የተራዊህ ሰላት ለጤና ያለው ፋይዳ

0
8446

ይህ አጠር ያለ ጽሁፍ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ ዓለማቀፋዊ ጥናቶችን በመመርኮዝ የቀረበ ነው።

የእስልምና ሃይማኖት በሰላት ውስጥ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ የስልጠና እንቅስቃሴዎች በቅንጅት የሚከናወኑበት ብቸኛው ሃይማኖት ነው፡፡ ሰላት ከመንፈሳዊ ጠቀሜታው ባለፈ አንድ ሰው ሰላትን ለማከናወን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላ ጥቅምም ያገኝበታል፡፡ አእምሮዊጭንቀቱንም ወደ ሰውነት ክፍሎቹ በመውሰድ አንድ ሰው ለአካሉም ሆነ ለነፍሱ ጥቅም ያገኝበታል፡፡

ምሁራን እንዳረጋገጡት ሰላት ከውዱእ ጀምሮ እስከ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ማለትም ተክቢራ፣ ሩኩዕ፣ ሱጁድ፣ መቀመጥና እስከማሰላመት ድረስ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ መንፈሳዊ የህክምና መሳሪያ በመሆኑ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከሱና እና ትርፍ ሰላቶች ውጭ ሙስሊሞች በቀን ውስጥ አምስት ጊዜ የግዴታ ሰላቶችን ይፈጽማሉ፡፡ በረመዳን ውስጥ ደግሞ ከነኚህ ሰላቶች በተጨማሪ ከዒሻ የግዴታ ሶላት በኋላ ተራዊህን ይሰግዳሉ፡፡

ምሁራን እንዳረጋገጡት ከስምንት እስከ ሀያ ረከዓ የሚሰገደው የተራዊህ ሰላት ጊዜ ለያንዳንዱ የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል ሚዛናዊ የሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በተለምዶ የሰው ልጅ በሚያደርገው ሚዛናዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ ተመጣጣኝ የሆነ የኦክስጆን መጠን አይደርሳቸውም፡፡ ኦክሲጅን ደግሞ ምግብንም ሆነ ሌሎች ጠቃሚ ነገሮችን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለማመላለስ ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡ በዚህም የተነሳ ኦክስጅን በሚገባ ያልደረሰው የሰውነት ክፍል የተኮማተረና የተጎዳ ሲሆን ሌላው የተፍታታ ሊሆን ይችላል፡፡ በሰላት ጊዜ ግን እንቅስቃሴው የደም ስሮችንም ጭምር ስለሚያፍታታ ደምም በቀላሉ ሊዘዋወር ይችላል፡፡ ወደ ልብ የሚመለስ ደምም መንገዱ ቀላል ይሆንለታል፡፡ ልብም ስራ ስለሚበዛበት በጫናው ምክንያት ግድግዳዎቹ ጥንካሬ ያገኙና ደም የመርጨት ስራውን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ ያስችለዋል፡፡

የዘርፉ ምሁራን ከኢፍጣር በኋላ የየሚፈፀመው ተራዊህ ሰላት የስኳር መጠን ለማስተካከል ከፍተኛ ሚና አለው ይላሉ፡፡ ከማፍጠር በፊት ባለው ሰዓት ውስጥ በደም ውስጥ የሚኖረው የስኳርና የኢንሱሊን መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከኢፍጣር አንድ ሰዓት በኋላ ግን የግሉኮስም ሆነ  የኢንሱሊን መጠን ከፍ ማለት ይጀምራሉ፡፡ ጉበትና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ደም ውስጥ የነበረውን ግሉኮስ መጠቀም ይጀምራሉ፡፡ ከአንድ እና ሁለት ሰዓት በኋላም የስኳር መጠን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ የተራዊህ ሰላት ስኳሩን ወደ ኦክስጅን እና ውሃ በመቀየር ረገድ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

የተራዊህ ሰላት ሰውነት ውስጥ የተከማቸን ትርፍ ካሎሪን ለማቃጠል ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡ ገላ ውበት እንዲያገኝና የሰውነት ክብደትም እንዲስተካከልና የተመጣጠነ እንዲሆንም ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ውጥረትን፣ ጭንቀትንና መጥፎ ስሜትንም ያስታግሳል፡፡

በአሜሪካ የኢስላማዊ የምርምር ተቋም ተመራማሪዎች እንደሚሉት የተራዊህ ሰላት አመጋገብን መሰረት ባላደረገ መልኩ ከመጠን በላይ የሆነ ክብደትን ለመቀነስና ትርፍ ካሎሪን ለማቃጠልም ይጠቅማል፡፡ ስለሆነም በኢፍጣር ወቅት ጤናማና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በመመገብ የተራዊህ ሰላትን መስገድ ክብደትን ለመቀነስን በሰውነት ውስጥ የተጠራቀመውን ስብ ለማቃጠል ብሎም ለማቃለል ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በግዴታም ሆነ በሱንና ሶላቶች ላይ የሚዘወትሩ ሰዎች ከፍተኛ በሆነ የስሜት ጥሩነት ይስተዋልባቸዋል፡፡ በእድሜ መግፋት ከሚያጋጥም የአጥንት መሳሳት እና መሰል በሽታዎችም የተጠበቁ ናቸው፡፡ በሽምግልና ዘመናቸውም በጥሩ ጤና ላይ የሚገኙ ሲሆኑ ከሌሎች አንፃርም ሲታይ የሞት መጠኑ በግማሽ የወረደ ነው፡፡

አላህ ሰላታችንን እና ጾማችንን ይቀበለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here