ጭላጭ /ሱእር/ (ጦሀራ – ክፍል 2)

1
2544

ጭላጭ ማለት ከመጠጣት በኋላ እቃ ላይ የሚቀር ውሃ ነው። አምስት አይነት ነው፦

1. የሰዎች ጭላጭ

ከሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ካልሆነ ሰው፣ ጀናባ ከሆነ ሰውም ሆነ የወር አበባ ላይ ካለች ሴት የተረፈ ውሃ ንፁህ (ጧሂር) ነው።

إِنَّمَا الْمُشْرِكُونَ نَجَسٌ

“አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው።” (አት-ተውባ፤ 28)

ይህ አንቀፅ የማይታይ ነጃሳቸውን፣ የእምነት ርክሰታቸውንና ከቆሻሻዎች የማይፀዱ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው። ዛታቸው እና አካላቸው ቆሻሻ ነው ለማለት አይደለም። ከሙስሊሞች ጋር አብረው ይኖሩ ነበር። መልእክተኞቻቸውና ልኡካኖቻቸው ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይመጣሉ። መስጂዳቸው ውስጥ ይገቡ ነበር። አካላቸው የነካውን የመስጂዳቸውን ቦታ ይታጠብ ብለው አላዘዙም። አዒሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፦

كنت أشرب وأنا حائض ، فأناوله النبي صلى الله عليه وسلم ، فيضع فاه على موضع في

“እኔ የወር አበባ ላይ ሆኜ ውሃ እጠጣ እና ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እሰጣቸው ነበር። የእኔ አፍ የነካው ቦታ ላይ አፋቸውን ያስነኩት ነበር።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

2. ስጋው የሚበላ እንስሳ ጭላጭ

ይህም ንፁህ ነው። ምክንያቱም ለሃጩ የሚወለደው ንፁህ ከሆነ ሥጋ ነው። ስለዚህ የእርሱን ብይን ይይዛል። አቡ በክር አል-ሙንዚር እንዲህ ይላሉ፦ “ሥጋው የሚበላ እንስሳን ጭላጭ መጠጣት እና በርሱ ዉዱእ ማድረግ እንደሚፈቀድ ዑለሞች ሁሉ ተስማምተዋል።”

3. የበቅሎ፣ የአሕያ፣ የአውሬዎች እና አዳኝ አእዋፋት ጭላጭ

ይህ ንፁህ ነው። የጃቢር (ረ.ዐ) ሐዲስ መረጃችን ነው።

سئل : أنتوضأ بما أفضلت الحمر ؟ قال نعم  وبما أفضلت السباع كلها

“አሕያ ባስተረፈው ውሃ ዉዱእ እናድርግ? ተብለው ተጠየቁ፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘አዎን አውሬዎች ባስተረፉት ውሃ በሙሉ ዉዱእ አድርጉ።” (ሻፊዒይ፣ ዳረቁጥኒይ እና በይሃቂይ ዘግበውታል)። “ሰነዶቹን አንዱን ከሌላው ጋር ስንደባልቅ ጠንካራ ይሆናሉ።” ብለዋል፤ በይሀቂይ።

4. የድመት ጭላጭ

ይህም ንፁህ ነው። መረጃችን የከብሻ ቢንት ከዕብ ሐዲስ ነው። የአቢቀታዳ (ረ.ዐ) ሚስት ነበረች።

أن أبا قتادة دخل عليها فسكبت له . فجاءت هرة تشرب منه فأصغى لها الاناء حتى شربت منه ، قالت كبشة : فرآني أنظر فقال : أتعجبين يا ابنة أخي ؟ فقالت : نعم . فقال : إن رسول الله صلى الله عليه وسلم قال : إنها ليست بنجس، إنها من الطوافين عليكم والطوافات

“አቡቀታዳህ ወደርሷ ገባና ውሃ አቀረበችለት። አንዲት ድመት መጣችና ከውሃው መጠጣት ጀመረች። እርሱም እቃውን ዝቅ አደረገላት። ‘ተደንቄ እያየሁት እንዳለ ተመለከተኝ።’ ትላለች ከብሻ። ‘የወንድሜ ልጅ ሆይ! ትደነቂያለሽ?’ አላት። ‘አዎን!’ አለች። ‘የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦ ‘እርሷ ነጃሳ አይደለችም፤ እርሷ በናንተ ላይ ዟሪ ከሆኑ አገልጋዮቻችሁ መሀል ናት።’ ሲሉ ሰምቻለሁ።’ አለ።” (አምስቱ ዘግበውታል። ቲርሚዚም ይህ ሐዲስ ትምህርቱ መልካም ሰነዱም ሶሒሕ ነው ብለዋል። ቡኻሪይና ሌሎችም ሶሒሕ አድርገውታል)

5. የውሻና የአሳማ ጭላጭ

ይህ ነጃሳ ነው። መጠንቀቅ ይገባል። የውሻ ትራፊ ላይ ቡኻሪና ሙስሊም አቡሁረይራን ዋቢ በማድረግ የዘገቡትን ሐዲስ መሰረት ማድረግ እንችላለን። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

إذا شرب الكلب في إناء أحدكم فليغسله سبعا

“ከአንዳችሁ እቃ ውሻ ከጠጣ ሰባት ጊዜ ይጠበው።” ይላሉ።

የአሳማ ትራፊን እዚህ ውስጥ የከተትነው ቆሻሻነቱ የከፋ እና አስጠያፊ ስለሆነ ነው። አላህ የተሻለ ያውቃል።

suer

1 COMMENT

 1. ♡♡S A W♡♡
  ♡♡Subhana Allah ♡♡
  Turu tmhirt agegnhubet
  ●●●●●●●●●●●●●●●●●□
  Minegna yamaru
  Hadisoch nchow. walahi alawkim nbr.
  Jazakum Allah kyren jaza

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here