት እየለመንን፣ ዱዓ እያደረግን፣ ይቅር እንዲለን እየተማፀንን ወደ አላህ መዞር አለብን።

የለሊት ሶላት ያመለጠው ሰው ከፈጅር እስከ ዙህር ድረስ ባለው ወቅት ቀዳ ያውጣው የሚል- ሙስሊም በዘገቡት ላይ- የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ምክር ላይ እናገኛለን።

አንዳንድ ጊዜ ከሱብሒ በፊት እንነቃና ወደ ሶላት ውስጥ ስንገባ ግን ልባችን ወደ ዱንያ ሸለቆ ይሸሸጋል። እርሱን ለመሰብሰብ ብንጥርም ከሽሽት መመለስ አልቻልንም። ምን እናድግ!?

ኢብኑል ጀውዚይ እንዲህ ይላሉ፡-

“በለሊቱ ጨለማ ውስጥ ከጌታህ ፊት ስትቆም የህፃን ባህሪ ተላብሰህ ቁም። ህፃን ከአባቱ የሆነን ነገር ፈልጎ ካልተሰጠው ያለቅስበታል።”

አደራ አላህን ችክ ብለን መለመን አለብን። ደጋግመን ምህረት መለመን አለብን። በሩ እስኪከፈትልን ማንኳኳት አለብን። አላህ እንዲህ ይለናል፡-

فَلَوْلَا إِذْ جَاءَهُم بَأْسُنَا تَضَرَّعُوا

“ታዲያ ቅጣታችን በመጣባቸው ጊዜ አይዋደቁም ኖሯልን?” (አል-አንዓም 6፤ 43)

ለሊት አለመቆም ወይም የለሊት ሶላት ጥፍጥና መነፈግና ልብ ወደ አላህ እንዳይዞር መከልከል አላህ እኛን የሚቀጣበት አንድ መንገድ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ወደርሱ መመለስ፣ መተናነስ፣ ምህረት መለመን… አለብን። ምናልባት በዚህ ሁኔታ ሲያየን ሊምረንና ይቅር ሊለን ይችላል።

5. ከተከበሩ ወቅቶች መጠቀም

ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ይላሉ፡-

“አላህ ለአንዳንድ ወራት የተለየ ክብር ሰጥቷል። አንዳንድ የለሊትና የቀን ክፍሎችን ልዩ ክብር እንደቸረ ማለት ነው። ለይለቱልቀድርን ከአንድ ሺህ ወራት በላይ እንድትሆን አድርጓል።… እያንዳንዱ ልዩ አጋጣሚ ወደ አላህ የምንቃረብበት የራሱ የሆነን ተግባር አካቷል። በእነዚሁ አጋጣሚዎች አላህም ለባሮቹ የሚቸረው ልዩ ስጦታ አለው። እድለኛ ማለት እነዚህን አጋጣሚዎች ጌታውን ለማገልገል በመንቀሳቀስ የተጠመደና በተከበሩት ወራትና ሰዓቶች ውስጥ ያለውን የጌታ ስጦታ የዘረፈ ሰው ነው። እነዚህን ስጦታዎች ማግኘት ማለት ከእሳት እራስን መጠበቅ ማለት ነው። የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይላሉ፡-ጌታችሁ በአመቱ ቀናት ውስጥ ታላላቅ ስጦታዎች (ነፈሓት) አሉት። እራሳችሁን ለነርሱ አቅርቡ። ምናልባት አንዱን ስጦታ ያገኘ ሰው ለዘላለም እድለቢስ አይሆንም።”

እራሱን ለነዚህ ነፈሓት ያቀረበ ያለጥርጥር ትርፎችን ያገኛል። ዝንጉ የሆነና እራሱን ለስጦታዎቹ ያላቀረበ የተነፈገ ሰው ነው!!

በሀያ አራት ሠዓት ውስጥ ወደ አላህ ይበልጥ የምንቀርብባቸው ሦስት ወቅቶች አሉ። እነርሱም የለሊቱ መባቻ፣ የቀኑ መጀመሪያ እና የቀኑ መጨረሻ ናቸው።

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይላሉ፡-

إن هذا الدين يسر ولن يشاد الدين أحد إلا غلبه فسددوا وقاربوا وابشروا واستعينوا بالغدوة والروحة وشيء من الدلجة

“ይህ ዲን ገር ነው። ዲንን የሚያካብድ ሰው የለም የሚያሸንፈው ቢሆን እንጂ። (በአላህ ትእዛዝ ላይ) ቀጥ በሉ። መሀለኛ ሁኑ። አይዟችሁ። በጧትና በከሰዓት እንዲሁም በለሊቱ ጥቂት ሠዐት ታገዙ።”

የጧትና የምሽት ውዳሴን የዘገቡ ብዙ ሐዲሶች ላይ ጧትና ማታ አላህን ማወደስ ልዩ ትርፍ እንዳለው ተጠቅሶ እናገኛለን። ሰለፎች በበኩላቸው የከሰዓት በኋላውን ጊዜ ከመጀመሪያው ይበልጥ ያልቁት ነበር።

ኢማም ሐሰን አል-በና እንዲህ ይላሉ፡-

أيها الأخ العزيز أمامك كل يوم لحظة بالغداة ولحظة بالعشى ولحظة بالسحر تستطيع أن تسمو فيها كلها بروحك الطهور إلى الملأ الأعلى، فتظفر بخير الدنيا والأخرة.. وأمامك مواسم الطاعات وأيام العبادات وليالي القروبات التي وجهك إليها كتابك الكريم ورسولك العظيم صلى الله عليه وسلم، فأحرص أن تكون فيها من الذاكرين لا من الغافلين، ومن العاملين لا من الخاملين.. واغتنم الوقت فالوقت كالسيف، ودع التسويف فلا أضر منه

“የተከበርክ ወንድሜ ሆይ! በጧት፣ ከሰዓት በኋላና ዶሮ ጩኸት አካባቢ ንፁህ መንፈስህን ወደ ላይኞቹ ባለሟሎች ማሳደግ ትችላለህ። ከዚያም የዱንያና የአኼራን ኸይሮች ታገኛለህ።… ከፊትህ ወደ አላህ የምትቃረብባቸው፣ ለአላህ ይበልጥ ታዛዥ መሆንህን የምትገልፅባቸው፣ አምልኮ ላይ የምትበረታባቸው ጊዜያት አሉ። እነዚህን ቀናቶች እንድትጠቀምባቸው ቁርአንና መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) አስተምረውሀል። ስለዚህ በነዚህ ጊዜያት አላህን ከሚያወሱ እንጂ ከሚዘናጉ እንዳትሆን። ከሠራተኞች እንጂ ከሥራ ፈቶች እንዳትደመር።… ጊዜህን በአግባቡ ተጠቀም። ጊዜ ሰይፍ ነው። ነገ-ዛሬ ማለትን ተው። ከርሱ የበለጠ ጎጂ ነገር የለምና።”

በየሳምንቱ የሚከሠቱ ልዩ ወቅቶችም አሉ። ከቀናት ውስጥ የጁሙዓ ቀን ታላቅ ክብር አለው። ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝበት ልዩ ሠዓትን በውስጡ አካቷል። ስለዚህ ለዚህ ቀን ስጦታ ራሳችንን እናቅርብ። ኢማም አን-ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፡-

“የጁሙዐህ ቀን ውስጥ ከፈጅር ጀምሮ ፀሐይ እስከሚጠልቅ ድረስ በሙሉ ዱዓ ማብዛት ይወደዳል። ምክንያቱም የኢጃባው (ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝበት) ሠዓት መች እንደሆነ ስለማይታወቅ እንዳያመልጠን ለማድረግ ነው። ይህ ቀን ላይ ለዒባዳ መታገል አለብን። ልዩ የዒባዳ ፕሮግራምም ልናወጣለት ይገባል። የጁሙዐህ ሶላታችንን ለማሳመር ጧት በጊዜ ወደ መስጂድ እንሂድ።…”

ረመዳን ከወራት መሀል ልዩ እንደመሆኑ ለይለቱል-ቀድር ደግሞ ከረመዳን ቀናቶች መሀል ልዩ ስፍራ አለው።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

من قام ليلة القدر إيمانا واحتسابا غُفر له ما تقدم من ذنبه

“ለይለቱል-ቀድርን በኢማንና ከአላህ አጅር አገኛለሁ ብሎ በማሰብ የቆመ ሠው ያስቀደመውን ኃጢያት ሁሉ ይማራል።”

ለይለቱል-ቀድርን መፈለግ የሚገባው አስሩ የመጨረሻ የረመዳን ቀናት ላይ ነው። ስለዚህ እጅግ በጣም መጠንከር ያስፈልጋል። ለዚህ ነው“የአላህ መልእክተኛ የረመዳን ወር የመጨረሻው አስር ቀን ሲገባ ሽርጣቸውን ያጠብቃሉ። ለሊታቸውን ህያው ያደርጋሉ። ቤተሰቦቻቸውን ያነቃሉ።”

ከእነዚህ ምርጥ የስጦታ አጋጣሚዎች መሀል ሌላኛው የዑምራ አጋጣሚ ነው። ሁላችንም ይህን ስጦታ ለማግኘት እንመኝ።ሁሉ ነገራችንን ለእነዚህ ስጦታዎች ለመጣድ እናሰናዳ። አንዱ አጋጣሚ ቢያመልጠን ሌላኛውን ለማግኘት እንታገል።

6. ኢዕቲካፍ

ኢዕቲካፍ መስጂድ ውስጥ መቆየት ማለት ነው። ረመዳን ውስጥም ይሁን ከረመዳን በኋላ የሚወደድ ዒባዳ ነው። በተለይ የረመዳን አስሩ ቀናት ውስጥ ይበልጥ ይወደዳል። ምክንያቱም እነዚህ ቀናት ውስጥ ከአንድ ሺህ ወራት በላይ የሚሆነው ለይለቱል-ቀድር ይገኛል። ኢማም አህመድ ኢዕቲካፍ የሚያደርግ ሰው ከሠዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ባይኖረው ይመርጣሉ። ቁርአን ለማስቀራት ወይም ዒልም ለማስተማርም ቢሆን ከሠዎች ጋር ባይገናኝ ጥሩ ነው። ኢዕቲካፍ ያደረገ ሰው መገለል ይወደድለታል። ከጌታው ጋር በመዋየትና በዱዓ ቢጠመድ መልካም ነው። ይህ መገለል (ኸልዋ) የጀመዓና የጁሙዓ ሶላት የማይተውበት ሸሪዓዊ ተግባር ነው። በረመዳን ቀናት ውስጥ ምንም ቢያጥር የተወሰነ ሰዓት ኢዕቲካፍ ነይተን የምንቀመጥበት ሠዓት ያስፈልገናል። በተለይም በአስሩ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ አብዝሀኛ ጊዜያችንን በመስጂድ ውስጥ ማሳለፍ አለብን። ቀን ሥራ ላይ የሚያሳልፍ ወይም በቀን ኢዕቲካፍ ማድረግ የማይችል ሠው ለሊቱን ይጠቀም። መስጂድ ኢዕቲካፍ ብለን ከገባን ደግሞ ከአላስፈላጊ ቅልቅልና ከማይጠቅም ወሬ መገለል ያስፈልጋል። ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ይላሉ፡-“የኢዕቲካፍ ዓላማ ለፈጣሪ ኺድማ ሲባል ከፍጡራን ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ ነው።”

ሙስሊም እህቶቻችንም በቤታቸው መስጂድ ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይችላሉ፤ እንደ ሐነፊያዎች አስተያየት። ስለዚህ ከቀን ውስጥ የተወሰኑ ሠዓታትን ወደ አላህ ለመዞር የቤቷ መስጊድ ውስጥ ብትቀመጥ ይበቃታል።

7. ዱዓ

“ዱዓ ዒባዳ ነው።” “ከርሱ በቀር ቀደርን የሚመልስ ሌላ ነገር የለም።” የነገሮች ባለቤትነት በእጁ ላይ ለሆነው አምላክ የሚደረግ መተናነስና መዋረድ የሚንፀባረቅበት ታላቅ ማሳያ ነው።…

ዱዓ ተወዳጅ የሚሆንባቸው ወቅቶች አሉ። ከእነዚህ መሀል እነዚህን እንጥቀስ። አዛንና ኢቃማ መሀል፣ ከፈርድ ሶላት በኋላ፣ የለሊቱ የመጨረሻው ሲሶ ሲቀር፣ የጁሙዓህ ቀን ኢማሙ ለኹጥባ ሚንበር ላይ ከወጣ አንስቶ ሶላት እስከሚያበቃ፣ የጁሙዓ ቀን የመጨረሻዎቹ ሰዓታት፣ ለይለቱል ቀድር ላይ፣ ዝናብ ሲዘንብ፣ ፆመኛ ሲያፈጥር፣ ሙሳፊር (መንገደኛ)…

የረመዳን እያንዳንዱ ለሊት ላይ ከእሳት ነፃ የሚደረጉ ሰዎች አሉ… ባርያ ወደ ጌታ ከሚቀርብባቸው ጊዜያት ዋነኛው ሱጁድ ላይ ነው። ስለዚህ እነዚህን አጋጣሚዎች እንጠቀምባቸው። ለአላህ ያለንን ክብርና መተናነስ እንግለፅባቸው። ከኃይልና ብልሀታችንም እንፅዳ። እዝነቱንና ቸርነቱን እንለምነው። የዱንያና የአኼራ መልካም ነገሮችን ሁሉ እንጠይቀው። ልባችን ሳንሰበስብ በምላሳችን ብቻ ከምናደርገው ዱዓም እንጠንቀቅ።

የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

واعلموا أن الله لا يستجيب الدعاء من قلب غافل لاه

“እወቁ! አላህ ዝንጉና ቸላተኛ ከሆነ ልብ ልመናን አይቀበልም።”

በየቦታው በበደል ለሚረግፉት እና ለሚጨፈጨፉት ሙስሊሞች የተለየ ዱዓ እናድርግ። እንዲሁም በየሥፍራው ድንበር የሚያልፉ እና በደል የሚፈፅሙ ጠማማዎች ላይ እርግማን እናውርድ። አላህ የሙስሊሙን ጭንቀት እንዲገላግል፣ ችግሩን እንዲቀርፍና ቃል የገባልንን ድል እንዲያወርድልን እንለማመነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَكَانَ حَقًّا عَلَيْنَا نَصْرُ الْمُؤْمِنِينَ

“ምእመኖቹንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ።” (አር-ሩም 30፤ 47)

8. ሶደቃ (ምፅዋት)

የአላህን ኪታብ የሚያጠና ሰው ሁሉ አላህ ሙስሊሞች ገንዘባቸውን በአላህ መንገድ ወጭ እንዲያደርጉ ሲቀሰቅስ ይመለከታል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከማንም በላይ ቸር ነበሩ። እጅግ በጣም ቸር የሚሆኑት ደግሞ በረመዳን ነው። አላህ እንዲህ ይላል

خُذْ مِنْ أَمْوَالِهِمْ صَدَقَةً تُطَهِّرُهُمْ وَتُزَكِّيهِم

“ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ።” (አት-ተውባ 9፤ 103)

ከሶደቃ የሚጠቀመው የመጀመሪያው ሰው ሶደቃ አድራጊው ነው። ምክንያቱም ከስስት ታጠራዋለች። ከኃጢያትም ትጠብቀዋለች። ከመከራም ትከላከልለታለች።

ነፍስ ወደ ላይ ከፍ ለማለት የምታኮበኩብበትና ከምድር ስበት የምትርቅበት የመጀመሪያ ርምጃዋም ከስስት መዳኗ ነው። ሁሌም ቢሆን ሶደቃ ማብዛት አለብን። ቸርነት የስብእናችን መገለጫ እስኪሆን ድረስ ወጪ መልመድ አለብን። ከዚያም ከገንዘብ ፍቅር እንድናለን። ለአኼራ ያለን ዝንባሌም ያብባል።

ሶደቃ በዱንያም ሆነ በአኼራ ታላቅ ትርፍ ያስገኛል። ህመምተኞችን ይፈውሳል። በላእን ይገፈትራል። ጉዳይን ያግራራል። ሪዝቅ ያመጣል። ከክፉ አወዳደቅ ይጠብቃል። የጌታን ቁጣ ያጠፋል። የኃጢያት ፋናን ያስወግዳል። የቂያም ቀን ለሶዳቂው ጥላ ይሆናል። ከእሳት የሚከላከልበት ጋሻም ይሆንለታል። ከቅጣት የሚከላከልበት መደበቂያ ይሆንለታል። ሶደቃ ወደ አላህ ከምናደርገው ጉዞ ጋር ጠንካራ ትስስር አለው።

አላህ እንዲህ ይላል፡-

فَآتِ ذَا الْقُرْبَىٰ حَقَّهُ وَالْمِسْكِينَ وَابْنَ السَّبِيلِ ۚ ذَٰلِكَ خَيْرٌ لِّلَّذِينَ يُرِيدُونَ وَجْهَ اللَّهِ ۖ وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“የዝምድናን ባለቤት ተገቢውን ስጠው። ለድኻም ለመንገደኛም (እርዳ)። ይህ ለእነዚያ የአላህን ፊት (ውዴታውን) ለሚሹ መልካም ነው። እነዚያም እነርሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።” (አር-ሩም ፤ 38)

ማንም ሰው ቢሆን ሰደቃ ማድረግ ይችላል። ሶደቃ የሚተውበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። ሶደቃ የምናደርግበት መጠን ገደብ የለውም። የምንችለውን ሶደቃ እናድርግ። በሩ ለሁሉም ክፍት ነው።

ሶደቃ ፍሬ እንዲኖረው በየቀኑ መደጋገም አለበት። አላህ እንዲህ አለ፡-

الَّذِينَ يُنفِقُونَ أَمْوَالَهُم بِاللَّيْلِ وَالنَّهَارِ سِرًّا وَعَلَانِيَةً فَلَهُمْ أَجْرُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ وَلَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ

“እነዚያ ገንዘቦቻቸውን በሌሊትና በቀን በድብቅም በግልጽም የሚለግሱ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው። በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም።” (አል-በቀራ 2፤ 274)

የተምር ክፋይ የሚያህልም ቢሆን በየቀኑ ሶደቃ እናድርግ። ቤታችን ውስጥ የሶደቃ ሳጥን እንወስን። ባመቸን ጊዜ ሶደቃችንን እናጠራቅምና ለሚገባቸው እናድርስ። በዚህ መልኩ ሶደቃ ላይ እንዘውትር።

9. ፊክርና ዚክር

አላህን ማውሳት የልብ ቀለብ ነው። የህይወቱም መሰረት ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

مثل الذي يذكر ربه والذي لا يذكر ربه مثل الحي والميت

“ጌታውን የሚያወሳ ሰውና ጌታውን የማይዘክር ሰው ምሳሌያቸው ህይወት እንዳለውና እንደሞተ ሠው ነው።”

ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ብለዋል፡-

الذكر للقلب مثل الماء للسمك، فكيف يكون حال السمك إذا فارق الماء ودور الجنة تبنى بالذكر، فإذا أمسك الذاكر عن الذكر أمسكت الملائكة عن البناء. فإذا أخذ في الذكر أخذو في البناء

“ዚክር ለቀልብ ልክ እንደ ውሀ ለአሳ ነው። አሳ ከውሀ ውስጥ ሲወጣ እንዴት ይሆናል!!?… የጀነት ቤቶች የሚሰሩት በዚክር ነው። ዛኪር ከዚክር ሲቋረጥ መላኢካዎቹም ከመገንባት ይቋረጣሉ። ሲዘክር ደግሞ ይገነባሉ።”

ሙስሊም ከዚክር እንዲጠቀም፣ ልቡንና ምላሱን አንድ እንዲያደርግ እና የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት እንዲረዳው ከተፈኩር (ከማስተንተን) ጋር ማስተሳሰር መልካም ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ فِي خَلْقِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافِ اللَّيْلِ وَالنَّهَارِ لَآيَاتٍ لِّأُولِي الْأَلْبَابِ * الَّذِينَ يَذْكُرُونَ اللَّهَ قِيَامًا وَقُعُودًا وَعَلَىٰ جُنُوبِهِمْ وَيَتَفَكَّرُونَ فِي خَلْقِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ رَبَّنَا مَا خَلَقْتَ هَٰذَا بَاطِلًا سُبْحَانَكَ فَقِنَا عَذَابَ النَّارِ

“ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ። (እነርሱም) እነዚያ ቆመው፣ ተቀምጠውም፣ በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወሱ በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ፡- ‘ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ ጥራት ይገባህ፤ ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን’ የሚሉ ናቸው።” (አሊ ዒምራን 3፤ 190-191)
“ዓቅል ያላቸው ሰዎች ዚክርን ከፊክር ጋር ፊክርንም ከዚክር ጋር ከማቆራኘት አልቦዘኑም። ከዚያም ልባቸውን አናገሩት ጥበብ ተናገረ።” ብለዋል፤ ሐሰኑል በስሪይ።

የዚክር መጀመሪያው ተፈኩር ነው። አንድን ጉዳይ አስታውሶ ከማስተንተን ዚክር ይወለዳል። ለምሳሌ አንድ ሰው ወንጀሉን ካስታወሰ እና ከአላህ መብት ያጓደለውን ካስተነተነ ኢስቲግፋርን ያስከትላል። የአላህን ጥበብና ኃያልነት የሚጠቁሙ ፍጥረታትንና ተአምራትን ሲመለከትና ሲያስተነትን ተስቢሕና ተሕሚድ (ምስጋናና አላህን ከጉድለት ማጥራት) ይከተላል። ከባድ ችግር ሲገጥመውና ወደ አላህ ያለውን ክጃሎት ሲያስብና ሲያስተነትን “ላሐውለ ወላቁው-ወተ ኢል-ላ ቢል-ላሂል-ዓሊዪል ዓዚም” ይላል፤ ከአላህ በቀር ኃይልና ብልሀት የለም ማለት። ሌሎችም ዚክሮች ላይ እንዲሁ፤ ከፊክር ዚክር ይወለዳል።

ለነፍሳችን የዚክርና የፊክር ፕሮግራም እናድርግ። ከዚያም የዚክር ፋይዳ ወደ ልብ እንዲደርስ የሚያስፈልገውን እናድርግ። የሥራችን ምንዳ የሚሟላው በሠራነው ሥራ ምሉዕነት ተመዝኖ ነው። ሥራዎች በቅርፃቸውና በቁጥራቸው አይለያዩም። የሚለያዩት ልብ ውስጥ ባለው የተመስጥኦ ልዩነት ብቻ ነው። ስለዚህ የሁለት ሥራዎች ቅርፅ አንድ ሆኖ የሠማይና የምድር ያህል ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል።

የጧትና የማታ ዚክር ውስጥና የአንዳንድ ሁኔታዎች (አዝካሩል አህዋል) ዚክር ላይ መንፈስን የሚያነቁ ታላላቅ ጉዳዮች ተወስተዋል። ስለዚህ እነዚህን ዚክሮች በወቅታቸው ስንላቸው ውስጣቸው ያቀፈውን ትርጓሜ መዘንጋት የለብንም። ማስተንተን አለብን።

10. ነፍስን መተሳሰብ

ከጥቂት የረመዳን ቀናት በኋላ ነፍስ ለጌታዋ መመሪያ ታዛዥ ትሆናለች። ስለዚህ ባሳለፈችው ጊዜ ስለሠራችው ሥራ መተሳሰብ ብንጀምር አታስቸግረንም። ነፍሳችንን የምንተሳሰብባቸው የተለያዩ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ጉዳዮች የሙስሊምን ህይወት በሙሉ የከበቡ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰው እያንዳንዱን የህይወቱን ክፍል መገምገም እና ማስተዋል ይጠበቅበታል። ከዚያም እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እግሩ ያረፈበትን ደረጃ መመልከት ይችላል። በተለይም ኃጢያታችንን ብንቆጥርና ያጓደልናቸውን ሐቆች ብንዘረዝር መልካም ተውበት እንድናደርግና አካሄዳችንን እንድናሳምር ጠቃሚ ጉልበት ይሰጠናል።

የሙሐሰባ (ራስን የመተሳሰብ) ፈኖች

  1. የአካል ዒባዳዎች፡- አምስት ወቅት ሶላቶችን በመጀመሪያ ወቅታቸው ላይ መስጂድ ውስጥ መስገድ፣ ፈርድ ሶላቶችን ተከትለው የሚመጡትን ሱናዎች መስገድ፣ የሶላት ዚክሮችን ማሟላት፣ የረመዳን ፆምና ሱና ፆሞች፣ በአላህ መንገድ አዘውትሮ መለገስ፣ የጧትና የምሽት ዚክር፣ ንግግርና ተግባር ላይ ሱናን መጠበቅ….
  2. የአካል ኃጢያቶች:- ሐሜት፣ ነገር ማዋሰድ፣ ሰው ላይ ማሾፍ፣ ስላቅ፣ ክርክር፣ የሠውን ምስጢር ማጋለጥ፣ ዘለፋ፣ ውሸት፣ ውድቅ ንግግር፣ የማያውቁትን ማውራት (ሰርሰራ)፣ ዓይንን ከክልክል እይታ አለመጨፈን፣ ብላሽ ነገር ውስጥ መዘፈቅ፣ ቸኩሎ መቆጣት፣ ቃል ኪዳንን ማፍረስ….
  3. የልብ አምልኮዎች:- ሶላት ውስጥ ኹሹዕ (ተመስጥዖ)፣ አላህን መፍራትና እርሱን መጠባበቅ (ሙራቀባህ)፣ የአላህን ውሳኔና ፍርድን መውደድ፣ በአላህ መመካት፣ በአደጋ ጊዜ መታገስ፣ በፀጋ ጊዜ ማመስገን…
  4. የልብ ኃጢያቶች:- በራስ ሥራ መደነቅ፣ መልካም ሥራው እንዲሠማለት መፈለግ፣ ትችትን መስጋት፣ ምቀኝነት፣ ራስን ማታለል፣ ፉክክር፣ በሥጦታ መመፃደቅ፣ ሌሎችን መናቅ፣ ስሜትን መከተል፣ ቂም…
  5. ሐቆች:- የሚስት/የባል ሐቅ፣ የልጆች ሐቅ፣ የወላጆች ሐቅ፣ የዝምድና ሐቅ፣ የጎረቤት ሐቅ፣ የመንገድ ሐቅ፣ የዳዕዋ ሐቅ፣ የወንድማማችነት ሐቅ….
  6. መልካም ሥራዎች፡- የሙስሊሞችን ጉዳይ ለመፈፀም መሯሯጥ፣ ጎንን ማቅለል፣ መተናነስ፣ ህመምተኛን መጠየቅ፣ አስክሬን መሸኘት፣ መልካምን ነገር ለሌሎች መዋል፣ አደራን መወጣት፣ ደስታንና ፈገግታን ማሳየት፣ ሥራን አሳምሮ መሥራት…

ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት እራሳችንን የምንገመግምባቸው ነጥቦች ናቸው። ከእያንዳንዱ ግምገማ በኋላ የአላህን ምህረት መለመን አለብን። ከተቻለንም በውስጧ ኢስቲግፋር የምናበዛባት ሶላት (ሶላቱት-ተውባ) ብንሰግድ መልካም ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ إِذَا فَعَلُوا فَاحِشَةً أَوْ ظَلَمُوا أَنفُسَهُمْ ذَكَرُوا اللَّهَ فَاسْتَغْفَرُوا لِذُنُوبِهِمْ وَمَن يَغْفِرُ الذُّنُوبَ إِلَّا اللَّهُ وَلَمْ يُصِرُّوا عَلَىٰ مَا فَعَلُوا وَهُمْ يَعْلَمُونَ

“ለእነዚያም መጥፎ ሥራን በሠሩ ወይም ነፍሶቻቸውን በበደሉ ጊዜ አላህን የሚያስታውሱና ለኀጢአቶቻቸው ምሕረትን የሚለምኑ ለኾኑት ከአላህም ሌላ ኀጢአቶችን የሚምር አንድም የለ። (በስሕተት) በሠሩትም ላይ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑ የማይዘወትሩ ለኾኑት (ተደግሳለች)።” (አሊ ዒምራን 3፤ 135)

የሁለተኛው ክፍል ማጠቃለያ

እዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት የረመዳንን ፍሬዎች የምንጠቀምባቸው አስር ነገሮች ናቸው። እነዚህን ጥቆማዎች አስታከን ወሩን በሙሉ የምንገለገልበት ፕሮግራም ብናወጣ መልካም ነው። ለእያንዳንዱ ቀንም የማንለውጣቸው ቋሚ ሥራዎች እንያዝ። መስጂድ ውስጥ ለምናደርገው ኢዕቲካፍ ቋሚ ጊዜ እንወስን። ከፈጅር ሶላት በኋላ ፀሐይ እስከሚወጣ ድረስ ብናደርገው፤ ይህን ካልቻልን ደግሞ ከዐስር ሶላት በኋላ እስከ መቅሪብ ሶላት ድረስ ብንወስን፤ ይህንን የኢዕቲካፍ ጊዜያችንን ከዚህ በፊት በተናገርነው መልኩ ቁርአን በመቅራት ብናሳልፍ ጥሩ ሠርተናል።

ቤታችን ውስጥ አንድ ሳጥን ብናዘጋጅና የየቀን ሶደቃችንን እዚያ ውስጥ ማጠራቀም ብንለምድ። ከፈጅር በፊት ሰላሳ ደቂቃም ቢሆን ከሶላቱ-ት-ተራዊሕ ውጭ ለተሀጁድ የተወሰነ ጊዜ ብናደርገው…

ከዚክሮች መሀል በቀን ቢያንስ መቶ ጊዜ “ሱብሐነል-ላሂ ወቢሐምዲሒ” ብንል፣ መቶ ጊዜ ኢስቲግፋር ብናደርግ፣ “አል-ላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወአሊሂ” እያልን መቶ ጊዜ በነብዩ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ሶለዋት (እዝነት) ብናወርድ፣ መቶ ጊዜ “ላሓውለ ወላ ቁው-ወተ ኢል-ላ ቢል-ላሂል-ዓሊዪል ዓዚም” ብለን ኃይልም ሆነ ብልሀት እንደሌለን ብናውጅ…. ከዚያም እነዚህን ዚክሮች ለቀንና ለሌት ብንመድባቸው ዚክራችንን አሳምረን ሰራን ማለት ነው።

ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝባቸውን ወቅቶች ጠብቀን አብዝተን ዱዓ ብናደርግ፣ ባህር ውስጥ ሊሰምጥ እንደቀረበ ችግረኛ ጌታችንን ብንለማመን፣ ለወንድሞቻችን እና ለሙስሊሞች ባጠቃላይ ዱዓ ብናደርግ ዱዓንም አሳምረን አደረግን ማለት ነው።

አንዳንድ ወቅቶች ላይ ደግሞ ከሠዎች ተነጥለን ያሳለፍነውን ሁሉ እያሰብን ምህረት ብንለምን ስራችንን በግምገማ ጠበቅነው። ያለንበትን የኢማን ደረጃም አወቅን ማለት ነው። ከዚያም ስህተታችንን ለማረምና ይበልጥ ለማደግ በኢስቲግፋር አዲስ መዝገብ መጀመር ነው።…

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here