ከወንጀል የማትታደግ ሰላት!

0
7391

ለምንድን ነው ሁኔታችን መጥፎ የሚሆነው? መስጂዶቻችን በሺዎች የሚቆጠሩ፤ የሰጋጆቹ ቁጥር በሚሊዩን የሚቆጠር ነው?! እዚህ ጋር አንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቃለን። መልሱም እንዲሁ ግልፅና ቀድሞም የታወቀ ነው። ነገር ግን የመልሱን እውነታ ለማወቅ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል። ያቀረብነውን ጥያቄም ምላሽ ለመስጠት የቁርአን መረጃዎችን በማጣቀስ እንመልሳለን። በዚህም በሰላት ላይ ያለንን አቋም እናውቃለን።

አላህ በመርየም ምዕራፍ ወዳጁ ስለሆኑት ነቢዩ ኢብራሂም ዓለይሂ ሰለም እና ዝርያዎቻቸው እንዲህ ይላል፡-

أُولَئِكَ الَّذِينَ أَنْعَمَ اللهُ عَلَيْهِم مِّنَ النَّبِيِّينَ مِن ذُرِّيَّةِ آدَمَ وَمِمَّنْ حَمَلْنَا مَعَ نُوحٍ وَمِن ذُرِّيَّةِ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْرَائِيلَ وَمِمَّنْ هَدَيْنَا وَاجْتَبَيْنَا إِذَا تُتْلَى عَلَيْهِمْ آيَاتُ الرَّحْمَنِ خَرُّوا سُجَّدًا وَبُكِيًّا * فَخَلَفَ مِن بَعْدِهِمْ خَلْفٌ أَضَاعُوا الصَّلاَةَ وَاتَّبَعُوا الشَّهَوَاتِ فَسَوْفَ يَلْقَوْنَ غَيًّا

“እነዚህ (ዐሥሩ) እነዚያ አላህ በእነሱ ላይ የለገሰላቸው ከነቢያት ከአዳም ዘር ከኑሕ ጋር (በመርከቢቱ ላይ) ከጫናቸውም (ዘሮች) ከኢብራሂምና ከእስራኤልም ዘሮች ከመራናቸውና ከመረጥናቸውም የኾኑት የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ። ከእነሱም በኋላ ሰላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ።” (መርየም፤ 58-59)

በዚህ የቁርአን አንቀፅ መሰረት፤በነብዩ ያዕቁብ (በኒ ኢስራኢል) እና ኢስማዒል ዘሮች (አረቦች) ሰላትን በተገቢው መንገድ አንዳልሰገዱት ያመለክታል።

ከዚህ የምንረዳው ሰላት ከነ ሙሉ ስርዓቷና ውበቷ ካለተሰገደች ሙሉ የሰላትን ዋጋ አታስገኝም። ፋቲሀ መቅራት፤ ሩኩዕ፤ ሱጁድ፤ መቆምና መቀመጥ የሰላት ሩክን (ምሰሶ) ቢሆኑም በተገቢው መንገድ ካልተፈፀሙ ሰላት መስገድን አያስኙም። አላህ

وَمَا كَانَ صَلَاتُهُمْ عِنْدَ الْبَيْتِ إِلَّا مُكَاءً وَتَصْدِيَةً ۚ فَذُوقُوا الْعَذَابَ بِمَا كُنْتُمْ تَكْفُرُونَ

“በቤቱ ዘንድም (በካዕባ) ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም። ትክዱት በነበራችሁትም ነገር ቅጣትን ቅመሱ (ይባላሉ)።” (አል-አንፋል፤ 35) እንዳለው ማለት ነው።

እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ሰላትን መስገድና ሰላትን ማቋቋም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።ሰላትምን ወቅቱን ጠብቆ አለመስገድም ሌላው የሰላት መጥፋት ምልክት ነው። ለመሆኑ “ኋላ የመጣው” ትውልድ ሰላቱን እንዳጠፋ እኛስ አጥፍተነዋልን? በርግጥ ሰላትን ማጥፋት ማለት ሙሉ በሙሉ መተው ማለት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን “ማጥፋት” ማለት “እየፈፀሙት አለመጠቀም” ማለት ነው። የ”ሰላት መጥፋት” ትርጉሙ ከሰላት ሊገኝ የሚገባውን መሰረታዊ የሆነው “ተቅዋን” ማጣት ማለት ነው።

ሰላት መዳረሻ ወይስ ዓላማ?

ሰላትም ሆነ ሌሎች ዒባዳዎች በራሳቸው ግቦች አይደሉም ። አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ اعْبُدُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُمْ وَالَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና

የመጨረሻ ግቡ “ተቅዋን” (አላህ መፍራት) ማስገኘት ነው። ሌሎቹም ዒባዳዎች እንዲሁ። ሰላትም እንዲሁ ሰጋጁን ከመጥፎ ነገር ሲያቅበው ሰውየው አላህ ፈርቷል ማለት ይቻላል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

اتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنَ الْكِتَابِ وَأَقِمِ الصَّلَاةَ ۖ إِنَّ الصَّلَاةَ تَنْهَىٰ عَنِ الْفَحْشَاءِ وَالْمُنْكَرِ ۗ وَلَذِكْرُ اللَّهِ أَكْبَرُ ۗ وَاللَّهُ يَعْلَمُ مَا تَصْنَعُونَ

“ከመጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ።ሰላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ።ሰላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና። አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል።” (አል-አንከቡት፤ 45)

ሶላትን በአግባቡ አለመስገድ በራሱ ወንጀል የሆነ ተግባር ነው። ምናልባት ሰጋጁ አማኝ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ነፃ ከሚወጡት ሰዎች ደግሞ መሆን አይችልም። ቀጣዩን አንቀፅ እናንብብ

وَالَّذِينَ هُمْ عَلَىٰ صَلَوَاتِهِمْ يُحَافِظُونَ أُولَٰئِكَ هُمُ الْوَارِثُونَ    -الَّذِينَ يَرِثُونَ الْفِرْدَوْسَ هُمْ فِيهَا خَالِدُونَ

“እነዚያም እነሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የኸኑት (አገኙ)። እነዚያ ወራሾቹ እነርሱ ናቸው። እነዚያ ፊርደውስን (ላዕላይ ገነትን)፤ የሚወርሱ ናቸው። እነርሱ በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው።” (አል-ሙዕሚኑን፤ 9-11)

ሰላትን ስርዓቷን ጠብቆ በመፈፀም ሲባል፤ በመተናነስ (ኹሹዕ) መስገድና ከሰላት በኋላ ወንጀል አለመፈፀም ጥብቅ ትስስር ያላቸው ጉዳዮች ናቸው። (ኹሹዕ) ለአንድ ሙዕሚን ኢኽላስ ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው። ምክንያቱም በየረከዓው አላህን “ትክክለኛውን መንገድ ምራን” የሚለው አንቀፅ ስለሚያነብ። በሰላት ውስጥ የሚኖር ኹሹዕና መጥፎ ስራን መስራት አብረው አይኖረም። ከሰላት በኋላም ወንጀል መስራት አብሮ አይገኝም። ምክንያቱም ያ ከሆነ “ትክክለኛውን መንገድ ምራን” ሚለው ልመናችን ትርጉም የለሽ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ሶላታችን ለሰው እይታ የሚሰገድ ራስን ማታለያ ነው የሚሆነው።

በቁርአን አገላለፅ  መሰረት ሰላት መስገድ ማለት፤ ኹሹዕና ጊዜዋን ጠብቆ በአንድ ላይ  አጣምሮ መፈፅም ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

إِلَّا الْمُصَلِّينَ   الَّذِينَ هُمْ عَلَىٰ صَلَاتِهِمْ دَائِمُونَ

“ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ። እነዚያ እነርሱ በስግደታቸው ላይ ዘውታሪዎች የኾኑት።” (አል-መዓሪጅ፤ 22-23)

በቁርአን ውስጥ “አቃመ” የሚለው ግስና የግሱ እርባታዎች ከሰላት በተያያዘ መልኩ አርባ ጊዜ ያህል ተወስተዋል። በአረብኛ ቋንቋም በቁርአን አገባብ መሰረትም በአንድ ነገረ ላይ ቆመ ማለት በነገሩ ዘወተረበት፣ ጠበቀው ማለት ነው። አላህም ከመልካም ሰሞቹ መካከል “አል-ቀዩም” አንዱ ነው።

اللَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ ۚ لَا تَأْخُذُهُ سِنَةٌ وَلَا نَوْمٌ

“አላህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። ሕያው ራሱን ቻይ ነው። ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም።” (አል-በቀራ፤ 255)

አንቀፅ “አል-ቀዩም” የሚለውን ስም ሲብራራ”በሁሉም ነገር ላይ አስተናባሪ ፤ ለአንድም ነገር ዝንጉ ያልሆነ” በሚል ነው። ከዚህ ትርጓሜ አንፃር አላህ ፍትህን ፤ሚዛናዊነትነ ጠባቂ አንድንሆን ያዘናል።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ بِالْقِسْطِ شُهَدَاءَ لِلَّهِ وَلَوْ عَلَىٰ أَنْفُسِكُمْ أَوِ الْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቀዋሚዎች በነፈሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ። (አል-ኒሳእ፤ 135)

ከዚህ አንፃርም ሰላትን በተገቢው መንገድ የማይሰግድ ሰው የትኛው እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ሁሉም ወንጀልን፤ ብልሹነትንና በደልን የሚፈፅሙና የሚያስፋፉ ሰዎች ሰላትን በትክክል የሚፈፅሙ አይደሉም። ምናልባት እነዚህ ሰዎች የሰላት ጉዳይ በሚገባ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሲሆኑ ይችላሉ። አላህ እንዲህ ይላል፡-

مَا كَانَ لِلْمُشْرِكِينَ أَنْ يَعْمُرُوا مَسَاجِدَ اللَّهِ شَاهِدِينَ عَلَىٰ أَنْفُسِهِمْ بِالْكُفْرِ ۚ أُولَٰئِكَ حَبِطَتْ أَعْمَالُهُمْ وَفِي النَّارِ هُمْ خَالِدُونَ إِنَّمَا يَعْمُرُ مَسَاجِدَ اللَّهِ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَأَقَامَ الصَّلَاةَ وَآتَى الزَّكَاةَ وَلَمْ يَخْشَ إِلَّا اللَّهَ ۖ فَعَسَىٰ أُولَٰئِكَ أَنْ يَكُونُوا مِنَ الْمُهْتَدِينَ

“ለከሓዲዎች በነፍሶቻቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲኾኑ የአላህን መስጊዶች ሊሠሩ አይገባቸውም። እነዚያ ሥራዎቻቸው ተበላሹ። እነሱም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው። (17) የአላህን መስጊዶች የሚሠራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣ ሶላትንም በደንቡ የሰገደ፣ ግዴታ ምጽዋትንም የሰጠ ከአላህም ሌላ (ማንንም) ያልፈራ ሰው ብቻ ነው። እነዚያም ከተመሩት ጭምር መኾናቸው ተረጋገጠ።” (አል-ተውባ፤ 17-18)

መልእክተኛው በነበሩበት ዘመን እንኳን ሙናፊቆች ሰላት ይሰግዱ ነበር። ነገር ግን የሚፈለገውን ሰላት አልነበረም የሚሰግዱት ። ሶላታቸው የይዩልኝ ሰላት ነበር ። ሶላታቸው ማታለያና ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ጊዜ ጠበቂያ ነበር። በርግጥ ራሳቸውን ነው ያታለሉት ፡-

إِنَّ الْمُنَافِقِينَ يُخَادِعُونَ اللَّهَ وَهُوَ خَادِعُهُمْ وَإِذَا قَامُوا إِلَى الصَّلَاةِ قَامُوا كُسَالَىٰ يُرَاءُونَ النَّاسَ وَلَا يَذْكُرُونَ اللَّهَ إِلَّا قَلِيلًا

“መናፍቃን አላህን ያታልላሉ። እርሱም አታላያቸው ነው። (ይቀጣቸዋል)። ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾች ስዎችን የሚያሳዩ ኾነው ይቆማሉ። አላህንም ጥቂትን እንጅ አያወሱም።” (አል-ኒሳእ፤ 142)

የሰላት ፍሬ

በቁርአናዊው የቃላት ብያኔ መሰረት ሰላትን ማቋቋም ማለት በውስጧ “በኹሹዕ” መስገድ፤ በተቅዋ መታነፅና በሶላቶች መካከል በስነ ምግባር መዋብ ማለት ነው። ሰላትን ማቋቋም በእኛ አረዳድ ሰዎች መስጅድ እንዲመጡ የምናደርገው ኢቃም ማለት ነው። በርግጥ “ቀድቃመቲ -አል-ሰላት” (ሰላት ቆመች) የሚለው ቃል የሰላት ስርዓት በአግባቡ ለመፈፀም ቁሙ ማለት ሲሆን የሰላት በአግባቡ መቋቋም በበጎ ነገር ከሌሎች ጋር መተባበር፣ በመልካም ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል የሚል ትርጉምም ይኖረዋል።

ሰዎች የሚያውቋቸው በጎ ስነምግባራት ለምሳሌ፡- እውነተኛነት፤ ለሰዎች መልካም መዋል፤ ፍትሀዊነት፤ አደራን መጠበቅ፤ ቸርነት፤ ሰላምታ፤ ሆደ ሰፊነትና (መቻቻል)ና ሌሎችም ከመልካም ነገሮች ይመደባሉ። ከመጥፎ መከልከል ሲባል ለምሳሌ፡- በደል፤ ድንበርን ማለፍ፤ስግብግብነት፤ አጉል እኔነት፣ መንበጣረርና ሌሎችም መጥፎ ምግባሮች ይካተታሉ። ይህ አይነቱ በመልካም የሚያዝና ከመጥፎ የሚከለክል ህብረተሰብ በረሱል ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጊዜ ተከስቶ የነበረውን የመዲና ህብረተሰብ ያሰታውሰናል። በዚህ ህብረተሰብ ውስጥ የሰላት ሚና በግልፅ ይታይ ነበር።

ሰላት እየሰገደ ሽርክ ውስጥ የሚዘፈቅና ወንጀል ውስጠ የሚንከባለል ሶላቱ ትርጉም የለሽና ዋጋ ቢስ ነው። አንዳንዶች ሰላትን የአካል አንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ የሚፈፅሙ ስህተት ላይ ያሉ ናቸው። ምክንያቱም ሶላታቸው ከወንጀል ይታቀቡ ዘንድ ምንክያት አልሆነላቸውምና። ይህ አይነቱ ሰው ሰላት በሰገደ ቁጥር የሰራውን ቢሰራ ወንጅሉ የሚማርለት ይመስለዋል። ይህ በራሱ ስህተት ላይ ይጥለዋል። በዲኑም እንዲያሰተባብል በር ይከፍትለታል።

أَرَأَيْتَ الَّذِي يُكَذِّبُ بِالدِّينِ

“ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?)” (አል-ማዑን፤ 1)

ከዚያ ቀጠል በማድረግ

فَذَٰلِكَ الَّذِي يَدُعُّ الْيَتِيمَ وَلَا يَحُضُّ عَلَىٰ طَعَامِ الْمِسْكِينِ فَوَيْلٌ لِلْمُصَلِّينَ الَّذِينَ هُمْ عَنْ صَلَاتِهِمْ سَاهُونَ الَّذِينَ هُمْ يُرَاءُونَ وَيَمْنَعُونَ الْمَاعُونَ

“ወዮላቸው ለሰጋጆች። ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)። ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለኾኑት። የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለኾኑት (ወዮላቸው)።” (አል-ማዑን፤ 4-7)

በዚህ አንቀፅ የሚገርመው ነገር ዲኑን እያስተባበለ፤ የቲሞችን እያንገላታ፤ ደሀዎችን ለማብላት የማያስብ ሰው፤ ከነዚህ መጥፎ ሰራዎች በተጨማሪ ሰላትነ ሰጋጅ ነው። ነገር ግን ሶለቱንም የረሳና ወንጀሉንም ችላ ያለ ነው። እንዲያውም በሶላቱ የሰዎችን እይታ ይሻል። በዚህ ብቻ ሳይቆም የሰውን ገንዘብ ያለአግባብ መብላትና ግልፅም ድብቅም ንፍቅናንም በግልጽ ያሳያል።

የአላህን ቁርአናዊ አንቀፅ በመጥቀስ ሀሳባችንን እንቋጭ፡-

لَيْسَ الْبِرَّ أَنْ تُوَلُّوا وُجُوهَكُمْ قِبَلَ الْمَشْرِقِ وَالْمَغْرِبِ وَلَٰكِنَّ الْبِرَّ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَالْمَلَائِكَةِ وَالْكِتَابِ وَالنَّبِيِّينَ وَآتَى الْمَالَ عَلَىٰ حُبِّهِ ذَوِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينَ وَابْنَ السَّبِيلِ وَالسَّائِلِينَ وَفِي الرِّقَابِ وَأَقَامَ الصَّلَاةَ وَآتَى الزَّكَاةَ وَالْمُوفُونَ بِعَهْدِهِمْ إِذَا عَاهَدُوا ۖ وَالصَّابِرِينَ فِي الْبَأْسَاءِ وَالضَّرَّاءِ وَحِينَ الْبَأْسِ ۗ أُولَٰئِكَ الَّذِينَ صَدَقُوا ۖ وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُتَّقُونَ

“መልካም ሥራ ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም። ግን መልካም ሥራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነቢያትም፣ ያመነ ሰው ገንዘብንም ከመውደዱ ጋር ለዝምድና ባለቤቶችና ለየቲሞች ለምስኪኖችም፣ ለመንገደኞችም፣ ለለማኞችም፣ ለጫንቃዎችም (ማስለቀቅ) የሰጠ ሰውና ሶላትንም ደንቡን ጠብቆ የሰገደ፣ ዘካንም የሰጠ፣ ቃል ኪዳንም በገቡ ጊዜ በኪዳናቸው የሞሉ (ሰዎች ሥራ) ነው። በችግር በበሽታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)። እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው። እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ እነርሱ ናቸው።” (አል-በቀራ፤ 177)

በዚህ አጋጣሚ ማንኛውም ሰው ከሰላት አንፃር ያለውነ ቦታ (አሰጋገዱን ውጤቱን) ማየትና መገምገም ይኖርበታል። ይህን ሲያደርግ፤ ከአላህ ዘንድ ያለውን ቦታ ማወቅ ያስችለዋል። አላሀ ሁላችንንም ትክክለኛውን መንገድ እንዲመራን እንጠይቀዋለን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here