በረመዳን ምን ይጠበቅብናል? (ክፍል 1)

1
6809

አላህ ለኛ ካለው እዝነትና ርህራሄ የተነሳ በዚህች ዱንያ ውስጥ ኢማን እና ተቅዋ የምንሰንቅባቸው ማረፊያዎችን አዘጋጀልን። በኛ ላይ የተንጠለጠሉ የኃጢያትና የመዘንጋት እድፎችን የምናወልቅባቸው ጊዜያትን ፈጠረልን። ነፍሳችንን ከፍ የምናደርግባቸው፣ የመዝገባችንን ስህተቶች የምናርምባቸው፣ በአዲስ መንፈስ የምንቀዝፍባቸው፣ ወኔያችን የሚጠነክርባቸው፣ የህይወትን ዐቀበት የምንወጣባቸው፣ አደጋዎቿን የምንቋቋምባቸው፣ አላህ እኛን የፈጠረበትን አላማ እንድንወጣ የምንታገዝባቸው… አንዳንድ ውድ ጊዜያትን አደረገልን።

እነዚህን ጊዜያት በቁጥር ለመገደብ የሚሞክር ሰው ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል።

በየቀኑ የሚመላለሱት የአምስት ወቅት ሶላቶች፣ በየሳምንቱ የሚናፈቀው ጁሙዓህ፣ በየአመቱ የሚመጣው ረመዳን፣ በእድሜ አንዴ የሚያጓጓው ሐጅ… ከእነዚህ መሀል የምንጠቅሳቸው ናቸው። እነዚህ ብቻ አይደሉም። በአመት ውስጥ ተበታትነው የምናገኛቸው፣ የአላህ እዝነት የሚንሰራፋባቸውና ብዙ ትሩፋቶች የሚገኙባቸው ጊዜያት አሉ።

እድለኛ ማለት የመልካም ሥራ መዝገቡን ያስተካከለ፣ ከእነዚህ የእዝነት ጊዜያት ለመጠቀም ራሱን ያዘጋጀ ሰው ነው። አትራፊ ማለት እድሉ ሳያመልጠው እጅጌውን ሰብስቦ በሥራ የተጠመደ ነው፤ ወደ አላህ ለሚያደርገው ጉዞ የሚያስፈልገውን ስንቅ ሳይሰንቅ እነዚህ ጊዜያት ያላመለጡት። አላህ እንዲህ አለ፡-

وَتَزَوَّدُوا فَإِنَّ خَيْرَ الزَّادِ التَّقْوَىٰ ۚ وَاتَّقُونِ يَا أُولِي الْأَلْبَابِ

ተሰነቁም፤ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህን መፍራት) ነው። የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ። (አል-በቀራህ 2፤ 197)

ለሙስሊሞች ከተከወኑ እነዚህ ማረፊያዎች መሀል በየአመቱ የሚከሰተው ረመዳን አንዱ ነው። ረመዳን የቀናት ጥርቅም ነው። በረከትን፣ ምህረትንና እዝነትን ይዞ የሚመጣ ወር። ነገር ግን በአግባቡ የተቀበሉትን እና ያስተናገዱትን ብቻ አክብሮ የሚከንፍ እንግዳ ነው። አላህ በመልካም ተግባሮች መሽቀዳደሚያ ያደረገው ወር።

ረመዳን ውስጥ የሚሰሩ ትርፍ ሥራዎች (ነዋፊሎች) ሌላ ጊዜ እንደሚሠራ አንድ ግዴታ (ፈርድ) ይታሰባል። እርሱ ውስጥ የሚሠራ አንድ ግዴታ (ፈርድ) ሌላ ጊዜ ከሚሠራ ሰባ ፈርድ ጋር ይስተካከላል።

ረመዳን – ኸይር ፈላጊ ሆይ! ፍጠን!… የሚል መፈክር አለው። በርሱ ውስጥ ሰይጣናት ይታሰራሉ። የእሳት ደጃፎች ይዘጋሉ። አየሩ በሙሉ ምህረትን፣ እዝነትን፣ ከእሳት ነፃ መባልን… ለማግኘት ምቹ ነው። ጀነት ትጣራለች። ወደኔ ዙሩ ፈጠን ብላችሁ ኑ! እያለች ናፋቂዎቿን ትጋብዛለች። ገበያው ክፍት ነው። ውድ እቃዎችም ተዘርግተዋል። ንጉሱም ቸር ነው።

እነሆ ረመዳንን ለመጠቀም እንቸኩል። ድንገት አልፎ እንዳንደነግጥ። ለዝግጅት የሚሆነን አንድ ቁም ነገር አለ። እነዚህን ጥያቄዎች መልሰን መገኘት። ከረመዳን ምን እንጠብቃለን? የእንግዳችንን ክብርስ ምን ያህል እናውቃለን? እንግዳችንን ለማስደሰትስ ምን እናድርግ?እነዚህ ፊታችን ያሉት ገፆች እነዚህ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሞክራሉ።

አላህ ከፍላጎታችን በላይ ያለን የሚያሟላ ጌታ ነው። ወደ ቀጥታ መንገድ የሚመራም እርሱ ነው።

የምህረት ወር

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

رغم أنف رجل دخل عليه رمضان ثم انسلخ قبل أن يغفر له

ረመዳን ገብቶ ከዚያም ምህረት ሳያገኝ የወጣበት ሰው አፍንጫው ይታሽ (ውርደት ያግኘው)!

በረመዳን ምህረትን ያላገኘ መቼ ያገኘዋል እንበል?…

ከአኼራ ርቆ የዱንያ ባህር ውስጥ እየዋኘ ምህረት ሊያገኝ?… የብርና የወርቅ ኮቴን እየላሰ… በልጆችና በሚስት ፍላጎት እየተነዳ ምህረት ሊቸር?…

በእርግጥ እኛ ማንንም ከአላህ ምህረት ተስፋ አናስቆርጥም። ነገር ግን አላህ እንደነገረን ምህረት ሠበቦች አሉት። ጀነት ለመግባት መስፈርቶች አሉ። ኢማን በምኞት አይደለም። ልብ ውስጥ የዘለቀ እና በተግባር የተረጋገጠ ካልሆነ። የምንለው እውነት ነው! ከፈለጋችሁ ይህን አንቀፅ አስተውሉት። እንዲህ ይላል፡-

وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ * الَّذِينَ يُنفِقُونَ فِي السَّرَّاءِ وَالضَّرَّاءِ وَالْكَاظِمِينَ الْغَيْظَ وَالْعَافِينَ عَنِ النَّاسِ وَاللَّهُ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ * وَالَّذِينَ إِذَا فَعَلُوا فَاحِشَةً أَوْ ظَلَمُوا أَنفُسَهُمْ ذَكَرُوا اللَّهَ فَاسْتَغْفَرُوا لِذُنُوبِهِمْ وَمَن يَغْفِرُ الذُّنُوبَ إِلَّا اللَّهُ وَلَمْ يُصِرُّوا عَلَىٰ مَا فَعَلُوا وَهُمْ يَعْلَمُونَ * أُولَٰئِكَ جَزَاؤُهُم مَّغْفِرَةٌ مِّن رَّبِّهِمْ وَجَنَّاتٌ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا وَنِعْمَ أَجْرُ الْعَامِلِينَ

ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ። ለእነዚያ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፣ ቁጭትንም ገቺዎች ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለኾኑት (ተደግሳለች) አላህም በጎ ሠሪዎችን ይወዳል። ለእነዚያም መጥፎ ሥራን በሠሩ ወይም ነፍሶቻቸውን በበደሉ ጊዜ አላህን የሚያስታውሱና ለኀጢአቶቻቸው ምሕረትን የሚለምኑ ለኾኑት ከአላህም ሌላ ኀጢአቶችን የሚምር አንድም የለ። (በስሕተት) በሠሩትም ላይ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑ የማይዘወትሩ ለኾኑት (ተደግሳለች) እነዚያ ምንዳቸው ከጌታቸው ምሕረትና በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶችም ናቸው። የሠሪዎችም ምንዳ (ገነት) ምንኛ አማረች! (አሊ ዒምራን 3፤ 133-136)

ለጀነት የተዘጋጀ ይኖር?!

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለው ጠየቁ፡-

ለጀነት የተዘጋጀ ሰው አለ?! ጀነት ልብ ውስጥ ትዝ ብላ የምታውቅ አይደለችም። በካዕባ ጌታ እምላለሁ አንፀባራቂ ብርሀን ናት! የሚንቀጠቀጥ ደስታ ያላት፣ ብርቱ ህንፃዎች ያሉባት፣ ሰፋፊ ጅረቶች ያሉባት፣ ብስል ፍራፍሬዎች የሞሉባት፣ ያማሩ ሚስቶች ያሉባት፣ ብዙ ሙሉ ልብሶች የሚገኙባት፣ ዘላለም የሚኖርባት፣ ሰላም የሠፈነባት፣ ባማሩ አረንጓዴ አትክልቶች የተሸፈነች፣ በታላቅ ደስታና አስገራሚ ፀጋዎች የተሞላች ሀገር ናት።

ጀነት መግባት- ከአላህ ከሚከጀል እዝነት በተጨማሪ- ብዙ ድካም ይጠይቃል። አላህን ለመታዘዝ የምንከፍለውን መስዋእትነት ይፈልጋል።አዎን! በዚህች ዱንያ ውስጥ የምንቆየው ጊዜ አጭር ነው። ከዚያም ረዥም አመታት ይከተላሉ። መጨረሻ የላቸውም። ቀብር ከዚያም የምፅአት ሀገር….በዚህች አጭር የዱንያ ህይወት ውስጥ ተዘናግተው ያለፉ ሰዎች ከአላህ ጋር ሂሳብ ለማድረግ በሚቆሙ ጊዜ ልባቸውን የሚሞላው ቁጭት ምን ያህል ከባድ ይሆን!? ከጌታቸው መብት ያጓደሉ ባሮች አስፈሪው ሚዛን ላይ ሲቆሙ የሚሰማቸው ብስጭትስ ምን ያህል የከፋ ይሆን?! እስቲ እነዚህን አንቀፆች እናስተውል፡-

قَالَ كَمْ لَبِثْتُمْ فِي الْأَرْضِ عَدَدَ سِنِينَ * قَالُوا لَبِثْنَا يَوْمًا أَوْ بَعْضَ يَوْمٍ فَاسْأَلِ الْعَادِّينَ * قَالَ إِن لَّبِثْتُمْ إِلَّا قَلِيلًا ۖ لَّوْ أَنَّكُمْ كُنتُمْ تَعْلَمُونَ * أَفَحَسِبْتُمْ أَنَّمَا خَلَقْنَاكُمْ عَبَثًا وَأَنَّكُمْ إِلَيْنَا لَا تُرْجَعُونَ

በምድር ውስጥ ከዓመታት ቁጥር ስንትን ቆያችሁ? ይላቸዋል። አንድ ቀንን ወይም ከፊል ቀንን ቆየን። ቆጣሪዎቹንም ጠይቅ ይላሉ። እናንተ (የቆያችሁትን መጠን) የምታውቁ ብትኾኑ ኖሮ (በእሳት ውስጥ በምትቆዩት አንፃር) ጥቂትን ጊዜ እንጂ አልቆያችሁም ይላቸዋል። የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?) (አል-ሙእሚኑን 23፤ 112-115)

የቀብር ሰዎች ውድ ምኞት ለአፍታም ቢሆን ወደ ዱንያ መመለስ ነው። አንድ ጊዜ ወደ ህይወት ተመልሶ አላህን ማወደስ፣ ሱብሀነሏህ ማለት፣ አንዲት ጊዜም ቢሆን ለአላህ መስገድ…

እኛስ ከነርሱ አንማርም!? አሁንም ከእንቅልፋችን አንነቃም?! የሚጠብቀንን ፍጥጫ ለመጋፈጥ አንዘጋጅም!? አሁን ዱንያ ውስጥ ፊታችን ላይ የቆሙ ለመጪው አለም የምንሰነቅባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ይኸው ረመዳን ወዲህ እየጠራን ነው። እስኪ እጅጌያችንን አጠፍ አድርገን፣ ፍራሻችንን ትተን፣ ቤተሰቦቻችንን አንቅተን፣ በነፍሳችንና በስሜታችን ላይ የጂሀድ ባንዲራ አንግበን እንነሳ!!

ኑ የአላህን ጥሪ አሺ እንበል!

اسْتَجِيبُوا لِرَبِّكُم مِّن قَبْلِ أَن يَأْتِيَ يَوْمٌ لَّا مَرَدَّ لَهُ مِنَ اللَّهِ ۚ مَا لَكُم مِّن مَّلْجَإٍ يَوْمَئِذٍ وَمَا لَكُم مِّن نَّكِيرٍ

ለእርሱ መመለስ የሌለው ቀን ከአላህ ከመምጣቱ በፊት ለጌታችሁ ታዘዙ። በዚያ ቀን ለእናንተ ምንም መጠጊያ የላችሁም። ለእናንተም ምንም መካድ የላችሁም። (አሽ-ሹራ 42፤47)

ሠዎችና ረመዳን

አዎን! ረመዳን በአመት አንዴ ብቻ የሚከሰት ታላቅ እድል ነው። ነገር ግን ሙስሊሞች በዚህ መልኩ ይተዳደሩት ይሆን? አንዳንዶች የዚህን ወር መምጣት እንደ ከባድ ሸክም ይመለከቱታል። ቶሎ እንዲያልቅም ይመኛሉ። እነዚህ ከረመዳን የሚያተርፉት ከረህመት መባረር ብቻ ነው። ረመዳን ገብቶ ወጣ እንጂ በህይወታቸው ላይ የሚጥለው መልካም አሻራ የለም። አንዳንዶች ደግሞ የረመዳንን ዋጋ ተረድተዋል። እንዲህ አይነቱ ሰው የበረታ ክንዱን አዘጋጅቷል። የቻለውን የአምልኮ ተግባር ለመፈፀም መንፈሱ ነቅቷል። ልቡ አብሮት ባይኖርም ብዙ ጊዜ ቁርአን ለማኽተም፣ ብዙ ለመስገድ፣ ብዙ ዒባዳዎችን ለመሥራት አቅዷል። ይህ አይነቱ ሰው መዳረሻ የነበሩትን የአምልኮ ተግባራት ግብ አድርጎ ይዟቸዋል። ፆም ሊያረጋግጠው የመጣለትን ትልቁን አላማ ግን ዘንግቷል። በእርግጥ ረመዳን በእነዚህኞቹ ልብ ላይ ጥሩ ስሜት ጥሎባቸው ያልፍ ይሆናል። ግን ረመዳን እንደወጣ ቀናት እንዳለፉ ወኔያቸው አብሮ ይከስማል።

አንዳንዶች ደግሞ ረመዳንን ቀልብን ህያው ለማድረግ፣ ከእንቅልፉ ለማንቃትና በውስጡ ላይ የተቅዋን ችቦ ለማቀጣጠልና የኢማንን ሥር ለመትከል ምርጥ አጋጣሚ አድርገው ያዙት። እነዚህኞቹ የፆምን አላማ ሲያስሱ ቆዩና አላህ እንዲህ ሲላቸው አገኙት፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና። (አል-በቀራ 2፤ 183)

አላህን መፍራት የሁሉም ዒባዳዎች መሪ ዓላማ ነው። አላህ እንዲህ አለ፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ اعْبُدُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُمْ وَالَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።(አል-በቀራ 2፤ 21)

በልብ ውስጥ ባለው የተቅዋ መጠንም የሰው ልጅ ለአላህ ያለው ቅርበትና ርቀት ይለካል።

إِنَّ أَكْرَمَكُمْ عِندَ اللَّهِ أَتْقَاكُمْ

አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው። አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው። (አል-ሑጁራት 49፤ 13)

እንደነዚህ ባሉት ሰዎች አመለካከት- ረመዳን- ሠዎችን ከጌታቸው ለማቅረብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የመጣ ነው። የሰዎችን ልብ ከዱንያ እድፍ ሊያፀዳ እና ምርጡን ስንቅ እንዲሰነቁ ሊያግዛቸው የተከሠተ ነው።

وَتَزَوَّدُوا فَإِنَّ خَيْرَ الزَّادِ التَّقْوَىٰ 

ተሰነቁም፤ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህን መፍራት) ነው። የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ። (አል-በቀራ 2፤ 197)

እርሶም የበረታ ክንዶን ይሰብስቡ። ኢስላም በዚህ ወር ውስጥ ያኖራቸውን የተቅዋ ምንጭ የሆኑ መሳሪያዎችን ተጠቀሙ። የልብና የአካል አምልኮዎችን በአንድነት ይከውኑ። ጥርጥር የሌለው እርግጠኛ ነገር እነዚህ ሦስተኞቹ ሰዎች የወሩ አትራፊዎች ናቸው። በረመዳን ተጠቅመው ልባቸውን አንፅተዋል። ከዚያም ወደ አላህ የሚያስጠጋቸውን የህይወት ስንቅ ይዘዋል። ለአመታት የሚቆዩበትን ወኔ ሰንቀዋል። ወደ አላህ ከሚጓዙ የአላህ ወዳጆች መሀል ተሰልፈዋል።

የቀልብ መስተካከል ምልክቶች

ረመዳን የሚያመጣው የልብ ፅዳት ምንድን ነው?! ስትል ያየሁህ መሰለኝ። ልብ ውስጥ ያለው ኢማን ሲነቃቃ… ሥሮቹም ልብ ውስጥ ሲጠልቁ የልብ ፅዳት ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። ነብያችን እንዲህ ይላሉ፡-

ألا إن في الجسد مضغة إذا صلحت صلح الجسد كله، وإذا فسدت فسد الجسد كله ألا وهي القلب

ንቁ! አካል ውስጥ ቁራጭ ሥጋ አለች። እርሷ ከተስተካከለች ሁሉም አካል ይስተካከላል። እርሷ ከተበላሸችም ሁሉ ነገር ይበላሻል። ንቁ እርሷም ልብ ናት!!

የዚህን ልብ ባለቤት ለመልካም ሥራዎች ሲጣደፍ፣ የአላህን ዲን ምልክቶችን ሲያከብር ትመለከተዋለህ። አላህ እንዲህ ይላል፡-

ذَٰلِكَ وَمَن يُعَظِّمْ شَعَائِرَ اللَّهِ فَإِنَّهَا مِن تَقْوَى الْقُلُوبِ

“(ነገሩ) ይህ ነው። የአላህንም የሃይማኖት ምልክቶች የሚያከብር ሰው እርሷ ከልቦች የኾነች ጥንቃቄ ናት። (አል-ሐጅ 22፤ 32)

የራስ ተነሳሽነቱ ያድጋል።

لَا يَسْتَأْذِنُكَ الَّذِينَ يُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ أَن يُجَاهِدُوا بِأَمْوَالِهِمْ وَأَنفُسِهِمْ  وَاللَّهُ عَلِيمٌ بِالْمُتَّقِينَ

እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም። አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው። (አት-ተውባ 9፤ 44)

ለተግሳፅ እና ለመመሪያዎች በፍጥነት ይታዘዛል።

ذَٰلِكَ يُوعَظُ بِهِ مَن كَانَ مِنكُمْ يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ

ዱንያን ችላ ሲል አላህ ዘንድ ላለው ምንዳ ሲሰስት ታየዋለህ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إذا دخل النور القلب أنشرح وأنفتح قالوا: يا رسول الله وما علامة ذلك؟ قال: الإنابة إلى دار الخلود والتجافى عن دار الغرور والإستعداد للموت قبل نزوله

ብርሀን ልብ ውስጥ ሲዘልቅ ይሰፋል፤ ይከፈታል። ባልደረቦቻቸውም የዚህ ምልክት ምንድን ነው? ብለው ጠየቁ። ወደ መዘውተሪያይቱ ዐለም መናፈቅ፣ ከመታለያይቱ ዓለም መራቅና ሞት ከመድረሱ በፊት መዘጋጀት። አሉ፤ መልእክተኛው።

እንግዲህ ይህ ከሆነ የአላማችን መሳካት ምልክቱ አንድ ጥያቄ ብቻ ይቀረናል። አላማችንን እንዴት እናሳካዋለን?

ግባችን እውን የሚሆንባቸውን አማካዮች (means/ ወሳኢል) እናውቃቸዋለን። እንደውም አብዛኞቹን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተግብረናቸዋል። አዲሱ ነገር እንዴት እንጠቀምባቸው የሚለው ነጥብ ነው። ረመዳን ውስጥ ለሚታሰቡት ዓላማዎች እንዴት እናውላቸው የሚለው ጥያቄ ነው አሳሳቢው። እነዚህን አማካዮች (means/ ወሳኢል) ለሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን።

  • አንደኛው ክፍል አንድ ባሪያ በርሱና በጌታው መሀል ያለን ችግር የሚያስተካክልበት ነው። አብዝሀኛ ትኩረቱም የመንፈስ እድገቱን የሚያበለፅጉት ላይ ነው።
  • ሁለተኛው ክፍልም አንድ ባሪያ ከማህበረሰቡ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ዙሪያ ያሉትን ነገሮች የሚያስተካክሉለት አማካዮች ናቸው።

ከእነዚህ ክፍሎች መሀል አንዱን ይዞ ሌላኛውን መተው አይበቃም። ሁለቱም የሙስሊምን የምድር ሚና የሚያሟሉ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው። አላህ እንዲህ አለ፡-

وَمَنْ أَحْسَنُ دِينًا مِّمَّنْ أَسْلَمَ وَجْهَهُ لِلَّهِ وَهُوَ مُحْسِنٌ وَاتَّبَعَ مِلَّةَ إِبْرَاهِيمَ حَنِيفًا ۗ وَاتَّخَذَ اللَّهُ إِبْرَاهِيمَ خَلِيلًا

እርሱ መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ለአላህ ከሰጠና የኢብራሂምንም መንገድ ቀጥተኛ ሲኾን ከተከተለ ሰው ይበልጥ ሃይማኖቱ ያማረ ማን ነው? አላህም ኢብራሂምን ፍጹም ወዳጅ አድርጐ ያዘው። (አን-ኒሳእ 4፤ 125)

ፊትን ለአላህ መስጠት መንፈሳዊና ከስሜት ጋር የተገናኘ ነገር ነው። ነገር ግን ለፍጥረት መልካም መዋል ሊከተለው ይገባል። አንዳንድ ሰዎች ግን ይህን ስተውታል። ለአንዱ ትኩረት ሰጥቶ ሌላውን ትኩረት ይነፍገዋል። ሙሉ ትጋቱን በርሱና በፈጣሪው መሀል ያለውን ርቀት ለማጥበብና ግንኙነቱን ለማስተካከል በማዋል ጥቅሙ ለሠዎች የሆነን ተግባር የተወ ሰው ኢማኑ ጎዶሎ ነው።

ኢማን ንግግርና ተግባር ነው። መልካም ሥራዎች የመልካም ሠሪውን ኢማን ይጨምራሉ። የኢማኑን መሠረቶችም ልብ ውስጥ ያሰርፃሉ። አላህ እንዲህ አለ፡-

إِلَيْهِ يَصْعَدُ الْكَلِمُ الطَّيِّبُ وَالْعَمَلُ الصَّالِحُ يَرْفَعُهُ

መልካም ንግግር ወደርሱ ይወጣል። በጎ ሥራም ከፍ ያደርገዋል። (ፋጢር 35፤ 10)

የአንዳንድ ቀደምት ሙስሊሞች ዘገባ ላይ የተገኘ ንግግርን እናድምጥ። እንዲህ ይላል፡-

إن العبد إذا قال لا إله إلا الله بنية صادقه نظرت الملائكة إلي عملة، فإن كان موافقاً لقوله، صعدا جميعاً، وإن كان العمل مخالفاً وقف قوله حتى يتوب من عمله

አንድ የአላህ ባሪያ በንፁህ ኒያ ላኢላሀ ኢልሏህ ሲል መላኢካዎች ሥራውን ይመለከታሉ። ተግባሩና ንግግሩ ከተጣጣሙ በአንድ ላይ ይዘዋቸው ያርጋሉ። ተግባር ከንግግር የተለየ እንደሆነ ከተግባሩ እስከሚቶብት ድረስ ንግግሩ እዚሁ ይቆያል።

በአንፃሩ በሰዎች መሀል የሚደረጉ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ መጠመድ፣ የሰዎችን ጉዳይ ለመፈፀም የሚደረግ ሩጫ፣ ችግራቸውን ለመፍታት የሚደረግ ርብርብ፣ ሰዎችን ለመርዳትና ለመጥቀም የሚሠራ ሥራ ከአላህ ጋር ግንኙነት ካለው ልብ ካልመነጨ አደጋ አለው። ምናልባትም በመልካም ሠሪው ልብ ውስጥ አሉታዊ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል። የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡-

مثل الذي يعلم الناس الخير، وينسى نفسه مثل الفتيلة، تضيء للناس وتحرق نفسها

ለሠዎች መልካምን ነገር እያስተማረ ነፍሱን የሚዘነጋ ልክ እንደ ሻማ ነው። ለሠዎች እያበራች እራሷን ታነዳለች።

አል-ራፊዒይ እንዲህ ይላሉ፡-

إن الخطأ أكبر الخطأ أن تنظم الحياة من حولك وتترك الفوضى في قلبك

ከስህተት ሁሉ ትልቅ ስህተት የሠዎችን ህይወት እያሳመርክ የራስህን ልብ ማዝረክረክ ነው።

ስለዚህ ሁለቱም ነገሮች በአንድነት መኖር አለባቸው።

 

1 COMMENT

  1. ይህንን ፔጅ እኔ እንደምወደው… አላህም ስራችሁን ወዶላችሁ ለጀነት መግቢያ ሰበብ እንዲሆንላችሁ ሁሌም ዱዓ አደርጋለሁ… በዱንያም በአኺራም ተደሰቱ… !!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here